Pages

Sunday, January 25, 2015

ከሳምንታት በኋላ ይወጣል



ውድ የመቅረዝ ቤተ ሰቦች እንዴት አላችኁ? እጅግ የምንወዳቸው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስብከቶችና ተግሣጻት እነሆ በአንድ ላይ በዐቢይ ጾም ዋዜማ ልናገኛቸው ነው፡፡ 201 ገጽ ባለው በዚኽ መጽሐፍ ውስጥ 56 የተለያዩ የሊቁ ስብከቶችና ተግሣጻት ተካተዋል፡፡ አጠር አጠር ብለው የተዘጋጁ ሲኾኑ ረዣዥም ጽሑፎችን ለማንበብ ትዕግሥቱና ጊዜ ለሌላቸው እጅግ ተመራጭ ናቸው፡፡ ይጠቀሙበት፡፡ ይኽን መጽሐፍ ሲገዙ በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ እንደ ማለት ነው፡
1. ነፍስዎን በቃለ እግዚአብሔር ይመግባሉ፤
2. የመቅረዝ ዘተዋሕዶን አገልግሎት ከዚኽ የበለጠ እንዲሰፋ ይደግፋሉ፡፡ 

Monday, January 12, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ሰባት)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ጥር 5 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ስለ እግዚአብሔር መኖር
 ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች እንዴት አላችኁ? ባለፉት ስድስት ተከታታይ የመግቢያ ትምህርቶች ጠቃሚ መንፈሳዊ ግንዛቤን እንዳገኛችኁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዛሬው ትምህርታችን ደግሞ የትምህርተ ሃይማኖት መሠረት ስለኾነው ስለ እግዚአብሔር መኖር እንማማራለን፡፡ የሊድያን ልቡና የከፈተ አምላክ የእኛንም የልቡናችን ዦሮ ከፍቶ ይግለጽልን፡፡ አሜን!!!   
 ስለ እግዚአብሔር መኖር ብዙዎቻችን እናምናለን፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር መኖር የማያውቅ ማኅበረ ሰብእ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት፡- “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል” እንዳለ /መዝ.14፡1/ አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔርን መኖር ጥያቄ ማንሣታቸው አልቀረም፡፡ በተለይም የምዕራቡ ዓለም የትምህርት ሥርዓት ከተስፋፋ ወዲኽ እንዲኽ ዓይነት ጥያቄዎች በአንዳንዶቹ ዘንድ የሚመላለስ ኾኗል፡፡