Pages

Monday, January 12, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ሰባት)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ጥር 5 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ስለ እግዚአብሔር መኖር
 ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች እንዴት አላችኁ? ባለፉት ስድስት ተከታታይ የመግቢያ ትምህርቶች ጠቃሚ መንፈሳዊ ግንዛቤን እንዳገኛችኁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዛሬው ትምህርታችን ደግሞ የትምህርተ ሃይማኖት መሠረት ስለኾነው ስለ እግዚአብሔር መኖር እንማማራለን፡፡ የሊድያን ልቡና የከፈተ አምላክ የእኛንም የልቡናችን ዦሮ ከፍቶ ይግለጽልን፡፡ አሜን!!!   
 ስለ እግዚአብሔር መኖር ብዙዎቻችን እናምናለን፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር መኖር የማያውቅ ማኅበረ ሰብእ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት፡- “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል” እንዳለ /መዝ.14፡1/ አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔርን መኖር ጥያቄ ማንሣታቸው አልቀረም፡፡ በተለይም የምዕራቡ ዓለም የትምህርት ሥርዓት ከተስፋፋ ወዲኽ እንዲኽ ዓይነት ጥያቄዎች በአንዳንዶቹ ዘንድ የሚመላለስ ኾኗል፡፡

 ኹሉም ባይኾኑም አብዛኞቹ ምዕራባውያን ስለ እግዚአብሔር መኖር ከተጠራጠሩና ከካዱ ሰነባብተዋል፡፡ ይኽ አካሔድም በሚገርም ፍጥነት ወደእኛ ሀገር እየተዛመተ ይገኛል፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጐች (ለምሳሌ ኦሾ የተባለው ሕንዳዊ ግለሰብ) የሚጽፏቸው ልበወለድ መጻሕፍት በሀገራችን ተርጓሚያን ጸሐፊዎች በብዙዎች እጅ ውስጥ መግባቱ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ግርታን መፍጠሩ አልቀረም፡፡
  “እግዚአብሔር የለም” ብለው የሚያስቡ ሰዎች “እግዚአብሔር የለም” እንዲሉ የሚያደርጓቸው ምክንያት አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያኽልም፡-
·        በኃጢአታቸው ምክንያት የሚጠይቃቸው አካል እንዲኖር ስለማይፈልጉ፤
·        በዳሰሳና በሙከራ መንፈስ የኾነውን እግዚአብሔር ለማግኘት ስለሚሹ፤
·        በአንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ (በተለይ ሀብታም ቤተሰብ) ትምህርተ ሃይማኖትን ማስተማር እየቀረና እየቀነሰ ስለመጣ፤
·        ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ዘዴውን በረቀቀ መንገድ ሰውን ከእምነት እያስወጣ መምጣቱ (ለምሳሌ በስመ ዲሞክራሲና የነጻነትን ትርጕም አዛብቶ በመተርጐም)፤
·        በብዙ ፈላስፎች ዘንድ “እግዚአብሔር አለ” ብሎ ማመን “በራስ ያለመተማመንና የፍርሐት ምልክት” ተደርጐ መወሰዱ፤
·        ቁሳዊ አመለካከት እየተስፋፋ መምጣቱ፤
·        ስለሌላም ብዙ ምክንያት፡፡
  በመኾኑም ስለ እግዚአብሔር መኖር ማመን ለብዙዎቻችን ቀላል እንደኾነ ኹሉ፥ ለአንዳንዶች ግን ቀላል አልኾነምና መማማሩ ተገቢነት አለው፡፡  
 የእግዚአብሔርን ህልውናና የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ዐውቆና ተረድቶ እንደ ሒሳብና እንደ ፊዚክስ ቁመቱ፣ ስፋቱ፣ ክብደቱ እንዲኽ ነው ብሎ ማስረዳት አይቻልም፡፡ “መጠኑ ይኽን ያክላል፤ መልኩ ይኽን ይመስላል” ብሎ ልክና መልክ ሊሰጠው አይችልም፡፡ ከነቢያት እስከ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት እስከ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ይኽን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ኾነው ተናግረዉታል፡፡ ለምሳሌ፡-
1.     “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለኽን? ወይስ ኹሉን የሚችል አምላክ ፈጽመኽ ልትመረምር ትችላለኽን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለኅ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለኅ? ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል፤” /ኢዮብ.11፡7-11/፡፡
2.    “የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ! በእውነት አንተ ራስኽን የምትሰውር አምላክ ነኅ” /ኢሳ.45፡15/፡፡
3.    “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ ዕውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ኹሉ ከርሱና በርሱ ለርሱም ነውና፤ ለርሱ ለዘለዓለም ክብር ይኹን፤ አሜን፤” /ሮሜ.11፡33-36/፡፡
4.    “ብቻውን አምላክ ለሚኾን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን፤” /1ኛ ጢሞ.1፡17/፡፡
5.    “ርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይኹን፤ አሜን፤” /1ኛ ጢሞ.6፡16/፡፡
6.    “ሕሊናት የማይመረምሩትና (የሚረቅና) ያልተፈጠረ የፈጣሪን ምሥጢር እንደምን ማወቅ ይቻለናል?” /ጐርጐርዮስ ገባሬ መንክራት፣ ሃይ.አበ.13፡16/፡፡  
7.    “መላዕክትና የመላዕክት አለቆች ኹሉ በየወገናቸው በየሥርዓታቸው ፍጡራን ከኾኑት ኹሉ ጋር አንድ ላይ በአንድነት ቢሰበሰቡ የእግዚአብሔርን ህላዌ በጥቂቱ ስንኳ ሊያገኙት አይችሉም” /ባስልዮስ ዘቂሣርያ፣ ሃይ.አበ.33፡14/፡፡
8.    “እግዚአብሔር በሰው ልጅ ሕሊና አይመረመርም፡፡ የሰው አስተሳሰብ መለኮትንና ህላዌ መለኮትን መርምሮ ማወቅ አይችልም፡፡ የመለኮት ህላዌ ከሰው ልጅ አስተሳሰብ የራቀ ነውና፡፡ ከሐሳቦች ኹሉ ይልቅ በጣም ከፍ ከፍ ያለ ነውና፤”  /ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ፣ ሃይ.አበ.53፡2/፡፡
9.    “አንደበት የርሱን ነገር እንደሚገባ አድርጐ መናገር አይቻለውም፡፡ አፈ ሕሊና (የሕሊና አንደበት) ሊጠራው እዝነ ልቡናም (የልቡና ዦሮ) ሊሰማው አይቻለውም፡፡ አንደበትስ ተወውና ከርሱ የሚበልጥ ሕሊና ልብ እንኳ ከጌታ ነገር ማናቸውንም ማወቅ መረዳት አይቻለውም፤” /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ የዕብራውያን መልዕክት ትርጓሜ፣ ድርሳን 2፡6-9/፡፡
10.  “ሰው ሆይ! ፍጥረታት ለማይመስሉት በምን ታመሳስለዋለኽ? የማይታሰበውንስ እንዴት አድርገኽ ልታስበው ትቃጣለኽ? በፍጡራን ሊያስተካክሉት የሚገባ አይደለም፡፡ በምንም በማናቸውም ስለ ግርማው በመብረቅ፣ ከፍተኛ ስለኾነው ብርሃኑ በፀሐይ፣ ስለ ልዕልናው በሰማይ፣ ስለ ስፋቱ በምድር፣ ስለ ጥልቀቱ በባሕር፣ እሳት ስለማቃጠሉ በእሳት፣ ስለ ርቀቱና (ረቂቅነቱና) ስለ ፍጥነቱ በነፋስ፣ ወይም በማናቸውም ቢኾን የእውነት አምላክን መለኮትነት ሊያስረዳ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይኽ ለፍጥረት ያልተሰጠውና፣ በምንም በማናቸውም ኹኔታውን ለመረዳት አይቻልም፡፡ ስለዚኽም ኹኔታውን ለመመርመር አይቻልም፤” /ርቱዐ ሃይማኖት /፡፡
11.    “በመመርመር ያገኘው የለም፤ መርምሮ የሚያገኝኽ የለም፡፡ በባሕርይኽ መርምሮ የሚያውቅኽ የለም፡፡ በርቀት (በረቂቅነትኽ) አንተን ማየት የሚቻለው የለም፤ ባሕርይኽን አንተ ታውቀዋለኽ እንጂ፤” /ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፣ 1፡4-5/፡፡
12.   “በሕሊና ተመርምሮ የማይገኝ ረቂቅ ነው፤ በልቡና ተመርምሮ የማይገኝ ምጡቅ ነው፡፡ በተልዕኮ የሚኖሩ መላዕክት የማይመረምሩት በተሰጥሞ (በተመስጦ) የሚኖሩ ጻድቃን የማይመረምሩት ረቂቅ ነው፤” /ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ 1፡6/፡፡
“ፍጡር አስቦ ሊደርስበት አይችልም፤ መርምሮም ሊያውቀው አይችልም፤” ማለት ግን እግዚአብሔር የለም ማለት አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ለሰዎች መገለጥን የማይወድ ዐይነ አፋር ነው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር ህላዌውን (መኖሩን) እንዲኽ የሰወረው ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያኽል፡-
1.    ሰዎች ወድደውና ፈቅደው እንዲፈልጉት ፈቃዱ ስለኾነ፤
 ለዚኽም ኹላችንም ርሱን እንድንፈልግ የምንገደድበት አዕምሮ በልቡናችን ውስጥ አሳድሯል /ሮሜ.2፡14-16/፡፡ የሥነ ፍጥረት ውበትና ሥርዓት እንዲኹም አቀማመጥ እየተመለከትን ይኽን ያደረገ ማን እንደኾነ እንድንመራመር የአዕምሮ ሕግ ሰጥቶናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “አካላዊ አቋሜን ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣኹት እኔ ነኝ፤ እኔው ራሴ ራሴን ፈጠርኩ፤ ከሌላ ቦታ ይልቅ አኹን ባለኹበት ቦታ ለመኖር ራሴ መረጥኩ” ለማለት እስካልደፈረ ድረስ ፈጣሪውን ለመፈለግ ይገደዳል፡፡
 እያንዳንዳችን ለአካላዊ አቋማችን አየር፣ ምግብ፣ ልብስ፣ ብርሃን፣ ጤና ማግኘት አለብን፡፡ ነገር ግን “እነዚኽን አስፈላጊ ነገሮች ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኋቸው እኔ ነኝ” ለማለት እስካልደፈርን ድረስ ፈጣሪያችንን ለመመርመር እንገደዳለን፡፡
 ዳግመኛም በሥጋችን የጤና ጕድለት፣ ረሃብ፣ ጥም፣ እርዛት፣ የተፈጥሮ መዛባት (ለምሳሌ ድርቅ፣ ውርጭ፣ በረዶ…)፣ እኛን የሚያጠቁ አውሬዎች ሲያስፈራሩንና ሲያሰቃዩን እናያለን፡፡ በደመ ነፍሳችንም ኀዘን፣ ጭንቀት፣ መከራ፣ ሥቃይ፣ ፍርሐት፣ ኃፍረት፣ ውርደት፣ ጥቃት ይደርስብናል፡፡ በመንፈሳችንም የኃጢአተኝነት፣ የበደለኝነት፣ ለኃጢአታችን የሚከፈል ዕዳ እንዳለብን እናስባለን፡፡ “ከዚኽ ኹሉ ማን ያስመልጠኛል? ማን ይታደገኛል?” ስንል ፈጣሪያችንን እንድንፈልግ እንገደዳለን፡፡
 እነዚኽ ከላይ የጠቀስናቸው ምሳሌዎች በጭራሽ የማንክዳቸው እውነቶች ናቸው፡፡ ለዚኽም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ኾነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ኹሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ኹሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢኾንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” ያለው /ሐዋ.17፡26-27/፡፡ ነገር ግን ኹሉም ሰው ፈጣሪውን አግኝቶታል ማለት አንችልም፡፡ ለዚኽ ዋና ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች አስተሳሰባቸውን ከትክክለኛው መንገድ ይልቅ በአሳሳችና ቅያስ ጐዳና ስለለወጡ ነው፡፡ አንዳንዶች ምንም ማድረግ በማይችሉ ፍጥረታት ይደገፋሉ፡፡ አንዳንዶች በአዕምሮአቸው በፈጠሩት ሌላ ፈጣሪ (ያውም ኅሊናቸው ውስጥ ካልኾነ በቀር ህልውናና አቋም የሌለው) ይደገፋሉ፡፡ “እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ ርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ዠምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ኾኖ ይታያልና፤ ስለዚኽም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ኾኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ” /ሮሜ.1፡19-20/።
2.   እግዚአብሔር በእግዚአብሔርነቱ የማይወሰን፥ የፍጡራን የተፈጥሮ አቋም፣ ዐቅምና ችሎታ ግን የተወሰነ ወይም የተመጠነ ስለኾነ፤
 በግዘፍ ያለና በችሎታው ውሱን የኾነው የሰው አቋም የማይታየውንና የማይወሰነውን መለኮታዊ ባሕርይን መጨበጥና መወሰን አይችልም፡፡ ይኸውም ሊቁ አባ ሕርያቆስ፡- “ይኽን ባሰብኍ ጊዜ ሕሊናዬ ወደ ላይ ሊወጣና ተሠውሮም ወጥቶ ሕያው የኾነ ጌታ የሚሠወርበት መጋረጃን ሊገልጥ ይፈቅዳል፡፡ ወዲያውም ከሚነድ እሳት ይፈራና የአየራት ግማሽ እንኳ ሳያጋምስ (ሳይደርስ) ይቀራል፡፡ ይኽን ባሰብኍ ጊዜም ሕሊናዬ በነፋስ ትከሻ ሊጫንና ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ዳርቻዎችም ኹሉ ሊበር ይፈልጋል፡፡ በኹሉም አከባቢና በኹሉም ዘንድ ሊጋልብ ይፈቅዳል፡፡ ዳሩ ግን መቀጠል ይሳነውና መዠመሪያ ወደነበረበት አቋም ይመለሳል” በማለት እንደመሰከረው ከዐቅምና ከችሎታ ማነስ የሚመጣ መሳን (አለመቻል) ነው /ቅዳሴ ማርያም፣ ቁ.85-88/፡፡ ካለመቻላችን የተነሣ እግዚአብሔርን ስላላወቅነው ግን፥ አስቀድመን እንደተናገርን የለም አንለውም፡፡ ይኸውም አንድ ማየት የተሳነው ሰው ፀሐይን ስላላያት የለችም እንደማይላት ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔርስ ይቅርና የፍጡራንን ህላዌ ጨርሶ ሊመርምር የቻለ የለም፤ ደግሞም አይችልም፡፡ ስለ ፀሐይ ማን ያውቃል? ስለ ከዋክብት ማን ያውቃል? ሰው ስለነዚኽ ማወቅ ካልተቻለውማ ስለ ፈጣሪያቸው እንደምን ማወቅ ይችላል? ስለነዚኽስ ይቅርና ስለ ገዛ ሕሊናው ምን ያውቃል? ስለ ገዛ ሕሊናው ማወቅ ካልቻለ ሕሊናን ስለ ፈጠረማ እንደምን ይችላል?
3.   ሰው ኹሉ በአዳም በደል ምክንያት ትክክለኛ የማሰብ ችሎታው ስለተበላሸበትና ስለወደቀበት፥ ራሱም ከሰይጣን ገዢነት ሙሉ ለሙሉ ስላልተላቀቀ በተጣራ አዕምሮ እግዚአብሔርን ሊፈልግና ሊመረምር ዐቅም የለውም፡፡
ታድያ የእግዚአብሔርን መኖር የምናውቀው እንዴት ነው?
 ምንም እንኳን ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ጌትነትኅ በአንተ ዘንድ የተሠወረ ነው፤ አንተ በአንተ አለኽ፤ ራስኽን ለራስኽ መጋረጃ አድርገኽ ትኖራለኽ፡፡ ራስኽን በራስኽ ትሠውራለኽ” እንዳለው እግዚአብሔር ከሕሊናት (ከምናስበው) በላይ ቢኾንም፥ ጭራሽ ልናገኘው አንችልም ማለት ግን አይደለም /ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፣ 1፡13/፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን ሰው ልቡናው ውስጥ በተቀመጠለት የመሻት አዕምሮው ተመርቶ ፈጣሪውን ቢፈልግ ያገኟል፡፡ ሊቃውንቱ “እግዚአብሔር በመሔድ አይገኝም፤ ቢፈልጉት ደግሞ አይታጣም” ያሉትም ስለዚኹ ነው /ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት፣ ገጽ 291፣ ቁ.11/፡፡ በመሔድ አይገኝም ማለት በሳይንስ፣ በመመራመር፣ በፍልስፍና፣ በሙከራ፣ በዳሰሳ አይገኝም ሲሉ ነው፡፡ ታድያ እንዴት ነው የሚገኘው?
·        እግዚአብሔር ራሱ ለሰው ከሚሰጠው የራሱን መገለጥ፤
 ይኸውም “ሥጋና ደም ይኽን አልገለጸልኽምነገር ግን በሰማያት የሚኖር አባቴ ይኽን ገልፆልኻልና” እንዳለው ነው /ማቴ.16፡17/፡፡ ፍጥረት ኹሉ ለርሱ የተፈጠረ ነውና፥ ፍጥረት እንዲያውቀውም ራሱን ይገልጥለታል ማለት ነው (ኹሉ ከርሱ፣ በርሱ፣ ለርሱ የተባለውም ይኽንኑ ነው)፡፡ አዳም /ዘፍ.3፡9-10/፣ ኖኅ /ዘፍ.7፡1/፣ አብርሃም /ዘፍ.18፡27/፣ ሙሴ /ዘጸ.3፡6/፣ ነቢያት /ኢሳ.6፡1-6፣ ዕንባ.3፡2/፣ ሐዋርያት የእግዚአብሔርን መኖር ያወቁት በዚኹ መንገድ ነው፤ ራሱ ከሰጣቸው የራሱ መገለጥ፤ ቃል በቃል አነጋግሯቸዋል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንኳን የተጻፉት በዚኹ መንገድ ነው፤ በመገለጥ /2ኛ ጴጥ.1፡19-20/፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ” ይላል /2ኛ ሳሙ.23፡2-3/፤ ነቢዩ ሳሙኤልም ይኽን መገለጥ ባገኘ ጊዜ “ባርያኽ ይሰማኻልና ተናገር” አለ /1ኛ ሳሙ.3፡10/፡፡ ስለዚኽ እግዚአብሔር ስለራሱ ካልገለጠ ማንም ሊያውቀው አይችልም፡፡ “የክርስትና ሃይማኖት የመገለጥ ሃይማኖት እንጂ ሰዎች በስምምነት ቃለ ጕባኤ ይዘው በጠረጴዛ ዙርያ ያጸደቁት አይደለም” የምንለውም ከዚኹ አንጻር ነው፡፡
·        ከእግዚአብሔር ቃል፤
  ሌላው እግዚአብሔርን የምናውቅበት መንገድ የራሱ እስትንፋስ የኾኑና ፈቃዱን የገለጠባቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ገና ሲዠምር “በመዠመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት የእግዚአብሔርን መኖር በመናገር ነው /ዘፍ.1፡1/፡፡ “በፍጡራን ኹሉ ዘንድ ፈጣሪን የሚመስለው የለም፡፡ ከንግግር በላይ ነው፡፡ ለመመርመር የማይደፈር (የማይቻል) ነው፡፡ ይኽን ታላቅ ምሥጢርና አስደናቂ ሥራውን ያገኙ ዘንድ ከላይ ከታችም ፍጥረታት ኹሉ ማወቁን አይችሉም፡፡ ነገር ግን እኛን በምሕረቱ ስለማረን፤ ለእኛ ባለው ደግነት ለእኛ ባሳደረብን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ይኽን ዐወቅን፡፡ እንዲኹም ንጹሐን ከኾኑት አበው፣ ደጋግ ከኾኑ ነቢያት ልንረዳው ቻልን፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እምነት ባስተማሩ በደጋግ መምህራን ትምህርትም ተረዳነው እንጂ፤” /የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ስኑትዩ፣ ሃይ. አበ. 110፡13/፡፡ “ይኽ እንደምን ተደረገ አንበል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደተናገሩ ረቂቅ የኾነ የማይመረመር የመለኮትን ነገር ሳንጠራጠር እንመን እንጂ፡፡ አብ የማይማረመር ነው፤ ወልድም የማይመረመር ነው፤ መንፈስ ቅዱስም የማይመረመር ነው፡፡ … እንደምን ኾነ በምን ሥራ ተደረገ ብለን አንመርምር፡፡ የፈጠረ ርሱ ነውና፡፡ ዕውቀትን ኹሉ ለእግዚአብሔር እንተው እንጂ የሚበልጠው ትእዛዝም በኦሪት በነቢያት በወንጌል በሐዋርያት ቃል እናምን ዘንድ ነው” /ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ሃይ.አበ.28፡39-41/፡፡ 
·        በሃይማኖት (በእምነት)፤
 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልጓልና” እንዳለው /ዕብ.11፡6/ እግዚአብሔር መንፈስ ስለኾነ፥ በመንፈሳዊ እጅ እንጂ በሥጋዊና ደማዊ እጅ (በሳይንሳዊ ምርምር) ልናውቀውና ልንዳስሰው አንችልም፡፡ እምነት ያስፈልጋል፡፡ ከትዕቢት፣ ከትምክሕት የነጻ ልቡና ያስፈልጋል፡፡ ተመስጦ ያስፈልጋል፡፡ ፆም ጸሎት ያስፈልጋል፡፡ ይኽን ስናደርግ የእግዚአብሔርን መኖር በትክክል እናውቃለን፡፡ “አንተ ግን ታውቅ ዘንድ የምትፈልግ ከኾንኅ የምድር አኗኗርኽን ተው፤ ከዋክብትንና የሥርዓታቸውን አቀማመጥ ተሻገር፡፡ ከዚኽ ኹሉ በላይም ከፍ ከፍ ካልኅ በኋላ የማይጨፈለቀውን አንዱን ልዩ ሦስትን በልቡናኽ አስብ” /ቅዱስ ያሬድ፣ ድጓ ስብከት መኃትው/፡፡ “እግዚአብሔርን ማወቅን ልንገልጽልኅ፣ አንተም ለራስኽ ልትመረምር ከወደድክ ሥጋዊ ደማዊ ግብርን ከአንተ አርቅ፡፡ ከምድራዊ ሥራ ራቅ፤ ከዓለማዊ ግብርም ተለይ፡፡ ሰማያዊ ነገርን አስብ፤ በፍጥነት የሚለዋወጡትንም ሰዓቶችን ዕወቅ፡፡ የከዋክብትን ጌጥ የሚያስደንቁትን ኹሉ ተው፡፡ ከምድር ያሉትንም ፍጥረታትን ተው፡፡ የሚመላለሱባቸውንም ሕግጋት ተው፡፡ የፀሐይንና የጨረቃን አስደናቂዎችን ከዋክብትን ኹሉ የተዋበና የሚያምር አከባቢያቸውን ኹሉ ለመረዳት ተጣጣር፡፡ የሚያስደንቅ ክበባቸውንና በየወገናቸው እንዴት እንደሚቀራረቡ ሲብለጨለጩ፣ ሲያብረቀርቁ ሲመላለሱ፣ በየጊዜው እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚቀራረቡና እንዴት እንደሚራራቁ ይኽን ኹሉ ለማወቅ መርምር፡፡ ይኽን ኹሉ መርምረኽ ከተረዳኽ በኋላ ከዚያው ወደ ሰማያት ከፍ ከፍ ብለኽ ውጣና በዚያን ጊዜ በሕሊናኽ ብቻ መንፈሳውያን ሠራዊት ወዳሉበት፣ ሰማያውያን መላዕክትና የዙፋን ቤቶች (ኪሩባውያን) ሥልጣናት አጋዕዝት ጌቶችና ኃይላት አለቆችና መኳንንት ወዳሉበት ደረጃና ቦታ መጥተኽ ተመልከት፡፡ ከዚኽም በኋላ ይኽን ኹሉ ፍጥረታት ካለፍኅ ወዲያ ሕሊናኽም እነዚኽን ኹሉ አልፎ ወደላይ መውጣት ከቻልኽ ከፍጡራን ኹሉ በላይ ወደሚኾን ነባቢ ወደኾነው የማይፋለስ ዙፋን በሚገኝበት በአርያም ላይ የልብኽን ዐይኖች ከፍ ካደረግኽ የማይታመም የማይደክም ፈጽሞ መለወጥ የሌለበትን የመለኮት ባሕርይ በዐዋቂ በንጹሕ ልቡና አስተውል” /ባስልዮስ ዘቂሣርያ፣ ሃይ.አበ.33፡15-20/፡፡  
·        በራዕይ፤
 ይኸውም ለሐዋርያት በደብረ ታቦር፣ ለዮሐንስ ወንጌላዊ በፍጥሞ ደሴት፣ ለቅዱስ ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ እንደታያቸው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በራዕይ ሲገለጥም፥ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መጠን መናገር እንጂ “እግዚአብሔር መልኩና ቁመቱ እንደዚያ ነው” ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር “ብርሃን ነኝ” ሲል ስለ አዕምሮአችን ደካማነት በብርሃን እንድንመስለው ስለፈቀደ እንጂ ከብርሃንም የሚያልፍ ነው፡፡ “ከነገር ኹሉ በፊት አስቀድሜ ለእግዚአብሔር ምንም ምሳሌ የለውም፤ በምንም በማናቸውም ሊመስሉት አይቻልም ብዬ በመናገር እዠምራለኍ፡፡ ልቡናዎቻችን ግን ደካማዎች ስለኾኑ በምሳሌ እንድንጠቀም ከፍለንም እንድንረዳ በነርሱ ልንመስለው ያስገድዱናል” /ሳዊሮስ ዘእስሙናይን፣ ገጽ 142/፡፡ 
·        በሥነ ፍጥረት፤
 ከትንኟ ዠምሮ እስከ ዝሆኑ፥ አዕምሮ ከሌለው ዠምሮ ከፍተኛ አዕምሮ እስካለው ፍጥረት ድረስ ኹሉም የእግዚአብሔርን መኖር ይመሰክራሉ፡፡ “እንስሶችን ጠይቅ ያስተምሩህማል፡፡ የሰማይ ወፎችን ጠይቅ ይነግሩህማል፡፡ ወይም ለምድር ተናገር ርሷም ታስተምርሃለች፡፡ የባሕር ዓሣዎችም ይነግሩሃል፡፡ የእግዚአብሔር እጅ ይኽን እንዳደረገ ከእነዚኽ ኹሉ የማያውቅ ማን ነው?” /ኢዮብ.12፡7-9/፡፡ “ሊቀ ነቢያት ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ፍጥረት ይናገራል፤ ይኸውም ሥነ ፍጥረትና መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ምስክሮች ስለኾኑ ነው፡፡ ሥነ ፍጥረት ስለምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ስለምናነበው ስለ እግዚአብሔር መኖር ይመሰክሩልናል፡፡ እነዚኽ ኹለቱም ዘወትር በኹሉም ስፍራ የሚገኙና የእግዚአብሔርን መኖር ለሚጠራጠሩ ሰዎች የሚገስጹ ናቸው” /St. Ephrem the Syrian, Hymns on Paradise 5:2/፡፡እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ ርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ዠምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ኾኖ ይታያልና፤” /ሮሜ.1፡19/፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም፡- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል፤” ብሏል /መዝ.19፡1/፡፡
·        በታሪክ አስረጂነት፤
 የሰው ልጅ ወደዚኽች ምድር ከመጣበት ዘመን አንሥቶ በፈጣሪ የማያምን እንደሌለ የተረጋገጠ ነው፡፡ ምናልባት ፈጣሪውን በትክክል ላያውቀው ይችል እንደኾነ እንጂ፤ ከርሱ ውጪ ሌላ ኃይል እንዳለ ግን ያምናል፡፡ ፍልስፍናው፣ የፖለቲካው ርዕዮቱ፣ አላህ፣ ድንጋዩ፣ ሰይጣን፣ ወንዙ አምላክ ነው ብሎ ሊያምነው ይችላል፡፡ ይኽን አስቀድመን እንደተናገርነው፥ (እግዚአብሔር) ርሱን እንዲፈልጉ የሚገደዱበት አዕምሮ በልቡናቸው ውስጥ ስላሳደረ ነው፡፡ በየትኛውም ዓይነት ኹኔታ ውስጥ ይኹን ሰው አደጋ ሲደርስበት ፍርሐት ይይዟል፤ ረዳት ይፈልጋል፡፡ ይኽ ርዳታ እንዲያደርግለት የሚፈልገው ኃይልም እግዚአብሔር ነው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ ለዘለዓለሙ አሜን!!! 


1 comment:

  1. አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን ወንድማችን

    ReplyDelete