Pages

Wednesday, December 31, 2014

“ነገር ኹሉ ለበጐ እንዲደረግ እናውቃለን” /ሮሜ.8፡28/

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 23 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  አንዳንዴ በሕይወታችን ምንም የማይጠቅሙ ነገሮችን ልንመርጥ እንችላለን፡፡ የሚያስፈልገንና የሚጠቅመን ግን መንፈስ ቅዱስ ሲመርጥልን ነው፡፡ አደጋና ስጋት፣ በሽታና ስቃይ፣ እጦትና ችግር፣ ራብና ጥማት፣ ኀዘንና ትካዜ የሌለው ሕይወት እጅግ ጠቃሚ እንደኾነ አድርገን እናስባለን፡፡ ነገር ግን ይኽ የሌለው ሕይወት ኹሉ ጠቃሚም ላይኾን ይችላል፡፡
  እስኪ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን ሕይወት እንደ ምሳሌ አንሥተን እንመልከተው፡፡ እግዚአብሔር በሰጠው ሀብተ ፈውስ የዕውራንን ዐይን የሚያበራው፣ የለምጻሞችን ለምጽ የሚያነጻው፣ ሙታንን የሚያነሣው፣ ሌላ ይኽን የመሰለ ተአምራትን የሚያደርግ ታላቁ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋውን የሚጐስም የሰይጣን መልእክተኛ ነበረው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የሰይጣን መልእክተኛ ያለው አባቶች በሦስት መንገድ ይተረጕሙታል፡፡ ሰይጣን ማለት ጠላት፣ ክፉ፣ ተቃዋሚ ማለት ነውና /1ኛ ነገ.5፡4/ ቅዱስ ጳውሎስ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ ሲል፡-

·        አንደኛ ጐኑን የሚወጋ ቀጭን ውጋት እንዲኹም በዘመናዊው አጠራር ሚግሬን ብለን የምንጠራው የራስ ፍልጠት፤
·        ኹለተኛ ወንጌል እንዳይስፋፋ የሚቃወም አላዊ ንጉሥ (እለእስክንድሮስ)፣
·        ሦስተኛ ምእመናን ከዋሉበት አላሳድር ካደሩበት አላውል እያለ ክርስቶስን ዕሩቅ ብእሲ (ተራ ሰው) እያለ ወንጌልን ዲቃላ ሕግ የሚል ሐሰተኛ ወንድም ተነሣብኝ ሲል ነው ይላሉ /የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከነትርጓሜው፣ ገጽ.239/፡፡
 እንግዲኽ ልብ በሉ! ቅዱስ መልአክ አይደለም፤ ሰይጣን፡፡ ያውም እግዚአብሔር የሰጠው፡፡ ሐዋርያው ይኽንን ያርቅለት ዘንድ እግዚአብሔርን ሦስት ጊዜ ቀኖና ገብቶ ለምኖት ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልስ ግን አይኾንም የሚል ነበር /2ኛ ቆሮ.12፡8-9/፡፡ ስጦታ ነዋ! እግዚአብሔር ደግሞ ክፉ ነገር አይሰጥም፤ እንኳንስ እግዚአብሔር ይቅርና ሰውም ለወዳጁ መጥፎ ስጦታ አይሰጥም፡፡ በእኛ እይታ አኹን ይሔ ኹሉ ክፉ ነው፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ግን ግሩም ስጦታ ነው፡፡ በኋላ ላይ ሐዋርያው ሰይጣኑ ለምን እንደተሰጠው ተረድቷል፤ “እንዳልታበይ ነው” ሲልም ነግሮናል /2ኛ ቆሮ.12፡7/፡፡ ከዚኽ በኋላ ነበር ሐዋርያው ሲያሳድዱት፣ ሲያንገላቱት፣ ሲያስጨንቁት ደስ ይለው የነበረው /2ኛ ቆሮ.12፡10/፡፡ “መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፡፡ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል” ያለውም ስለዚኹ ነው /ሮሜ.8፡26/፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃዱም ይኸው ነው፤ የራሳችንን ሳይኾን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስን ሐሳብ እንድናደምጥ፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ የምናደምጥ ከኾነ በስደታችን እንደሰታለን፤ በእንግልታችን ሐሴት እናደርጋለን፤ በሚያስጨንቁን መካከል ደስ ይለናል፡፡ ስደቱ ስደት፣ እንግልቱ እንግልት፣ ጭንቀቱም ጭንቀት የሚኾንብን ከእግዚአብሔር ሐሳብ ይልቅ በራሳችን ሐሳብ ስንያዝ ነው፡፡
 እንደ ራሳችን ሐሳብ ሳይኾን እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ስንጓዝ ግን ነገር ኹሉ ለበጐ ነው /ሮሜ.8፡28/፡፡ ነገር ኹሉ ሲባልም በእኛ እይታ በጐ ነው የምንለው ብቻ አይደለም፤ ክፉ ነው የምንለውም ጭምር እንጂ፡፡ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ሲኾን ማግኘትም ማጣትም፣ ጤንነትም በሽታም ለበጐ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ መልካም የሚያደርግልን በጐ ነው ብለን በምናስበው ነገር ብቻ አይደለም፡፡ እጅግ ክፉና አስቸጋሪ መስለው ከሚታዩን ኹኔታዎችም ለእኛ ለልጆቹ እጅግ የሚደንቅና በጐ ነገርን ማድረግ ይችልበታል፡፡ “ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፤ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ” እንዲል ቃሉ /መሳ.14፡14/፡፡
  ቅዱስ ጳውሎስ የሰይጣን መልእክተኛ ስለተሰጠውና በሥጋ ስለታመመ ሰይጣኑ ወይም የሥጋው ድካም መንግሥተ ሰማያትን ከመግባት አይከለክለውም፡፡ ይልቁን ይኽን የሚከለክለው ትዕቢቱ ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ከመግባት የሚከለክለው አገልግሎቱ በእግዚአብሔር ጸጋ ሳይኾን በራሱ ጉልበት የሚያገለግል እንደኾነ ካሰበ ነው፡፡
  በእኛ እይታ ወደ እሳት ውስጥ መጣል ክፉ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የምንጓዝ ከኾነ ግን ይኽም ክፉ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሳቱ እቶን እንዳይጣሉ አላደረገም፤ ከተጣሉ በኋላ ግን እሳቱን ውኃ አደረገላቸው፡፡ ንጉሡም የተደነቀው በእኛ እይታ ሠለስቱ ደቂቅ “ክፉ ነገር (እሳት) ውስጥ” ሳሉ ነው፡፡ በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ በእኛ እይታ ተገርፏል፤ ተንገላትቷል፤ ተሰቅሏል፤ እግሮቹ ተሰብረው ሞቷል፡፡ ገነትን ለመግባት ግን የቀደመው የለም፡፡ መገረፉ፣ መንገላታቱ፣ መሰቀሉ፣ እግሮቹ መሰባራቸው ለበጐ ነበር ማለት ነው፡፡  
 እግዚአብሔር ነገርን ኹሉ በጐ እንዲያደርግልን ከፈለግን አንድ ነገር ብቻ ይጠበቅብናል፤ እንደ ሐሳቡ መጓዝ፡፡ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የማንሔድ ከኾነ ግን በእኛ እይታ ጠቃሚ ነው በምንለው ነገር እንኳን እንጐዳለን፡፡ እዚኽ ጋር አይሁድን እንደ ምሳሌ ልንወስዳቸው እንችላለን፡፡ አይሁድ ተአምራትን ይወዳሉ /1ኛ ቆሮ.1፡22/፡፡ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ስላልሔዱ በነቢያትም፣ በጌታም፣ በሐዋርያትም፣ የተደረገው ተአምራት ምንም አልጠቀማቸውም፤ እንደዉም የባሰ ጐዳቸው እንጂ፡፡ ጌታችንን እንዲሰድቡት አደረጋቸው እንጂ አንዳች አልጠቀማቸውም /ዮሐ.8፡48/፡፡ እንደ ጌታ ሐሳብ ይጓዙ ስላልነበረ “ከባሕርይ አባቴ ጋር አንድ ነኝ” ሲላቸው ሊገድሉት ነው የተነሣሡት፡፡
 አይሁድ ጌታችንን የገደሉት እንደ ሐሳቡም ያልሔዱት ለመዳን ስላልጠራቸው አልነበረም፡፡ ጥሪው ያልጠቀማቸው፥ እንደ ሐሳቡ ለመሔድ “አቤት!” ስላላሉ ነው፡፡ እንደ ሐሳቡ ለሔዱት ግን የልጁን መልክ እንዲመስሉ ወስኗል፡፡ ልጁ በኵር ኾኖላቸው እነርሱም የእግዚአብሔር ልጆች እንዲኾኑ አድርጓቸዋል፡፡ በኵር ኾነላቸው መባሉም በትስብእቱ እንጂ በመለኮታዊ ባሕርዩ አይደለም፤ በመለኮታዊ ባሕርይ ልጅ ርሱ ብቻ ነውና፡፡
 የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅዱ እንደዚኽ ነው፤ ሰው ኹሉ እንደ ሐሳቡ ተጕዞ የልጁን መልክ ይዞ ርስቱንና መንግሥቱን እንዲወርስ፡፡ ዛሬ ወደ ክርስቶስ ስለቀረብን ድንገት የመጣን ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከዘለዓለም አንሥቶ ሐሳቡ ይኸው ነበር፤ የልጁ መልክ እንዲኖረን፡፡
 አስቀድሞ እንዲኽ የመረጣቸውን፣ የወደዳቸውን እንደ ሐሳቡም የተጓዙትን ነው ወደ ዘለዓለማዊ ዕቅዱ የጠራቸው፡፡ መጥራት ብቻም አይደለም፤ በሃይማኖት ያጸደቃቸው፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድም ውሉዳን (ልጆች) ብሎ ያከበራቸው፡፡
 እንግዲኽ ስለዚኽ ነገር ምን እንላለን? በጥቂቱ እንደ ሐሳቡ ስለ ተጓዝን ነገር ኹሉ ለበጐ ካደረገልን፣ በእኛ እይታ መጥፎ የሚመስለውን እንኳን ጣፋጭ ካደረገልን ምን እንላለን? ዘለዓለማዊ ዕቅዱ የልጁን መልክ እንድንይዝ ከኾነ፣ ይኽንን እንድንይዝ ከወሰነን፣ ለተወሰንንበት ዓላማ ከጠራን፣ ጠርቶ ካጸደቀን፣ በልጅነት ሥልጣን ካከበረን ምን እንላለን?  
 በሰው እይታ አሳፋሪ በሚመስል፣ በእግዚአብሔር እይታ ግን እኛ የምንከብርበት ከኾነ ስለ ጌታችን መከራ መስቀል ምን እንላለን? እየሞተ፣ እየተገረፈ፣ እየተሰቃየ ካዳነን ስለዚኽ ድንቅ ጥበቡ ምን እንላለን? በእኛ እይታ በሕይወታችን እጅግ ቀፋፊ፣ አሳዛኝ፣ ኪሳራ፣ ዕድለ ቢስነት የሚመስሉ ነገሮችን ለበጐ የሚያደርግልን ከኾነ ተመስገን ከማለት በቀር ምን እንላለን?
  እንደ ሐሳቡ ከተጓዝንና ነገርን ኹሉ ለበጐ የሚያደርግልን ከኾነ ታድያ ማን ይቃወመናል? በእኛ እይታ ዓለም የእኛ ተቃዋሚ ናት፡፡ ክፉ መሪዎች የእኛ ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ግን እነዚኽ ኹሉ የእኛ ተቃዋሚዎች አይደሉም፡፡ እነዚኽ ኹሉ የእኛን ክብር፣ የእኛን ሹመትና ሽልማት የሚጨምሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው እንዲኽ እንድንከብር አስበውልን አይደለም፤ እንደ ሐሳቡ ስለተጓዝን እግዚአብሔር የእነዚኽን ክፋት ለእኛ ጥቅም (ለበጐ) ስላደረገልን እንጂ፡፡
  በእኛ እይታ ዲያብሎስ ክፉ ነገር በኢዮብ ላይ አመጣበት፡፡ ሚስቱንና ጓደኞቹን አነሣሣበት፡፡ ንብረቱንና ልጆቹን አሳጣበት፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ግን እነዚኽ ኹሉ ኢዮብን የሚጠቅሙ ነበሩ፡፡ ኢዮብ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የሚሔድ ቅን ሰው ነበርና ነገር ኹሉ ለበጐ ኾነለት፡፡ በሐዋርያት ዘንድ የኾነውም እንደዚኹ ነው፡፡ በእኛ እይታ ዓለም ኹሉ ሐዋርያትን የሚቃወም ነበር፡፡ አይሁድም ብትሉ፣ አሕዛብም ብትሉ፣ ረሃቡም ብትሉ፣ ማጣቱም ብትሉ፣ ነገሥታቱም ብትሉ፣ ተራው ሰው እንኳን ሳይቀር የሐዋርያት ተቃዋሚዎች ነበሩ፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ግን ከእነዚኽ አንዱ ስንኳ የሐዋርያት ተቃዋሚ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ክብር እንዲያገኙ አደረጋቸው እንጂ፤ ሐዋርያት፡፡ በዓለም ላይ እጅግ የተከበረ ነው፤ የተቀናጣ ነው የምንለው ንጉሥ ወይም የሀገር መሪ እንኳን እንደነዚኽ ሐዋርያት የከበረ የለም፡፡ ዛሬ ዓለም ኹሉ ሐዋርያት እነማን እንደኾኑ ያውቃል፤ ክብራቸውንም እንደዚኹ፡፡ ሐዋርያትን ያሳደድዋቸው ስማቸው ማን ማን እንደሚባል የሚያውቅ አለን? ታድያ ማን ነው የተጐዳው? ማንስ ነው የከበረው? የተሰደዱት ሐዋርያት ወይስ አሳዳጆቹ?
  በዓለም ላይ እጅግ የተከበሩ ናቸው፤ እጅግ የተፈሩ ናቸው፤ እንዲኹም እጅግ ኃያላን ናቸው የምንላቸው መሪዎች ባላንጣዎች አሏቸው፡፡ በስውርም በገሃድም ተቃዋሚዎች አሏቸው፡፡ እነርሱም ይኽን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እንዳይሞቱ ፈርተው ታጅበው ነው የሚሔዱት፡፡ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የሚሔዱት ግን ማንም አይቃወማቸውም፡፡ ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ አይደሉም፤ አጋንንትም ጭምር እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የሚሔዱትን አይቃወሟቸውም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ለሚሔዱ ሰዎች ገንዘባቸውን ብንወስድባቸው እኛ “አትስረቅ” የሚለውን ሕግ ተላልፈን ሌቦች እንባል እንደኾነ እንጂ እነርሱ አይጐዱም፤ እንደዉም ይኽን ስለታገሡ ሹመት ሽልማታቸው ይጨምራል፡፡ ብንሰድባቸው እኛ እንጐዳ እንደኾነ እንጂ እነርሱ አይጐዱም፤ እንደዉም ክፉውን በክፉ አትመልስ የሚለውን ሕገ አምላክ አክብረው ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ይቀበላሉ፡፡ የሚበላ ነገር ብንከለክላቸው እኛው በጨካኝነታችን ፍርድ እንቀበል እንደኾነ እንጂ እነርሱ ምንም አይጐዱም፡፡ የመጨረሻው ክፉ ነው ብለን በምናስበው በሞት እንኳን “ብንቀጣቸው” የሰማዕትነትን አክሊል እንዲቀዳጁ እናደርጋቸዋለን እንጂ ምንም አንጐዳቸውም፡፡ አቤት! ክርስትና እንዴት ግሩም ሕይወት ነው! ለዚኽስ አይደል ሐዋርያት “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከኾነ ማን ይቃወመናል?” ያሉት?!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!


ምንጭ፡- ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች

1 comment: