Pages

Tuesday, December 30, 2014

ለይሖዋ ምስክሮች ኑፋቄ የተሰጠ ምላሽ (ክፍል አራት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ታኅሳስ 21 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

የሥላሴ ትምህርት በጕባኤ ኒቅያ አበው
 ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች እንደምን ሰነበታችኁ? በጥያቄና መልስ ዓምዳችን ለይሖዋ ምስክሮች የስሕተት ትምህርት ኦርቶዶክሳዊ ምላሽ መስጠት ከዠመርን የዛሬው አራተኛው ክፍል ነው፡፡ በክፍል አንድ ምላሻችን የይሖዋ ምስክሮች የስሕተት ትምህርቶች ምን ምን እንደኾኑ፥ እንዲኹም መሠረታዊ የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት በመጠኑ ዐይተናል፡፡ በክፍል ኹለት ክፍለ ጊዜአችንም ከብሉይ እና ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በማመሳከር ምሥጢረ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እንደኾነ ተመልክተናል፡፡ በክፍል ሦስትም ከሐዋርያነ አበው ዠምረን እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምን ብለው እንዳስተማሩ ተመልክተናል፡፡ ስለ ቅድስት ሥላሴ የመጨረሻው ክፍል በኾነው በዛሬው ምላሻችን ደግሞ በአጠቃላይ በጕባኤ ኒቅያ የነበረውን ሒደትና ውሳኔ እንመለከታለን፡፡ ይኽን የምናደርግበት ምክንያትም በክፍል ሦስት ምላሻችን እንደነገርናችኁ የይሖዋ ምስክሮች የሥላሴ ትምህርት የተወሰነው በ325 ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ አስገዳጅነት ነው ስለሚሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን አሜን!!!

 ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የነበረው አንቀጸ ሃይማኖት በየአከባቢው በሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት የሚዘጋጅ እንጂ ዓለማቀፋዊ ይዘት አልነበረውም፡፡ ዓለማቀፋዊ ይዘት ባይኖረውም ግን በተለያየ አገላለጽ የሚገለጽ ስለ እውነተኛይቱና ቀጥተኛይቱ ሃይማኖት የሚመሰክሩበት ነበር፡፡ ይኽ የኾነበት ዋናው ምክንያትም በየአከባቢው የሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት በአከባቢያቸው በእምነትም ይኹን በምግባር ችግር የሚያመጡ ሰዎችን ትምህርታቸው ስሕተት እንደኾነ ምእመናን ዐውቀው እንዲጠበቁ ለማድረግ ነበሩ፡፡ እንዲኽ ሲባልም ያልነበረ ነገር አምጥተው ይጨምሩ ነበር ማለት ሳይኾን አንዱን እውነት ምእመናን ግራ እንዳይጋቡ በአጭርና ግልጽ በኾነ አገላለጽ ከነማብራርያው ይቀርብ ነበር ለማለት ነው፡፡ በ268 ዓ.ም. በጳውሎስ ሳምሳጢ ምክንያት በአንጾክያ በተካሔደው ጉባኤ የተዘጋጀው አንቀጸ ሃይማኖትም አንዱ ማሳያ ይኾናል፡፡ ከሐዋርያት በኋላ ዓለማቀፍ ጕባኤ ተካሒዶ ዓለማቀፍ ይዘት ያለው አንቀጸ ሃይማኖት የተዘጋጀው ግን በ325 ዓ.ም. በጕባኤ ኒቅያ ነው /Early Christian Creeds, By J.N.D. Kelly, pp205-207/፡፡ ለዚኹ ዓለማቀፋዊ ጕባኤ ዋናው ምክንያቱም የአርዮስ ክሕደት ነበር፡፡
የአርዮስ ግለ ታሪክ
·        በ257 ዓ.ም. በሊብያ ተወለደ፡፡
·        መዠመሪያ ክርስቲያን ነበር፡፡
·        ከቤተ ክርስቲያን ያጣላውን ትምህርት ያስተማረው ሉቅያኖስ ይባላል፤ በአንጾክያ ትምህርት ቤት፡፡
·        ትምህርቱን ሲጨርስ ወደ እስክንድርያ ሔደ፡፡
·        ዲቁናንም ከተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ (የእስክንድርያ ፓትሪያርክ) ተቀበለ፡፡
 በኋላ ግን ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ በራዕይ በተገለጠለት መሠረት አርዮስ ከባድ የስሕተት ትምህርት እንደሚያስተምር ዐወቀ፡፡ ከስሕተቱ እንዲመለስና በኦርቶዶክሳዊት እምነቱ እንዲጸናም አስጠነቀቀው፡፡ አርዮስ ግን አሻፈረኝ ብሎ በክሕደቱ ቀጠለ፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስም አርዮስን  ከክህነቱ ሽሮ አወገዘው፡፡
 ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ በዚያን ጊዜ በነበረው የክርስቲያኖች ስደት ምክንያት ወደ ወህኒ ወረደ፡፡ አርዮስም “ፓትሪያሪኩ ከውግዘቴ ሳይፈታኝ ሊሞት ይችላል” ብሎ በመፍራት ከውግዘቱ እንዲፈታው አማላጆችን ላከ፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ግን ውግዘቱን አጸናው፡፡ ይኽን ያደረገበት ዋና ምክንያት ምን እንደኾነም ለደቀ መዛሙርቱ ለአርኬላኦስና ለእለ እስክንድሮስ ነግሯቸዋል፡፡ እንዲኽ በማለት፡- “እግዚአብሔር የሰማያት አምላክ ሰማዕትነቴን ለፍጻሜ ለማድረስ ይርዳኝና ከዛሬ በኋላ ተመልሳችኁ በሕይወት አታገኙኝም፡፡ አንተ አርኬላኦስ ከእኔ በኋላ ፓትሪያርክ ትኾናለኽ፡፡ ወንድምህ እለእስክንድስም ከአንተ በኋላ ፓትሪያርክ ይኾናል፡፡ በአርዮስ ላይ ጨካኝ የኾንኩና የተደበቀ ተንኰል ያለኝ አይምሰላችሁ፡፡ አርዮስን ያወገዝኩት እኔ ሳልኾን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚኽች ሌሊት ጸሎቴን ጨርሼ በተኛኹበት ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚያበራና እስከ እግሩ ድረስም ረዥም ልብስ የለበሰ አንድ ወጣት ወደ እኔ ሲገባ አየኹ፡፡ ልብሱም ተቀድዶ የተቀደደውን ልብስ ቁራጭ በእጁ ይዞ ስላየኹት፡- ጌታዬ ሆይ! ልብስህን ማን ቀደደብህ ብዬ በመጮኽ ብጠይቀው ልብሴን የቀደደብኝ አርዮስ ነውና አትቀበለው፡፡ ይቅርታ እንድታደርግለት ሊጠይቁህ ዛሬ የሚመጡ ሰዎች አሉና አትታዘዛቸው አለኝ፡፡ ስለዚኽ እናንተም ከርሱ ጋር ኅብረት እንዳይኖራችኁ” ብሎ አደራ ሰጣቸው፡፡
 በ312 ዓ.ም. ላይ ግን አርኬላኦስ ፓትሪያርክ ሲኾን የተፍጻሜተ ሰማዕት የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል በአግባቡ ባለማጤን ከአርዮስ የተላኩ አማላጆችን በመቀበል አርዮስን ቅስና ሾመው፡፡ ኾኖም በፕትርክናው አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው በሞት ተለየ /ዐሥራት ገብረ ማርያም፣ ትምህርተ መለኮት፣ ገጽ 60/፡፡ ይኸውም በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የአባቱን የጴጥሮስን ቃል ኪዳን ስላልጠበቀ የመቅሰፍት ሞት ነው ተብሎ ይወሰዳል /የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ አባ ጐርጐርዮስ (የሸዋ ሊቀ ጳጳስ)፣ ገጽ 90/፡፡
 በ313 ዓ.ም. ላይም እለእስክንድሮስ ፓትሪያርክ ኾነ፡፡ ፓትሪያርክ እለስክንድሮስ በጣም የዋኅ ስለነበር በሕዝቡና በካህናቱ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነበር፡፡ ይኽን ያወቀ አርዮስም ፓትሪያርክ እለስክንድሮስን ያታልለው ዘንድ ሞከረ፡፡ ኾኖም ፓትሪያርኩ የዋኅነትን ከጥበብ ጋር የያዘ ስለነበር የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስን ቃል አሰበ፡፡ ንስሐ ካልገባ በቀርም ሊቀበለው እንደማይችል አስታወቀው፡፡ አርዮስ ግን ንስሐ ከመግባት ይልቅ የክሕደት ትምህርቱን አጠናክሮ ቀጠለ፤ እለእስክንድሮስንም በይፋ መቃወም ዠመረ፡፡ በሊብያ የነበሩ ኹለት ጳጳሳትንም እስከማሳመን ደረሰ፡፡
 አርዮስ ትምህርቱን ለማስፋፋት በቀላል አገላለጦች በግጥም እያዘጋጀ ለእንጨት ሰባሪዎች፣ ለውኃ ቀጂዎች፣ ለነጋዴውና ለአራሹ ያሰራጭ ነበር፡፡ የዛሬዎቹ የይሖዋ ምሰክሮችም የሚጠቀሙት በየመንገዱና በየጥጋጥጉ በመቀመጥ ይኽን የአርዮስ ዘዴ ነው፡፡ ሌሎች መናፍቃንም ቢኾኑ የተራውን ምእመን ልብ ለመሳብ የሚጠቀሙት በተለይ “መዝሙር” እና “ትራክት” ነው፡፡ በዚኹ “መዝሙር” እና “ትራክት” ምእመኑ በቀላሉ ሊረዳው የማይችል የኑፋቄ መርዝ ተለውሶበት የሚቀርብ ነው፡፡ ይኸውም አርዮስ ትምህርቱን በግጥሞቹ መካከል እየሰነቀረ ያቀርብ እንደ ነበር ማለት ነው፡፡
 አርዮስ ትምህርቱን በተጠናከረና በይፋ ማስፋፋት የዠመረው በ318 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንም የተቃውሞ ደወሏን በይፋ ማሰማት ግድ ኾነባት፡፡ በመኾኑም ፓትሪያርክ እለእስክንድሮስ በ319 ዓ.ም. ላይ በእስክንድርያ ጕባኤ አዘጋጀ፡፡ አርዮስና ተከታዮቹም ያለ ምንም መሸማቀቅ አመለካከታቸውን በጕባኤው ፊት ቀርበው እንዲያስረዱ ተደረገ፡፡ እለእስክንድሮስም ለእያንዳንዱ የአርዮስ የተሳሳተ አመለካከት መልስ ሰጠ፡፡ ኾኖም አርዮስ አልቀበልም አለ፡፡ እለእስክንድሮስም አርዮስን ከምእመናን አንድነት ለየው፡፡
 አርዮስ እጅግ በጣም እየባሰበት ሔደ፡፡ ታጋሹ፣ የዋኁና የዕድሜ ባለጸጋው ፓትሪያርክ እለእስክንድሮስም ለኹለተኛ ጊዜ በ321 ዓ.ም. ላይ አንድ መቶ የሚያኽሉ የሊብያና የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶሳት የተገኙበት ሌላ ጕባኤ አዘጋጅቶ የአርዮስን አስተሳሰብ ገለጸላቸው፤ ብዙ ጊዜ እንደመከረውና ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልኾነም አስረዳቸው፡፡ አርዮስንም ከስሕተቱ እንዲመለስ ጠየቀው፡፡ አርዮስ ግን አኹንም እምቢኝ ስላለ ከኹለቱም በቀር በ98ቱ ጳጳሳት በአንድ ድምጽ ተወገዘ፡፡
 አርዮስ አመለካከቶቹን በዝርዝር የገለጠለት አውሳብዮስ ኤጲስ ቆጶስ ዘኒቆሚድያ ግን አርዮስን አይዞህ ብሎ ተቀበለው፡፡ አውሳብዮስ ዘኒቆምድያ አርዮስን አይዞህ ያለበት ዋናው ምክንያትም፡-
·        አንደኛ እለእስክንድሮስ የሰባልዮሳውያን ትምህርት ነው የሚያስተምረው ስላለው፤
·        ኹለተኛ በአንጾክያ ትምህርት ቤት አንድ ላይ ስለተማሩ የቅርብ ጓደኛው ስለነበረ ብቻ ሳይኾን አመለካከታቸውም አንድ ስለነበረ ነው፡፡
 በመኾኑም ከላይ እንደተናገርነው አውሳብዮስ ዘኒቆምድያ አይዞህ አለው፡፡ ኒቆሚድያ ማለት በዚያ ሰዓት ቁስጥንጥንያ እስክትመሠረት ድረስ የምሥራቁ ሮም ዋና ከተማ የነበረች ነች፡፡ አውሳብዮስ ዘኒቆሚድያም በቆስጦንጢኖስ ቤተ መንግሥት ባለ ሙሉ ሥልጣን ስለነበር ሥልጣኑን ተጠቅሞ በዚያ ቅርብ ርቀት የሚገኙትን ኤጲስ ቆጶሳት አርዮስን ደግፈው እለ እስክንድሮስን እንዲያወግዙ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ እንደተባሉትም በርሱ መሪነት በ322 እና በ323 ዓ.ም ላይ ባደረጉት ኹለት ተከታታይ ስብሰባ ተሰብስበው ፓትሪያርክ እለእስክንድሪስን “ሰባልዮሳዊ” ብለውና ውሳኔውን ሽረው አርዮስን ከውግዘቱ “ፈቱት”፡፡ እዚኽ ጋር መረሳት የሌለበት ጕዳይ ቢኖር በዚኽ ጕባኤ የተሰበሰቡት “ኤጲስ ቆጶሳት” አብዛኞቹ በሉቅያኖስ የስሕተት ትምህርት ተጠልፈው የነበሩና ከአርዮስ ጋር ተመሳሳይ አመለካከት የነበራቸው እንደኾነ ነው፡፡ በጣም የሚደንቀው ደግሞ ይኽ ኹሉ ሲኾን የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ መጠየቅ ሲገባትም አልተጠየቀችም፡፡
 አርዮስ ከዚኽ በኋላ ተመልሶ የሔደው ወደ እስክንድርያ ነበር፡፡ እዚያ ሔዶም ከዚኽ በፊት ሲያስተምረው ከነበረው በላይ ገፍቶበት ብዙ ሰዎችን ከክርስትና እምነት አስወጣ፡፡ በዚኽም ምክንያት በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን በቆስጠንጢኖስ ቤተ መንግሥትም ትልቅ ሥጋትን አሳደረ፤ አስተዳደራዊ ችግር ስለመሰለው፡፡ ቆስጠንጢኖስም አንድ የስፔን ጳጳስን ወደ እስክንድርያ በመላክ ነገሩ የሃይማኖት ወይም የአስተዳደር ችግር እንደኾነ እንዲመረምር ላከው፡፡ የተላከው ጳጳስም ነገሩ ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለው በመግለጥ ይኽ ሊፈታ የሚችለው በጕባኤ እንደኾነ ለንጉሡ ጠቆመው፡፡ ቆስጦንጢኖስ ጉባኤ ኒቅያን የጠራው በዚኹ ምክንያት ነበር፡፡
 የጉባኤው ሒደት
ሀ) የጕባኤው ተሳታፊዎች
 ለመዠመሪያ ጕባኤው እንዲደረግ ታስቦ የነበረው በዕንቆራ ነበር፡፡ በኋላ ግን ባልታወቀ ምክንያት በኒቅያ እንዲካሔድ ተወሰነ፡፡ በዚኽም መሠረት በጕባኤው ኤጲስ ቆጶሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተሰበሰቡ፡፡ ከተሰበሰቡት አባቶች አምስት ብቻ ከምዕራብ አውሮጳ የመጡ ሲኾኑ የተቀሩት ግን ምሥራቀውያን ነበሩ፡፡
 ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ እንደተናገረው ቁጥራቸው 318 ሲኾኑ ከእነዚኽም ውስጥ በሕይወታቸው በንጽሕናቸውና በቅድስናቸው መሰል ያልነበራቸው ነበሩ፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ በመክስምያኖስ ስደት ምክንያት ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጅ እግራቸው የተቈረጠ አባቶችም ነበሩበት፡፡ በተጨማሪም ተአምራትን የሚያደርጉ እጅግ ከፍ ያለ ዝና የነበራቸው ነበሩ፡፡
 በጕባኤው የተገኙት ግን እነዚኽ አባቶች ብቻ አልነበሩም፡፡ ሶዞሜን የተባለ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ እንደተናገረው የግሪክ ፈላስፎችና የአርዮስ ደጋፊዎች እንዳያሙ ተጠርተው መጥተው ነበር /ዝኒ ከማኁ፣ ገጽ 110/፡፡ 
ለ) ጕባኤውን እንዲመሩ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ተመረጡ፡፡
 ጕባኤው በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የመግቢያ ንግግር ተከፈተ፡፡ የመዠመሪያ አጀንዳ ያደረጉትም ጕባኤውን የሚመራ አባት መምረጥ ነበር፡፡ በመኾኑም ጉባኤውን እንዲመሩ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ተመረጡ፡፡ እነርሱም የእስክንድርያው እለ እስክንድሮስ፣ የአንጾክያው ኤውስጣቴዎስ እና ቆስጠንጢኖስ ነገሩን ያጠና ዘንድ ወደ እስክንድርያ ልኮት የነበረው የስፔኑ ኤጲስ ቆጶስ ኦስዮስ ናቸው /ዝኒ ከማኁ፣ ገጽ 111/፡፡ በዋናነት የመራው ግን ሊቀ ጳጳስ ኦስዮስ ነው፡፡
 ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤውን ጠራ እንጂ የይሖዋ ምስክሮች እንደሚሉት ንጉሡ ጉባኤውን አልመራውም፡፡ ጉባኤውን ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እንዳልመራውም በሚከተሉት ምክንያቶች መረዳት እንችላለን፡-
1.  የጉባኤው አጀንዳ ሃይማኖታዊ እንጂ አስተዳደራዊ ችግር ስላልኾነ ለሥልጣኑ የሚፈጥርበት ስጋት አልነበረም፡፡ በመኾኑም የራሱን አስተሳሰብ በጉባኤው ላይ ሊያስወስን ይችላል ተብሎ ሊታሰብ አይችልም፡፡
2.  ሊወስን ይችላል ተብሎ ቢታሰብ እንኳን ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ይልቅ ለነገሥታት ሐሳብ ይገዛሉ ተብሎ ሊገመት አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በፊት በነበረው የሰማዕታት ዘመን ክርስቲያኖች ከእምነታቸው ሊያያስወጧቸው ለሚሞክሩ ነገሥታት ትእዛዝ እንደማይታዘዙ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡
3.  ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በኋላ ላይ ከቅዱስ አትናቴዎስ ጋር የነበረው አለመግባባትም ይኽን ፍንተው አድርጐ ያሳያል፡፡
4.  ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በዚኽ ሰዓት ገና አልተጠመቀም፡፡ ሊቃውንቱ ያልተጠመቀን መሪ ለዚኹ ታላቅ የሃይማኖት ጕባኤ ሊቀ መንበር አድርገው ይቀበላሉ ብሎ ማሰብ የማይኾን ነገር ነው፡፡
5.  ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጉባኤው ውይይት አልነበረም፡፡ ጉባኤውን አስዠምሮ ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመልሷ እንጂ /ዝኒ ከማኁ፣ ገጽ 113/፡፡
ስለዚኽ “ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የኒቅያን ጕባኤ በሊቀ መንበርነት መርቶታል፤ አርዮስም የተወገዘው በንጉሡ ተጽዕኖ ነው” የሚሉት ተረፈ አርዮሳውያንና የዛሬዎቹ ጀሆቫውያን ታሪክ ጸሐፊዎች ብቻ መኾናቸው ልብ ይሏል፡፡   
ሐ) አርዮስ ምን ማለቱ እንደኾነ ተጠየቀ
 ጕባኤው ሊቀ መንበሩን ከመረጠ በኋላ ውይይቱን ቀጠለ፡፡ በአርዮስ ላይ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊትም የአርዮስን አመለካከት በጥልቀት ለማድመጥ ተስማማ፡፡ አርዮስ ሐሳቡን አስረዳ፡፡ አበውም ምን ማለቱ እንደኾነ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በማንሣት እንዲያብራራው ጠየቁት፡፡ 

መ) ውይይቱ በአትናቴዎስ እና በአርዮስ ቀጠለ
 አርዮስ፡- “በምሳሌ 8፡22 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ፡- እግዚአብሔር የመንገዱ መዠመሪያ አደረገኝ፤ በቀድሞ ሥራው መዠመሪያ” ብሏል፡፡
አትናቴዎስ፡- “የመንገዱ መዠመሪያ አደረገኝ ሲል ምን ማለቱ እንደኾነ እዚያው ምዕራፍ ላይ የተገለጠ ነው፡፡ ወረድ ስትል ከጥንት ዠምሮ ከዘለዓለም ተሾምኁ፤ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ፡፡ ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድኹ ይላልና፡፡”
ተጨማሪ ማብራርያ፡- ሰው የሚወልደውን ፈጠረው፤ ሠራው አይባልም፡፡ የሠራውንም የወለደው አይባልም፡፡ ይኽም ቢኾን ለምሳሌ ያኽል እንጂ የአብ መውለድ የወልድ መወለድ በሥጋ ለባሽ ሥርዓት ወይም በሥነ ፍጥረት ሕግ የሚተረጐም አይደለም፡፡ ሰው ህልውናውን የሚዠምረው በዘመን ነው፡፡ ወልድ ግን ዘለዓለም ወልድ ነው /ሚክ.5፡2/፡፡
አርዮስ፡- “ወልድ፡- ከእኔ አብ ይበልጣል ብሏልና /ዮሐ.14፡28/ ወልድ ከአብ ጋር አንድ ሊኾን አይችልም፡፡ ራሱ እንደተናገረው ያንሳል እንጂ፡፡”
አትናቴዎስ፡- “ወልድ ከአብ ያንሳል የተባለው በለበሰው ሥጋ ነው፡፡ ወደ አብ እሔዳለኹ ሲልም በለበሰው ሥጋው ነው፡፡”
ተጨማሪ ማብራርያ፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለበሰው ሥጋ እንኳንስ ከአብ ይቅርና ከመላእክትም አንሷል፡፡ ምክንያቱም መላእክት አይሞቱም፤ ጌታችን ግን በለበሰው ሥጋ ለድኅነተ ዓለም ሞቷል፤ ሞቶም ተነሥቷልና፡፡
አርዮስ፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ሥልጣን ኹሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ ብሏል /ማቴ.28፡18/፡፡”
አትናቴዎስ፡- “ተሰጠኝ ማለቱ ልጅ መኾኑን የሚያስረዳ እንጂ የሚያንስ መኾኑን አያሳይም፡፡ የማይበላለጡ መኾናቸውን ለማሳየትም እዚያው አንቀጽ ወረድ ስትል እንግዲኽ ሒዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ይልሃል፡፡”
አርዮስ፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምጽአት ቀኗን እንደማያውቃት እንዲኽ ሲል ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል፡- ‘ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢኾኑ ልጅም ቢኾን የሚያውቅ የለም’ /ማቴ.24፡36/፡፡ ስለመጨረሻይቱ ቀን የማያውቅ ኾኖ ሳለ እንዴት ብሎ አምላክ ይባላል?”
አትናቴዎስ፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲኽ ያላቸው ስለዚያች ቀን ማወቅ ለደቀ መዛሙርቱ ስላልተፈቀደላቸው ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ጌታችን ኹሉንም እንደሚያውቅ መስክሯል /ዮሐ.21፡15/፡፡”
ተጨማሪ ማብራርያ፡- በማቴ.11፡28 ላይ ከአብ በቀር ወልድን ከወልድም በቀር አብን የሚያውቀው እንደሌለ ተጽፏል፡፡ ስለዚኽ የፈጠረውን ጊዜ ከማወቅ ያልተፈጠረውን አብ ማወቅ እጅጉን ይከብዳልና ሐሳቡ ሌላ እንደኾነ መረዳት አያስቸግርም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት መዝገብ ኹሉ በርሱ ዘንድ ነውና /ቈላስ.2፡3/፡፡ ታድያ ሐሳቡ ምንድነው ያልን እንደኾነም አንደኛ ሰዎች ኹል ጊዜ ተዘጋጅተው መኖር አለባቸው እንጂ የሚመጣበትን ቀን ዐውቀው በመጨረሻ ሰዓት ብቻ መልካም ሰዎች እንዲኾኑ ፈቃዱ ስላልኾነ ነው፡፡ ኹለተኛ የምጽአቱን ቀን እየተጠባበቁ ሰዎች ምድራዊ ኑሮአቸውን ይዘነጋሉ፡፡ ይኽ እንዲኾን ደግሞ አምላክ ፈቃዱ አይደለም፡፡ ልናስተውለው የሚገባ ነገር ቢኖር ስለዚያች ቀን ብዙ ምልክቶችን መናገሩ ነው፡፡ ስለዚኽ ልጅም ቢኾን የሚያውቅ የለም መባሉ ስለዚያች ቀን ከዚኽ በላይ እንዳይጠይቁት ለማድረግ የተናገረው ቃል እንደኾነ መረዳቱ ቀላል ነው /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ የማቴዎስ ወንጌልን ሲተረጕም ድርሳን 76 ላይ ከተናገረው የተወሰደ/፡፡
አርዮስ፡- “ወልድ ከራሱ አንዳች ነገር ሊያደርግ እንደማይችል ተናግሯል /ዮሐ.5፡30/፡፡ ስለዚኽ ወልድ ከአብ ያንሳል፡፡”
አትናቴዎስ፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያየ ስፍራ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መኾኑን መስክሯል፡፡ ለምሳሌ አብን ያየ እኔን አይቷል፡፡ እኔ በአብ እንዳለኹ አብም በእኔ አለ፡፡”
ተጨማሪ ማብራርያ፡- ጌታችን ይኽንን ሲል፡- “እኔ ምንም ምን ከራሴ ብቻ አንቅቼ አላስተምርም፤ በህልውና እንደሰማኹ የሰማኹትን አስተምራለኹ እንጂ፡፡ ትምህርቴም እውነት ነው፤ የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ ልዩ ኾኖ የእኔ ፈቃድ ብቻ ሊደረግ አልወድም፤ ወልድ ያልወደደው አብም አይወደውምና” ማለቱ ነው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 481/፡፡

አርዮስ፡- “እግዚአብሔር (አብ ብሎ ባይጠራውም አብ ማለቱ ነው) አንድ ነው፡፡ ርሱ አይወልድም፡፡ ርሱ ብቻውን ጥንታዊ ቀዳማዊ፣ መዠመሪያ የሌለው ነው፡፡ እውነት፣ የማይሞት፣ ጥበበኛ፣ ደግ፣ ፈራጅ ርሱ ብቻ ነው፡፡ ይኽ ፈጣሪ አይወልድም፡፡ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር ስለኾነ ፍጡር አይደለም፡፡ አስገኚ የሌለው አስገኚ ነው እንጂ፡፡ ባሕርዩን ለማንም አያካፍልም፡፡ ባሕርዩን ለሌላ አካል የሚያካፍል ከኾነ ግን ተለዋዋጭ አምላክ ነው ያሰኝብናል፡፡ መለኮታዊ ባሕርዩ ለሌላ ያካፍላል ብለን ካሰብን ብዙ አማልክት አሉ ያሰኝብናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አንድ ብቻ ነው፡፡ ስለዚኽ ከርሱ ውጪ ያለው ማንኛውም አካል በርሱ ፈጣሪነት ካለ መኖር ወደ መኖር የመጣ (የተገኘ) ፍጡር መኾን አለበት” /Early Christian Creeds, By J.N.D. Kelly, pp 232/፡፡
 አትናቴዎስ፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፤ አዳኝ ነው /ማቴ.1፡21/፡፡ ማዳኑን ካመንኅ የባሕርይ አምላክነቱንም ማመን አለብኽ፡፡ ምክንያቱም የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መኾኑን መጽሐፍ ቅዱስ መስክሯልና /ኢሳ.45፡21፣ ሆሴ.13፡4/፡፡… ርሱ አምላክ ካልኾነ ግን እኛም አልዳንም ማለት ነው፡፡ በርሱ መዳናችንን ካመንን ግን ያዳነን ርሱ አምላክ መኾኑን ማወቅና ማመን አለብን፤ ራሱ መዳን የሚያስፈልገው ስለኾነ ፍጡር ፍጡራንን ማዳን አይችልምና፡፡ ለምሳሌ በወንጌል የተማርነው የጠፋው በግ ምሳሌ መላውን የሰው ዘር የሚያመለክት ነው፡፡ ፈላጊውም ቃል የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ቃል ፍጡር ከተባለ የጠፋው ርሱ ራሱ ነዋ!”
 አርዮስ፡- “በእግዚአብሔር ህልውና ውስጥ ጥበብና ቃል የሚባሉ ኀይላት ነበሩ፡፡ ከእነዚኽ ሌላ ደግሞ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ ዓለምን ለመፍጠር ስላሰበ መሥፈሪያና መለኪያ እንዲኾነው ሌላ ጥበብን ፈጠረ፡፡ አንጥረኛ መዶሻውን፣ ሸክላ ሠሪ መደቧን አስቀድማ እንደምትሠራ ኹሉ ከፍጥረት ዓለም ጥቂት ቀደም ብሎ የተፈጠረው ይኽ ጥበብ በተፈጥሮ ያገኘው አካልና ህላዌ አለው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ጥበብ፣ ወልድ፣ ቃል፣ አርአያ እየተባለ ይጠራል፡፡ በባሕርዩ ፍጡር ስለኾነ ያልነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ከመፈጠሩ በፊት አልነበረም፡፡ ባሕርዩ ፍጹም ስላልኾነ የአብን አምላካዊ ባሕርይ ለማየትም ለማወቅም አይችልም፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር ከኢምንት ከዓለማት በፊት የተፈጠረ ነውና፡፡ ፍጡር እንደመኾኑ ማዘን፣ መተከዝ፣ መደሰት፣ መበሳጨት የባሕርዩ ነው፡፡ ሰው መኾኑ ከአብ እንደሚያንስ ያሳያል፡፡ ቃል ሰው ለመኾን ያመጣው ምክንያትም የመታዘዝ ግብር ስለነበረበት ነው፡፡ ስለዚኽ አብ በርሱ ዘንድ ኅቡእ ሲኾን ርሱንም ለማወቅ የወልድ ባሕርያዊ ዕውቀቱ የተወሰነ ነው፡፡ ታድያ እንደዚኽ ያለውን የባሕርይ አምላክ እንደምን ይቻላል?” /የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ አባ ጐርጐርዮስ (የሸዋ ሊቀ ጳጳስ)፣ ገጽ 91/፡፡ “ርግጥ ነው ወልድ ፍጡር ነው፡፡ ነገር ግን ከሌሎች ፍጥረታት ይበልጣል፡፡ አብ ከፈጠራቸው ፍጥረታት የመዠመሪያው ነው፡፡ የጳውሎስ ትምህርትም ይኽን ያስረዳል /1ኛ ቆሮ.8፡6፣ 2ኛ ቆሮ.5፡18/፡፡ በኋላም በመዋዕለ ሥጋዌ ባሳየው ታዛዥነትና የተጋድሎ ጽናት ከእግዚአብሔር ቡራኬን፣ ጸጋን ተቀብሎ እንደ ጻድቃን፣ እንደ ሰማዕታት ሱታፌ አምላክነትን አገኘ” /ዝኒ ከማኁ፣ ገጽ 92/፡፡ ይኽ የአርዮስ አመለካከት የማኒ አስተምህሮ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ማኒያውያን አስተምህሮ ወልድ አምላክነትን ያገኘው በሱታፌ ነው፤ ዓለም ለማዳን የረዳውም ይኸው ሱታፌው ነው ብለው ያምኑ ነበርና /Early Christian Creeds, By J.N.D. Kelly, pp 233 /፡፡
አትናቴዎስ፡- “ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር አንድ ነው፡፡ ፍጡር ነው ካልነው ግን ለክርስቶስ የአምልኮ ስግደት ማቅረብ አምልኮ ጣዖት (ባዕድ) ነው፡፡ ክርስቶስ በዚኽ ምድር በተመላለሰበት ወራት በሥጋዌ ሥርዓት ሐዋርያትን ደቂቀ አዳምን ወንድሞቼ ማለትን አላፈረም፤ ወልደ እግዚአብሔር ወልደ አዳም ኾኗልና /ዕብ.2፡11/፡፡ የአብ የባሕርይ ልጅነቱን በተናገረበት አንቀጽ ግን ራሱን ከጻድቃን ከሰማዕታት ጋር ቈጥሮ አልተናገረም፡፡ አባቴ አባታችኁ አለ እንጂ አባታችን አላለም፡፡ አብም ተቀዳሚ ተከታይ (ታላቅም ታናሽም) ለሌለው ለአንድ ልጁ አባትነቱን በመሠከረበት አንቀጽ በዮርዳኖስ ከዮሐንስ ጋር አዳብሎና አቀናጅቶ ወይም በደብረ ታቦር ከዮሐንስ፣ ያዕቆብና ከጴጥሮስ ጋር አዳብሎ ልጆቼ አላለም፤ አጥርቶና ለይቶ ልጄ አለው እንጂ” /የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ አባ ጐርጐርዮስ (የሸዋ ሊቀ ጳጳስ)፣ ገጽ 113-114/፡፡ “ወልድ ከአባቱ ጋር ማለትም እንደ አባቱ የስግደት የአምልኮት ባለቤት ነው፡፡ እንደ አባቱ በፍጥረት ኹሉ ሥልጣን አለው፡፡ ምክንያቱም “የአባቴ የኾነው የእኔ ነው” ብሏልና /ዮሐ.5፡17/፡፡ በርሱ ኹሉም ተፈጠረ፡፡ የኹሉ ድኅነት የተገኘው በርሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ለመፍጠር እስካለመቻል ደርሶ ደካማ አይደለምና ወይም ዓለምን ለመፍጠር እስካለመፍቀድ ደርሶ ትዕቢተኛ አይደለምና ፈጥሮ ፈጠረበት ብሎ ማሰብ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ከእያንዳንዱ ፍጥረቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ነውና /ማቴ.6፡27፣ 10፡29/፡፡ ወልድ በገድል በትሩፋት ለራሱ አምላክ ለመኾን የሚጥር ከኾነ እኛን የጸጋ አማልክት እንድንኾን እንዴት ይቻለዋል? ለራሱ የማይተርፈውና በስጦታ ያገኘውን አምላክነትንስ ለሌላ ሊለግሰው አይችልም፡፡ ስለዚኽ ወደ እኛ ወርዶ ራሱን ያሻሻለ አይደለም፤ ይልቁንስ መሻሻል የሚያስፈልገውን ሰው አሻሻለ እንጂ፡፡ … ጴጥሮስም የአምላካዊ ባሕርይ ተካፋዮች ናችኁ ያለን /2ኛ ጴጥ.1፡4/ ወልድ እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ያደርገን ዘንድ ስለመጣ ነው፡፡ አብን በወልድ እናውቋለን፤ ባሕርያቸው አንድ ነውና /ዮሐ.14፡8፣ ዝኒ ከማኁ፣ ገጽ 97-98/፡፡
ሰ)  አንቀጸ ሃይማኖት ረቀቀ
 ከዚኽ በኋላ የአርዮስ ትምህርት ከሐዋርያት ከተቀበሏት እምነት ያፈነገጠ መኾኑ ኹሉም ተስማሙ፡፡ እምነታቸውን ከዚኽ ክሕደት ለመጠበቅም አንቀጸ ሃይማኖት ብለን የምንጠራውን ያረቀቁት በዚኹ ጊዜ ነበር፡፡ ይኽ አንቀጸ ሃይማኖት ዛሬ በኹሉም (በምዕራባውያንም በምሥራቃውያንም) አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ በተለይ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. የዘወትር ጸሎት ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ አንቀጸ ሃይማኖቱ በመዠመሪያ የተጻፈውም በግሪክኛ ነው፡፡  
ከዚኽ በኋላ ጕባኤው አንቀጸ ሃይማኖቱን የሚያዘጋጁ ሦስት ሰዎችን መረጠ፡፡ እነርሱም የእስክንድርያው ፓትሪያርክ እለእስክንድሮስ፣ የእለእስክንድሮስ ሊቀ ዲያቆን ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲኹም የቀጰዶቅያዋ ቂሳርያ ሊቀ ጳጳስ የሚኾን ሊዮንቲዮስ ናቸው፡፡
 ረ) ተጨማሪ ውግዘት እንዳስተላለፉ
 “ከዚኽ ኦርቶዶክሳዊ የሃይማኖት ቀኖና አልፈው አንዱን አካል ወልድን ከአብ ለይተው ያልነበረበት ጊዜ ነበረ የሚሉ ወይም ከመወለዱ በፊት አልነበረም የሚሉ ወይም ካለ መኖር ወደ መኖር ተፈጠረ የሚሉ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ማዘን፣ መተከዝ፣ መደሰት፣ መበሳጨት የባሕርዩ ነው የሚሉ እነዚኽን ኹሉ በኹሉ ያለች ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ታወግዛቸዋለች” ሲሉ ውሳኔአቸውን በውግዘት ዘግተዋል /ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምእት 17፡14/፡፡
ማጠቃለያ
 በአጠቃላይ ሠለስቱ ምዕት የመለኮት አንድነትን፣ የአካላት ሦስትነትን፣ የወልድ አምላክነትን በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አንቀጸ ሃይማኖታቸው ነው ያጸደቁት፡፡ ስለዚኽ ሠለስቱ ምዕት የነቢያትን፣ የክርስቶስ የራሱና የሐዋርያትን ትምህርት “ከዚኽ አትለፍ፤ ከዚኽ አትትረፍ” ብለው አጽንተው ተመለሱ እንጂ የይሖዋ ምስክሮች እንደሚሉት አዲስ ትምህርትን ለማጽደቅ አልተሰባሰቡም /ዝኒ ከማኁ 17፡2/፡፡ ሃይማኖት ከእግዚአብሔር አንድ ጊዜ የተሰጠች እንጂ በዚኽ ዘመን እንደሚደረገው በስብሰባና በእጅ ብልጫ የሚወሰን አይደለምና፡፡ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ከዚኽ በኋላ የመዝጊያ ንግግር እንዲያደርግ መጥቶ ነበር፡፡
 ለማይበታተን ሦስትነታቸው፣ ምስጋና ለማይጨመርበት አንድነታቸው አኰቴት ለማይከፈል ህልውናቸው ጌትነት ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይገባል ለዘለዓለሙ አሜን አሜን አሜን!!!

No comments:

Post a Comment