Pages

Monday, March 16, 2015

ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ (ደረጃ አራት)





በዲ/ን ሳምሶን ወርቁ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
መታዘዝ
የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፥ የመንግሥተ እግዚአብሔር ተጓዦች እንዴት ሰነበታችሁ? አራተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ እነሆ በምናባችን ዛሬ መመልከታንን እንቀጥላለን፡፡ አስቀድመን የመጀመሪያውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ጀርባችን ለዓለም በመስጠት ጀምረን፣ ሁለተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ከዓለማዊ መሻት መለየትን አስከትለን፣ በሦስተኛው የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ የሆነውን እንደ እንግዳ መኖርን በባለፉት ጊዜያት ተመልክተናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ዘላዕለይ አራተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ መታዘዝ ሲል ይገልጸዋል፡፡ ይህንንም ሲገልጽ መታዘዝ ማለት የእኔ የምንለውን ሐሳብ፣ ፈቃድ በመተው በምትኩ እኛ ራሳችንን አስገዝተንለታል ለምንለው ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመታዘዝ መኖር ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ሲያብራራው “ሰው ታዛዥ ለመሆን አስቀድሞ የራሱን ማንኛውንም ሐሳቡን ማመን የለበትም፡፡ ይልቅስ ይህ ሀሳብ ከማን ነው? ከሰው ወይንስ ከእግዚአብሔር ነው?” ብሎ መመርመር አለበት፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች እነርሱ በጎ የመሰላቸውን ሐሳብ ብቻ የሙጥኝ በማለት ላለመታዘዛቸው የገዛ አመለካከታቸው እንቅፋት ሲሆንባቸው ይስተዋላል፤ ስለዚህ ለመታዘዝ ዘወትር በውስጣችን ያለውን ፈቃዳችንን መጠርጠር ይገባል፡፡ ይህንን ሐሳብ ቅዱስ ዮሐንስ በሌላ በኩል ሲያብራራ በመታዘዝ ሰው ፈቃዱን ይቀብራል፡፡ ይህም ማለት የተቀበረ እንደማይታይ ሁሉ ፈቃዱን በመታዘዝ የቀበረ ሰውም በእርሱ ፈቃድ ፈንታ ፈቃደ እግዚአብሔር  በሕይወቱ ይታይበታል ሲል ነው፡፡
የመታዘዝን አስፈላጊነት ቅዱስ ዮሐንስ ሲያጸናው “ሰው ሳይታዘዝ ፈጽሞ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ሲል ይገልጻል፡፡ ለዚህም አባታችን አዳም ባለመታዘዙ ገነትን ያህል ቦታ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ አጣ፡፡ ዳግመኛ በወልደ እግዚአብሔር መታዘዝ አጥቶት የነበረውን ሁሉ አገኘ፡፡ ዛሬም ሰዎች ከእግዚአብሔር መንግሥት በመታዘዝ ይገባሉ፤ ባለመታዘዝ ይለያሉ፡፡ ብዙዎቻችን የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ ምሕረት፣ ፍቅርን እንሻለን፡፡ ጥያቄው ግን እንታዘዛለንን? የሚል ነው፡፡ ብዙዎች ወደ ምንግሥተ ሰማያት መግባትን ሲያስቡ የማይቻል አድርገው ያስባሉ፡፡ ከዚያም የሕይወት ልምምድ ውስጥ ይገቡና ተስፋ ወደ መቁረጥ ይደርሳሉ፡፡ ነገር ግን በመታዘዝ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ እንደሚችሉ ለመታዘዝ ደግሞ ፈቃዳቸውን መተው እንደሚገባ ስላልተረዱና ምንአልባትም መተው ስላልወደዱ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሌላው ቀርቶ በክርስቲያኖች ኅብረት ውስጥ ሰላም ጠፍቶ በምትኩ ጠብና ክርክር ነግሦ የክርስትናን ዓላማ እስከ መዘንጋት የሚደረሰው “ሁልጊዜ የእኔ ሐሳብ የተሻለ ነው፤ እኔ ያልሁት ብቻ ካልሆነ” በሚሉ ከመታዘዝ ይልቅ ማዘዝ ፈቃዳቸውን ከመተው ይልቅ ፈቃዳቸውን መጫን የሚያዘወትሩ ግለሰቦች መብዛት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በግል የመንፈሳዊ ሕይወታችን የአንድ ሰሞን ፆመኛ፣ ጸሎተኛ ሆነን የምንቀረው ለሕግ፣ ለሥርዓት ከሁሉ በላይ ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ ሁሉን በፈቀድን በወደድን ጊዜ ማድረግ ስለምንፈልግ ነው፡፡ ይህን በግልጽ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ገና መታዘዝን እንደሚገባ እንዳልተለማመድን ነው፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በምናደርገው ጉዞ ወደ ቅድስና ለመድረስ ለሕግ፣ ለሥርዓት ለሰው ሁሉ ከሁሉ በላይ ለእግዚአብሔር መታዘዝን መለማመድ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ቅዱስ አባት ስለ ቅድስና ሕይወቱን ምስጢር ሲጠየቅ፡- “ለአንዲት ቀን እንኳ የራሴን ፈቃድ አልፈጸምኩም፤ ራሴ የማልፈጽመውን ለአንድ ጊዜ እንኳን አላስተማርኩም” ሲል መልሷል፡፡ የራስን ፈቃድ አለመፈጸም ራስን ማሸነፍ ነው፡፡ ራሱን ያሸነፈ ደግሞ ራሱን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ይችላል፡፡
ለማን እንታዘዝ?
ሀ. ለባለሥልጣኖች መታዘዝ
በሥራ ፣በት/ቤት፣ በቤተክርስቲያን እና በቤታችን በሚኖሩ በእኛ ላይ ኃላፊነት ላለባቸው ሰዎች ሁሉ በሙሉ ፈቃደኝነት በደስታ ያለማንገራገር ልንታዘዝ ይገባል፡፡ የኛን መንፈሳዊ ሕይወት እስካላጓደለ ድረስ እነርሱ አድርጉ የሚሉንን ነገር ሁሉ መፈጸም ተገቢ ነው፡፡ እነርሱ የሚያዙን እያንዳንዷ ትእዛዝ ለእኛ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለማደግ ይጠቅመናል፡፡ “ነፍስ ሁሉ በላይ ላሉት ባለሥልጣኖች ይገዛ፡፡……….ባለሥልጣኖችም በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” /ሮሜ.13፡1/፡፡ ስለዚህ በእኛ ላይ የሠለጠኑ ሰዎችን ዕውቀታቸውን፣ መንፈሳዊነታቸውን መዝነን ሳንፈርድ ይልቅስ ለእኛ መንፈሳዊ ሕይወት እድገት እኛ ለእነርሱ መታዘዛችን እንደሚጠቅመን ልንረዳው ይገባል፡፡
ለ. ለንስሐ አባቶች መታዘዝ
ብዙ ጊዜ የንስሐ አባቶችን የምንፈልገው ኃጢአታችንን ተናዘን ቀኖና ለመቀበልና ወደ ሥጋወደሙ ለመቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን በተሳሳተ የሕይወት ጎዳና ተመላልሰን በኃጢአት ከመውደቃችን በፊት እነርሱ በሚመሩን መንገድ ለመሄድ ብንታዘዝ የቱን ያህል መልካም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ብዙዎች የሕይወት አጋራቸውን በራቸው ሐሳብ ብቻ ተመርኩዘው ከመረጡና ረጅም ርቀት ከሄዱ በኋላ ነው ለንስሐ አባቶቻቸው ለማጸደቅ ያህል የሚያሳውቁት፡፡ ይህ የሚመነጨው ደግሞ “ምን አልባት ይቅርብህ (ሽ) ቢሉኝ ኋላ ለቃላቸው ባልታዘዝ” ብሎ ላለመታዘዝ ሲባል ወዳልተገባ ነገር ይገባሉ፡፡ ነገር ግን የንስሐ አባቶቻችን የእኛን መንፈሳዊ ሕይወት አቅጣጫ የሚመሩ ኃላፊነትም ያለባቸው መሆናቸውን ተረድተን በሕይወታችን በሚያጋጥሙን ዐበይት ጉዳዮች ላይ መመካከር ለእነርሱም ትእዛዝ መታዘዝ ተገቢ ነው፡፡ “ለዋኖቻችሁ ታዘዙ እና ተገዙ እነርሱም እንደሚሰጡ አድርገው ይህን በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያደርጉት ይህን የማይጠቀቅማችሁ ነበርና ስለነፍሳችሁ ይተጋሉ” /ዕብ.13፡17/፡፡
ሐ. ለቤተሰቦቻችንና ለባልንጀሮቻችን መታዘዝ
“የሌላው ሰው መሻት ለእኔ ትዕዛዝ ነው” የሚል አባባል አለ፡፡ ክርስትና ስለሌላው ሰው የሚኖሩት  የእኛን ሳይሆን የሌሎችን መሻት የምንፈጽምበት ሕይወት ነው፡፡ ታዲያ እኛ ስንት ጊዜ ስለቤተሰቦቻችን ስለባልንጀሮቻችን ብለን የእኛን ፍላጎት ወደ ጎን ትተን ለእነርሱ መሻት ታዘን ይሆን? ይህ ማለት የተራበ ሰው ስናገኝ እንድንመግበው እየታዘዝን ነው፤ የተጠማ ሰው ስናገኝ እንድናጠጣው እየታዘዝን እንደሆነ የእኛ እርዳታ የሚያስፈልገውን ሰው እንድንረዳው እየታዘዝን እንደሆነ ልብ ልንል ያስፈልጋል፡፡ ሁልጊዜም ለመታዘዝ የተዘጋጀ ልብ ካለን በዕለት ተዕለት የኑሮ ምልልስ ውስጥ በመታዘዝ በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ በርካታ  እድሎችን እናገኛለን፡፡ ታድያ ተጠቅመንባቸው ይሆን? ወይስ እኛ በምንፈልገው ጊዜ በምንፈልገው ሁኔታ ካላጋጠመን አንታዘዝም? እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ በምናደርገው ጉዞ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ትንሽ ትልቅ ሳንል፣ የእኛን እርዳታ ተጠይቀንም ሆነ ሳንጠየቅ፣ በጊዜና በቦታ ሳንወሰን ራሳችንን ለመታዘዝ እናዘጋጅ፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት በመታዘዝ የምትሰጥ ናትና፡፡                      
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ይቆየን

1 comment: