Pages

Monday, March 30, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል ስምንት

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ መጋቢት 22 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
        ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች! እንዴት አላችኁ? ባለፉት ሰባት ተከታታይ ትምህርቶች ስለ መሠረታዊው ትምህርተ ክርስትና ደኅና አድርገን ለመማማር ሞክረናል፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ኾኖ ዛሬም በዚኽ ክፍል ተገናኝተናል፡፡ እግዚአብሔርም ያስተምረናል፡፡

የእግዚአብሔር ባሕርይ መገለጫዎች
ከኹሉ አስቀድመን “ባሕርይ” ምን እንደኾነ እንመልከት፡፡ ባሕርይ ማለት አካል ከህልውና ላለው አካል የሚነገር ሲኾን ትርጓሜውም ለዚኽ ህልውና አለው ለተባለው አካል ለህልውናው (ለመኖሩ) ምክንያት፣ ምንጩ፣ ሥሩ፣ መፍለቂያው፣ መገኛው፣ ጥንቱን የሚያስረዳ ቃል ነው /አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ፣ ገጽ 262/፡፡ በመኾኑም ባሕርይ፡-
·        ስለ እግዚአብሔር ሲነገር እግዚአብሔር ለህልውናው መነሻ፣ ጥንት፣ ምክንያት የሌለው ዘለዓለማዊ መኾኑን፤
·        ለፍጡራን ሲነገር ግን የፍጡሩ የመፈጠሩ ወይም የመገኘቱ ጥንትን ያስረዳል፡፡
በመኾኑም ባሕርዩ ስለማይታወቅ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ መገለጫዎች መናገር የሚቻል አይደለም፡፡ ከዚኽ በታች የምናያቸውም ለጊዜው በመለኮታዊ ቋንቋ ሳይኾን በእኛ በሚገባን ቋንቋ ከተገለጡት እጅግ የተወሰኑት ብቻ ናቸው፡-  
v ሙሉዕ በኵለሄ ነው (Omnipresence)፡፡ በኹሉም ቦታ መኖሩን ያመለክታል፡፡ በገነትም በሲዖልም፣ በሰማይም በምድርም በአጭሩ በኹሉም ቦታ እግዚአብሔር አለ፡፡ ይኸውም ክቡር ዳዊት፡- “ከመንፈስኽ ወዴት እሔዳለኁ? ከፊትኽስ ወዴት እሸሻለኁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለኽ። ወደ ሲዖልም ብወርድ፥ በዚያ አለኽ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅኽ ትመራኛለች፥ ቀኝኽም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትኾናለች፤ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲኹ ብርሃንዋ ነው” ብሎ እንደ ገለጸው ነው /መዝ.139፡7-12/፡፡
v የማንንም ርዳታ የማይፈልግ ነው (ኹሉን ቻይ ነው - Omnipotence)፡፡ ነቢዩ “አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልኽና በተዘረጋች ክንድኽ ፈጥረኻል፥ ከአንተም የሚያቅት ነገር የለም” /ኤር.32፡17/ እንዳለ ከኀሊነቱ መጠን፣ ገደብ የለውም፡፡
v ዘለዓለማዊ ነው (Eternity)፡፡ ከርሱ በፊት ማንም አልነበረም፤ ከርሱ በኋላም ከቶ ማንም አይኖርም፡፡ ርሱ ብቻ ቀዳማዊ ነው፤ ርሱ ብቻም ደኃራዊ ነው” /ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቁ.4/፡፡
v የማይለወጥ ነው፡፡  “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” /ሚል.3፡6/ እንዲል ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ያው ነው፡፡ በአኗኗሩ፣ በሐሳቡም አይለወጥም፡፡
v የማይታይ መንፈስ ነው፡፡ ከነፋስ ይልቅ ነፍስ ትረቅቃለች፤ ከሰው ነፍስ ይልቅ መላዕክት ይረቅቃሉ፤ ከመላዕክት ይልቅ ደግሞ እግዚአብሔር ይረቅቃል፡፡ በመኾኑም እግዚአብሔርን በእግዚአብሔርነቱ ማንም ሊያየው አይችልም /ዮሐ.1፡18/፡፡
v ኹሉን ዐዋቂ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በርሱ ፊት የተሠወረ ነገር (ፍጥረት) የለም” እንዳለ /ዕብ.4፡13/ ያልታሰበውን እንኳን የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡
v ጠቢበ ጠቢባን ነው፡፡ የሥነ ፍጥረቱን ሥርዓት መመልከት ለዚኽ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ርሱ ብቻ ፍጹም ሐኪም ነው፤ ርሱ ብቻ ፍጹም መሃንዲስ ነው፤ ርሱ ብቻ ፍጹም መሪ ነው፤ ርሱ ብቻ ፍጹም ፕላን ነዳፊ (አርክቴት) ነው፡፡  
v ቅዱስ ነው፡፡ ከኃጢአት የተለየ ነውና ቅዱስ ነው፤ በዚኽ ጊዜ በደለ የማይሉት ንጹሕ ነውና ቅዱስ ነው፤ እከብር አይል ክቡር ነውና ቅዱስ ነው፤ መቼም መች ደክሞ ሰንፎ አያውቅምና ቅዱስ ነው፡፡
v እውነተኛ ዳኛ (ፈታሒ በጽድቅ) ነው፡፡ የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም /ሮሜ.2፡11/፡፡ ጻድቁን ጻድቅ፣ ኃጥኡን ኃጥእ ይሏል እንጂ ፍርድ አይጠመዝዝም፡፡ ለአንዱ ሰጥቶ ለአንዱ አይከለክልም፡፡ ቢሰጥም ቢከለክልም ተቀባዩ ባለው የመቀበል ዓቅም አንጻር እንጂ አያዳልም፡፡  
v ሰውን ወዳጅ፣ ደግና መሐሪ ነው፡፡ ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ኹልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘለዓለምም አይቈጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲኹ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲኹ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲኹ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤” ብሎ እንደገለጸው /መዝ.104፡8-13/ ሰውን የሚወድበት መጠን እንደዚኽ ነው ተብሎ መግለጥ አይቻልም፡፡
v እውነተኛና ታማኝ ነው፡፡ “ምሕረቴን ግን ከርሱ አላርቅም፥ በእውነቴም አልበድልም፤ ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም። ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልኍ” እንዳለ /መዝ.89፡33-35/ ለቃሉ ታማኝ ነው፡፡ ሰዎች በዓቅም ማነስ የገባነውን ቃል ላንጠብቅ እንችል ይኾናል፤ እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነው፡፡
ስሙ ማን ነው? /ዘጸ.3፡13/
        የእግዚአብሔር ስሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ ስፍራ ተጽፎ እናገኟለን፡፡
1.     የአንድነት ስሞች (On the Level of Ousia)፡- አምላክ /መዝ.17፡31/፣ መለኮት /ሮሜ.1፡20-22/፣ ኤልሻዳይ /ዘፍ.17/፣ ያህዌ /ዘጸ.6፡3-8/፣ አዶናይ /ሕዝ.7፡2-5/፣ እግዚኣ ፀባዖት /ኢሳ.6፡3/፣ ኤሎሄ /መዝ.21፡1፣ ማቴ.27፡45/፡፡
2.   የሦስትነት ስሞች (On the Level of Hypostasis)፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ /የአካላት ስም፣ ማቴ.28፡19-20/፣ ልብ ቃል እስትንፋስ /የኵነታት ስም፣ መዝ.32፡6-11፣ ዮሐ.1፡1-30/፣ ወላዲ አሥራፂ ተወላዲ ሠራፂ /የግብራት ስም፣ መዝ.2፡7፣ 109፡3፣ ዮሐ.15፡26/፡፡
  እነዚኽ ስሞች ስለ አንዱ እግዚአብሔር ህላዌ መለኮትና ስለ ቅድስት ሥላሴ (ልዩ ሦስትነት) መታወቅ የተነገሩና በውስጣቸው እጅግ ብዙ ምሥጢራትን የቋጠሩ ናቸው፡፡ ከያዙት ምሥጢር በተጨማሪም በገዛ ራሳቸው ጠቋሚና አመላካች እንዲኹም አንጸባራቂ ናቸው፡፡ አስቀድሞ የገለጻቸውም ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ ሰዎች የተናገሯቸው አይደሉም፡፡ በሌላ አገላለጽ እግዚአብሔርን የምንጠራው ርሱ ራሱ ርሱን እንድንጠራበት በገለጠው መንገድ ነው፡፡
        ነገር ግን እነዚኽ ከላይ የተጠቀሱት ስሞች ምናልባት ከእግዚአብሔር ባሕርይ ግብሮች አንዱን ያብራሩ እንደኾነ እንጂ ኹለንተናውን መግለጥ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ስለ ፈጠረ ፈጣሪ፣ ስለሚመለክ አምላክ፣ ሕያው ስለሚያደርግና ስለሚያድን ማኅየዊ፣ ስለሚያስተዳድርና ስለሚመግብ መጋቢ ሠራዒ፣ ኹሉን ስለሚችል ኤልሻዳይ፣ ኃያል አምላክ ስለኾነ ኤል፣ እንደ ባሕርዩ ስለሚሠራ ያህዌ፣ የዓለም ጌታ ስለኾነ እግዚአብሔር ይባላል፡፡ ከዚኽ ባለፈ ግን ከቅዱሳን ወገን አንድ ስንኳ የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ ይኽ ነው ብሎ የተናገረ የለም፡፡ እግዚአብሔር ራሱም የባሕርይ ስሜ ይኽ ነው ብሎ የተናገረበት ኹናቴ የለም፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ፡- “እኔ ፊተኛ ነኝ፤ እኔም ኋለኛ ነኝ፤ ከእኔም ሌላ አምላክ የለም” ብሎ እንደተናገረ /ኢሳ.44፡6/ ልዩ፣ ቅዱስ ስለኾነ የሰው ልጅ ልቡና የእግዚአብሔርን የባሕርይ ስም የመረዳት ዐቅሙ ውሱን ነው፤ ዳግመኛም የሰው ልጅ ቋንቋ የእግዚአብሔርን ስም ለመግለፅ ዓቅም የለውም፡፡
አረጋዊ መንፈሳዊ ይኽን መግለጽ ቢያቅተው የጸለየውን ጸሎት እስኪ አብረን እናድምጠው፡- “አቤቱ በምን ስም እጠራኻለኁ? አንተን የምጠራበት ስም አላውቅም፡፡ አምላክ ብልኽ የባሕርይ ስሜ አይታወቅም ትለኛለኽ፡፡ አኹንም እገሌ ተብሎ መጠራት፤ ይኽን ይመስላል ተብሎ መመሰል ካንተ የራቁ ናቸው፡፡ ክቡር ገናና ሆይ! ምን ብዬ እጠራኻለኁ? በምን እመስልኻለኁ?” /አረጋዊ መንፈሳዊ፣ ድርሳን 43፣ ገጽ 319/፡፡
        ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ ብቻ ሳይኾን፣ የመላእክትና የነፍስ የባሕርይ ስማቸውም ከማወቅ የራቀ እንደኾነ እንዲኽ ሲል ያስረዳናል፡- “ወዳጄ ሆይ! ጳውሎስ የተናገረውን አስተውል፡፡ አስቀድሞ የክብሩ መንጸባረቅ ካለ በኋላ ቀጥሎም በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ ብሏልና /ዕብ.1፡3-5/፡፡ ሐዋርያው የባሕርይ ስሙን የሚያስረዳ ስም ባያገኝ በግርማው ቀኝ ብሎ ተናገረ፡፡ በግርማው ቀኝ የሚለው አገላለጽ በራሱ ግን የባሕርይ ስሙን አያስረዳም፡፡ ይኽም አስቀድሜ ከተናገርኩት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድን ነገር እንረዷለን፤ ኾኖም እንደሚገባ አድርገን በቋንቋ መግለጥ አንችልም፡፡ የእግዚአብሔርን ምላቱን ስፋቱን ርቀቱን እንረዷለን፤ እንደሚገባ አድርገን ግን መናገር አይቻለንም፡፡ የጌታ የባሕርይ ስሙም እንደዚያ ነው፡፡ የባሕርይ ስሙን መርምረን ልናውቀው አንችልም፡፡ ወዳጄ ሆይ! የጌታን የባሕርይ ስሙ አይታወቅም ስለተባለ አትደነቅ፡፡ የእግዚአብሔርንስ ተወውና የአንድ መልአክ የባሕርይ ስሙም አይታወቅም፡፡ የነፍስም እንዲኹ ነው፡፡ ነፍስ ማለት የሥጋ ሕይወት መኾኗን ብቻ ያስረዳል እንጂ የባሕርይ ስሟ አይደለምና፤ ለባሕርይዋ የሚስማማ ስም የላትም፡፡” /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 2፡179-198/፡፡     
        ሊቀ ነቢያት ሙሴ የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ ማን እንደኾነ ጠይቆ ነበር /ዘጸ.3፡14/፡፡ ርሱም፡- “ያለና የሚኖር (የምኾን፣ ኋኝ) እኔ ነኝ” ብሎታል፡፡ ነገር ግን ይኽ አገላለጽ የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ህልውናውን የሚናገር ቅጽል እንጂ የባሕርይ ስሙን አያስረዳም፡፡ ይልቁንም በዚኽ አነጋገሩ እግዚአብሔር ብቻውን እንደሚኖርና የሌሎች ፍጥረታት መኖር ከርሱ ዘለዓለማዊነት አንጻር ሲታዩ እንደሌሉ የሚያስቈጥር መኾኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የባሕርዩ ስም ያለመታወቁ ምሥጢርም እዚኹ ጋር ነው፡፡ የባሕርይ ስሙ መመርመር የማይቻለው እግዚአብሔር ለአኗኗሩ፣ ለህልውናው፣ ለኋኝነቱ ምክንያት፣ መነሻ፣ ጥንት ስለሌለው ነው፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ለመንገዱ ፍለጋ የለውም” እንዳለው ነው /ሮሜ.11፡33/፡፡ አስቀድመን “ባሕርይ ማለት አካል ከህልውና ላለው አካል የሚነገር ሲኾን ትርጓሜውም ለዚኽ ህልውና አለው ለተባለው አካል ለህልውናው (ለመኖሩ) ምክንያት፣ ምንጩ፣ ሥሩ፣ መፍለቂያው፣ መገኛው፣ ጥንቱን የሚያስረዳ ቃል ነው” ብለናልና እግዚአብሔር አስገኝ ስለሌለው የባሕርይ ስሙም አይመረመርም፡፡
ሰማዕቱ ዮስጢኖስ (Justin the Martyr) ይኽን አንቀጽ የበለጠ ሲያብራራው እንዲኽ ብሏል፡- “ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ አዳምንና ሔዋንን ሲያስታቸው ልክ እንደ ርሱ እግዚአብሔርን አልታዘዝ ቢሉ፥ እንደ እግዚአብሔር የባሕርይ አማልክት እንደሚኾኑ ነገራቸው፡፡ በዚኽ አነጋገሩም ከእግዚአብሔር ውጪ የሌሉትን አማልክት እንዳሉ አስመስሎ አሳያቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔርን አንታዘዝም ቢሉ እንደነዚኽ አማልክት እንደሚኾኑ ለማታለል እንዲመቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ይኽን የዲያብሎስ ትምህርት ያውቃል፡፡ በመኾኑም ያለና የሚኖር እኔ ነኝ በማለት ከእነዚኽ ህላዌ ከሌላቸው ብቻ ሳይኾን ከየትኛውም ፍጥረት ጋር የማይነጻጸር መኾኑን ለሙሴ ነገረው፡፡ ሰው የዲያብሎስን ማታለል አመነ፡፡ እግዚአብሔርን አልታዘዝ ብሎም ከገነት ወጣ፡፡ ከገነት ሲወጣ ግን ከእግዚአብሔር ሳይኾን ከዲያብሎስ በተማረው መሠረት ህላዌ የሌላቸውን የሌሎች አማልክት መኖርን በልቡናው ይዞ ወጥቷል፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት እንዲወጡ ያደረጋቸው የተሰጣቸው ትእዛዝ ከባድ ስለነበረ አይደለም፤ የባሕርይ አማልክት መኾን ስለፈለጉ እንጂ፡፡ ከገነት ሲወጡ የእግዚአብሔር ትእዛዝ በመተላለፋቸው እንጂ ሌሎች አማልክት አሉ በማለታቸውም ጭምር እንደወጡ አልገባቸውም ነበር፡፡ እንዲኽም በመኾኑ ከርሱ በኋላ የተገኙ ሰዎችን እንኳን አማልክት ብለው ለመጥራት አላንገራገሩም፡፡ ይኽ የአማልክት መኖር የሐሰት ትምህርት ኹሉ የተማሩት ከሐሰት አባት ከዲያብሎስ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ብዙ አማልክት የሚለው የሐሰት ትምህርት በሰው ልጆች ላይ እንደነገሠ ዐውቆ ይኽን አስተሳሰብ ከልጆቹ ያርቅ ዘንድ ወድዶ ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ ያለና የሚኖር እኔ ነኝ አለው፡፡ ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ለመምራት ከኹሉም በፊት እግዚአብሔር ብቸኛው አምላክ መኾኑን ማወቅ ነበረበትና፡፡” / ANF01. The Apostolic Fathers with Justin Martyr and Irenaeous, Wm. B. Eerdmans Publishing Co., reprint  2001, pp 464/፡፡
ከዚኽ መረዳት እንደምንችለው እነዚኽ በዲያብሎስ የተዋወቁት ጣዖታት ጥንት፣ መነሻ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን ለአኗኗሩ መነሻ የለውም፡፡ ስለዚኽም “ያለና የሚኖር፣ ኋኝ እኔ ነኝ” አለ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment