Pages

Tuesday, April 7, 2015

በአስቆሮቱ ይሁዳ ዙርያ የሚነሡ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 30 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
        ጌታችንን አሳልፎ የሰጠው ከዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት የነበረው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው፡፡ አስቆሮት በይሁዳ አውራጃ የሚገኝ ቂርያትሐጾር የሚባል መንደር ነው /ኢያሱ.15፡25/፡፡ የሐዋርያት ገንዘብ ያዥ ኾኖ ሳለ ለራሱ ገንዘብ ይሰርቅ ነበር፡፡ በኋላም ስለ ገንዘብ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቷል፡፡ ብዙ ሰዎች በይሁዳ ዙርያ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሣሉና ለዚኽ መልስ ይኾነን ዘንድ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስ ወንጌልን በተረጐመበት 81ኛው ድርሳኑ ላይ የተናገረውን ወደ አማርኛ መልሼ አቅርቤላችኋለኁ፡፡ መልካም ንባብ!!!
 
        ወንጌላዊው “በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ኹለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ” ይላል /ማቴ.26፡20/፡፡ ወዮ! የይሁዳ ሐፍረተ ቢስነቱ እንደምን የበዛ ነው? ምንም እንኳን ክፉ አውሬ ቢኾንም በበጎቹ መካከል ይቀመጣል፡፡ ከምሥጠሩ ይካፈል ዘንድ ይመጣል፡፡ እንደሚያምን ሰው ከማዕዱ ይበላ ዘንድ ይዘጋጃል፡፡
        ወንጌላዊው (ማቴዎስ) ይኽን ያስረዳ ዘንድ የኾነውን ኹሉ በግልጽ ጽፎልናል፡፡ ማዕድ ይበሉ ዘንድ በተቀመጡ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ እንደሚሰጥ እንዲኹም የይሁዳ ክፋቱ እንደምን የበዛ እንደኾነ እንደተናገረ ጽፎልናል፡፡   
        ደቀ መዛሙርቱ እንዳዘዛቸው ማዕዱን ካዘጋጁ በኋላ፣ ምሽትም በኾነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዐሥራ ኹለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር በማዕድ ተቀመጠ፡፡ ሲበሉም “እውነት እላችኋለኁ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ፡፡ ለማዕዱ ከመቀመጣቸው በፊት እግሩን አጥቦታል፡፡ እንዲኽ አሳልፎ ለሚሰጠው ለይሁዳ እንዴት ይጠነቀቅለትና ያዝንለት እንደነበረ ተመልከቱ፡፡ ምክንያቱም ሲናገር “ይሁዳ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሳይኾን “ከእናንተ አንዱ” ነውና የሚለው፡፡ ይኸውም ይሁዳ የልቡን ዐውቆ ሌላ ሰው ሳያውቅበት ንስሐ ይገባ ዘንድ ነው፡፡ አንዱን ይሁዳን ለማዳን ብሎም ኹሉንም አስደነገጣቸው፡፡ “ከእናንተ መካከል፣ ከዐሥራ ኹለታችኁም አንዱ፣ የአፌን ትምህርት የእጄን ተአምራት ያደመጠና ያየ፣ ከእኔ ተለይቶ ያማያውቀው፣ ጎንበስ ብዬ እግሩን ያጠብኩለት፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን የሰጠኁት ርሱ አሳልፎ ለሞት ለመከራ ይሰጠኛል” በማለት ኹሉንም አሳዘናቸው፡፡
        ያ የተቀደሰው ጉባኤ በአንዱ በይሁዳ ምክንያት በከባድ ጭንቀትና ኀዘን ውስጥ ገባ፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም፡- “ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደተናገረ አመንትተው ርስ በርሳቸው ተያዩ” ይላል /ዮሐ.13፡22/፡፡ ምንም እንኳን ዐሥራ አንዱ ጌታን አሳልፈው ለመስጠት ባያስቡም በይሁዳ ምክንያት ርስ በርሳቸው በፍርሐት ተጠያየቁ፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ “እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፡- ጌታ ሆይ የሚያስይዝኅ እኔ እኾንን? ይሉት ዠመር” ይላል፡፡ ጌታችንም መልሶ፡- “ከእኔ ጋር እጁን ወደ ወጪቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ የሚሰጠኝ ርሱ ነው” አለ፡፡
        በየትኛው ሰዓት ይሁዳ መኾኑን እንደገለጠው ታስተውሉ ዘንድ እማልዳችኋለኁ፡፡ ኹሉንም ከጭንቀታቸው ሊያላቅቃቸው በወደደ ጊዜ፣ በፍርሐት ተንጠው ሊሞቱ በተቃረቡ ጊዜ፣ ብዙ ጥያቄም ባነሡ ጊዜ አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደኾነ ተናገረ፡፡ ነገር ግን ይኽን በዚኽ ሰዓት መናገሩ እነርሱን ከኀዘናቸው ዕረፍት ለመስጠት ብቻ አይደለም፤ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ከስሕተቱ ይመለስ ዘንድም ነው እንጂ፡፡ ምክንያቱም ጌታችን እንዲኹ ስሙን ሳይጠቅሰው በደፈናው ሲናገር ሰምቶ ሊታረም አልቻለምና ዓይነ ልቡናውን የጋረደው ጭምብል አውልቆ ርሱ እንደኾነ ገልጦ እየነገረው ነበርና፡፡
        ኹሉም በከባድ ኀዘን ተይዘው ሳለ፡- “ጌታ ሆይ! እኔ እኾንን?” ይሉት ነበር፡፡ ርሱም መልሶ፡- “ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ርሱ ነው፡፡ የሰው ልጅስ ስለ ርሱ እንደተጻፈ ይሔዳል፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፡፡ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር” አለ፡፡
        አንዳንድ ሰዎች ይሁዳ እጁን ከጌታችን ጋር ያጠለቀው ለጌታ ያለውን ንቀት ለማሳየት ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን እንዲኽ አልልም፡፡ ይልቁንም ይኽን ያደረገው ጌታችን ነው እላለኁ፡፡ ይኸውም አስቀድሜ እንደተናገርኩት ይሁዳ ከስሕተቱ ይመለስ ዘንድ ይቀሰቅሰው ዘንድ ነው፡፡
        ተወዳጆች ሆይ! እነዚኽን ነገሮች እንዲኹ በቸልታ የምናልፋቸው ሊኾኑ አይገባም፡፡ ኹል ጊዜ በልቡናችን ሠሌዳ ላይ የተቀረጹ ሊኾኑ ይገባል እንጂ፡፡ ከዚያም ቁጣ በልቡናችን መቼም መች ስፍራን አያገኝም፡፡ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ከመድኃኔዓለም ጋር ተቀምጦ፣ ጌታም ይሁዳን በትሕትናና በየውኀት በኀዘኔታም ልብ እየተመለከተው በመዓዱ አብሮ መቀመጡን እያየ የስድብና የቁጣ መርዙን ተፍቶ የማይጥል ማን ነው? እስኪ ሰው ወዳዱ ጌታ እንዴት በትሕትና እንደሚናገር አስተውሉ፡- “የሰው ልጅስ ስለ ርሱ እንደተጻፈ ይሔዳል፡፡”
        ይኽን ሲልም ደቀ መዛሙርቱ፥ ጌታችን የሚቀበለው መከራ መስቀል ደካማ ኾኖ እንዳልኾነ እንዲያውቁ ነው፤ ዳግመኛም ይሁዳን ለማሻሻል የተነገረ ነው፡፡
        “የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር” አለ፡፡ በዚኽ ተግሣፁም የትሕትናውን፣ የርኅራኄውን ብዛት አስተውሉ፡፡ ምክንያቱም ይኽ ንግግሩ የወቀሳ አይደለም፤ የፍቅርና የአቅርቦት ነው እንጂ፡፡ ይኸውም ይሁዳ አስቀድሞ ምንም ስላላስተዋለ አኹንም የበለጠ እንዳያስተውል የሚያደርገውን ክፉ ነገር እንዲያስተውልና ካለበት ድንዛዜ እንዲነቃ ነው፡፡ ለዚኽም ነው ይኽን በሰማ ጊዜ ይሁዳ “መምህር ሆይ! እኔ እኾንን?” የሚለው፡፡ ወዮ እንደምን ያለ ስንፍና ነው! ራሱ የሚያደርገውን እያወቀ መልሶ “እኔ እኾንን?” እያለ ይጠይቃልና፡፡ ወንጌላዊውም ይኽን የይሁዳ አነጋገር ቢያስደንቀው የተናገረውን በግልጽ ጻፈልን፡፡ ሰው አፍቃሪውና ትሑቱ ኢየሱስስ ምን አለው? “አንተ አልኅ፡፡” “አንተ ኃጥእ፣ አንተ ርኵስ፣ አንተ የሰይጣን ማደሪያ፣ አንተ ፈሪሐ እግዚአብሔር የተለየኅ ሰነፍ፣ አንተ አታላይ፣ አንተ በራስኅ መንገድ የምትመራ ከሐዲ፣ ይኽን ሥራኽን ማለትም እኔን በመሸጥ በሠላሳ ብር እንደተስማማኅ ሰውረኅ ደግሞ መልሰህ እኔ እኾንን ብለኅ ትጠይቀኛለህን?” አላለውም፡፡ ምን አለ ታድያ? “አንተ አልኅ”፡፡ ይኸውም ትዕግሥትን ሲያስተምረን ነው፡፡
        ከእናንተ መካከል፡- “ይሁዳ እነዚኽ ነገሮች እንደሚደርሱበት አስቀድሞ ትንቢት የተነገረበት ከኾነ ለምንድነው ተጠያቂ የሚኾነው? ያደረገው አስቀድሞ ስለርሱ የተጻፈ አይደለምን?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚኽ ትንቢቶች የተነገሩት ይሁዳ እንዲያደርጋቸው ተብለው አይደለም፡፡ ይሁዳ ወዶና ፈቅዶ እንደሚያደርጋቸው ስለታወቀ ተጻፉ እንጂ፡፡ እንዲኽ ካልኾነማ ሰይጣንም አንዳች ስሕተት የለበትም ያሰኝብናል፡፡ ነገር ግን እንዲኽ አይደለም፡፡ ይሁዳም ሰይጣንም ከተጠያቂነት የሚያመልጡ አይደሉም፡፡ ጌታችን የሞተው እኛም የዳንነው ይሁዳ አሳልፎ ስለሰጠው አይደለም፡፡ የዳንነው የክፉዎችን ክፋት በጥበቡ ለእኛ መልካም በሚያደርግ በጥበበኛው እግዚአብሔር ነው፡፡
        አኹንም፡- “ይሁዳ አሳልፎ ባይሰጠው ኖሮ ሌላ ሰው አሳልፎ ይሰጠው አልነበረምን?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ ታድያ ይኼ ቀድሞ ከተነሣው ጥያቄ ጋር ምን ግንኙነት አለው? “ክርስቶስ ይሞት ይሰቀል ዘንድ ግድ ከኾነ አሳልፎ የሚሰጠው ሰው የግድ ያስፈልጋል፡፡ አሳልፎ የሚሰጠው ሰው ደግሞ የግድ እንደ ይሁዳ መኾን አለበት፡፡ እንዲኽ አሳልፎ የሚሰጥ ከሌለ ይልቁንም ኹሉም ሰው መልካም ቢኾን ኖሮ ጌታ ስለ እኛ ባልተሰቀለ ነበር፡፡” በፍጹም!!! እንደ ይሁዳ አሳልፎ የሚሰጥ ባይገኝ እንኳን እንዴት ያድነን እንደነበር የሚያውቀው የጥበብ ባለቤት ርሱ ብቻ ነው፡፡ ጥበቡ ከኅሊናት በላይ የማይመረመር ጥልቅ ነውና፡፡ ስለዚኽ ማንም ቢኾን ይሁዳ ለዚኽ ግብር የተፈጠረ ሰው ነው ብሎ እንዳያስብ ጌታችን ክርስቶስ የዚኽን ሰው ክፋቱ በዝርዝር ተናገረ፡፡
        አኹንም ከእናንተ መካከል፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ለይሁዳ አለመወለድ ይሻል ከነበረ ለምን እንዳይወለድ አላደረገም? ይሁዳ ብቻም ሳይኾን ለምን ሌሎች ክፉ ሰዎች እንዲወለዱ ይፈቅዳል?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ዓቅሙና ችሎታው እያላቸው ከክፋታቸው መውጣት ያልተቻላቸውን ሰዎች መውቀስ ሲገባችኁ ያለ ውዴታቸውና ፈቃዳቸው ክፋትን እንደሚያደርጉ አስባችኁ ስለምን እግዚአብሔርን ለመውቀስ ትነሣሣላችኁ?
        “እግዚአብሔር መልካም ሰዎች ብቻ እንዲወለዱ ቢያደርግ ኖሮ ሲዖል፣ ፍርድ፣ ወንጀለኛ መቅጫ የሚሉት ኹሉ ባልተፈጠሩ ነበር፡፡ ስለዚኽ ክፉ ሰዎች ባይወለዱ ይሻላቸው ነበር፡፡ ቢወለዱም ብዙ ሳይቆዩ መሞት ነበረባቸው” ብሎ የሚቀጥል ሊኖር ይችላል፡፡
        ከኹሉም በማስቀደም የሐዋርያውን ቃል ላስታውሳችኁ እወዳለኁ፡፡ እንዲኽ ያለውን፡- “አንተ ሰው ሆይ! ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነኅ? ሥራ ሠሪውን ለምን እንዲኽ አድርገኅ ሠራኸኝ ሊለው ይችላልን?” /ሮሜ.9፡20/፡፡
        ተጨማሪ ምክንያትን የምትሹ ከኾነ ግን እንዲኽ ብዬ እጨምርላችኋለኁ፡- መልካም ሰዎች ስለ መልካምነታቸው የሚወደሱት በእነዚኽ ክፉዎች መካከል መልካም ኾነው ሲገኙ ነው፡፡ ምክንያቱም ትዕግሥታቸውንና ራሳቸውን መግዛታቸው ይበልጥ የሚገለጠው እንዲኽ ሲኾን ነው፡፡ ከላይ እንደጠየቃችኁት ቢኾን ግን የድካማቸውንና የተጋድሎአቸውን ዋጋ አያገኙም፡፡ “ታድያ መልካሞቹ እንዲኽ አክሊል ሽልማትን ያገኙ ዘንድ እነዚያ ሊቀጡ ይገባልን?” ልትሉ ትችላላችኁ፡፡ በፍጹም! የሚቀጡት ክፋትን በማድረጋቸው ብቻ ነው፡፡ ክፉዎቹ ክፉዎች የኾኑት ወደዚኽ ዓለም ስለመጡ አይደለም፤ በራሳቸው ውዴታ ነው እንጂ፡፡ የሚፈረድባቸውም ስለዚኹ ነው፡፡ ብዙ በጎ ምግባርን የሚያስተምሯቸው መምህራን በአጠገባቸው ሳሉ ይኽን በጎነት ባለመማራቸው እንደምን ፍርድ አያመጣባቸውም ብለን እናስባለን? መልካሞቹ የሚወደሱትም ስለ ኹለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ ስለ ራሳቸው መልካምነት፤ ኹለተኛ ከክፉዎቹ ክፋትን ባለመማራቸው፡፡ እነዚያም የሚወቀሱት ስለ ኹለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ ስለ ራሳቸው ክፋት፤ ኹለተኛ ከመልካሞቹ መልካምነትን ሊማሩ አልወደዱምና፡፡
        እስኪ ወደ ይሁዳ እንመለስ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክፋቱን በነገረው ጊዜ ምን ነበር ያለው? “መምህር ሆይ! እኔ እኾንን?” ከመዠመሪያው አንሥቶ እንዲኽ ያልጠየቀውስ ስለምንድነው? ጌታችን፡- “ከእናንተ አንዱ” ብሎ ስለተናገረ ያለወቀው መስሎት፡፡ እንዳወቀው በግልጽ ሲነግረው ግን መልሶ ጠየቀው፡፡ ለምን? ምንም እንኳን ከክፋቱ ባይመለስም እንዲኹ ይምረኛል ብሎ አስቦ፡፡
        ወዮ! እንደምን ያለ ዕውርነት ነው? ይሁዳ ይኽን ኹላ እንዲያደርግ ያደረገውስ ምንድነው? ፍቅረ ንዋይ፡፡ ፍቅረ ንዋይ እንዲኽ ሰውን ዕብድ ያደርጋል፡፡ ያደነዝዛል፡፡ ምንም ፍርድ እንደሌለብን አድርጎ ያሳየናል፡፡ ከሰውነት አውርዶ እንደ ውሾች ያደርገናል፡፡ ከውሾች በባሰ መልኩም እንደ በረኻ አውሬ እንድንኾን ያደርገናል፡፡ ከውሾች በላይ ውሉደ አጋንንት እንድንኾን ያደርገናል፡፡ ይኽም ከይሁዳ መማር እንችላለን፡፡ ጌታችን በጣም ብዙ ርዳታ ቢያደርግለትም (ይሁዳ) በፈቃዱ ሰይጣን ስለኾነ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ፍላጎቶቻቸውን የማይገድቡ ይልቁንም ይኽንንም ያንንም ላግኝ የሚሉ ሰዎችም ገንዘብ እንደ ይሁዳ ያደርጋቸዋል፡፡ በመጨረሻም ባዶ እጃቸውን ያስቀራቸዋል፡፡
        ከእናንተ መካከል፡- “ወንጌላዊው ማቴዎስና ሌሎቹ፡- ይሁዳ ጌታን አሳልፎ እንደሚሰጠው ከተስማሙ በኋላ ሰይጣን ገባበት ሲሉ፥ ወንጌላዊው ዮሐንስ ግን፡- ቁራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት” ይላል /ዮሐ.13፡27/፡፡ አይጣላምን?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ አይጣላም፡፡ ዮሐንስም ቢኾን ከዚኽ አስቀድሞ፡- “እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው ሐሳብ ካገባ በኋላ…” ይላል /ዮሐ.13፡2/፡፡ “ታድያ መልሶ ቁራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት ለምን አለ?” ካላችኁም የሰይጣን አገባቡ በቀስታ ስለኾነ ነው ብዬ እመልስላችኋለኁ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ በሐሳብ ይገባል፤ ቀጥሎም በገቢር፡፡ አስቀድሞ ብዙ ሙከራዎችን ያደርጋል፡፡ በሐሳብ፣ በንግግር ይፈትናል፡፡ የሚፈተነው ሰው እንደሚቀበለው ዝግጁ እንደኾነ ሲያውቅም ፈጥኖ ይገባበታል፡፡ ክፉ መርዙንም እፍ ይልበታል፡፡ ሙሉ ለሙሉም ይቈጣጠሯል፡፡…
         ምንም እንኳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመለስ ዘንድ ብዙ ነገር ቢያደርግለትም ይሁዳ ግን ከክፋቱ ሊመለስ አልቻለም፡፡ ስለኾነም ጨምሮ፡- “ለዚያ ሰው ወዮለት” አለው፡፡ ከድንዛዜው ይነቃ ዘንድ “ባልተወለደ ይሻለው ነበር” አለው፡፡ በክፉ ሥራው ያፍር ዘንድ “እኔ ቁራሽ አጥቅሼ የምሰጠው ርሱ ነው” አለ /ዮሐ.13፡26/፡፡ ይሁዳ ግን በፍቅረ ንዋይ ዓይነ ልቡናው ታውሯልና ፈጽሞ ሊነቃ አልቻለም፡፡ ይኸውም አንዳንድ ሰዎች በክፉ በሽታ ተይዘው ራሳቸውን ስተው እንደምናያቸው ዓይነት ነው፡፡ ክፉ በሽታ እንደዚኽ ያደርጋል፡፡
        ክፉ ሰው እንዲኽ ጌታውን እስከ መግደል ይደርሳል፡፡ ይኽ ክፉ ሰው እጁን ይሰበስብ ዘንድ አይወድም፡፡ ስለ ሠላሳ ብር ብሎ በዋጋ የማይተመነውን ንጹሕ ደም አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ይሁዳ ምንም እንኳን ፍጹም ጤናማ እጅግም መልካም ተደርጎ ቢፈጠርም በራሱ ፈቃድ ክፋቱ እጅግ የበዛች ኾነች፡፡

         ወስብሐት ለእግዚአብሔር

11 comments:

  1. ቃለ ሂወት ያሰማልኝ

    ReplyDelete
  2. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
  3. Kale hiwotn yasemaln tilk meliekit new gebrsh ....
    Ftsamehn yAsamriln

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  6. የአስቆሮቱ ይሁዳ ሙሉ ታሪክ ማወቅ እፈልጋለሁ ደቀመዝሙር ከመሆኑ በፊት

    ReplyDelete
  7. ሰይጣን አስቀድሞ በሐሳብ ይገባል፤ ቀጥሎም በገቢር፡፡ አስቀድሞ ብዙ ሙከራዎችን ያደርጋል፡፡ በሐሳብ፣ በንግግር ይፈትናል፡፡ የሚፈተነው ሰው እንደሚቀበለው ዝግጁ እንደኾነ ሲያውቅም ፈጥኖ ይገባበታል፡፡ ክፉ መርዙንም እፍ ይልበታል፡፡ ሙሉ ለሙሉም ይቈጣጠሯል፡፡… አገልገሎትህ የትባረክ ይሁን ቃለ ህይወት ያሰማለን ወንድማችን

    ReplyDelete
  8. ቃለ ህይወት ያሰማልን።

    ReplyDelete
  9. ምን ሆኖ ሞቴ?

    ReplyDelete