Pages

Monday, May 18, 2015

ይድረስ ለሯጩ ወንድሜ

በአሃ ገብርኤል
ከዓምደ ሃይማኖት /ሰ/ት/ቤት
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 11 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
        ይድረስ ለወንድሜ ተስፋ እግዚአብሔር! እንደምን ሰንብተኻል? እኔ ቸሩ እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነኝ፡፡ “በተመረቅኩት ሥራ ብዙ ዓመታት መሥራቴን ታውቃለኅ፡፡ አኹን ግን ትቼው አትሌት ኾኛለኁ፡፡ ለመኾኑ ሯጭነት ኃጢአት ነውን?” ብለኽ የጻፍክልኝ ደብዳቤ ደርሶኛል፡፡
        ውድ ወንድሜ! ሩጫችን ይለያያል እንጂ ኹላችንም ሯጮች ነን፡፡ በርግጥ የሚገባና የማይገባ ሩጫ እንዳለ ልትዘነጋ አይገባም፡፡ ጥያቄኽ የኹላችንም ጥያቄ በመኾኑ የጥያቄአችን መልስ የሚኾነን ደግሞ ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ታስታውስ እንደኾነ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ከኾንን በኋላ በጕባኤ “ታገኙ ዘንድ ሩጡ” /1ኛ ቆሮ.9፡24/ በሚል ርእስ ተምረን ነበር፡፡ ዛሬ አንተ ሯጭ ኾነህ በምሳሌ የተማርነውን በተግባር እያስታወስከው እንድትማርበት ዕድሉን በማግኘትህ ደስ ልትሰኝ ይገባኻል፡፡

        ዛሬ ለአገልግሎት፣ በጕባኤ ቁጭ ብሎ ለመማር፣ ወደኋላ፥ ለማይጠቅመው ነገር በመሻማት ሰላም ለምናጣበት ግን ጊዜ ሰጥተን ወደፊት እንደምንሮጥ ኹሉ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም ከእግዚአብሔር ወደ ኋላ ብለው ትርፍ ለሌለበትና ወደ ሞት በሚወስድ መንገድ በመሮጣቸው ቅዱስ ጳውሎስ “ታገኙ ዘንድ ሩጡ” ብሎ ያስተማረው ትምህርት ለኹላችንም ትምህርት ነው፡፡
        ሯጭነት በራሱ ኃጢአት አይደለም፡፡ ለሩጫው ጊዜ እንደምንሰጠው ኹሉ ለቅዳሴ፣ ለቃለ እግዚአብሔር፣ ለንስሐ፣ ለቁርባን፣ በጎ ለማድረግ ጊዜ ሳንሰጥ የምንሮጥ ከኾነ ግን ኃጢአት ይኾንብናል፡፡
        “እግዚአብሔር በአንድም መንገድ በሌላም ይናገራል፡፡ ሰው ግን አያስተውለውም” /ኢዮብ.33፡14/ እንደተባለ ሙያህ ለብዙ ሰው በምሳሌነት እየተጠቀሰ፣ በትምህርትነት ከማገልገሉም በላይ ዛሬ አስተውለህ እንድትማርበት የሙያው ባለቤት አድርጎኻል፡፡ በዚኽ ፈጣሪን ልታመሰግነው ይገባል፡፡
        ሯጭ ለዓላማ መሮጥ አለበት፡፡ ደመወዙ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ ክርስቲያንም ለዓላማ መሮጥ አለበት፡፡ በቃል መነገሩ፣ በልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ.6፡33 ላይ “አስቀድማችኁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይኽም ኹሉ ይጨመርላችኋል” እንዳለ ኋላ ለሚመጣውና ለሚጠፋው ነገር መሮጥ የለብንም፡፡
        ውድ ወንድሜ! ለዓላማ መሮጥ ልምምድ ማድረግን ይፈልጋል፡፡ ፀሐዩ፣ ድካሙ፣ ብርዱ ሊያስቸግረን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሻግረን ለምናመጣው ውጤት ምንም አይደለም፡፡ በክርስትናም በአንዴ ወደ ፍጹምነት አይደረስም፡፡ በወጣኒነት መንፈሳዊ ልምምድ ማድረግ፥ በልምምድ ውስጥ ያሉትን ፈተናዎች ለመቋቋም ያስችላል፡፡ መቋቋም የምንችለው አሻግረን ተስፋ ስንሰንቅ ነው፡፡ ከልምምድ በኋላ ምግብ መብላት ያስፈልጋል፡፡ በክርስትናም ልምምድ ያለ ምግብ አይኾንም፡፡ የነፍስ ምግብ ቃለ እግዚአብሔርን እንደ አእምሯችን መጠን መመገብ ያስፈልጋል፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት የልምምድ ምግቦች ናቸው፡፡ ጌታችንም በማቴ.4 ላይ ተፎካካሪያችንን የምናሸንፈው በቃለ እግዚአብሔር እንደኾነ አስተምሮናል፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ወደ ንስሐ ወደ ሥጋ ወደሙ ያደርሳል፡፡ ምግብ የተባለውም ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡
        በውድድርም ኾነ በልምምድ ጊዜ ትጥቅ መልበስ ያስፈልጋል፡፡ ሱፍ፣ ከረቫት፣ ሌላ ጫማ አድርጎ መሰለፍ አይፈቀድም፡፡ የክርስትና ትጥቅም ትሕትና፣ ቸርነት፣ የዋኅነት፣ ታራቂነት ነው፡፡ ይኼ የሚገዛውም በቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ይኽን ትጥቅ ያልለበሰ ንግግሩ አያምርም፤ የተራቆተ ንግግር ነው፡፡ አለባበሱም አያምርም፤ ለልምምድ ለውድድር ስላልተዘጋጀ ሰይጣን ልብሱን አውልቆበት ራቁቱን ኾኗል፡፡ አባታችን አዳም “ራቁቴን ስለኾንኁ ፈራኹ” ያለው ባለመታዘዙ የመጣበት እግዚአብሔርን የማጣት ዕራቁትነት ነው፡፡ ኋላ ግን ራቁትነቱን በንስሐ ሸፍኖለታል፡፡ ዛሬም በንስሐ እንሸፈን፡፡
ከውድድር ውጪ ላለመኾን መስመርኽን ጠብቀህ መሮጥ አልብህ፡፡ በክርስትናም በመጠን፣ በአግባቡና በሥርዓቱ ካልተሮጠ እንኳን ያልተፈቀደውን የተፈቀደውም ለበሽታ ይዳርጋል፡፡
ጽናት ያስፈልጋል፡፡ ሊተፉብን፣ ሊጎሽሙን ይችላሉ፡፡ ሩጫውን አቋርጠን አንጨቃጨቅም፡፡ ችሎ መሮጥ ብቻ ነው፡፡ ክርስትናም ፈተናን እንዲርቅ ሳይኾን የምንቋቋምበትን ኃይል እንዲሰጠን እየጸለይን ችለን መሮጥ ነው፡፡
“አሸንፋለኁ” ብሎ መዠመር ያስፈልጋል፡፡ ልክ እንደዚኹ “እንቅልፍ ካላሸነፈኝ ነገ አስቀድሳለኁ፤ ካልደከመኝ ቤተ ክርስቲያን እሔዳለኁ” አይባልም፡፡
እስከ አኹን የደከምንለት ለሥጋችን ነው፡፡ የበለጠ ልንደክምለት የሚገባው ግን ለነፍሳችን ነው፡፡ በሥራ የደከመ ሰውነታችን ብርታትን የሚያገኘው ከመቅደሱ ዘንድ ነውና፡፡
በአግባቡ የሮጠ ሯጭ አሸናፊ ኾኖ ሽልማት ይቀበላል፡፡ የእኛ ሽልማታችን መንግሥተ ሰማያት መውረስ ነው፡፡ “ስማችኁ በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችኁ” /ሉቃ.10፡20/ ነውና የተባልነው፡፡
ሩጫ ሲዠመር ያልነበረ መሳተፍ አይችልም፡፡ አቋርጦ የወጣም ተመልሶ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ግን በእንቅልፍ ከተመሰለው ኃጢአት ነቅተን በንስሐ ከተመለስን ይምረናል፡፡ እኛ መሮጥ ስለቻልን ብቻ ሳይኾን እንድንሮጥ ያደረገን ቸርነቱን ተጠቅመን ልንሮጥ ያስፈልጋል፡፡
ውድ ወንድሜ! በዚኽ መልኩ የትኛውንም ሩጫ የምንሮጥ ከኾነ ኃጢአት አይኾንብንም፡፡ ቸር ያገናኘን፡፡                         

1 comment: