Pages

Sunday, May 24, 2015

አልማዝ - መድሎተ ጽድቅ



በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
      “መድሎተ ጽድቅ - የእውነት ሚዛን” በሚል ርእስ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ያዘጋጀው መጽሐፍ ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ብጹዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ አበው ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባክያነ ወንጌል እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ደማቅ መርሐ ግብር መመረቁ ይታወሳል፡፡ በዕለቱም ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የመጽሐፉን ዳሰሳ አቅርቦ ነበር፡፡ ዳሰሳው ካለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አንጻር እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡ መልካም ንባብ!!!

                       የመጽሐፉ አጠቃላይ መግለጫ                
የመጽሐፉ ርእስ - መድሎተ ጽድቅ
የመጽሐፉ አዘጋጅ - ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ
ቋንቋው - አማርኛ
የሕትመት ዘመን - 2007 ዓ.ም.
የገጽ ብዛት - 525
ዋጋ - 195 ብር
ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ያዘጋጀውን የመድሎተ ጽድቅ መጽሐፍን ከሥነ ጽሐፋዊው እና ነገረ ሃይማኖታዊ አቀራረብ አንጻር ለማየት የመጽሐፉን ዓይነት ከይዘቱና ከአቀራረቡ አንጻር መረዳት ማስቀደም ይጠይቃል፡፡
መድሎተ ጽድቅ ይዘቱ ሃይማኖታዊ በአቀራረቡ ደግሞ ዕቅበተ እምነታዊ (Apologetic) ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ በመኾኑ የሥነ ጽሑፋዊ አቀራረቡ ክርክራዊ (Argumentative) እንዲኾን ይጠበቅበታል፡፡ በርግጥም ደግሞ መጽሐፉ የቀረበው ሙግታዊ ወይም ክርክራዊ ኾኖ ነው፡፡ ምንም እንኳን ዕቅበተ እምነትን መሠረት አድርገው የሚጻፉ ኹሉ በግልጥ ክርክራዊ በኾነ መንገድ ባይቀርቡም የሚሞግቱት አስተምህሮ ወይም ሐብሳና ጉዳይ አልነበራቸውም ማለት ግን አይደለም፡፡ ይህ መጽሐፍ ግን ፊት ለፊት ሥርዓት ባለው መንገድ ተሟጋችና ተከራካሪ መጽሐፍ ነው፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ ምናባዊ ወይም የፈጠራ ከሚባሉት የልቦለድ፣ የግጥም እና የታሪክ መጻሕፍትም መካከል በአቀራረባቸው ክርክራዊ ኾነው የተጻፉ መጻሕፍት ቢኖሩም መድሎተ ጽድቅ ግን አኹንም ይለያል፡፡ ምክንያቱም ይህ መጽሐፍ ሃይማኖታዊ፣ በዚያውም ላይ ዕቅበተ እምነት ስለኾነ፡፡ ስለኾነም ይህ መጽሐፍ እነዚያ በሚታዩባቸው ሐሳባዊ ንድፈ ሐሳቦች ሊመዘን አይችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሥነ ጽሑፋዊውንና ነገረ ሃይማኖታዊ ዳሰሳውን ለማሳየት የምሞክረው የመጽሐፉን ማንነት በሚውስኑት በክርክራዊና ዐቃቤ እምነታዊነቱ ላይ በማተኮርና አጠቃላይ ማንኛውም ጽሑፋዊ ሥራ በሚመዘንባቸው ጥቂት ነጥቦች ላይ ብቻ ተመሥርቼ ይኾናል፡፡
የዕቅበተ እምነት ጽሑፍ መሠረታዊ ጠባዮች
አንድ መጽሐፍ በአቀራረቡ “ዐቃቤ እምነት ነው” ሊባል የሚችለው በኹለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ሃይማኖት የተቀበልነው መኾኑን ተረድቶ ጭማሪን፣ ቅነሳንና ብረዛን በሙሉ መከላከል ሲችል ነው፡፡ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ /ይሁዳ.1፡3/ ተብሎ እንደተጻፈ ሃይማኖት እግዚአብሔር ለቅዱሳን የሰጠው ነው፡፡ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠኻቸው፤ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ኹሉ ከአንተ እንደ ኾነ አኹን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት ዐወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ /ዮሐ.17፡6-8/ በማለት ሃይማኖታዊ ዕውቀቱም ትምህርቱም ከሥላሴ እንደኾነ አስረግጦ ነግሮናል። ከዕርገቱም በኋላ ሐዋርያቱ ስለሚጓዙበት ፍኖተ እምነት ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ ርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ ርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ /ዮሐ.15፡27/ በማለት መንገዱ በርሱ ትምህርትና በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ላይ የተመሠረተ እንደኾነ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ... ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ” /2ኛ ጢሞ.4፡7/ ያለው ለዚኽ ነው፡፡ ስለዚኽ ሃይማኖት የሰዎች የአእምሮ ውጤት ስላልኾነና ፍጹም እውነትም ያደረገው ከራሱ በባሕርዩ ፍጹም እውነት ከኾነው ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ስለኾነ ነው፡፡ ስለዚኽም ሃይማኖትን ልንጠብቀው እንጂ ከርሱ ልናጎድል በርሱም ላይ ልንጨምር አንችልም ማለት ነው፡፡ ይኽ ከኾነ ዘንድ በዚኽ በተገለጠው እውነት ላይ የሚደረግ ጭማሪን፣ ቅነሣን፣ ብረዛን፣ ተመሳስሎንና የመሳሰሉትን ለመከላከል የሚጻፉ ኹሉ ዕቅበተ እምነት ይባላሉ፡፡
ኹለተኛው መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለዓለም መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ በኋላ ለመጪው ትውልድ የሃይማኖት መምህራንን የሾመው ርሱ የፈጸመውን ማዳን ለኹሉም እንዲያዳርሱ ነው፡፡ ይህም በሉቃስ ወንጌል ላይ ተመዝግቦ በምናገኘው የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ውስጥ በአግባቡ ተገልጾአል፡፡ ስለዚህም ደጉ ሳምራዊ /ሉቃ.10፡25-37/ እንዳደረገው በምሳሌው ወንበዴ የተባለው ዲያብሎስ በክህደትና በኑፋቄ ራስ ራሳቸውን መትቶ የጣላቸውን፣ ልባቸውን ወይም አእምሮአቸውን ያሳጣቸውን ኹሉ ቁስለ ነፍሳቸውን ማጠብ፤ ዘይትና ወይን በተባለው የነፍስ ሕክምና (ምግበ ነፍስ፣ መድኃኒተ ነፍስ፤ መሥዋዕተ ነፍስ እና ብርሃነ ሕሊና በኾነው ቃለ እግዚአብሔር) እንዲገባ አክሞ ማዳንን አንተም እንዲሁ አድርግ ሲል ጌታችንን ያዘዘውን መፈጸም ተገቢ በመኾኑ ነው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖቱን የተረዳና የሚጠብቅ ኹሉ አንዱ እምነቱን የሚጠብቀው በሰዎች ሕሊና ውስጥ መኾኑን ተረድቶ በጠላት ዲያብሎስ ክፉ አሠራር የሰዎች ሕሊና እንዳይቆሽሽ ወይም ደግሞ ራሳቸውን እየፈተኑ የሚመሩበት ፍኖተ ሃይማኖት ከተቀበልነው አስተምህሮ ያላፈነገጠ መኾኑን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ዕቅበተ እምነትን ዓላማው ያደረገ መጽሐፍ ይጻፋል ማለት ነው፡፡
“ታዲያ እነዚህን መሠረታዊ ምክንያቶች መሠረት አድርጎ የሚጻፍ መጽሐፍ ሊያሟላ የሚገባው ምን ምን ነገሮችን ሲያሟላ ነው?” የሚለው የዚህ መጽሐፍ ዋና መመዘኛው ይኾናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ዕቅበተ እምነትን መሠረት አድርጎ የሚዘጋጅ አንድ መጽሐፍ ቢያንስ የሚከተሉትን ጉዳዮች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡
1) ጠባቂነትን (የሃይማኖትን ምንነት በንጹሕ ቤተ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ መግለጥ)
ሀ) እምነትም ሃይማኖትም በአመክንዮና በፍልስፍና የማይደረስባቸውን መለኮታዊ ሐሳቦችን ወይም የእምነት ምንት (Object of faith) ራሱ የምናምነውን ነገር ማንነት በተገቢው መንገድ ማሳየት፤
መድሎተ ጽድቅ በአንቀጸ (ጸሎተ) ሃይማኖት የምንመሰክራቸውንና ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የነበሩትንና የደረሱንን አንቀጾች ይዟል፤ እነርሱንም ገልጦ የምናምልከውን እግዚአብሔርን ርሱ ለእኛ የገለጠውን እውነት የምናምንበት መኾኑን አበክሮ ያስረዳል፡፡
ለ) እነዚህ የተቀበልናቸው ነገሮች በየዘመኑ እየተጠበቁ የመጡና አሁንም ያለው እምነታችን ያው መሆኑን አስረግጦ ማሳየት፤
ሐ) እነዚህ ነገሮች ኹልጊዜም ቢኾን በሰው የአስተሳሰብ ደረጃና መረዳት ልክ የማይወሰኑ መኾናቸውን ማሳየት፤
መ) ሃይማኖቱ በዚሁ መንገድ ተጠብቆ መድረሱንና የርሱም እምነት በዚሁ መሠረት መኾኑን እውነተኛና ተአማኒ ማስረጃዎችን ተጠቅሞ ማሳየት፤
ሠ) በጥንቱ ዘመን የተወገዙ ኑፋቄዎች በአዲስ መልክ ሲመጡ ከእነዛ ጋር ያላቸውን አንድነትና ልዩነት ከእውነት ጋር ያላቸውንም መሠረታዊ ተቃርኖ በተጨባጭ ማስረጃዎች ማሳየት፤
ረ) አዳዲስና ያልነበሩ ኑፋቄዎች የተገለጠውን እምነት ለመበከል ሲጥሩ ስሕተቱን መግለጥና አማኞችን መርዳት፤
ሰ) በቀደሙ ዐቀብተ እምነት ስም የሚቀርብ የመናፍቃን ማጭበርበር ካለ ርሱን መግለጥና ኑፋቄው የአባቶች አለመሆኑን ማሳየት፤
2) እውነት ላይ ብቻ ማተኮር
የዐቃቤ እምነትነት ያለው ጽሑፍ ዓላማው አሸናፊነት ሳይኾን እውነት ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳ ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንኾን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም ሐሳብ በእግዚአብሔርም ዕውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ኹሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ኹሉ እንማርካለን /2ኛ ቆሮ.10፡3-5/ ብሎ በገለጠው መሠረት መከራከርና ማስረዳት ቢጠበቅበትም ዓላማው እውነትን መግለጥ ብቻ ስለኾነ ከንቱ አርበኝነት አይታይበትም፡፡ ከዚህ ይልቅ እውነትን በንጽህ ለማቅረብና አለማመንን ለማራቅ ይጥራል፡፡ ስለዚህም ንጽህናን ገንዘብ አድርጎ ጌታውን (ደጉን ሳምራዊ) መስሎ ቁስልን ይጠርጋል፤ ነፍስንም ያክማል እንጂ የሥጋ ሥራዎችን ተሳዳቢነት፤ ተሳላቂነት፤ ሐሰተኝነትንና የመሳሰሉትን ተጠቅሞ የትኛይቱንም ነፍስ በቁስሏ ላይ ጥዝጣዜ አይጨምርም፡፡ መምታት ሲያስፈልገውም እንደ ጥሩ ባለሰይፍ ለይቶ ይቈርጣል እንጂ እንደ ቦንብ ጣይ ያለውን ኾሉ ወርውሮ በጅምላ ሁሉንም ለማቆስልና ለመበታተን አይሯሯጥም፡፡ ተልእኮው የማዳን እንጂ የመግደል፤ የማንሣት እንጂ የመጣል አይደለምና፡፡
ስለዚህም የሚያነጣጥረው ወደ ስሕተቱና ወደ ኑፋቄው እንጂ ወደ ተሳሳተው ሰውና ወደ መናፍቁ አይደለም፡፡ መድኃኒት በሽታን እንጂ በሽተኛውን ለማጥቃት እንደማይሰጠው ኹሉ መድኃኒቱን ለበሽተኛው ብንሰጠውም ሰውየውን ሳይኾን በሽታውን ለማጥቃት እንደኾነው ኹሉ አንድ ዐቃቤ እምነት ጽሑፍ ጸሐፊም በአቀራረቡ እንዲሁ መኾን ስሕተቶንችን ለይቶ ቆርጦ የሚጥልና ተሳሳቹን ከስህተት ለመመለስ የሚጥር ሊሆን ይገባዋል፡፡
3) አሳማኝነት
ሐሳብን እንደማስረዳት በተለይም ክርክር ያለበትን ጉዳይ ከባድ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ የክብደቱ ምክንያት ደግሞ ሐሳቦቻችን ለማስረዳት የምንጠቀምባቸው ቃላት ከሚወከሉለት ሐሳብ ጋር ተፈጥሮአዊ ዝምድና የሌላቸው ከመኾኑ አንጻር በሚፈጠረው የትርጉም ብዥታ ብቻ ሳይኾን በተጨባጩ ተዋስኦ ጊዜም በአብዛኛው በእኛ መረዳት ልክ እየተወሰኑ ክርክሩን ማስፋት መቻላቸው ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ቃላት ደግሞ የሚወክሉት መንፈሳዊ ወይም መለኮታዊ ሐሳብን ስለኾነ ቃላቱ እጅግ ጥልቅ መለኮታዊ ሐሳቦችን ይሸከማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ኃላፊነቱ እጥፍ ድርብ ከባድ ይኾናል፡፡ በዚህ ምክንያት በእንዲህ ዓይነት ሥራ ወቅት ቢያንስ ቢያንስ የምንሠራውን ሥራ ከባድነት መረዳት ይጠይቃል፡፡ ጌታችን በወንጌል እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው /ዮሐ.6፡63/ ሲል እንዳስተማረው ሊወሰን የማይችል መንፈስ የኾነውን ትምህርቱን በእኛው ቃል ለሰው እንደማድረስ ያለ ከባድ ሥራ ሊኖር አይችልምና፡፡ ከዚህም የተነሣ አንድ ክርክራዊ ጽሑፍ ሐሳቡን ከሚከራከረው አካል በሚሻል ብቻ ሳይኾን በሚጽፈው ጽሑፍ የሚጽፍለትን አካል እውነቱን ለማስረዳት ይቻለው ዘንድ ሕሊና ሊቀበለው በሚችለውና በሚገባው መጠን የማቅረብ ሃይማኖታዊ ግዴታም ይወድቅበታል፡፡ ስለዚህ ይህን ከባድ ኃላፊነት መወጣት አለመወጣቱን ለመፈተሸ የሚቻለው ደግሞ ሥነ ጽሑፋዊ አቀራረቡን በመመርመር ስለኾነ ክርክራዊ ሥነ ጽሑፍን በሃይማኖታዊ መጻሕፍት ለመጠቀም ወሳኝ የኾኑትን ነገሮች በመድሎተ ጽድቅ መጽሐፍ ውስጥ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋሉ በመጠኑም ቢኾን ማየት ይገባል፡፡ አሳማኝነቱ የሚመነጨው ከዚሁ ክርክሩን እንዲረዳ አድረጎ በማቅረብ አለማቅረቡ ላይ የሚጣል ነውና፡፡
ክርክራዊ ሃይማኖታዊ ጽሑፍ
የዚህ ዓይነት መጽሐፍ ዋና ዓላማው እንደተገለጸው ሌሎች እውነት ያሉትን ነገር እውነት እንዳልኾነና እውነቱ ርሱ የሚያምንበት መኾኑን ዐውቀው ወደ መረዳት ከዚያም ራሳቸውን ወደ ትክክለኛው ሃይማኖት እንዲመለሱ፤ በርሱ እምነት ውስጥ ያሉት ደግሞ እንዲጸኑ መርዳት ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ኹሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ኹኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይኹን /1ኛ ጴጥ.3፡15/ ሲል እንደገለጸው የሚከራከራቸውን አካላት ከስሕተታቸው ለማዳን በምን መንገድ ማቅረብ እንዳለበት መዘጋጀት ይጠበቅበታል ማለት ነው።
እንደዚህ ከኾነ እንዴት ነው ማሳመንና መመለስ እምነትንም መጠበቅ የሚቻለው የሚለውን ጥያቄ ጸሐፊው ማሰብና ከዚያም ትልሙን ነድፎ መጓዝ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከኾነ  በክርክር ውስጥ ስኬታማ የሚያደርጉ የሰው ልጅን አመክንዮዋዊ የአስተሳሰብ መሠረቶችን ታሳቢ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እነዚህም፡-
1) መረዳት (understanding)
2) መፍረድ ወይም መወሰን (Judgment)
3) አጠይቆት (reasoning) ናቸው
እነዚህ የሚገለጡት ደግሞ፡-
1) መረዳትን (እምነታዊ ረቂቅ ጽንሰ ሐሳቦችን) መፍጠር የሚቻለው ለሐሳባችን የሚመጥኑ ቃላትን (words) ተጠቅሞ በማቅረብ ነው፡፡
2) ፍርድ ወይም ደግሞ ሰዎችን ወደ ቆምንለት እውነት ወይም ወደምንፈለገው መንገድ ውሳኔ ላይ ለማድረስ ደግሞ ወደዚያ ሊያደርሱ የሚችሉ ቀመራዊ ሐሳቦችን (propositions) አስቀድሞ ማቅረብ አስፈላጊ ይኾናል፡፡
3) በመጨረሻም አጠይቆትን ወይም ሰዎችን በስሕተት ውስጥ ሊጥሏው ይችላሉ ብሎ ያሰባቸውን፣ ያያቸውን ፣ ያወቃቸውን አመክንዮቶች ወይም አጠይቆቶች በሙሉ በሰላ ክርክር (Argument) ስሕተት መኾናቸውን ገልጦ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

እውነቱን ለመናገር የዲያቆን ያረጋል መጽሐፍ ዲዛይኑ ጥሩ ኾኖ ተጠናቅቆ ከተሠራ በኋላ እንደሚገነባ ቤት እንዚህን ኹሉ በተሳካ ኹኔታ የሚያሟላ ኾኖ አግኜቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ ያህል የክርስትና እምነት ማእከል የኾነውን ነገረ ድኅነትን በተመለከተ በጉዳዩ ላይ የቀረቡትን የተሐድሶ አስተምህሮዎች በቀጥታ እየጠቀሰ ካቀረበ በኋላ ስሕተታቸውን ነቅሶ ያወጣል፡፡ እምነታቸውን የገለጹባቸውን አመክንዮዎችንም ድክመት ያሳያል፡፡ ከዚያም ትምህርተ ድኂን በዘመናት ምን እንደነበር ካሳየ በኋላ ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት ምን እንደኾነ በጥሩ አገላለጽ ያቀርባል፡፡ አንድ አንባቢ ከላይ የተገለጹትን የሦስቱንም ነጥቦች አጠቃቀሙን በአጭሩ ለመቃኘት ለመፈተሸ በሚከተሉት መመዘኛነት ማየት ይቻላል፡፡
ሀ. በቃላት አጠቃቀሙ
አንድ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ የቃላት አጠቃቀሙ ጥሩ ነው የሚባለው የማያሻሙና ሐሳብን አጉልተው ማስረዳት የሚችሉ ቃላትን በወጥነት መጠቀም ሲችል ነው፡፡ ይህም ማለት ሃይማኖታዊ ወይም ዶክትሪን የምንላቸውን ነገሮች በኦርቶዶክስና በሌሎቹ ያለውን ልዩነት በማያሻማ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ መድሎተ ጽድቅም በዚህ እጅግ ምስጉን ነው፡፡ እንኳን የምናውቀውን ልዩነት ሊያደበሰብስ ይቅርና ብዙ ሰው ላያስተውላቸው የሚችላቸውን ስህተቶችም በማይክሮስኮፕ እንደሚታዩ ተሐዋስያን አግዝፎ አሳይቶበታል፡፡ በበሽታው ለተጠቁትም መድኃኒቱንም ሳይደክሙ እዚያው ላይ እንዲያኙ ይረዳል፤ መዳን የፈለጉ በሽተኞችም በማየት ሳይኾን በመዋጥ ሊድኑበት ይቻላቸው ዘንድ ዕድሉ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ላልታመሙትም ቢወስዱት ክትባት ይሆንላቸዋል፡፡
ለ. የቀመራዊ ሀሳቦች አጠቃቀም
ይህ ደግሞ ሰዎች ልዩነቱን ዐውቀው ክርክሩ ገብቷቸው አቋም እንዲይዙ ለመርዳት ምቹ አድርጎ ማቅረብ ማለት ነው፡፡ ይህን ስንፈትሽ ኹለት ነገሮችን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ የመጀመሪያው እንደተባለው ነገሩን ግልጽ አድርጎ ማሳየት ነው፡፡ ለዚህ የተለመደው ብቻ ሳይኾን የሚጠበቀው ደግሞ የተከራካሪያችን እምነት ወይም ሐሳብ፤ ያ ሐሳብም ምን ማለት እንደኾነ ወይም ምን እንደሚያሰከትል ማሳየትን ያስቀድማል፡፡ ከዚያም በኋላ የተገለጠውን እውነት ለሰው እንዲረዳ አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ 
ኹለተኛው ጭብጥ ደግሞ ስለ ሌሎቹም ስለ ራሱም እምነት የሚጠቅሳቸውን ምንጮች ይመለከታል፡፡ በአጭሩ ለክርክሩ የሚጠቀምባቸው ማስረጃዎች፡-
v  የሚከራከረውን አካል እምነት በተመለከተ ሲጠቅስ ጸሐፊው ስለ እነርሱ ባለው አመለካከት ላይ ተመሥርቶና የሚከራከራቸውን ለማስጠላት ወይም ለማንኳሰስ በሚያመች መንገድ ራሱ የቀመረውን ሳይኾን ራሳቸው አማኞቹ በጻፉት ላይ ብቻ ተመሥርቶ መሆን አለበት፡፡ ዲያቆን ያረጋል በዚህ በመድሎተ ጽድቅ መጽሐፉ ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡ ራሰቸው ያሉትን በቀጥታ ከጽሑፎቻቸው ጠቅሶ ካሳየ በኋላ የሐሳባቸውን ድክመት፣ ስሕተትና ክሕደት ያሳል እንጂ ካነበበ በኋላ ርሱ የተረዳውን እንደነርሱ ጽሑፍ አድርጎ ያቀረበበትን ቦታ አላስታውስም፡፡ እውነተኛ ክርክርም ይኼው ነው፡፡ ይህም አንደኛ “እውነቱን እውነት በሉ” የተባለውን አምላካዊ ቃል ለመጠበቅ ሲረዳው በዋናነት ግን ከቆመለት ዓላማ ከእውነት ጋር እንዳይጋጭ ይጠብቀዋል፡፡ እውነትን በሐሰት ማስረጃዎች ማስጠበቅ አይቻልምና፡፡ እውነቱን ለመናገር ዲያቆን ያረጋል በዚህ በኩል እነርሱ ስለእኛ ያሉትን ስሕተትም ስላጋለጠ ይህን ስሕተት ፈጽሞ ቢገኝ ጥፋቱ ከባድ ይኾን ነበር፡፡ ነገር ግን ስለነርሱ ያቀረባቸው በሙሉ ራሳቸው ስለራሳቸው ከጻፏቸው ላይ በአግባቡ ምንጮቹን ጠቅሶ ስለኾነ መጽሐፉን አፋችንን ሞልተን በርግጥም ዐቃቤ እምነት እንድንለው አመቻችቶልናል፡፡
v  ከዚህም ጋር ግልጽ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ መግለጫዎችን መያዙ መፈተሸ አለበት፡፡ ካለበለዚያ ምን እየጠበቀ እንደኾነ አይታወቅምና፡፡ መጽሐፉ ግን ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርትን አስቀድሞ ክብረ ድንግልን፤ ነገረ ቅዱሳንንና ሌሎች ሰባት ታላላቅ ጉዳዮችን በየምዕራፉ ስላነሣ በዚህ ለመመዘን ማውጫውን መመልከት ብቻ ሊበቃ ይችላል፡፡
v  ሦስተኛው ነጥብ ደግሞ በእውነትና በኾነው ወይም በተደረገው ላይ ብቻ መመሥረት አለመመሥረቱ ነው፡፡ ይህም ማለት ሥነ ልቡናዊ ርግጠኝነትን (certitude - Psychological certainty) አለመጠቀም ማለት ነው፡፡ ይህም አሁን አሁን በብዙ ጸሐፍት ላይ እየተለመደ የመጣውንና የሰዎችን አለማወቅ ተጠቅሞ “መቼም ሳያነብ አይጽፈውም” ወይም ደግሞ “ምንጩን ቢያገኝ ነው እንጂ” ከሚያሰኝና በትርጉምም በግእዝ ፤ በእንግሊዝኛ ወይም በሌላ ቋንቋ ያለን ጥቅስ ለራስ ሐሳብ በሚያመች መንገድ ቆርጦና ቀጥሎ ካስቀመጡና በራስ ሐሳብ ተርጉሞ ወይም ሳይተረጉሙ በራስ ሐሳብ በማብራራት ሰዎች ላይ ሥነ ልቡናዊ ጫናና ርግጠኝነት በመፍጠር ለማሸነፍ መሞከርን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ የዲያቆን ያረጋል መድሎተ ጽድቅ ግን ተሐድሶዎችን የሚከራከረው በግእዝ ጥቅሶች ሰበብና ከአንዳንድ ቀደምት ሊቃውንት ቆነጻጽለው በየመጽሐፎቻቸው የተጠቀሙበትን ካባ ወይም የበግ ለምድ አውልቆ በመጣልና ይህን መንገዳቸውንም በማጋለጥም ጭምር ስለኾነ የራሱን ጽሑፍ ከዚህ ስሕተት ጠብቆታል፡፡ እንዲህ ከኾነ መንገዱ ኹሉ እውነት ነው ማለት ነው፡፡

ክርክሩ ወይም ሙግቱ
በክርክር ሒደቱም ቢያንስ ከኹለት ድክመቶች መታቀብ ቢችል በጣም ጥሩ ይኾናል፡፡ የመጀመሪያው አለመንሸራተትን ይመለከታል፡፡ አንድ ጥሩ ተከራካሪ በክርክሩ የሰዎችን ሕሊና ወደ ሐሳቡ ለማምጣት የሚችለው ከላይ በቀመራዊ ሐሳብ አቀራረብ ላይ የተቀመጡትን መሠረት አድርጎ ነጥብ በነጥብ ሲሞግትና ማስረዳት ብሎም መርታት ሲችልና ከተነሣበት ቀመረ ሐሳብም ርቆ ወይም ተንሸራትቶ የጎንዮሽ ሔዶ ሌላ ነገሮች ላይ ሳይዘበዝብ ሲቀር ነው፡፡ ዋና ጥያቄውን ትቶ ወይም እስከሚረሳው ድረስ ተንሸራትቶ ቀጥተኛ ያልኾኑ ነገሮች ላይ ካረዘመ “አህያውን ትቶ መደላድሉን” ይኾናል፡፡ ስለዚህ “ችግር አለበት” ብሎ ለጠቀሰው በቀጥታ በቂና ግልጽ መስጠት መቻል አለበት፡፡ መድሎተ ጽድቅም ይህን ከማቅረብ አልፎ ስለተነሣው ጉዳይ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ሊቃውንት ያስተማሩትን በተደጋጋሚ ሳይሰለች በማቅረብ መሠረቱ ያልተናወጠና እስከዘመናችን የደረሰን አስተምህሮ በዘመናት ተጠብቆ የደረሰን መኾኑን በግልጽ ያስረዳል፡፡
ኹለተኛው ደግሞ ከተጠየቃዊ ተቃርኖ (logical fallacy) መጽዳት መቻል ነው፡፡ አንዱን ለመርታት ሲል የሚቀበለውን ሌላውን ለመሞገት ሲል የሚቃረነው መኾን የለበትም፡፡ ዲያቆን ያረጋል በዚህ መጽሐፉም እንኳን ርሱ ሊደግመው ተሐድሶዎች በአንባቢያቸው ላይ ሥነ ልቡናዊ ጫና ለመፍጠር ሲሉ የጠቀሷቸውን የማሳሳቻና ለእውነት የቆሙ የማስመሰያ ነገር ግን ደግሞ በሌላ ቦታ እነዚያኑ ተችተው የሚያቀርቧቸውን ነግሮችም አውጥቶ በማሳየት ችግሩ በእነርሱ መኖሩንና እርሱም የሚጸየፈው መሆኑን በመንታ ምስክርነት አረጋግጦልኛል፡፡  
አመክንዮው
በመጨረሻም ይህ ኹሉ ክርክሩ ላይ መለኮታዊ ሥልጣንን ማለትም የትምህርቱ ምንጭ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዘመናት አስተምህሮ መኾኑን፤ ከዚህም ጋር ራሱ ሌሎችን ስለመርዳት በልቡና ውስጥ ያለ እምነትን፣ ተስፋን፣ ፍቅርን (ማዳንን)፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎችን፤ ምልክቶችን ይዞ ወይም እንደ መልካም ባልንጀራ ሳይነጣጥል አሰናስሎ መጠቀም መቻል ይኖርበታል፤ ርሱም አድርጓል፡፡ የአመክንዮው ወይም የክርክሩ ጥግ ይህ መኾኑንና የሚከራከረውም የሚያስረዳው የአምክንዮው ምንጭ የነበረውንና የሚነረዉን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ  መሠረት አድረጎ መኾኑን ገልጾአል፡፡ መጽሐፉ ሃይማኖታዊ እንጂ ፍልስፍናዊ ባለመኾኑ ይህን ማድረጉ ይጠበቃልና፡፡ ከዚህ መውጣት ኑፋቄ መኾኑም ተገልጧል፡፡
ተጨማሪ ሥነ ጽሑፋዊ ጉዳዮች
ከላይ ከተገለጹት ነጥቦች በተጨማሪ የቃላት አመራረጥና የዐረፍተ ነገር አጠቃቀም፣ ግልጽነት፣ ፍሰት፣ ወጥነት፣ ሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም፣ የሌሎችን ሥራዎች ተገቢ ዕውቅና መስጠት አለመስጠትና በመሳሰሉት ሥነ ጽሑፋዊ መሥፈርቶች ሊመዘን ይችላል፡፡ በእኔ ንባብ እነዚህ ኹሉ በአግባቡ ተስተናግደዋል፡፡ አንድ ነገር ለማንሣት ያህል ብቻ የሚከራከራቸውን አካላት አንዳንድ ጊዜ በኹለተኛና ሦስተኛ መደብ ብዙ ቁጥር (እናንተ፤ እነርሱ) በማለት አንዳንድ ጊዜም በነጠላ ቁጥር መጠቀሙ ጥሩ የአስፋልት መንገድ ላይ አልፎ አልፎ እንደወደቁ ጠጠሮች ሊጉራብጡ ከመቻላቸው በቀር ይህ ነው የሚባል ጉልህ ችግር አላገጠመኝም፡፡
ትርጉም
በዚህ ሥራ ውስጥ እጅግ ብዙ ሥራዎች ተተርጉመው ቀርበዋል፡፡ ስለዚህ በትንሹም ቢኾን ነገሩን ማውሳት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ወጥ ሥራ በመኾኑና በመሠረቱ የትርጉም ሥራ ባለመኾኑ ከትርጉም አንጻር መታየት እንደሌለበት ባምንም ብዙ አሥረጂዎችን ተርጉሞ በየርእሱ መጨረሻ ላይ ስለሚያቀርብ ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
መጽሐፉ ትርጉም ባለመኾኑ ምን ዓይነት የትርጉም ሥልት እንደተጠቀመ ራሱ ባይነግረንም በእኔ እምነት ያመጣቸውን ቀደምት ሥራዎችን የተረጎመበትን የትርጉሙ ዓይነት - ነጠላ ትረጉም (literal translation) እንደኾነ ግን ከሠራው መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት እንደ ቃል ለቃል ትርጉም (word for word translation) በአቀባይ ቋንቋ ሰዋስው ተጽዕኖ ያልወደቀ፤ እንደ ነጻ ትርጉምም የፈለገውን ጥሎ የፈለገውን ያላንጠለጠለ፣ ለመጽሐፉ ባለቤቶች ታማኝ የኾነና በእነርሱ ስም የራሱን ሐሳብ አሸክሞ ያላበለ መኾኑን ከምንጫቸው ጋር ለሚያተያይ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ይህም ለሥራው ተገቢውን መንገድ እንደተጠቀመና ብዙዎች (የቱ ለምን እንደሚውል ሳያውቁት ይመስለኛል) ለሃይማኖታዊ ሥራዎች “ውርስና ነጻ ትርጉም” እያሉ በመለጠፍ ሥራቸውን እንድንርቀው ራሳቸው ከሚጋብዙን ስላልደረበው ደስታዬ ታላቅ መኾኑን መሰወር አልችልም፡፡
የነገረ መለኰታዊ አቀራረብ ዳሰሳ (Theological approach review)
ቀደም ብለን እንዳየነው የሃይማኖትን ምንት (Object of faith) የማይለወጥ ቢኾንም ኹልጊዜም ልዩነት ለመፈጠሩ አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች አንዱ ግን ይህን የምንረዳበት ወይም ለመረዳትና ለማስረዳት የምንጠቀምበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ጥንቱንም አንዱ የመከፋፈል ምክንያት ቢኾንም አሁንም ተመሳሳይ ችግሮችን ላለመጨመር በትንሹም ቢኾን መቃኘቱ የሚከፋ አይደለም፡፡ ኾኖም ጉዳዩን በዚህ ዐውድ ለማትየትና በተለይም ከእኔ ዓቅም አንጻር በጣም ከባድ ቢኾንም ቢያንስ ሌሎች ባለሞያዎችንና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ጠይቀን ለመረዳት መቆስቆሱ አይቀርምና በወፍ በረር ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ስለዚህም የእኛ ወይም የኦሬንታል ነገረ መለኮታዊ አገላለጽ መሠረታዊ መንገዶች የኾኑትን በአጭሩም ቢኾን በማቅረብ መጽሐፉን በምናነብበት ጊዜ ለመታዘብ ሊጠቅም ይችላል ብዬ ስለማምን እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁ፡፡
Ø  ንጽጽራዊ ምልሰት (Recapitulation)፡- ይህ ማለት “አዳም ርብ ተፈጥሮ፤ ዓርብ ስለሳተ፤ ጌታችንም በዕለተ ዓርብ ተሰቅሎ አዳነው፤ ሔዋን ባለ ማመን ሞትን አመጣችብን፣ እመቤታችን ደግሞ በማመን ሕይወትን አመጣችንልን” እየተባለ የሚሰጠው ዓይነት ሃይማኖታዊ አቀራረብ ነው፡፡ ይህን መንገድ ትምህርተ ሃይማኖትን ለማስረደት በመጠቀምና በማስፋፋት የሚታወቀው ቅዱስ ሔሬኔዎስ ቢኾንም የሶርያ አባቶች እነ ቅዱስ ኤፍሬምም በደንብ ይታወቁበታል፡፡ በእኛም ሊቃውንት የትርጓሜና የሐተታ መንገድ ላይ ጎልቶ እናየዋለን፡፡ መድሎተ ጽድቅም በተለይ ስለ ነገረ ድኅነትና ስለ እመቤታችን ሲከራከር ይህን አቀራረብ ተጠቅሞበታል፡፡
Ø  ምሳሌያዊ ፍካሬ (Typological interpretation)፡- ይህ ደግሞ በአንድምታ ትርጓሜቻንም ኾነ በሊቃውንቱ ትምህርቶች ከእኛ ቅዱሳን ሊቃውንት ደግሞ በተለይ ደግሞ በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ሥራዎች በተለይም በእንዚራ ስብሐት እንደምናየው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ ምሳሌዎችን፣ ምልክቶችንና ትእምርቶችን በማተትና በመተርጎም ነገረ ሃይማኖትን ማሥረዳት ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥም ይህ አተረጓጎም በተግባር ላይ ውሏል፡፡
Ø  ተቃርኖአዊ ገለጻ (Paradox)፡- ደግሞ በማድነግ የመፈከሪያ ወይም ወደ መረዳት መውሰጃ መንገድ ነው፡፡ ይህም በቅዳሴ ማርያም ላይ በተደጋጋሚ እንደምንሰማው “አንቺ ታናሽ ብላቴና ሳለሽ ሰማይና ምድር የማይወስኑትን እንደምን ቻልሽ? ሰባቱ የእሳት መጋረጃዎች በየት በኩል ተተከሉ?” የሚለውን ዓይነት አገላለጽ ሲኾን በነገረ መለኮት ተማሪዎች ዘንድ “ተቃራኒውን በመግለጽ ማስረዳት (Apophatism)” የሚባለው መንገድ ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍም የእግዚአብሔር ባሕርይ በምን መንገድ እንደሚገለጽ ብቻ ሳይኾን እንዴት እንደሚገለጽም ታትቶበታል፤ ቀርቦበታልም፡፡
Ø  ሥነ ቃላታዊ ፍካሬ (etymological analysis)፡- ይህ ደግሞ አንድን ልዩ ሐሳብ ለመወከል የተጠቀምንበትን ቃል ከቃሉ አፈጣጠር ተነሥቶ በዘመናት ያካሔዳቸው ለውጦች ካሉ እነርሱን እያሳየ መጥቶ አሁን በጥቅም ላይ ያለው ቃል የምንፈልገውን ሐሳብ እንዴት እንደሚወክል በማስረዳት ለመንታ ትረጉምና ለኑፋቄ ወይም ለመንሸራተት ምክንያት የሚኾኑትን ግልጽ በማድረግ የሚሰጥ ዕቅበተ እምነታዊ አስተምህሮ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በእኛ እንደ ባሕርይ፤ ጸጋ፤ ተዋሕዶ፤ ቱሳሔ፣ ቡዓዴ፣ ፍልጠት፣ ሚጠት፣ ... ያሉት እንደሚታዩ ማለት ወይም የትርጓሜ መምህራን “ግሰሰው” ብለው ግስ አስወርደው ከዚያ እንደሚነሡት ያለ ማለት ነው፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ ከሞላ ጎደል በሌሎቹም ጥቅም ላይ የሚውሉ ስለኾኑ እነዚህ ነገሮች ከምሥራቅ በተለይም ከኦሬንታል ነገረ ሃይማኖት ጋር ያላቸውን አቀራረብ ማየት በእጅጉ አስፈላጊ ይኾናል፡፡ የኦሬንታል በተለይም የኢትዮጵያና የሶርያ የነገረ ሃይማኖት አቀራረብ በጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ዕብራዊ (Biblical or Hebraic) ሲባል የሌሎቹ ደግሞ ሄለናዊ (Hellenestic or Dualstic) ይባላል፡፡ የላቲን ደግሞ እውቃተዊነትም (Scholastic) ይጨመርለታል፡፡ ይህ ደግሞ በዚህ መጽሐፍም በግልጽ ስለቀረበ ጊዜ ማባከን አያስፈልግም፡፡
“የእኛ ዕብራዊ ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሚባለው ለምንድን ነው?” ብንል በመጽሐፍ ቅዱስ ሰው የነፍስና የሥጋ ውሑድ ኾኖ ነው የሚቀርበው፡፡ ይህም ማለት ሄለናዊ ወይም ግሪካዊ በሚባለውና ሥጋን ብቻውን የክፉ ኹሉ መገኛ አድርጎና ነፍስን ለይቶና ገንጥሎ ኹለትነትን ወይም ምንታዌን ከሚያቀነቅነው በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ይህ ቀራረብ ደግሞ ለጥንቶችም ኾነ ለቅርቦቹ የስሕተት መነሻነት ትልቁ ዕንቅፋት ነው፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ብንመለከት ግን የመልክዐ መልክዕ ድርሰቶችን ብቻ ብናይ ነገረ ሃይማኖታችን ምን እንደኾነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ልክ በመኃልየ መኃልይ ላይ እንደተገለጸው የአካል ብልቶች ለየብቻ እየተገጹ ምስጋና ማቅረብ ዋሕድነትን - ተዋሕዶን በግልጽ ያስረዳል፡፡ በሌሎቹ በሄለናውያን ግን እንዲህ ያለ ምስጋና አይገኝም፤ የእኛን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ዕብራዊ የሚያሰኘው ይህ ነው፡፡
ኹለተኛው መሠረታዊ መለያ ግን ለመሠረታዊ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች በተለይም ስለ እግዚአብሔርና መለኮታዊ ነገሮች ስለፈጸመውም ማዳን ብያኔ (Definition) የሚባል የለንም፡፡  ምክንያቱም ብያኔ ማለት ለነገሮች ወሰን ድንበር ማበጀት ስለኾነ እግዚአብሔር ደግሞ በባሕርዩ ስለማይወሰን አይበየንም፤ ማዳኑም እንደዚሁ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት በዋናነት በእኛ ቤት ተግባር ላይ የሚውሉትም ይህን ከመጸየፍ የተነሣ ነው፡፡ በርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚለዩት ላቲኖችና ከእነርሱ የወጡት ፕሮቴስታንቶችና ልጆቻቸው ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህም ነገረ ሃይማኖትን ከላይ በገለጽናቸው በአራቱ መንገዶች ብቻ በትርጓሜ እናስረዳለን እንጂ አንወስነውም፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም የተዋሕዶ ዕቅበተ እምነት መጻሕፍት አቀራረብ በዚሁ መሠረት መኾኑን ማየት በእጅጉ አስፈላጊ ይኾናል፡፡ የዲያቆን ያረጋል መድሎተ ጽድቅም ወሳኝ ሐሳቦችን እነዚህን ተጠቅሞ የሚያስረዳ ስለኾነ በርግጥም መድሎተ ጽድቅ ነው፡፡

ማጠቃለያ
አንድ ሊቅ በይዘቱ ዕቅበተ እምነት የኾነ መጽሐፍ እነዚህን ነገሮች አሟልቶ በጥሩ ሙግት (Argument) የሚዘጋጅ ከኾነ ርሱ እንደ አልማዝ ነው ይላል፡፡ ምክንያቱም አልማዝ፡-
ü  መልካምና ደስ ያሚያሰኝ ብርሃንን ስለሚያንጸባርቅ፤
ü  ብርሃኑን ራሱ የሚያመነጨው ሳይኾን የከቀን የወሰደው ስለኾነ፤
ü  ውድ ስለኾነ፤
ü  ጠንካራና በቀላሉ የማይሰበር ነገር ግን ሌሎቹን የሚሰብር ስለኾነ፡፡
በነቢዩ ሕዝቅኤል ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢኾኑ አትፍራቸው ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ /ሕዝ 3፤9/ ተብሎ እንደተጻፈው በእኔ ግምገማ መድሎተ ጽድቅም እንደ አልማዝ በጨለማ አለማወቅ ላሉት ብርሃን ተዋሕዶን የሚያበራ፣ ብርሃኑንም ከራሱ ያመነጨው ሳይኾን እንደ አልማዝ ከቀን (ከቀደሙ ሊቃውንት) የተቀበለው ስለኾነ ለተከራካሪዎቹም በቀላሉ የማይሰበር እንደ አልማዝ ጠንካራ ከይዘቱና ከአቀራረቡም አንጻር እንደ አልማዝ ውድ ስለኾነና እነዚህን ኹሉ ስለሚያሟላ ለእኔ አልማዝ ብዬዋለሁ፤ አልማዝ - መድሎተ ጽድቅ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


1 comment:

  1. መጽሐሁ አካሄዱ እንደ መድሎተ አሚን ነው... መጽሐፉን በብዙ ደስታ አነበብሁት እግዚአብሔር የነ መልአከ ብርሃናትና አባ ጎርጎርዮስ የነቅ/አትናቴዎስና የነቅ/ዮሐንስ አፈወርቅን በረከት እንዳሳደረበት ተሰምቶኛል እግዚአብሔር ይጠብቅህ..... ተኩላዎችን የሚያሳድድ ድንቅ መጽሐፍ

    ReplyDelete