Monday, June 8, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ዐሥራ አንድ)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 2 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የእሑድ ዕለት ፍጥረታት
የእሑድ ሰዓተ ሌሊት ፍጥረታት
እሑድ ማለት የዕለታት መጀመሪያ ማለት ሲኾን ይኸውም እግዚአብሔር ፍጥረቱን የፈጠረበት የመጀመሪያው ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት ስምንት ፍጥረታት የተፈጠሩ ሲኾን፥ እነርሱም፡-
ü  በመጀመሪያ ሰዓተ ሌሊት - አራቱ ባሕርያተ ሥጋ እና ጨለማ፣
ü  ከኹለተኛው ሰዓተ ሌሊት እስከ ዘጠነኛው ሰዓተ ሌሊት - ከእሳት ሙቀቱን ትቶ ብርሃኑን ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን፣
ü  በዘጠነኛው ሰዓተ ሌሊት ደግሞ መላእክትን ፈጠረ፡፡
እስኪ እያንዳንዳቸውን በመጠን በመጠኑ እንመልከታቸው፡፡

አራቱ ባሕርያተ ሥጋ
ስለ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ በክፍል ዐሥር ትምህርታችን የተማርነው ስለኾነ በዚያ ይመልከቱ፡፡ እዚህ ላይ የምንጨምረው ነገር ቢኖር ግን እነዚህ ባሕርያተ ሥጋ የሚባሉት ዛሬ ላይ እንደምናየው በዓለም ላይ የመሉ አለመኖራቸውን ነው፡፡ በመጀመሪያ ሲፈጠሩ ጥቂት ጥቂት ነበሩ፡፡ “ብዙ ተባዙ፤ ስፉ ተስፋፉ” ብሎ በኀልዮ (በማሰብ) ሲያዛቸው ግን በዙ፤ ተባዙ፤ ሰፉ፤ ተስፋፉ፡፡ ሕሊና እግዚአብሔር የመጠነላቸውን መጠን ደርሰውም ቆሙ፤ በከኀሊነቱ ጸኑ፡፡
ጨለማ
እግዚአብሔር ጨለማን መፍጠሩ ጨለማ ውስጥ ያለ ነገር እንደማይታወቅ ኹሉ መሠወሪያውን በጨለማ ያደረገው እግዚአብሔርም በባሕርየ መለኮቱ እንደማይመረመር /መዝ.16፡11/፤ የሚመረመረው በሃይማኖት ብቻ እንደኾነ እንድናውቅ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች “ጨለማ ማለት የብርሃን አለመኖር ነው” ብለው ይላሉ፡፡ ይህንን ሐሳብ ከሚያራምዱ መካከልም አውግስጢኖስ ይገኝበታል፡፡
ሰባቱ ሰማያት
v  ጽርሐ አርያም፡- ሰማየ ሰማያት፣ ከሰማያት ኹሉ በላይ ያለች ሰማይ ናት፤ ዳር ድንበሯ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም አያውቀውም፡፡
v  መንበረ ስብሐት፡- አራት ቅርጽ ያላት ሲኾን ድንኳን ትመስላለች፤ የምንኖርባትን ዓለም ታክላለች፤ ሥላሴ በፈለጉት መጠንና መልክ ለቅዱሳን ይገለጡባታል፤ ሰባት የእሳት መጋረጃም አላት /ዘፍ.28፡12-17፣ ኢሳ.6፡1-2/፡፡
v  ሰማይ ውዱድ፡- ኪሩቤል የሚሸከሙት የሥላሴ ዙፋን ነው /ሕዝ.10፡19-20/፡፡
v  ኢዮር፣ ራማ፣ ኤረር፡- እነዚህ ሦስቱ የመላእክት ከተሞች ሲኾኑ ከአድማስ እስከ አድማስ የተዘረጉ ናቸው፡፡ ከላይ ወደ ታች፥ መጀመሪያ ሰማይ ውዱድ፤ ቀጥሎ ኢዮር፣ ቀጥሎ ራማ፣ ቀጥሎ ኤረር የተያያዙ ናቸው፡፡ ስፋታቸውም እኩል ነው፡፡
v  ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፡- አራት መዓዘን፣ 12 በሮች አሏት፡፡ በውስጧ የብርሃን ሳጥን የተቀረጸ ከሥላሴ ፀዳል የተሣለባት ታቦት ዘዶር አለች፡፡ ይህቺም የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዓይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማው፣ በሰውም ልብ ያልታሰበ፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጃት ያላት ይህቺው ናት /1ኛ ቆሮ.2፡9-10/፡፡ መጠኗም የተወሰነ ነው፡፡ ባለ ራእዩ ዮሐንስ አዲሲቱ ሰማይ ያላትም ይህቺው ናት /ራእ.21፡2-3/፡፡ በጕበኖቿ የ12ቱ ሐዋርያት ስም፤ በመድረኮቿ የ12ቱ ነገደ እስራኤል ስም፣ በአዕማዶቿ የጻድቃን የሰማዕታት ስም ተጽፎባታል /ራእ.21፡11-15/፡፡

መላእክት
መልአክ የሚለው የግእዝ ቃል ኹለት ትርጉሞች አሉት፡፡ አንደኛው አለቃ፣ ሹም ማለት ነው፡፡ በዮሐንስ ራእይ ላይ የምናገኛው ሰባቱ የአቢያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች መላእክት ተብለው መጠራታቸውም ከዚህ አንጻር ነው /ራእ. 2 እና 3/፡፡ ኹለተኛውና ከተነሣንበት ርእስ አንጻር ስናየው ደግሞ መልክእተኛ፣ የተላከ የሚል ትርጕም አለው /ዕብ.1፡14/፡፡ ይኸውም የመላእክት ተግባር ምን እንደኾነ የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ መላእክት ከእግዚአብሔር ወደ ሰው፥ ከሰውም ወደ እግዚአብሔር የሚላላኩ መናፍስት ናቸውና፡፡ መላእክት በሌላ ስማቸው የሰማይ ሠራዊት ተብለው ይጠራሉ፡፡
መላእክት ኹለት ወገን ናቸው፡፡ ብርሃናውያን መላእክትና የጨለማ አበጋዝ የኾነው የዲያብሎስ ሠራዊት የኾኑት እኩያን መላእክት፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን መላእክት ከሌሎቹ መላእክት በአጠራር የምንለያቸው ቅዱስ በሚል ቅጽል ነው፡፡
ከሰባቱ ሰማያት በኋላ መፈጠራቸው ለምን እንደኾነ አክሲማሮስ ሲገልጥ፡- “በፊት ፈጥሯቸው ቢኾን እኛም አብረነው ፈጠርን፤ ያዝንለት፤ ተራዳነው ባሉ ነበር፡፡ አንድም ርሱ ቢመሠርት እኛ ገነባን፤ ርሱ ቢገነባ እኛ መሠረትን ባሉ ነበር፡፡ ይህም ሳጥናኤል በኋላ እኔ ፈጠርኳችኁ እንዳለው ማለት ነው” ይላል፡፡ ተፈጥሮአቸውም ካለ መኖር ወደ መኖር ነው፡፡ መላእክት እንደ እሳት የሚሞቁ፣ እንደ ነፋስ የሚረቁ ስለ ኾነ፤ አንድም እንደ እሳት እንደ ነፋስ ፈጣኖችና የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽሙ ኃያላን ስለኾነ ባሕርያቸውን ለመግለጥ ከነፋስና ከእሳት ተፈጠሩ ይባላሉ /መዝ.103፡4፣ መዝሙረ ዳዊት ንባቡ ከነትርጓሜው፣ ገጽ 489 /፡፡ 
በዐሥረኛው ሰዓተ ሌሊት እግዚአብሔር ኢዮርን ለ4 ከፈላት /ሕዝ.10፡1-2/፡፡ በዚያም 40 ነገደ መላእክት በ4 ከፍሎ አኖራቸው፡፡ ዐሥሩን አጋእዝት፣ ዐሥሩን ኪሩቤል፣ ዐሥሩን ሱራፌል፣ ዐሥሩን ኃይላት ብሎ ሰየማቸው፡፡ አለቆቻቸውም በቅደም ተከተል ሳጥናኤል (በኋላ ወድቋል)፣ ኪሩብ፣ ሱራፊ፣ እና ቅዱስ ሚካኤል ናቸው /ኄኖክ.10፡2-10/፡፡
  ኪሩቤል የሚባሉት አራት ራስ አራት ገጽ አላቸው፡፡ ገጻቸውም ገጸ ሰብእ ገጸ አንበሳ ይመስላል፡፡ ሰውነታቸው ኹሉ በዓይን የተሸለመ ሲኾን ዓይናቸውም እንደ ነብር ቆዳ ዥንጕርጕር ነው /ሕዝ.1፡6-7፣ 18-19/፡፡ አገልግሎታቸው በቀሳውስት አምሳል የሥላሴን ዙፋን መሸከም ነው፡፡
  ሱራፌል የሚባሉት በዲያቆናት አምሳል ለጸሎት የሚተጉና የሚያተጉ የምስጋና መላዕክት ናቸው፡፡ ገጻቸው ገጽ ንስር ገጸ እንስሳ ይመስላል፡፡ ስድስት ስድስት ክንፍ አላቸው /ኢሳ.6፡2-3/፡፡
  ኃይላት የሚባሉት የሥላሴ ሰይፍ ጃግሬዎች ናቸው፡፡
በዐሥራ አንደኛው ሰዓተ ሌሊት ከ60ዎቹ 30ዎቹን በሦስት ከፍሎ በራማ አኖራቸው፡፡ ዐሥሩን አርባብ፣ ዐሥሩን መናብርት፣ ዐሥሩን ሥልጣናት አላቸው፡፡ አለቆቻቸውም በቅደም ተከተል ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል እና ቅዱስ ሱርያል ናቸው፡፡
  አርባብ የሚባሉት በሥላሴ ፊት በአጋፋሪ በአስተናጋጅ አምሳል የሚቆሙ ናቸው /ኄኖክ 10፡7-8፣ ሉቃ.1፡19/፡፡
  መናብርት የሚባሉት በጋሻ ጃግሬ አምሳል ያገለግላሉ፡፡ የመብረቅ ጋሻ የእሳት ጦር ይዘው ዘለዓለም እንደ ነፋስ ሲበሩ ይኖራሉ፡፡
  ሥልጣናት የሚባሉት የሥላሴ አዋጅ ነጋሪዎችና መላዕክትን በየጊዜው ለጸሎትና ለምስጋና የሚያተጉ ናቸው፡፡
በዐሥራ ኹለተኛው ሰዓተ ሌሊት የተቀሩትን ሠላሳውን ነገደ መላእክት በኤረር አሰፈራቸው፡፡ ዐሥሩን መኳንንት፣ ዐሥሩን ሊቃናት፣ ዐሥሩን መላእክት አላቸው፡፡ አለቆቻቸውም በቅደም ተከተል ሰዳካኤል፣ ሰላታኤል፣ እና አናንኤል ይባላሉ፡፡
  መኳንንት የሥላሴ ቀስተኞች ናቸው፡፡ ተራራ የሚንድ፣ ድንጋይ የሚሰነጥቅ፣ የእሳት ፍላፃ የእሳት ቀስት ይዘው ሰውን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሲጠብቁ ይኖራሉ፡፡ በትንሣኤ ዘጕባኤ ጊዜ የሰውን ኹሉ አጥንት ሰብስበው ለትንሣኤ የሚያበቁ እንዚኽ ናቸው /ማቴ.24፡31-42/፡፡ 
  ሊቃናት የሥላሴ ፈረስ ባልደራስ ናቸው፡፡ የእንስሳት ጠባቂ መላዕክት ናቸው፡፡ 
  መላእክት እንደ ብረት የጸና የእሳት ነጐድጓድን ወደ ምድር የሚወነጭፉ፣ ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን ከምድር በላይ ከሰማይ በታች የተፈጠሩትን የሚጠብቁ ናቸው /ኩፋሌ 2፡6-8/፡፡
እነዚህ መቶ ነገደ መላእክት ለተልእኮ ፈጣሪ ካላዘዛቸው በስተቀር ከስፍራቸው አይለቁም፡፡ ሲያዛቸው ግን ወደ ላይ እስከ ጽርሐ አርያም ወደ ታች እስከ በርባሮስ ድረስ ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ፡፡
      የመላእክት ባሕርይ እንዴት ነው?
የመላእክት ባሕርይ ከሰው ጋር የሚያመሳስለውም የሚያለያየውም ነጥብ አለው፡፡ ከሰው በምን ይለያሉ ቢሉ መላእክት፡-
·         ረቂቃን ናቸው፡፡ ከነፋስ ነፍስ ትረቃለች፤ ከነፍስ መላእክት ይረቃሉ፤ ከመላእክት የመላእክት ሕሊና ይረቃል፤ ከመላእክት ሕሊና ደግሞ ሥላሴ ይረቃሉ፡፡ ሊቁ “የመንፈሳውያን (የመላእክት) የሕሊናቸው ርቀ’ት በአንተ ዘንድ እንደ ሥጋ የገዘፈ ነው” እንዲል፡፡
·         እንደ ሰው አይራቡም፤ አይጠሙም፡፡ ልብስ፣ መጠለያ አይፈልጉም፡፡ “እኔም ተገለጥኩላችኁ፤ ነገር ግን እይታን አያችኁ እንጂ ከእናንተ ጋር አልበላኹም፤ አልጠጣኹምም” /ጦቢት 12፡19/፡፡
·         የመላእክት ምግባቸውም ኾነ ዕረፍታቸው የእግዚአብሔር ምስጋና ነው፡፡ ሊቁ “ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፥ ዕረፍታቸውም ምስጋናቸው፤” በማለት እንደተናገረ፡፡
·         መላእክት ፆታ የላቸውም /ማቴ.22፡30-31/፡፡ በመኾኑም አይጋቡም፤ አይዋለዱም፡፡
·         መላእክት መንፈሳውያን በመኾናቸው ስለ ነገ አይጨነቁም፡፡
·         መላእክት ከዝንጋዔ የራቁ፣ ባለ አዕምሮ የኾኑ፣ ዕውቀት ያላቸው፣ ይዋኄንና ትዕግሥትን ገንዘብ ያደረጉ፣ ለዘለዓለም የማይነጥፍና የማያቋርጥ ይልቁንም ዘወትር እንደ ዥረት ውኃ የሚወርድ ምስጋና ያላቸው ናቸው፡፡ 
·         ምንም እንኳን ከሰው በፊት ቢፈጠሩም አያረጁም፡፡ ዘወትር ውቦች፣ ብርቱዎችና ውርዙዋን ናቸው፡፡
·         ኢ-መዋትያን ናቸው (አይሞቱም) /ሉቃ.20፡36/፡፡ ይኸውም ልክ እንደ እኛ ነፍስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ ነው፡፡ 
·         እንደ ሰው አንድ ጊዜ ደግ ሌላ ጊዜ ክፉ በመሥራት አይዋልሉም፡፡
ከሰው ምን ያመሳስላቸዋል ስንል ደግሞ፡-
ü  ምንም ረቂቃን ቢኾኑም ህልውና ከአካል ጋር አላቸው፡፡ ዮሐንስ ዘደማስቆ የተባለ አባት ይኽን ሲያብራራው፡- “መላእክት ረቂቃን ናቸው የምንላቸው ከእኛ አንጻር ነው፡፡ ከማንም ጋር ከማይነጻጸረው ከእግዚአብሔር አንጻር ሲታዩ ግን ግዙፋን ናቸው፡፡ ፍጹም ረቂቅ እግዚአብሔር ብቻ ነውና” ብሏል፡፡
ü  ምንም ረቂቃን ቢኾኑም ውሱናን ናቸው፡፡ እንደ ሰው በቦታ የሚገቱ ባይኾኑም መጠን አላቸው፡፡ መጠናቸውና አርዐያቸውም የተለያየ ነው፡፡ ቁመታቸው ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መላእክት አሉ፡፡ በክንፋቸው ብቻ አንድ አገር የሚያለብሱ መላእክት አሉ፡፡ ራሳቸው ብቻ ተራራ የሚያክሉ መላእክት አሉ፡፡ በዓይን የተቀረፁ የተሸለሙ ኹለንተናቸው ዓይን የኾነ መላእክት አሉ፡፡ ስድስት ክንፍ ያላቸው መላእክት አሉ፡፡ መብረቅ ለብሰው መብረቅ ተጐናጽፈው የሚኖሩ መላእክት አሉ፡፡ ነፋስ ለብሰው ነፋስ ተጐናጽፈው የሚኖሩ መላእክት አሉ፡፡ ብሩህ ደመና ጠምጥመው የሚኖሩ መላእክት አሉ፡፡ እግራቸው ዓምደ እሳት የሚመስል መላእክት አሉ፡፡ የእነዚኽን መላእክት አርዓያቸውን መጠናቸውን ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቀው የለም /ኩፋ.2፡7-8/፡፡
ü  ዐዋቂዎች ናቸው፡፡ ዕውቀታቸው ግን ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው ከሰው እጅግ ከፍ ያለ ነው /2ኛ ጴጥ.2፡11/፡፡ ምንም ከሰው እጅግ ከፍ ያለ ቢኾንም ግን ዕውቀታቸው መጠን አለው፡፡ ከእግዚአብሔር በቀር ፍጹም ዕውቀት ያለው ፍጥረት የለምና፡፡ እኛ ዕውቀታችን እንደ መላእክት ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ነው /1ኛ ቆሮ.13፡12/፡፡
ü  ነጻ ፈቃድ አላቸው፡፡
ü  እንደ ሰው ባሕርያቸውን የሚገልጽ ስም አላቸው፡፡
ሰው ከመበደሉ በፊት ልክ እንደ መላእክት ንጹሕ፣ ውብና ብርቱ ነበር፡፡ በፍጥረታት ላይ ሥልጣን ነበረው፡፡ ርሱ ሲበድል ግን ከሥልጣን የወረደ ሰው እንደ ድሮ የሚያከብረው እንደሌለ ኹሉ ፍጥረታቱ አዳምን አልታዘዝ አሉት፡፡ እንደዉም ተበረታቱበት፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውም ወደ ቀድሞ ክብራችን ወደ ልጅነት ወደ ቀድሞ ቦታችን ወደ ገነት ከዚያም በላይ ወደ መንግሥተ ሰማያት ሊመልሰን ነው፡፡ በመኾኑም ሰው ምንም እንኳን በዚኽ ዓለም ሳለ ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢያሳልፍም በመጨረሻ መላእክትን ይመስላል፡፡ ለዚኽም ነው ቅዱሳን መላእክት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብ.1፡14 ላይ እንደገለጸው ታናሽ ወንድማቸውን ሰውን በማገልገል ላይ ያሉት፡፡
የመላእክት የባሕርይ ስም ይታወቃልን?
ምንም እንኳን በስም በስም ብንጠራቸውም ስማቸው ነገረ እግዚአብሔርን አንድም ተልእኮአቸውን የሚያስረዳ እንደኾነ እንጂ በቅጥነተ ኅሊና ስናስተውለው ማን ማን እንደሚባሉ አይታወቁም፤ ስም የሌላቸው ኾኖ ሳይኾን የሰው አእምሮ ሊረዳው አይችልም፡፡ ለምሳሌ ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነው፡፡ ይኽም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ነገረ ሥጋዌን የሚገልጽ እንጂ የመልአኩ የባሕርይ ስም አይደለም፡፡ ሚካኤል ማለት መኑ ከመ እግዚአብሔር ማለት ሲኾን ይኸውም እግዚአብሔር አምሳያ የለሽ መኾኑን የሚገልጽ እንጂ የመልአኩ የባሕርይ ስም አይደለም፡፡
መላእክት መልክ አላቸውን?
      በመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን መላእክት በተለያየ መልክ እንደተገለጹ እናነባለን፡፡ ለምሳሌ፡-
v  በእሳት አምሳል /ዘጸ.3፡2-4/፤ ለሙሴ፤
v  በዓምደ ብርሃንና ደመና አምሳል /ዘጸ.13፡21፣ 23፡20-21፣ ዘኅ.20፡16/፤ ለሕዝበ እስራኤል፤
v  በተራ ሰው አምሳል /መሳ.6፡12-23/፤ ለጌድዮንና ለጦቢት፤
v  በነቢይ አምሳል /መሳ.13፡6/፤ ለማኑሄ ሚስት፤
v  በእሳት ፈረስና ሰረገላ አምሳል /2ኛ ነገ.6፡16-17/፤ ለኤልሳዕ ሎሌ፤
v  በእሳት አምሳል /ሕዝ.8፡2/፤ ለነቢዩ ሕዝቅኤል፤
v  በፍታ እንደ ለበሰ፣ ወገቡም በወርቅ እንደታጠቀ ሰው /ዳን.10፡5/፤ ለነቢዩ ዳንኤል፤
v  ልክ እንደ ትሑት ሰው /ሉቃ.1፡12-13/፤ ለዘካርያስና ለእመቤታችን፤
v  የጌታ ክብር በዙርያቸው ኾኖ /ሉቃ.29-30/፤ ለእረኞች፤
      ይህም ማለት መላእክቱ ሰው እንዲገባው በሰው አእምሮ መጠን ተገለጡ ማለት እንጂ መልካቸው ተለዋዋጭ ነው፤ የራሳቸው የኾነ ቋሚ መልክም የላቸውም ማለት አይደለም፡፡
የመላእክት ተግባር ምንድነው?
የመላእክት ተግባር እንደሚከተለው ማየት ይቻላል፡-
Ø  ያለማቋረጥ እግዚአብሔርን “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ ያመሰግናሉ /ኢሳ.6/፤
Ø  የእግዚአብሔርን መልካም ዜና ወደ ሰው ያመጣሉ፡፡ ይኸውም ለአጋር፣ ለአብርሃም፣ ለሐና እመ ሳሙኤል፣ ለካህኑ ዘካርያስ ለእመቤታችን እንዳመጡላቸው ማለት ነው፡፡
Ø  ማስተዋልንና ጥበብን ለሰው ልጆች ያድላሉ፡፡ ይኸውም ቅዱስ ገብርኤል ለነቢዩ ዳንኤል፣ ቅዱስ ዑራኤልም ለዕዝራ እንዳደረጉት ማለት ነው፡፡ 
Ø  ሰውን ከጥፋት ያድናሉ፡፡ ይኸውም ሎጥን ከሰዶምና ጐመራ ሰዎች ጋር እንዳይጠፋ /ዘፍ.19/፣ ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነድ እሳት እንዳዳኗቸው ማለት ነው /ዳን.3፡12-30/፡፡ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት፡- “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል” /መዝ.34፡7/፤ በሌላ ቦታም “ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም መቅሰፍትም ወደ ቤትህ አይገባም፡፡ በመንገድህ ኹሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፡፡ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሱኻል” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.91፡10-12/፡፡
Ø  ሰውንም መልእክት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፡፡ የሰውን መልእክት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ ሲባል ምን ማለት እንደኾነ የቆጵረሱ ሊቀ ጳጳስ ሊቁ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ መጽሐፉ ላይ፡-“ (የካህናተ ሰማይ ማዕጠንት) የጻድቃን ጸሎት፤ የሰማዕታት ገድል፤ የደጋግ ሰዎች ምግባር ነው” ብሎ ያብራሯል /መጽሐፈ አክሲማሮስ፣ ገጽ 51/፡፡
Ø  የእግዚአብሔርን ቁጣ ወደ ሰዎች ያስተላልፋሉ፡፡ እነርሱም የመዓት መላእክት የሚባሉ ሲኾኑ በትዕቢቱና በክፋቱ ከሥልጣኑ የወረደው የዲያብሎስ ሠራዊት የነበሩና በኋላ ግን አለቃቸው ሲክድ ያልካዱ በእምነታቸው የፀኑ ከሣጥናኤል ሠራዊትነት ተለይተው ከነቅዱስ ሚካኤልና ከነቅዱስ ገብርኤል ጋር የተደመሩት ናቸው፡፡ እነዚኽ የመዓት መላእክት እጅግ ቁጡዎችና ቀናተኞች ናቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

1 comment:

FeedBurner FeedCount