Pages

Monday, July 13, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ዐሥራ ኹለት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 6 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ክሕደተ ሰይጣን
ሰይጣን በዕብራይስጥ ሲኾን ዲያብሎስ ደግሞ በግሪክኛ ነው፡፡ ትርጓሜውም አሰናካይ፣ ባለ ጋራ፣ ወደረኛ፣ ጠላት፣ ከሳሽ፣ ተቃዋሚ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተቃወመው ጊዜ፡- “ወደኋላዬ ሒድ አንተ ሰይጣን፤ … ዕንቅፋት ኾነህብኛል” መባሉም ስለዚሁ ነው /ማቴ.16፡23/፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ከ40 በላይ በኾኑ የተለያዩ ስሞች ተገልጾ እናገኟለን፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም፡-
·         የቀድሞ ክብሩን ለመግለጽ - የአጥቢያ ኮከብ /ኢሳ.14፡12/፤
·         ምእመናንን እንዲሁ በሐሰት ይከሳልና- ከሳሽ /ራእ.12፡10/፤
·         ገዳይነቱንና ኃይለኝነቱን ለመግለጽ - ዘንዶ /ራእ.12፡3/፤
·         ክፋት እንዲበዛ የሚያደርግ ነውና - ክፉው /ማቴ.13፡19/፤
·         ከዋነኞቹ ግብሮቹ ለመግለጽ - ፈታኙ /ማቴ.4፡3/፤
·         የርኩሰት ጌታዋ ነውና - ብዔል ዘቡል /ማቴ.12፡24-27/፤
·         ወዘተርፈ
ሰይጣን እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የኾኑትን ተቃውሞ የወደቀው የመጀመሪያው መልአክ ነው፡፡ ምንም እንኳን መልካም የኾነውን ኹሉ እየተቃወመ የራሱን መንግሥት ሊያቆም የሚጥር ቢኾንም ከእግዚአብሔር ጋር የተካከለ መንግሥት (መለኮታዊ ባሕርይ) የለውም፤ መለኮታዊ ባሕርይ የእግዚአብሔር ገንዘብ ብቻ ነውና፡፡

የሳጥናኤል ጥንተ ተፈጥሮ
ሰይጣን (በቀድሞ ስሙ ሳጥናኤል) እንደ ሌሎቹ መላእክት በመጀመሪያው ቀን የተፈጠረ ሲኾን እስኪበድል ድረስ ፍጹም፣ ንጹህ፣ ጥበብን የተሞላ፣ በውበቱም እጅግ ያማረ ነበር፡፡
ብዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩት ስለ ሳጥናኤል ጥንተ ተፈጥሮ በስፋት የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 28 ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ የጢሮስ ንጉሥ ተብሎ የተገለጠው ይኸው ሳጥናኤል ሲኾን፥ እግዚአብሔር ለሳጥናኤል ሰጥቶአቸው የነበሩ ስጦታዎች ተገልጠዋል፡፡ ጥቂቶቹም የሚከተሉት ናቸው፡-
1.  ጥበብ፡- ሳጥናኤል ከነቢዩ ዳንኤል ይልቅ ጥበበኛ ነበረ /ሕዝ.28፡3/፡፡ ንጉሥ ብልጣሶር ያየውን ራእይ እና ትርጓሜው ምን እንደኾነ እግዚአብሔር ለነቢዩ ዳንኤል እንደገለጠለት ኹሉ /ዳን.5/፥ ለሳጥናኤል ደግሞ ከዚህ በበለጠ መንገድ ብዙ ሰማያዊ ምሥጢራትን ይገልጥለት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሳጥናኤልን የሚያነጋግረው እንደ ቅርብ ወዳጁ ነበር፤ የማይገልጽለት ምሥጢርም አልነበረም፡፡ ከአፍአ ሳይኾን ከውሳጤ ከሰማያዊ ኃይላት ይልቅ በጥበብ የተሞላና የውበት መደምደሚያ (ጣሪያ) ነበር፡፡ አወዳደቁ እጅግ የከፋ ያደረገውም ከዚሁ ልዕልና ፍጹም ስለወደቀ ነው፡፡
2.  ፍጹም ደስታ፡- ነቢዩ ሕዝቅኤል ሲናገር፡- “(ሳጥናኤል) በእግዚአብሔር ገነት በኤደን” ነበር ይላል /ሕዝ.28፡13/፡፡ ኤደን ማለት ደስታ ማለት ነው፡፡ ይህ ደስታ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም” ብሎ እንደተናገረ /ዮሐ.14፡27/ ከዚህ ዓለም እንደምናገኘው ደስታ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር የኾነ ደስታ ነው እንጂ፡፡ ማዕርጉ አጋእዝት ለተባሉት ነገደ መላእክት አለቃ ኾኖ የተሾመ መልአክ ስለ ነበር ሥራውም የሥላሴን መጋረጃ እየከፈተና እየዘጋ በፍጹም ደስታ መኖር ነበር፤ “አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ” እንዲል /ሕዝ.28፡14/፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ሥላሴ በአንድ ክፍል ውስጥ ተወስነው የሚኖሩ ናቸው ለማለት ሳይኾን ሳጥናኤል ምን ያህል ቅሩበ እግዚአብሔር እንደነበር መናገር ነው፡፡
3.  ሥራ፡- እግዚአብሔር የሥራ አምላክ ነው፡፡ ሥራ መሥራትን ያቆመበት ጊዜ የለም፡፡ ይህ ሥራስ ምንድነው? ቢሉ ፍጥረታቱን መጠበቅ፣ መመገብ፣ ማዳን እና የመሳሰለ ኹሉ ነው፡፡ ይህም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ገልጦታል፡- “አባቴ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራል፤ እኔ ደግሞ እሠራለሁ” /ዮሐ.5፡17/፡፡ ይህ ባሕርዩም ለመላእክትና ለሰዎች በጸጋ ሰጥቶናል፡፡ ሰይጣን ግን ይህ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ስጦታ ለእግዚአብሔር ክብር፣ አንድም ለራሱ ድኅነት፣ ለራሱ ቅድስና ሳይኾን ለጥፋቱ ተጠቀመበት፤ አሁንም እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ነቢዩ ይህን ሲገልጠው እንዲህ ይላል፡- “በጥበብህና በማስተዋልህ ብልጥግናን ለራስህ አግኝተሃል፤ ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል፡፡ በታላቅ ጥበብህና በንግድህ ብልጥግናህን አብዝተሃል፤ በብልጥግናህም ልብህ ኰርቶአል” /ሕዝ.28፡4-5/፡፡ ይህ ጥበብና ብልጥግና (በረከት) ከእግዚአብሔር ያገኘው ነበር፤ ነገር ግን የራሱ እንደኾነ አስቦ ታበየ፡፡ በማዕረግ ከሌሎች መላእክት ይልቅ ከፍ ያለ ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ማዕረጉ የሌሎች መላእክት ፈጣሪ እንደኾነ አስቦ ታበየበት፡፡ እንዲህ የታበየውም እግዚአብሔር እነዚህ ከላይ የገለጥናቸውን በረከቶች (ለምሳሌ ጥበብ፣ ማስተዋል፣ ውበት፣ ንጽህና፣…) ስለሰጠው አይደለም፡፡ እነዚህ በረከቶች የራሱ እንደኾኑ አስቦ ስለታበየባቸው እንጂ፡፡
4.  ልብሱ የከበረ ዕንቍ የነበረ /ሕዝ.28፡13/፡፡ እንደዚህ ተብለው የተገለጡትም ለሳጥናኤል የተሰጡ መክሊቶች እንደኾኑ ግብጻዊው አባት አባ ታዋድሮስ ያዕቆብ ማላቲ ይህን የትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ በተረጎሙበት አንቀጽ ገልጠዉታል፡፡ በመኾኑም ለሳጥናኤል የተሰጠው መክሊት እንደ ማዕርጉ በጣም ብዙ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህን ብዙ መክሊቶች ለትዕቢት ስለተጠቀመባቸው መፈራረጃ ኾነዉበታል፡፡  
5.  እሳታዊ ተፈጥሮ፡- እንዲህ እንዲል፡- “አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፤ በተቀደሰውም በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ” /ሕዝ.28፡14/፡፡ ይኸውም ባይሰጠኝ ነው፤ እንደ ሌሎች መላእክት ባልፈጠር ነው ብሎ ምክንያት እንዳያመጣ ነው፡፡ ለዚህም በርሱ ማዕርግ የነበሩና አሁንም ያንን ቅድስናቸውን ይዘው የጸኑት ቅዱሳን መላእክት በመጨረሻው ቀን ይፈርዱበታል፤ ዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት ያላመኑትን አይሁድ እንደሚፈርዱባቸው ማለት ነው /ማቴ.19፡28/፡፡              
ነቢዩ ሕዝቅኤል ከተናገራቸው በተጨማሪ ሰይጣን፡-
v  ረቂቅ ነው፡፡ ነገር ግን ህልውና ከአካል ጋር አለው፡፡ ረቂቅነቱ ከእኛ አንጻር ነው፡፡ ዳግመኛም ውሱን ነው፡፡ መጠን አለው፡፡
v  ምንም እንኳን ዓቅሙና ክህሎቱ እንደ እግዚአብሔር ባይኾንም ከሰው ልጆች ግን እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡
v  እንደ ሰው አይራብም፤ አይጠማም፡፡ ልብስ፣ መጠለያ አይፈልግም፡፡
v  ምንም እንኳን በወንድ አንቀጽ ብንጠራውም ፆታ የለውም፡፡ በመኾኑም አይጋባም፤ አይዋለድም፡፡
v  እንደ ሌሎች መላእክት ከዝንጋዔ የራቀ፣ ባለ አእምሮ የኾነ፣ ዕውቀት ያለው ነው፡፡
v  -መዋቲ ነው (አይሞትም)፡፡ ይኸውም ከመኖር ወዳለመኖር አይሔድም ለማለት እንጂ ሞትስ ሕይወት ከኾነው ከእግዚአብሔር መለየት ነውና ሞቷል፡፡ 
v  ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ መውደቁም ይህን ነጻ ፈቃዱን ስለተጠቀመ ነው፡፡
የሳጥናኤል ውድቀት
ሳጥናኤል የወደቀው እግዚአብሔር እንዲወድቅ ብሎ አስቀድሞ ስለወሰነው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አንዱን ለመንግሥተ ሰማይ ሌላውንም ለምረረ ገሃነም የፈጠረው አንድም ፍጥረት የለም፡፡ የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ሐሳብ (ሳጥናኤልን ጨምሮ) መላእክትና ሰዎች በምግባር በእምነት ጸንተን መንግሥቱን እንድንወርስ ነው፡፡ ብንበድልም እንኳን፡- “በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን?... ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?” እንዲል /ሕዝ.18፡23/ ንስሐ ገብተን እንድንመለስ እንጂ እንዲሁ እንድንጠፋ አልፈጠረንም፡፡
በመኾኑም ሳጥናኤል፥ ሰይጣን ይኾን ዘንድ አስቀድሞ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይህን በማስመልከት ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል፡- “የኃጢአት ጠንሳሽና የክፋት አባቷ ዲያብሎስ ነው፡፡ ይህ ንግግርም የእኔ አይደለም፤ የጌታ እንጂ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ኃጢአትን የሠራው ዲያብሎስ ነው፤ ከርሱ በፊት የሠራ የለም፡፡ ኃጢአትን የሠራው ግን ኃጢአትን ይሠራ ዘንድ ስለተላከ አይደለም፡፡ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ እንዲኖረው ተደርጎ ስለተፈጠረ ወይም ደግሞ የኃጢአት ምንጭ እንዲኾን ተደርጎ ስለተፈጠረም አይደለም፡፡ እንዲህ ብለን ከተናገርንስ የኃጢአት ምንጯ የሳጥናኤል ፈጣሪ እግዚአብሔርን እናደርጓለን (ሎቱ ስብሐት)፡፡ ሲፈጠር መልካም ፍጥረት ነው፤ ሰይጣን የኾነውም ነጻ ፈቃዱን አለአግባብ ተጠቅሞ ነው፡፡ ሰይጣን የሚለው ስም ያገኘውም ከዚሁ ግብሩ ነው፡፡ የመላእክት አለቃ ነበር፤ በሐሜት ምክንያት ግን ዲያብሎስ ኾነ፡፡ እግዚአብሔርን ከሚያገለግሉ ቅዱሳን መላእክት ተለይቶም ዲያብሎስ ኾነ፤ ዲያብሎስ ማለት ተቃዋሚ ማለት ነውና፡፡ እግዚአብሔርም ሰይጣን ብሎ ትክክለኛ ስም ሰጠው፤ ሰይጣን ማለት ተቃዋሚ ማለት ነውና፡፡ ይህ ትምህርትም ከልቤ አንቅቼ የምናገረው አይደለም፤ ነቢዩ ሕዝቅኤል በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስለ ሰይጣን እየተመለከተ ያለቀሰው ለቅሶ ነው እንጂ፤ እንዲህ ሲል፡- ‘ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደምያ አንተ ነህ፡፡ በእግዚአብሔር ገነት በኤደን ነበርህ፡፡ … ከተፈጠርክበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ’ /ሕዝ.28፡12-15/፡፡ “በደል እስኪገኝብህ ድረስ” አለ፡፡ ይህም ማለት ዲያብሎስ በደል የመጣበት ከአፍኣ አይደለም፤ እርሱ ራሱ አመነጫት (ከራሱ አንቅቶ ወለዳት) እንጂ፡፡ ይህን ያስረዳ ዘንድ (እግዚአብሔር) እንዲህ አለው፡- ‘በውበትህ ምክንያት ልብህ ኮርቷል፡፡ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልኩህ’ /ሕዝ.28፡17/፡፡ ይህም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ከተናገረው ቃል ጋር የተስማማ ነው፤ እንዲህ ሲል፡- “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” /ሉቃ.10፡18፣ St. Cyril of Jerusalem; Catechetical Lectures; 2:4/፡፡” ስለዚህ ሳጥናኤል ሰይጣን የኾነው ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ነጻ ፈቃድ አለአግባብ በመጠቀሙ ነው፡፡
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስም የሳጥናኤል አወዳደቁ እንዴት እንደነበር እንዲህ ሲል ይነግረናል፡- “መላዕክት ዐዋቂ ኾነው ተፈጥሯልና እግዚአብሔር ያውቁት ዘንድ ፈጥሮ ተሰወራቸው፡፡ እርስ በርሳቸውም አንተ ምንድነህ? ከየት መጣህ? ተባባሉ፡፡ እነርሱም አመጣጤ ከየት እንደኾነ አላውቅም ብለው ተነጋገሩ፡፡ ታድያ ማን ፈጠረን? ብለውም ተጠያየቁ፡፡ ሳጥናኤልም ከርሱ በላይ ማንም እንደሌለ ባየ ጊዜ፡- ይህ ሕዝብ ፈጣሪውን አጥቶ ተጨንቋል፡፡ እኔ ፈጠርኋችሁ በማለትም ፈጣሪነትን በእጄ ልያዝ ብሎ አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረ እኔ ፈጠርኋችሁ አላቸው” /አባ ሠናይ ምስክር፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ገጽ 33/፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ሕዝቅኤል፡- “ልብህ ኰርቷል፤ አንተ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እግዚአብሔርም በባሕር መካከል እንዲቀመጥ እኔም ተቀምጫለሁ ብለሃልና” በማለት የተናገረው /ሕዝ.28፡2/፡፡
ሳጥናኤልን ከነበረበት ልዕልና የጣለው ይኸው ትዕቢቱ ነው፡፡ አዳምን ሲያታልለው እንኳን በዚህ ተመሳሳይ በኾነው ትዕቢት ነው፤ “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርሷ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትኾኑ፣ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” እንዲል /ዘፍ.2፡4-5/፡፡ 
ሳጥናኤል ትዕቢትን እንደዚህ እንዲያስባት ያደረገውና ያሰናከለው ወይም ያታለለው አካል አልነበረም፡፡ “ፈጠርኳችሁ” ብሎ ሲናገር ከራሱ ከልቡ አመንጭቶ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “(ሰይጣን) ሐሰትን በሚናገርበት ጊዜ ከራሱ አንቅቶ ይናገራል፤ ሐሰተኛ ነውና፤ የሐሰትም አባት ነውና” ያለውም ስለዚሁ ነው /ዮሐ.8፡44/፡፡
ሳጥናኤል ቢበድልም እግዚአብሔር ለንስሐ ጠርቶት ነበር፡፡
ንስሐ እንዲስማማቸው ኾነው የተፈጠሩት ፍጥረታት ሰዎችና መላእክት ናቸው፡፡ በመኾኑም ሳጥናኤል ንስሐ ይገባ ዘንድ ተጠይቆ እንደነበር ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በረቡዕ አክሲማሮሱ ላይ በስፋት ይገልጧል፡፡
·         እፈጥራለሁ ብሎ እሳቱን ቢነካ እንደተቃጠለና እግዚአብሔር ሐፍረቱን ሳይገልጥበት በአርምሞ እንደፈወሰው፤
·         ነገር ግን እግዚአብሔር አላወቀብኝም ብሎ ድጋሜ ሊፈጥር ሲል ድጋሜ እንደጮኸና እግዚአብሔርም ንስሐ ይገባ ዘንድ እንደጠየቀው፤
·         ሳጥናኤል ለአዳም ተብላ በተፈጠረችው በኤደን ገነት ሲቀና አይቶ ቸሩ እግዚአብሔር የሳጥናኤል መመለሱን እንጂ መውረዱን አይወድምና፡- “ይህችን ምድር ከሰማይ መርጠሃት እንደኾነ ብሰጥህ በወደድሁ” ብሎ እንደጠየቀው፤ ሳጥናኤል ግን ትዕቢተኛ ነውና፡- “የእኔ እጅ ምን ኾኖ ነው አንተ የምትሰጠኝ፡፡ ይህቺም ያቺም አያመልጡኝም፤ ገና ጐረቤቷን ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን መንበረ ስብሐትን እጨምራለሁ ብዬ አስባለሁ” እንዳለ፤ ጌታም፡- “ለአንተ ለፍጡሩ ሰማይን ምድርን አንድ ጊዜ ማየት አይቻልህም፡፡ ሰማይን የወደደ ምድርን አያገኛትም፤ ምድርንም የወደደ ሰማይን አያገኛትም” ሲለው ሸክላ ሳጥናኤል ዝም እንዳለ /ሮሜ.9፡20-21/ አስፍቶ አምልቶ ይነግረናል፡፡
በመኾኑም እግዚአብሔር ሳጥናኤል ይመለስ ዘንድ ብዙ ጊዜ ለምኖታል፡፡ ትዕቢቱን ትቶ ወደ ልቡ ይመለስ ዘንድ መክሮታል፡፡ ሳጥናኤል ግን “ብትምረኝ ደስ አይለኝም፤ ሠራዊቶችህ በድለዉኛልና፡፡ እኔን በእነዚያ ካሠለጠንከኝ እንደ ሰደቡኝ ሰድቤአቸው እንዳጐሳቆሉኝ አጐሳቁያቸው ከየዙፋናቸው ከየድንኳናቸው ጥያቸው ቢኾንም ባይኾንም ከዚያ በኋላ ነው እንጂ አለዚያስ አልቃጣውም አይደረግም” በማለት በትዕቢት ላይ ትዕቢት በዓመፅ ላይ ዓመፅ የቀጠለው ሳጥናኤል በመላእክተ ብርሃን ላይ ይታበይ ጀመር፡፡ ጭራሽንም የሚችለኝ የለም፤ በፊቴ መቆም የሚችል መልአከ ብርሃን የለም ማለት ጀመረ፡፡ ጦርነቱን ጀምሮም በኤረርና በራማ ያሉትን መላዕክተ ብርሃን ድል አደረጋቸው፡፡ በኢዮር ያሉ ያሉ መላዕክትም “ፈቃድህ ባይኾን ነውን” ብለው ወደ ጌታ ቢያመለክቱ የብርሃን ትእምርተ መስቀል ሲሰጣቸው ሳጥናኤልን ድል አድርገዉታል /ራእ.12፡7/፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እግዚአብሔር እንደማይመለስ ዐውቆ በሳጥናኤል ላይ ጽኑ መከራ ያመጣበት፡፡ በመኾኑም ስመ እግዚአብሔር በተጠራበት ኹሉ የሚርድ የሚንቀጠቀጥ እንዲኾን አደረገው፡፡ ዕውቀትን፣ ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ትዕግሥትን ነሳው፡፡ እርሱም ሲቻለው የማይምር ኾነ፤ ስሙም ሰይጣን ዲያብሎስ ጋኔን ተባለ፡፡
በመጨረሻም ጌታ ባዘዛቸው መሠረት መላእክተ ብርሃን እያዳፉት እያሽከረከሩት እያጋፉት ጣሉት፡፡ እርሱም እንደ ድንጋይ እየተንከባለለ እንደ ግተት እየተሽከረከረ ከክብሩ ከልዕልናው ወደቀ፡፡ “እውነት ነው ፈጥረኸናል” ያሉት አብረዉት እንጦርጦስ ወርደዋል፤ “እኛም እንፈጥራለን” ያሉት አብረው ወደ ምድር ወርደዋል (ዛሬ በምድር ላይ ሰውን ኹሉ ስተው ሲያስቱ የሚኖሩትም እነዚህ ናቸው)፤ “ፈጥሮን ይኾን?” ብለው የተጠራጠሩት ደግሞ በአየር ላይ ቀርተዋል (ዛሬ ነፍስ ከሥጋ ተለይታ ስትወጣ የጻድቃንን ነፍስ እያስደነገጡ የኀጥአንን ነፍስ እየቀጠቀጡ የሚኖሩ የአየር አጋንንት የሚባሉ እነዚህ ናቸው)፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም የዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላዕክት አለቃ ኾነ፤ ልዑል መንበርም ተባለ፡፡  
የዲያብሎስ ግብር
የዲያብሎስ ሥራ ምእመናንን እርሱ እንደወደቀው አወዳደቅ መጣል ነው፡፡ እንዲህ የሚያደርገውም እርሱ የሚጠቀም ኾኖ አይደለም፤ እንዲሁ ቅንአት እንጂ፡፡ ቅንአት ማለትም በሌላው ዕድልና ሀብት ማዘን ወይም መበሳጨት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ አርባዕቱን ወንጌል ሲተረጉምና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ሰው እንደኾነ በተናገረበት በመጀመሪያው ክፍል ላይ፡- “ሰይጣን እንዲሁ (ምንም ላይጠቀም) ሰዎች እንዲሞቱ አደረገ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ (ምንም ላይጠቀም) ሰዎችን አዳናቸው” ማለቱም ይህን በመረዳት ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ዲያብሎስ፡-
ü  ያለመኑት ሰዎች እግዚአብሔርን እንዳያውቁት ልቡናቸውን መሰወር (ማደንቆር)፤
ü  ዕለት ዕለት ቃሉ የሚነገራቸው ክርስቲያኖች የተነገራቸውን ቃል ፈጥነው እንዲረሱት (ዝንጋዔ እንዲያገኛቸው) ማድረግ /ማቴ.13፡4/፤
ü  ሐሰተኛ ወንድሞችን በመጠቀም ሐሰተኛ ሃይማኖት እንዲስፋፋ ማድረግ /2ኛ ቆሮ.11፡13-15/፤
ü  ክፋትን በተቀበሉት ሰዎች ልብ ውስጥ ማሳደር /ዮሐ.13፡2/፤
ü  በምእመናን መካከል ፍቅር አንድነት እንዲጠፋ ማድረግ /2ኛ ቆሮ.2፡10-11/፤
ü  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናይበት እይታ ማዛባት /2ኛ ቆሮ.11፡3/፤
ü  ምግባረ ብልሹ እንኾን ዘንድ መፈተን /1ኛ ቆሮ.7፡5/፤
ü  ምእመናንን መክሰስ /ራእ.12፡10/፡፡
ü  ዛሬ ጭራሽ በእርሱ ስም የሚያምኑና “የሰይጣን ኅብረት - Satan Church” በሚል ስም ተሰባስበው እርሱን የሚያመልኩ አሉ፡፡ “መጽሐፈ ሰይጣን - The Satanic Bible” የሚል የራሳቸው መጽሐፍም አላቸው፡፡
ü  ወዘተርፈ…
ሰይጣን እንደተፈረደበት
      አስቀድመን እንደተነጋገርነው አልመለስ ባለ ጊዜ ከቀደመ ክብሩ ተጥሏል፡፡ በሰዎች ላይ የነበረው ሥልጣንም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ ተሽሯል፡፡ ትምህርተ ሕቡአት የተባለ የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ፥ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ፥ ዲያብሎስ የተናገረውን ንግግር እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል፡- “አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን በእኔ ሥልጣን ተይዞ የነበረ ሥጋን ተዋሕዶ እኔን ድል የነሣኝ ይህ ማን ነው? እኔን ያጠፋኝ ዘንድ በእኔ ሥልጣን ተይዞ የነበረ ሥጋ የተሰጠው ይህ ማን ነው? ሥጋን የተዋሐደ ይህ ማን ነው? እርሱስ ሰማያዊ ኑሮ እኔ አላውቅ ብዬ ነው እንጂ /ዮሐ.3፡11-12/፡፡ መለወጥ ባለው ባሕርይ የተወለደ ይህ ማን ነው? እርሱስ የማይለወጥ ኑሮ እኔ አላውቅ ብዬ እንጂ /ሚልክ.3፡6/፡፡ ከእኔ ሕግ (ሕገ ዲያብሎስ) ልዩ የሚኾን ይህ ማን ነው? ከእኔ ወገን እየማረከ የሚወስድ ይህ ማን ነው? ነደ እሳት በሚኾን ኃይል ከእኔ ሞት ጋር የሚሰላለፍ ይህ ማን ነው? እኔን ጽልመትን ድል የነሣኝ ይህ ማን ነው? እርሱን በማየት እምወደው ሥራ የተከለከለብኝ ይህ እንግዳ ብርሃን ማን ነው? ኃጢአት ሳይሠራ የሞተ ይህ ማን ነው? በወገኖቼ ላይ እሠለጥን ዘንድ ያልተወኝ ይህ ማን ነው? አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን በእኔ ሥልጣን ተይዘው የነበሩ ነፍሳትን በክብር በግብር ወደላይ ያወጣል /ዮሐ.12፡7/፡፡ ሥጋ እንዳትፈርስ እንዳትበሰብስ የሚከለክል ይህ ብርሃን ማን ነው? መንካቱ መዳሰሱ የማይቻለኝ ይህ ማን ነው? ከተሰጠ የማይነሣ ካደረ የማይለይ ብርሃን የከበበው ይህ ማን ነው? ከዚህ ብርሃን ተለየሁ፡፡ ከወገኖቹ ከምእመናንም ተለየሁ፡ እንግዲህ ወዲህ ሠልጥኜ የምጎዳው የለኝም፡፡ እኔ አላውቅ ብዬ እንጂ እርሱስ እኔ ያሰቀልኩት ኢየሱስ ክርስቶስ ኑሮ፡፡ በግራ የነበረ አዳም ወደ ቀኝ ያለፈበት፣ ወደ ታች ወርዶ የነበረ አዳም ወደላይ የወጣበት ደሓራዊ ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ የኾነበት” /መጽሐፈ ቅዳሴ ንባቡና ትርጓሜው፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ 1988 ዓ.ም.፣ ገጽ 16-18/፡፡ እዚህ ጋር ልናስተውለው የሚገባን ግን ዲያብሎስ ከሥልጣኑ የተሻረው ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ በመስቀል ላይ ፍጻሜውን አገኘ እንጂ ጌታችንስ ካሣውን የጀመረው ገና ከማኅፀን አንሥቶ ነው፡፡
      ክርስቲያኖችም እርሱን ድል የምናደርግበት ኃይል ተቀብለናል፡፡ ይህን ኃይል ተጠቅሞ ዲያብሎስን መቃወምና ድል ማድረግ ግን የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ዛሬ ዲያብሎስ እኛን የሚያሳስተው የቀድሞ ኃይሉ ድል ስላልተደረገ ሳይኾን በራሳችን ስንፍና ነው፤ በቃላችን “እክሕደከ ሰይጣን” እያልን በተግባር ግን ከእርሱ ስለባስን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment