Tuesday, July 21, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ዐሥራ ሦስት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 14 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የእሑድ ሰዓተ መዓልት ፍጥረታት
ሀ) በአንደኛው ሰዓተ መዓልት፡- እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ “ብርሃን ይኹን” ብሎ ብርሃንን በስተምሥራቅ በኩል ፈጠረ፡፡ ከዚህም በኋላ መንፈስ ቅዱስ ዓለምን እንደ እንቁላል በክንፉ ዕቅፍ አድርጐ ለመላእክት ታያቸው፡፡ መላእክቱንም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፡- “ይህ ኹሉ ሰማይ የእኔ ነው፡፡ ታዲያ ከቤቴ ማን አገባችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ?” መላእከቱም፡- “አቤቱ ከግሩማን በላይ ያለህ ግሩም አንተ ነህ፡፡ በዚህን ያህል ድንጋፄ ያራድከን ያንቀጠቀጥከን እናውቅህ ዘንድ አንተ ማን ነህ?” አሉት፡፡ መንፈስ ቅዱስም “ሰማይን፣ ምድርን፣ እናንተንም ለፈጠረ ለአብ ሕይወቱ ነኝ” አላቸው /ኄኖክ.13፡21-22/፡፡ መላእክትም “አቤቱ ጌታችን የፈጠረንንስ፣ ያመጣንንስ ከቤትህስ ያገባንን አንተ ታውቃለህ እንጂ እኛ ምን እናውቃለን” ብለው ፈጣሪነቱ የባሕርዩ እንደኾነ አመኑለት፤ መሰከሩለት፡፡
ሳጥናኤልም መላእክትና መንፈስ ቅዱስ ሲነጋገሩ ቢሰማ ደነገጠ፤ ሐሳቡ ከንቱ ስለኾነበትም አፈረ /ኢሳ.14፡12-16/፡፡ ወዲያውም ያ በምሥራቅ የተፈጠረ ብርሃን እንደ ምንጭ እየፈሰሰ እንደ ጐርፍ እየጐረፈ ደርሶ አጥለቀለቃቸው፤ ዋጣቸው፡፡ ብርሃኑ የመጣው እግዚአብሔር ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ አንዲቱ ማለትም እሳቲቱን ብርሃን ውለጂ ብሎ ሲያዝዛት ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ብርሃኑን መዓልት ብሎ ጠራው፡፡ ከዚያ በፊት ተፈጥሮ የነበረው ጨለማውን ደግሞ ሌሊት ብሎ ጠራው /ዘፍ.1፡5-6/፡፡ በዚሁም የብርሃንን ሥራና የጨለማ ሥራ ለይተን እንኖር ዘንድ ሲያስተምረን ነው፡፡

ሥላሴ እስከ አሁን ፍጥረታትን ሲፈጥሩ በአርምሞ ነበር፡፡ ብርሃንን ሲፈጥሩ ግን “ይኹን” ብለው ድምጽ አሰምተው (በነቢብ - በመናገር) ነው፡፡ ይኸውም ሰማዕያን (የሚሰሙ) መላእክት ስላሉ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግን የሚሰማ የሚያደምጥ ፍጥረት አልነበረም፡፡
እግዚአብሔር አስቀድሞ ጨለማን ፈጥሮ፥ ቀጥሎም ብርሃንን መፍጠሩ ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም፡-  
v  ጨለማ የዚህ ዓለም አምሳል ነው፤ ብርሃን ደግሞ የወዲያኛው ዓለም፡፡ በዚህ ዓለም ሕሊናን የሚያደነዝዝ፣ ልቡናን የሚያናውዝ ሥራ ይሠራባታል፡፡ የወዲያኛዋ ዓለም ግን ስብሐተ እግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብባት የጽድቅ የብርሃን ከተማ ናት፡፡
v  ጨለማ የኦሪት አምሳል ነው፤ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በጨለማ ነበርንና፡፡ ብርሃን ደግሞ የወንጌል፤ በወንጌል ጽድቅ የምንሠራበት ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ብርሃን ወጥቶልናልና /ኢሳ.9፡2/፡፡
v  ጨለማ ያለማወቅ አምሳል ነው፤ ብርሃን ደግሞ የማወቅ፡፡
v  ጨለማ የገሃነም አምሳል ሲኾን ብርሃንም የመንግሥተ ሰማያት አምሳል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መንግሥተ ሰማያትን የኹላችንንም እናት እንደኾነች ገልጦ /ገላ.4፡26/፥ ጨምሮም “ኹላችሁም የብርሃን ልጆች ናችሁ” ማለቱ ይህን የሚያስረዳ ነው /1ኛ ተሰሎ.5፡5፣ መጽሐፈ  አክሲማሮስ፣ ገጽ 39-40/፡፡
v  ከዚህም በተጨማሪ በፊት የሚያልፈውን ይህን ዓለም አውርሶ በኋላ የማያልፈውን መንግሥተ ሰማያትን እንደሚያወርሰን፤ በፊት የምታልፍ ኦሪትን ሠርቶ በኋላ የማታልፈውን ወንጌል እንደሚሠራልን፤ በፊት መከራውን አምጥቶ በኋላ ጸጋውን ክብሩን እንደሚሰጠን ለማሳየት አስቀድሞ ጨለማን ፈጥሮ ከዚያም ብርሃንን ፈጠረ /የኦሪት ዘልደት ትርጓሜ፣ ገጽ 8/፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች እናስተውል! ይህ ብርሃን ከፀሐይ የተገኘ ብርሃን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፀሐይ የምትፈጠረው ገና በአራተኛው ቀን ማለትም ረቡዕ ላይ ነውና፡፡ ይህ ብርሃን በመጀመሪያው ቀን ከተፈጠረው እሳት ተጠንፍፎ (ተለይቶ) የመጣ ነው፡፡ ዓላማውም በጥልቁ ላይ የነበረውን ጨለማ ማስወገድ (መልክ ማስያዝ) ነው፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍን ሲተረጉም ይህን ይበልጥ ሲያብራራው፡- “ይህ ብርሃን እንዲህ ነው ብለን ልንገልጸው የማንችል፥ ግን ደግሞ እስራኤላውያንን በሌሊት ሲመራቸው እንደነበረው ዓይነት ብርሃን፤ በአራተኛው ቀን እንደተፈጠረችው ፀሐይ በቦታ የማይታጠርና ጠፈር ደፈር የማይጋርደው ብርሃን ነው” ይልና፤ ቀጥሎም፡- “ይህ ብርሃን ከሦስተኛው ቀን በኋላ ለሚፈጠሩ ፍጥረታት ሕይወታቸው ነው፡፡ ከሦስተኛው ቀን (ከማክሰኞ) በኋላ በምድር የሚፈጠሩትን ፍጥረታት ስንመለከት በብርሃንና በውኃ የተጠጉ ናቸውና” ይላል /የኦሪት ዘፍጥረት ትርጓሜ ገጽ 79-80/፡፡ በርግጥም እነዚህ ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት ስንመለከት ያለ ውኃና ብርሃን ሙታን ናቸው፡፡ ይህም በቅጥነተ ሕሊና ካስተዋልነው ፍጥረት ኹሉ ያለ ጽድቅ ፀሐይ፣ ያለ ሕይወት ውኃ ክርስቶስ ሕይወት እንደሌለው የሚያስገነዝብ ነው፡፡
“ብርሃን መልካም እንደኾነ አየ” የሚል አገላለጽ አለ /ዘፍ.1፡4/፡፡ ይህ ማለት ግን እኛ  አንድን ነገር ሠርተን መልካም መኾኑን አረጋግጠን እንደምንደነቀው ዓይነት እግዚአብሔር አዲስ ነገርን ስለፈጠረ ተደነቀ፤ ተደመመ ለማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ፍጥረታትን መፍጠር ፈቃዱ ስለነበረ ያንን በማድረጉ ተደሰተ ለማለት ነው፡፡ አሁንም ተደሰተ ሲባል እኛ እንዲገባን በእኛ አነጋገር መናገር እንጂ እግዚአብሔር እንደ እኛ ሐዘንና ደስታ የሚፈራረቅበት፣ አንዳንድ ጊዜ ፊቱ የሚቋጠር በሌላ ጊዜ ደግሞ ፈገግ የሚል ኾኖ አይደለም /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ የኦሪት ዘፍጥረት ትርጓሜ፣ ድርሳን 3/፡፡ ከዚህ መረዳት እንደምንችለው እግዚአብሔር አንድም ፍጥረት (ሳጥናኤልን ጨምሮ) ክፉ አድርጎ የፈጠረው እንደሌለ ነው፡፡     
ብርሃኑ ጨለማውን አስወገደው ማለት ግን ከመኖር ወደ አለመኖር ወሰደው ለማለት እንዳልኾነ ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ቃሉ እንደሚል ብርሃንና ጨለማ የየራሳቸው ድንበር ተበጀላቸው ማለት ነው እንጂ፡፡ ድንበሩም እኛ እንደምናውቀው ዓይነት አጥር ቅጥር ሳይኾን ሰዓት ነው እንጂ፡፡
በሌላ መልኩ ብርሃኑ መጥቶ ጨለማውን እንዳስወገደው አይተናል፡፡ ይህም በቀጥታ ከነገረ ሥጋዌ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሰው በበደሉ ምክንያት ጨለማ ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ፡- “ለሰው ኹሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” እንዳለ /ዮሐ.1፡9/ ብርሃን ክርስቶስ በሰው ልጆች ላይ የነበረውን ድንቁርና እንዳራቀ የሚያስረዳ ነው፡፡
ለ) በኹለተኛው ሰዓተ መዓልት፡- መንፈስ ቅዱስ ጽርሐ አርያምን፣ ሰማይ ውዱድን፣ መንበረ ስብሐትን መሠረቷን ኹለንተናዋን ቀብቶ አከበራት፤ ንጽሕት ብርህት አደረጋት፡፡ የሚያመሰግኑ መላእክትም አሰፈረባት፡፡
ሐ) በሦስተኛው ሰዓተ መዓልት፡- ኢዮርን ቀባት፤ ቀደሳት፤ በውስጧ አስፍሯቸው የነበሩትን መላእክትንም ቀባቸው፡፡ በሰባተኛው ሰዓተ መዓልት ራማን፤ በዐሥረኛው ሰዓተ መዓልት ደግሞ ኤረርን ቀባቸው፡፡
“መላእክት ተቀቡ ሲባል ምን ማለት ነው?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ መላእክት ተቀቡ ሲባል ከዝንጋዔ የራቁ፣ ባለ አእምሮ የኾኑ፣ ዕውቀት ያላቸው፣ ይዋሄንና ትዕግሥትን ገንዘብ ያደረጉ፣ ለዘለዓለም የማይነጥፍና የማያቋርጥ ይልቁንም ዘወትር እንደ ጅረት ውኃ የሚወርድ ምስጋና አፍልቆ ሰጣቸው ማለት ነው /ሥነ ፍጥረት፣ በቀሲስ ስንታየኁና በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የተዘጋጀ፣ ገጽ 34/፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በየሰማያቱ ያሉትን መላእክት ሲቀባቸው ፍጡራን እንደኾኑ እንዲያውቁ የብርሃን መጐናጸፊያ አጐናጸፋቸው፡፡(መጐናጸፊያ ከአካል በላይ እንደሚታይ ኹሉ እግዚአብሔርም ከነርሱ በላይ መኖሩን እንዲያውቁ መጐናጸፊያ አጐናጸፋቸው ተባለ፡፡) “ተገዢዎች ናችሁ” ሲላቸው የብርሃን ዝናር አስታጠቃቸው፡፡ “ለተልእኮ መውረድ መውጣት አለባችሁ” ሲላቸው የብርሃን ጫማ አጫማቸው፡፡ “ሠራዊቶቼ ናችሁ” ሲላቸው ማኅተመ መስቀል ያለበት የብርሃን ዘንግ (በትር) አስያዛቸው፡፡ “የብርሃን ዘውድ የጸጋ ክብር የጸጋ መንግሥት አነግሣችኋለሁ” ሲል የብርሃን አክሊል ደፋላቸው፡፡ “እኔን ማየት በወደዳችሁ ቀን ያለ ምክንያት ልታዩኝ አይቻላችሁም” ሲል የብርሃን መነጽር (መስታወት) አደረገላቸው /መጽሐፈ አክሲማሮስ፣ ገጽ 43/፡፡
ኹሉንም ቀብቶ ከመንበሩ በክብርና በልዕልና በይባቤ መላእክት ተቀመጠ፡፡ ወዲያውም ከነገደ ኪሩቤል ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳ ያላቸውን፤ ከነገደ ሱራፍኤል ገጸ ንስርና ገጸ ላሕም ያላቸውን ወስዶ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት በላይ ከሰማይ ውዱድ በታች በአራቱ ማዕዘን በምሥራቅ በምዕራብ፣ በሰሜን በደቡብ አቆማቸው፡፡ ያቆማቸውም ጀርባቸውን ወደ ውስጥ ፊታቸውን ወደ ውጪ አድርጐ ነው፡፡ በመኾኑም ፊት ለፊት አይተያዩም /ራእ.4፡6-9/፡፡
ዓይናቸው እንደ ነብር ዥንጉርጉር ነው፡፡ ከእግር እስከ ራሳቸው እንደ መስታወት ልሙጥ ነው፡፡ ከወገባቸው በላይ ዐሥራ ስድስት ከወገባቸው በታች ዐራት ናቸው፡፡ ክንፋቸውም ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ይኾናል /ሕዝ.1፡27-28/፡፡
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ከሠራዊተ ሩፋኤል ሃያ አራት ሊቃናትን መርጦ በመንበረ ስብሐት በመጋረጃዋ ውስጥ ዙርያዋን ክንፍ ለክንፍ ገጥሞ አቁሟቸዋል /ሕዝ.1፡11-12/፡፡ እነዚህንም ስማቸው ካህናተ ሰማይ አላቸው፡፡ የእሳት የወርቅ ጽና አስያዛቸው፤ ጳዝዮን የሚባል እሳታዊ የኾነ የዕንቍ አክሊል ደፋላቸው፤ ማኅተሙ መስቀል የኾነ የብርሃን ዘንግ አስያዛቸው፤ ኅብረ መብረቅ የመሰለ የብርሃን ካባ አለበሳቸው /ራእ.4፡4-6/፡፡ እነዚህ ካህናተ ሰማይ በአንድ ላይ ባጠኑ ጊዜ ከማዕጠንታቸው የሚወጣው ጢስ መልኩ መብረቅ፣ ድምጹ ነጐድጓድ፣ መዓዛው መልካም የኾነ ነው /ራእ.8፡3-5/፡፡
“ካህናተ ሰማይ የሚያጥኑት ምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ የቆጵረሱ ሊቀ ጳጳስ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ መጽሐፉ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡-“የጻድቃን ጸሎት፤ የሰማዕታት ገድል፤ የደጋግ ሰዎች ምግባር ነው” /ገጽ 51/፡፡
“የኪሩቤልና የካህናተ ሰማይ አቋቋማቸው እንደምን ነው?” ቢሉ ኪሩቤል በቀኝ እንደ ቀሳውስት፤ ሱራፌል እንደ ዲያቆናት በግራ፣ ካህናተ ሰማይ ደግሞ ዝቅ ብለው ክንፍ ለክንፍ ገጥመው ቁመው ይኖራሉ፡፡
*** “ማታም ኾነ ጧትም ኾነ” የሚል አገላለጽ አለ፡፡ ይኸውም ሙሴ ለጊዜው የሚጽፍላቸው ለእስራኤላውያን ስለኾ ነው፡፡ እነዚህ እስራኤላውያንም አንድን ቀን የሚጀምሩት ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ስለኾነ ነው፡፡
እመቤታችንና ዕለተ እሑድ
አስቀድመን እንደተናገርን አራቱ ባሕርያተ ሥጋ የተባሉት እሳት፣ ውኃ፣ ነፋስና መሬት ለፍጥረት ኹሉ መገኛዎች ናቸው፤ ከመላእክትና ከነፍስ በቀር፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም፥ ይህንን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣ ያለ ርሱ ቃልነት ያለ ርሱ ህልውና ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፣ አምጻኤ ዓለማት ፈጣሬ ዓለማት፤ በአጭር ቃል አሥራወ ፍጥረት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተገኝቷልና በዕለተ እሑድ ትመሰላለች /ዮሐ.1፡3፣ ውዳሴ ማርያም ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው፣ ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ 15-17/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount