Pages

Tuesday, August 18, 2015

መንፈሳዊ አገልግሎት



በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 12 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አገልግሎት የሚለው ቃል ገልገለ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ገልገለ (አገለገለ) ማለት ተገዛ፣ ታዘዘ፣ ዐገዘ፣ ረዳ፣ ጠቀመ፣ ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ጌታውን  ደስ አሰኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎት ማለት መታዘዝ፣ መገዛት፣ መርዳት፣ መጥቀም…ማለት ይሆናል፡፡  ማንኛውም ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥራ አገልግሎት ነው፡፡ ለመንግሥት የሚሠራ የመንግሥት አገልጋይ፣ ለግለሰብ የሚሠራ የግለሰብ አገልጋይ፣ ለእግዚአብሔርም የሚሠራ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ አገልጋዮችን በተለያየ ስያሜ ጠርቷል፡፡ ምንም አይነት መብት በራሱ ላይ የሌለውንና በጌታው ሐሳብ ፍፁም አዳሪ የሆነውን ተገዢ ባሪያ በማለት ገልፆታል፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ‘ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ’ በማለት የተናረው ይህን ያጠናክራል፡፡ (1ቆሮ. 9÷19) አብሮት የሚያገለግለውን ቲኪቆስንም  ‘በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ’ በማለት ጠርቶታል፡፡ (ቁላ 4፡7) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ቅዱሳን ባሪያዎች ሁኑ በማለት አገልግሎታችን በፍፁም መገዛት እንዲሆን ይመክረናል፡፡ (1ጴጥ. 2‘፡16) በራሱ ላይ ሙሉ ነፃነት ያለውን አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱስ ሠራተኛ ይለዋል፡፡ (ሉቃ 10፡2፣ ቁላ 4፡11፣ 2ጴጥ 1፡8) ይህ ከባሪያ ይልቅ በራሱ ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው ነው፡፡ ከፈለገ አለማገልገል ይችላል፡፡ በባሪያና በሠራተኛ መካከል ነፃነቱ መካከለኛ የሆነው ደግሞ ብላቴና፣ ሎሌ ተብሎ የተጠራው ነው፡፡

መንፈሳዊ አገልግሎት የምንለው የእግዚአብሔር የሆነውንና መንፈሳዊ ዓላማን መሠረት በማድረግ የሚገለገለውን ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎትን ከሌሎች አገልግሎቶች/ሥራዎች የሚለዩት በርካታ ጠባያት አሉ፡፡ ትልቁና መሠረታዊው ልዩነት ዓላማው ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የመንፈሳውያን ሰዎችና የሰማያውያን መላእክት ረቂቅ ኅብረትና አንድነት የሚገለፅበት በማይታይ ፀጋ ወደ ክርስቶስ በእውነትና በፍቅር የሚያሳድግ (ኤፌ 4፡15) የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሥራ ነውና ልዩ ነው፡፡ አገልግሎትን ስንተረጉም ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ጌታውን ደስ ማሰኘት ነው ካልን መንፈሳዊ አገልግሎትም ጌታው አንድ እግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ማንኛውንም ሥራ መሥራት ነው፡፡ (ሮሜ.12፡1)
እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የሚቻለው ደግሞ በዕምነት ብቻ በመሆኑ (ዕብ. 11፡6) መንፈሳዊ አገልግሎት የመታመን ሥራ ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ማመንና መታመን ማለት እንደመሆኑ አምላክን አምነን የምንታመነው በመንፈሳዊ አገልግሎት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
መንፈሳዊ አገልጋይ ማነው?
ፍጥረታት ሁሉ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ቅድስት ሥላሴ አንዱንም ፍጥረት ካለዓላማ እንዲሁ በዘፈቀደ አልፈጠሩምና ይልቁንስ አበው እንዳስተማሩት ሰውና መላእክትን እንዲያመሰግኑ ሌሎቹን ፍጥረታት ደግሞ ለአንክሮ፣ ለተዘክሮ፣ ለምስክርነት ፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ ላያገለግል የተፈጠረ ፍጥረት የለም፡፡ ካልእ ፍጥረታት የሰው ልጅ አገልግሎቱን በዘነጋ  ጊዜ ስለ አምላክ እየመሰከሩ ሰውን ወደተፈጠረበት ዓላማ (አገልግሎት) ለመመለስ በመጣር አገልግለዋል፡፡ የበለዓም አህያ (ዘፍ 22) እና  የቢታንያ ድንጋዮች (ሉቃ 19) ለዚህ ምስክሮች ናቸው፡፡
ስለ ቅዱሳን መላእክት መንፈሳዊ አገልጋይነት በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ቦታ ተጽፏል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ 1 ቁጥር 14 ላይ ‘ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?’ በማለት ከርቀታቸው (ረቂቅነታቸው) የተነሳ መናፍስት ብሎ የሚያገለግሉ ያላቸው መላእክትን ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊትም ‘መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል’ በማለት (መዝ 103፡4) ይህንኑ አጠናክሯል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስና ነባቤ መለኮት ዮሐንስም የምስጋና አገልግሎታቸውን በራእይ ተመልክተው ጽፈውታል፡፡ (ኢሳ. 6፡1-6፣ ራዕ. 4፡5-8)

“እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ” ዘፀ. 7፡16

እግዚአብሔር አምላክ እስራኤላውያንን ከዘመናት የግብፅ ስደት ወደ ምድረ ርስት የመመለሻው ወቅት በደረሰ ጊዜ በሙሴ በኩል ፈርኦንን ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ (ዘፀ 7፡16) ብሎታል፡፡ የእስራኤላውያን ከስደት መመለስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከስደት የመፈታታቸው ዓላማ አገልግሎት ነው፡፡ ከስደት ተመልሶ እግዚአብሔርን የማያገለግል በስደት ቢኖር ይሻለዋል፡፡ ‘ እንዲያገለግሉኝ’ ብሏልና፡፡ በተመሳሳይ የሰው ልጅ የመፈጠሩ ዓላማ ሃይማኖት እንደመሆኑና ሃይማኖት ደግሞ የማመንና የመታመን ጉዳይ በመሆኑ፣ እንደዚሁም መታመን በመንፈሳዊ አገልግሎት ስለሆነ እግዚአብሔርን የማያገለግል ሰው የመፈጠሩን ዓላማ ስቷልና ባይፈጠር ይሻለዋል፡፡ እዚህ ጋ መንፈሳዊ አገልግሎት ስንል በጠበበው ትርጉሙ  የተለመዱትን የክህነት፣ የሰ/ት/ቤት ወይም የመንፈሳዊ ማኅበራትን አገልግሎት ብቻ ማለታችን አይደለም፤ መሠረታዊ የክርስትና ተግባራትንና የምስጋና ሕይወትን አጠቃለልን እንጂ፡፡ በዚህ አረዳድ ሰው ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስም ሰውን የእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ ብሎ የጠራው፡፡ (1ቆሮ. 3፡16)
ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሉቃ 6፡38 ላይ ጌታችን ‘ስጡ ይሰጣችሁማል’ ያለውን ቃል ሲተረጉመው መንፈሳዊ አገልግሎትን የተመለከተ ቃል ስለመሆኑ መስክሯል፡፡ ጌታ ስጡ ማለቱ አገልግሉ ማለቱ ነው፡፡ የምድሩን ትታችሁ፣ ጊዜያችሁን ሰውታችሁ፣ ጉልበታችሁን ገብራችሁ፣ ዕውቀታችሁን አፍሳችሁ፣ ገንዘባችሁን በጅታችሁ ብታገለግሉ እኔ ደግሞ በጸጋ ላይ ጸጋ፣ በበረከት ላይ በረከት፣ በሕይወት ላይ ቅድስናን  እሰጣችኋለሁ ሲል ነው ይላል ሊቁ፡፡
የመንፈሳዊ አገልግሎት መለያዎች

ምንም እንኳን አንድ ሰው ቅዳሴ፣ ምስጋና፣ ምስክርነት እና የመሳሰሉትን ከኹላዊት ቤተክርስቲያን የተገኙ ሁሉንም የሚያሳትፉ ኹላዊ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ግዴታው ቢሆንም በሰንበት ት/ቤቶች፣ ቤተክርስቲያን ማኅበራት ወይም በተለያዩ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች ለማገልገል የሚያስብ ከሆነ የመንፈሳዊ አገልግሎት የተለዩ ጠባያትን አጥርቶ ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ አገልግሎቱ እንደማንኛውም ዓለማዊ ሥራ ከመሆኑም ባሻገር በረከት የተለየው ድካም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ነጥቦች በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ  ላሉ አገልጋዮችም ሆነ ለማገልገል ለሚሹ አስፈላጊ ናቸው፡፡
1.  በእምነት (በመንፈስ) ማገልገል

መንፈሳዊ አገልግሎት በምድራዊ አመክንዮ (logic) ያልተሳሰረ መሠረቱም ጉልላቱም ረቂቅ እምነት የሆነ የአምልኮ ዘርፍ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ሳያምኑ መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይቻልም፡፡ ዕምነት የመጀመሪያው አንድ አገልጋይ ሊያሟላ የሚገባው ሰማያዊ የመንፈሳዊ አገልግሎት ስንቅ ነው፡፡ ሳያምኑ ማገልገል ድካም ነው፡፡ የመንፈስ ዝለትንም ያመጣል፡፡ አንድ ጥሩ እምነት ያለው አገልጋይ ከአላስፈላጊ ጭንቀት  ነፃ ስለሆነና መንፈስ ቅዱስን የአገልግሎቱ መሪ ስለሚያደርግ የሚያገለግለው በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደለም፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱ የረቀቀ ነው፡፡ ምናልባትም ከአእምሮ በላይ ሆኖ በምን ችሎታ ይህን አደረገው? በየትኛው ጊዜው ሠራው ብለን የምንደነቅበት ነው፡፡
ብዙ አገልጋዮች ትልቁ ችግራቸው አገልግሎታቸው በአእምሯዊ ቀመር (calculation) ብቻ የተሰላ መሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በፀሎት የሚጠይቁ እንኳን ጥቂት ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው ግዙፍ ግዙፉን እንጂ ረቂቁን ርካታና ፀጋ አያገኙም፡፡ ቀመራዊ ስለሆኑና የእምነት መነፅር ስለሌላቸው የፀበል ይዘት እንደማንኛውም ውሃ የሃይድሮጅን እና የኦክስጅን ውሕድ እንጂ ያለበት መንፈሰ እግዚአብሔር አይረዳቸውም፡፡ ምክንያቱም ምድራዊ ቤተሙከራን እንጂ መንፈሳዊነትን አያውቁም፡፡ መናፍቃኑ ስንሳለም አይተው ድንጋይን ይስማሉ (ይቅር ይበላቸውና) እንደሚሉን መንፈሳዊነት ጎድሏቸው በመንፈስ የማያገለግሉት እነዚህ አገልጋዮችም ‘እግዚአብሔር በጎደለው ይሙላ’ የሚልን ንግግር የማያውቁ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሉ ነገር በእነርሱ ዝግጅትና ድካም ብቻ የሚሳካ ይመስላቸዋል፡፡ መዝሙር ላይ ተመስጦ የሚባል ነገር አያውቃቸውም፡፡ የማን ድምፅ ወጣ? የማን ወረደ? እንዴት ልራመድ  እንዴት ላጨብጭብና ሰውን ላስደስተው?  ከበሮ አመታቴ ያምር ይሆን ሰው ደስ ብሎት ይሆን? በሚሉና በመሳሰሉት ሐሳቦች ከመጠን በላይ ስለሚዋጡ በመዝሙር ተመስጠው አያውቁም፡፡ ግን ደግሞ የቅዱስ ያሬድን የመዝሙር ተመስጦ ታሪክ በደንብ ያውቁታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዐፄ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር ከመመሰጡ የተነሳ ምድራዊን ነገር ሁሉ፣ የራሱንም ሥጋ ጭምር ረስቶ በሕሊናው ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ ከመላእክት ጋር  ያመሰግን ነበር፡፡ እሱ ይቅርና ንጉሡም ተመስጠው በጦር እስኪወጉት ድረስ በመንፈስ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ንጉሡ በተመስጦ ሲንቀሳቀሱ የያዙትን ጦር እንደመቋሚያ እያንቀሳቀሱ እግሩን ድንገት ቢወጉትም መወጋቱ እንኳን እርሱን ከተመስጦው የመመለስ ኃይል አልነበረውም፡፡ በኋላ ዝማሬያቸውን ጨርሰው ዝቅ ቢሉ ምድር ላይ ደም አዩና ነገሩን በዛ ተረዱ፡፡ በእርግጥ ጀማሪ አገልጋይ ሁሉ እንዲህ መሆን አለበት አይባልም፡፡  እየዘመርን ጉንዳን ስትበላን የምንተረማመስ ሰዎች ጦርን ያህል የቻሉትን ቅዱሳንን እንሁን ማለትም ተገቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን እነሱን በመምሰል የተመስጦን ሕይወት፣ የእምነትን ብርታት የመንፈሳዊነትን መዐዛ ለሰውነታችን ማለማመድ የግድ ነው፡፡ ጉባኤ ሲዘረጋ፣ ተውኔት ሲሠራ፣ ሲዘመር እና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ሲገለገል ቢያንስ ጸሎት ያስፈልጋል፡፡
ከመንፈሳዊነት የራቀ የጉባኤ ድምቀትን አምጥቶ ሰውን ለማስደሰት መጣር ይሁዳን መሆን ነው፡፡ መጀመሪያ እግዚአብሔርን ማስደሰት ይቀድማል፡፡ እርሱን ደግሞ ካለ እምነትና መንፈሳዊነት ማስደሰት አይቻልም፡፡ (ዕብ. 11፡6) እግዚአብሔርን ስናስደስት የእርሱ የሆኑት ሁሉ ይደሰቱብናል፡፡ ለዚህ ነው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ‘መንፈሳዊነት ከተለየው አገልግሎት አገልግሎት የሌለው መንፈሳዊነት ይሻላል’ ብለው የተናገሩት፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በተመስጦ ከሚታወቁትና በመንፈሳዊነታቸው ከሚመሰገኑት አገልጋዮች አንዱ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት በአታቸው ውስጥ ሆነው ሥራቸውን እየሠሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በሩ ይንኳኴል፡፡ ሄደው ሲከፍቱ አንድ መነኩሴ “አባ ቅርጫት እንዲሰጡኝ ነው የመጣሁት” ይላቸዋል፡፡ አባ ዮሐንስም በተመስጦ ውስጥ ስለነበሩ ቅርጫቱን ሊሰጡት ወደ ውስጥ ገቡና ዘንግተውት ያቋረጡትን ምስጋና ቀጠሉ፡፡ በር ላይ የቆመው መነኩሴ ቢቆዩበት መልሶ አንኳኳ፡፡ አባም በሩን ከፈቱና ምን ነበር አሉት፡፡ መነኩሴውም አባ ቅርጫት ብዬዎት ነበርኮ አላቸው፡፡ ነገር ግን አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ ውስጥ ሲገቡ እንደገና ወደ ተመስጦአቸው ተመለሱ፡፡ መነኩሴው ሲቆዩበት እንደገና አንኳኳ፡፡ አባ ዮሐንስ በሩን ከፈቱና “ምን ነበር?” አሉት፡፡ መነኩሴው ጉዳዩን መልሶ ቢያስታውሳቸው አባ ዮሐንስ እጁን አፈፍ አድርገው ወደ በዓታቸው አስገቡትና “ና የፈለግከውን መርጠህ ውሰድ፡፡ እኔ ለእንደዚህ አይነቱ ጊዜ የለኝም” አሉት፡፡
አንድ መንፈሳዊ አገልጋይን በመንፈስ እንዳያገለግል  ዘወትር የሚያንኳኩበት ጉዳዮች አሉት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ ቤተሰባዊ፣ ኅብረተሰባዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች የሥጋ ፍላጎት፣ ወዘተ…ዘወትር በጭንቀት እንጂ በመንፈስ እንዳያገለግል ያንኳኩበታል፡፡ በዚህን ጊዜ እንደ አባ ዮሐንስ ሐጺር ፈፅሞ የመርሳት የብቃት ደረጃ ላይ ባይደርስ እንኳን በመንፈሳዊነትና በፀሎት ማሸነፍ መቻል ይጠበቅበታል፡፡
መንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ መሆን አለበት ስንል ሌላው መርሳት የሌለብን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ‘ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት’ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ (1ቆሮ 14፡40) እንደ ቤተክርስቲያን ሕግና እንደ እግዚብሔር ቃል ማገልገላችንን መመርመር ያስፈልጋል፡፡

2.  ሰማያዊ ዋጋን አስቦ ማገልገል

አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ማንኛውንም ምድራዊ ሽልማት  አስቦ ማገልገል ከጀመረ ምድራዊውን ዋጋ ሲያጣ አገልግሎቱ ይቆማል፡፡ እግዚአብሔርን  ሳይሆን እገሌን ብሎ የሚመጣ እገሌ ሲጠፋ ወይም ሲጣላው አገልግሎቱን ያበቃል፡፡ እግዚአብሔርን ብሎ የመጣ ግን ቢጣላና ቢሰደብ እንኳን ቢደበደብና ቢገደል እንኳን ‘ስለ ክርስቶስ ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ’ የሚለውን ቅዱስ መፅናኛ ያስባል፡፡ (1ጴጥ. 4፡14) ሰማያዊ ዋጋን አስቦ የመጣ ሰው ጊዜና ነገሮች ሲመቻቹለት ሳይሆን አመቻችቶ ያገለግላል፡፡ ኑሮው ሲሞላለት፣ ሀብት ሲሰፋለት፣ ዘመድ ሲበዛለት ጊዜን ለሰጠ ጌታ ጊዜ አጣሁ  ብሎ አይቀርም፡፡ የነበረው ከሆነም ቤቱ ሲቀዘቅዝ፣ ድህነት ሲያንቀው፣ ወዳጅ ዘመን ሲያጣ ተማሮ አይጠፋም፡፡ የምድራዊ ሁኔታዎች መቀያየር ከአገልግሎት አይለየውም፡፡ ይልቁንስ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል? መከራ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት ወይስ ራብ፣ ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን? በማለት ፀንቶ ይዘምራል፡፡ (ሮሜ 8፡35)  ሰማያዊ ዋጋን የሚያስብ አገልጋይ አይበረግግም፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የመንግሥት መለወጥ፣ የፖሊሲ መቀየር እና ሌሎች ምድራዊ ነገሮች አያስደነግጡትም፡፡ ሁሌም ፅኑዕ ነው፡፡ የፅናቱ መጠን ይደንቃል፡፡ የብርታቱም ልክ ይገርማል፡፡ መመካቱም በእግዚአብሔር ነው፡፡
የይታይልኝ አመል የለበትም፡፡ ሰው አየው አላየው ግድ የለውም፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያየው ያውቃል፡፡ በብዙ ድካም የተዘጋጀበት መርሐ ግብር  ተሰረዘ ሲባል አያኮርፍም፡፡ ገና አገልግል ሲባል ‘አቤት  ያ ሁሉ ሕዝብ ሲያየኝ’ ብሎ ሳይሆን ሰማያዊውን ክፍያ አስቦ ያገለግላል፡፡ የሕዝብ አለመብዛት የሚያስጨንቀው ለጥቂት ሰው የተዘጋጀሁትን አቀርባለሁ ብሎ ሳይሆን የቀረውን ሰው ከቤተክርስቲያን መራቅ በማሰብ ነው፡፡
ሰማያዊ ዋጋን ማሰብ አንድን አገልጋይ ከዓለማዊ ሠራተኞች የሚለየው ታላቅ ሀብት ነው፡፡ ምድራዊ ሕሊና ያላቸው እግዚአብሔርን ለገንዘብ  ማግኛነት ይጠቀሙበታል ሰማያዊ ሕሊና ያላቸው መንፈሳዊያን አገልጋዮች ግን በገንዘብ እግዚአብሔርን ያገለግሉበታል፡፡

3.  በትሕትና ማገልገል

ትሕትና ለክርስቲያኖች ከተሰጡ ሀብቶች ሁሉ ውቧ ነች፡፡ ‘ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው፡፡’ (ምሳ. 22፡4)፡፡ ‘እግዚአብሔር ትሑታንን ይወዳል፡፡ (ያዕ. 4፡6)፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ እንድንማር ካዘዘን ነገሮች አንዱ ትሕትናው ነው፡፡ ‘ከእኔ ተማሩ እኔ የዋሕ በልቤም ትሑት ነኝ፡፡’ (ማቴ. 11፡29)፡፡
ካለ ትሕትና መንፈሳዊ አገልግሎትን መከወን ማለት ፍሬን የበጠሰ (የሌለው) መኪናን መንዳት ማለት ነው፡፡ መኪናው ሄዶ ሄዶ እንደሚጋጨው አገልጋዩም ከሆነ አካል ጋር መጋጨቱ አይቀርም፡፡ ካለ ትሕትና በትዕቢት አገልግሎ የፀደቀ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ እንደውም ትልቁን ክብርና ልዕልና ያገኙት በትሕትና የተጓዙ ቅዱሳን ናቸው፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ምንም እንኳን በመልአክ እየተመገበች በቅድስና ብታድግም፣ ሴቶች ጌታን የምትወልድ ብለው በሹፈትም ቢሆን ቢጠቁሟትም፤ ቅዱስ ገብርኤል ‘ትፀንሲ፣ ትወልዲ’ ቢላትም እሷ ግን ያቺ የጌታ እናት በኔ ዘመን ኑራ ምነው ባሪያ በሆንኳት ትል ነበር፡፡ መልአኩ ለሦስተኛ ጊዜ በቤተመቅደስ እስኪነግራት እና የጌታ እናትነቷን እስከታውቅ ድረስ ሐሳቧ ይኸው ነበር፡፡ ትሑታንን የሚያከብር እግዚብሔርም መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ አደረጋት፡፡ ሙሴንና ኤርሚያስን የመሳሰሉት ቅዱሳንንም ብናነሳ አይገባኝም፤ አልችልም እያሉ እንደተጋደሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ ‘ወደ ፈርኦን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማነኝ’ (ዘጸ. 3፡11)፡፡ ‘ወዮ ጌታ እግዚብሔር እነሆ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም’  (ኤር. 1፡6)፡፡ እኔ እያለሁ በማለት ፈንታ እኔ ማነኝ፣ እኔ አውቃለሁ በማለት ፈንታ አላውቅም ብለው ከበሩ፡፡
ጌታ በወንጌል ትሕትናን ለሐዋርያት ሲያስተምር የሚከተለውን ብሏል፡፡ ‘ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደታናሽ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን፡፡ በማዕድ የተቀመጠ ወይንስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ’፡፡ ሉቃ. 22፡26፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት በመሸነፍ ማሸነፍ፣ በመሰደብና በመዋረድ ክብር፣ በመሞት ድል የሚገኝበት የትሕትና ባሕር ነው፡፡ ከትሕትና የራቀ አገልጋይም ከባሕር ውስጥ የወጣ አሳ ነው፡፡
ፍሬ የያዘ ዛፍ (ቅርንጫፍ) ዝቅ ይላል ይላሉ አበው፡፡ አባ ኤስድሮስ የተባሉ አባት ‘ሁል ጊዜ የምትጾም ከሆነ በትዕቢት ራስህን ወደ ላይ አታውጣ፣ ከዚህ የተነሣ ራስህን ከፍ አድርገህ የምትመለከት ከሆነ ግን ሥጋ ብትበላ ይሻላል፡፡ ለአንድ ሰው ራሱን በትዕቢት ከመንፋትና ራሱን ከማክበር ሥጋ ቢበላ ይሻለዋልና፡፡” ብለው የትሕትናን ጥቅም አብራርተዋል፡፡ አንድ ሌላ አባትም ‘ካልበደለና ጻድቅ ነኝ ከሚል ሰው ይልቅ የበደለና ኃጡአተኛነቱን የሚያምን ሰው ይሻለኛል’ ብሎ ስለ ትሕትና ገልጿል፡፡
አባ መቃርዮስን በአንድ ወቅት ሰይጣን ተገናኘውና “ካንተ የተነሳ የሚደርስብኝ መከራ ታላቅ ነው፡ ጉዳት ላደርስብህ ስፈልግ አልችልም፡፡ ነገር ግን አንተ የምታደርገውን ማንኛውም ነገር እኔም አደርገዋለሁ ያውም ካንተ አብልጩ አደርገዋለሁ፡፡ አንተ አብዝተህ ትጾማለህ፣ እኔ ግን ምግብ የሚባል ነገር ፈጽሞ አልበላም፣ አንተ ሌሊት እንቅልፍ በማጣት በትጋት ታድራለህ፣ እኔ ግን ጨርሶም አልተኛም፡፡ አንተ እኔን የምትበልጠኝና እኔም እርሱን የምመሰክርልህ በአንድ ነገር ብቻ ነው፡፡” አለው፡፡ መቃርዮስም “እርሱ ምንድን ነው?” ሲለው ጋኔኑ “በትሕትና ነው” አለው፡፡ ቅዱሱም ይህን የረቀቀና የመጨረሻ ፈተና ለማስወገድ መሬት ላይ ወደቀ፤ ሰይጣኑም ወደ አየር ተኖ ጠፋ፡፡” (ይህ ፈተና ትሑት ነኝ ብሎ እንዲመካ የቀረበ ረቀቂ ፈተና ነበርና)
አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ለአገልግሎቱ ስኬት ትሕትና ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡

4.  በፍቅር /በመሥዋዕትነት ማገልገል

ፍቅር ግብሩ መስጠት ነው፡፡ የሚሰጡበትን ምክንያት ሳይፈልጉ እንዲሁ መስጠት፡፡ አብ ዓለምን እንዲሁ ካለምክንያት ወዶ አንድያ ልጁን እንደሰጠ፡፡ (ዮሐ 3፡16)፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲህ አይነቱን ሕይወት ይሻል፡፡ የመስጠት ሕይወትን፡፡ አገልጋዮች የአገልግሎት ፍቅር ሲገባቸው ጊዜያቸውን ባለመሰሰት ይሰጣሉ፡፡ ጉልበታቸውን ፣ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን በጣም የበረቱትም ሕይወታቸውን ጭምር አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡
መንፈሳዊ አገልግሎት የሚታይ፣ የሚጨበጥን ነገር ሰጥተው የማይታይ፣ የማይጨበጥ ፀጋን የሚቀበሉበት የፍቅር/የመስጠት ሕይወት ነው፡፡ ስጡ ይሰጣችሁማል (ሉቃ. 6፡38) የተባለው ለዚሁ ነው፡፡ በዳግም ምፅአቱ ጌታ ጻድቃንን በቀኝ ኃጥአንን በግራ አሰልፎ የሚጠይቀው የፍቅር/የመስጠት ጥያቄን ነው፡፡ ተርቤ አብልታችሁኛል? ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል?፣….(ማቴ. 25) የፍቅር/የመስጠት ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ፍቅር የሌለው አገልጋይ የእግዚአብሔር መሆን አይችልም፡፡ ኃጢአቱ እንኳን የማይሸፈንለት ምስኪን ነው፡፡ በፍቅር የሚያገለግል ግን የኃጢአቱ ብዛት በፍቅር ይሸፈንለታል፡፡ (1ጴጥ 4፡8፣ ምሳ. 10፡12) ካለ ፍቅር እግዚብሔርን ማወቅና ወደእርሱ መቅረብ አይቻልም፡፡ ወንጌል የፍቅር ሕግ ናት፡፡ ክርስትና የፍቅር ሃይማኖት ናት፡፡ እግዚአብሔርም ፍቅር ነው፡፡ ለዚህ ነው  ቅዱስ ጳውሎስ ምንም የሰመረ አገልግሎት ቢኖርም ካለፍቅር ከንቱ እንደሆነ ያስተማረው፡፡ የሰውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ የመላአክትንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፣ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮህ ነሐስ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው፡፡ ትንቢት ብናገር፣ የተሰወረውን ሁሉ፣ ጥበብን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራ እስከ ማፍለስ የሚያደርስ ፍጹም እምትም ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ገንዘቤን ሁሉ ለምጽዋት ብሰጥ፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል ብሰጥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡’ 1ቆሮ. 13፡1-3
ፍቅር የሌለው አገልጋይ መስጠትን አያውቅም፡፡ መስጠትን የማያውቅ ደግሞ ጊዜውን፣ ጉልበቱን፣ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን በመለገስ ማገልገል አይችልም፡፡ ስለዚህ ፍቅር የሌለው መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡

5.  በትጋት፣ በጸሎትና በቅንዐት ማገልገል

አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ትጉህ፣ ጸሎተኛና ቅንዓተ ቤተክርስቲያን ያለው መሆን ይገባዋል፡፡ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው (ምሳ 12፡27) እንዳለ ጠቢቡ ትጋትን የመሰለ ሀብት ከአገልጋይ ሊለየው አይገባም፡፡ ትጋትን ገንዘብ ያደረገ አገልጋይ ለደካማ ጎኖቹ ዘወትር መፍትሔ ያበጃል፡፡ አባ ቢሾይ የተባሉ አባት በትጉህ ጸሎተኝነታቸው ይታወቃሉ፡፡ በትጋኃ ሌሊት የፀኑ ከመሆናቸው የተነሳ እንቅልፍ እንዳይጥላቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አስረው ይፀልያሉ፡፡ እንቅልፋቸውን በርትቶ ዝቅ ሲሉ ፀጉራቸውን ስለሚነጫቸው በርትተው ይፀልዩ ነበር፡፡ አባ አርሳንዮስም ለፀሐይ ማታ ጀርባቸውን ሰጥተው ለፀሎት ይቆሙና ጠዋት በምስራቅ በፊት ለፊታቸው ስትወጣ ሥጋቸውን ያሳርፋሉ፡፡ በእነዚህ አባቶች ብቃት ደረጃ መገኘት ቢከብድም የእነርሱን ብርታት አርአያ በማድረግ ግን  መትጋት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ወሳኝ ነጥብ አንድ አገልጋይ ቅንዓተ ቤተክርስቲያን ሊኖረው የሚገባ መሆኑን ማወቁ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ መከራና ግፍ ቢደርስበትም ‘የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ነው፡፡’ እንዳለው (2ኛ ቆሮ. 11፡28) በዚህ መናፍቃን በበዙበት ዘመን አገልጋዮች ለቤተክርስቲያን የሚቀኑ ሰይፎች መሆን ይገባቸዋል፡፡
ባጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎትን በመኪና ከመሰልነው እምነትን/መንፈሳዊነትን (መንፈስ ቅዱስ) በመሪ፣ ትሕትናን በፍሬን፣ ሰማያዊ ዋጋን ማሰብ በመስታወት ፍቅርን በቤንዚን/ነዳጅ፣ ትጋትን በጎማው መመሰል እንችላለን፡፡ መኪና ካለመሪው አቅጣጫ እንደማይኖረውና ወደ መድረሻው እንደማይሄድ ሁሉ ካለእምነት/መንፈሳዊነት መንፈሳዊ አገልግሎትም እንዲሁ ነው፡፡ ካለፍሬን መኪና አደጋ ላይ ይወድቃል ይጋጫል፡፡ አገልግሎትም ካለ ትሕትና እንዲሁ ነው፡፡ ካለ መስታወት የፊቱን ማየት እንደማይቻል ሰማያዊ ዋጋን ማሰብም የፊቱን በተስፋ እንድናይ ይረዳናል፡፡ ካለ ቤንዚን/ነዳጅ መኪና የማይንቀሳቀስ ቆርቆሮ ነው፡፡ ካለ ፍቅርም አገልግሎት ከንቱ ድካም ነው፡፡ መኪና በጎማው ይሄዳል፣ መንፈሳዊ አገልግሎትም በአገልጋዩ ትጋት ይገፋል፡፡
አገልጋዮችና ለማገልገል የሚፈልጉ መገንዘብ ያለባቸው የመጨረሻው ነጥብ መንፈሳዊ አገልግሎት ከፈተና ርቆ እንደማያውቅ ነው፡፡ ከረቂቁ እስከ ግዙፉ ድረስ ሁሉም ፈተና በአገልግሎት ላይ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የቤተክርስቲያን ምሥረታዋ በመስቀል ላይ እንደመሆኑ ከፈተና  ርቆ በምድር ደልቶት የፀደቀ ቅዱስ የለም፡፡ የመንፈሳዊ አገልጋይ ሕይወትም በፈተና የታጀበ ሊሆን ይችላል፡፡ አገልጋዩ እየበረታ በሄደ ቁጥር በፈተናው ይበረታል፡፡ በዚህን ጊዜ በጸሎት፣ በጾምና በስግደት መጋደል ያስፈልጋል፡፡ ከጭስ ለመሸሽ እሳት ውስጥ አይገባምና ተሸንፎ ማገልገልን ማቆም እሳት ውስጥ መውደቅ ነው፡፡ ፀጥ ያለ ባሕር ምርጥ ዋናተኛ አያፈራም እንዲሉ የአገልግሎት ባሕር ፀጥ ያለ አለመሆኑን ተገንዝቦ ምርጥ ዋናተኛ ለመሆን መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በረከት አይለየን፡፡
አገልግሎታችንን ቅዱስ አምላካችን ይባርክልን፡፡ አሜን፡፡

1 comment: