Pages

Tuesday, October 13, 2015

የረቡዕ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል ዐሥራ ስድስት
ቸሩ እግዚአብሔር በዚህ በአራተኛው ቀን ሦስት ፍጥረታትን ማለትም፡- ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጥሯል፡፡ የፀሐይ አፈጣጠር ከእሳትና ከነፋስ ሲኾን የጨረቃና የከዋክብት ደግሞ ከውኃና ከነፋስ ነው፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ምናልባት ልንጠይቀው የምንችል ጥያቄ፡- “በመጀመሪያው ቀን ላይ ብርሃን ተፈጥሯል፡፡ ሌላ ብርሃን ታዲያ ለምን አስፈለገ?” በማለት ይጠይቅና እርሱ ራሱ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “አስቀድሞ የተፈጠረው የብርሃን ተፈጥሮ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ቀድሞ ለተፈጠረው ብርሃን መሣሪያ ትኾን ዘንድ ፀሐይ ተፈጠረች፡፡ ኩራዝ ማለት እሳት ማለት አይደለም፡፡ እሳት የማብራት ባሕርይ አለው፡፡ ኩራዝን የሠራነው ያ እሳት ሥርዓት ባለው መልኩ በጨለማ ላይ እንዲያበራልን ነው፡፡ እነዚህ የብርሃን አካላትም የተፈጠሩት ልክ እንደዚሁ አስቀድሞ የተፈጠረውን ብሩህና ጽሩይ ብርሃን መሣሪያ እንዲኾኑ ነው” /አክሲማሮስ፣ ክፍለ ትምህርት 6 ቍ. 2/፡፡

አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፀሐይ ስለምን በዚህ ዕለት ማለትም በአራተኛው ቀን ላይ እንደ ተፈጠረች ሲናገር እንዲህ ይለናል፡- መጽሐፍ ቅዱስ፥ በስንፍናቸው የሚወድቁ ሰዎች እንደሚነሡ አስቀድሞ በማወቅ፡- “ያለ ፀሐይ ምድር ምንም ነገር ልታስገኝ አትችልም” ተብሎ እንዳይታሰብ፥ እግዚአብሔር ፍጥረታትን መፍጠር ከጀመረ ከሦስት ቀን በኋላ፣ ዕፅዋት፣ አዝርእትና አትክልት ከበቀሉ በኋላ፣ አትታይና ያልተዘጋጀች የነበረችው ምድርም ከተዘጋጀች በኋላ፥ ይህቺ ፍጥረት (ፀሐይ) እንደ ተፈጠረች ነገረን፡፡ በመኾኑም ዕፅዋቱ፣ አዝርእቱና አትክልቱ የሚበቅሉት “ምድር የዘር ቡቃያዎችን ታብቅል” ብሎ በተናገረው በፈጣሪ ሳይኾን በፀሐይ ነው ብለን እንዳናስብ ይህቺ ፍጥረት ከመምጣቷ በፊት እንደተፈጠሩ ነገረን፡፡ እነዚህ ሰዎች፥ የምድር ዕፅዋቶች ፍሬ እንዲሰጡ ፀሐይ የራሷ የኾነ ድርሻ አላት ብለው ቢናገሩ አልቃወማቸውም ነበር፡፡ ይህም ከገበሬዎቹ ጋር ተመሳሳይ ነው፡- ምንም እንኳን በሬን ጠምዶ የሚያርሳት፣ የሚኮተኩታት፣ የሚያለሰልሳት እርሱ ቢኾንም፥ ገበሬው የራሱን ድርሻ ተወጣ እላለሁ እንጂ ኹሉንም ነገር እርሱ እንዳደረገው አድርጌ አልወስደውም፡፡ ምክንያቱም ሺሕ ጊዜ ገበሬዎች ተሰብስበው ቢያርሱም፣ አዝርእትን ዕፅዋትንና የምድር ቡቃያዎችን ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣቸው እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር የእነዚህ ገበሬዎች ድካማቸው ኹሉ ፍሬ ቢስ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ፥ ምንም እንኳን ገበሬው ካረሰ በኋላ የፀሐይ ብርሃን፣ የጨረቃ /ዘዳ.33፥14/ እና የአየር ንብረት የተስተካከለ መኾን እርዳታ እንዳለው የታወቀ ቢኾንም፥ እግዚአብሔር ካልፈቀደ ግን እነዚህ ኹሉ ምንም ነገር ሊያመጡ አይችሉም፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሲኾን ግን የእነዚህ ኹሉ ፍጥረታት ድርሻ ትልቅ ነው /ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ክፍለ ትምህርት 6 ቍ.12-13/፡፡
     ሰው ወዳጁ አምላካችን እነዚህን ድንቅ ፍጥረታት ሲፈጥር፥ መላእክት ይህን የፀሐይ መሞቅ፣ የጨረቃ መድመቅ፣ የከዋክብትንም ብርሃን መበላለጥ አይተው አመስግነዉታል /ኢዮ.38፡7/፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ግን እነዚህ ፍጥረታት ለመላእክቱ የተፈጠሩ አይደሉም፤ ለሰው እንጂ፡፡ መላእክቱ ግን እኛ ሳንፈጠር ለእኛ የተፈጠሩትን ፍጥረታት እያዩ ስለ እኛ ያመሰግኑ ነበር፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እንግዲህ መላእክትን ስንመስል ለእኛ ስለ ተደረገ ብቻ ሳይኾን ለሌሎች ወንድሞቻችን በተደረገ መልካም ነገርንም ልናመሰግን ሲያስተምሩን ታያላችሁን?
የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንደሚነግረን፥ እግዚአብሔር አምላካችን ዕፁብ ድንቅ የምትኾን ፀሐይን በፈጠረ ጊዜ ለማን እንደፈጠራት ጠይቀዉት እርሱም “ይህቺም ያችም ኢየሩሳሌም ሰማያዊት የብርሃን ቆንጆ የብርሃን ሙሽራ ገና ለምፈጥረው ለአዳም ስፍራው ቦታው የሚኖርባት ናት፡፡ እነዚህም ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት ለአዳም የሚያበሩለት ፋናዎች (መብራቶች) ናቸው፡፡ እነዚህም ነፋሳት፣ ደመናት ውኃ ቀድተው ዝናምን የሚያዘንሙለት ናቸው፡፡ መባርቅቱም ነጐድጓዱም የሚበላውን የሚጠጣውን አዝርእቱን አትክልቱን እንዲያብቡ እንዲያፈሩ የሚያደርጉለት ናቸው፡፡ ገነት ግን ግንቡ መናገሻው ናት” ብሎ እንደ ነገራቸው ያስተምረናል፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት ስለ አዳም ምንነት ጠይቀዉታል፡፡ ጌታ እግዚአብሔርም ምንም እንኳን በአካሉ ከእነርሱ (ከመላእክቱ) በጣም ያነሰ ቢኾንም መልኩ ግን እርሱን (እግዚአብሔርን) እንደሚመስል ሲነግራቸው የሰው ልጅ እስኪፈጠር ድረስ እጅግ ጓጉተውና ናፍቀው ነበር፡፡ ምክንያቱም መላእክቱ እስከ አሁን ድረስ ጌታን በድምፁና በግብሩ እንጂ መልኩን አይተዉት አያውቁምና፡፡ ከሦስቱም አካላተ ሥላሴ አንዱ የሚኾን አካላዊ ቃል ሰው ሲኾን በቤተልሔም ግርግም ሲተኛ እጅግ የተደነቁት፣ ከሰውም በላይ ያመሰገኑት፣ ይህንንም ድንቅ እንዲያዩ እረኞችን ያቻኮሉት ስለዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ሳጥናኤል ግን ይህንን ኹሉ (የእግዚአብሔርና የመላእክቱ ንግግር) እየሰማ ይቀና ነበር፡፡ ተመልከቱ! ቅዱሳን መላእክቱ ለእኛ በተደረገና በሚደረገው ነገር እጅግ ተደሰቱ፤ ይደሰታሉም፡፡ ዲያብሎስ ደግሞ በተቃራኒው ስለ እኛም አላመሰገነም፤ ጭራሽ አመስግኑኝ አለ እንጂ፡፡ እኛ ስንድንም ይከፋዋል፡፡ ቅናት እንደዚህ ነዋ! ይህ ቅናቱም ነው በኋላ ላይ ወደ ምቀኝነት የተቀየረው፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! ፀሐይ በምዕራብ ገብታ በሰሜን ዙራ በምሥራቅ ወጥታ ታበራለች፤ መዓልቱንም ትገዛለች፡፡ ጨረቃም በምሥራቅ ወጥታ ስታበራ ታድራለች፡፡ ከዋክብትም የጨረቃ ተከታይ ስለ ኾኑ ከጨረቃ ጋር ሲያበሩ ያድራሉ /መዝ.135፡8-10/፡፡ ምናልባት ግን፡- “ፀሐይ ስለምን ቀኑን ብቻ አብርታ ቀረች ስለምን ሌሊቱንም ጨምራ አላበራችም?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ፀሐይ ሌሊቱን ጨምራ ብታበራ ኑሮ ከሙቀቷ የተነሣ ፍጥረት ኹሉ በነደደ በተቃጠለ ነበር፡፡ ጨረቃ ሌሊቱን ብቻ ማብራቷም ከውርጩ ብዛት ከቁሩ ፅናት የተነሣ ፍጥረት ኹሉ ባረረ፤ በተኮማተረ ነበር፡፡ እንግዲህ ፍጥረታቱን ብቻ ሳይኾን ሥርዓታቸውንም እንዴት ለእኛ እንዲስማሙ አድርጎ እንደ አዘጋጃቸው ታስተውላላችሁን?
ከከዋክብት መካከል ዕለትን፣ ወርን፣ ወቅትን የሚመግቡ ማለትም የሚመሩ ከዋክብት አሉ፡፡ በሌላ አገላለጽ፡- ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉትን ዕለታት የሚመግቡ (የሚመሩ) ሰባት ከዋክብት አሉ፤ በዓመት ውስጥ ያሉትን ወራትን የሚመግቡም እንደዚሁ 12 ከዋክብት አሉ፤ ልክ እንደዚሁ ወቅታትን የሚመግቡ አራት ከዋክብትም አሉ፡፡
ነገር ግን ልንጠነቀቅ የሚገባው ነገር ስለ እነዚህ ነገሮች እንዲህ መነጋገራችንና እግዚአብሔርም እነዚህን ፍጥረታት መፍጠሩ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች እንድንኾን አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንድ ሰነፍ ሰዎች እንደሚያደርጉት የሰውን ዕጣ ፈንታ እንድንመለከትባቸው ወይም የተወለድንበትን ቀን በማየት ምን ዓይነት ጠባይ እንደሚኖረን የሚነግሩን አይደሉም፡፡ እነዚህ ፍጥረታት እንዲህ መፈጠራቸው እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ጥልቅ ፍቅር እንዲያበሩልን እንደተፈጠሩ፣ በምሳሌነታቸውም እንድንማርባቸው እንጂ፡፡ ፀሐይ በመዓልት ሠልጥና ሰዎች የዕለት ተዕለት ሥራችንን እንድናከናውን ታበራልናለች፡፡ በፀሐይ የሚመሰለውና የጽድቅ ፀሐይ የተባለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ /ሚል.4፡2/ የነፍሳችን ብርሃን እንደ ኾነ እንድንገነዘብ፣ ደግሞም በእርሱ ፈንታም ማንንም እንዳናነግሥ ነው፡፡ ጌታችን የቤተ ክርስቲያን ብርሃኗ ነው፡፡ ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላትና ጨለማን ለማሸነፍ ከፀሐይ ተቀብላ እንደምታበራ ኹሉ በጨረቃ የምትመሰል ቤተ ክርስቲያንም /ራእ.12፡1/ ከብርሃን ክርስቶስ ተቀብላ በጨለማው ዓለም ትደምቃለች፤ ታበራለች፡፡ ከዋክብት ጨረቃን ተከትለው እንደሚሠለጥኑት በከዋክብት የሚመሰሉ ምእመናንም /ዳን.12፡3/ ቤተ ክርስቲያንን ተከትለው በዓለም ያበራሉ፡፡ አንድ ኮከብ በምድር ላይ ለማብራት የግድ በሰማይ ጠፈር ላይ መኖር (መቆየት) አለበት፡፡ ወደ ምድር የሚወርድ ከኾነ ለምድር ብርሃን መኾኑ ቀርቶ ጭራሽ ምድርንም የሚጐዳት ይኾናል፡፡ ልክ እንደዚሁ በኮከብ የሚመሰለው አንድ ክርስቲያንም ለሌሎች ብርሃን መኾን ሲገባው ጭራሽ በፍቅረ ዓለም የሚወድቅ ከኾነ አንደኛ ብርሃን ክርስቶስ በሕይወቱ አይበራም፤ ኹለተኛ ሌሎች ሰዎችን ያሰናክላል፡፡ ስለዚህ ምድርን ልንወዳት የሚገባን በሰማያዊ ስፍራችን በመጽናት እንጂ ወደ እርሷ በመውረድ አይደለም፡፡ እንደ ሳጥናኤል ከስፍራችን የምንወርድ ከኾነ ግን እንደተባለው አንደኛ ራሳችንን በጨለማ እንኖራለን፤ ኹለተኛ ሌሎች ሰዎችን እናሰናክላለን፡፡ ስለዚህ ከምንም በፊት ንቁም በበህዋላዌነ - በያለንበት በሃይማኖት በምግባር እንቁም፡፡ ይህን ስናደርግም ብርሃን ክርስቶስን ለሰዎች ማሳየት ይቻለናል፡፡ በዚህ ዕለት ከተፈጠሩት ፍጥረታት ልንማረው የሚገባን ይህንን ነው፡፡ በሌሎች ቀናት ስለ ተፈጠሩት ፍጥረታትም እንደዚህ ልናደርግ ይገባናል፡፡ እንዲህ ካልኾነ ግን ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ በሌላውም ቀን ምን እንደ ተፈጠረ በማወቃችን ብቻ ምንም አንጠቀምም፡፡
እመቤታችንና ዕለተ ረቡዕ
በዕለተ ረቡዕ የተሰወረውን የሚገልጡ፣ የጨለመውን የሚያስለቅቁ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ተገኝተዋል፡፡ ከእርሷም በብርሃኑ ኅልፈት መለወጥ የሌለበት፣ ጠፈር ደፈር (ግርዶሽ) የማይከለክለው፣ መዓልትና ሌሊት የማይፈራረቀው፣ የጽድቅ ፀሐይ (ለመንፈሳዊያን ምግብ) የሚኾን ጌታ ተገኝቷልና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዕለተ ረቡዕ ትመሰላለች፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ አሜን!

2 comments: