(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 9 ቀን
2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ
ሃይማኖት - ክፍል 17
ሐሙስ የሚለው ሐመሰ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲኾን አምስት አደረገ ማለት ነው። ለሥነ ፍጥረት
አምስተኛ ቀን ስለኾነ ሐሙስ ተብሏል።
በዚህ ቀን እግዚአብሔር፡- “ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾችን ታስገኝ” ብሎ አዘዘ /ዘፍ.1፥20-21/፡፡
በዚሁም መሠረት በእግራቸው የሚሔዱ፣ በልባቸው የሚሳቡና በክንፋቸው የሚበሩ ሦስት ወገን ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡
እነዚህ ፍጥረታት ተፈጥሮአቸው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ - ማለትም ከመሬት፣ ከውኃ፣ ከእሳትና ከነፋስ - ሲኾን በደመ ነፍስ
የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ደመ ነፍስ ማለትም በደም ነፍስነት፣ በደም ኃይል የሚንቀሳቀሱ፣ ደማቸው ሲቆም ሕይወታቸውም አብሮ የሚቆም
ማለት ነው፡፡ ይህም እስትንፋስ እያልን የምንጠራው ነው፡፡ ይህ እስትንፋስ - ማለትም ደመ ነፍስ - በሰውም ዘንድ አለ፡፡
እነዚህ በዚህ
ዕለት የተፈጠሩት ፍጥረታት ካለ መኖር ወደ መኖር የመጡት እግዚአብሔር ስላዘዘ እንጂ ውኃው በራሱ ኃይል ያስገኛቸው አይደለም፡፡
ይኸውም እግዚአብሔር ካልፈቀደና ካላዘዘ በስተቀር ምድር አንዲት ቡቃያስ እንኳን ማብቀል እንደማትችለው ማለት ነው፡፡ ምድር
እነዚያን ቡቃያዎች ስታበቅል አስቀድሞ ተዘርቶባት አይደለም፡፡ ውኃይቱም እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸውን ፍጥረታት ያስገኘችው
አስቀድሞ እነዚህን ፍጥረታት ሊያስገኝ የሚችል ንጥረ ነገር በውስጧ ስለያዘች ሳይኾን እንዲሁ እግዚአብሔር ስላዘዛቸውና እነዚህን
ፍጥረታትንም የማስገኘት ዓቅም ስለ ሰጣቸው እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር፥ የእነዚህ ፍጥረታት ዋናው መገኛቸው ቃለ እግዚአብሔር
ነው፤ ቃሉ ኃይልን የተመላና ሕይወትን የሚያስገኝ ቃል ነውና፡፡
በዚህ ቀን የተፈጠሩት ፍጥረታት በእኛ እይታ ምንም
ጥቅም የማይሰጡ ሊመስለን ይችላል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግን በጊዜው ለነበሩት መናፍቃን ሲመልስ እንዲህ ይላል፡- “ለምን ተፈጠሩ ብላችሁ ለመጠየቅ የምትዳክሩት ለምንድነው? የእነዚህ
ፍጥረታት መፈጠር ረብ የለውም ብላችሁ በመናቅ ነውን? ፈቃዳችሁ የቀና የተስተካከለ ቢኾን ኖሮ ግን፥ በእነዚህ ፍጥረታት አማካኝነት
የእግዚአብሔር የአምላካችሁ ኃይሉና ከመናገር የሚያልፈው ፍቅሩ እንደምን የበዛ እንደኾነ ማየት በተቻላችሁ ነበር፡፡ ኃይሉ - እነዚህ የሕይወት እስትንፋስ ያላቸውን ፍጥረታት በቃሉ ትእዛዝ ብቻ
ከውኃ እንዲገኙ ማድረጉ ነው፡፡ ፍቅሩ - ከፈጠራቸው በኋላ ለእያንዳንዳቸው የሚኖሩበትን ስፍራ መለየቱ፣ አንድ ቦታ ላይ ታጉረው
አንዳቸው አንዳቸውን እንዳይጎዳዱ፣ ፍጹም ልዩ የኾነውን የእግዚአብሔር ኃይሉ እንዲያስተምሩን፣ በሰው ልጆች ላይም ጉዳት እንዳያደርሱ
ብሎ ያንን የመሰለ ድንበር የለሽ ባሕር መስጠቱ ነው፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ፍጥረታት፥ ቢያንስ ኹለት ዓይነት ጥቅም መገኘቱ፥ ይኼን
ያህል ፍቅሩን የሚያስረዳ አይደለም ትላላችሁን? ይኸውም አንደኛ በቀና ልቡና ኾነን ለምናያቸው ለእኛ እግዚአብሔርን እንድናውቅ ያደርጉናል፤
ኹለተኛ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በእነዚህ ለቍጥር እንኳን የሚበዙ ፍጥረታት ጉዳት እንዳይደርስበት ማድረጉ
በእጅጉ እንድንደነቅ ያደርገናል፡፡ አያችሁ! እያንዳንዱ ፍጥረት የተፈጠረው እንዲሁ እኛ እንድንገለገልበት ብቻ አይደለም፡- ከለጋሥነቱ
የተነሣ አንዳንዶቹን እኛ እንድንጠቀምባቸው ከመፍጠሩም በላይ፥ ሌሎቹ ደግሞ ከሃሊነቱን ይመሰክሩ ዘንድ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ
ከእንግዲህ ወዲህ … “ይህ እና ያ ፍጥረት ለምን ተፈጠረ?” በማለትም በማይረባ አጠይቆት ውስጥ ራሳችሁን አትክተቱ፡፡” [1]
በዚህ ቀን ከተፈጠሩት ፍጥረታት መካከል አንዳንዶቹ የሚበሉ ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ የማይበሉ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸውን እዚህ
መግለፅ ባይቻልም እንኳን ዓሦችን ብቻ እንደ ማሳያ በመመልከት ለምን እንደማይበሉ እንመልከት፡፡ ሊበሉ የሚገባቸው ዓሦች እነማን
እንደኾኑ መጽሐፍ ሲነግረን እንዲህ ይላል፡- “ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን” /ዘሌ.11፥9-12/፡፡ እነዚህ ክንፍ
ያላቸው ዓሦች ጸጋ መንፈስ ቅዱስን አጋዥ በማድረግ በእምነት ይህን ዓለም መቅዘፍ የሚችሉትን ክርስቲያኖችን ይወክላሉ፡፡ ቅርፊቱም
ራሳቸውን ከክፋት ኹሉ የሚጠብቁበት ንጽህናቸው ነው፡፡ ስለዚህ አምላካችን “ቅርፊትና ክንፍ የሌላቸውን ዓሦች አትብሉ” ሲል “እምነት
ይኑራችሁ፤ ከክፋት ኹሉ ትጠበቁ ዘንድም ንጽህናን ገንዘብ አድርጉ” ሲል ነው፡፡ ከጤንነት አንጻር ስንመለከታቸው ግን እነዚህ ክንፍና
ቅርፊት የሌላቸው ዓሦች (ኦይስተር፣ ክላምስ፣ ሽሪምፕ፣ ክራብስ፣ ሎብስተር፣ ወዘተ) እጅግ አደገኞች መኾናቸውን እንገነዘባለን፡፡
ክንፍና ቅርፊት ያላቸው (ንጹሃን) ዓሦች በውኃ ውስጥ በሚገባ የሚዋኙ ዓሦች ናቸው፤ በነጻነትና በውኃ ላይ መንሳፈፋቸውም በጥገኛ
ተሐዋስያን በቀላሉ እንዳይጠቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ቅርፊትና ክንፍ የሌላቸው ዓሦች ግን ጥንብ አንሣ በመኾናቸውና ከውኃው ሥር ያለውን
ጭቃና አፈር እየበሉ ስለሚኖሩ በጥገኛ ተሓዋስያን በቀላሉ ይጠቃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉት ባለሙያዎች እንደገለፁትም
እነዚህ “ሼል ፊሽ” የተባሉት የዓሣ ዝርያዎች በየቀኑ ብዙ መጠን ያለውን ውኃ ስለሚያጣሩ ኬሚካሎችን፣ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን፣
ጐጂ ባክቴሪያዎችን፣ ጥገኛ ተውሳኮችንና ቫይረሶችን የያዘ ፍሳሽ በሰውነታቸው ላይ ይጫናል፡፡ በመኾኑም በብዙ ቦታዎች ውስጥ ለኮሌራ
ወረርሽኝ የመፈንዳት ምክንያት ይኾናሉ፡፡ [2] ከዚህም በተጨማሪ እንዳይበሉ በተከለከሉት የዓሣ ዝርያዎች በአብዛኛዎቹ ብዙ የሜርኩሪ
መጠን በሰውነታቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ ሜርኩሪ ደግሞ ለአእምሮአችን እጅግ አደገኛ የኾነ ንጥረ ነገር ነው፡፡ በተለይም እነዚህን የዓሣ
ዝርያዎች የሚመገቡ ጨቅላ ሕፃናት ከኾኑ የነርቭ እድገታቸው የተስተጓጐለ ስለሚኾን የአእምሮ ዝግመት ያጋጥማቸዋል፡፡
ነገር
ግን ልናስተውለው የሚገባን፥ እነዚህ “ንጹሃን አይደሉም - ማለትም አይበሉም” ተብለው የተጠቀሱት ዓሦች በተፈጥሮአቸው እንከን ኖሮባቸው
አይደለም፤ ከመንፈሳዊ ትርጉማቸው በተጨማሪ በውስጣቸው ከሰው ጋር የማይስማማ ንጥረ ነገር ስላላቸው ነው እንጂ፡፡ ይኸውም፥ መርዝ
በራሱ መጥፎ እንዳይደለና በውስጡ ያለው ንጥረ ነገር ግን ከሰው ሰውነት ጋር ስለማይስማማ “ንጹህ አይደለም” እንደምንለው ነው፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ አባትነቱ በነፍሳችን ብቻ ሳይኾን በሥጋችንም ይጠነቀቅልናልና እንዳንበላቸው አዘዘ፡፡ ፍትሐ ነገሥት ይህንን
ሲያስረዳ፡- “እኒህንም የሚከለክሏቸው … ነፍስንም ሥጋንም የሚጎዳ ሕማም በውስጡ ስላለ ነው፡፡ ይህች መፈጠርን ወደ ማጥፋት በሚያደርስ
ጥፋት የሥጋን ባሕርያት ስምምነት ታጠፋለችና፡፡ ዳግመኛም አካልን ወደ ማጉደል ታደርሳለችና” ይሏል፡፡ [3]
ተወዳጆች ሆይ!
በዚህ ዕለት የተፈጠሩትን ፍጥረታት ከአኗኗራቸው አንጻር ስንመለከታቸው፥
አንዳንዶቹ በተፈጠሩበትና በባሕሩ ውስጥ ጸንተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ በመኾኑም እግዚአብሔር በእነዚህ ፍጥረታት አንጻር
በስሙ አምነን፣ ልጅነትን አግኝተን ጥንተ ተፈጥሮአችንን ባገኘንባት በቤተ ክርስቲያን ጸንተን ልንኖር እንደሚገባን ሲያስተምረን
ነው፡፡ ወጣ ገባ እያሉ እንደሚኖሩት እንደ አንዳንዶቹ እንስሳት አንዴ ወደ ኃጢአት፣ ሌላ ጊዜም ወደ ክሕደት የምንወጣና
የምንወላውል ልንኾን አይገባም፤ በምግባር በሃይማኖት ጸንተን ልንኖር ይገባናል እንጂ፡፡
በዚህ ዕለት
የተፈጠሩትን ፍጥረታት እያንዳቸው እንዲህ ስንመለከታቸው ለሕይወታችን እጅግ የሚያስደንቅ ነገር እንማርባቸዋለን፡፡ ለምሳሌ፥
ዓሦች ንጹህ ውኃን ይመርጣሉ፤ እኛም ንጹህ እምነትንና ሕይወትን ልንመርጥ እንደሚገባን ሲያስተምሩን ነው፡፡ ዓሦች አውሎ ነፋስ
ወይም ጎርፍ በሚበዛበት አከባቢ አይኖሩም፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ውኃው ከሚገባው በላይ ሲሞቅና ሲቀዘቅዝ
የሚኖሩበትን አከባቢ ይመርጣሉ፡፡ ነገር ግን ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው እነዚህ እንስሳት ደመ ነፍሳዊ ዕውቀት እንጂ እንደ
ሰው ለባዊነት ስላላቸው አይደለም፡፡ እንግዲህ፥ እነዚህ ዓሦች ምን እንደሚረባቸውና እንደማይረባቸው በደማዊት ነፍሳቸው የሚያውቁና
ለሕይወታቸው ጥንቃቄ የሚያደርጉ ከኾነ፥ ለባዊት ነፍስ የተሰጠችን፣ ሕገ እግዚአብሔር ከልቡና አልፎ በጽሑፍም የታደልን፣ ርስተ
መንግሥተ ሰማያትን እንደምንወርስ ቃል የተገባልን፣ መንፈስ ቅዱስ ጥበቡን የሰጠን እኛ’ማ ከእነዚህ ዓሦች አንሰን ብንገኝ ምን
ዓይነት ተስፋ ድኅነት ነው የሚደረግልን? እነዚህ ዓሦች ሕይወታቸው ቀጣይ ይኾን ዘንድ ራሳቸውን ከምን መጠበቅ እንዳለባቸው
ያውቃሉ፤ እኛ ግን ስለ ቀጣዩ - ማለትም ስለ ወዲያኛው ዓለም - ሕይወታችን እጅግ ግድ የለሾች ነን፡፡ ዓሦች መልካሙን ስፍራ
ያገኙ ዘንድ ባሕሩን ኹሉ ያቋርጣሉ፤ እኛ ግን የክፋት ኹሉ ስር በምትኾን በስንፍና ተይዘን የምንኖር ነን፡፡ ለባዊት ነፍስ
የተሰጠችን ግን ከእነዚህ እንስሳት በላይ ለራሳችን መልካም የኾነውን እንድንመርጥና ክፉው የኾነውን ኹሉ ከእኛ እንድናርቅ
ነው፡፡
ከእነዚህ ዓሦች
በተጨማሪ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ በጣም ትናንሹን እንስሳት ስንመለከት፥ በጣም በሚያስደንቅ ኹኔታ ከየትኛው አቅጣጫ ማዕበል
እንደሚነሣ ያውቃሉ፡፡ በመኾኑም፥ ማዕበሉ እስኪያልፍ ድረስ ራሳቸውን ወደ ውኃው ጥልቅ በማስገባት ከትልቅ ድንጋይ ጋር
ያጣብቃሉ፡፡ ከክብደታቸው ማነስ የተነሣ ማዕበሉ በቀላሉ እንዳይጎዳቸው ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ለእኛ ቀላል ትምህርትን የሚሰጥ
አይደለም፡፡ ስለዚህ፥ በየጊዜው ከሚመጡና ሃይማኖታችንንና ምግባራችንን ሊያስተዉን የሚችሉ ነፋሶችና ጎርፎች መጥተው ጠራርገው
እንዳይወስዱን ራሳችንን ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን በማቅረብ ከማይነቀነቀው ዓለት - ከክርስቶስ - ጋር ልንጣበቅ
ያስፈልጋል፡፡ ይህን ያደርግን እንደኾነ ዓይናችን እስከ አሁን ድረስ ያላየችው፣ ጆሮአችን ሰምቶት የማያውቀው፣ እነዚህስ ይቅሩና
ልቡናችንም አስቦትና አሰላስሎት የማያውቀውን ርስቱን መንግሥቱን እንወርሳለን፡፡ ከባሕርይ
አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር፣ ኃይልና ጌትነት የባሕርይ ገንዘቡ የኾነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ለዚህ ክብር የበቃን የተዘጋጀን እንድንኾን ይርዳን፡፡ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ፤ አሜን!!!
[1]
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ክፍለ ትምህርት
7፥ 11-12
[2] መጋቤ ሐዲስ
ሮዳስ ታደሰ፣ መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ፣ 2004 ዓ.ም.፣ ገጽ 35-36
[3]
ፍትሐ ነገሥት 23፥603
kalehiwot yasemalen. Mengestesemayten yawersilen tsegawen yabezalachu
ReplyDeletekalehiwot yasemalen
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር
ReplyDelete