Pages

Tuesday, October 6, 2015

የማክሰኞ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል ዐሥራ አምስት
ሦስተኛይቱ ዕለት ዕለተ ሠሉስ ትባላለች፡፡ ሠሉስ ማለት ለፍጥረት ሦስተኛ ማለት ነው፡፡ በአማርኛ ማግሰኞ ትባላለች፤ የሰኞ ማግስት እንደ ማለት ነው፡፡ በተለምዶ ግን ማክሰኞ እንላለን፡፡ እኛም አንባብያንን ግራ ላለማጋባት በዚህ አካሔድ እንቀጥላለን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ሰኞ ላይ ውኃዉን ከሦስት ከፍሎ ምድርን ግን ከውኃ እንዳልለያት ተነጋግረን ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ማለትም ማክሰኞ ላይ ግን በዚህ ዓለም የነበረውን ውኃ ወደ አንድ ስፍራ እንዲሰበሰብ አድርጓል፡፡ ውኃው ሲሰበሰብም ምድር ተገልጣለች፡፡ ነገር ግን ተገለጠች እንጂ ቡቃያ አልነበረባትም፡፡ በመኾኑም በምሳር የሚቈረጡ (እንደ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወዘተ)፣ በማጭድ የሚታጨዱ፣ በጥፍር የሚለቀሙ (እንደ ሎሚ፣ እንደ ትርንጎ ያሉ) አዝርእትን፣ አትክልትንና ዕፅዋትን እንድታስገኝ አዘዛት፡፡ ምድርም የቃሉን ትእዛዝ አድምጣ እነዚህን ሦስት ፍጥረታትን አምጣ ወለደች /ዘፍ.1፡12-14/፡፡

ሰው ወዳጁ እግዚአብሔር በዚህ ዕለት ከላይ ከጠቀስናቸው ፍጥረታት በተጨማሪ ብሩህ ብሩሁን መሬት በምሥራቅ በኩል በናጌብ (በምድር ዳር) ጠቅልሎ አኑሮት ነበርና በምሥራቅ ኤደን ገነትን ተክሏል፡፡ ስለ ገነት ምንነት ስለ ሃያው ዓለማት ስንነጋገር የምንመለስበት ሲኾን ለጊዜው ግን በገነት ውስጥ ስለ በቀሉት ዕፅዋት እንማማር፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በገነት ውስጥ (ለአዳም) ሦስት ዓይነት ዕፅዋትን ፈጥሮለታል፡፡ አንዱ የሚጠብቀው - ዕፀ በለስ፣ አንዱ የሚመገበው፣ ሦስተኛው ደግሞ የሚታደስበት - ዕፀ ሕይወት፡፡ እስኪ በጥቂቱም ቢኾን ስለ እነዚህ ዕፅዋት እንመልከት፡-
እንዲመገባቸው የተሰጡት ዕፅዋት
ሰው ወዳጁ እግዚአብሔር በገነት ውስጥ ታላላቅና ታናናሽ ዕፅዋትን ያበቀለ ሲኾን ታናናሹ ብቻ ቅጠላቸው ዐሥራ ኹለት ዐሥራ ኹለት ክንድ ያክላል፡፡ እንደ ኮከብም ያበራል፡፡ ፍሬአቸውም ክብ ነው፡፡ ዛሬ እነዚህን ዕፅዋት የሚመገቡት በብሔር ብጹዓን ያሉ ጻድቃን ቅዱሳንና በገነት ያሉ አዕዋፍ ናቸው፡፡ የሚያመጣላቸውም ነፋስ ነው፤ ነፋሱ እንደ ዝናብ ያዘንብላቸዋል፡፡ ያን ተመግበውም ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ይኖራሉ /ገድለ ዞሲማስ/፡፡
ዕፀ ሕይወት
አበው እንደሚነግሩን ዕፀ ሕይወት ጫፏ ከሰማይ ይደርሳል፡፡ ፍሬዋ እንደ ሮማን ፍሬ ተነባብሮ ከእግር እስከ ራሷ ምሉ ነው፡፡ ከዕፀ ሕይወት ፍሬ አንዲቱን ቆርጦ በአፉ ጎርሶ አላምጦ ሳይውጣት እንደ ቀድሞው ፍሬ ተክታ ትገኛለች /ሕዝ.47፡12-13፣ ራእ.22፡2-3/፡፡ ከዕፀ ሕይወት አንዲቱን ፍሬ በበሏት ጊዜ ጣዕሙ ከአፍ፣ መዓዛው ከአፍንጫ ሳይለይ እስከ ሰባት ቀን ይቀመጣል /ኄኖ.7፡6-16/፡፡ ከዚህች ዕፅ የቀመሱ ሰዎች “እንዲህ ያለውስ ምግብ ያለ እግዚአብሔር ቸርነት ለፍጡር አይገባውም ነበር” እያሉ ያደንቃሉ፡፡ ቅጠሏ፣ አበባዋ፣ ፍሬዋ ያለ ደዌ ያለ ሕማም ነፍስን ከሥጋ ይለያል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ዕፀ ሕይወትን ብላም አትብላም አላለውም፡፡ ይህ ለምን እንደ ኾነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲመልስልን እንዲህ ይለናል፡- “አዳም ቢፈልግ ኖሮ፥ ይህን ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን ዛፍ ከሌሎች ዛፎች ጋር አብሮ መብላት ይችል ነበር፤ በመኾኑም ስለ ዕፀ ሕይወት ብላም አትብላም አላለውም፡፡” በኋላ ላይ ይበልጥ እያብራራነው እንድምንሔድና ከዚህ መረዳት እንደምንችለው፥ የሰው ልጅ (አዳም) የራሱ የኾነ ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ ይህ ነጻ ፈቃዱ እንኳንስ ዲያብሎስ እግዚአብሔርም ቢኾን ጣልቃ የሚገባበት አይደለም፤ ሰው ራሱ እንደ ውዴታው የሚያዘው እንጂ፡፡ በመኾኑም በዚህ ነጻ ፈቃዱ፥ ከፈለገ ይህን ዕፀ ሕይወት በልቶ ለዘለዓለም መኖር ይችል ነበር፡፡ ውሳኔው ለራሱ ለአዳም የተተወውም ስለዚሁ ነው፡፡
መረዳት ያለብን ግን ዕፀ ሕይወት ሲባል ዕፁ በራሱ ሕይወትን የሚሰጥ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ዕፁ የመታዘዝ ምልክት ነው፤ እግዚአብሔርን ቢታዘዝና እንደ ሕጉ ቢኖር ይህቺን ዕፅ በልቶ ይታደስ ነበር፡፡ ይታደስ ነበር ሲባል የሰው ልጅ በመዋቲነትና በኢመዋቲነት መካከል ኾኖ ተፈጥሮ ስለ ነበር ወደ ኢመዋቲነት ይሸጋገር ነበር ማለት ነው፡፡ በበደለ ጊዜ ይህቺን ዕፀ ሕይወት እንዳይበላ መከልከሉም ስለዚሁ ነው፡፡ ምክንያቱም ከበደሉ ሳይነጻ ይህቺን ዕፅ ቢበላ ኖሮ ለዘለዓለም እየበደለ ነበር የሚኖረው፡፡ በበደሉ ምክንያት የመጣበት ጉስቁልና ለዘለዓለም አብሮት ነበር የሚኖረው፡፡ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔር ግን መጀመሪያ ሞቱንና ጉስቁልናዉን አስወግዶ ወደ ቀድሞ ቦታው ወደ ገነት ወደ ቀድሞ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ከገነት እንዲወጣና ከዚህች ዕፅ እንዳይበላ አደረገው፡፡ ዛሬ ይህ ዕፀ ሕይወት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ኾኖ ተሰጥቶናል /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/፡፡    
ዕፀ በለስ
ይህቺ ዕፅ እግዚአብሔር በገነት በምዕራብ በኩል የተከላት ሲኾን አዳምና ሔዋን እንዳይበሏት የከለከላቸው ብቸኛይቱ ዕፅ ነች፡፡ እንዳይበሏት ሲከለከሉ እንኳን ሔዋን ራሷ እንደ ተናገረችው ነፍጓቸው ወይም ተመቅኝቶዋቸው ሳይኾን፡- አንደኛ) ስለ ፍቅሩ ለፈጠረው ለእግዚአብሔር በፍቅር በመታዘዝ እንዲመልስ፤ ኹለተኛ) ፍጡርነቱን እንዲያውቅባት፤ ሦስተኛ) ነጻ ፈቃዱ እንዲገልጥባት የተሰጠችው ናት፡፡ ቸሩ እግዚአብሔር “ትሞታለህ” ሲለው እንኳን እግዚአብሔር ስለ ጥልቅ ፍቅሩ አዳምን የመከረው እንጂ ጠበኛ አምላክ ኾኖ የተናገረው አይደለም፤ እገድልሃለሁ አላለውምና፡፡
እዚህ ጋር መረዳት ያለብን ዕፀ በለስ በራሷ መልካም መኾኗን ነው፡፡ ፍሬዎቿም እንደዚሁ መልካም ናቸው፡፡ በውስጧ ሞትን የተሸከመች፣ ወይም መርዝነት ያላት አይደለችም፡፡ ስለዚህ ዕፀ በለስ ልክ በዕፀ ሕይወት ላይ እንደተነጋገርነው የሕግ ምልክት ናት፡፡ በመኾኑም አዳም የሞት ሞትን የሞተው የሕግ ምልክት ኾና የተሰጠችውን ዕፅ ባለመታዘዙ ስለ በላት እንጂ ዕፀ በለስ የምትገድል ኾና አይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ አዳምን የጣለው አለመታዘዙ ነው፤ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ ግድ የለሽነቱ ነው፡፡ ይህን ሐሳብ ስለ ሰው ልጅ ውድቀት ስንነጋገር በስፋት እንመለስበታለን፡፡
በዕፀ በለስ ውስጥ ከዕውቀት በቀር ምንም የለም፡፡ ዕውቀት ሲባል ራሱ አዳምና ሔዋን ከክብር መዋረዳቸውን ማወቅን ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ዕፀ በለስ በጎ ዕውቀትን የምታሳውቅ ዛፍ ብትኾን ኖሮ ኃጢአት “ኃጢአት” ሳይኾን “የዕውቀት አስተማሪ” በተባለ ነበር፤ እባብ በእርሱ አንጻርም ዲያብሎስ ባልተወቀሰ፣ “የሐሰት” ሳይኾን “የጥበብ አማካሪም” በተባለ ነበር፡፡ ነገር ግን አይደለም፤ አዳምና ሔዋን መልካም የተባለው መታዘዝ፣ ክፉ የተባለውንም አለመታዘዝ ከመውደቃቸው በፊት ያውቁ ነበር፡፡
ዛሬ በዕፀ በለስ ምክንያት የመጣው ሞት በዕፀ መስቀል ምክንያት ተወግዶልናል፡፡
ዕፅዋት ዕለተ ማክሰኞ ላይ የመፈጠራቸው ምክንያቱ ምንድነው?
እያንዳንዱ ፍጥረት የተፈጠረበት ቀንና ቅደም ተከተል የራሱ የኾነ ጥልቅ ምክንያት አለው፡፡ በዚህ ዕለት ማለትም ማክሰኞ ላይ የተፈጠሩት ፍጥረታትም በዚሁ ዕለት መፈጠራቸው የራሱ የኾነ ምክንያት አላቸው፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያህልም፡-
v  ዕፅዋት የሚበቅሉት በፀሐይ ምክንያት ብቻ ነው ብለን እንዳንደመድም ፀሐይ ከመፈጠሯ በፊት ፈጠራቸው፡፡ ይህን በማስመልከት አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አንቀጽ ሲተረጉምልን እንዲህ ይለናል፡- “ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔር ቃል በተናገረ ጊዜ፥ በምድር ላይ የበቀሉ ፍጥረታት እንደምን ካለ መኖር ወደ መኖር እንደመጡ ታስተውሉ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ እነዚህ አዝርእቶች የበቀሉት ገበሬ ስለ ጣረ፣ ወይም ስላረሰ፣ ወይም በሬዎች ስለ ተጠመዱ፣ ወይም ሌላ ፍጥረት ደክሞባቸው የበቀሉ አይደሉም - እንዲሁ ኹሉም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አዳመጡ፤ እነርሱም ከምድሪቱ በቅለው ወደ መታየት መጡ፡፡ ዛሬም፥ የአዝርእት ምርትን የምናገኘው፥ በገበሬዎች ጥረት ወይም በሌሎች ሠራተኞች ድካም ሳይኾን፥ ከእነዚህ በፊት እግዚአብሔር ጥንቱን እንዳደረገው፥ አሁንም በቃሉ ትእዛዝ የምናገኝ እንደኾነ ከዚህ እንማራለን፡፡ ሰዎች በስንፍናቸው ምክንያት፥ በኋላ ዘመን የሚያመጡትን ስሕተት ያቀና ዘንድ፥ ከልቡናቸው አንቅተው የሚናገሩትንና “የምድር ዘሮች የሚበቅሉት በፀሐይ አማካኝነት ነው” ብለው ለሚነሡ ኹሉ ምክንያት ያሳጣቸው ዘንድ፥ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ስለ እያንዳንዱ ሥነ ፍጥረት አፈጣጠር በዝርዝር ነገረን” /ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ክፍለ ትምህርት 5 ቍ.12/፡፡ ሊቁ ይህንን የሚለን ፀሐይ ድርሻ የላትም ለማለት ሳይኾን የእነዚህ ፍጥረታት መገኘት ከፀሐይ መኖር ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ብለን እንዳናስብ ነው፡፡
v  እነዚህ ዕፅዋት ለሰው ብቻ ሳይኾን ሐሙስና ዓርብ ለሚፈጠሩ ለእንስሳትም ምግብ ናቸውና ከእንስሳቱ በፊት አስቀድመው ተዘጋጁ፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር አስደናቂ ፍቅሩ ለሰው ብቻ ሳይኾን ለእንስሳቱም ጭምር እንደ ኾነ እንማራለን፡፡ ይኸውም በኋላ ላይ፡- “የሚበቅለው ሐመልማል ኹሉ መብል ይኹንላቸው” ባለው ይታወቃል /ዘፍ.1፥30/፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ! ርስት መንግሥተ ሰማያት ለማይወርሱ ለእንስሳቱ እንኳን እንዲህ የሚያስብላቸው አምላክ፥ ለእኛ ደግሞ እንዴት እንደሚያስብልንና እንደሚያፈቅረን እንኳንስ በመናገር በማሰብም አንደርስበትም፡፡ 
ተወዳጆች ሆይ! እንዲህ እያደረግን ፍጥረታቱ የተፈጠሩበትን እያንዳንዱን ቀን ብንመረምረው እንደዚህ እጅግ እንደነቃለን፡፡ 
እመቤታችንና ዕለተ ማክሰኞ
በዕለተ ሠሉስ ምድር ገበሬ ሳይጥርባት፣ ሳይደክምባት፣ ዘር ሳይወድቅባት በቃሉ ብቻ በእጅ የሚለቀሙ አትክልት፣ በማጭድ የሚታጨዱ አዝርእት፣ በምሳር የሚቆረጡ ዕፅዋት ለሥጋውያን ምግብ የሚኾኑ ተገኝተዋል፡፡ ከእመቤታችንም የወንድ ዘር ሳይወድቅባት ዕፀ ሕይወት፣ ፍሬ ሕይወት (የመንፈሳዊያን ምግብ) የሚኾን ጌታ ተገኝቷልና በዕለተ ሠሉስ ትመሰላለች /ውዳሴ ማርያም ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው፣ ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ 15-17/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!  

1 comment:

  1. ኣለ ህይወት ያሰማልን መምህር የኣገልግሎት ዘመንዎ ይባረክ

    ReplyDelete