Wednesday, November 4, 2015

የዓርብ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል 18
ዓርብ ዐረበ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን ተካተተ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዓርብ ማለት መካተቻ መደምደሚያ ማለት ነው። ምዕራብ ስንል መግቢያ፣ መጥለቂያ (ለምሳሌ የፀሐይ መግቢያን ምዕራብ እንደምንለው) ማለት ሲኾን ዐረብ ሲባልም ተመሳሳይ ነው - ከኢየሩሳሌም ምዕራባዊ አቅጣጫ ያሉ ሀገራት የዐረብ ምድር ይባላሉና። ዐርብ የተባለበት ምክንያት በዕለተ እሑድ መፈጠር የጀመሩት ፍጥረታት ተፈጥረው ያበቁበት፣ የተካተቱበት ቀን ስለ ኾነ ነው፡፡
በዚህ ቀን እግዚአብሔር “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ እንስሳትን ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ ታውጣ” ብሎ አዘዘ /ዘፍ.1፥24/፡፡ በዚሁም መሠረት ልክ እንደ ሐሙስ ፍጥረታት በእግራቸው የሚሔዱ፣ በልባቸው የሚሳቡና በክንፋቸው የሚበሩ ፍጥረታት ናቸው፡፡ የሐሙስና የዓርብ መኾናቸውን የምንለየውም በአኗኗራቸውና በግብራቸው ሲኾን የሐሙስ ፍጥረታት በባሕር፣ የዓርብ ፍጥረታትም በየብስ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ቀን በአራተኛ አዳምን ፈጥሯል። ይህንን በኋላ እንመለስበታለን፡፡
በሳይንሳዊ መንገድ ሔደን ምድር እነዚህን ፍጥረታት እንዴት ልታስገኛቸው ቻለች ብለን ብንጠይቅ መልስ የለውም፡፡ የተገኙት እግዚአብሔር ስላዘዘ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምድሪቱን አዘዛት፤ እርሷም አረገዘች፤ ወለደቻቸውም፡፡ ዛሬም ይህ እውነት እንደ ኾነ የምናይበት ኹናቴ አለ፡፡ ዝናብ ወደ ሰኔ አከባቢ መዝነብ ሲጀምር አስቀድመን ያላየናቸው ፍጥረታት ከምድር ወጥተው ሲበሩ፣ እንዲሁም እንደ እንቁራሪት ያሉ ፍጥረታት ወደ መኖር ሲመጡ እናያቸዋለን፡፡ አስቀድሞ ባልተጣለ ዕንቁላል የተለያዩ ዓይነት ትላትሎች ከጭቃ ውስጥ ሲፈጠሩ እናያቸዋለን፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ጥበብ ታያላችሁን?
  
የዓርብ ፍጥረታት የቤትና የበረኻ ተብለው ይከፈላሉ፡፡ አስቀድሞ - ማለትም የሰው ልጅ ከመበደሉ በፊት - ግን እንደዚህ አልነበሩም፡፡ ኹሉም ለአዳም የሚገዙለትና የሚታዘዙለት ነበሩ እንጂ፡፡ እንዲህ ተብለው የተከፈሉት ከበደል በኋላ ነው፡፡ ይህም የኾነበት ዋናው ምክንያትም የእግዚአብሔር ቸርነት ነው፡፡ “ይህስ እንዴት ነው?” ያልን እንደ ኾነም፥ የቤት እንስሳ የሚባሉት የሰው ልጅ ለእርሻ፣ ለምግብነት፣ ለመጓጓዣነት፣ ለልብስ፣ ወዘተ የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ “በፊትህ ወዝ እንጀራህን ትበላለህ” ተብሎ የተፈረደበት የሰው ልጅ /ዘፍ.3፥19/ ወዙና ድካሙ አስጨናቂ እንዳይኾንበት እነዚህ እንስሳት ጭንቀቱንና ድካሙን እንዲጋሩት የተሰጡት ናቸው፡፡
የበረኻ እንስሳት የሚባሉት ደግሞ ከሰው ርቀው በዱር በበረኻ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነዚህ አስቀድመው ለአዳም ይገዙና ይታዘዙ የነበሩት እንስሳት ከሰው ርቀው መኖራቸውም እንደዚሁ የእግዚአብሔር ቸርነት ነው፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ እንስሳት የምንፈራ የምንቀጠቀጥ ኾነናል፡፡ ይኸውም በዚህ ፍርሐትና መንቀጥቀጥ በደላችን እንደ ምን የበዛች እንደ ኾነች፣ ክብራችንን ምን ያህል ከባሮቻችን - ከእነዚህ ከእንስሳት - በታችስ እንኳን ዝቅ ዝቅ እንዳደረግነው የሚያስተምሩን ናቸው፡፡ ዛሬ በዘመነ ሐዲስ ላይ እንኳን ኾነን እነዚህ እንስሳት እኛን ማስፈራራታቸው ካሳው ስላልተከፈለ ሳይኾን እግዚአብሔር ከምን ያህል በደል እንዳዳነን ዐውቀን በምስጋና እንድንኖር፣ እንዲሁም የተሰጠንን ድኅነት በአግባቡ ይዘን ብንወድቅም እንኳን በንስሐ እየታደስን በተጋድሎ እንድንኖር ለማስተማር እግዚአብሔር ባወቀ ለእኛ ጥቅም የተደረገ ነው፡፡ ቅዱሳን እየበቁ ሲሔዱ ግን እነዚህ እንስሳት ተገዢዎች ናቸው፡፡ እነ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባን፣ እነ አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞን ማሰብ በቂ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ እንስሳት ለእኛ የሚሰጡት ሌላ ምንም ጥቅም የላቸውም የምንላቸው አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ሐኪሞች አንዳንድ መድኃኒተ ሥጋን ለመቀመም እነዚህን እንስሳት ይጠቀማሉና፡፡ ዳግመኛም ኹሉም ፍጥረት እንድንገለገልበት የተፈጠረ አይደለም፡፡ እርሱን አይተን እንድንማርበት፣ እንድናደንቅበት፣ ነገረ እግዚአብሔርን እንድናስብበት - በአጭሩ ለአንክሮ ለተዘክሮ - የተፈጠረም አለና፡፡
ልክ እንደ ሐሙስ ፍጥረታት በዚህ ዕለት የተፈጠሩ ፍጥረታትም የሚበሉና ንጹሃን፣ የማይበሉ ንጹሃን ያልኾኑ ተብለው ይከፈላሉ፡፡ ነገር ግን የሐሙስ ፍጥረታትን ስንማማር እንደ ተነጋገርነው “አይበሉም - ንጹሃን አይደሉም” የተባሉት እንስሳት “በባሕርያቸው ርኩሳን ናቸው” ማለት አይደለም፡፡ በመጠኑም ቢኾን ግንዛቤ ይኖረን ዘንድም አጠር አጠር እያደረግን እንመልከታቸው፡-  
ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት /ዘሌ.11፥1-11/
ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው፥ ሰኮናቸው የተሰነጠቀ ማለት በኹለቱም ኪዳናት - ይኸውም በብሉይና በሐዲስ ኪዳን - የተሰጡትን ሕግጋተ እግዚአብሔርን የሚቀበሉና የሚያምኑ፥ አንድም ሕገ እግዚአብሔርን ለዚህ ዓለም ኑሮአቸውም ኾነ ለሚመጣው ሰማያዊ ሕይወታቸው የሚጠቀሙትን ማለት ሲኾን፤ የሚያመሰኩ ማለት ደግሞ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሕገ እግዚአብሔርን አንድም ቃለ እግዚአብሔርን በመዓልትና በሌሊት የሚመለከት ሰው ንዑድ ክቡር ነው” እንዳለ /መዝ.1፥2/ የተማሩትንና ያመኑትን ቃለ እግዚአብሔር የሚያሰላስሉና መልሰው መላልሰው ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚረዱ ማለት ነው፡፡ ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀ ማለት ደግሞ በኹለቱም ኪዳናት የማያምኑ፣ ወይም ደግሞ ከፍለው የሚያምኑ ማለት ነው፡፡ የማያመሰኩ ማለትም የተማሩትን፣ ወይም ያነበቡትን ቃለ እግዚአብሔር መልሰው ማሰላሰልና ማመሣጠር የማይችሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር፡- “ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳትን አትብሉ” ሲል “ከኹለቱም ኪዳናት ከፍለው ከሚያምኑ፣ የቃሉንም ምሥጢር ለመረዳት ሳይኾን አፍአዊውን (Litteral) ትርጓሜውን ብቻ በመያዝ በስንፍናና በምንፍቅና ከተያዙ ሰዎች ጋር ኅብረት አይኑራችሁ” ሲል ነው፡፡
እያንዳንዱ የተጠቀሰው እንስሳም (ግመል፣ ጥንቸል፣ ሽኮኮ፣ እሪያ፣ ወዘተ) የራሱ የኾነ ምሳሌአዊ (Allegorical) መልእክት አለው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር “እሪያን አትብሉ” ሲል “በቆሻሻ ነገር ደስታን ለማግኘት አታስቡ፤ መልካም ነገራችሁንም በርካሽ ሥፍራ ላይ አትጣሉት” ሲል ነው፡፡
ከጤንነት አንጻር ስንመለከታቸው ደግሞ እነዚህ እንዳይበሉ የተከለከሉት እንስሳት እጅግ ጎጂ እንደ ኾኑ እንገነዘባለን፡፡ እንደ ምሳሌ የአሳማ ሥጋን እንመልከት፡-
ü  ትሪኪኖሲስን (አሳማ ሥጋ ውስጥ በሚገኝ ትል የሚመጣ የጡንቻ እብጠት፣ ማቅለሽለሽ ወዘተ) በሽታ ያሰራጫል፡፡
ü  እንዲበሉ በተፈቀዱት እንስሳት ውስጥ ያለው ስብ በቀላሉ ለመለየት በሚቻል መልኩ ነው፡፡ የአሳማ ስብ ግን የሚገኘው ሥጋው ውስጥ ተደባልቆ ነው፤ ለመለየት አስቸጋሪ ስለ ኾነ ያለው አማራጭ ዝም ብሎ መብላት ነው፡፡ ስብ ደግሞ ከካርቦ ሃይድሬትና ከፕሮቲን አንጻር ኹለት ዕጥፍ ካሎሪ ስላለው በቀላሉ በሰውነት ውስጥ ይከማቻል፡፡ ደጋግመው የአሳማን ሥጋ የሚበሉ ሰዎች ቶሎ የሚወፍሩትም ስለዚሁ ነው፡፡ የዚህ ሥብ አስቸጋሪነቱ ደግሞ በቀላሉ የማይፈጭ መኾኑ ነው፡፡ በመኾኑም ቅጥ ያጣ ውፍረት እንዲመጣ ያደርጋል፡፡
ü  ስብ ብዙውን ጊዜ ከኮሌስትሮል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኮሌስትሮል በዛ ማለት ደግሞ በቀላሉ የደም ግፊት እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ ደም ግፊት አለ ማለትም የደም ቀጂ ቧምቧ ጠባብ ስለሚኾን ልብ ከዓቅሟ በላይ በኾነ መጠን ደጋግማ ደም እንድትረጭ ትደረጋለች፡፡ ስለዚህ የልብ ድካም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በቀላሉ እንዲመጣ ያደርጋል፡፡
ü  የአሳማ ሥጋ ፎስፈረስ በተባለ ንጥረ ነገር የበለጸገ ነው፡፡ በሰውነታችን ውስጥ ፎስፈረስ ሲበዛ ደግሞ ለሪህ፣ ለቁርጥማት እንጋለጣለን፤ በእያንዳንዱ አከርካሪ አጥንት መካከል የሚገኘው ዲስክም በቀላሉ እንዲጐዳ ያደርጓል፡፡
ü  የአሳማ ሥጋ “ግሮውዝ ሆርሞን” በተባለ ንጥረ ነገር የበለጸገ ነው፡፡ ይህ እድገትን የሚያፋጥን “ሆርሞን” ደጋግመን በላን ማለት ሰውነታችን አለቅጥና አለቅርጽ እንዲያድግ ያደርጓል፡፡ መቀመጫ፣ አገጭ፣ እንዲሁም የተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ከመጠን በላይ ወጣ ወጣ እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ü  የአሳማ ሥጋ ጭንቀትን የሚፈጥር ንጥረ ነገር በውስጡ አለው፡፡
ü  በአሳማ ሥጋ ውስጥ የሚገኘው ኮሌስትሮል በቀላሉ የማይፈጭ ስለኾነ በትርፍ አንጀት ውስጥ ሔዶ የመከማቸት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በመኾኑም ለትርፍ አንጀትና ለሐሞት ጠጠር በሽታ ያጋልጣል፡፡ ትርፍ አንጀቷም ተቈርጣ ካልወጣች በስተቀር ሌላ መድኃኒት የላትም፡፡
ሌሎችን እንስሳትም እንደዚህ እያንዳንዳቸውን ብንመለከታቸው ካላቸው መንፈሳዊ መልእክት ባሻገር ለጤናችን እጅግ ጎጂ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ ስለዚህ እነዚህን እንስሳት እንዲህ አድርገን እየተመለከትን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ልንመዝንባቸው ይገባናል፡፡ ዳግመኛም እነዚህን እንስሳት ባለ መብላት ሐኪማችን እግዚአብሔር እን ደመከረን ማድረግ (አለ መብላት) ይገባናል፤ ርኵሳን ናቸው ብለን ሳይኾን ለጤንነታችን አደገኛ ስለ ኾኑ፡፡ 
አንዳንድ የወፍ ዝርያዎች /ዘሌ.11፥13-19/
በዚህ አንቀጽ የተጠቀሱት አዕዋፍ (ንስር፣ ገዲ፣ ዓሣ አውጪ፣ ጭላት፣ ጭልፊት፣ ቍራ በየወገኑ፣ ሰጎን፣ የሌሊት ወፍ፣ ዝዪ፣ በቋል፣ ጉጉት፣ እርኩም፣ ጋጋኖ፣ አሞራ፣ ወዘተ) በባሕርያቸው ንጥቂያን፣ ቅሚያን፣ ሌላዉንም ማጥቃት እንዲሁም ጥንብ ነገርን መብላት የሚወዱ ናቸው፡፡ በመኾኑም፥ ከተንኰል፣ ከንጥቂያ፣ ወንድምን ከመጉዳትና ከስግብግብነት ልንጠበቅ እንደሚገባን ሲያስተምረን አምላካችን እግዚአብሔር እነዚህን እንስሳት እንዳንበላ አዘዘን፡፡ “የሌሊት ወፍን አትብሉ” ሲል “የጨለማ ሥራን አትውደዱ” ሲል ነው፤ “የውኃ ዶሮን አትብሉ” ሲል  - አንገታቸው ቀጥ ያለ ስለ ኾነ - “አንገተ ደንዳናና ትዕቢተኞች አትኹኑ” ሲል ነው፡፡ “ሰጐንን አትብሉ” ሲልም “ራስን መግዛት ገንዘብ አድርጉ” ሲል ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በእነዚህ እንስሳት እንደ ምን እንደሚያስተምረን ታያላችሁን? መልካም! አሁን ደግሞ ከመንፈሳዊ መልእክታቸው ባለፈ ከጤናችን አንጻር እንያቸው፡፡ ፍትሐ ነገሥትም መልስ ይሰጠናል፤ እንዲህ ሲል፡- “… ይኸውም መርዝ ያላቸውን እንስሳት የሚነጣጥቁ አራዊትን ጥፍርና መውጊያ ያላቸውንና መርዞችን የሚመገቡ አራዊትን እነዚህን የመሳሰሉትን ከመብላት ከአትክልትም ወገን ቢበሏቸው አእምሮ የሚያጠፉትን አካል የሚያጐድሉትን እንድንከለከል ነው” /ፍት.ነገ.23፥807/፡፡
አራት እግርና ክንፍ ያላቸው ነፍሳት /ዘሌ.11፥20-25/
 በዚህ አንቀጽ እንዳይበሉ የተከለከሉት ነፍሳት ኹለት ነገርን ማሟላት አለባቸው፡፡ አንደኛው አራት እግር ያላቸው ሲኾን፥ ኹለተኛ ደግሞ መብረር የሚችሉ ናቸው፡፡ አራት እግር ኖሮአቸው መብረርም የሚችሉ ከኾኑ ደግሞ የኋለኛው እግራቸው ከፊተኛው እግራቸው ይልቅ ረጅም ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ ከሚካተቱት እንስሳትም ዝንብ፣ ንብ እንዲሁም የወባ ትንኝ ይገኙባቸዋል፡፡ ዝንብ ተስቦን፣ ተቅማጥን እና ኮሌራን ስታስተላልፍ፥ የወባ ትንኝ ደግሞ ወባንና ቢጫ ወባን ታስተላልፋለች፡፡ እነዚህን መብላት ደግሞ ምን ያህል አደገኛ ሊኾን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡  
በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት /ዘሌ.11፥29-30/
እነዚህ እንስሳት (ሙልጭልጭ፣ አይጥ፣ እንሽላሊት በየወገኑ፣ ዔሊ፣ አዞ፣ እስስት፣ ወዘተ) የምድርን ነገር ከማሰብ በቀር ሰማያዊ ነገርን ማሰብና ማሰላሰል ለማይችሉ ሰዎች አምሳል በመኾናቸው እንዳንበላቸው ታዝዘናል፡፡ እንደ ምሳሌም ዮሴፍንና የጴጢፋራ ሚስትን መውሰድ እንችላለን፡፡ የጴጢፋራ ሚስት እንደ በደረታቸው እንደሚሳቡ እንስሳት የምድርን ነገር የምታስብ ሴት ስትኾን ዮሴፍ ደግሞ ከዚህ ምድር ከፍ ብሎ ሰማያዊ ምሥጢርን አንድም ሊመጣ ያለውን ዘለዓለማዊ ሕይወቱን ዘወትር የሚያስብ የሚያሰላስል ሰው ነው፡፡ እኛስ ማንን እንመስላለን? የጴጢፋራ ሚስት ወይስ ዮሴፍን?
ከጤና አንጻርም እነዚህ በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት በምድር ላይ የወዳደቁ ቆሻሻ ነገሮችን የሚበሉ ስለ ኾኑ እጅግ አደገኛ በሽታዎችን ያስተላልፋሉ፡፡ በመኾኑም እግዚአብሔር ባወቀ እንዳይበሉ በማዘዝ ሕዝቡን ከበሽታ ሲታደግ ኑሯል፡፡ እኛም እንደ ቃሉ የምንሔድ ከኾነ ሊመጡ ከሚችሉ አደገኛ የጤና መታወኮች እንጠበቃለን፡፡
ተወዳጆች ሆይ! በዚህ ዕለት የተፈጠሩትን ፍጥረታት እያንዳንዳቸውን ልብ ብለን ብንመለከታቸው እጅግ እንደነቃለን፡፡ የእኛንም ስንፍና እጅግ ያስገርመናል፡፡ እስኪ ጉንዳኖችን እንመልከታቸው! ጉንዳን በክረምት አይንቀሳቀስም፤ ዝናብ ነውና፡፡ በመኾኑም ቀለቡን የሚሰበስበው በጋ ላይ ነው፡፡ ይኸውም ለመንግሥተ ሰማያት ስንቅ የሚኾነንን ምግባር ትሩፋት በዚህ ዓለም ሳለን ልንሰበስብ እንደሚገባን ሲያስተምሩን ነው፡፡ ቀበሮ በሰውነቷ ላይ ቁስል ቢወጣባት የጥድ ዛፍ ወዳለበት ሔዳ ከጥዱ ከሚወጣው ፈሳሽ አድርጋ ቁስሏን ታደርቃለች፡፡ እባብ ራሷ በሰውነቷ ላይ ቁስል ቢወጣባት ቁንዶ በርበሬን በመብላት ከዚያ ቁስሏ እንደምትድን ታውቃለች፡፡ ውሻ ለባለቤቱ እንዴት ታማኝ እንደ ኾነ ኹላችንም እናውቃለን፡፡ እንግዲህ አእምሮ ለብዎ አለን ብለን የምናስብ እኛ ክርስቲያኖች ምን ያህል ከእነዚህ እንስሳት አንሰን እንደምንገኝ ታያላችሁን? እነዚህ እንስሳት እንዲህ እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ከመጀመሪያውኑ የሰጣቸው ተፈጥሮ ነው፡፡ ለእኛም እግዚአብሔርን የመምሰል ክሂለ ከዊን ገና ስንፈጠር ተሰጥቶናል፡፡ ኃጢአት ሕመም ነውና የበሽታ ጎጂነትን ለማወቅ ምንም አስተማሪ አያስፈልገንም፡፡ ነገር ግን እንዲህም ኾኖ - ማለትም አስተማሪም ተሰጥቶን - እንኳን ከእነዚህ እንስሳት አንሰን ራሳችንን ስንጎዳ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ እጅግ ቢያሳፍርም በክብር ከእኛ ከሚያንሱ እንስሳት እንማርና እንመለስ! ከወደቅንበት እንነሣ፡፡ ይህን ያደረግን እንደ ኾነም ቸሩ እግዚአብሔር ርስቱን መንግሥቱን ይሰጠናል፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በእውነት ያለ ሐሰት ክብር፣ ኃይልና ጌትነት የባሕርይ ገንዘቡ የኾነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ይህን እንድናደርግ ይርዳን፡፡ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ፤ አሜን!!!    

1 comment:

FeedBurner FeedCount