Pages

Friday, December 11, 2015

አዲስ መጽሐፍ በቅርብ ቀን


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 2 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ውድ የመቅረዝ ዘተዋሕዶ አንባቢያን! እንደ ምን ሰነበታችሁ? ላለፉት አምስት ሳምንታት ገደማ በመቅረዝ ላይ አዲስ ጽሑፍ ሳልለጥፍ በመቆየቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ እንዲህ የኾንኩበት ዋና ምክንያት ግን ላለፉት ስድስት ወራት ስተረጉመው የቆየሁትንና ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አያሌ መጻሕፍት አንዱ የኾነው የኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያ ቅጽ መጽሐፍን የመጨረሻዉን ቅርጽ ለማስያዝ ብሎም ወደ ኅትመት ለማስገባት በነበረብኝ ጫና ምክንያት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ በእኔ ዓቅም በብዙ ድካም የተተረጎመው ይህ አዲስ መጽሐፍ በቅርብ ጊዜ ወደ እናንተ ይደርሳል፡፡ ለማቆያ ያህልም ከመጽሐፉ መቅድም ከዚህ በታች አቅርቤላችኋለሁ፡-

(1) የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ በክርስቲያኖች ዘንድ የሕግ፤ በአይሁዶች ቶራ (ትምህርት ማለት ነው) በግሪኮች ደግሞ ፔንታቱክ (አምስት ጥቅል ማለት ነው) ተብለው ከሚታወቁት አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት የመጀመሪያው ነው፡፡
(2) አይሁዳውያን መጻሕፍቶቻቸውን የሚጠሯቸው ከመጽሐፉ የመጀመሪያው ቃል ተነሥተው ነው፡፡ በመኾኑም፥ ይህ መጽሐፍ ሲጀምር “በመጀመሪያ እግዚአብሔር …” ስለሚል “Pi – Rashet - በመጀመሪያ” ብለው ይጠሩታል፤ ኦሪት ዘጸአትንም፡- “የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው” ነው የሚሉት፡፡ በክርስቲያኖች ዘንድ ግን ኦሪት ዘልደት ወይም ኦሪት ዘፍጥረት ይባላል፡፡ ይኸውም በቀጥታ ከሰባ ሊቃናቱ ቅጂ የተወሰደ ነው፡፡ ሰባ ሊቃናቱም ይህን መጽሐፍ ኦሪት ዘልደት ያሉት፡- የሰማይና የምድር፣ የሰው ልጅ፣ የሰንበት፣ የጋብቻ፣ የኃጢአት፣ የመሥዋዕት፣ የትንቢት፣ የሰው ሥልጣን፣ የሀገራት እንዲሁም የሕዝበ እግዚአብሔር ልደት ስለሚናገር ነው፡፡
(3) አንድ ሰው ወደ እኛ መጥቶ፡- “መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ክርስትናን ለመማር ከየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መጀመር አለብኝ?” ብሎ ቢጠይቀን ብዙዎቻችን ከወንጌል እንደምንል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በጥንታዊቱ ቤተ ክርስቲያን ግን እንዲህ አልነበረም፡፡ የጥንቱ ክርስቲያኖች ንኡሰ ክርስቲያኖችን ለማስተማር የሚጀምሩት ከብሉይ ኪዳን - ከኦሪት ዘፍጥረት ነበር፡፡ ይኸውም፡- 
አንደኛ) መጀመሪያ ላይ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት አልተጻፉም ነበር፡፡ ሐዋርያት ቅዱሳት መጻሕፍትን ከጻፉ በኋላም ቢኾን ወዲያው ቀኖና ስላልተሠራላቸው ምእመናን እነዚህን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በአንድ ላይ ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡
ኹለተኛ) ወደ ክርስትና ይመጡ የነበሩት ንኡሰ ክርስቲያኖች ከይሁዲነትም ጭምር ቢኾኑም አብዛኞቹ ከአሕዛብ የሚመጡ ነበሩ፡፡ በክርስቲያን ወላጆች ያደጉም ቢኾን በዙሪያቸው ባለው የማኅበረ ሰብኡ አስተሳሰብ የተከበቡ ነበሩ፡፡ ክርስትና በአራተኛው መ.ክ.ዘ. ላይ ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጥቶት እንኳን ወይም ለክርስትና የወርቃማው ዘመን ሊቃውንት የነበሩበትና በደንብ የተስፋፋበት ጊዜ ቢኾንም እንኳን በሮማ ክፍለ ግዛት የነበረው አብዛኛው ሰው ግን በግሪክ ፍልስፍና የተከበበ ነበር፡፡ አንዳንዱ “ቁስ አካል ዘለዓለማዊ ነው” ይላል፤ ሌላው የአፍላጦንን ፍልስፍና ተከትሎ “ይህ ግዙፍ ዓለም የክፋት ውጤት ስለ ኾነ ክፉ ነው፤ መልካም የሚባለው ረቂቁ ዓለም ብቻ ነው” ይላል፤ ወይም ደግሞ እንደ ግኖስቲኮቹ፡- “ይህ ዓለም በእግዚአብሔር አልተፈጠረም” ይላል፤ አንዳንዱ “ነፍሳችን በተከፍሎ ከእግዚአብሔር የተገኘች ነች” ይላል፡፡ አንዳንዱ በመርቅያን ትምህርት ተታልሎ፡- “የሐዲስ ኪዳን አምላክ የብሉይ ኪዳኑ አምላክ አይደለም” ይላል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ከአሕዛብ ይመጡ የነበሩት ንኡሰ ክርስቲያኖች ከአይሁድ ከሚመጡት ይልቅ የግሪክ ፍልስፍናን ይማሩ ስለ ነበር በሥነ ፍጥረትና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እምነት የተለየ ነበር፡፡ ስለዚህ ዓለም አመጣጥ፣ ስለ እግዚአብሔር ማንነት፣ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮና የመሳሰለው ኹሉ ከክርስትና አስተምህሮ የተለየ ነበር፡፡
(4) ዛሬም ቢኾን ይህን አስተምህሮ የሚያራምዱ ሰዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሂንዲዩዝም፣ ሞርሞኒዝም “ብዙ አማልክት አሉ” ብለው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ የአዲሱ ትውልድ አማኞች የሚባሉም “ነፍስ የባሕርይ አምላክ ናት” የሚሉ ናቸው፡፡
(5) ዳግመኛም በብዙ ሳይንቲስቶች ዘንድ ይህ የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ “የሳይንስ ጸር” ነው፡፡ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ይህ በጣም ተደጋግሞ የሚነሣ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ልክ እንደ ጥንቱ ክርስቲያኖች አስቀድመን ከብሉይ ኪዳን መጀመራችን “በዚህ ዘመን ለምንኖር ክርስቲያኖች ትርጓሜ ኦሪትን ማጥናታችን ይኼን ያህል አስፈላጊያችን አይደለም” የምንለው ጉዳይ አይደለም፡፡
(6) በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድም ቢኾን አንዳንድ የተሳሳቱ አባባሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ሲሞት፡- “መሞት ያለ ነው፤ የሰው ሕይወት አንድ አካል ነውና” ማለት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እንደምንሞት እርግጥ ቢኾንም ሞት የእኛ ባሕርይ አይደለም፤ እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ስናየው፡- “ሰው አይደል?” እንላለን፡፡ ይህም ቢኾን ትክክል አይደለም፤ ምክንያቱም፡- “ኢይደሉ ትትኈለቍ ኃጢአት ኀበ ህላዌ አላ ኀበ ሕሊና - ኃጢአት የሕሊና እንጂ የባሕርይ ናት ልትባል አይገባም” እንዲል ኃጢአት ዝንባሌ እንጂ የባሕርይ አይደለችምና /ሃይ.አበ.ዘዮሐ. 52፥17/፡፡ ስለዚህ ይህንና የመሳሰሉ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን የምናርቀው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍን ስናጠና ነው፡፡
(7) ከላይ በቍ. 3 ላይ እንደተነጋገርነው በጥንታዊቱ ቤተ ክርስቲያን “ግዙፉ ዓለም ክፉ ነው” የሚል የግሪክ ፍልስፍና እጅግ የተስፋፋበት ጊዜ ስለ ነበር ወቅቱ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ በመኾኑም፥ ፈላስፎቹና ሌሎች መናፍቃን በዚህ ሐሳብ ተጽዕኖ ስር በመውደቅ ኹለት አካሔዶችን ይሔዱ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈረውን የሥነ ፍጥረት ትምህርት ጭራሽ አለመቀበልን ሲመርጡ፤ በሌላው ወገን የነበሩት ደግሞ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈረውን የሥነ ፍጥረት ትምህርት እንዳለ ከመቀበል ይልቅ ምሳሌያዊ የኾነ ትርጉምን በመስጠት ግዙፉ ዓለም የእግዚአብሔር ፍጥረት መኾኑን ይክዱ ነበር፡፡ ቃል (ሎጎስ)፣ መላእክት፣ ኤዎን (የብርሃን ፍንጣሪዎች) ምሳሌ ናቸው ይሉ ነበር፡፡ ይህን ሐሳብ በዋናነት የሚያራምዱት ግኖስቲኮች ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ግን ይህን ክሕደት አጥብቀው በመቃወም፡- “የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ በቅድሚያ ያለ ምንም ምሳሌያዊ ትርጉም ልንረዳው ይገባናል” ይሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያና ዲዲሞስ ዓይነ ስውሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊም ልክ እንደ እነርሱ የኦሪት ዘፍጥረትን መጽሐፍ መተርጎም ሲጀምር የሚጀምረው እንዲህ በማለት ነው፡- “በስድስቱም ቀን ሥነ ፍጥረት ኅብረ አምሳላዊ ነው ብሎ ማንም አያስብ፡፡ … ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ሲል ስለ አማናዊ ሰማይና ምድር እንጂ በእውነት ስለሌለ ሰማይንና ምድርን አይደለም…” /ገጽ 74/፡፡ ይህ ማለት ግን ጭራሽ ምሳሌያዊ ትርጉም የለውም ማለታቸው ሳይኾን “ቅድሚያ የሚይዘው ቀጥተኛው ትርጉሙ ነው፤ ምሥጢራዊ ትርጉሙ ከዚያ በኋላ ነው” ሲሉ ነው፡፡
(8) ኹሉም ኦርቶዶክሳውያን አባቶች እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ይህ ግዙፍ ዓለም ክፉ ወይም ርኩስ እንዳልኾነ ለመግለጥ የወልደ እግዚአብሔር ፍጹም ሰው መኾን፣ ሰው ኾኖ በእውነት በበረት መወለዱን፣ በእውነት መሰደዱን፣ መጠመቁን፣ መጾሙን፣ ማስተማሩን፣ መጸለዩን፣ መንገላታቱን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ በሦስተኛው ቀን መነሣቱን፣ በአርባኛው ቀን ማረጉን፣ ዳግም መምጣቱን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት መኾኑን አጽንተው የማስተማራቸው አንዱ ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ የክርስቶስን ሥጋዌ ስትናገር መናፍቃኑ እንደሚሉት ሳይኾን እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ምን ያህል ግንኙነት እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ ሥነ ፍጥረትን “ርኩስ ነው” ማለት የአካላዊ ቃል ሥጋዌን መካድ ነው፡፡ የአካላዊ ቃል ሥጋዌን መካድም ድኅነተ ዓለም አልተፈጸመም ማለት ነው፤ ሎቱ ስብሐት፡፡

(9) በመኾኑም፥ ይህ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ ወደ አማርኛ የመመለሱ ዋና ዓላማው፡-
አንደኛ፡- እግዚአብሔር ለመቍጠር ከሚታክቱ ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ ከሰው ጋር ያለው እጅግ የጠለቀ ፍቅር - ነገረ ሰብእ - እንዴት እንደ ኾነ ስለሚያሳይ፤
ኹለተኛ፡- በተለያየ ምክንያት በስሕተት ጎዳና - ለምሳሌ በዳርዊን ንድፈ ሐሳብ - ያሉትን ሰዎች እውነቱን ስለሚያስረዳ፤
ሦስተኛ፡- ሊቁ በሚሰጠው እጅግ ጠንካራ ተግሣጽና ምክር መንፈሳዊ ሕይወታችንን ከፍ ስለሚያደርግ፤
አራተኛ፡- የሥነ ፍጥረት ትምህርት ዋና ዓላማው በፍጥረታቱ ላይ እንድንመራመር፣ ወይም እንዲሁ ከነገረ ድኅነታችን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን ዕውቀት እንድናከማች ሳይኾን ሊቁ በሚያስተምረን መንገድ የተፈጠሩበትን ዓላማ እንድንመለከታቸው፣ ጥንት የነበሩበትም ኾነ አሁን ያሉበትን ኑባሬ እያየን እንድንማርባቸውና እንድንድንባቸው የተሰጡን እንደ ኾነ ስለሚያስተምረን ነው፡፡
የመጽሐፉ የእንግሊዘኛ ርእስ “The Fathers of the Church, St. John Chrysostom, Homilies on Genesis, Homilies 1-17 - የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ድርሳን 1-17” የሚል ሲኾን እኔ ግን ከኹለተኛው መጽሐፍ ክፍለ ትምህርት ዐሥራ ስምንትንም ጭምር ወደዚህ መጽሐፍ በማምጣት “ኦሪት ዘፍጥረት፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው፣ ክፍለ ትምህርት 1-18” በሚል ተዛማጅ ርእስ ተርጉሜዋለሁ፡፡ †

በተረፈ ይህ መልእክት ለብዙዎች ይደርስ ዘንድ አካፍሏቸው /Share አድርጉላቸው፡፡
ተጨማሪ መረጃ የሚፈልጉ ከኾነም በ0912 07 45 75 መደወል ይችላሉ፡፡
ክብር ኹሉ ለእግዚአብሔር ይኹን!!!

2 comments:

  1. የቅዱሳን አምላክ የአገልግሎት ዘመንህን ፣ይባርክልህ , ፍጻሜህን ያሳማርልህ , እኛም አንበን እንዲንኖርበት እሱ ይርዳን 

    አሜን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያስማልን መንግስተ ሰማያት ያውርስልን መጽሐፍን አንብበት ቃሉ ሕይወት እንዲሆነን ይርዳን፡፡ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፡፡

    ReplyDelete