Pages

Monday, February 22, 2016

ትንቢተ ዮናስ - ክፍል ኹለት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 14 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!


ምዕራፍ ኹለት


ዮናስ ወደ ባሕሩ ተጣለ፡፡ ኾኖም ይሞት ዘንድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነውና ይሞት ዘንድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የነነዌን ሰዎች እንዲያድናቸው ወዷልና ዮናስ የተጣለው እንዲሞት አይደለም፡፡ በሰዎች እይታ ዮናስ ለዚህ የተገባ አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ግን የተገባ ነው፡፡ አሁንም እግዚአብሔር ይወዷል፤ ልጄ ይሏል፤ የእኔ ነቢይ ብሎ ይጠራዋል፡፡ ምንም እንኳን ለወገኖቹ ለእስራኤል አዝኖ አልታዘዝ ቢልም፣ አለመታዘዙ ወደ ሌላ ኃጢአት እንዲገባ ቢያደርገውም አሁንም እግዚአብሔር ዮናስን ይፈልገዋል፡፡ ነነዌን ያድናታል፡፡ እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ ነው፡፡ እንደ እኛ ለፍርድ አይቸኩልም፡፡ ለመቅጣት አይቸኩልም፡፡ በወደቁ ልጆቹ ፈጥኖ አይፈርድም፡፡ ለፍርድ የምንቸኩለው እኛ ነን፡፡ ከወደቁ ሰዎች ጋር ያለን ግንኝነት ፈጥነን የምናቋርጥ እኛ ነን፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ጠባቂ ነው፡፡ በጣም ብዙ ጊዜ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ በትዕግሥት የሚጠብቀን ባይኾን እስከ አሁን ማን ይቆይ ነበር? ማን ቀና ብሎ ይሄዳል? የቆየነው እንጀራ ብቻ በልተን አይደለም፤ መድኃኒት ውጠንም አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ስለጠበቀን እንጂ፡፡ ስንበድል ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶን እንጂ፡፡ ስንቶቻችን መርዝ በጥብጠናል? ስንቶቻችን ገመድ አንጠልጥለናል? ስንቶቻችን ስለት ስለናል? እግዚአብሔር ግን ከዚያ ጠበቀን፡፡ አሁንምልጄ! እወድሃለሁ፤ ልጄ! እወድሻለሁይለናል፡፡

ዮናስ ወደ ባሕሩ ተጣለ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከታች እጁን አንጥፎለት ነበር፡፡ እኛ ስንወድቅ ሰይጣን ከስር ድንጋይ ያነጥፉብን ይኾናል፡፡ አፍቃሪያችን ግን ድንጋዩ እንዳይጐዳን ስለ እኛ የቆሰለው እጁን ያነጥፍልናል፡፡ ከክፉውም ኹሉ ይጠብቀናል፡፡ ዮናስ ወደ ባሕሩ ተጣለ፤ ኾኖም የእግዚአብሔር እጅ ተቀበለው፡፡ የማዕበሉ መነዋወጥ እንዳይጐዳው ተንከባከበው፤ አቀፈው፡፡ አንሥቶም በከርሠ አንበሪ አስቀመጠው፡፡ ዮናስን ይውጠው ዘንድ ትልቅ ዓሣ አዘጋጀለት፡፡ እንዲገድለው አይደለም፤ እንዲጠብቀው እንጂ፡፡ እንዲቀጣው አይደለም፤ እንዲጠለልበት እንጂ፡፡ ዮናስ ገባ፡፡ ብርድ የለም፤ ማዕበሉ አያስቸግርም፤ የነፋስ ንውጽውጽታ የለም፡፡ መርከቡ ላይ ከነበረበት ይልቅ አሁን እጅግ ተመቸው፡፡ ዓሣው ምንም ዓይነት ንጥረ ነገር (Enzyme) እንዳያመነጭና በሆዱ እንዳይፈጨው እግዚአብሔር አዝዞታል፡፡ ውሀ ከሌለበት ቦታ በነነዌ አንጻር እስኪተፋው ድረስ ይንከባከበው ዘንድ እግዚአብሔር አዝዞታል፡፡ ዓሣውም እግዚአብሔር የነገረውን ቃል ይጠብቅ ነበር፡፡ ዮናስ ውሀ ውስጥ ነው፡፡ ግን ትን አይለውም፡፡ እግዚአብሔር አስደናቂ የኾነ ቤት አዘጋጅቶለታልና፡፡
ዮናስ መጓዝ ጀመረ፡፡ በመርከብ አይደለም፤ በዓሣ፡፡ ዮናስ በከርሠ አንበሪ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አደረ፤ ኾኖም ዓሣው ዮናስን አልበላውም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አድሮ ሞት እንዳላሸነፈው፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔር ያዘጋጀልን ትልቅ ዓሣ ሲውጠን አንዘን፤ የምናማርርም አንኹን፡፡ ዮናስ እንዳደረገው በዓሣው ውስጥ ኾነን እግዚአብሔርን እናመስግን እንጂ፡፡ ዓሣው ቢውጠንም እንደማይጐዳን የምናምን እንኹን፡፡ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎ በእኛ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አያደርስም፡፡ በእግዚአብሔር ሲታዘዝ ዓሣው እኛን የሚተፋበት ጊዜ አለው፡፡ ፍቁራን ሆይ! በምንም ዓይነት መከራ ውስጥ ስንኾን የዮናስ አምላክ ከእኛ ጋር እንደኾነ እናስብ፡፡ እግዚአብሔር ይኸን ዓሣ (መከራው) ያዘጋጀው አንድ ቦታ (መልካም ምግባር) ላይ እንዲያደርሰን የተዘጋጀ መኾኑን እንመን፡፡አምላኬ ሆይ! ይህ የደረሰብኝ ነገር ምንድነው? ይኸ እንዲውጠኝ ያዘጋጀኸው ትልቅ ዓሣ ምንድነው? ስለምን አታድነኝም?” ብለን የምናማርር አንኹን፡፡ እግዚአብሔር የሚመልስልን መልስ አንድ ነው፡፡ ይኸውም፡- “ልጄ አትፍራ/! እኔ ከአንተ/ ጋር ነኝና አትፍራ/ሪ፡፡ ምንም እንኳን አንተ ዓሣው ውስጥ ብቻህን ያለህ ቢመስልህም እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትሸበር፡፡ ከቶ አልለይህምየሚል ነው፡፡ ስለዚህ በምንም ዓይነት ዓሣ ውስጥ ብንኾንም አንፍራ፡፡ከመከራ የሚሸሽ ከአምላኩ ይሸሻልየሚለውን የአባ ጳውሊ ቃል እናስታውስ፡፡
ዮናስ በትልቁ ዓሣ ውስጥ ራሱን አገኘው፡፡ ደነቀው፡፡ እጅግ በጣም በሚያምር ቪላ ቤት እንዳለ ቈጠረው፡፡ ከዚያስ ምን አደረገ? ወደ ራሱ ተመለሰ፤ ተንበረከከ፡፡ ለካስ እግዚአብሔር እንዲህ ዓሣ የሚያዘጋጅልን እንድንመለስ ነው፤ እንድንበረከክ ነው፡፡ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳያናግረው አኩርፎ ኰበለለ፡፡ ወዳጁ እግዚአብሔር ግን ልቡ ያመላለሰውን ኩላሊቱ ያጤሰውን ስለሚያውቅ እንዲህ ዓሣ አንበሪ አዘጋጀና እንዲያነጋግረው ቀረበ፡፡ ቀርቦምልጄ! ለምን ታኮርፋለህ? ወገኖችህ እስራኤል እኮ እነርሱ ስለተዉኝ እንጂ እኔ ትቻቸው አይደለም፡፡ እስኪ ንገረኝ? ስንቶቹ ነቢያቶቼን ገደሉብኝ? ስንቶቹን አሰቃዩብኝ? ስንቶቹንስ ገረፉብኝ? እኔ ለጥቅማቸው ብዬ እንዲህ ባደርግ ስለምን እንዲህ አደረጉብኝ? እንግዲያውስ እንታረቅይለው ነበር፡፡ ዮናስም ታረቀ፤ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ተመለሰ፤ አመነ፤ ከፊቱም ተንበረከከና አምላኩን ያመሰግነው ጀመር፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሣዊ ይህን አንቀጽ በተረጐሙበት ክፍል እንዲህ ብለዋል፡- በሕይወቴ እንዲህ ዓይነት ጸሎት አንብቤ አላውቅም፡፡ ዮናስ ከአምላኩ ፊት ከመኰብለሉ በፊት እንዲህ ቢጸልይ ኖሮ የደረሰበትን ኹሉ ባልደረሰበት ነበር፡፡ በእርግጥ መከራ የጸሎት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ዮናስበመከራዬ ሳለኹ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽኹ፤ እርሱም ሰማኝብሎ ሲጸልይ መደነቅ ይይዘኛል፡፡ እንዲህ ብዬም እጠይቃለሁዮናስ ሆይ! የምትናገረው ምንድነው? አሁን ያለኸው ዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ነው፤ ታድያ መቼ ነው አምላክህ ጩኸትህን የመለሰልህ? “አምላኬ ሆይ! ከመከራዬ ታድነኝ ዘንድ ወደ አንተ እጮኻለኹብትል አይቀልምን? ለካስ ዮናስ እንዲህ የሚያመሰግነው በኋላ የሚያገኘውን አሁን እንዳገኘው ቈጥሮ ነው /Contemplation on the Book of Jonah, By H.H. Pope Shenouda III, p. 34/፡፡


ዮናስ አስደናቂ የኾነ ጸሎቱን ቀጠለ፤ እንዲህ ሲል፡- “በጥልቁ ባሕር ውስጥ ሳለኹ አንድም በከርሠ አንበሪ ውስጥ ሳለኹ የልመናዬን ነገር ሰማኸኝ፤ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ጣልኸኝ፤ ውሆች ከበቡኝ፤ ማዕበሉና ሞገዱም ኹሉ በላዬ አለፈ፡፡ እኔም ከባለሟልነትህ እንደወጣኹ ቀረሁን አልኹ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ከአንበሪው ሆድ ወጥቼ ወደ ቤተ መቅደስህ እመለከታለኹ አልኹ፡፡እንዲህ እያለ ጸሎቱን አቀረበ፤ ጸሎት ብቻ ሳይኾን እንደሚወጣ አምኖ አመሰገነ፡፡ ስለኾነም ጸሎቱን እንዲህ በማለት ደመደመውውሀው ሰውነቴን እስከ ማስጠም ደርሶ ስርግርግ አደረገኝ፤ ከበበኝ፤ እነሆ ራሴ በተከፈለው ተራራ (በዓሣው አንጀቱና ጉበቱ) መካከል ነው፤ መልሕቅ በጣሉት ጊዜ ወደ ታች እንዲወርድ ወደ ጥልቁ ወረድኹ፡፡ አንተ ግን አምላኬ ሕይወቴን ከጥልቁ አወጣኻት፡፡ ሰውነቴ በመከራ እለይ እለይ ባለችብኝ ጊዜ አንተን አሰብኹ፡፡ ጸሎቴም በፊትህ ወደ መመስገኛህ ቦታ ወደ ጽርሐ አርያምህ ገባች፡፡ ከንቱ ነገርን፣ ሐሰት ጣዖትን የሚመለከቱ ሰዎች ግን አንተን ተዉ፡፡ እኔ ግን ከምስጋና ጋር በመገዛት እሠዋልኻለኹ፤ በከርሠ አንበሪ ሳለኹ ያመሰገንሁትን ያህል ከከርሰ አንበሪ ከወጣኹ በኋላ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አመሰግንሃለሁ፡፡እንዴት ያለ እምነት ነው? በኋላ ሊኾን ያለውን ነገር በተስፋ እጁ ውስጥ እንደገባ ይናገራል፡፡ የዮናስ እምነት በዚህ አስደናቂ ደረጃ ከደረሰ በኋላ እግዚአብሔር ዮናስን ውሀ ከሌለበት ቦታ ያወጣው ዘንድ አንበሪዉን አዘዘው፡፡ ዓሣውም ዮናስን በታዘዘው ሰዓት፣ በታዘዘው ቦታ ምንም ሳይጐዳ ተፋው፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን፡፡ ተወዳጆች ሆይ! አስቀድመን እንደተናገርን እንዲህ የምስጋናና የእምነት ሰዎች ከኾንን ዓሣው ምንም ሳይጐዳን በትክክለኛው ሰዓት፣ በትክክለኛው ቦታ ይተፋናል፡፡
ይቀጥላል

2 comments: