Pages

Thursday, March 3, 2016

“ሦስቱ የኃጢያት አለቆች” ማቴ ፬፥፩-፲፩



ዳዊት ተስፋይ
ከተክለ ሳዊሮስ ሰ/ት/ቤት
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 24 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
        ኃጢያት ኃጥአ አጣ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ማጣት ማለት ነው፡፡አንድ ሰው ኃጢያትን ሲሰራ እግዚአብሔርን ፣ እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ፣ ቅዱሳኑንና ፣ የከበረች መንግስቱን ያጣልና ኃጢያት ማጣት የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በዓለም ላይ ብዙ አይነት ኃጢያቶች ቢኖሩም እናታችን ቅድስት ቤ/ክ ኃጢያቶች ሁሉ ሦስት አለቆች እንዳሏቸው ታስተምራለች፡፡ እነዚህም ስስት ፣ ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃጢያቶች ‹‹አለቆች›› መባላቸውም የሁሉም ኃጢያቶች መገኛ ስለሆኑና እነዚህን ሦስቱ ኃጢያቶች ድል ያደረገ ሌሎቹንም ኃጢያቶች ድል ያደርጋልና ነው፡፡ ለዛሬ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ‹‹ሦስቱን የኃጢያት አለቆች›› እንዴት ድል እንዳደረጋቸውና እኛም እንዴት ድል ልናደርጋቸው እንደምንችልና እንዲሁም ታሪኩ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ምን ትምህርት እንደምናገኝበት የቅዱሳን አባቶቻችንን ትርጓሜ መነሻ አድርገን በአጭሩ እንነጋነጋለን፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ታሪኩን እንዲህ እያለ መተረክ ይጀምራል፡- “ማቴ ፬፥፩ ከዚህ በኋላ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ጌታችንን ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ ወሰደው ፤ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ ፤ ከዚህም በኋላ ተራበ ”፡፡

በዚህች ዓረፍተ ነገር ውስጥ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ቁምነገሮች ስላሉ እያንዳንዱ ቃል ከጀርባው የያዘውን ምሥጢር እንድንረዳ አንድ በአንድ ለማይት እንሞክር፡፡
፩.“ ከዚህ በኋላ ” ሲል፡-
ከተጠመቀ በኋላ ልዋል ልደር ሳይል ዕለቱን ወደ በረኃ መሄዱን ለመግለጽ ነው፡፡ዕለቱን እንደ ተጠመቀ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ  መሄዱም “እናንተም እንደተጠመቃችሁ ነገ ዛሬ ሳትሉ መንፈሳዊ ተጋድሎ ጀምሩ” ሲለን ነው፡፡“ኦርቶዶክሳውያን የምንጠመቀው በሕጻንነታችን ነው እንዴት በዚያ ጊዜ መንፈሳዊ ተጋድሎ ልንጀምር እንችላለን?” የምንል ሰዎች እንኖራለን፡፡ “እናንተም እንደተጠመቃችሁ ነገ ዛሬ ሳትሉ ተጋድሎ ጀምሩ” የሚለው ኃይለ ቃል የተነገረው፡-
፩.፩. ለንዑሰ ክርስቲያን፡-  እንደሚታወቀው ንዑሰ ክርስቲያን የሚባሉት ከጣዖት አምልኮ ወይም ከሌሎች የእምነት ድርጅቶች መጥተው የቤ/ክ ትምህርት ተቀብለው ለመጠመቅ እየተማሩ በዝግጅት ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ንዑሰ ክርስቲያን እንደተጠመቁ አንደአቅማቸው ተጋድሎ ይጀምራሉ እንጂ “መቼ በደንብ ተማርኩ ?” እያሉ ከተጋድሎ ሊሸሹ አይገባም ሲል ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም እንደተጠመቁ ተጋድሎ የጀመሩ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡-የሐር ሻጯዋ ልድያ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት እንዳመነች “ሐዋ ፲፮፥፲፫ ለእግዚአብሔር አማኝ ካደረጋችሁኝ ወደ ቤቴ ገብታችሁ እደሩ” በማለት በተጠመቀችበት ቀን ልዋል ልደር ሳትል ቅዱሳኑን በማሳደር አገልግሎቷን(ተጋድሎዋን) ስትጀምር ፤ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ የታሰሩበትን እስር ቤት ይጠብቅ የነበረው መቶ አለቃም እንደተጠመቀ የቅዱሳኑንን እግር በማጠብና ማዕድ በማቅረብ አገልግሎቱን ጀምሯል፡፡‹‹ሐዋ ፲፮፥፳፫—፴፬ ወዲያውኑም በሌሊት ወስዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው እርሱም በዚያው ጊዜ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር ተጠመቁ፡፡ ወደ ቤቱም አስገብቶ ማዕድ አቀረበላቸው”እንዲል፡፡
፩.፪. ለኦርቶዶክሳዊያን፡- ደግሞ በትምህርት(በቃለ እግዚአብሔር) ዳግመኛ የሚወለዱ ክርስቲያኖች አምላካቸውን እንዳወቁ ዕለቱን መንፈሳዊ ተጋድሎ መጀመር አለባቸው ሲል ነው፡፡ ነገር ግን በስንፍና “ዛሬ ልተኛ ነገ እጸልያለሁ፣ የአሁኑን ጾም ልብላ በሚቀጥለው እጾማለሁ ፣ ዛሬ ኃጢአት ልሥራ ለወደፊቱ ንስሐ እገባለሁ ›› ሊሉ አይገባም ፤ ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል “ የመዳን ቀን ዛሬ ነውና፡፡
፩.፫. በ፵ በ፰ ለሚጠመቁ ሕጻናት ፡- “እናንተም እንደተጠመቃችሁ ነገ ዛሬ ሳትሉ ተጋድሎ ጀምሩ” የሚለው ቃል ሕጻናትንም ይመለከታል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ሥርዓት መሰረት አንድ ሕጻን በሚጠመቅበት ዕለት ሦስት ታላላቅ ምስጢራትን ይፈጽማል፤ እነርሱም ምሥጢረ ጥምቀት፤ ምሥጢረ ሜሮን፤ ምሥጢረ ቁርባን ናቸው፡፡ ሕጻናቱ ለጥምቀት ከመቅረባቸው በፊት የእናታቸውን ጡት ሊጠቡ ይችላሉ፤ ምሥጢረ ጥምቀትን ከፈጸሙ በኋላ ግን ምርር ብለው ቢያለቅሱ እንኳን እስከ ቁርባን ድረስ የእናታቸውን ጡት አይጠቡም፤ ይህም እንደ ጾም(እንደተጋድሎ) ይቆጠርላቸዋል፡፡ ታዲያ ኦርቶዶክሰውያን መንፈሳዊ ተጋድሎን በሕጻንነታችን ጀመርን ማለት አይደለም? መናፍቃን በግልጽ ባይናገሩትም በኦርቶዶክሳውያን ከሚደነቁባቸው ነገሮች አንዱ ኦርቶዶክሳውያን  “እንዴት አድርገው ነው በዓመት ከ፪፻ ቀናት በላይ የሚጾሙት?›› የሚል ነው፡፡ ለዚህ መልሱ ቀላል ነው የመጀሪያው በጥምቀት የምናገኘው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከላይ ለመግጽ እንደተሞከረው ኦርቶዶክሳውያን ተጋድሎን በሕጻንነታችን ስለምንጀምር ነው፡፡
. “ መንፈስ ወሰደው ”
ሲል ምን ለማት ነው? መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ነፍስ›› ‹ሰው›› ‹‹ሓሳብ›› በሚሉም ትርጉሞች ቢፈታም ከትምህርታችን አውድ ላለመውጣት በሁለት መልኩ ተርጉመን እንመለከተዋለን፡፡
፪.፩.መንፈስ የተባለው ፈቃዱ ነው ፡- የራሱ ፈቃዱ አነሳሳስቶት(በራሱ ፈቃድ) ወደ በረኃ ወረደ ሲል ነው፡፡ ይህም ጌታችን ሁሉን ነገር በፍቃዱ እንደሚያረግ ሲያስተምረን ነው፡፡ዮሐ 10፤18
፪.፪. መንፈስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው ፡- መንፈስ ቅዱስ ወደ በረኃ ወሰደው ሲል ነው፡፡ ይህ ማለት ግን መንፈስ ቅዱስ ሰማዕታትን አነሳስቶ ወደ ደም ፤ ጻድቃንን አነሳስቶ ወደ ገዳም እንደሚወስደው ያለ ግን አይደለም፡፡ታዲያ ለምን “መንፈስ ወሰደው” አለ? ቢሉ ሦስቱ አካላት በባሕሪይ አንድ ከሚያረጓቸው ነገሮች አንዱ በፍቃድ አንድ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ማለት ከሦስቱ አካላት አንዱ በራሱ ፍቃድ ብቻ የሚሰራው ነገር የለም፡፡ ታዲያ ለምን ለይቶ መንፈስ ቅዱስን ብቻ ጠራ ቢሉ ? ቅዱሳን መጻሕፍት ረቂቅ የሆነ ነገር ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥቶ መናገር ልማዳቸው ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-‹‹ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስን ይመራዋል›› ስንል በጉባዔው አብና ወልድ የማይገኙ ሆነው አይደለም ፤ የረቀቀ ነገር ለመንፈስ ቅዱስ መስጠት ልማድ ስለሆነ እንጂ፡፡ ‹‹ ሉቃ ፩;#5 መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል›› ሲልም ተመሳሳይ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወሰደው ሲባልም በፈቃድ አንድ ናቸውና በአብ፣በወልድ፣በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ወደ በረኃ ሄደ ለማለት ነው፡፡
፫.“ ጾመ ” ሲል ፡-
አንድ ኦርቶዶክሳዊ ቢፆም እቀደስ እከብር ብሎ ወይም ሥርየተ ኃጢያተ ወይም ፍትወታት እኩያትን ድል የሚደርግበት ኃይል አገኛለሁ ብሎ ነው፡፡ ጌታችን ግን መጠመቁ ለምን ይሆን ? ‹‹እቀደስ ብሎ ነው ›› እንዳንል ክብር ይግባውና በባሕሪው ቅዱስ ነው ፤ ኃጢያት ለባሕሪው የማይስማማ ነው፡፡ እንዳንዷን ጥቃቅን ነገር የሚከታተሉት ፈሪሳውያን እንኳን ‹‹ ዮሐ 10 ከእናንተ መካከል ስለኃጢያት የሚወቅሰኝ ማነው?›› ባላቸው ግዜ ‹‹ ስለመልካም ሥራህስ አንወግርህም ሰው ስትሆን እራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው ›› ማለታቸው ጌታችን ምንም ኃጢያት እንዳልሰራና እንደማይሰራ ያሳየናል ‹‹ የተላት ምስክር የተማነ ነው›› እንዲል፡፡ ‹‹ እከብር ብሎ ነው ›› እንዳንል ክብር ይግባውና እርሱ የባሕርይ አምላክ ስለሆነ ከዚህም በላይ ክብር ስለሌለ ሌላ ክብር የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ በአስሩ ቅዱሳን ማዕረጋት ከነፅሮተ ሥሉስ ቅዱስ የበለጠ ማእረግ አለመኖሩ ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን እግዚአብሄርን ከማየት የበለጠ ጸጋ ስለሌለ ነው፡፡ ታዲያ እግዚአብሄርን ከማየት የበለጠ ጸጋ ከሌለ እግዚአብሔር ከመሆን የበለጠ ክብር ወዴትአለ ?
v ታዲያ ጌታችን ለምን ጾመ ?
ጌታችን መጾሙ የሚያገኝው ጥቅም ኖሮ ሳይሆን ሥርዓት ሲሰራልን ፡፡ጌታችን እርሱ ሳያደርግ አድርጉ ብሎ ያዘዘን አንድም ትእዛዝ የለም፡፡ ሁሉንም አድርጎ ነው ‹‹አድርጉ›› ያለን፡፡ የሌሎች እምነት ድርጅቶች መስራቾች ግን ከዚህ በተቃራኒ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እነርሱ በሰይፋቸው የብዙ ምስኪኖችን ደም እያፈሰሱ ‹‹ አንድ ሰው መግደል ዓለምን እንደማ ጥፋት ይቆጠራል ›› እያሉ የሚያሾፉ ፤‹‹ ሕገ እግዚአብሔር ስለተጣሰ ከሰብዓ እሮምያ(ተገቢ ባይሆንም በዘልማድ ካቶሊክ) ተገነጠልን ›› እያሉ እለት ዕለት ግን እናቱንና ቅዱሳኑን በመሳደብ ታላላቅ ህጎችን የሚያፈርሱ ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚቆነጻጽሉ ልበ ደንዳኖች ፤ በመጻሕፍቶቻቸው ‹‹ በንጽህና በቅድስና ኑሩ ›› እያሉ እነርሱ ግን ባሉት የማይገኙ ሐኬተኛ አገልጋዮች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ስለዚህ ጌታችን መጾሙ እውነተኛ መምህር ነውና ጾሞ ጹሙ ሲለን ነው፡፡
፬. “ ለምን በምድረ በዳ ጾመ ? ”
ጌታችን በከተማ በቤተ መቅደስ ሆኖ መጾም ሲችል በበረኃ መጾሙ ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡-
፩. አድምና ሔዋን ከዚህች ምድር ርቃ በምትገኝ በገነት ሳሉ በዲያብሎስ ድል ተነስተዋል ፤ ጌታችንም ከከተማ ርቃ በምትገኝ በምድረ በዳ ዲያብሎስን ድል ሊያደርግላቸው ብሎ አንድም
፪. ጌታችን በጥምቀቱ ጥምቀታችንን በስደቱ ስደታችንን ባርኮ እንደሠጠን የብህትውናንና የምንኩስናን ሕይወት ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን ወዶ በበረሃ ጾመ፡፡
፭. “፵ ቀንና ሌሊት ለምን ጾመ?”
ጌታችን ከፍ ብሎ ፵፩ ዝቅ ብሎ ፴፱ ቀናት ሳይጾም ፵ ቀናት የጾመበት ምክንያት ምንድን ነው፡፡
፩. ሙሴ አርባ ቀን ጾሞ በሲና ተራራ ፲ሩን ትዕዛዛት እንደ ተቀበለ እናንተም ፵ ቀን ብትጾሙ ከእግዚአብሄር ስጦታ ትቀበላላችሁ ሲለን
፪. ኤልያስ አርባ ቀን ጾሞ ብሔረ ሕያዋን እንደገባ እናንተም ፵ ቀን ብትጾሙ ገነት መንግስተ ሰማያት ትገባላችሁ ሲለን አንድም
፫. ዕዝራ ፵ ቀን ጾሞ ምስጢራት እንደተገለጡለት እናንተም ፵ቀን ብትጾሙ ምሥጢራት ይገለጽላችኋል ሲለን ነው፡፡

ጌታችን ፵ቀናትን ብቻ ጾሞ ሳለ እኛ ለምን ፶፭ ቀናትን እንፆማለን ?
፩. ከፊት ጾመ ሕርቃልን አንደ ሳምንት ከኋላ ለህማማቱ መታሰቢያ የሚሆን አንድ ሳምንት ስለተጨመረ፡-ጾመ ሕርቃል መጨመሩ የጌታችን መስቀል በእየሩሳሌም በነበረ ጊዜ ፋርሶች ከእሩሳሌም ማርከው ወስደውት ነበርና ንጉስ ሕርቃል ከእየሩሳሌም ካህናትና ምዕመናን ጋር ተነጋግሮ ተዋግቶ መስቀሉን ስላስመለሰ ለመታሰቢያ እንዲሆን የሚጾም ሲሆን ፤ ለህማማት አንድ ሳምንት መጨመሩም ኦርቶዶክሳውያን የጌታችንን ሕማምና መከራ ዘወትር ማሰብ እንደሚገባን ቤ/ከ ብታስተምረንም ከሌሎችም ግዜ በበለጠ እንድናስበው የተሰራልን ደገኛ ስርዓት ነው፡፡
፪.በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲን ሥርዓት ቅዳሜና እሁድ ከጥሉላት መባልእት ብንጦምም እንደ ሌሎች ቀናት እስከ ፱ሰዓት አይጾምም ምክንየቱም ቅዳሜ ስድስት ቀናትን ፈጥሮ ያረፈበት ስለሆነ ፤ እሁድ ደግሞ የትንሳኤው፣ የፅንሰቱ፤ እንዲሁም ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋሪያት መላኩ የሚታሰብበት ስለሆነ እስከ ምሽት አንጾምባቸውም፡፡ በዚህ መነሻነት ከምንጾማቸው ፵ቀናት ውስጥ ፩፭ቱ ቀናት ጥሉላት መባልእት ባንበላባቸውም ስለማንራብባቸው እነዚህን የሚተኩ ፩፭ቀናት ስለሚጨመርባቸው በአጠቃላይ የጾሙ ጊዜ ፶፭ ቀናት ይሆናሉ፡፡ እዚህ ጋር ግን ሁልጊዜ ግርም የሚለኝ በጌታችን ስም የሚጠራ አንድ ጾም እንኳን የሌላቸው መናፍቃን ጨምረን በመጾማችን ሊያደንቁ ሲገባ ለጌታችን ተቆርቋዋሪ በመምሰል ‹‹ እንዴት በጌታ ጾም ላይ ፲፭ ቀናትን ትጨምራላችሁ ›› ብለው መጠየቃቸው ነው፡፡
፫. አቢይ ጾም ጌታችን የጾመው በመሆኑ ቅድስት ቤ/ክ ሌሎች ቅዱሳን ከፆሙት ፆም የተለየ መሆኑ ልታስተምረን ከፊቱ አንድ ሳምንት ከኋላው አንድ ሳምንት በማድረግ በአጃቢ ስለምትቀበለው ነው፡፡
፮.“ ተራበ ”፡-
ይህ ቃል የተነገረው ለፍጡራን ቢሆን ምንም አያስደንቅም ፤ ነገር ግን ግዙፋኑንና ረቂቃኑን ፍጥረታት ሁሉ የሚመግብ እግዚአብሔር ተራበ ሲባል እጅግ ያስደንቃል፡፡‹‹መዝ ፻፫ ፤ ፳፯-፳፰ ምግባቸውን በየግዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ ፤ በሰጣሃቸውም ጊዜ ይሰበሰባሉ እጅህን ፈትተህ ከቸርነትህ የተነሳ ሁሉን ታጠግባለህ›› እንዲል፡፡ ጌታችን የተራበው እንደኛ በማጣት ሳይሆን በፈቃዱ ነው፡፡በፈቃዱ መራቡም ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው ፡-
፩. ለካሣና፡- አዳም በመብል ምክንያት ከገነት እንደወጣ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም ካሳ እንዲሆን ተራበ
፪. ለአፅድቆተ ትስብዕት፡- ጌታችን ከተዋህዶ በኋላ አምላክም ሰውም ነው፡፡ በተዋሕዶ የቃል ገንዘብ ለሥጋ ፤ የሥጋ ገንዘብ ደግሞ ለመለኮት ሆንዋል፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ለአይን ጥቅሻ ለከንፈር ንክሻ ያክል እንኳ መለያየት የለም፡፡ ጌታችን ፵ ቀን ጾሞ ‹‹ተራበ›› የሚለው ቃል ባይጻፍ እንደተለመደው አስቀድመን የጠቀስነው አማናዊ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን በመቃወም ‹‹ጌታችን ሥጋን አልተዋኃደም ፤ ምትሐት ነው ›› የሚሉ መናፍቃን ይነሳሉና እንዲህ አለ፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ጌታችን “ተራበ” መባሉ ጾም ማለት ጊዜ ጠብቆ መብላት ብቻ ሳይሆን ረሃብ ድካም ሲሰማን መብላት እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፡፡ ሁሉም ነቢያት ጾማቸው ረሓብና ድካም ያልተለየው መሆኑም መነሻው ይሄ ነው፡
፩.ስስት
‹‹ ማቴ. ፬፥፫ የሚፈታተነውም ቀርቦ ‹ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክስ እነዚህን ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ ›› በማለት ሰይጣን የመጀመሪያውን ፈተና ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የባሕሪ አባቱ በሰማይ ሆኖ “ የምወደው ልጄ ” ሲል ሠምቷልና ‹‹ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ›› አለ፡፡ ዮሴፍ የወንድሞቹን  ምግብ ይዞ በተራበ ጊዜ እግዚአብሔር ድንጋዩን ዳቦ አድርጎ እንዳበላውም ያውቃልና ‹‹እነዚህን ድጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ ›› አለው፡፡ዲያብሎስ በሁለቱም በኩል አሸናፊ የሚያደርገውን ፈተና ይዞ ነው የቀረበው፡፡ ይኸውም ‹‹ ‹ እንዳልኩት ድንጋዩን ወደ ዳቦ ቢለውጥ የሰይጣን ታዛዥ ብዬ አስነቅፈዋለሁ ፤ እምቢ ቢለኝ ደግሞ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ድንጋዩን ዳቦ አድርጎ አብልቶታል፤ ይህ ግን እግዚአብሔር አይደለምና እምቢ አለ› ብዬ አምላክነቱን አጠራጥራለሁ” የሚል ነው፡፡ ዲያብሎስ ብዙ ጊዜ ለተፈታኙ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ለፈታኙ(ለራሱ) ደግሞ በሁለቱም በኩል ድል ሊያስገኙ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎችን በአይሁድ እያደረ ለጌታአችን አቅርቧል፡፡ ለምሳሌ፡- “ሉቃ፳፥፳-፳፮ እነርሱም እንዲህ ብለው ጠየቁት ‹‹ መምህር ሆይ አንተ እውነት እንደምትናገርና እንደምታስተምር ፊት አይተህም እንደማታዳላ የእግዚአብሔርንም መንገድ በቀጥታ እንደምታስተምር እናውቃለን፡፡ ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባል ? ወይስ አይገባም? ተንኮላቸውንም አውቆ ‹ ለምን ትፈትኑኛላችሁ ? ገንዘቡን አሳዩኝ › አላቸው፡፡ አምጥተው አሳዩት ‹ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው፡፡ እነርሱም ‹የቄሳር ነው › ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም የቄሳርን ለቄሳር ፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ › አላቸው፡፡ በህዝቡም ሁሉ ፊት በአነጋገሩ ማሳሳት ተሳናቸው መልሱንም አድንቀው ዝም አሉ፡፡ ” ተመልከቱ አሁን ጌታችን ገብሩ ቢላቸው የሚገብሩ አትገብሩ ቢላቸው መገበራቸውን ሚተው ሆነው አይደለም፡፡ነገር ግን ‹‹ገብሩ›› ቢል ‹‹ ለጣላቶቻችን ገብሩ ይላል ›› ብለው ሀገራቸውን ከሚወዱ ከአይሁዳውያን ጋር ለማጣላት ፤ ‹‹አትገብሩ›› ቢል ከሮማውያን ለማጣላት እንዲህ አሉ፡፡ በዮሐንስ ወንጌልም ተመሳሳይ ታሪክ እናገኛለን፡፡ “ዩሐ ፰፥፮-፲፩ እንዲህ አሉት ‹ መምህር ሆይ ይህቺን ሴት ስታመነዝር አግኝተን ያዝናት እንደዚህችም ያለችውን በድንጋይ እንድትደበደብ ሙሴ በኦሪት አዘዘን ፤ እንግዲህ አንተ ስለእርስዋ ምን ትላለህ ? በእርሱ ምክንያት ሊያገኙ ሲፈትኑት ይህን አሉ፡፡››  ይህን ማለታቸው ከላይ ካየነው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹‹ ትወገር ›› ቢል ‹‹የፍቅር ሕግ አመጣ ትላላችሁ ይኸው ትወገር እያለ አይደለምን ›› ብለው ኃጥአንን ከእርሱ ለመለየት፤ ‹‹ አትወገር ›› ቢል ‹‹ የሙሴን ህግ ሻሪ ›› ብለው ያመኑ አይሁድን ከእርሱ ለመለየት ነበር፡፡ ጌታችንም ተንኮሉን ያውቃልና በስስት የመጣበትን ሰይጣን “ ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተብሎ ተጽፏል ” በማለት በትዕግስት ድል አድርጎታል ዘዳ.፰፥፫፡፡
        ከዚህ በተጨማሪ ሌላው ማስተዋል ያለብን ዲያብሎስ ጌታችን የፈተነው በ፳ኛው በ#ኛው ቀን ሳይሆን በ፵ኛው ቀን በኃላ በተራበ ጊዜ ነው፡፡ይህም ሰይጣን ሰዎችን ፈትኖ ለመጣል ምቹ ጊዜ እንደሚጠብቅ ያስገነዝበናል፡፡ ጌታችን ጾሙን እንደ ጀመረ በምግብ ቢፈትነው በወቅቱ ረሃበ ሥጋ ስላልተሰማው “እሺ በጄ” አይለኝም ብሎ ፈተናውን ለጊዜው አዘገየ፡፡፵ ቀኑን ፈጽሞ በተራበ ጊዜ ግን ዳቦ ይዞ ቀረበና “ብላ” ብሎ ፈትኖታል፡፡ዛሬም ዲያብሎስ እኛን በኃጢአት ለመጣል ጾሙ ተፈቶ እንደፈለግን ያለልክ መባላት እስክንጀምር ምቹ ጊዜ ይጠብቃል፡፡  ሰይጣን ፀሎትን ይጠላልና  ጸሎታችንን እንድናቆም ብዙ ጥረት ያደርጋል፡፡ነገር ግን ፆም ላይ በመሆናችን እንቢ ብንለው ጾሙ አልቆ በመንፈሳዊ ህይወታችን የምቀዛቀዝበትን ምቹ ጊዜ ይጠብቃል፡፡ምቹ ግዜ ሲያገኝም ጠጋ ብሎ “ዛሬ ተኛና ነገ ትጸልያለህ” እያለ በህሊናችን ይመክረናል፡፡እኛም እሺ እንለዋለን፡፡ስለዚህ እስካሁን በኃጢአት ባለመውደቃችን ፆም ጸሎት ባለመተዋችን ልንደሰት አይገባም ፤ ምናልባት ሰይጣን “ምቹጊዜ” እየጠበቀልን ይሆናልና፡፡ ‹‹ ሉቃ፳፪ ፥ ፩-፮ ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር፡፡›› እንዲል
፪. ትዕቢት
      ሰይጣን በስስት ጌታችን ፈትኖ  ድል ቢደረግም ተስፋ ሳይቆርጥ  እንዲህ እያለ በትዕቢት ይፈትነው ጀመር፡፡
“ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ መቅደስ ጫፍ ላይ አቆመው፡፡ አንተ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ከዚህ መር ብለህ ወደታች ውረድ ይጠብቅህ ዘንድ ስለ አንተ መላእክቱን ያዝዝልሃል እግርህም በድንጋይ እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሱሀል ተብሎ ተጽፏል አለው ፡፡ ”
፪.፩. “… ወሰደው…”  ፡- ሲል ሰይጣን ጌታችንን የሚወስደው ሆኖ ሳይሆን ፈቃዱን አውቆ ሔደለት ሲል ነው፡፡ የሰይጣን ፈቃድ ምን ነበር ? ቢሉ ‹‹ በመጀመሪያው ፈተና ድል ያደረገኝ በበረሃ ስለሆነ ነው እነጂ ካህናትን ድል በምነሳበት በቤተ መቅደስ ቢሆን መች ድል ይነሳኝ ነበር ›› የሚል ስለነበር ይህን ፈቃዱን አውቆ ምክንያት ለማሳጣት ወደ ቤተመቅደስ ሔዷልና ‹‹ ወሰደው ›› ተባለ፡፡
፪.፪.“ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ መር ብለህ ውረድ ” ማለቱ ‹‹ ወድቆ ተሰብሮ ከሞተ ተገላገልኩ ምንም ካልሆነ ደግሞ ምትሐት ነው አስብላለሁ ›› ብሎ ከቤተመቅደስ ጫፍ ተወርውረህ ወርደህ ምንም ባለመሆን ባለመሰበር ባለመሞት አምላክነትህን ግለጽ ሲል በትዕቢት ፈተነው፡፡
፪.፫.  ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለአንተ ያዝዛል ” አለው፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሰይጣን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመዝ ፺ ፥ ፲፩ ላይ ጠቅሶ ለመፈተን ሞኩሯል፡፡ እዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን እናስታውሳለን፡፡
፩. ሰይጣን ጥቅስ ቢጠቅስም ጥቅሱን አውቆ ሳያሟላ ጠቅሷል፡፡ ሰይጣን ተንኮለኛ ነውና “መንገድ” የሚለውን መሰረታዊ ቃል አውጥቶ ጠቅሷል፡፡ ይህን ያደረገው “መንገድ” የሚለው ቃል ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ ስለሚያፈርስበት ነው፡፡ እንዴት ቢሉ? “መንገድ” በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ትርጉም ቢኖረውም መንገድ ፈቃደ እግዚአብሔር ፤ ሃይማኖት ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ኤር 6፲6፡፡ ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ሃሳብ በአንዲት ሃይማኖት ለሚጓዙ መከራ ቢደርስባቸው መልአኩን ልኮ ያድነዋል እንጂ ዝም ብሎ ከቤተ መቅደስ ለሚዘሉ ይህ ነገር ፈቃደ እግዚአብሔር አይደለምና አያድንም ›› በማት እንዳይረታው ‹“መንገድ” የምትለውን ቃል አወጣ፡፡ ዛሬም ሰይጣን በግብር ወልዶ ያሳደጋቸው መናፍቃንም ይህንኑ አይነት አካሔድ ሲከተሉ ይታያል፡፡
፪.ጥቅስ መጥቀስ ፣ መጽሐፍትን ማወቅ ፣ የእውነተኛ ሰዎች ምልክት አለመሆኑን እንማራለን፡፡ዲያብሎስ ጌታችንን በትዕቢት የፈተነው በመጀመሪያ ራሱ ‹‹ እኔ ፈጣሪ ነኝ ›› በማለት ስለወደቀባት በኃላም እንደ ናቡከደነፆር(ዳን፬፥፩) ፣ እንደ ሔሮድስ (ሐዋ፲፪፥፳—፳፫) ያሉ ብዙ ትዕቢተኞችን ስለጣለባት ነው፡፡ ጌታችንም የዲብሎስን ተንኮል ያውቃልና “አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፏል” ብሎ በትዕቢት የመጣበትን ሰይጣን በትህትና አሸንፎታል፡፡ ቅዱሳኑም ጌታችንን አብነት  አድርገው እንደ አምላካቸው በሕይወታቸውዘመን ሁሉበፍጹም  ትህትና ኖረዋል፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ቅዱስ ጳውሎስን ‹‹ ምርጥ እቃ ›› እያለው እርሱ ግን “ ፩ ጢሞ ፩፥፲፭ ነገሩ የታመነ ነው ሁሉም ሊቀበሉት የሚገባነው ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያቸው የሆነሁ ኃጥአንን ሊያድን ወደ ዓለም መጣ ” ያለው ፣ ልበ አምላክ ዳዊት ለሚያሳድደው ለሳኦል “ ፩ ሳሙ ፳፬፥፲፭ አሁን ምየእስራኤል ንጉስ ማንን ለማሳደድ መጥተሃል? የሞተን ውሻ ታሳድዳለህን ? ወይስ ቁንጫን ታሳድዳለህን ? ” በማለት አምላካቸውን በግብር የመሰሉት፡፡ ዛሬ በዘመናችን ግን አለመታደል ሆኖ ሰይጣን እንኳ የማይናገረውን “እኛም በዚያ ዘመን ብንኖር ጌታን እንወዳለን ፤ ቅዱሳን ከሞት በኃላ ምንም አያውቁም ›› የሚሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃልሉ ፤ ካህናትን የሚያዋርዱ በዚህም ስራቸው ሰይጣንን እንኳን በትእቢታቸአው የሚያስቀኑ አሉ፡፡ ስለ እነዚህም ይሁዳ እንዲህ ሲል መልካም ተናገረ “ይሁዳ ፩፥፰ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በሕልማቸው ስጋቸውን ያረክሳሉ ጌታቸውንም ይክዳሉ ክብሩንም ይሰድባሉ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንኳ ስለሙሴ ስጋ ከሰይጣን ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብ ቃልን ሊናገር አልደፈረም እግዚአብሔርይ ገስጽህ አለው እንጂ፡፡ እነዚህ ግን የማያውቁትን በመሳደብ ይበድላሉ”፡፡
      ትዕቢት ብዙ የንስሐ ጊዜ እንኳን የሚሰጠው ኃጢአት አይደለም፡፡ይሔንንም ከናቡከደነጾር ወደ አውሬነት መለወጥ ፤ ከሔሮድስ ቅስፈት፤ ከፈርኦን ሞት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ለዚህ ነው እመቤታችን “ሉቃ. ፩፥፶፩-፶፪ በልባቸው ሃሳብ የሚታበዩትን በታተናቸው ኃያላኑን ከዙፋናቸው አዋረዳቸው” ያለችው፡፡ ሐዋርያውም “ ፩ ጴጥ ፭፥፭ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ያዋርዳል”፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትን ያልተማሩ አሕዛብ በትዕቢት እንዲህ የሚቀጡ ከሆነ የእግዚአብሔርን በትህትና ሰው መሆን ያየን እኛማ ምን ያህል አብልጠን ትሁታን ልንሆን ይገባን ይሆን?  ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን ሲጠቅስበት መጥቀሱ  ‹‹ ጠቅሰው ለሚመጡባችሁ ጠቅሳችሁ መልሱ ››ሲለን ነው፡፡  “ለተጠየቃችሁት መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃች ሁ ፩ጴጥ. ፫፥፲፭››
፫.ፍቅረ ነዋይ
  ሰይጣን በሁለቱ ታላላቅ ኃጢያቶች ጌታችንን መርታት ቢያቅተው በሌላ ኃጢአት ይፈት ነው ጀመር፡፡ ይኸውም ፍቅረ ነዋይ ነው፡፡
“ከዚህ በኃላ ዲያብሎስ እጅግ ረዥም ወደሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለሙን ሁሉ መንግስታት ክብራቸውን ሁሉ አሳየው፡፡ ‹ብትሰግድልኝ እጅ ብትነሣኝም ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ› አለው፡፡”
፫.፩. “ ወሰደው ”ሲል፡- ሰይጣን ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወስድ የሚያመጣው  ሆኖ ሳይሆን  ‹‹ ነገሥታቱን ድል በምንነሣበት በተራራ (ነገሥታት በተራራ ቤተ መንግስታቸውን ይሠራሉና) ቢሆን መች ድል ይነሳኝ ነበር›› ብሎ አስቧልና፡፡ አሁንም ምክንያት ለማሳጣት ከረጅም ተራራ በራሱ ፍቃድ ወጥቷልና “ወሰደው” ተባለ፡፡ሰይጣን ሳያፍርና ሳይፈራ “ብትሰግድልኝ እጅም ብትነሣኝ ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ” ብሎ ብዙዎችን ድል ባረገበት በፍቅረ ነዋይ የመጨረሻ ፈተናውን አቀረበ፡፡በእውነቱ ከሆነ ዛሬ በዚህ ፈተና ያልተሸነፈ የለም፡፡ሁላችንም እንደምናውቀው በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም ጦርነቶች ሌላምክንያት ቢሰጣቸውም ዋናው ምክንያታቸው ፍቅረ ነዋይ ነው፡፡ዘፈኑ፤ዝሙቱ፤ስርቆቱም ምንጫቸው ፍቅረ ነዋይ ነው፡፡እናምናለን ከምንለውም ሰዎች ብዙዎቻች በዚህ ኃጢያት ስለተያዝን ቤተክርስቲያናችን በብዙ ችግር ውስጥ ሆና እንኳ እያየናት ካህናቶችዋ የአብነት ተሪዎችዋ ተርበውና ታርዘው እያን ለአስራት ለበኩራታችን ታማኞች አይደለንም፡፡ታዲያ ሰይጣን በፍቅረ ነዋይ ድል አላደረገንም ትላላችሁ ?
ጌታችን ግን ይሄን ሁሉን ተንኮሉን ያውቃልና “ብትሰግድልኝ ይሄን ሁሉ እሰጥሃለሁ”ብሎ በፍቅረ ነዋይ የፈተነውን ሰይጣን “አንተ ሰይጣን ከአጠገቤ ሒድ ፤ ለጌታ ለእግዚአብሔር ስገድ እርሱን ብቻ አምልክ ተብሎ ተፅፏልና ” ብሎ በጸሊአ ነዋይድልአድርጎታል፡፡
፫.፪.“አንተ ሠይጣን ከአጠገቤ ሒድ”፡- ሲለው ጌታችንየሌለበት ቦታ ኖሮ ወደዚያ ሒድ ያለው አይደለም፡፡ይልቁንም“ከእኔ በኃላ ከሚነሱ ከኦርቶዶክሳዊያን ልቦና ሒድ ሲለው” እንጂ ማቴ. ፲፮፥፳፫፡፡ ከዚህ በኋላ ሰይጣን በዘመነ ሐዲስ የወደቀ የተጣለ ነውና በራሳችን ፍላጎት በኃጢአት እንወድቃለን እንጂ ሰይጣን ሰዎችን ማሸነፍ አይችልም፡፡

፫.፫. “ለጌታ ለእግዚአብሔር ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ”፡- መናፍቃን እንደ አባታቸው ቁንጽል ጥቅስ ይዘው የሚሮጡ ናቸውና ይህን አንብበው ‹‹ለመላእክት ስግደት አይገባም፤ ስግደት የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን ቃሉ የሚለው “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ” ነው ፤ ‹‹ለእግዚአብሔር ብቻ ስገድ›› አይልም፡፡ ቀጥሎ ግን የአምልኮ ስግደት የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ “እርሱንም ብቻ አምልክ” ተብሏል፡፡ እነርሱ ግን ለመላእክት ስግደት እንደማይገባ የተነገረ በማስመሰል ሲጠቀሙበት እናያለን፡፡
፫.፬.“ከዚህም በኋላ ዲያብሎስ ተወው መላእክትም ሊያገለግሉት መጡ“-መላእክት ከድል በኃላ ሊያገለግሉት መገለጻቸው ሰይጣን      ‹‹ መላእክቱ ባይረዱት መች ድል ያደርገኝ ነበር›› እንዳይል፤ አንድም እናንተም ‹‹ ሦስቱን የኃጢያት አለቆች ድል ስታረጉ መላእክት ይገለጹላችኃል ›› ብሎ ሲያስተምረን ነው፡፡ ከዚህ በኃላ ዲያብሎስ በዕለተ አርብ በአይሁድ ልቦና አድሮ መከራ እስኪያደርስበት ድረስ“ሉቃ. ፬፥፲፫ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ” ተብሎ ተጻፈ፡፡ እኛም ዲያብሎስን በዚህ ፆም ድል ብንነሳው ከእኛ የሚለየው እስከ ጊዜው መሆኑን ማወቅአለብን፡፡ ጌታችንን ምቹ ጊዜ ጠብቆ በእለተ ዓርብ ተመልሶ እንደመጣ ወደ እኛም ተመልሶ የሚመጣባት ከባድዋ ‹‹ዓርብ›› አትታወቅምና በፆም፣ በጸሎት ፀንተን እራሳችንን ከክህደትና ከኃጢያት ልንጠብቅ ይገባናል፡፡

v በመጨረሻም ጌታችን በሦስቱ አርዕስተ ኃጣውእ መፈተኑ ምሥጢር አለው፡፡
፩.የመነኮሳት ፆራቸው ስስት ነው በፈለጉ ጊዜ ምግባቸውን አያገኙምና ‹‹ ያለችን ብንመፀውት ሰውን ብናበላ ያለችን ታልቅብናለች ከዚያ ምን እንበላለን›› እያሉ በስስት ይፈተናሉ፡፡ ዲያብሎስ በመነኮሳት ቦታ በበረሃ በስስት ቢመጣበት በትዕግሰት ድል አድረጎላቸዋል፡፡
፪.የካህናት ፆራቸው ትዕቢት ነው፤‹‹ እኛ አእምሮአችን ረቂቅ ማዕረጋችን ምጡቅ ›› እያሉ በትዕቢት ይፈተናሉ፡፡ ዲያብሎስ በካህናት ቦታ በቤተመቅደስ በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና ድል አድርጎላቸዋል፡፡
፫.የነገስታት ፆራቸው ፍቅረ ነዋይ ነውነገስታት ቤታቸውን ከተራራ ሰርተው አላፊ አግዳሚውን ሕዝብ እየተመለከቱ‹‹ የዚህ ሁሉ ሕዝብ ኑሮው በእኛ እጅ ነው›› እያሉ ገንዘብ በመሰብሰብ በፍቅረ ነዋይ ይፈተናሉ፡፡ ዲያብሎስ በነገስታት ቦታ በተራራ በፍቅረ ነዋይ ቢመጣበት በጸሊአ ነዋይ ድል አድርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በኃላ ኃጢአት ከሥሩ እንደተነቀለ ዛፍ ሆናለች፡፡
ጌታችን ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል እንዳረገ ለእኛም ድል አድርገን መንግስቱን ለመውረስ የእናታችን የቅድስተ ቅዱሳን የንጽሕተ ንጹሓን የወላዲተ አምላክ የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎትና ልመና ከሁላችን ጋር ለዘለአለም ይኑር፡፡ አሜን አትሉም?
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

3 comments:

  1. ቃለ-ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን ጸጋውን ያብዛሎት እንደናንተ አይነት ወንድሞችን ያብዛልን፡፡

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete