Pages

Saturday, March 12, 2016

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ቀን ላይ የተሰጠ ተግሣጽ



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 03 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ይህ ተግሣጽ ሊቁ የኦሪት ዘፍጥረትን መጽሐፍ እየተረጎመላቸው ሳለ በዐቢይ ጾም ስድስተኛው ቀን ላይ በዚያ ሰዓት እንደ ትልቅ መዝናኛ ይቈጠር የነበረውን የፈረስ ግልቢያን ለማየት ጉባኤዉን ትተው ለሔዱ ምእመናን የሰጠው ተግሣጽ ነው፤ ልክ የዛሬ 1620 ዓመት መኾኑ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ተግሣጽ በእኛ ዘመን ኾኖ ቢያስተላልፈው ኖሮ እኛ እንደ ትልቅ መዝናኛ የምናያቸውን እንደ እግር ኳስ፣ ፊልም፣ እና የመሳሰሉትን ሊጠቀም እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ለማንኛውም እስኪ እያንዳንዳችን ከያለንበት ኹናቴ እያየን ተግሣጹን ለእኔ ብለን እናድምጠው፡፡ አሁን ወደ ሊቁ፡- 
(1) ዛሬም እንደተለመደው ትምህርታችንን እንድንቀጥል እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን እያመነታሁ ነው፡- ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ከብቦኛል፤ ግራ ገብቶኛል፤ ውስጤ ታምሟል - ተስፋ መቁረጥ ብቻ አይደለም፤ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፤ የጥርጣሬ ስሜት ውስጤን ልምሾ አድርጎታል፡፡ ዕለት ዕለት ከዲያብሎስ ግብር ትርቁ ዘንድ ስናስተምራችሁና ስንመክራችሁ እንዳልነበረ፥ እናንተ ግን ወደዚያ ዲያብሎሳዊ ግብር ጥርግ ብላችሁ ሔዳችሁ፡፡ ከቃለ እግዚአብሔር ይልቅ የፈረስ ግልቢያው ማረካችሁ፡፡ እስከ አሁን ድረስ በማስተምራችሁ ትምህርት ለውጥ ካላመጣችሁ ከዚህ በላይ ላስተምራችሁ የምችለው ምን ብዬ ነው? ከምንም በላይ ተስፋ እንድቆርጥባችሁና ብስጭቴ ጣራ እንዲነካ ያደረገው ደግሞ ይኸን ኹሉ እየመከርናችሁ እየዘከርናችሁ ሳለ ዐቢይ ጾሙን መናቃችሁና ራሳችሁን በዲያብሎስ መረብ ውስጥ መጣላችሁ ነው፡፡ የፈለገ ያህል ልቡናው እንደ ድንጋይ ቢጠነክር እንዴት በዐቢይ ጾም ውስጥ ሰው እንደዚህ ያደርጋል? እመኑኝ! በጣም አፍሬባችኋለሁ፤ እስከ አሁን ድረስ ያስተማርኩት ትምህርት ምንም ጥቅም እንዳላስገኘ በማየቴና ጭንጫ ላይ ስዘራ በመክረሜ በጣም አፍሬባችኋለሁ፡፡

(2) አሁንም የማስተምራችሁን ትምህርት ከልብ አደመጣችሁኝም አላደመጣችሁኝም እኔ ዋጋዬ አይቀርብኝም፡፡ ምክንያቱም ማድረግ የምችለውን ኹሉ አድርጌያለሁ፡- እናንተን ለማስተማር ስል ብዙ ደክሜያለሁ፤ መናገር ያለብኝን ማስጠንቀቂያ ኹሉ ተናግሬያለሁ፤ ጥቂት የሚያሳስበኝ ቢኖር እንዲህ በማድረጌ በፍርድ ላይ ፍርድ እንዳልጨምርባችሁ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር፡- “የጌታውን ፈቃድ ዐውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል” ይላልና /ሉቃ.12፥47/፡፡ ይህን ስል ከእናንተ ማንም “ይህን ያደረግኩት ሳላውቅ ነው” ሊል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይህንና ይህን የመሰለ ቃል ዕለት ዕለት ከእኛ ጋር ሲማር ይውላል፤ የዲያብሎስ የማጥመጃ መንገዶች ምን ምን እንደኾኑ በሚገባ አስተምረኗል፤ ሊኖርበት የሚፈቅድና በምግባር በትሩፋት ያጌጠ ሰው እንደ ምን ያለ ጥቅም እንደሚያገኝ ነግረኗል፡፡ ስለ ድኅነታቸው ምንም ደንታ የሌላቸውና አንዴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ዲያብሎስ ወጥመድ የሚመላለሱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከውሾች ጋር እንደሚያነጻጽራቸው አታውቁምን? እንዲህ ነውና የሚለው፡- “ከኃጢአቱ የሚመለስና ተመልሶም ወደ እርስዋ የሚሔድ ሰው ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ነው” /ምሳ.26፥11/፡፡ እንግዲህ ያንን ሥርዓት የለሽ ትርኢትን ለማየት የሔዱ ሰዎች ማንን እንደሚመስሉ ታያላችሁን? በልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ፣ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ክርስቶስ፡- “ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ኹሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል፡፡ ዝናብም ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መቱት፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ኾነ” ብሎ የተናገረውን ቃልስ አላደመጣችሁምን? /ማቴ.7፥26-27/፡፡ አሁን የፈረስ ግልቢያን ለማየት የሔዱ ሰዎች ከዚህ የባሰ አወዳደቅ የወደቁ ናቸው፡፡ ተመልከቱ! ያ ቤት ታላቅ የኾነ አወዳደቅ የወደቀው ተገፍቶ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወንዝ ወይም ስለ ነፋስ የሚነግረን አንድ ወንዝ ላይ ስላለው የውኃ ሙላት ወይም በአንድ አከባቢ ላይ ስላለው የነፋስ መጠን መናገር ዓላማው ኾኖ አይደለም፤ በወንዙ ወይም በነፋሱ አንጻር የፈተናውን ክብደት መናገር ነው እንጂ፡፡ ስለ ቤት ሲነግረንም እኛ ስለምናውቀው ግዙፍ ሕንፃ እየተናገረ አይደለም፡፡ በዚህ ምንባብ ውስጥ የተጠቀሰው ታሪክ በጥቂት ፈተና ተፍገምግማ ስለምትወድቅ ነፍስ ነው፡፡ ከእናንተ አንጻር ስናየውም ምንም ዓይነት የውቅያኖስ ወይም የጎርፍ ማዕበል አልገፋችሁም - ከዚያ ይልቅ ዲያብሎስ በመንገዳችሁ ላይ በጥቂቱ እፍ አለባችሁ፤ እናንተም ተጠራርጋችሁ ነጎዳችሁ፡፡
(3) ወዮ! ከዚህ የከፋ ስንፍና ምን ይኖር ይኾን? እስኪ ንገሩኝ! ለምንድን ነው ታዲያ የምትጾሙት? ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣታችሁ ምንድን ነው ጥቅሙ? የሚገባችሁ እንዴት አድርገን ብንገሥጻችሁ ነው? መከርናችሁ፤ እናንተ ግን ለብዙ ጊዜያት ያጠራቀማችሁትን መንፈሳዊ ሀብት በአንድ ጊዜ አባከናችሁት፤ ደጀ ልቦናችሁን ለክፉው (ዲያብሎስ) ሰተት አድርጋችሁ ከፍታችሁ በማስገባት መንፈሳዊ ሀብቶቻችሁን በሙሉ ያለ አንዳች ችግር ጠራርጎ እንዲወስዳቸው አደረጋችሁ፡፡ ለማያደምጡን ጆሮዎች እንዲሁ ስንጮኽና በከንቱ ስንደክም ስለ ነበረ፣ ፍሬ ለማናገኝበትም ዘሩን ዕለት ዕለት ስንዘራ በመክረማችን በጣም አዝነናል፡፡ እስኪ ንገሩኝ! እንዲያ አድርገን ስናስተምራችሁ ዓላማችን እንዲሁ ጆሮዎቻችሁን ደስ ለማሰኘት ወይም የእናንተ ጭብጨባ አምሮን ነበርን? በምንነግራችሁ ነገር ምንም ካልተጠቀማችሁ እስከ አሁን ድረስ ምንም ነገር ባንነግራችሁ ይሻል ነበር፡፡ ለኵነኔያችሁ ምክንያት መኾንን አልፈልግማ!
(4) በጣም ብዙ ዕቃን ከገዛ ይህንን ዕቃዉንም ጭኖ እየመጣ ሳለ ድንገት ማዕበል ተነሥቶ መርከብ ከሰጠመችበት፣ ለሚያዩት ኹሉ በአንድ ጊዜ ድኻ ከኾነው፣ በቅጽበት ባዶውን ከቀረ፣ ከሚያስደንቅ የሀብት ማማ ላይ ፍጹም ወደ ኾነ ድኽነት ከገባ ነጋዴ ጋር ልታነጻጽሩት ትችላላችሁ - ዲያብሎስ ያደረጋችሁ እንደዚህ ነው፡፡ መንፈሳዊ መርከባችሁ በብዙ ሀብት እንደ ተመላ ተመለከተ፤ በመጾማችሁና ዕለት ዕለት በምትማሩት ቃለ እግዚአብሔር ውድ ሀብታትን እንዳከማቻችሁ አስተዋለ፤ እንደ ማዕበሉም ለእናንተ ምንም ረብሕ የሌለውንና ጎጂዉን የፈረስ ግልቢያ እንድታዩ አደረገ፡፡ በዚህም ባዶ እጃችሁን እንድትቀሩና ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ንብረት ሳይኖራችሁ ሌጣ እንድትኾኑ አደረገ፡፡
(5) ተግሣጼ እንዲሁ መሸፋፈን የሌለበትና ግል’ጥ ያለ እንደ ኾነ ዐውቃለሁ፤ ለዚህ ይቅርታ እጠይቃችኋለሁ - በነፍሴ ውስጥ ላለው ሐዘን ማውጫ (index) ነው፡፡ እነዚህን ቃላት የምናገራቸው ከጥላቻ አይደለም፤ ለእናንተ ካለኝ ሐሳብና ከልብ የመነጨ ፍቅር እንጂ፡፡ ስለዚህ የነቀርሳ በሽታው እንዳይስፋፋ በመመርመር በመጠኑም ቢኾን ባለኝ ኃይል ካሳየኋችሁ ዘንድ ይበቃኛል፡፡ ተወዳጆች ሆይ! አሁን የምፈልገው ተስፋ ካልቆረጣችሁና መንፈሳዊ ተጋድሏችሁን ካላቆማችሁ ጤናማ የኾነ ተስፋ ድኅነትን እንድትይዙ ማበረታታት ነው፡፡ የነፍስ ነገር እንዲሁ ቀላል አይደለም፡፡ አስቀድሞ በምግባር በትሩፋት ይተጋና ባለጸጋ የነበረን ሰው በኋላም ከዚህ መንፈሳዊ ማዕረጉ የወረደንና የተራቆተን ሰው በአንድ ጀምበር ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለስ አይቻልም፡፡ እኛ ፈቃዱ ካለን፣ ከልባችን ከተጸጸትን፣ ስንፍናችንንም አደብ ካስገዛነው ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ረድቶን ወደ ቀድሞ ሀብታችን መመለስ ይቻለናል፡፡ ጥንቱም እጅግ ቸርና ደግ አምላክ ነው ያለን፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃዱም ማንም ሰው እንዲጠፋ አይደለም፡፡ ይኸውም በነቢዩ ሕዝቅኤል አድሮ እንዲህ ሲል አሰምቶ ነግሮናል፡- “ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፤ ከመንገዱ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ ነው እንጂ” /ሕዝ.18፥23/፡፡
(6) ንግግሬን ከልብ ያደመጣችሁ አሁን ስሕተታችሁን እንደ ተገነዘባችሁ ዐውቄያለሁ፡፡ የበደላችሁን ታላቅነት ማወቃችሁ ደግሞ ወደ ምግባር ወደ ትሩፋት ለመመ’ለስ ለምታደርጉት ጥረት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ከእንግዲህ ወዲህም፡- “የፈረስ ግልቢያን ማየት ኃጢአትነቱ ምኑ ላይ ነው?” የሚልና በዚያ ዲያብሎሳዊ ግብር የሚታለል ማንም አይገኝ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ያለውን ነገር ከልብ ኾናችሁ ብታስተውሉት እያንዳንዱ ነገር በሰይጣን አጋፋሪነት የሚካሔድ እንደ ኾነ ትገነዘባላችሁ፡፡ በሌላ አነጋገር እዚያ ያለው ነገር እንዲሁ ፈረስ ግልቢያን ማየት አይደለም፡- ከልክ ያለፈ መጯጯኽና መሰዳደብ አለ፤ ሌሎች ጸያፍ ንግግሮችም እንደዚሁ፡፡ ገላቸውን ገላልጠው ትርኢትን የሚያሳዩ ሴቶች አሉ፤ ከሥርዓተ ተፈጥሮ ወጥተው እንደ ሴት የሚያደርጋቸው ወጣት ወንዶችም አሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ነገሮች ነፍሳችሁን ለማጥመድ የሚያመጡት ተጽዕኖ ቀላል ነውን? ያላየናቸው ግን ደግሞ በጆሯችን ብቻ የምንሰማቸው ነገሮች እንኳን መንፈሳዊ ነገራችንን እንድንረሳና እንድንወድቅ ዕመቀ ዕመቃትንም እንድንወርድ የሚያደርጉን ከኾነ ለዚህ ዓላማ (ሰውን ለማሰናከል) ተብለው በተዘጋጁት ስፍራዎች ላይ ቁጭ ብለው ማየት የማይገባቸውንም ትዕይንት የሚያዩ ከኾነ’ማ እንዴት? ምን ሊጎዳን እንደሚችል፣ የዲያብሎስ ተንኰል፣ ሌሎችም ብዙ ፈተናዎች ምን ምን እንደ ኾኑ የሚያውቅ እጅግ ቸርና መፍቀሬ ሰብእ እግዚአብሔር እነዚህን ድል የምናደርግበት ጋሻ አስታጥቆናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የዲያብሎስ አሽክላዎችን ድል የምናደርግበት ሕግ ሰጥቶናል፤ እንዲህ ሲል፡- “አንዲትን ሴት በዝሙት ዓይን የሚመለከት ወንድ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” /ማቴ.5፥28/፡፡ ይኸውም ምኞትን አመንዝራነት ብሎ ሲጠራው ነው፡፡ 
(7) ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ፡- “ጊዜዬን የፈረስ ግልቢያን በማየት ባሳልፈው ጉዳቱ ምንድን ነው?” ብላችሁ አትንገሩኝ፡፡ ምክንያቱም ነፍሳችሁን ለመጉዳት አንዲት የፈረስ ግልቢያ ትርኢት ትበቃለች፡፡ ምንም እርባና በሌላቸው ነገሮች ላይ ውድ ጊዜያችንን ስናጠፋ፣ ነፍሳችንን ምንም ካለመጥቀማችንም በላይ ጭራሽኑ ስንጎዳት፣ ምንም ጥቅም በማይሰጡ ነገሮች ላይ ስንጨቃጨቅ፣ ክፉውንና ደጉን ስንነጋገር የሚደረግልን ይቅርታ እንዴት ያለ ይቅርታ ነው? የምንሰጠው ምክንያትስ ምን ዓይነት ነው? በንጽጽር ለማየት፡- በቤተ ክርስቲያን የምንሰጠው ትምህርት ጥቂት ረዘም ስናደርገው ብዙዎቹ ያቁነጠንጣቸዋል፤ ትዕግሥት ያጣሉ፡፡ ምንም እንኳን ትምህርታችን ከዚህ ኹሉ ሊያወጣቸው ይችል የነበረ ቢኾንም ምንም ዓይነት ብርድ ወይም ዝናብ ወይም ነፋስ ባይኖርም ዕረፍት አልባ ይኾናሉ፤ ይደካክማሉ፡፡ የፈረስ ግልቢያን ሲመለከቱ ግን ከባድ ዝናብም ቢኖር፣ ኃይለኛ ነፋስም ቢነፍስ፣ ከፍተኛ የኾነ ሐሩርም ቢኖር ለአንድ ወይም ለኹለት ሰዓታት ብቻ አይደለም፤ ለብዙ ሰዓታት ታግሠው ያያሉ፡፡ ዕድሜያቸው የገፉና ፀጉራቸው ጥጥ የመሰሉ ሰዎች የፈረስ ግልቢያን ሲያዩ ምንም አይሰቀጥጣቸውም፤ እነዚህን ሽማግሎች እንደ አርአያ የሚወስዱ ወጣቶችም ምንም ሐፍረት እንኳ አይሰማቸውም፡፡ ነገር ግን በነፍሳቸው ጥፋት እንዲህ ደስ መሰኘታቸው ራስን ማታለል መኾኑን፣ ከመገኘቱ የሚጠፋ መኾኑ ብቻ ሳይኾን (ለጊዜው) ደስ የተሰኙበት ነገር ጉዳት የሚያመጣባቸው መኾኑን፣ ከሕሊና ወቀሳ በላይ ዘለዓለማዊ ስቃይ እንደሚያመጣባቸው አለማሰባቸው ታላቅ ስሕተት ነው፡፡
(8) አሁን የአንዳንድ ሰዎችን ፊት እየተመለከትኩ ነው፤ የነፍሳቸውን ኹናቴና አሁንኑ ምን ያህል ንስሐ እንደ ነካቸው ሳስበው አስደንቆኛል፡፡ መልሳ’ችሁ በዚያ በተመሳሳይ ኃጢአት የምትወድቁ፣ ተግሣጻችንን ችላ በማለት ወደዚያ ሰይጣናዊ ግብር የምትሔዱ ከኾነ ግን በግልጽ እነቅፋቸዋለሁ፡፡ አንድ ደዌ ዘሥጋ በሚሰጠው መድኃኒት ፈጥኖ የማይድን ከኾነ ፈጥኖ ይድን ዘንድ ጠንከር ያለና ከባድ መድኃኒት ሊሰጠው ግድ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ይኸን ያህል ተግሣጽና ምክር ሰጥተናቸው ሳለ ከመመለስና ከመማር ይልቅ በዚያ ስንፍናቸው የሚቀጥሉ ከኾነ በፍጹም ልንታገሣቸው እንደማንችል ይወቁ፡፡ ወደዚያ የጥፋት መንገድ ተመልሰው እንዳይሔዱና እንደዚህ ቃለ እግዚአብሔርን እንዳይንቁ ቀኖና እንሰጣቸዋለን፤ ወቀሳችንንም እንደዚሁ እናበረታባቸዋለን፡፡ ነገር ግን ይህንን ቃል የምናገረው በዚህ ጉባኤ ለተሰበሰባችሁ ለኹላችሁም አይደለም፤ ለጠቀስኩት ጥፋት ተጠያቂ ለኾኑት እንጂ፡፡ ምንም እንኳን ትምህርታችንን ለእከሌ ለእከሌ ሳንል የምንሰጠው ብንኾንም እያንዳንዱ ሰው እንደየራሱ ችግር ተርጉሞ አስፈላጊውን መፍትሔ ሊወስድ ይገባል፡፡ ጥፋተኞቹ ግን ስንፍናቸውን አሁኑኑ ያስወግዱ፤ ከእንግዲህ ወዲህም እንዲህ አያድርጉ፡፡ በፍርሐት በረዓድ ኾነው ይመለሱ፤ ስሕተታቸውንም ለማስተካከል ይፋጠኑ እንጂ ድጋሜ በዚያ መንገድ አይሒዱ፡፡ በዚህ ጥፋት ያልወደቃችሁ ሰማዕያን ደግሞ ተመልሰው ወደ እንደዚህ ዓይነት መታለል እንዳይገቡ ጠብቋቸው፡፡
ምንጭ
በቅርቡ የታተመው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ፣ ገጽ 82-87

2 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ እግዚአብሔር አምላክ እንደናንተ አይነቶችን መምህራንን ያብዛልን፣

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete