Pages

Saturday, April 2, 2016

ዕለተ ምጽአት



ምንጭ፡- ቅዳሴ አትናቴዎስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 24 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ይህቺ ዕለት (ቅድስት ሰንበተ ክርስቲያን) በምትሠለጥንበት ጊዜ አዲስ ሥራ አዲስ ነገርም ይኾናል፡፡ ያን ጊዜ የፀሐይና የጨረቃ የከዋክብትም ብርሃን ወይም ፀዳል ወይም በጋ የለም፡፡
በውስጥዋ በነፍስ ሕያው ኾኖ የሚንቀሳቀስ ፍጥረት ሳይኖርባት ምድር ሰባት ቀን ታርፋለች፡፡ እንደ ረቂቅ ፉጨት ያለ ቃል ይላካል፡፡ በዚያችም ቃል የሰማያት ጽንዕ ይወገዳል፤ የምድር ግዘፍ ይነዋወጻል፡፡
ያን ጊዜ መቃብራት ይከፈታሉ፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈረሱ ሙታን ፈጥነው እንደ ዓይን ቅጽበት ይነሣሉ፡፡ አብ መንግሥቱንና ፍርዱን ለልጁ ይሰጣል፡፡ ግሩም የኾነ የነጐድጓድም ቃል ይሰማል፡፡ ከመጀመሪያው (ከጥንት) ጀምሮ ጆሮ ያልሰማው ዓይንም ያላየው!
የእሳት ክንፎች ያሏቸው ግሩማን መላእክት በፊቱ ይቆማሉ፡፡ ስም የሌላቸው፣ እገሌና እገሌ የማይሏቸው በአብ መጋረጃ ውስጥ የሚኖሩ ባለሟሎች መላእክት ናቸው፡፡ የሊህም ክንፍ ከክንፍ ጋር ይሳበቃል፤ ይሰማሉ፤ ያንጐደጕዳሉ፤ ሰይፋቸውንም ይመዛሉ፤ ጽናታቸውንም ያሳዩ ዘንድ ይበራሉ፡፡

ያን ጊዜ የእሳት ባሕር እስከ መሠረቷ ትገለጣለች፡፡ በበታቿ ያለ የውርጭ ጕድጓድም የእሳት ወንዝም ይፈሳል፡፡ ኹሉ ተጠብቆለት ያለውን ያይ ዘንድ!
ያን ጊዜ መጻሕፍት ይገለጣሉ፤ ሥራም ይገለጣል፤ አንደበትም ዝም ይላል፤ የተከፈተ አፍም ድዳ ይኾናል፡፡ ፍጥረትም ኹሉ በመፍራት በመንቀጥቀጥ በታላቅ ጸጥታም ይቆማል፡፡ ምድር ኹላ ከእግር መሔጃ ልክ በቀር አትበቃም፡፡ እንደ ጽፍቀተ ሮማን ይጨናነቃል፡፡
ያን ጊዜ አጭርና ረዥም፣ ቀይና ጥቁር የለም፡፡ አንድ አካል አንድ መልክ ነው እንጂ፡፡ ያን ጊዜ የነፍስ ቤዛ የለም፡፡ ወንድ በሚስቱ መለወጥም ቢኾን፣ አባት በልጁ እናትም በልጇ፣ አንዱም አንዱ የሥራዉን ፍዳ ይቀበላል እንጂ፡፡
ባለጸጋዉም ስለባለጸግነቱ አያፍረውም፤ እንደተገመተለት ነው እንጂ፡፡ ለድኻውም ስለ ድኽነቱ አይራራለትም፤ እርሱን ደስ ካላሰኘው!
ያን ጊዜ ጻድቃን ደስ ይላቸዋል፤ በሕይወታቸው አልቅሰዋልና፡፡ ኃጥአንም ያለቅሳሉ፤ ሳቅንና ስላቅን ስለ ወደዱ የፍርድ ቀን ደርሶባቸዋልና፡፡
ያን ጊዜ ባለጸጎች ይደኸያሉ፤ ተድላ ደስታቸውን በዐመፅ ጨርሰዋልና፡፡ ነዳያንም ባለጸጎች ይኾናሉ፤ ድኽነታቸውን በምስጋና ተቀብለዋልና፡፡
ያን ጊዜ ተርበው የነበረ ይጠቅባሉ፤ በሕይወታቸው ተቸግረው ነበሩና፡፡
ያን ጊዜ ተናጋሪዎች የነበሩ ዝም ይላሉ፤ ከንቱንና ብላሽን ነገር ተናግረዋልና፡፡ ትዕግሥተኞች የነበሩ ይናገራሉ፡፡ አንደበታቸውን ወደ ሐሜት ይሮጥ ዘንድ አልተዉትምና፤ ባለንጀራቸውንም ፈጽሞ አላሳዘኑምና፡፡
ያን ጊዜ ጽኑዓን የነበሩ ይደክማሉ፤ ሥጋቸውን በዝሙት አድክመዋልና፡፡ ደክመው የነበሩት ይጸናሉ፤ ኃይላቸውን በሰጊድ በመዓልትና በሌሊትም በመትጋት አድክመዋልና፡፡
ያን ጊዜ ኃያላን ልምሾ ይኾናሉ፤ እጃቸውን ለመቀማት ዘርግተዋልና፡፡ ባልቴትንና አባት እናት የሞቱበትን አስለቅሰዋልና፡፡
ያን ጊዜ የተናቁት እንደ አንስርት ይበራሉ፡፡ ክንፋቸውም ይወጣል፡፡ ጎልማስነታቸውም ይታደሳል፡፡
ያን ጊዜ ትዕቢተኞችና ኩሮች ይገለጻሉ፤ ሐፍረታቸውም ይገለጻል፡፡
ያን ጊዜ የታረዙት ይለብሳሉ፤ የዝናምና የጠል ካፊያ አርሷቸዋና፤ ብርድና ውርጭ አስቸግሯቸዋልና፤ የፀሐይ ሐሩርም አቃጥሏቸው ነበርና፡፡
ያን ጊዜ ጦርና ጋሻ ቀስትና ፍላጻ የለም፤ በምድር የነበረ ኹሉ ተሸሯልና፡፡
ያን ጊዜ ንጉሥ አድልዎ በሌለበት በቅን ፍርድ ይፈርዳል፡፡
ያን ጊዜ ኃጥአን ከጻድቃን መካከል ይለያሉ፤ ርኵሳንም ከንጹሃን መካከል ይለያሉ፡፡


የዚያን ጊዜ አውያት፣ የዚያን ጊዜ ጩኸት፣ የዚያን ጊዜም ለቅሶ ምን ያህላል? እርሱ ቅሉ ፈጣሪ ወደ ጥፋት መንገድ ሲሔዱ ባያቸው ጊዜ እጁ ስለ ፈጠራቸው ፍጥረቶቹ እስኪያለቅስ ድረስ!
ያን ጊዜ ኃጥአን ስለ ራሳቸው ያለቅሳሉ፤ ጻድቃንም ስለ ዘመዶቻቸው ያለቅሳሉ፤ የሰማይ መላእክትም ስለ ፍጥረት ያዝናሉ፡፡
ኹሉ ከተፈጸመ በኋላ ያን ጊዜ ለመረጣቸው ለወዳጆቹ ለጻድቃኖቹ የብርሃን ድንኳን ይተከላል፤ ሰባት መሠወሪያ ያለው የእሳት መጋረጃ ይዘረጋል፡፡
የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስም ከዚያ ወደዚህ ምሥጢር ይገባል፡፡ ለግብር ሥርዓት ቀሳውስትን በቀኙ ዲያቆናትንም በግራው ያቆማቸዋል፤ የምሥጢር ሥርዓት ያሳያቸው ዘንድ፡፡
ምን ይመስላል? ስሙስ ምንድን ነው? የዚያን ጊዜውስ ምሥጢር ምን ይባላል? ዛሬ ሊናገሩት አይቻልም፤ በሰው ልቡናም የለም፡፡

2 comments: