☞ (በመምህር ሽመልስ መርጊያ የተተረጎመችውና ከአራት ዓመት በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ ታትማ ግንቦት አንድ ቀን በገበያ ከምትውለው - የትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ - መጽሐፍ የተቀነጨበ፣ ገጽ 17-19)
☞ … ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ ሚስትህ ለአንተ ትገዛልህ ዘንድ ትሻለህን? ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት አንተም እንዲሁ ለሚስትህ አድርግላት፡፡ ሕይወትህን ስለ ርሷ አሳልፈህ መስጠት ካለብህ ስለርሷ ሕይወትህን አሳልፈህ ስጥ፤ መከራም መቀበል ካለብህ መከራን ለመቀበል አትሰቀቅ፡፡
አንተ ይህን ብትፈጽመው ስንኳ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ካደረገላት ጋር ሲነጻጸር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንተ ይህን ያደረግኸው ከአንተ ጋር ፈጽማ ለተዛመደችህ ለአንዲት ሴት ነው፡፡ “But He for one who turned on Him and hated Him” “እርሱ ግን ከእርሱ ለተመለሰችውና ለጠላቸው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡” ርሱ ከርሱ የተመለሰችውንና የጠላችውን እንዲሁም ያቃለለችውን ገንዘቡ ሲያደርጋት በማስፈራራት፣ በማስገደድ ወይም ይህን በመሳሰሉ ነገሮች አልነበረም፤ ነገር ግን ኀዘን ባልተቀላቀለበት ፍጹም በሆነ ፍቅር በመሆን ነበር፡፡ አንተም ለሚስትህ እንዲሁ አድርግላት አዎን! ምናልባት ሚስትህ አንተን ልታመናጭቅህ፣ ልትንቅህ፣ ልታፌዝብህም ትችላለች፤ ቢሆንም ግን አንተ ለርሷ ካለህ አርቆ አሳቢነት ንጹሕ ፍቅርና ኀዘኔታ የተነሣ ልትታገሣት ይገባሃል፡፡
ከሰው ሁሉ ጋር ተስማምቶ ለመኖርም ከእነዚህ የተሻሉ ነገሮች ፈጽሞ አናገኝም፡፡ በተለይም ለባልና ለሚስት፡፡ አንድ ሰው አገልጋይ ባሪያውን በማስፈራራት ለመግዛት ቢሞክር ለጥቂት ጊዜአት ሊገዛለት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ባሪያ እንዲህ ዓይነት አገዛዝ ስለማይመቸው ከእርሱ ፈጥኖ ይሸሻል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የሕይወቱን አጋር፣ የልጆቹን እናት፣ የደስታው ሁሉ ምንጭ የሆነችውን ሚስቱን በፍቅርና በፍጹም አክብሮት እንጂ ልክ እንደ ባሪያ በፍርሃት ሰንሰለት በማሰር ወይም በማስጨነቅ ርሷን ሊገዛት መሞከር አይገባውም፤ ሚስት በባልዋ ምክንያት የምትሸበር ከሆነ አንድነታቸው ምን ዓይነት አንድነት ነው?
ከባሪያ ጋር እንደ መኖር ከሚስት ጋር መቀመጥ ለባል የሚፈጥርለት ምን ዓይነት ደስታ ነው? አዎን ይልቁኑ አንተ ስለ ርሷ ስትል ብዙ መከራዎችን መቀበል ሲገባህ በተቃራኒው በቁጣ ርሷን በማስጨነቅና በማሸበር ታስፈራራታለህን? ክርስቶስ እንዲህ አላደረገም፡፡
“በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ አንዲቀድሳት ስለ ርሷ (ስለ ቤተ ክርስቲያን) ራሱን አሳልፎ ሰጠ (ቁ.፳፮)፡፡ ከቃሉ እንደምንረዳው ቤተ ክርስቲያን (እኛ) አስቀድማ ንጽሕት አልነበረችም፤ ጉድፍ ነበረባት፤ መልከ ጥፉም ነበረች፡፡ ስለዚህም ለእርሱ የተገባች አልነበረችም፡፡ አንተ እንደ ቤተ ክርስቲያን የሆነችውን ሴት ሚስትህ ትሆን ዘንድ አትመርጥም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ የተለየችውን ያህል ከአንተ ፈጽማ የማትስማማውን ሴት ሚስትህ ትሆን ዘንድ ወደ አንተ አታቀርባትም፡፡
ርሱ ግን እጅግ መልከ ጥፉ ብትሆንም አልጠላትም፣ አልተጸየፋትም፣ ስለ መልከ ጥፉነቷ የተጻፈውን መስማት ትፈልጋለህን? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ርሷ ምን እንደሚል ስማ “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ” (ኤፌ.፭፡፰) አላት፤ የገጽታዋን መጥቆር ትመለከታለህን? ከጨለማስ የበረታ ጥቁረት ምን አለ?
የአመሏን መክፋት ደግሞ ስማ “በክፋትና በምቀኝነት” ይልና “የምንኖር” ይላል፤ ስለ ነውሮቿ ደግሞ “የማንታዘዝና የምንስት ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ” ይላታል (ቲቶ.፫፡፫)፡፡
ነገር ግን ለርሷ ስለተደረገላት በጎነት ምን ማለት ይቻለኛል? ርሷ ስንፍናን የተሞላችና ክፉ አንደበት የነበራት እንዲሁም በነውሮቿ ሁሉ ያደፈች ብትሆንም እነዚህ ሁሉ ጠባዮቿ ከርሷ አላራቀውም፡፡ ነገር ግን ልክ የደስ ደስ እንዳላት ልጃገረድ በአፍቀሪም ዘንድ ለምትወደድ ውብ ሴት እንደሚደረገው ርሱ ስለ ርሷ ራሱን አሳልፎ የሰጠ አይደለምን? ይህንንም በማድነቅ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለጽድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት ስንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኛል” ይልና “ነገር ግን ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና”(ሮሜ.፭፡፯-፰) ብሎአል፡፡ በዚህ መልክ ርሷ ለርሱ ትሆን ዘንድ አቀረባት፤ በመንፈሳዊ ውበትም አስጌጣት፤ ንጽሕት አደረጋት፤ ስለ ርሷም ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ስንኳ የጨከነ ሆነ፡፡…
Share plsss
ቃለ ህይወት ያሰማልን ።
ReplyDelete