በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የአቡነ ቴዎፍሎስ ዝክረ-ሥምዕ በቤተ ክህነቱም በአዲሱ ትውልድም ዘንድ እየተዘነጋ ሄደ፡፡እኛ ስንዘነጋው ታሪካቸው በቆናጽላን (ተሐድሶዎች) እንዳልሆነ-እንዳልሆነ ተተረከ፡፡የአቡነ ቴዎፍሎስን በመሥዋዕትነት የከበረ ታሪክ የቤ/ክ ታሪክ አድርጎ ለማየት ፍላጎት ጠፋ፤ሰቆቃቸው የሚዲያ ሽፋን ተነፈገ፡፡እንዲያ ተሰማኝ!ይሕን ሁሉ ችለን ሕመማችንን እንዳናስታምም ወዲህ ከቤተ ክህነት፣ወዲያ ከአብዮታውያን ወገን ያሉ ትሩፋን አበው ጭራሽ አጽመ-ቴዎፍሎስን በግፍ በወደቀበት እንበለ-ርኅራኄ አነወሩ፡፡ሲሻቸው ለቀ.ኃ.ሥ ተቆርቋሪ መስለው፣ሲሻቸው የሲሶ ግዛትን ተረክ ከለላ በማድረግ ከ2 ወገን በሚወረወር የብዕር ፍላጻ መቃብሩን እየፈለሱ በወደቀበት አለሳርፍ አሉት፡፡መንበሩን በግፍ ከለቀቀ 40 ዓመት የደፈነው ግፉዕ እረፍት አጣ፡፡ አላስተኛ አሉት፡፡ዘለግ ያለችውና መቼቷ ከ1953-1971 ዓ.ም የሆነው የዚህች ክታብ ‹ምክንያተ-ጽሕፈት› ይኸው ነው--ሕማሙ፡፡የሚከተሉት አርእስት ለነዚህ ዐፅመ-ቴዎፍሎስን እንቅልፍ ለሚነሱ ልብ ሰባሪ ከሳሾች ‹‹እናንት የዛሬ ሕያዋን!ስለ ጉልበታችሁ አምላክ፤ሟች ሞቱን ይሙትበት፤ዐፅሙን ሰላም አትንሱ!›› ለማለት ያህል ከማስረጃ ጋር ተከረተሱ፡-
1. የሲሶ ግዛት ተረክ …‹‹ሲሶ ግዛት›› ወይስ ‹‹የቶፋ ሥርዓት››?!
2. አብዮታዊ ኢ-አማኒነትና የአቡነ ቴዎፍሎስ ምዕዳን!
3. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ… ቅድመ-ሞት፣ጊዜ-ሞት፣ድኅረ-ሞት...ሞትህ ደጅ አደረ!
4. ዝክረ-ቴዎፍሎስ በአፈ-ጳጳሳት ወሊቃውንት!
የሚሉ አርእስትን መራኅያን አድርጌ በተቻለኝ መጠን ስሜቴን ገትቼ (እንዲያው መግታቱ ከሆነልኝ) የመዛግብቱን ሀቅ ለማሳየት እሞክራለሁ፤ለዚህም የአምላከ ግፉዐን ረድኤትና ጥበቃ እንደማይለየኝ አምናለሁ፡፡
1. የሲሶ ግዛት ተረክ … ሲሶ ግዛት ወይስ የቶፋ ሥርዓት?!
በትርጓሜ-ቃላት እንጀምር፡፡
(1) ‹‹ያ! ትውልድ››
የምለው በተለምዶ ‹‹ተራማጅ/ የተማሪው ንቅናቄ/ የ1960ዎቹ ትውልድ›› እየተባለ የሚጠራውን ድኅረ-ፋሽስት ወረራ ተፈጥሮ ለአዲስ ኅብረተሰባዊ ግንኙነትና የሥርዓት ለውጥ የታገለ ቀለም-ቀመስ ትውልድ ነው፡፡አደረጃጀቱ ብሔር-ተኮር ወይም ኅብረ-ብሔራዊ ሊሆን ይችላል፡፡
(2) ‹‹ሲሶ ግዛት›› ማለት የኢኦተቤክ (አንድ-ሦስተኛ ወይም 33%) የሀገር ሀብት (መሬት) ተጋሪነት ለማለት ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው፡፡ቀሪዎቹ ባለሲሶዎች ‹‹ነጋሽ›› (መንግሥት) እና ‹‹አንጋሽ›› (ሕዝብ) ናቸው!
(3) ‹‹ተረክ›› የምትለዋ ቃል የኢህአፓው ጃርሶ ሞት ባይኖር ኪሩቤል መለያ ቃል ናት፡፡ ጃርሶ ይቺን ቃል ‹‹ተረትና ታሪክ አንድ ላይ ተሠርተው ሲቀርቡ›› የሚሰጡትን ትርጓሜ ለመግለጽ እንደሚጠቀምባት ተናግሮ ነበር (ሩሕ መጽሔት፣ የካቲት 1993)፡፡ በሲሶ ግዛት ዙሪያ የሚጻፉ መዛግብት እንዲያ አይነት ማለትም ተረትና ታሪክ የቀላቀሉ ሆነው ስለሚሰሙኝ ቃሉን ከጃርሶ ተዋስኩት፡፡
‹(4) ‹ቶፋ›› የሚለው ቃል በጽሑፉ ውስጥ በተደጋጋሚ በዝርዝር ይብራራል፡፡ባጭሩ ‹‹በቤ/ክ ሥም በዘር በወረደ የእልቅና ወይም ሌላ የክሕነት ተግባር የሰሞን መሬት ለያዘ/ለያዘች ባላባት ለአገልግሎት ተገዝቶ ቅዳሴና ውዳሴው እንዳይታጎል እየሸፈነ በምላሹ ቀለብ የሚቆረጥለት ገባር ቄስ/ደብተራ/ዲያቆን›› ማለት ነው፡፡ አሁን ወደ ተረኩ እንሂድ…
1.1. የያ ትውልድ የሲሶ ግዛት ተረኮች!
1.1.1. የሲሶ ግዛት ተለዋጭ ሥሙ ‹‹የሰሞን መሬት›› ነው፡፡ ‹‹ሰሞን›› ትርጓሜው በየሳምንቱ (በየ8 ቀኑ) የሚዞር የካሕናት የፈረቃ አገልግሎት ማለት ነው፡፡በግእዝ ‹‹ዕብሬት›› እንለዋለን፡፡ ‹‹የሰሞን መሬት›› ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ነበር! በመዝገብ ትርጓሜው ‹‹የሰሞን መሬት፡- የእልቅና፣ የግብዝና፣ የቅስና፣
የዲቁና፣ የደብተርነትና ሌላም ይህነን የመሳሰለ ከቤተ መቅደስ የገባ የቤተ ክርስቲያን ርስት ነው፡፡… አለቃው … በሹመቱ ጊዜ … መትከያ የሆነ ማደሪያ ይቀበላል፡፡ በያውራጃው አንዳንድ ቦታ ‹አቅንቶ› ርስቱ ሆኖ የሚኖር ደግሞ መንግሥት ፈቅዶለት ለተከለው ታቦት ‹እልቅናውን ርስት ያስደረገ› አለ›› ተብሎ ተተርጉሟል (ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ፣ዝክረ ነገር፡ገ.120)፡፡
ከዚህ ትርጓሜ 2 ቁም ነገሮች እንወስዳለን፡፡ (1) የሰሞን መሬት እንደ መርህ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ነው፡፡ (2) ነገር ግን መንግሥት የፈቀደለት አለቃ አለቅነቱን በሰሞን መሬት ላይ ርስት ማስደረግ ይችላል፡፡‹አለቅነት ርስት ሆነ› ማለት ባለቤትነቱ ለሥም ያህል (bare possession -- ሌጣ ይዞታ) የቤተ ክርስቲያን እየተባለ የመሬቱ ፍሬ ተጠቃሚዎች ግን ከአለቃው ሞት በኋላ እልቅናው በዘር የሚተላለፍላቸው የአለቃው ተወላጆች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡የያ ትውልድ ፀሐፍት የሚስቱት ዓቢይ ነጥብ ይሕ ነው፡፡ተራማጆቹ ይሕን ሀቅ ይራመዱታል!
1.1.2. ያ! ትውልድ ጽንሰቱን ከ1953 ዓ.ም የታሕሳስ ግርግር ጋር ያያይዛል፡፡ ተራማጁ ኃይል በአደባባይ የነጄ/ል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ደጋፊ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ መንበር የነበሩት ቀዳማይ ፓትርያርክ ወእጨጌ አቡነ ባስልዮስ ደግሞ ከተራማጆች በተቃራኒ ቆመው መፈንቅሉን በማውገዝ ለክሽፈቱ አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አቡነ ባስልዮስ በመፈንቅለ መንግሥቱ አድራጊዎች ላይ ያስተላለፉት ውግዘት አስመራ ታትሞ ሻለቃ ቸርነት በተባሉ መኰንን አማካይነት በየክፍል ሀገሩ በአውሮፕላን ተበትኗል (ብርሃኑ አስረስ፣ማን ይናገር የነበረ፡ገ.223)፡፡ ይሕ የአባታችን ድርጊት የመፈንቅሉ ደጋፊ በነበረው ተራማጅ ምሁር ዘንድ ቤተ ክርስቲያኗ እንደ ተቋም ‹‹የፊውዳሉና ከፊል ካፒታሊስቱ አሮጌ ሥርዓት ተቀጽላ›› ተደርጋ የጎሪጥ እንድትታይ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ በዚህ የተነሳ ማዕከላዊውን የቤተ ክሕነት ተቋም፣መሪዎቹን ጳጳሳትና ፓትርያርኮችን ዒላማ ያደረጉ ፕሮፖጋንዳዎች ይካሄዳሉ፡፡ አንዳንዶች ጠቅላላ ሃይማኖቱ ላይ ሲዘምቱ የተወሰኑት ደግሞ ካሕናቱን በተዋረድ ጭቁን የሆኑና ያልሆኑ በማለት በመደብ ከፋፍልው ለማየት ሞከሩ፡፡ ቅስቀሳው በአብዮቱ የመሬት ላራሹ አዋጅ ዋዜማ በተለይ ተጡዋጡዋፈ፡፡
1.1.3. ኮ/ል ፍስሐ ደስታ እንደነገሩን ደርግ የነበረው አቋም ከሀገራችን መሬት ‹‹30 ከመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተያዘ ነው›› ወደሚል ያጋደለ ነው (አብዮቱና ትዝታዬ፡ገ.236)፡፡ ኢሕአፓ በበኩሉ ከሀገሪቱ መሬት ውስጥ ‹‹ከመቶው ሥሳ አምስት /65%/ እጁ የእርሻ መሬት በንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ይገኛል›› ካለ በኋላ ከቀሪው 35 በመቶ ውስጥ ደግሞ ‹‹ከሃያ እስከ ሠላሳ በመቶው /20-30%/ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እጅ ይገኛል›› ብሎ ነበር (ዲሞክራሲያ፣ ቅጽ 1፣ ቁጥር 12፡ገ.2)፡፡ የአንዳንድ የኦሮሞ ተራማጅ ልሂቃንን ያልተስማማሁባቸው አንዳንድ አመለካከቶች ከዚህ በፊት ያቅሜን ለብቻው ስለዳሰስኩ አልመለስባቸውም፡፡ ህወሓትን በሚመለከት በትግራይ የነበሩ ገዳማት ሰፋፊ እርሻ ይዘው እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ‹‹ሕምሾ›› (20%) የምርት ውጤት ከአራሾች ይወስዳሉ ተብሎ ይታመን እንደነበር በአረጋዊ በርሀ በኩል ተነግሮናል (Aregawi Berhe,A Political History of the Tigrays
People’s Liberation Front: p.285-287)፡፡ ሥርወ-ድርጅቱን ከያ ትውልድ የሚመዘው ኢህአዴግ እንዲሁ የኛዋ ‹‹የክርስትና ሃይማኖት የአገሪቱን ሲሶ መሬት ስትቆጣጠር›› እንደነበር ይገልጻል (የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ፣ 2006 ዓ.ም፡ ገ.63)፡፡ ብዙኃኑ ተራማጅ ድርጅቶች ይህን የሲሶ መሬትና ሌላ ሌላም ትረካ በደምሳሳው እንደ መፈክር ከማንሳት በቀር ዝርዝር መረጃ አይሰጡንም፡፡
1.1.4 ያም ሆኖ ዶክመንቱ እንደሚያሳየው ከነዚህ የያ ትውልድ አባላት (ተራማጅ ድርጅቶች) ውስጥ ግነትና ኵሸት ባያጣውም የወቅቱን ነባራዊ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ተጠቃሚ በመለየትና በመረዳት ረገድ ኢሕአፓ የተሻለ ዘርዘር ያለ ግንዛቤ የነበረው ይመስላል፡፡ ምናልባት በውስጡ እነ ፀገየወይን ገብረመድኅን (ደብተራው) እና የእስጢፋኖስ ካሕን ከነበሩ ወላጅ የተገኘው ኃይሉ ዮሐንስ (ገሞራው) የመሳሰሉ መደባቸው ለማዕከላዊ ቤተ ክህነት አስተዳደር ቅርብ ከሆነ ቤተሰብና አኗኗር የሚመዘዝ አባላት ስለነበሩበት ይሆናል፡፡ የኢሕአፓን ዝርዝር ትንታኔ ከድርጅቱ ዝነኛ ልሳን ዲሞክራሲያ እንጨልፍ፡፡
1.1.5. ኢሕአፓዊቷ ዲሞክራሲያ በጥያቄ ነው የምትጀምረው፤ ‹‹ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሬት ሲባል ምን ማለት ነው? ድኃ ቀሳውስትና ዝቅተኛ ካሕናት የያዙት መሬት ማለት ነውን? በርግጥ በቤተ ክርስቲያን መሬት የሚጠቀምበት ማነው? አብዛኛው በቤተ ክርስቲያን ሥም የሚጠራው መሬት በተዘዋዋሪ መንገድ የንጉሣውያን ቤተሰብ ሀብት ነው፡፡ ስማቸው እንዳይጠፋ፣ ብዙ መሬት መያዛቸው እንዳይታወቅባቸው፣ ንጉሣውያን ቤተሰብ በልዩ ልዩ አድባራት ሥም በመጠቀም፣ ደባትሩ፣ ቀሳውስቱ፣
ዲያቆናቱ… ወዘተ ጥቅሙ ሳይደርሳቸው ርስቱንና ግብሩን በነሱ ሥም በማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያን ከለላ ሆነው ሠፊውን ሕዝብ ከማታለል ከመበዝበዛቸውም ሌላ በምዕመናኑ ላይ ተሣልቀዋል፡፡ በምሳሌ ለማሳየት፣ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ብቻ ንጉሣውያን ቤተሰብና ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ዝምድና መጥቀሱ ይበቃል›› ትላለች የኢሕአፓ ልሳን በቅጽ 1፣ቁጥር 12፣ጥቅምት 5 ቀን 1967 ዓ.ም እትሟ)፡፡ በመቀጠልም አልጋ ወራሹ (ልዑል አስፋወሰን) በሐረር ጠቅላይ ግዛት ባሉት አደሬ ጢቆ ሥላሴና ሐረር መድኃኔዓለም ሥም የያዙትን ከ50-70 ጋሻ የሚለካ መሬት፣ልዕልት ተናኘወርቅ በነዚሁ አድባራት፣ በጊዮርጊስና ተ/ሃይማኖት ሥም በደብተርነት፣ ግብዝና፣ መንበር እየተባለ በውርስ የያዟቸውን 13 ጋሻ መሬቶች፣ እንዲሁም ልዑል ሣሕለሥላሴና ልዕልት አይዳ በግብዝና ሥም የያዟቸውን በብዙ ጋሻ የሚቆጠሩ መሬቶች ትዘረዝራለች፡፡
1.1.6. እንዲህ እንዲያ ሲባል የመሬት ላራሹ አዋጅ አዲስ ማኅበረሰባዊ ግንኙነት ለማዋለድ ሀገሪቱን ‹ማርያም! ማርያም!› ሊያሰኛት ይጀምራል፡፡ በዚህ ጊዜ የያ!ትውልድ አባላት በቤተ ክርስቲያን ሥም በተያዘው መሬት እጣ ፈንታ ላይ አስተያየቶቻቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ የኢሕአፓዎችን አስተያየት እንይ፤ ‹‹አብዛኛው ሕዝብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ባልሆነባቸው ቦታዎች ቤተ ክርስቲያንና ገዳማቷ የያዟቸውን የእርሻ መሬቶች ያለምንም ካሳ ወርሶ መሬት ለሌላቸውና ላነሳቸው ገበሬዎች በነጻ መስጠት፣…አብዛኛው ሕዝብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ በሆነባቸው ደጋ ክፍለ ግዛቶች /ጎጃም፣ በጌምድር፣ ትግራይ፣
ሸዋ…ወዘተ./ ቤተ ክርስቲያንዋና ገዳማቷ የሚይዙት የእርሻ መሬት ልክ በሕግ ይወሰናል፡፡ /ንጉሣውያን ቤተሰብ በቤተ ክህነት ሥም የሚጠቀሙትን አይጨምርም፡፡/ ከዚህ ልክ በላይ የሆነው ትርፍ መሬት በሁለት ክፍል ተመድቦ፣ አንደኛው ክፍል ያለ ምንም ካሣ ተወርሶ ደሞዝ ወይንም በቂ መሬት ለሌላቸው ቄስ ገበሬዎች በነጻ ይሰጣል፡፡ ሁለተኛውን ክፍል መንግሥት ከቤተ ክርስቲያንና ገዳማቷ ወስዶ መሬት ለሌላቸውና ላነሳቸው ገበሬዎች በነጻ ይሰጣል፡፡የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት…በሕግ ከሚወሰነው ሳያልፉ መሬት ለመያዝ ያላቸውን መብት መንግሥት ያከብርላቸዋል፡፡ ቅጽረ ግቢያቸውንና ንብረታቸውንም ይጠብቅላቸዋል›› (ዝኒ ከማሁ፡ ገ.5 እና ክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ፣ ቅጽ 1፡ ገ.292)፡፡
1.1.7. የመላ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) በመሬት ላራሹ አዋጅ ዋዜማ በቤተ ክርስቲያን ሥም ስለተያዙ ይዞታዎች ያለውን አቋም ‹‹በቤተ ክርስቲያን ሥም የተያዘው መሬት ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በቅድሚያ ተከፋፍሎ፣የተረፈው ለሌላው አርሶ አደር እንዲደለደል፣በአርሶ አደሩ ላይ የተጫነውም በቤተ ክርስቲያን ሥም የሚሰበሰብ ልዩ ልዩ ግብር (?) እንዲሰረዝ፣ ቤተ ክርስቲያን ከምዕመናን በምታገኘው እርዳታና ምጽዋት ብቻ እንድትተዳደር›› በማለት በወቅቱ የድርጅቱ ልሳን ከነበሩ ባንዱ ‹‹የሕዝብ ድምጽ›› ጋዜጣ የመጋቢት 23 ቀን 1966 ዓ.ም እትም አስታውቆ ነበር፡፡
1.1.8. በደርግ በኩል የመሬት አዋጅ ከረቂቁ እስከ ማጽደቁ በተጓዘው ሂደት በቤተ ክርስቲያን ሥም ስላሉ ይዞታዎች ብልጠትና ጥልቀት የተሞላባቸው ዝግጅቶች ሳይካሄዱ አልቀሩም፡፡ የመሬት አዋጁን ረቂቅ ለደርግ ያቀረቡት የአዋጁ መሐንዲሶች እነ አቶ ዘገየ አስፋው ‹‹በቤተ ክሕነት ይዞታ ስር የሚገኘው መሬትና በጭሰኝነት የሚተዳደረውም የገበሬ ብዛት በቀላሉ የማይገመት ስለሆነ ቤተ ክህነትም የያዘችው መሬት መወረስ ይኖርበታል፡፡በዚህ የተነሳ ቤተ ክህነት ችግር እንዳይገጥማት መንግሥት በየዓመቱ የተወሰነ ገንዘብ በበጀት መልክ ሊመድብላት ይችላል›› አሉ፡፡ በዚህ ማብራሪያ ላይ ኮ/ል አጥናፉ ‹‹ቤተ ክህነት የምትተዳደረው ከመሬት በምታገኘው ጥቅም ሲሆን መሬት በመወረሱ ምክንያት ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች እንደሚዘጉና በዚህም የተነሳ ከምዕመናን ጋር ቅሬታ እንደምንገባ›› ተረድታችሁ ማሻሻያ አድርጉ የሚል ድምጽ አሰሙ፡፡ ከመድረኩ የተሰጣቸው ምላሽ ‹‹ቤተ ክህነትን በሚመለከት መንግሥት በቂ በጀት ከመመደቡም በላይ ከምዕመናን ከሚሰበሰበው ዕርዳታና ከተለያዩ ገቢዎች መተዳደር ስለምትችል በዚህ በኩል ችግር አይገጥመንም›› የሚል ነበር (ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ እኛና አብዮቱ፡ ገ.181-182)፡፡
1.1.9. በወቅቱ ከቤተ ክህነት ለሚወረሰው መሬት በቂ ማካካሻ ተብሎ የተመደበው ገንዘብ ለ17 ዓመታት ያለምንም ማሻሻያ የዘለቀ የ4 ሚሊዮን ብር ተቆራጭ ሲሆን በዚህ ረቂቅ የቤተ ክህነቱን አስተያየት ለመስማት የተደረገ ጥረት ስለመኖሩ የተመዘገበ ታሪክ አላነበብኩም፡፡በዚህ የተነሣ ውይይቶቹ በቤተ ክርስቲያን ሥም መሳፍንትና መኳንንት የያዟቸውን ንብረቶች ሁሉ ጠቅልሎ የቤተ ክርስቲያን የማስመሰል መንፈስ ይነበብባቸዋል፡፡ ያም ሆነ ይሕ ከየካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚፀና የሚገልጸው ሚያዚያ 21 ቀን 1967 ዓ.ም የታተመው ‹‹የገጠርን መሬት የሕዝብ ሀብት ለማድረግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 31/1967›› በስፋት የሚተረከውን ‹‹የሲሶ መሬት ድርሻ›› በሥም ሳይጠቅስ በአንቀጽ 3(2) ‹‹ማንኛውም ሰው ወይም የንግድ ማኅበር ወይም ሌላ ድርጅት የገጠር መሬትን በግል ባለሀብትነት መያዝ አይችልም›› ሲል ደነገገ፡፡ይሕ ድንጋጌ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ወይም ቤተ ክሕነት›› የሚለውን ቃል ቀጥታ ወስዶ አልተጠቀመም፡፡ነገር ግን ‹‹ድርጅት›› የሚለውን ቃል በአንቀጽ 2(6) ሲተረጉም በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 398 የተመለከተውን እንደሚያጠቃልል ይገልጻል፡፡ይሕ የፍትሐ ብሔር ድንጋጌ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና መዋቅሮቿ የሕግ ሰውነት የሚደነግግ ነውና የመሬት አዋጁ በለሰስታ የሰሞን መሬት ስሪትን መናዱን እንረዳላን፡፡
1.1.10. የሰሞን መሬት ፋይል በዚሁ ተዘጋ፡፡ ታሪክ ሆነ፡፡
አሁን የሚያከራክረን የታሪኩ አተራረክ ነው፡፡ የተወሰኑ የያ ትውልድ አባላት ዛሬ ድረስ የ1967 ዓ.ም አዋጅ ከቤተ ክርስቲያን ሲሶ ሥልጣንና ሲሶ የመሬት ድርሻ የገፈፈ አንጸባራቂ ድል አድርገው አጋንነው ያቀርባሉ፡፡ ገፋ ሲልም በወቅቱ በነበሩት ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ እና የቤተ ክሕነት ኃላፊዎች ላይ ለተወሰዱ ኢ-ሰብአዊና ሰቆቃዊ ግድያዎች መሸፋፈኛ ለማድረግ ሲሉ በሙታን አጽም ላይ ክስ ይደረድራሉ፡፡ ኢሕአፓ ከላይ በተጠቀሰችው ልሳኑ አቡነ ቴዎፍሎስ ከ120-180 ጋሻ የሚደርስ መሬት ነበራቸው ሲል በማጋነን ይከስሳል፡፡ ገድሎ ሥም ማውጣት የሚያዘወትረው ደርግ አባል የነበሩት ኮ/ል ፍስሐ ደስታ ያላንዳች ርኅራኄ፣ ያላንዳች ማጣቀሻ፣ ያላንዳች ይሉኝታ ቤተ ክርስቲያንና አቡነ ቴዎፍሎስን በወረፉበት ብዕር ‹‹…ምንም እንኳ መንግሥት የ4 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ድጎማ ቢሰጣትም ቤተ ክሕነት የመሬት ውርሱን በፀጋ አልተቀበለችውም፡፡ በቀድሞው ሥርዓት ቀብታ የምታነግሥ ሲሶ መንግሥት ስለነበረች ሶሻሊዝም ሲታወጅ ተሰሚነቱዋንና የነበራትን ቦታ እንደምታጣ ከወዲሁ መገንዘቧ አልቀረም፡፡ ፓትርያርኩ አቡነ ቴዎፍሎስም የራሳቸውን ወዳጆች በመሾምና በመመደብ በደርግ ላይ ውስጥ ውስጡን የመቃወምና የማጥላላት ዘመቻ ጀመሩ›› ይላሉ (ኮ/ል ፍስሐ ደስታ፡ ገ.199)፡፡ ለነዚህ ተረኮች ዛሬ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ተከሳሽ አበው የሉም፤አልፈዋል፡፡ ቢሆንም ‹‹እመ ነባቢሁ ተቀብረ፤አምጣነ ንባቡ ኢይትቀበር…ተናጋሪው ቢቀበር ንግግሩ አይቀበርም›› ብለን በወቅቱ የነበሩ የቤተ ክሕነት መዛግብት ስለ ሲሶ ግዛት ባዶ የቃላት ጋጋታነት ካኖሩልን በመጠኑ እንጠቅሳለን፡፡
1.2. ‹‹የቶፋ ሥርዓት››! ... በተራማጆች ጆሮ የተነፈገው የታሪክ ጩኸት!
1.2.1 በአቡነ ባስልዮስ 9ኛ የበዓለ-ሲመት አከባበር ወቅት ማለትም በ1960 ዓ.ም መንበረ ፓትርያርኩ ባወጣው ርእሰ አንቀጽ ‹በ13ኛው ክ/ዘ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና የአጼ ይኩኖ አምላክ ቃል ኪዳን ወለደው› የሚባለው ሲሶ ግዛት ወደ ‹‹ተረክነት›› ስለመውረዱ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡ ‹‹ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተሰጠው ሲሶ መንግሥት ግን አሁን አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በመሰረቱ ግምቱ (የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ) የምታገኘው ጠቅላላ የዓመት ገቢ (ብር) 1,821,142.24 ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም ከዓሥራት 1,259,872.93 ሲሆን ከትምህርት ታክስ (በፊደል አስቆጣሪነት ሚናዋ) ደግሞ 561,269.31 (ብር) ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ የቤተ ክርስቲያናችን ገቢ ከአንድ ሚሊዮን ተኩል ብዙ የማይበልጥ ሲሆን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሶ መንግሥት አላት ማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ገቢ 3 ሚሊዮን ብቻ ነው ማት ይሆናል፡፡የመንግሥቱ ገቢ ይሕ ብቻ አለመሆኑ በማንም ዘንድ በግልጥ ስለሚታወቅ በአሁኑ ጊዜ ‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሶ መንግሥት አላት› የሚባለው ወሬ እውነት አይደለም›› ሲል የቀዳማይ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ጽ/ቤት አቋሙን ይገልጻል፡፡
1.2.2. አስከትሎም የያ ትውልድ አባላት ከጽንሰታቸው እስከ ዕርግናቸው ዐይናችንን ግንባር ያድርገው ብለው የሚገድፉትን የ‹‹ቶፋ›› ሥርዓት ያብራራል፡፡ ከፈረሱ አፍ እንስማ፤‹‹ቀድሞ የተሰጠው ሲሶ ሀብት የት ሄደና ነው ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገቢ ይሕ ብቻ የሆነው? የተባለ እንደሆነ ርግጥ ይሕ ሲሶ ሀብት በማንኛውም ንጉሥ አዋጅ አልተሻረም፡፡…ይሁን እንጂ ይህ የቀዳሽ ወይም የቤተ ክርስቲያን ተብሎ የተሰጠው ሀብት በቀን ብዛት ወደ አንጋሹ [ነጋሹ ቢባል ይሻል ነበር] እየተደረበ ሄዷል፡፡ለዚህም ምክንያት የሆነው ቀዳሹ ቤተ ክርስቲያን እያገለገለና እየቀደሰ በልዩ ልዩ ትክል ማለት በእልቅና፣ በግብዝና፣ በመሪጌትነት፣
በሰዓታት፣ በቅዳሴ ይሕን በመሳሰለው አገልግሎት ተተክሎ እንዲጠቀምበት በደመወዝ መልክ ከተሰጠው በኋላ እስከ ዕድሜው ያገለግልና ሲሞት ያንን ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ርስት ለልጆቹ ያወርሳል፡፡ ልጆቹ ደግሞ በሞያና በክህነት አባታቸውን መስለው ስለማይወጡ ለቤተ ክርስቲያኑ ግብር ‹ቶፋ› የሚባል ደጀ ጠኚ ይገዙና እነሱ መሬቱን ይዘው ወደ ሌላ ሥራቸው ይሄዳሉ፡፡ለቶፋውም እንኳ በቂ ደመወዝ አይሰጡትም፡፡ ምናልባት ደጎች የሆኑ እንደሆነ በዓመት ከ10 ብር እስከ 15 ብር ቢሰጡት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ነው ሲሶ ለቀዳሽ ተብሎ የተሰጠው ሲሶ መንግሥት ወደ አንጋሹ [ነጋሹ] ተደርቦ ሊሄድ የቻለው›› ይላል የአቡነ ባስልዮስ 9ኛ በዓለ-ሲመት መታሰቢያ መጽሔት ከገጽ 16-18 ባሳፈረው ሐተታ፡፡ ‹‹ቶፋ›› የተባለው አለቅነትን ከዘር ወርሶ በቤ/ክ ሥም የመሬት ይዞታን ለተቆናጠጠ ተወላጅ ተቀጥሮ የሚሠራ ቄስ፣ዲያቆን፣ደብተራ ነው፡፡ለምሳሌ በበቾ አካባቢ ‹‹ቶፍነት›› ለሚሠራ ዲያቆን በዓመት ከብ 10-14 ሲከፈል ለቄስ ደግሞ ከብር 18-20 ይከፈል ነበር፡፡ ክፍያው ስሙ ‹‹ግዢ›› ነው፡፡ዲያቆን ወይም ቄስ ‹‹ገዝቶ አስቀደሰ›› ነው የሚባል(ዝክረ ነገር፡ገ.136)፡፡
1.2.3. አብዮቱ መፋጀት ሲጀምር ለአቡነ ቴዎፍሎስ 3ኛ ዓመት በዓለ-ሲመት በወጣው ‹‹አዲስ ሕይወት፣ቁጥር 4›› መጽሔት ተመሳሳይ ሐሳብ ይንጸባረቃል፡፡ መጽሔቱ የሲሶ መንግሥት ተረክን ከላይ በሰፈረው አኳኋን ካብራራ በኋላ ሐተታውን በምሬት ሲደመድም ‹‹…የሲሶ መንግሥት ቃል ኪዳን ጥንታዊውን የታሪክ መዝገብ ይዞ የሚገኝ እንጂ ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ካለው የመንግሥት ገቢ ላይ ሲሶውን አግኝታለች ወይም ታገኛለች ማለት አለመሆኑና ቤተ ክርስቲያን ባሁኑ ጊዜ እንኳንስ የመንግሥቱን ሲሶ ገቢ ይቅርና ከመቶ አንዱን እንኳ የማታገኝ መሆኗ ባጭር የተሰጠው ሐተታ በቀላሉ ሊያስረዳ ይችላል›› ይላል (አዲስ ሕይወት፣ ቁጥር 4፣ ግንቦት 1 ቀን 1966፡ ገ.29)፡፡
1.2.4. እነ ኮ/ል ፍስሐ ደስታ በመሬት ላራሹ የተገኘውን ድል ያሳንስብናል ብለው ሳይሆን አይቀርም ይሕን ቤተ ክሕነታዊ ድምጽ መስማት አይፈልጉም፡፡ ኮለኔሉ በትዝታቸው ገጽ 145 ስለ አክሱም አካባቢ የመሬት ስሪት ሲያብራሩ ‹‹የአክሱም ጽዮን ገዳም በርካታ ጉልት ስለነበራት በደርግ የመሬት አዋጅ እስኪታወጅ ድረስ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ መነኮሳት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመስጠት ብቻ የገዳሚቱን ርስተ ጉልት እያሳረሱ ይተዳደሩ ነበር፡፡ሌላው ቀርቶ የቤተ ክርስቲያኒቱን ንብረት ከአይጥ ለሚጠብቁ ድመቶችና በየዓመቱ የንግሥ በዓል በወግ ልብስ ተሸልመው ለሚወጡ በቅሎዎች ሳይቀር በስማቸው ከተያዘው የጉልት መሬት ቀለብ ይሠፈርላቸዋል›› ይላሉ፡፡የተከበሩ ኮሎኔል ለዚህ አባባለቸው አስረጅ አልጠቀሱልንም፤‹እማኝ ነኝና እመኑኝ› ነው የሚሉ፡፡ግና ቃላቸውን እንደወረደ እንዳንቀበል ቤተ ክሕነታዊ ምንጮቻችን ይገዳደሩናል፡፡
1.2.5. ኮ/ል ስለ አክሱም ጽዮን አካባቢ የመሬት ስሪት የጻፉትን ታሪክ በሌላው ትግራዋይ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊ ገ/ዮሐንስ ገብረ ማርያም(M.T) ‹‹ክርስትና በኢትዮጵያ›› መጽሐፍ በቀላሉ ማፍረስ ይቻላል፡፡ ገ/ዮሐንስ የአክሱም አካባቢ የመሬት ሥሪት ቅርጹን የቀየረው በአጼ ዮሐንስ 4ኛ ዘመን መሆኑን ይተርካሉ፡፡ ንጉሡ ሕዝቡ መሬቱን ለእሳቸው እንዲሰጥ አስገደዱት፡፡ ሕዝቡ በምሬት ወደ ምዕራብ ትግራይ ሸሸ፡፡ንጉሡ ሕዝቡን ‹‹ወደ ቦታህ ተመለስ፤ምሬሃለሁ›› ካሉት በኋላ የመሬቱን ዋጋ ጨርቅ እየሰጡ የትም እንዳይሄድ በወታደር አስጠበቁት፡፡ መሬቱን ግን ለመጤ ደባትር፣ ለካሕናት፣ ለወይዛዝርት፣
ለመኳንንት አደሉት፡፡
ይሕ ድርጊት ይላሉ የዐጼ ዮሐንስን ዓለምአቀፋዊ ገናና ታሪክ ሳይስቱ ድክመታቸውን የሚጠቅሱት ገ/ዮሐንስ፣ ‹‹ይሕ ድርጊት የአጼ ዮሐንስ ደካማ ጎናቸው ነው፡፡ …ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ የከበደ ቀንበር በአክሱም አካባቢ ነዋሪ ተጫነበት፡፡በሌሎች አድባራት ትክለኛ ሲሞት ትክለኛ ይተካ ነበር(?)፡፡ ‹የአክሱም የአጼ ዮሐንስ ትክለኛ ግን በትክለኛነት የተረከበውን መሬት ለልጅ ልጁ አወረሰ›፡፡ ደብተራው፣ መኰንኑና ሴት ወይዘሮዋ ከየትም የተጠራቀሙ ቢሆኑም ተተከሉ፡፡ ገበሬው ደግሞ ከአያት ከቅድመ አያቶቹ ጀምሮ በነበረበት ቦታ ለአስከፊ ባርነት ተዳረገ፡፡ የተገላቢጦሽም መጻተኛ ተባለ፡፡ በዚህም እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ኖረ›› ይላሉ (ገ/ዮሐንስ ገ/ማርያም፣ ክርስትና በኢትዮጵያ፣ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 19፡ ገ.165)፡፡ ስለዚህ አክሱም የነበረው ስሪት ኮ/ል እንደሚሉት የካሕናት ሲሶ ድርሻ ሳይሆን ያው በተቀረው አገር እንደነበረው ‹‹ቶፋ›› የሚባለው መሳፍንታዊ ሥርዓት ነው፡፡
1.2.6. የተከበሩ ኮ/ል ትኩረት ሰጥተው በጊዜው አላስተዋሉትም እንጂ በደርግ ቡራኬ አቡነ ቴዎፍሎስ ወርደው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ መንበሩ ሲመጡ ካሕናቱ ያስደመጡት ድምጽ በመሰረታዊነት በቀደሙት ፓትርያርኮች ከተሰማው የተለየ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ለበዓለ ሲመቱ የታተመው መጽሔት በገጽ 36 እንዲህ ይላል፤‹‹…መሳፍንቱና መኳንንቱ እልቅናውንና ግብዝናውን ርስት አድርገው ስለሚይዙት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቀላዶችና ጋሻ መሬቶች በተዘዋዋሪ መንገድ ተመልሰው ወደ ልዑላኑ እጅ ይገባሉ፡፡ ወይዛዝሮቶቹ፣
ባህሉና ሥርዓቱ የማይፈቅድላቸው የቤተ ክርስቲያንን የሹመት መዓርግ በተጽእኖ እየያዙ ምሁራን ካሕናትን በትንሽ አበል እየገዙና ‹ቶፋ› የሚል የዝቅተኝነት መጠሪያ ሥም እየሰጡ ሲያስገብሩት ኖረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ስሙ የቤተ ክርስቲያን፣ጥቅሙ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ ሆኖ ቆይቷል›› ብሎ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል? !ኮ/ል አላይተው፣ አልሰምተው! አሁን ድረስ በሕይወት ያሉት ታላላቅ ብፁዐን አበው እነ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር) እና አቡነ ቀውስጦስ የሲሶ ግዛትን ተረክነት መናገር አላቆሙም፤ አድማጩ ቢያንስም፡፡ ስለ ቶፋ ሥርዓትና ስለ ባለግብር ድመቶች ካሕናትን የሚወነጅል ምውት ወቀሳ የተሰነዘረው ተቃውሞ(ማስተባበያ) በደረቅ ንባብ ካልተሰማ በ1968 ዓ.ም ካሕናት ካቀረቡት ግጥም እንቀንጭብ፡-
…የዱሮ መሳፍንት፤ለጉዳቸው፣
ምርቱን እየበሉ፤እራሳቸው፣
ሰሞን መሬት፤ማለታቸው፡፡
እነኝህ ሞኞች፤ያልተማሩ፣
መሬት በደወል፤የሚጠሩ፣
ቀዳሹ እያለ፤ካሕኑ፣
መሬት በድመት፤ወሰኑ፡፡
ብለው ነበር፤
የኛ ባለ ‹‹ሲሶ ግዛት›› ተራኪዎች ግን ወይ ፍንክች! በመጽሐፋቸውም፣ በንድፈ ሐሳብ የሥልጠና ሰነዶቻቸውም ወይ ፍንክች! ሲሶ! ሲሶ! ሲሶ! ኧረ የሥላሴ ያለህ! ልባቸው መጠንከሩ! 50 ዓመት ሙሉ--ሳያምኑ!
2. አብዮታዊ ኢ-አማኒነትና የአቡነ ቴዎፍሎስ ምዕዳን!
በ1978
ዓ.ም የታተመው ‹‹ማርክሲስስት ሌኒንስት መዝገበ ቃላት›› ሃይማኖትን ሲተረጉመው ‹‹…ቀኖና ላይ የተመሠረተ ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት… በማስፈራራት ሰዎች በጭፍን እንዲያምኑ በማድረግ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የሚጥር የሳይንሳዊ ዕውቀት ፍጹም ተጻራሪ የሆነ አመለካከት ነው፡፡… ሃይማኖት ገዥ መደቦች የሚጠቅማቸውን ሥርዓት ለማቆየትና ለማጠናከር ዋነኛ የርዕዮተ ዓለም መሣሪያም በመሆን ሰፊውን ሕዝብ አደንዝዘውና አደንቁረው ለመግዛት እንዲቻላቸው ያገለግላል፡፡… ጭቆናና ብዝበዛ ከነሱም ጋር በዝባዥ መደቦች ሲጠፉ ሃይማኖቱም አብሮ ይከስማል፡፡ ይሕ እውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ በኮሚኒስት ኅብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ብቻ ነው፡፡… ይሑንና የሃይማኖት መጥፋት ወይም መደምሰስ ቅጽበታዊ ሂደት አይደለም፡፡… ሰፊውን ሕዝብ በኢ-አማኒነት መንፈስ የማነጹ ተግባር ሰፊ የሳይንስን ዕውቀት፣ የማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም ትምህርትንና ፕሮፖጋንዳን ባልተቋረጠ ሁኔታ አጠናክሮ ማካሄድን ይጠይቃል›› ብሎ ነበር፡፡ ብዙኃኑ የያ ትውልድ አባላት ከዚህ ትርጉም የተስማማ አቋምን በጊዜያቸው አንጸባርቀዋል፡፡ ጥቂት እንጥቀስ፡፡
2.1. መጀመሪያ አካባቢ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተባባሪ ደርግ ሶሻሊዝምን እንደ ርዕዮተ ዓለም መመሪያ በገሀድ ስላልተቀበለ
ከላይ ከተጠቀሰው የማሌ (ማርክሲስት ሊኒንስት) የሃይማኖት ትርጓሜ ጋር
የተዋወቀ አይመስልም፡፡ ይሕም ሰኔ 1966 ዓ.ም በተደረገ ጉባኤ እያንዳንዱ የደርጉ አባል እንደየእምነቱ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርዐን በመያዝ ‹‹እኔ…የጦር ኃይሎች አስተባባሪ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ትቅደም ብሎ በተነሳበት ዓላማ መሠረት የኢትዮጵያን ሕዝብ…የግል ጥቅሜንና ሕይወቴን መሥዋዕት በማድረግ በፍጹም ታማኝነት አገለግላለሁ፡፡… በሕያው እግዚአብሔር/ አላህ ሥም ምያለሁ›› ሲል በሀልዎተ-ፈጣሪ ማመኑን ይጠቁመናል (አብዮቱና ትዝታዬ፡ ገ.81)፡፡ ደርጎች ሰኔ 26 ቀን 1966 ዓ.ም ጃንሆይ ፊት ቀርበው ለንጉሡ ያላቸውን ታማኝነት ሲገልጹ በሃይማኖተኛነት ቃና ‹‹ለግርማዊነትዎ ረጅም እድሜ እየለመንን ኢትዮጵያ ትቅደም ብለን ለተነሣንበት ዓላማችን የኃያሉ እግዚአብሔር ድጋፍ እንዳይለየን እንጸልያለን›› ብለው ለዚሁም የጃንሆይን ይሑንታ አግኝተው ነበር (ዝኒ ከማሁ፡ ገ.82)፡፡ በዚህ የተነሣ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚለው መፈክር ወደ ቤተ ክህነቱም ገብቶ ከፓትርያርኩ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ የደብዳቤና የመግለጫ ማሳረጊያ ሆኖ ነበር፡፡ ‹‹የኃያሉ እግዚአብሔር ድጋፍ አይለየን›› ተማጽኖ የነመንጌ ሥላቅና ወጥመድ መሆኑን ማን ልብ አለው!
2.2. ደርግ እየቆየ በማርክሲዝምና ሌኒንዝም በይፋ ተጠመቀ፡፡ ይሕን የተረዳው ተቃዋሚው የመሳፍንት ባለነፍጥ ፓርቲ ኢዲህ (የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅብረት) ጠንካራ ኦርቶዶክሳዊ መሠረት ባለው የሰሜኑ ሕዝብ ዘንድ ደርግን በፀረ-ኦርቶዶክስነት እየከሰሰ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ከፈተበት፡፡ የደርግ አመራሮች ይሕን ለመቀልበስ ወደ ሰሜን ሄደው በምዕመኑ መካከል ቆመው እስከማስቀደስ በደረሰ የማሳመን ዘመቻ ተጠመዱ፡፡ ‹‹…ደርግ ሃይማኖት የለሽና ሃይማኖትን ለማጥፋት የመጣ ኃይል ሳይሆን በተቃራኒው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ነጻነቷን አግኝታ እንድትጠናከርና እንድትስፋፋ ለመርዳት ከጎኗ የቆመ መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ ለማሳመን ተሞከረ፡፡… ለአንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚውሉ ንዋየ-ቅድሳት በመንግሥት ሥም በመስጠታቸው ምዕመናኑ አደነቁ›› ይላሉ ሻምበል ፍቅር ሥላሴ ወግደረስ (እኛና አብዮቱ፡ ገ.207)፡፡ በኤርትራ ለነበረው ግጭት እንዲሁ ‹‹ጄ/ል አማን በሻዕቢያ ውስጥ ያሉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የኤርትራን አቶኖሚ በመቀበል ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን በመቆም ሌሎቹን ይወጋሉ የሚል እምነት ስለነበራቸውም በሽማግሌዎች በኩል ግንኙነት እንዲደረግ ፈቀዱ››፤ሆኖም የኢትዮጵያን መንግሥት ከሻዕቢያ ጋር ያግባባሉ ተብለው የተላኩት ክርስቲያን ሽማግሌዎች በተቃራኒው ሻዕቢያንና ጀብሃን አስታርቀው የጄነራሉን ክርስትናን ተስፋ ያደረገ የሰላም እቅድ ውሃ ቸለሱበት (ኮ/ል ፍስሐ ደስታ፡ ገ.117)፡፡
2.3. የደርግን ርዕዮተ ዓለማዊ የሃይማኖት እይታ ፍቅረሥላሴ አርዓያ የተባሉ የፖለቲካ ምሁር ባጭሩ ሲገልጹት ‹‹ደርግ መጀመሪያ ሲነሣ ፀረ ሃይማኖት ሆኖ ነበር የተነሣው፡፡… ቆይቶ ወደ አለመቃወም ነበር የመጣው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በሃይማኖቱ አስተምህሮና መዋቅር መጣ›› ይላሉ በሐመር መጽሔት የ1998 ዓ.ም ኅዳር/ ታሕሣሥ እትም ባሰፈሩት መጣጥፍ፡፡ በዚህ የምሁሩ አመለካከት ላይ ደርግ ፀረ ሃይማኖት የነበረው ከመጀመሪያ ሲነሳ ሳይሆን ታሕሳስ 11 ቀን 1967 ዓ.ም በግልጽ ሶሻሊዝምን እንደ ርዕዮተ ዓለም ከተቀበለ በኋላ ነው ብዬ ከማመን በቀር በሌላው እስማማለሁ፡፡ በሃይማኖቱ አስተምህሮና መዋቅር ለመጠቀም መሞከርን በሚመለከት በሥራ አስኪያጅ ቀጥተኛ ምደባ፣በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ፣ መሪጌቶችን ለቀበሌ ሊቀ መንበርነት በመመልመል፣በየሸንጎው ጳጳሳትንና ፓትርያርኮችን በማስገባት፣ የተሐድሶ ጉባኤ የተባለውን ኢ-መዋቅራዊ ተቋም በማጠናከር ደርግ እጁን በሰፊው ወደቤተ ክሕነት ሰድዶ ነበር፡፡ የሚገርመው የመደብ ጀርባው ከያ! ትውልድ የሚመዘዘው ኢህአዴግም ‹‹ሕዝባችን ጠንካራ የሃይማኖት እምነት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አስተሳሰቡና ባህሉ በተቋማቱ ተጽዕኖ ስር ማደሩ በፍጹም የማይቀር ጉዳይ ሆኗል፡፡ እናም እምነቶቹ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ እንደምታ ባለው መልኩ እንዲቀረጹ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው›› ሲል የደርግን ሌጋሲ በለሆሳስ የማስቀጠል ዝንባሌ ያሳያል (የተሐድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ሕዳሴ፣ 2006፡ ገ.102)፡፡ መቀመጫውን በዋናነት አሜሪካ ያደረገው የያ ትውልድ ተረፍ የሆነ ልዩ ልዩ ተቃዋሚ ኃይል ዛሬ ድረስ ለሰልፉ በካሕን መታጀብን እንደ ትግል ስልት አድርጎታል፡፡ በጥቅሉ ያ ትውልድ እንደ ንጉሣዊው ሥርዓት በግላጭ አይሁን እንጂ ተቋማትን እንደተቋም ሳይሆን እንደመሳሪያ የመጠቀም (instrumentalist) አዝማሚያ ያንጸባርቃል፡፡ በዚሁ አንጻር በየዘመኑ የሚነሱ የቤ/ክ መራኅያን በአጸፋ መንግሥትን መሳሪያ በማድረግ ተቋማዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መጣጣራቸውንም መግለጽ ይገባል፡፡ ‹ማን የበለጠ ሌላውን መሳሪያ አድርጎ ጥቅሙን አስከበረ?› የሚለው እንዳለ ሆኖ አንዱ ባንዱ የራስን ግብ ከፍጻሜ ለማድረስ መሳሪያ የማድረግ ውሳጣዊ መገፋፋት በ2ቱም ወገን ነባራዊ ክስተት ሆኖ ይታየኛል--አሁን ድረስ!
2.4. ወደ ኢ-አማንያን ሶሻሊስቶች እንመለስ፡፡ኢ-አማኒነት የደርግ የብቻው መለያ አይደለም፡፡ኢሕአፓን ጨምሮ ብዙኃኑ የማሌ ድርጅት አባላት ተራማጅነታቸውን የሚያሳዩ አስቀድሞ ኢ-አማኒ በመሆን ይመስላል፡፡ከሞላ ጎደል የሁሉም የ1960ዎቹ የብሔር-አቀፍና ኅብረ-ብሔራውያን ድርጅቶች መሪዎች የማርክሲስት ሌኒኒስት አስተሳሰብ የሰረጻቸው ኢ-አማኒዎች ነበሩ ብንል ስህተት አይሆንም፡፡ለምሳሌ፡- በኢሕአፓ የአንጃ መሪ ተብሎ የተሳደደው ብርሃነመስቀል ረዳ በመርሐ ቤቴ (ሰሜን ሸዋ) ስለነበረው የአመጽ ቆይታ ለደርግ መርማሪዎች በ1971 ዓ.ም በሰጠው ቃል ገጽ 45 ‹‹እኛ ረቡዕና ዓርብ ባንጾም ወይም ቤተ ክርስቲያን ባንሄድም የሌሎችን ሃይማኖት እንደማንሰድብና እስላም ወይም ክርስቲያን እኛ ጋ ቢቀላቀል ሃይማኖቱን እንደምናከብርለትና የኛን እምነት እንዲቀበል እንደማናስገድደው በሰፊው እንገልጽ ነበር›› ይላል፡፡ እዚህ ላይ
ብርሃነመስቀል ‹‹የኛ እምነት›› የሚለው ሶሻሊዝም መሆኑ ነው፡፡
2.5. ለኢሕአፓ ለድል ያለመብቃት ምክንያቶች አንዱ ርዕዮተ ዓለሙን ከሚታገልበት አካባቢ ሕዝብ ባህልና ሃይማኖት ጋር ያለማጣጣም ችግር እንደነበር በራሱ መስተጋድላን ተብራርቷል፡፡
‹‹…ለድል ያላበቃን፤ ነበረን ዐላማ፣
ሕይወት የሰጠነው፤
ምንም ሳናቅማማ፡፡…››
እያለ ያንጎራጉር የነበረው ተጋዳይ አስማማው ኃይሉ ኢሕአፓ ለስኬት ካልበቃበት ምክንያት ውስጥ፤‹‹ወጣቱ ለትግል ከነበረው ጉጉት አንጻር ከአገራችን ባሕላዊ፣ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ጋር ሊጋጭና ሊስማማ የሚችልበትን መመዘኛ ከወዲሁ አላጤነም፡፡…አገሪቱ በባዕድ በተወረረች ቁጥር ርስትህን የሚቀማና ሃይማኖትህን የሚያረክስ ጠላት መጥቶብሃልና ለዘመቻ ተዘጋጅ ሲባል በሬዎችን ሳይከውን ጋሻና ጦሩን አንግቦ በሚነሣ ሕዝብ መካከል የማርክሲስዝም ሌኒንዝምን ርዕዮት አንግቦ የሶሻሊስት ሥርዓት ለመመስረት መነሣት ከታሪክ፣ከባህልና ሃይማኖት ጋር መጋጨታችንን ልብ አላልንም›› ሲል ግለ-ሂስ ያወርዳል (አስማማው ኃይሉ፣ ኢህአሠ፣ ቅጽ ሁለት፡ ገ.306)፡፡ ሌላኛው የኢሕአፓ አባል ዶክተር ዮናስ አድማሱ ለያ ትውልድ ሕልምና ራዕይ ክብራቸውን ሳያጓድሉ በሰጡት ትችት-አዘል አስተያየት ‹‹የኔ የምለው ትውልድ በትንሹም ቢሆን ጥራዝ ነጠቅ የመሆን አዝማሚያ ነበረው፡፡ የንድፈ ሐሳቡም ይሁን የሚያቅዳቸው እቅዶች መሠረት በብዙው ድምፁን ያሰማለትና ደሙን ያፈሰሰለት ሕዝብ እውነታ ከመሆን ይልቅ በሌላ ጊዜና ቦታ የተካበቱ ሐሳቦችን አምጥቶ ባለውና ሙሉ ለሙሉ አወቅን ልንለው በማንችለው ሁኔታ ላይ ለመጫን የሞከረው ረቂቅ እውቀት ነበር›› ብለው ነበር (ጦቢያ መጽሔት፣7ኛ ዓመት፣ቁጥር 3፣1992 ዓ.ም፡ ገ.16)፡፡
2.6. በዚህ ጊዜ ግን በተራማጆች ጫጫታ የተዋጠ አንድ የፓትርያርክ ድምጽ ‹‹ተው! ከሀገራዊ ባህልና ሃይማኖት ያልተገናዘበ የፖለቲካ ብሂል አያዛልቅም›› ይል ነበር፡፡ ማንም አልሰማው፡፡ ታሪክ መዝግቦ ያቆየውን የግንቦት 17 ቀን 1967 ዓ.ም ድምጽ አሁን እንስማው፡፡
‹‹…ምዕመናን ሆይ!...ኅብረተሰቡ ውስጥ በደል የሚደርሰው የኅብረተሰቡ ሥነ ሥርዓት የቤተሰብን ሥነ ሥርዓት አልመስል ሲል ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ከሌላ የመጣ ሳይሆን በመጠኗ በፍላጎቷ የተሠራ ሥርዓት ለማውጣት ሁላችንም እንትጋ፡፡ ጥረቱም በበለጠ ፍሬ እንዲያፈራ በያለንበት ድምጻችንን ከፍ አድርገን እንጸልይ፡፡ እያንዳንዱ ለአቅመ-ውክልና የደረሰ ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውን ሥርዓት እስካልተናገረ ድረስ የሚቋቋመው የአስተዳደር ሥርዓት በምንም ዓይነት ኢትዮጵያዊ ስለማይባል ዘላቂ አስተዳደርን ለማቋቋም ያለው ዘመቻ መላ ኢትዮጵያን እንጂ እንደሌሎች ዘመቻዎች ‹ለወታደሮች ብቻ የሚተው አይደለም›፡፡ ጸጥታና እርጋታ በሌለበት ጊዜ በጽሞና ለማሰብ ስለማይችል ሁለተኛም ካሁን በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሕን አይነቱን ሥርዓተ-መንግሥት የማቋቋም ልምድ ስለሌለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የማወቅ፣ የማስተዋል፣ የማማረጥ፣
የማሰብ ሱባዔ ያስፈልገዋል፤ሆኖም ለአሁኑ የአስተዳደር ዘመን በዚህ ምክንያት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማዘጋጀት የማስተማር ግዳጃችንን በያለንበት እንፈጽም፤ ጸሎታችንንም አናቋርጥ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጃትን ለመሥራት እንትጋ፤ ኩራታችንም እኛ በሠራነው፣ እኛ ባስገኘነው ይሁን፤ የኛነታችን መገለጫ የሆነውን ባህላችንን እንጠብቅ›› (አዲስ ሕይወት፣ቁጥር 5፣ግንቦት 1/19967 ዓ.ም)፡፡
2.7. በአቡነ ቴዎፍሎስ ቃለ-ምዕዳን ውስጥ ‹‹ዘላቂ አስተዳደርን ለማቋቋም ያለው ዘመቻ መላ ኢትዮጵያን እንጂ እንደሌሎች ዘመቻዎች ለወታደሮች ብቻ የሚተው አይደለም›› የምትለዋ ሐረግ የቴዎፍሎስን ሕልውና ማክተሚያ ያቃረበች፣ ሐብለ-ሰማዕትነትን በአንገታቸው ላይ የጠመጠመች፣ በተቀናቃኞቻቸው ወጥመድ ሰተት ብለው እንዲገቡ ያደረገች ናት፡፡ ከዚህ በኋላ ክሱ በገፍ መቅረብ ይጀምራል፡፡ ፓትርያርክ የማውረዱ ሴራ ኮ/ል አጥናፉ ተጠሪ በሆኑለት ‹‹የተሐድሶ ጉባኤ›› በተባለ መፍቀሬ-ደርግ ኮሚቴ ይጎነጎናል፡፡ ከሰሳና ወቀሳ ይዥጎደጎዳል፡፡ የሰቆቃወ-ቴዎፍሎስ ምጽአት ይቃረባል፡፡ ተከታዩ ርእሳችን እሱ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment