Thursday, January 12, 2017

ህየንተ “ወልታ ጽድቅ” - እንተ ይእቲ ሐዳስ መጽሐፍ!



በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 3 ቀን፣ 2009 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ባለመወድሱኩሉ ይሤኒ ለእመ አሠንይኮ – (አንተ) ለበጎ ካደረግኸው ሁሉም ለበጎ ይሆናልእንዲል ማኅበራዊ ሚዲያን (እስከ ተቻለን) ስለ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትም ሆነ ስለ ተቀረው አገራዊ ጉዳይ ለበጎ ዓላማ ለማዋል ሳንታትር የቀረን አይመስለኝም፡፡  ከታተርንባቸው አርእስተ ጉዳዮች ደቂቀ እስጢፋኖስንና ጥንተ አብሶን የተመለከቱ በእመቤታችን ዙሪያ እያጠነጠኑ ታሪክና ዶግማ የሚያጣቅሱ ረዘም ያሉ መጣጥፎ ይጠቀሳሉ፡፡ መረጥናቸው፡፡ አየናቸው፡፡ ከለስናቸው፡፡ በክለሳው የፍቁራን ወንድሞቼ ብርሃኑ አድማስ፣ የኄኖክ ኃይሌና የገብረ እግዚአብሔር ኪደ በቀና ልቡና የታጀበ ጥልቅ አስተያየት ታከለበት፤ ከእነርሱ በመጣ ጥቆማ መነሻነት መጣጥፎቹን በተጨማሪ ማጣቀሻ አዳበርናቸው፡፡ ዳበሩ፡፡ ተገጣጠሙ፡፡ ከግጥምጥሙወልታ ጽድቅየምትሰኝ ደንቧላ መጽሐፍ በሽልም ወጣች፤ ተወለደች! መወለዷ ጥሩ! ዜና ልደቷን ተሻግረን እስኪ የጽንሰቷን ነገር እንስማው

  1. ደቂቀ እስጢፋኖስ
ደቂቀ እስጢፋ(ኖስ) እንቅስቃሴየሚባለው አባ እስጢፋኖስ (1387-1437 ./ ... 1394-1444) በተሰኘ በአቡነ ሳሙኤል ዘቈየጻ እጅ የመነኰሰ የትግራይ/ አጋመ ተወላጅ የተመራና መጠነኛ አገራዊ ገጽታ የነበረው በዋናነት 15ኛው / ሁለተኛ ሩብ ተነቃቅቶ በክፍለ ዘመኑ መገባደጃ ያበቃ ሃይማኖታዊ አመጻ/ እንቅስቃሴ ነው፡፡ እንቅስቃሴው 1421 .. ሽሬ አካባቢ በይፋ እንደ ተጀመረና ኋላ ከሽሬ ተገፍቶ ወደ ምሥራቃዊ የትግራይ ጫፍ (ጉንዳ ጉንዶ/ ከስዋ/ ደብረ ገሪዛን/ ደብረ ገርዜን) እንደ ሄደ ይገመታል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በኢ..... ታሪክ ለመስቀልና ለእመቤታችን በሚደረግ ነባር የጸጋ ሰጊድ ትውፊት ላይ አማጺ በመሆን ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ውጭ ቀደም ባለው ጊዜ እንቅስቃሴው በአፈንጋጭነት እስከ መቼ እንደ ቀጠለ፣ በውስጡ ከመሪው ባሻገር እነ ማን እንደ ነበሩ፣ ፍጻሜው እንዴት እንደ ሆነበሕዝባውያን ዘንድ (በምሁራኑም ጭምር) በዝርዝር አይታወቅም፤ አይነገርም፡፡ ይሁን እንጂ 1996 .. / ጌታቸው ከእንቅስቃሴው አባላት 3ቱን ገድላት ከአበው ወአኃው ገድል ጋር ተርጉመው ካሳተሙ በኋላ እንቅስቃሴው የግኝት ያህል ተነግሮለታል፤ ተዘክሮለታል፡፡ መነገሩና መዘከሩ ክፋት አልነበረውም፡፡ ችግሩ ወዲህ ነው! ሃይማኖታዊ ገጽታው አንድም ደበዘዘ፤ አንድም በተጋነነ መልኩ ኦርቶዶክሳዊነትን ለማነወር በቈናጽላን ተቈነጸለ፡፡
ለቁንጸላው ትልቁ የይለፍ ወረቀት ከታሪኩ ቀደምት አጥኚዎችና ከገድላቱ መተርጉም የግል አስተያየት የተገኘ ይመስለኛል፡፡ የገድላትና የብራና ጽሑፍ አጥኚ ዘመናውያን ምሁራን በምሁርነታቸው ቢደነቁም ከሃይማኖት አንጻር ግን (በእኔ ትሁት አተያይ) አንድ ጉልህ ችግር አለባቸው – Instrumentalism! የእነሱ ቀዳሚ ዐላማ ከገድላቱ የሚገኘውን ረድኤትና በረከት ወይም የነጠረ ሃይማኖታዊ ፋይዳ ማጉላት አልነበረም፡፡ ዐላማቸው ከገድላቱ አዕማድና መስመሮች የቀደመውን ዘመን የፖለቲካ አሻራ መንቀስ ነበር፡፡ በነዚህ ዘመናውያን አጥኚዎች የቤተ ክርስቲያኗ ታሪክም ሆነ የሥነ ጽሑፏ ትሩፋት ፖለቲካዊ ወይም ታሪካዊ ክስተት የሚነጻጸርበርት መሳሪያ እንጂ ዶግማና ቀኖናው በራሱ ግብ ሲሆን አይታይም፡፡ ለእነሱ ዶግማና ቀኖና የጥናት ወረቀት ግብዐት እንጂ ውጤት አይደለም፡፡ Instrumentalism!
እንዲያ ባለፉት 40 ዓመታት ክፉኛ ከተቈነጸሉት ውስጥ በቀዳሚነት የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ የሚጠቀስ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ (በተለየ ጽንፍና አንጻር) የደቂቀ እስጢፋኖስ ገድላት ዋነኞች ሁነዋል፡፡ ዘመናውያኑ ጸሐፍት የደቂቀ እስጢፋኖስ በኩር የሆነውን የአባ እስጢፋኖስና የተወሰኑ ተከታዮቹን የአጭር ጊዜ እንቅስቃሴ መንፈሳዊ ገጽታው እጅጉን እስኪደበዝዝ ፖለቲካዊ ትርጓሜ ሰጡት፡፡ እንቅስቃሴውን ሲያሻቸው ከክልላዊነት፣ ሲያሻቸው ከሰሎሞናዊ ሥርዓተ መንግሥት ጋራ እያላጠቁ ለቁንጸላ አመቻቹት፡፡ አጥኚዎቹ በኦርቶዶክሳዊ ክበብ ውስጥ ሆኖ በመጠነኛ አፈንጋጭነት (heterodox movement) ሊታይ የሚችለውን እንቅስቃሴ ያለቅጥ በትርጓሜ በመለጠጥ አንዴ ‹‹ተሐድሶ›› ሌላ ጊዜ ‹‹ሉተራዊ›› ሌላ ጊዜ ‹‹ፈንዳሜንታሊስት/ አጥባቂ ፕሮቴስታንትነት›› እንደ ገና ሌላ ጊዜ ‹‹አይሁዳዊ›› ገጽታ እየሰጡ አንድምታውን አበረከቱት፡፡ በእነሱ ገደብ የለሽ አንድምታና Instrumentalist ጉዞ ላይ የኛ ቸልተኝነት ሲታከል ታሪኩ ለውጹአን ‹‹እልል በቅምጤ›› ሁኖ አረፈው፡፡ ከገድሉ ይልቅ አንድምታው በዝቶ የታሪኩ ሂደትና ባለታሪኮቹ ተረሱ፡፡ 15 በላይ ከሆኑት ገድላተ ደቂቀ እስጢፋኖስ ውስጥ ገድለ እስጢፋኖስንና በከፊል ደግሞ ገድለ አበው ወአኃውን ብቻ በማጮህ እንቅስቃሴው በፕሮቴስታንቶች ዘንድ ‹‹የጨነገፈ ሉተራዊነት›› በቤተ እስራኤላውያን ‹‹ተሐድሶ የታወጀበት ርቱዕ አይሁዳዊነት›› በፖለቲከኞች ‹‹የከሸፈ የአብርሆት /enlightenment/ እንቅስቃሴ›› በብዙኃን የቤተ ክርስቲያኗ ታረክ ጸሐፍት ‹‹ፀረ ማርያሞች የተቀጡበት አመጻ›› ተደርጎ ቀረበ፡፡ 12 የሚልቁት የገድላተ ደቂቀ እስጢፋኖስ ይዘቶች ተመልካች አጡ፡፡ ‹‹በቡሃ ላይ ቆረቆር…›› እንዲሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አንዳንድ ወንድሞቻችን እንቅስቃሴውን በብሔር መነጸር ለማንጸር ዳዳቸው፡፡


‹‹ወልታ ጽድቅ›› እነዚህን ተጻራሪ እይታዎች በአንድ ድኩም ኦርቶዶክሳዊ ደብተራ እይታ ለማንጸር ትወተረተራለች፡፡ በደቂቀ እስጢፋኖስ ታሪክ ማንጸሪያነት ረገድ በዋናነት የፕ/ ጌታቸው ትርጉም፣ የመ/ ካሕሳይ ሐተታ፣ የፕ/ ታደሰ ታምራት ምጥን ጥናት፣ የዶ/ ሥርግው /ሥላሴ አማርኛ የቤ/ መዝገበ ቃላት፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ፣ ያልታተሙ 12 ገድላተ ደቂቀ እስጢፋኖስ (በመጠኑ) የዲ/ዳንኤል ‹‹አራቱ ኃያልን›› የተለያዩ ገድላት፣ ፀዋትወ ዜማዎች፣ የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዜና መዋዕል፣ በሥዕላትና በሰጊድ ዙሪያ የተጻፉ ኦርቶዶክሳውያን ጽሑፎችና በውጭ አገር ሰዎች የተሰሩ ጥናቶችና ሌሎችም ጽሑፎች በግብዐትነት ውለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ጽሑፉ ለተጨማሪ ጥናት በተለይም ደግሞ ለኦርቶዶክሳዊ እይታ መነሻ እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡ ለጊዜው በፕ/ ጌታቸው በተተረጎሙት ላይ ባተኩርም የተቀሩትን ገድላት በሌላ ዐይን ማየት የሚሹ ካሉም ተጨማሪዎቹ ያልታተሙት 12 የሚልቁ ገድላት ስለ ኢሮብ ሕዝብ፣ ስለ ትግራይና ስለ አንዳንድ የኤርትራና የተቀረው ኢትዮጵያ ክፍል ጂኦግራፊዎች፣ ስለ ግራኝና ስለ ኦሮሞ ሕዝብ 15ኛና 16 / እንቅስቃሴ፣ በየዘመኑ ስለነበሩ የምስጢረ ሥላሴና የምስጢረ ሥጋዌ ክርክሮች ፍንጭ ያገኙባቸዋል፡፡
እንቅስቃሴው በብሔር ተዋጽኦ ረገድ የኢሮብና የአጋመ ተወላጆች በርክተው ቢታዩበትም በውስጡ እነ ኢዮሳብ ዘአምሐራ (አንጎት/ ወሎ) እነ ገብረ ክርስቶስ ዘእምነገደ ዟጉ (አገው) እነ ሀብተ ሥላሴ ዘብሔረ ደዋሮ (አርሲ?) የመሳሰሉ በአበምኔት ደረጃ የነበሩ መነኰሳትም አልፈውበታል፡፡ ስለሆነም ቢወደስም ቢነቀፍም ኅብረ ብሔራዊ ገጽታ ነበረው፡፡ ለመስቀልና ለእመቤታችን ከሚደረግ ሰጊድ ካፈነገጠው አባ እስጢፋኖስ ገድል ውጭ የሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ገድላቱ ለኦርቶዶክሳዊ አንባቢ ቅርብ ናቸው፤ ለእመቤታችንና ለመስቀል ከሌሎች ኦርቶዶክሳውያን ገድላት የተለየ አተያይ የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ‹‹ወልታ ጽድቅ›› ዐላማ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ታሪኩን ለሌሎች ከመተው ይልቅ በስክነትና በኃላፊነት መንፈስ አንጥረው ወደ ራሳችን ቅጽር እንዲመልሱት፣ በምንታዌ ውስጥ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን እንቅስቃሴው ሲጀምር ፈንገጥ ያለ ቢሆንም ተደጋግሞ በሚነገረው መልኩ በፍጹም ፕሮቴስታንታዊ/ ተሐድሶ/ ይሁዲ ሊሰኝ እንደማይችል በማመላከት ባሉበት እንዲፀኑና ከቈናጽላን ቅሰጣ ራሳቸውን ለማቀብ እንዲችሉ መጠነኛ ትጥቅ ለማቀበል ነውወልታ ጽድቅመከተቧ!
  1. ጥንተ አብሶ
ጥንተ አብሶን በሚመለከት ከቃሉ እስከ ብያኔው አባቶቻችን የሌሎቹን በተለይም የምዕራብ እና የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ያህል ለብቻው ትኩረት በመስጠት አንጥረውና አብጠርጥረው ያኖሩት አይመስለኝም፡፡ ዛሬ Original Sin የሚለውን ቃል ለጎግል ብናቀብለው እልፍ አእላፍ የምዕራብና የምሥራቅ ዶክትሪን ያስነብበናል፡፡ በኛ ዘንድ ግን እንዲህ ያለ ጽሑፍ በቀላሉ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ርእሱ የሚነሣው ብዙ ጊዜ ከእመቤታችን ጋር ተያይዞ እንጅ ከቃሉ ጀምሮ እስከ ምስጢራዊ ትርጓሜው ተብራርቶ በነገረ ድኅነት አንጻር ሲቀርብ አናይም፡፡ ይህ ማለት ግን ጽንሰ አሳቡ በተለያየ መንገድ በየመጻሕፍቱ አይነሣም ማለት አይደለም፡፡ ይነሣል፡፡ ያም ሆኖ በቀደመው ጊዜ በዚህ ረገድ የብሒል ልዩነት የሚጋብዝ ክርክር ስላልነበረ ቃሉ ነጥሮና ተቃዋሚ ቢመጣ በቀላሉ ተቀባብሎ ሊደገን በሚችል መልኩ የተቀናጀ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው የተወሰኑ የኛው ሰዎች ወደ ውጭ ለሥነ መለኰት ጥናት ወጥተው ሲመለሱ የሚያመጡትን ብሒል በንግግር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በሐሜት እያድበሰበስን፣ ወዲህ ወዲያ በሚወነጨፍ የተጋነነ ፍረጃ እያጅብን፣ አንዳንድ አስተዳደራዊ አለመግባባቶች ሲከሰቱ ለተጨማሪ የክስ ግብዐት እየተጠቀምን ተገዳዳሪ ብሒሎቹን ከማንጠር ይልቅ ‹‹ዐቀባ›› ‹‹አንጽሐ›› ተቧድነን ስድቡንና ፍረጃውን ያጎላነው፡፡ ይህ በኦርቶዶክሳዊ ክበበ-ሕሊና ውስጥ ሁነን ብንወያይበት ቀስ እያለ እልባት ሊያገኝ የሚችል ጉዳይ ባልተገባ መፈራረጅ የውጹአንን ቁንጸላ መጋበዙ ቅር ያሰኛል፡፡ ‹‹ወልታ ጽድቅ›› በዚህ ቅሬታና የበዛ ብዥታ ውስጥ አልፋ መጠነኛ ብርሃን ለመፈንጠቅ ጭል ጭል የምትልና ውጹአንን ለመወደር የምትውተረተር መጣጥፍን በውስጡ ይዛለች፡፡ በመጽሐፊቱ በምንታዌ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ወንድም እኅቶቼ እንዲፀኑባትና መስተጻርራንን እንዲወድሩባት (እንዲመክቱባት) ‹‹አርምሞ ተዐቅብ ሃይማኖተ›› በሚል የተሐራሚ ትህትና ወጭ ወራጁን የሚታዘቡ ሊቃውንት ለተሻለና ለተፍታታ ጽሁፍ እንዲነሳሱባት ምኞቴ ነው፡፡
በወልታ ጽድቅ፡- በጥንተ አብሶ አንጻር ተደጋግማ የምትነሣው የነፍስ ተፈጥሮና ባሕርይ በኦርቶዶክሳዊ እይታ፣ ጥንተ አብሶ ከቃሉ ትርጓሜ ጀምሮ እስከ ምስጢራዊ ትርጓሜው፣ የየአብያተ ክርስቲያናቱ የነፍስና ተፈጥሮና የጥንተ አብሶ አረዳድ፣ ጥንተ አብሶ ከምልዐተ ኃጢአት ያለው ልዩነት፣ ጥንተ አብሶ ሲባል ኃጢአቱ ነው ወይስ የኃጢአቱ ውጤት ጭምር፣ ተላለፊ ነው የሚባለው በምን መልኩ ነው፣ ድምሳሴው እንዴት ተከናወነ፣ ጥንተ አብሶ አሁን ድረስ አለ ወይስ የለም፣ ለዚህ ሁሉ የኢ..... መጻሕፍት ምን ይላሉ፣ በአንጽሐ ብሒል ውስጥ ያሉ የውስጥ ልዩነቶች፣ በዐቀባ መካከል ያሉ ልዩነቶች፣ የኢ..... ዝንባሌ ወደ የትኛው እንደሆነ፣ በዐቀባና በአንጽሐ መካከል አጨቃጫቂ የሆኑ ቁልፍ ቃላት፣ በክርክር ሒደቱ የሚታዩ መፈራረጆችና እየፈጠሩት ያለው ክፍተት እስከ ተቻለ የቤተ ክርስቲያናችንን ትውፊት ማዕከል በማድረግ ተዳስሰዋል፡፡ አሁን ተራው የእናንተ ነው፡-
‹‹ንሥኡ ወልታ ጽድቅ!››

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount