Pages

Friday, August 4, 2017

ዓላማውን ያልሳተ ሕይወት

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አንድ እኁ (ወንድም) ወደ አባ ሄላርዮን መጣና፡- “አንድ ሰው ሌሎች እርሱን የሚመስሉ አኀው ወደ ዓለም ተመልሰው ሲወድቁ አይቶ እንደ እነርሱ ላለመውደቅ ምን ማድረግ አለበት?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም እንዲህ አሉት፡- “አንድ ታሪክ ልንገርህ፡፡ ጥንቸሎችን ለማደ’ን የሚሮጡ ውሾችን አስብ፡፡ ከእነዚህ ውሾች መካከል አንዱ በሩቅ ያለችን ጥንቸል ተመለከታት፡፡ ወዲያውም እርሷን ለመያዝ ሩጫውን ጀመረ፡፡ አብረዉት የነበሩ ውሾችም አንዱ ሲሮጥ አይተው ጥንቸሊቱን ሳያዩዋት ተከትለውት ሮጡ፡፡ ለጊዜው አብረዉት ሮጡ፡፡ ሲደክማቸው ግን ሩጫውን አቆሙ፡፡ ማቆም ብቻ ሳይኾን እያዘገሙ ቅድም ወደ ነበሩበት ስፍራ ተመለሱ፡፡ ያ አንዱ ውሻ ግን ሩጫውን ቀጠለ፡፡
ሌሎቹ ውሾች አብረዉት ባይሮጡ እንኳን ብቻውን ቀጠለ፡፡ በጣም ቢደክመውም እንኳን በርትቶ ቀጠለ፡፡ የሌሎች ውሾች መመለስ ተስፋ አላስቆረጠውም፡፡ ድንጋዩ ቢያደናቅፈው፣ ጢሻ ቢገጥመው ከእነዚህ የተነሣ ሰውነቱ ቢቆሳስልም የሚያየው ጥንቸሊቱን ስለ ነበረ እነዚህን ችግሮች ችላ አላቸው፡፡
ልክ እንደዚሁ የክርስቶስን ፍቅር ለመያዝ የሚሮጥ እኁም ብዙ ሰዎች ወደ ኋላ ብለው ቢወድቁም እርሱ ግን በዚያ የተሰቀለውን ክርስቶስ እስኪይዝ ድረስ ዓይኑን በክርስቶስ መስቀል ላይ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡”
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? አንድ ሰው የሚኖረውን ኑሮ የኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ዋና ዓላማ ወይም ግብ የኾነው ይኸውም ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነትና በኅብረት ለመኖር ዓላማ አድርጎ ሊኖር ይገባዋል፡፡
ይህን ዓላማ ያላደረገ ሕይወት ቀጣይነት ያለው አይኾንም፡፡ ይህን ዓላማ ያላደረገ ጸሎት፣ ይህን ዓላማ ያላደረገ ጾም፣ ይህን ዓላማ ያላደረገ ምጽዋት፣ በአጠቃላይ ይህን ዓላማ ያላደረገ ማንኛውም ምግባር ጥቃቅን ምክንያቶችን ወይም ሰበቦችን ሲያገኝ ይዝላል፡፡ እያዘገመም እንደ እነዚያ ውሾች ትቶት ወደ ኼደው የዓለም ሕይወት ይመለሳል፡፡

ይህን ዓላማ ያላደረገ መንፈሳዊ ጉዞ ጥቂት ፈተና፣ ጥቂት መከራ፣ ጥቂት ቁንጥጫ፣ ጥቂት ቀቢጸ ተስፋ፣ እንደ እነዚህም ያሉ ነገሮች ሲገጥሙት ሃይማኖትን እስከ መተው ያደርሳል፡፡
በዚህ ባለንበት ዘመን ክርስትናን ለካንሰር በሽታ መፈወሻ፣ ለዚህ ዓለም ጭንቀት ማራገፊያ፣ በአጠቃላይ ለዚህ ዓለም ኑሮ ማስተካከያና ማደላደያ ካደረጉት ዓላማውን የሳተ ሕይወት ነው፡፡ ይህ ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት አይደለም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ግቡ አንድና አንድ ነው - ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትና ኅብረት መፍጠር! ሌሎች በዚህ ምድር የምናከናውናቸው ነገሮች ወደዚህ የሚያደርሱን ናቸው፡፡ ይህ ካልኾነ ግን ዓላማውን የሳተ ሕይወት ነው፡፡
ታዲያ ስንቶቻችን በዚሁ አቅጣጫ እየኼድን እንኾን? ዓላማውን ያልሳተ ሕይወት የምንመራ ስንቶች ነን? 

1 comment:

  1. አሜን እሜን

    ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ግቡ አንድና አንድ ነው - ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትና ኅብረት መፍጠር!

    ReplyDelete