በዲ/ን ሕሊና
በለጠ
ዘኆኅተብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 12 ቀን
2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አገልግሎት የሚለው
ቃል ገልገለ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ገልገለ (አገለገለ) ማለት ተገዛ፣ ታዘዘ፣ ዐገዘ፣ ረዳ፣
ጠቀመ፣ ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ጌታውን
ደስ አሰኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎት ማለት መታዘዝ፣ መገዛት፣ መርዳት፣ መጥቀም…ማለት ይሆናል፡፡ ማንኛውም ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥራ አገልግሎት ነው፡፡
ለመንግሥት የሚሠራ የመንግሥት አገልጋይ፣ ለግለሰብ የሚሠራ የግለሰብ አገልጋይ፣ ለእግዚአብሔርም የሚሠራ የእግዚአብሔር አገልጋይ
ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ
አገልጋዮችን በተለያየ ስያሜ ጠርቷል፡፡ ምንም አይነት መብት በራሱ ላይ የሌለውንና በጌታው ሐሳብ ፍፁም አዳሪ የሆነውን ተገዢ
ባሪያ በማለት ገልፆታል፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ‘ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደባሪያ
ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ’ በማለት የተናረው ይህን ያጠናክራል፡፡ (1ቆሮ. 9÷19) አብሮት የሚያገለግለውን ቲኪቆስንም ‘በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ’ በማለት ጠርቶታል፡፡ (ቁላ
4፡7) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ቅዱሳን ባሪያዎች ሁኑ በማለት አገልግሎታችን በፍፁም
መገዛት እንዲሆን ይመክረናል፡፡ (1ጴጥ. 2‘፡16) በራሱ ላይ ሙሉ ነፃነት ያለውን አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱስ ሠራተኛ ይለዋል፡፡
(ሉቃ 10፡2፣ ቁላ 4፡11፣ 2ጴጥ 1፡8) ይህ ከባሪያ ይልቅ በራሱ ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው ነው፡፡ ከፈለገ አለማገልገል
ይችላል፡፡ በባሪያና በሠራተኛ መካከል ነፃነቱ መካከለኛ የሆነው ደግሞ ብላቴና፣ ሎሌ ተብሎ የተጠራው ነው፡፡