Thursday, July 5, 2012

ማንም ኋለኛ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቁረጥ- በቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ!


ከመጀመርያ ጀምሮ መልካም ነገርን መምረጥ ክፉ አይደለም፤ በመልካምነት አለመቀጠል ግን ብዙ ወቀሳን ያመጣል፡፡ የብዙ ሰዎች ክፉ መሆን በዚሁ የሚመደብ ነው፤ ብዙዎች ሕይወታቸውን በመልካም ጀምረው በኋላ ግን በክፋት መርዝ ተጠምቀው ሲሰክሩ ተመልክቻለሁና፡፡

 እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፡፡ ምንም እንኳን አሁን ወደ ክፋት ጥልቅ ወርዳችሁ ቢሆንም “ከዚሁ ተመልሰን መነሣት አይቻለንም፤ መለወጥም አይሆንልንም” በማለት ተስፋ የምትቈርጡ አትሁኑ፡፡ እናንተ ስትፈቅዱ እግዚአብሔርም ሲረዳችሁ ከክፋት ዐዘቅት መውጣት በእጅጉ ቀላል ነውና፡፡

 ከሁሉም በላይ አመንዝራ ተብላ በከተማው ዘንድ ትታወቅ የነበረችውን ሴት በመልካምነቷ እንዴት እንደምትወደስ አልሰማችሁምን? እየነገርኳችሁ ያለሁት በዮሐንስ ወንጌል ላይ ስለተጠቀሰችው ሴት አይደለም፡፡ በእኛ ዘመን ስላለችውና ፍኒሳ ከተባለችው ጋጠ ወጥ ከተማ ስለተገኘችው ሴት እንጂ፡፡ ይህች ሴት አስቀድማ በመካከላችን በአመንዝራነቷ ትታወቅ ነበር፡፡ በክብር ቦታ ሁሉ የመጀመርያን ስፍራ የምትይዝ ሴት ነበረች፤ ስሟ በሀገሩ ሁሉ የገነነ ነበር፤ በእኛ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሲልስያ እና በቀጰዶቅያም ጭምር እንጂ፡፡ ይህች ሴት ብዙ ከተሞችን አፍርሳለች፤ የብዙ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ንብረት በልታለች፡፡ ብዙዎችም “መተተኛ ናት” ይሏታል፤ ውበቷን ብቻ ሳይሆን መድኃኒትም ጭምር ትጠቀም ነበርና፡፡ ከዚሁ የተነሣ በአንዱ ቀን የንግሥቲቱን ልጅ እስከ ማማለል ደርሳለች፡፡ ጭካኔዋ የክፉ ክፉ ነበር፡፡

 ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ግን ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ ሆኖም ግን በዓይኔ ፍጹም ተለውጣ ራሷን በእግዚአብሔር የጸጋው ዙፋን ፊት ድፍት አድርጋ ስታለቅስ አየኋት፡፡ አሁን የቀድሞ ክፉ ሥራዎቿን ሁሉ እርግፍ አድርጋ ትታለች፤ በእርሷ ላይ ከነበሩት የአጋንንት ጭፍራ ተፋትታ አሁን የክርስቶስ ሙሽሪት ሆናለች፡፡

 በእውነት ከእርሷ የሚከፋ ሰው በዐይኔ አላየሁም፡፡ በኋላ ግን ራሷን ከእንደዚህ ዓይነቱ ክፉ ሥራ ከለከለች፡፡ ከዚህ በፊት ስትለብሳቸው የነበሩት የምንዝር ጌጦች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሁሉ በእርሷ ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ እነዚህን ሁሉ አወላልቃ ጥላ ለእግዚአብሔር በሚገባ የማቅ ልብስ ለብሳ ራሷን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አድርጋለች፡፡ ይህችን ሴት ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ለመመለስ የሀገሪቱ መኳንንት ከዙፋናቸው ወርደው ለምነዋት ነበር፤ ወታደሮች ትጥቃቸውን ታጥቀው በመምጣት አስፈራርተው ሊወስዷት ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ሊመልሷት አልተቻላቸውም፤ ከተቀበሏት ደናግላን በዓት ሊያስወጧት አልተቻላቸውም፡፡

 ይህች ሴት ከዚያ አስነዋሪ ሕይወቷ ተመልሳ ለቅዱስ ቁርባን በቅታለች፤ ለእግዚአብሔር ጸጋ የተገባ ሆና ተገኝታለች፤ ኃጢአቷን ሁሉ በጸጋው አጥባለች፤ ከተጠመቀች በኋላ ራሷን መግዛት ችላለች፡፡ ይህች ሴት የቀድሞ ሕይወቷን፣ ገላዋን ለብዙ ወዳጆቿ ያሳየችበትን ሕይወት “የእስር ቤት ሕይወት” ብላ ትጠራዋለች፡፡ በእውነት “ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ” የሚለው የከበረው የጌታ ቃል በእርሷ ሲፈጸም አየነው፤ መለወጥ ከፈለግን እኛን ማሰናከል የሚቻለው ኃይል እንደሌለ አወቅን ተረዳን፡፡

 እንግዲያስ ተወዳጆች ሆይ! ተስፋ በመቁረጥ በኃጢአት ዐዘቅት ሰምጠን የምንቀር አንሁን፡፡ ከእኛ መካከል በጽድቅ በረሀነት የሚኖር ማንም አይገኝ፡፡ ፊተኛ ነኝ የሚልም ከቶ አይኑር፤ ብዙ አመንዝሮች እርሱን አልፈዉት ሊሄዱ ይችላሉና፡፡ ማንምም ኋለኛ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቁረጥ፤ ከልቡ ከተጸጸተና ከተመለሰ ፊተኛ መሆን ይቻለዋልና፡፡

 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- “ይህም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተመለሰችም፡፡ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች” /ኤር.3፡7/፡፡ ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ የቀድሞ ኃጢአታችንን አያስበውም፤ እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ በእውነት እርሱ በቀድሞ ኃጢአታችን የሚወቅሰን አይደለም፡፡ እርሱ እንደ ሰው አይደለምና፡- “እስከ አሁኑ ሰዓት ወዴት ነበርክ?” የሚለን አይደለም፡፡ ብቻ እኛ እንመለስ እንጂ እርሱ እንዲህ ያለ አምላክ አይደለም፡፡

ይህን እንደናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!   

Monday, July 2, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- ክፍል ሦስት!


      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 በክፍል ሁለት ትምህርታችን ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ሥርዓት ከሰዎች ተመርጠው ከሚሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹም የሚለይባቸውን ነጥቦች ማሳየት ጀምረን ነበር፡፡ የሚምር ነው፤ የታመነ ነው፤ በሰማያት ያለፈ ነው፤ በድካማችን የሚራራልን ነው ብለን አራት ነጥቦችን አይተናል፡፡ ለዛሬም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡ ቢችሉ አስቀድመው ይጸልዩ!
1. በመሐላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ መሐላ የማይለወጥ ነገርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው ይህን አላደርግም እንዲህም አላደርግም ብሎ ከማለ የነገሩን ሓቅነት ያመለክታል፡፡ “ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው (ሎሌ በጌታው፣ ገረድ በእመቤቷ፣ ደቀ መዝሙር በመምህሩ፣ ልጅ በአባቱ) ይምላሉና ለማስረዳትም የሆነው መሓላ የሙግት (የክርክር የጸብ) ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ (አብዝቶ) ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ እግዚአብሔር ሊዋሽ (ሊፈርስ፣ ሊታበል) በማይቻል በሁለት  በማይለወጥ ነገር በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ በመሐላ (በሥጋዌው) በመካከል ገባ፤ ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን (ተስፋችንን አጽንተን ለያዝን ለእኛ ልቡናችን እንዳይነዋወጥ እንደ ወደብ የሚያጸናን ፍጹም ደስታ አለን)፤ እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ (እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሹሞ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት የገባ የዘላለም አስታራቅያችን ፊተውራርያችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ነው” እንዲል /ዕብ.6፡16-19/፡፡ እንግዲያውስ ከሌዋውያን ክህነት በሚበልጥ ክህነት፣ እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ዘላለማዊ በሆነ ክህነት የተሾመ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ጥሪ የተመረጡ ቢሆኑም አገልግሎታቸው ጊዜአዊ ስለ ነበረ ያለ መሓላ የተሾሙ ነበሩና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከኦሪት ለምትበልጥ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማይም አስታራቂ ሆኖአልና በመሓላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያውም ስለዚሁ ሲናገር እንዲህ አለ፡- “እነርሱም ያለ መሓላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፡- ጌታ፡- አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሓላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሓላ ካህን እንዳልሆነ መጠን እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል /ዕብ.7፡20-22/፡፡ በዚህም ኦሪት ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስላልቻለች እንደተሻረች ወንጌል ግን ማዳን ስለቻለች፣ ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስለቻለች ሕልፈት ሽረት እንደሌለባት አወቅን፤ ተረዳን፡፡ ካህኑም አገልግሎቱም እንደዚሁ፡፡ ለምን ቢሉ ያለ መሓላ ከተሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ይልቅ በመሓላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ይበልጣልና፡፡  
2. የማይለወጥ ክህነት ያለው ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የቀደሙት ሊቃነ ካህናት ያለ መሓላ ለተሠራችው ሕገ ኦሪት የተሾሙ ስለ ነበሩ አንድም መዋትያን ስለ ነበሩ ካህናት የሆኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመሓላ ለተሠራችው ወንጌል የተሾመ ስለሆነ አንድም ሞትን በሞቱ ገድሎ ተነሥቶ በሕይወት የሚኖር ሥግው ቃል ስለሆነ ወራሽ የሌለው አንድ ነው፡፡ ክህነቱም (ኃጢአት የማሥተስረይ ችሎታውም) የባሕርዩ ስለ ሆነ በሞት (ሞት ሊያሸንፈው ስላልቻለ) አይለወጥም፡፡ የባሕርዩ የሆነውን ለእነዚያ በጸጋ ሰጥቷቸው ነበርና ሥጋ ለብሶ በክህነት ሲገለጥ ባሕርያዊ ሥልጣኑ የማይሻር ሆነ፡፡ ሐዋርያውም ይህን አስመልክቶ ሲናገር፡- “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው አለን /ዕብ.7፡23-24/፡፡
3. ሞትን አሸንፎ በሕይወት የሚኖር ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና፡፡ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” /ዕብ.7፡25/፡፡ ካቶሊክ ሳትታሰብ ፕሮቴስታንትም ሳትታለም ከ325 እስከ 389 ዓ.ም የነበረውና የቀጰዶቅያ አውራጃ ለምትሆን የቂሳርያ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ይህን ሲተረጕመው እንዲህ ይላል፡- “ይህ ቃል የሚያመለክተን የጌታችን አስታራቂነቱን ነው፡፡…  ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው  (ሰው ሆኖ ሰውና እግዚአብሔርን ያስታረቀ) ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም (ለሁሉ ቤዛ አድርጎ ራሱን አሳልፎ ለሞት ለሕማም የሰጠ) ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው /1ጢሞ.2፡5-6/፡፡ አሁንም ይህ ሥግው ቃል ከመቃብር በላይ ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ “በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” እንላለን /1ኛ ዮሐ.2፡1/፡፡ ሆኖም ግን ይህን በአብ ፊት በመውደቅና በመነሣት የሚያደርገው አይደለም፤ በዕለተ ዐርብ በተቀበለው መከራ ባደረገው ተልእኮ እንጂ”  /On The Son, Theological Oration, 4(30):14/፡፡ ከ347 እስከ 407 ዓ.ም የነበረውና የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል፡- “የቀደሙት ሊቀነ ካህናት መዋትያን ስለ ነበሩ ብዙ ናቸው፡፡ እርሱ ግን የማይሞት ሕያው ስለሆነ አንድ ነው፡፡ የማይሞትም ስለ ሆነ እርሱን አምነው የሚመጡትን ሁሉ ሊያድናቸው ይቻለዋል፡፡ እንደምንስ ያድናቸዋል? የሚል ሰው ካለም “በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ነው” ብለን እንመልስለታለን፡፡ በሃይማኖት በንስሐ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን የሚያድናቸው በዕለተ ዐርብ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ በኋላም ጭምር እንጂ፡፡ በወደደበት ጊዜም ለመነላቸው፡፡ ሁል ጊዜ ይለምናል ብሎ የሚያስብስ ከቶ እንደምን ይኖራል? ጻድቃንስ እንኳ አንድ ጊዜ በለመኑት ልመና የሚሹትን የሚያገኙ አይደሉምን?… ሐዋርያውም ሁል ጊዜ ቁሞ የሚያገለግል እንዳያስመስሉት በማሰብ በመትጋት መሥዋዕት አንድ ጊዜ እንደሠዋ አስረዳ፡፡ አንድ ጊዜ ሰው እንደ ሆነ አንድ ጊዜ ተሾመ፤ አንድ ጊዜ እንደ ተሾመ አንድ ጊዜ አገለገለ፡፡ ሰው በሆነ ጊዜ የሰውነትን ሥራ በመሥራት ጸንቶ እንዳልኖረ ሁሉ ባገለገለ ጊዜም በማገልገል ጸንቶ አልኖረም፡፡ አሁን ቢያገለግል ኖሮ ሐዋርያው ቆመ እንጂ ተቀመጠ ባላለ ነበርና፡፡ መሥዋዕቱ ቁርጥ ልመናውን አንድ ጊዜ ወደ እዝነ አብ (በአብ ጀሮ) ወደ ገጸ አብ (በአብ ፊት) የደረሰች ስለሆነች እንደ ቀደሙት ሊቃነ ካህናት ሁል ጊዜ ሊያገለግል አያስፈልገውም” /Homily on the Epistle of Hebrews, Hom.13/፡፡ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትርጓሜም ተመሳሳይ ነው፡- “በዕለተ ዐርብ ባደረገው ተልእኮ እስከ ምጽአት ድረስ ሲያድንበት የሚኖር ስለ ሆነ በእርሱ አስታራቂነት ወደ እግዚአብሔር የቀረቡትን ማዳን ይቻለዋል” /የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከነ ትርጓሜው፣ ገጽ 434/፡፡ እንግዲያውስ ተወዳጆች ሆይ! “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል” የሚል ጥሬ ምንባቡን ብቻ በመያዝ እንዳይሳሳቱ ይጠንቀቁ፡፡ ይህ ማለት አስቀድመን እንደነገርንዎት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ዐርብ የማስታረቅ አገልግሎት ከአዳም መፈጠር ጀምሮ እስከ ዕለተ ዐርብ ላሉት ሁሉ ብቻ ሳይሆን እስከ ዕለተ ምጽአት የሚፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በዚሁ የዕለተ ዐርቡ የማስታረቅ አገልግሎት እያመነ እንደሚድን ደሙም የማስታረቅ ችሎታ እንዳለው የሚገልጽ ነውና /ዮሐ.17፡20-21/፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የሠዋው መሥዋዕት እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት መሥዋዕት ተረፈ ኃጢአት (ያልተደመሰሰ ኃጢአት) አስቀርቶበት አሁን ያንን ለማስተስረይ የሚወድቅ የሚነሣ አይደለምና፡፡ ጸሎቱና መሥዋዕቱ ምልአተ ኃጢአትን (ኃጢአትን ሁሉ) ለመደምሰስ አንድ ጊዜ ተፈጽሟልና /ዮሐ.19፡30/፡፡ ስለዚህ ይማልድልናል ስንል “የዕለተ ዐርቡ ቤዛነት፣ ካሣ፣ ሞት፣ ደም መፍሰስ አዲስና በየዕለቱ ንስሐ የሚገቡትን የሚያቀርብ የሚያድን ነው” ማለት መሆኑን ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡  ስለዚህም ነው ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች “ከእርሱ ውጪ ሌላ ሊቀ ካህን የለንም፤ ከቅዱስ ሥጋዉና ከክቡር ደሙ ውጪ ሌላ በየቀኑ የምናቀርበው መሥዋዕት የለንም” የምንለው፡፡ ክህነቱ የማይለወጥ፣ መሥዋዕቱም አንድ ጊዜ ቀርቦ በጊዜ ብዛት የማይበላሽ ሕያው አሁንም ትኵስ ነውና፡፡ ትኵስ መባሉም ነፍስ ስላለው ሳይሆን መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ነው፡፡
4. በእርሱ በኵል (እርሱን አምነው) ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድን የሚችል ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” /ዕብ.7፡25/፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጌታችን ራሱ እንዲህ ብሏል፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔ የበጎች በር (ደጅ) ነኝ… በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ (በእኔ ያመነ) ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል (ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ያገኛል፤ መንግሥተ ሰማያትንም ይወርሳል)” /ዮሐ.10፡7፣9/፤ “እኔ መንገድና እውነት ነኝ (የሕይወትና የጽድቅ መንገዷ እኔ ነኝ) በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም (እኔን ልጅ ካላለ በቀር አብን አባት የሚለው የለም አንድም በእኔ የማያምን ከአብ ጋር መታረቅ አይችልም)” /ዮሐ.14፡6-7/፡፡ እውነት ነው! የሕይወት መሥመር ክርስቶስ ነውና ክርስቶስን አምኖ የሚኖር ሰው ሕይወትን ያገኛል፡፡ ማንም ይሁን ማን ክርስቶስን ካላመነ ቢጾምም ቢጸልይም ያለ ክርስቶስ ዋጋ የለውም፤ በክርስቶስ ካልሆነ በቀር ዓለም በራሱ ሕይወት የለውም፤ በክርስቶስ ቤዛነት የማያምን በሌላ በምንም መንገድ አይድንም፡፡
5. ድካም የሌለበት ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ድካምን የሚለብሱ እንደነበረ መጽሐፍ የሚሰክረው የታወቀ የተረዳ እውነት ነው፡፡ ይህም በጣም የተገለጠ ድካም በታየባቸው በኤሊ ልጆች መረዳት እንችላለን፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉ የኤሊ ልጆች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ሥጋ ለግል ጥቅማቸው በማዋል እግዚአብሔርን ያሳዝኑ ነበር፡፡ ይህም ሳይበቃቸው በመገናኛው ድንኳን ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ያመነዝሩ ነበር /1ሳሙ.2፡12-22/፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ጻድቅና ቅን፣ ነቀፋ የሌለበት እውነተኛ፣ ከኃጢአት ሁሉ ፈጽሞ የራቀ የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ ነው /ዕብ.7፡26/፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን ሲመሰክሩ እንዲህ ይላሉ፡- “በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም” /ኢሳ.53፡9/፤ “ኃጢአት ያላወቀው” /2ቆሮ.5፡21/፤ “እርሱ ኃጢአትን አላደረገም” /1ጴጥ.2፡22/፤ “በእርሱ ኃጢአት የለም” /1ዮሐ.3፡5/፡፡ ጌታችንም ራሱ እንዲህ ብሏል “ከእናንተ ስለ ኃጢአት (ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ) የሚከሰኝ ማን ነው?” /ዮሐ.8፡46/፡፡ ለሞት አሳልፈው የሰጡት ተቃዋሚዎቹም ሳይቀሩ ይህን መስክረዋል፡- “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” /ማቴ.27፡4/፤ “በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም” /ሉቃ.23፡4/፡፡  
6. ስለ ራሱ መሥዋዕት የማያሻው ነውር የለሽ ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ዕሩቅ ብእሲና እንደ ማንኛውም ሰው ኃጢአተኞች ስለነበሩ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር በመሥዋዕት በጸሎት ከማስታረቃቸው በፊት ስለ ራሳቸው ቁርባን መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር /ዘሌ.9፡7፣ ዘሌ.16፡6፣ ዕብ.5፡3-4/፡፡ ሊቀካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስቀድመን እንደተናገርነው በባሕርይው ድካም የሌለበት ቅዱስ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት ንጹሕ፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ሳይጐድልበት የሚያድል ባዕለ ጸጋ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ ቡሩክ፤ ከኃጢአተኞችም የተለየና ነውር የሌለበት ፍጹም ስለሆነ “እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈለገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና” /ዕብ.7፡27/፡፡ 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር (ሳምንት ይቀጥላል)!

Saturday, June 30, 2012

ስምህ


 ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! መንፈሳዊ ምስጋና ሁሉ ለአንተ ይገባል፡፡ ዋጋው የማይታወቅ ነጋዴ ገንዘቡን ሁሉ ሰጥቶ የተወዳጀው እውነተኛ ዕንቁ ደንጊያ አንተ ነህ፡፡ ይህንን የዕንቁ ደንጊያ በሰውነታችን ውስጥ ያበራ ዘንድ ደግሞ ዛሬ ለእኛ አድርግልን፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የተቀደሰው ስምህ የልባችን ደስታ የሰውነታችን ሽልማት ጌጥ ነው፡፡

Friday, June 29, 2012

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለ2004 ዓ.ም. ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የዘማናችሁን ዐሥራት ሳይሆን መላ ዕድሜአችሁን ለወንጌል አገልግሎት የሰጣችሁ፣ ዘመናዊውን ዓለም ተላምዳችሁ ዘመናውያን ሰዎች ለመሆን ሳይሆን መንፈሳዊውን ዕውቀት ቀስማችሁ የዓለም ብርሃን ለመሆን በመንፈሳውያን ኰሌጆች ውስጥ እየተማራችሁ የምትገኙና የትምህርታችሁን የመጀመርያው ምዕራፍ አጠናቃችሁ በእግዚአብሔር ስም ልትመረቁ የበቃችሁ የተወደዳችሁ ልጆቼ! በፍቅሩ ቅመም አልጫውን ምድር ባጣፈጠው፣ ጨለማውን ዓለም በቃሉ ባበራው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰላም እላችኋለሁ፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቼ! እግዚአብሔር አምላካችን የአንድ ቀንን መታመን የማይረሳ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማገልገል ብቁዎች መሆን አለብን ብላችሁ ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የመጣችሁበትን የአንዷን ቀን ፍቅራችሁን የሚያስብ አምላክ ነው፡፡ ምንም እንኳን የጓዳውና የቤቱ ሥራ አስፈላጊና የማይታለፍ ቢሆንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከማርታ ይልቅ በማርያም ደስ ተሰኝቷል፡፡ ማርታ ያላትን ለትልቁ እንግዳ ልታቀርብ ባለቤቱን ጌታ እንደ እንግዳ ቆጥራ መባረክን ጀመረች፡፡ ማርያም ግን በቤቷም የሚያስተናግዳትን፣ የታዛዋ ብቻ ሳይሆን የሕይወቷም ራስ የሆነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልታደምጥ ከእግሩ ሥር ቁጭ አለች /ሉቃ.10፡38-42/፡፡ ጌታችን ለእርሱ ከማድረጋችን በፊት ያደረገልንን፣ ስለ እርሱ ከመናገራችን በፊት የነገረንን እንድናስተውል ይፈልጋል፡፡ የማርታ እኅት ማርያም ይህን የተረዳች ትመስላለች፡፡ እናንተም ደቀ መዛሙርት ያሳለፋችኋቸው ዓመታት ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብላችሁ ድምፁን የሰማችሁበት ዓመታት ናቸውና ደስ ይበላችሁ! ምንም እንኳን የዘወትር ትካዜአችን እንደ ቃሉ መኖር አለመቻል ቢሆንም በቃሉ የመኖርን ኃይል በንስሐና በጸሎት ልንለምን ይገባናል፡፡

  የተወደዳችሁ ደቀ መዛሙርት ልጆቼ! እስከ ዛሬ የሚታሰብላችሁ ልጆች ነበራችሁ፡፡ ዛሬ ግን የምታስቡ ወላጆች እንድትሆኑ ለወንጌል ሙሽራይት ቤተ ክርስቲያን ትድራችኋለች፡፡ በዘመናት ሁሉ እንደታየው ወንጌል ዝም ማለት የማትወድ ናት፡፡ ወንጌልም መክና አታውቅም፡፡ የወንጌል የማጌጫ ዘውዷ አክሊለ ሦክ፣ የሥልጣን ዘንጓም መስቀል፣ መገለጫዋም መገፋት ነው፡፡ የማትገድለው ወንጌል ለሰማዕትነት የጨከነች ናትና አዲሱ ኑሮአችሁን ቤተ ክርስቲያን ትመርቃለች፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቼ! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ያህል ካስተማራቸው በኋላ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ከልሎ ወደ ዓለም ልኳቸዋል፡፡ እናንተም ላለፉት ዓመታት የደቀ መዝሙርነት ትምህርታችሁን ተከታትላችኋል፡፡ ትምህርታችሁን በሞገስ ለሕዝብ እንዲደርስ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል የምታገኙት በጽሞናና በጸሎት በመቆየት ነው /ሉቃ.24፡49/፡፡ ቤተ ክርስቲያን እናንተን መምህራን አድርጋ ሳይሆን ደቀ መዛሙርት አድርጋ መርቃለች፡፡ ስለዚህ የሁል ጊዜ ተማሪዎች እንደሆናችሁ፣ ትምህርቱም የማያልቅ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባችኋል፡፡

  የተወደዳችሁ ልጆቼ! ምንም ብታስተምሩ፣ ምንም ብትጽፉ ዓለም አበባ ይዛ እንደማትቀበላችሁ እወቁ፡፡ ይህ በእናንተ የተጀመረ ሳይሆን የዓለም መገለጫዋ መሆኑን አትዘንጉ፡፡ ልዩ ልዩ ነቀፋና ስደት ሲመጣባችሁ ከዓለም እንደተጣላችሁ አትቁጠሩት፡፡ እንዲያውም ከዓለም ጋር እንደተዋወቃችሁ ቁጠሩት፡፡ ዓለም እንደዚህ ናትና፡፡ ጎበዝ የሚባለው ሳይቀር በመገፋት ውስጥ በኀዘን ይጐዳል፡፡ የሚታይ ተስፋ እያጣም በብቸኝነት ይንገላታል፡፡ ይሁንና ሰው መተማመኛ የማይሆን የሸምበቆ ምርኩዝ መሆኑን ቃሉ ይነግረናል /ኢሳ.36፡6/፡፡ ስለዚህ በሁሉም ነገር ውስጥ የጠራችሁን ጌታ ክርስቶስን ተመልከቱ /ዕብ.3፡1/፡፡ የተቀበላችሁትን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ያልተቀበላችሁትንም ለመስጠት ፈቃደኞች ሁኑ፡፡ ፍቅርን አላያችሁ ከሆነ ከእናንተ ይልቅ የፍቅርን ረሀብ የሚያውቅ የለምና ፍቅርን ስጡ፡፡ የሚያዝንላችሁ አባት አላገኛችሁ እንደሆነ ለሚጠጓችሁ እናንተ ደግሞ አዛኝ አባቶች ሁኑ፡፡ ተራራውን ስትጨርሱ መስክ እንደሚያጋጥማችሁ እያሰባችሁ በተራራው አትዘኑ፡፡ እናንተ ዱር መንጣሪዎች ናችሁና የተመቸ ቦታን ፍጠሩ እንጂ ምቹ ቦታን አትጠብቁ፡፡ የደረሰባችሁ ችግርም እስከ ዕድሜአችሁ ፍጻሜ የምትናገሩትን ትምህርት ይሰጣችኋልና አትበሳጩ፡፡ ከምትፈልጉት ነገር ይልቅ ያገኛችሁት ይበልጣል፤ እርሱም የሰማይ ዜጐች መሆናችሁ ነውና ደስ ይበላችሁ!

የተወደዳችሁ ልጆቼ! እግዚአብሔር የሚባርከው አሳባችሁን ሳይሆን ቃል ኪዳናችሁን ነውና አገልግሎታችሁን በቃል ኪዳን ያዙ፡፡ መጽናናትን የሚሹ ብዙዎች ኀዘንተኞች፣ በማዕበል የሚንገላቱ ብዙዎች ደካሞች እየጠበቋችሁ ነውና ፍጠኑ፡፡ እናንተን ኑ ለማለት አቅም የሌላቸው ብዙ አሉና ሳይጠሯችሁ ሂዱ፤ ወንጌል ሀገሯ እስከ ምድር ዳርቻ ነውና፡፡ ዘመናዊነትና ሥልጣኔ የማይሞላው የሕይወትን ክፍተት በወንጌል የምትሞሉ እናንተ ናችሁ፡፡ የያዛችሁት እንደ ቀላል አትቁጠሩት፡፡ የዓለምን ኃይልና ዕውቀት ሁሉ የምትማርኩ የዕውነት ዘማቾች ናችሁ፡፡ እንደማይፈለግ ሰው ራሳችሁን አትቁጠሩት፡፡ የሞተላችሁ ጌታ ውበቱ የማያረጅ፣ ዛሬም ያደመቃችሁ እርሱ ነው፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቼ! ዋጋችሁ በሰማያት እንደሆነ እያሰባችሁ በትንንሽ የምድር ዋጋ ክብራችሁን እንዳትጥሉ ተጠንቀቁ፡፡ እኔም በጸሎትና በአባታዊ ፍቅር ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በሰማያዊና በምድራዊ በረከቱ ይባርካችሁ! ዛሬ እንደ ያዕቆብ በሌጣ ወጥታችሁ፣ ለከርሞ ግን በብዙ ፍሬ ይመልሳችሁ! እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ! የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም ልጅ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ!”
      

FeedBurner FeedCount