Wednesday, September 4, 2013

“ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ” - የዮሐንስ ወንጌል የ48ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.13፡1-19)

ገ/እግዚአብሔር ኪደ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ነሐሴ 29 ቀን፥ 2005 ዓ.ም.)፡- የነገረ መለኮት ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ከዚህ ከ13ኛው እስከ 17ኛው ምዕራፍ ያሉት የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፎች ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ያደረጋቸውን የፍቅር ድርጊቶችንና ትምህርቶቹን አጠቃልለው ስለያዙ “የፍቅር ወንጌል” ብለው ይጠሩዋቸዋል፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች ብቻ ወንጌላዊው “ፍቅር” እያለ 20 ጊዜ ጽፏል፡፡ የፍቅር ግብር ምሥጢረ ትሕትና የበለጠ የተገለጠው በዚህ ዕለት ነው፡፡ የፍቅር ማዕድ ምሥጢረ ቁርባን የተመሠረተው በዚህ ዕለት ነው፡፡ የምሥጢረ ጸሎት ትምህርትም በስፋት በጌቴ ሴማኒ የአታክልት ስፍራ የተማርነው በዚህ ዕለት ነው፡፡  እኛም ለዛሬ ከወንጌላዊው ጋር በሕፅበተ እግር ስለተገለጠው ስለ ምሥጢረ ትሕትና እንማማራለን፡፡ ምሥጢሩን ይግለጥልን!

Thursday, August 22, 2013

ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች - በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ለተሐድሶዎች የተሰጠ ምላሽ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- እንኳን ለእመቤታችን በዓለ ዕርገት አደረሳችሁ፡፡

ዘሰ ይብል አፈቅረከኪ ወኢያፈቅር ተአምርኪ [ትንሣኤኪ ወዕርገትኪ] ክርስቲያናዊ፤
ኢክርስቱን ውእቱ አይሁዳዊ ወሠርፀ እስጢፋ ሐሳዊ፤
አንሰ እቤ በማኅሌተ ሰሎሞን ሰንቃዊ፤
አፈቅሮ ለፍግዕኪ ወለተ ይሁዳ ወሌዊ፤
ከመ መርዓቶ ያፈቅር ጽጌኪ መርዓዊ፡፡

Tuesday, August 20, 2013

ሥጋ ሥጋት ሲኾን

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ከኢትዮጵያ ውጭ ለመኖር በኹኔታዎች ተገድዶ ወደ ጀርመን የሔደ አንድ ወንድማችን በሚኖርበት ሀገር እጅግ በሽተኛ ኾኖ ይቸገራል፡፡ ጾም አይጾም፤ ምግብ አይመርጥ የነበረው ሰው የፈለገውን ቢያደርግም ለጤናው ሽሎት ያጣል፡፡ በሚኖርበት ሀገር በሕክምና ዕውቀት በጣም ያደገ ስለነበር እጅግ ብዙ ሙከራዎችን ቢያደርግም ተስፋ ያጣል፡፡ በመጨረሻ በአመጋገብ ብቻ ሕክምና ወደምታደርግ ስፔሻሊስት ሐኪም ይላካል፡፡ ሐኪሟም የበሽተኛውን የሕማም ታሪክ ጊዜ ወስዳ በተደጋጋሚ ካጠናች በኋላ ሕክምናውን ለመጀመር ኹለት ዝርዝሮች አዘጋጅታ ጠበቀችው፡፡ ከዝርዝሮቹ አንደኛው ሊመገባቸው የሚገባውን የምግብ ዐይነቶች የያዘ ሲኾን ኹለተኛው ደግሞ ሊመገባቸው የማይገባውን የያዘ ነበር፡፡ ዝርዝሩን ይዞ ወደ ቤቱ በመሔድ በትእዛዙ መሠረት መዳኑን እየተጠባበቀ መመገብ ጀመረ፡፡ ለውጡን በመጠኑ እያየ ደስ እያለው ሳለ እንዲበላቸው የታዘዛቸው ምግቦች ቀደም ብሎ በብዛት ከሚመገባቸው የተለዩ ስለነበሩና ቀድሞ በብዛት ይመገባቸው የነበሩት ደግሞ ከተከለከላቸው ውስጥ ስለነበሩ ኹኔታዉን ደጋግሞ ሲመለከት አንድ ነገር ይከሰትለታል፡፡ የተከለከላቸው ምግቦች በሙሉ ሲያያቸው በሀገር ቤት በፍስክ የሚበሉት ሲኾኑ እንዲመገባቸው የታዘዙለት ደግሞ በሙሉ የጾም ምግብ ከሚባሉት ኾነው ያገኛቸዋል፡፡ በኹኔታው በጣም ከተገረመ በኋላ “የጾም ምግብ ለጤና ተስማሚ ከኾነ ለምን አልጾምም?” ይልና ፈጽሞ ረስቶት የነበረውን ጾም ድንገት በሰኔው የሐዋርያት ጾም ይጀምራል፡፡ ልክ አንድ ሳምንት ከጾመ በኋላ ኹል ጊዜም እንደሚያደርገው ለክትትል ወደ ሐኪሙ ያመራል፡፡ የላባራቶሪ ውጤቶቹ ሲመጡ በተለይ እነ ደም ግፊት፣ ስኳርና የመሳሰሉት በሽታዎች በከፍተኛ ኹኔታ ቀንሰዋል፡፡

Saturday, August 17, 2013

የእሑድ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡-  በዚህ ዕለት እመቤታችን ከወትሮው ይልቅ ቀደም ብላ መጥታለች፡፡ “ዛቲ ዕለት ተዓቢ እምኩሎን ዕለታት፤ ወውዳሲያቲሃኒ የዓብያ እምኵሉ ውዳሴያት - ከዕለታት ኹሉ ይህቺ ዕለት ታላቅ ናት፤ ከውዳሲያቱም ኹሉ የዚች ዕለት ውዳሴ ታላቅ ነው” አለችውና ባረከችው፡፡ እርሱም በቤተ መቅደስ ባሉ ንዋያት ማለትም፡- በመሶበ ወርቅ፣ በተቅዋመ ወርቅ፣ በማዕጠንተ ወርቅ፣ በበትረ አሮን እየመሰለ ሲያመሰግናት አድሯል፡፡

FeedBurner FeedCount