Monday, March 16, 2015

ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ (ደረጃ አራት)





በዲ/ን ሳምሶን ወርቁ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
መታዘዝ
የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፥ የመንግሥተ እግዚአብሔር ተጓዦች እንዴት ሰነበታችሁ? አራተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ እነሆ በምናባችን ዛሬ መመልከታንን እንቀጥላለን፡፡ አስቀድመን የመጀመሪያውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ጀርባችን ለዓለም በመስጠት ጀምረን፣ ሁለተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ ከዓለማዊ መሻት መለየትን አስከትለን፣ በሦስተኛው የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ የሆነውን እንደ እንግዳ መኖርን በባለፉት ጊዜያት ተመልክተናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ዘላዕለይ አራተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ መታዘዝ ሲል ይገልጸዋል፡፡ ይህንንም ሲገልጽ መታዘዝ ማለት የእኔ የምንለውን ሐሳብ፣ ፈቃድ በመተው በምትኩ እኛ ራሳችንን አስገዝተንለታል ለምንለው ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመታዘዝ መኖር ማለት ነው፡፡

Thursday, March 12, 2015

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 03 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
     በየዓመቱ መጋቢት 5 የምናከብረው በዓል አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያረፉበት በዓል ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋም በትምህርቷም ኹሉ እኒኽን ታላቅና ቅዱስ አባት ታነሣለች፤ ታወድሳለች፤ ተጋድሎአቸውንም ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡
ሀገራቸው ንሒሳ (ግብጽ) ሲኾን አባታቸው ስምዖን እናታቸውም አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው 30 ዓመታት ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ እኛ አንድ ነገርን ለምነን በእኛ አቈጣጠር ካልተመለሰልን ስንት ቀን እንታገሥ ይኾን? ዛሬ በልጅ ምክንያት የፈረሱ ትዳሮች ስንት ናቸው? ለመኾኑ እግዚአብሔርን ስንለምነው እንደምን ባለ ልቡና ነው? ጥያቄአችን ፈጥኖ ላይመለስ ይችላል፡፡ ያልተመለሰው ለምንድነው ብለን ግን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “የምንለምነውን የማናገኘው በእምነት ስለማንለምን ነው፤ በእምነት ብንለምንም ፈጥነን ተስፋ ስለምንቆርጥ ነው” ይላል፡፡ ሰውን ብንለምነው እንደዘበዘብነው፣ እንደ ጨቀጨቅነው አድርጎ ሊቈጥረው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን እንዲኽ አይደለም፡፡ “ለምኑ ታገኙማላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” ያለን ርሱ እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ የሚያስፈልገን ከኾነ ያለ ጥርጥር ይሰጠናል፡፡ መቼ? ዛሬ ሊኾን ይችላል፤ ነገ ሊኾን ይችላል፤ ወይም እንደ ስምዖንና እንደ አቅሌስያ የዛሬ 30 ዓመት ሊኾን ይችላል፡፡  ጭራሽኑ ላይሰጠንም ይችላል፡፡ አልሰጠንም ማለት ግን ጸሎታችን ምላሽ አላገኘም ማለት አይደለም፡፡ የለመንነው እኛን የሚጎዳን ስለኾነ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሲሰጥ ስለ ፍቅሩ፤ ሲነሳም ስለ ፍቅሩ ነውና፡፡

Tuesday, March 10, 2015

ኹለት መንፈሳውያን መጻሕፍት ተመረቁ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ረቡዕ 02 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- “ሰማዕትነት አያምልጣችሁ” እና “ነጽሮተ ሀገር” በሚል ርእስ የተዘጋጁ ኹለት መንፈሳውያን መጻሕፍት የካቲት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው አበው ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባክያነ ወንጌል እና የመቅረዝ ዘተዋሕዶ ድረ ገጽ አንባብያን በአጠቃላይ ከ400 በላይ ታዳምያን በተገኙበት ደማቅ መርሐ ግብር ተመረቁ፡፡ “ሰማዕትነት አያምልጣችሁ” የሚል ርእስ የተሰጠው አንደኛው መጽሐፍ በመቅረዝ ዘተዋሕዶ ድረ ገጽ ዋና አዘጋጅ በገ/እግዚአብሔር ኪደ የተተረጐመ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥራ ሲኾን ኹለተኛው መጽሐፍ ደግሞ በመምህር ዘሪኹን መንግሥቱ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ በጸሎት የተከፈተ ሲኾን ዘማሪት ጽጌ ወቅቱን የተመለከተ ያሬዳዊ መዝሙር አቀረበች፡፡

Wednesday, March 4, 2015

በመጽሐፍ ምረቃ ቀን እንዲገኙ ተጋብዘዋል



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ረቡዕ የካቲት 28 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
     ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ ውድ የመቅረዝ አንባብያን፡፡ እንደምን ሰነበታችሁ? እግዚአብሔር ቢወድና ቢፈቅድ ቀጣይ ቅዳሜ ማለትም የካቲት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በገ/ጽ/ቅ/ጊ/ቤተ ክርስቲያን (ፒያሳ) ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ዠምሮ ኹለት መጻሕፍት አንድ ላይ ይመረቃሉ፡፡ አንደኛው መጽሐፍ በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ ሲኾን ኹለተኛው መጽሐፍ ደግሞ የዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት የትምህርት ክፍል ሰብሳቢ በኾኑት በመምህር ዘሪኹን መንግሥቱ የተዘጋጀ ነው፡፡

FeedBurner FeedCount