በሥርጉተ
ሥላሴ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 22 ቀን፣
2008 ዓ.ም.)፡- በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ልጅነት
ቅዱስ ፖሊካርፐስ የተወለደው ከክርስቲያን ቤተሰቦች በ70 ዓ.ም. በጥንታዊቷ ሰምርኔስ ከተማ (ቱርክ ውስጥ የአሁኗ እዝሚር) ነው፡፡ ቤተሰቦቹን በልጅነቱ ስላጣ ካሊቶስ/ካሊስታ
የተባለች ደግ ክርስቲያን አሳድጋዋለች፡፡ ከእርሷም በኋላ የሰምርኔስ ከተማ ጳጳስ ቡኩሎስ ወስዶ ትምህርተ ሃይማኖትን በሚገባ እያስተማረ አሳድጎታል:: ይህ
ቅዱስ ቡኩሎስ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ስለነበር ቅዱስ ፖሊካርፐስ ዮሐንስ ወንጌላዊን እና ሌሎችንም ሐዋርያት የማግኘት
ዕድል ነበረው:: ቅዱስ ቡኩሎስ ቅንዓቱንና ትጋቱን አይቶ ዲቁና ሾመው፤ ቀጥሎም ቅስናን ሾመውና የቅርብ ረዳቱ አደረገው:: ቅዱስ
ዮሐንስ ወንጌላዊ ሐዋርያዊ ጉዞ በሚያደርግበት ወቅት አስከትሎት ይሄድ ነበር፤ ከሌሎች ሐዋርያት ረዘም ላለ ጊዜ በምድር ላይ ስለነበር
ለብዙ ዓመታት የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ቅዱስ ቡኩሎስ ካረፈ በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ የሰምርኔስ ከተማ ጳጳስ አድርጎ ሹሞታል::
ቅዱስ ፖሊካርፐስ ወንጌልን ከሐዋርያት በተለይም ከዮሐንስ በቀጥታ እየሰማ ያደገ፣ የሐዋርያትን
ትውፊት በሚገባ የወረሰ፣ በሥራዎቹ በሙሉ እነርሱን መስሎ እነርሱን አክሎ የተነሣ አባት ነው፤ ቁጥሩም ከሐዋርያውያነ አበው መካከል
ነው:: የሰምርኔስን ቤተ ክርስቲያን በሚገባ የጠበቀእና በካህናትና ምእመናን ዘንድም እጅግ ተወዳጅ የነበረ አባት ነው:: ብዙ ደቀ
መዛሙርትን ያፈራ ሲሆን ከእነዚህም ታላላቆቹ ቅዱስ ሄሬኔዎስ እና ቅዱስ ፓፒያስ ይገኙበታል:: የአንጾኪያው ጳጳስ ቅዱስ አግናጥዮስ
ቅዱስ ፖሊካርፐስን እጅግ ይወደውና ያከብረው ነበር:: ሁለቱ ቅዱሳን ሰፊ የሆነ የዕድሜ ልዩነት የነበራቸው ቢሆንም በሐዋርያት መካከል
አዋቂውም ሕፃኑም ቃላቸውን ለመስማት ይሰበሰብ ስለነበር በዚያ ተዋወቁ:: ስለዚህም ሁለቱም የዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዛሙርት ናቸው::
ቅዱስ አግናጥዮስ ለሰማዕትነት ወደ ሮም ሲጓዝ ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተው እንዲህ ብሎታል:- “የአንጾኪያን ቤተ ክርስቲያን አደራ፤
እኔ መልእክት ላልጻፍሁላቸው አብያተ ክርስቲያናት አንተ ጻፍላቸው::” በዚህም ምክንያት ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፎ ለሌሎች
አብያተ ክርስቲያናት የተጻፉ የአግናጥዮስ መልእክታትንም ጨምሮ ልኮላቸዋል:: በመጨረሻም ቅዱስ አግናጥዮስ ለግሉ በስሙ ደብዳቤ ጽፎለታል፤
ይህም ለግለሰብ የጻፈው ብቸኛው መልእክት ነው::
የእምነት ጠበቃ
ቅዱስ ፖሊካርፐስ ጠንካራ የኦርቶዶክስ እምነት ጠበቃ ነበር:: ዘመኑ መናፍቃን ከቀናችው የሐዋርያት
ትምህርት የወጣ ልዩ ልዩ ትምህርቶችን ያፈሉበትና ምእመናንን የሚያደናግሩበት ወቅት ስለነበር እነርሱን በመርታት ትክክለኛውን የሐዋርያት
ወንጌል ያስተምር ነበር:: በምንፍቅና ትምህርት የተወሰዱ ብዙዎችንም ወደ ቀናችው ትምህርት መልሷል:: ደቀ መዛሙርቱንም “ልጆቼ
እባካችሁ ከስህተት ራቁ” እያለ በተደጋጋሚ ይመክራቸው ነበር:: በአስተምህሮውም ሁሉ መምህሩን ወንጌላዊ ዮሐንስን ይመስል ነበር::
ለምሳሌ ወደ ፊልጵስዩስ ከጻፈው መልእክቱ ብንመለከት:- “ማንም ኢየሱስ
በሥጋ እንደመጣ የማያምን ፀረ-ክርስቶስ ነው:: በመስቀል ላይ መከራ መቀበሉን የማያምንም ዲያብሎስ ነው:: ማንም የክርስቶስን ትምህርት
ለራሱ እንደሚመቸው የሚያጣምም፤ ትንሣኤና የመጨረሻ ፍርድ የለም የሚል ይህም የሰይጣን የበኩር ልጅ ነው. . .” ይህም ነገረ ሥጋዌን የካዱትን በሚመለከት የጻፈው ሲሆን ከሐዋርያው ቃል ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል:-
“የእግዚአብሔርን
መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን
መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ
ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥” (1ዮሐ.
4፥2-3):: በእስያ
ብቻ ሳይሆን ሮም ድረስ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በዚያ በነበሩ መናፍቃን የተወሰዱትን ምእመናን አስተምሮ መልሷል::
ቅዱስ ፖሊካርፐስ ከሐዋርያት
ትምህርት የወጣ አስተምህሮ ሲሰማ ያለቅስ ነበር፤ እጅግም ስለሚዘገንነው ሥፍራውን ለቆ ይወጣ ነበር:: ይህንንም ከሐዋርያው ዮሐንስ እንደተማረው
ያደርግ ነበር፤ በነገር ሁሉ እርሱን ይመስለው ነበርና:: ቅዱስ ሄሬኔዎስ ቅዱስ ፖሊካርፐስ እንዲህ ሲል ተሰማ በማለት ጽፏል:
“ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በኤፌሶን ወደ አንድ መታጠቢያ ክፍል ሲገባ መናፍቁ ቀሪንጦስን አየውና ‘ከዚህ እንሽሽ የእውነት ጠላቷ
ቀሪንጦስ በዚህ አለና’ እያለ ወዲያውኑ ክፍሉን ለቆ ወጣ::” እርሱም ቀንደኛ የሆኑ መናፍቃንን መንገድ ላይ በሚያገኝበት ጊዜ እንዲሁ ያደርግ ነበር:: ወደ
ሮም በተጓዘበት ወቅት መርቅያን የተባለውን መናፈቅ አየውና ትኩር ብሎ በመመልከት ሲቃወመው መርቅያን “ታውቀኛለህን” አለው:: ፖሊካርፐስም
“አዎን አውቅሃለሁ፤ አንተ የዲያብሎስ
የበኩር ልጁ ነህ” ብሎ መልሶለታል:: ቅዱስ ሄሬኔዎስም ለመናፍቃን ምላሽ በጻፈው መጽሐፉ ውስጥ ፍሎሪነስ ለተባለው መናፍቅ መልስ
በሰጠበት ክፍል ስለፖሊካርፐስ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “. . .
ነግር ግን ይህ ቅዱስ [ፖሊካርፐስን ነው] እንዳንተ ትምህርት ያለ የተሳሳተ ትምህርት ሲሰማ እንደልማዱ ፈጥኖ ጆሮውን በመያዝ እንዲህ
በማለት ይጮሃል ‘አቤቱ ቸር ፈጣሪዬ ሆይ እስከዚህ ዘመን ድረስ ያቆየኸኝ ይህን ነገር ልታሰማኝ ነውን?’ . . .ወዲያውም ይህን
ዓይነት የክህደት ትምህርት የሰማበትን ሥፍራ ለቆ እያለቀሰ በፍጥነት ይወጣል::”
ሰማዕትነት
የቅዱስ ፖሊካርፐስ የሰማዕትነቱ ዜና የተገኘው የራሱ የሆነችው የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነቱን
በአካል በተከታተሉ ወንድሞች አማካኝነት ጽፋ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከበተነችው መልእክት ነው:: በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት
የሰማዕትነታቸው ሁኔታ፣ ሳይፈሩ ሰውነታቸውን ለሰይፍ ለስለት እንዴት እንደሰጡ፣ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር እንዴት ይጨክኑ እንደነበር በሙሉ ዜና ገድላቸው እየተጻፈ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይሰራጭ ነበር:: እንደ አግናጥዮስ
ሁሉ (በሮም) ፖሊካርፐስ ሰማዕት በሆነበት ጊዜም በሰምርኔስ ከተማ የሕዝብ በዓል ተደርጎ ነበር:: እንደልማዳቸው በዓሉ በሚከበርበት በእስታድየማቸው
የአራዊት ትርኢት ነበር:: አሬኒከስ የተባለ አንድ ክርስቲያንም የአሕዛብ ጣዖታትን ካላመለክህ ለአራዊት እንሰጥሃለን ብለውት አሻፈረኝ
ብሎ በመፅናቱ በዚያ በአራዊት ተበልቶ ሰማዕት ሆነ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲፀኑ የሚያስተምራቸው ዋነኛው
ፖሊካርፐስ ነው እርሱ ተይዞ ይምጣ እያሉ ጮሁ::
ቅዱስ ፖሊካርፐስ የሞት ፍርድ ሲፈረድበት ፀንቶ በከተማዋ ቢቆይም ምእመናን እንዲሸሽ እያለቀሱ
ስለለመኑት ባጠገብ ወዳለች መንደር ሸሸ::በዚያ ሳለ ሰማዕት እንደሚሆን በራእይ ተረድቶ እንደሚሞት ለወንድሞችና እህቶች ነገራቸው::
ወዲያው በጥቆማ ተይዞ ወደ ሰምርኔስ ከተማ እያንገላቱ ወስደው ሕዝብ በተሰበሰበበት በበዓሉ አደባባይ አቆሙት:: እርሱም ክርስቶስ
በሕዝብ አደባባይ ቆሞ የተቀበለውን መከራ እያሰበ የመከራው ተካፋይ ስላደረገው በፍጹም ደስታ መከራውን ይቀበል ነበር:: በሕዝቡ
ፊት አቁሞ የሚያናዝዘው ሹም ክርስቶስን እንዲክድ ብዙ ማግባቢያዎችንና ማስፈራሪያዎችን ቢያቀርብለትም ያለፍርሃት ፀንቶ ክርስቲያንነቱን
ስለመሰከረ በእሳት እንዲቃጠል ተፈረደበት:: ወታደሮቹ እሳቱ ውስጥ ከገባ በኋላ የሚያመልጠን መስሏቸው ለማጠር ሲዘጋጁ አይቶ “ወደ
እሳቱ እንድገባ ያበረታኝ ጌታዬ በእሳቱ ውስጥም ፀንቼ እንድቆይ ያስችለኛል” አላቸው:: ወታደሮቹ እጅና እግሩን አስረው ወደ እሳቱ
ሲያቀርቡት አይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ በማለት የመጨረሻ ጸሎት አደረገ:- “አቤቱ ልዑል
እግዚአብሔር የተወደደው ልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ በልጅህ አንተን እንድናውቅ ሆነናል:: የመላእክትና የኀይላት እንዲሁም
የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ አንተ ነህ፤ ፍጥረታትም ሁሉ የሚኖሩት ባንተ ነው:: በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ለዘላለማዊ ሕይወት ትንሣኤ
ያለፍርሃት ከክርስቶስ መከራ ተካፋይ ከሆኑት ከሰማዕታት ወገን እንድቆጠር ስላደረግኸኝ እና በዚህች ቀንና ሰዓት በሚገባ ስላስተማርኸኝ
አመሰግንሃለሁ:: እንደ እነርሱ ዛሬ በፊትህ ተቀብያለሁና እንደ መልካምና የተወደደ መሥዋዕት አድርገህ ተቀበልልኝ:: አንተ አስቀድመህ
እንዳሳየኸኝ እና እንዳዘጋጀኸኝ : አንተ እውነተኛና ታማኝ አምላክ ነህና ስለሁሉ ነገር አመሰግንሃለሁ፣ አከብርሃለሁ፣ ከፍ ከፍ
አደርግሃለሁ:: ከሰማያዊው ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ከተወደደው ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ: ከእርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብርና
ምስጋና ለአንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን!”
የጸሎቱ ይዘት ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታስተምረው ምሥጢረ ሥላሴ ጋር አንድ አይነት ሲሆን
ይህንኑም የመሰለ ጸሎት አላት:: በዚህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጥንታዊና ከምንጮቹ ከሐዋርያት የተረከበችው ለመሆኑ
ታላቅ ማስረጃ ነው:: ቅዱሱ ጸሎቱን ሲጨርስ በእሳቱ ውስጥ ወረወሩት::
በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ተአምር የሚሠራ እግዚአብሔር ለምእመናን መጽናኛ የሚሆን ድንቅ ተአምርን አደረገ:: እሳቱ የቅዱሱን ሰውነት
ዙሪያውን እንደግድግዳ ከቦ የማያቃጥለው ሆነ;: ሕዝቡም እሳቱ እንዳላቃጠለው ባዩ ጊዜ በጦር ተወግቶ ይሙት እያሉ ጮሁ፤ ወታደሮቹም
በጦር ወጉትና በዚህ ሰማዕትነቱን ፈጸመ:: ክርስቲያኖች እንዳያመልኩት በሚል የከበረ ሥጋውን አቃጠሉ፤ በዚህ ጊዜ ደስ የሚያሰኝ
የእጣንና የሽቶ መአዛ ሸተተ:: ክርስቲያኖችም ተረፈ አፅሙን በክብር ወሰደው ቀበሩት: ቤተ ክርስቲያንም በስሙ ሠሩለት:: ለእግዚአብሔር
ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ቅዱስ ጸሎት ይማረን አሜን!
ዋቢ መጻሕፍት:
1.
ወ/ሮ ዘውዴ ገ/እግዚአብሔር፣ ቅዱስ
ፖሊካርፐስ ሐዋርያዊ ጳጳስ ወሰማዕት፣ 2001 ዓ,ም.
2.
ANF01.The Apostolic Fathers with Justin Martyrand
Irenaeus, Schaff, Philip (1819-1893) (Editor), Grand Rapids, MI: Christian Classics
Ethereal Library.
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሠማልን
Deleteቃለ ሂወት ያሰማልን
ReplyDeleteቃለ ህይወትን ያሰማልን የሰማዕቱ አባታችን በረከቱ ይደርብን
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን በእድሜ በፀጋ ይጠብቅልን
ReplyDelete