Sunday, February 21, 2016

ትንቢተ ዮናስ - ክፍል አንድ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 13 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
መግቢያ፡
ትንቢተ ዮናስ 46 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ የመጽሐፉ ጸሐፊም ነቢዩ ዮናስ ይባላል፡፡ ዮናስ ማለት ርግብ፣ የዋኅ ማለት ሲኾን የነበረበትም ዘመን በዳግማዊ ኢዮርብአም ዘመነ መንግሥት /825-784 .../ ነው፡፡ በትውፊት እንደሚነገረው ዮናስ ነቢዩ ኤልያስ ከሞት ያስነሣው የሠራፕታዋ መበለት ልጅ ነው /1ነገ.1810-24/፡፡ ነቢዩ ዮናስ ምንም እንኳን የእስራኤል ነቢይ ቢኾንም ያስተማረው ከምድረ እስራኤል ውጪ ማለትም በነነዌ ስለኾነ፣ ነቢየ አሕዛብ ይባላል፡፡ ሊቃውንት እንደሚናገሩት ይህቺ ነነዌ በጤግሮስ ወንዝ ምሥራቃዊ ቆሬ፣ ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ 350 .. ርቀት ላይ ነበረች፡፡ የትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ ዋና መልእክት እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይሆን የአሕዛብም አምላክ እንደሆነና በንስሐ ወደ እርሱ የተመለሱትን ሁሉ በምሕረት እንደሚጐበኝ ማሳየት ነው፡፡ በመሆኑም በአራት ተከታታይ ክፍል የእያንዳንዱን ምዕራፍ ትርጓሜ በተለይ ደግሞ ከሕይወታችን ጋር እያገናዘብን እንመለከተዋለን፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን ይህን የነነዌን ጾም ከዓቢይ ጾም ኹለት ሳምንት አስቀድመን እንድንጾመው ማድረጋቸው ያለ ምክንያት አይደለምና፡፡ በዚህ መጽሐፍ በሁዳዴ ጾም ልናከናውነውና ሊኖረን የሚገባ የንስሐና የጾም ዓይነት ምን ሊመስል እንደሚባ፣ የእግዚአብሔር ፍቅርና ጥበብ እንደምን የበዛ እንደኾነ፣ ነቢያት እንኳ ድካም እንደነበረባቸውና እንደምን እንደተነሡ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን፡፡


 ምዕራፍ አንድ 

 በትንቢተ ዮናስ እግዚአብሔር ሊያስገነዝበን ያሰበው ነገር አለ፡፡ ይኸውም ነቢያት እንኳ እንደ እኛ ድካም እንደነበረባቸው፤ ኾኖም ግን በእግዚአብሔር አጋዥነት ኹሉንም ድል እንደነሡ /2.47/፡፡ ምንም እንኳን ዮናስ ድካም ቢኖርበትም እግዚአብሔር ጥበበኞች ነን የሚሉትን ያሳፍር ዘንድ ተጠቅመቦታል፡፡ ከዚህም እግዚአብሔር የእኛን ደካማነት እንደምን ሊጠቀምበት እንደሚችል እንረዳለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፡- ተነሥተህ ወደዚያች ሀገር ወደ ነነዌ ሄድና አስተምር፡፡ ድሀ መበደላቸው አንድም ከቤተ ጣዖት ገብተው በዓል ሆይ ስማን በዓል ሆይ ስማን እያሉ መጮኻቸው በዝቷልና፡፡ አዎ! እስራኤላውያን ቃለ እግዚአብሔርን ከመስማት ጀሮአቸው ተደፍኗልና እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አሕዛብ አዞረ፤ ዮናስንም ሊልክላቸው ወደደ፡፡ ዮናስ ግን አልታዘዝም አለ፤ ይኰበልልም ጀመረ፡፡ 347-420 . የነበረው ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ጀሮም ነቢዩ ዮናስ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲናገር፡- “ዮናስ ወደ አሕዛብ ሀገር አልሄድም አለ፤ ኾኖም ግን ጠልቷቸው አልነበረም፡፡ የእርሱ ወደ አሕዛብ መላክ የወገኖቹ የእስራኤል መጥፋት የሚያመለክት መኾኑን በትንቢት መነጽር ስላየ እንጂ፡፡ በዚህም አባቱ ሙሴን መሰለ፡፡ ምክንያቱም እስራኤላውያን በበደሉና እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው በወደደ ጊዜ ሙሴ፡- ይህን ኃጢአታቸው ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ ብሏልና /ዘጸ.3232/፡፡ ሙሴ እንዲህ በመጸለዩ እስራኤል ከሞት ዳኑ፤ ሙሴም ከመጽሐፈ ሕይወት ሳይደመሰስ ቀረ፡፡ ዳግመኛም ዮናስ ሐዋርያው ጳውሎስን መሰለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ወገኖቹ ስለ እስራኤል ከክርስቶስ ተለይቶ የተረገመ እንዲኾን ይጸልይ ነበርና / ሮሜ.93/” እያለ በጥልቀት ያብራሯል፡፡ ኾኖም ግን ዮናስ እንዲህ ባለመታዘዙ ምክንያት ወደ ሌላ የከፋ ኃጢአት ይገባ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሙሉዕ በኵለሄ መኾኑን እንዲዘነጋ አደረገው፡፡ እንደ አዳምና እንደ ቃኤል ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሎ በባሕር ለመሸሸግ ሞከረ፡፡ እግዚአብሔር ግን በዚያም ነበረ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው ወደ ሰማይ ብንወጣ እግዚአብሔር በዚያ አለ፤ ወደ ጥልቅ ባሕር ብንወርድ እርሱ በዚያ አለ፤ እንደ ንስር ክንፍ ብናበቅልና እስከ አድማስ ብንደርስ አሁንም እግዚአብሔር በዚያ አለ፡፡ ስለኾነም ዮናስ ባሕርን ከፈጠረ ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሎ ወደ ባሕር ገባ /መዝ.139 7-10/፡፡ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርን ሳንታዘዝ ስንቀር እንዲህ ዓይነ ልቡናችን ይታወራል፡፡ እውነቱን ማየት አቅቶን ወዴት መሄድ እንዳለብን እንኳን ሳናውቅ እንዲሁ እንቅበዘበዛለን፡፡ ዮናስ ባሕርን ከፈጠረ ጌታ ሸሽቶ ወደ ባሕር ሲሄድ መርከብ አገኘ፡፡ ከመርከበኞች ጋር ወደ ደሴቱ ይሄድ ዘንድም በገንዘብ ተስማምቶ ወደ መርከቡ ወጥቶ ተቀመጠ፡፡ ሰዎች ስንባል በጣም እንገርማለን፡፡ ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ ገንዘባችንን ብቻ ሳይኾን ሌላም ሌላም እንከፍላለን፡፡ ወደ ባሕርም (ወደ ዓለም) ራሳችንን እንጥላለን፡፡ ዮናስ ገንዘብ ባይኖረው ኖሮ (ምናልባት?) እንዲህ ባላደረገ ነበር፡፡ ገንዘብ ከፍሎ ሲሄድ ግን አንደኛ ገንዘቡን አጣ፤ ኹለተኛ መታዘዙን አጣ፡፡ እግዚአብሔርስ ምን አደረገ? እግዚአብሔር የዮናስን አለመታዘዝ ለመልካም ይጠቀምበት ነበር፡፡ ዮናስ አልታዘዝ ብሎ ወደ ባሕር ሸሸ፡፡ ከበላተኛ ውስጥ መብል፣ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥን ማውጣት የሚቻለው እግዚአብሔር ግን /መሳ.1414/ የዮናስ አለመታዘዝ ሌሎች ሰዎችን ለማዳን ተጠቀመበት፡፡ ከእርሱ አለመታዘዝ መርከበኞቹ ዳኑ፡፡ በመርከቢቱ ውስጥ እንደ ነነዌ ሰዎች መዳን ይገባቸው የነበሩ አሕዛብ ዳኑ፡፡ እግዚአብሔር ዮናስን እንዲህ ይለው ነበር፡- “ዮናስ ሆይ! የደንዳኖቹ የወገኖችህ ጥፋት አሳዝኖህ ከእኔ ፊት የሸሸህ ይመስለሃልን? በፍጹም! እንደውም ልክ እንደ ነነዌ ሰዎች ድኅነት ወደሚገባቸው ወደ መርከበኞች እልክሃለሁ፡፡ ኾኖም ግን እንደ ነቢይ አይደለም፤ እንደ ሰባኪም አይደለም፤ ራሱን እንደሚወቅስ እንደ ኃጢአተኛ ሰው እንጂ፡፡ በዚያም እነዚያን መርከበኞች አድናቸዋለሁ፡፡ አለመታዘዝህ ለበረከት አደርገዋለሁ፡፡ ወደ ባሕር ውስጥ ሲጥሉህ እንኳን ባሕሩም የእጄ ፍጥረት ስለኾነ አንተን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ አዘጋጅቼ ለእኔ ሞትና ትንሣኤ ምሳሌ አደርግሃለሁ፡፡በእውነት እግዚአብሔር ሥራው ግሩም ነው! የጲላጦስ ደካማነት የይሁዳም አሳልፎ ሰጪነት ዓለምን ለማዳን ተጠቅሞበታል፡፡ የልቡ ሐሳብ ምን እንደኾነ የሚያውቅ እግዚአብሔር የዮናስ አለመታዘዝም መርከበኞቹን ለማዳን ተጠቀመበት፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ከዚህ ዕፁብ ድንቅ ከኾነው የእግዚአብሔር ጥበብ ደካሞች የምንኾን እኛም የምንጠቀም እንኹን፡፡ ከመራራው ጣፋጭን ማውጣት እንማር፤ ከበሽታ መልካም ነገርን ማውጣት እንማር እንጂ አንማረር፡፡ እግዚአብሔር ግዑዛን በኾኑ ነገሮች ዮናስን ይገስጸው ጀመር፡፡ ዮናስ ወደ መርከቢቱ ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር ጽኑ ነፋስን አመጣ፡፡ ነፋሱም አምላኩን ታዝዞ ሥራውን ይሠራ ነበር፡፡ ከአምላክ የተላከ መልእክተኛ ነውና ሰዎቹን ለጸሎት ቀሰቀሳቸው፡፡ አስቀድሞ ሞገዱን ከፍ ከፍ አደረገው፡፡ እስኪሰበር ድረስም መርከቡን ስርግርግ አደረገው፡፡ መርከበኞቹም እንሰጥማለን ብለው ፈሩ፡፡ ኹሉም ወደየአምላካቸው ጮኹ፡፡ ፍጥረት ኹሉ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ስለኾነ ፈቃደ እግዚአብሔርን ይፈጽም ነበር፡፡ ነፋሱን ሲልከው መጣ፤ ዓሣውን ዋጠው ሲለው ዋጠው፤ ትፋው ሲለውም ተፋው፡፡ በትንቢተ ዮናስ የምናገኛቸው ፍጥረቶች በሙሉ ማለትም ነፋሱ፣ ዓሣው፣ ትሉ፣ ፀሐይዋ እግዚአብሔርን ታዝዘውታል፡፡ እግዚአብሔር ከመታዘዝ እምቢ ያለው ነቢዩ ዮናስ ብቻ ነበረ፡፡ ዛሬስ ማን ይኾን ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ያለው? እኛ ብቻ አይደለንምን? ፀሐይዋ አንድ ቀን ስንኳ በቃኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አልወጣም ብላ አታውቅም፡፡ ዝናቡ አልዘንብም ብሎ አያውቅም፡፡ ምድሪቱ ለሚያራቁታትና ለሚያጐሳቁላት ሰው ፍሬ አልሰጥም ብላ አታውቅም፡፡ አሁንም አልታዘዝ ያልነው እኛው ሰዎች ብቻ ነን፡፡ አንዳንድ ጊዜ እደነቃለኹ፡፡ እነዚህ ፍጥረታት እንደ እኛ የሚያወጡበትና የሚያወርዱበት ንቃተ ኅሊና የላቸውም፡፡ ኾኖም ግን ከእኛ በላይ ለፈጣሪያቸው ይታዘዛሉ፡፡ አምላካቸውን ከእኛ በላይ ይሰሙታል፡፡ ፈቃዱንም ይፈጽማሉ፡፡ መርከበኞቹ አሕዛብ ናቸው፡፡ ኾኖም ግን እጅግ የሚያስደንቅ ነገር ከእነርሱ እንማራለን፡፡ መርከባቸው ልትሰበር ስርግርግ ባለች ጊዜ እንሰጥማለን ብለው ፈሩ፤ ወደየአምላካቸውም ጮኹ፡፡ ከዚህ ድርጊታቸው እንደምናስተውለው አምላካቸውን አስቀድመዋል፡፡ አስቀድመው ጸለዩ፤ በመቀጠልም መርከባቸው ይቀልላቸው ዘንድ በውስጧ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ስለኾነም ጸሎት በመርከበኞቹ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ነበረው፡፡ ዮናስን ሲቀሰቅሱት እንኳእግዚአብሔር ያድነን ዘንድ የፈጣሪህን ስም ጥራአሉት እንጂተነሥተህ ዕቃችንን ወደ ባሕሩ በመጣል አግዘንአላሉትም፡፡ ስለኾነም በዚያ የጭንቅ ሰዓት ኹሉም ይጸልይ ነበር፡፡ የማይጸልየው አንዱ ዮናስ ብቻ ነበር፡፡ ከቀሰቀሱት በኋላ እንኳ እንደጸለየ መጽሐፍ አይነግረንም፡፡
አስደናቂ ነው! በዚያ የጭንቅ ሰዓት ጥፋተኛ መኾኑን ስለሚያውቅ ዮናስ ራሱን ለመደበቅ ወደ ከርሠ ሐመሩ ወርዶ ተኝቶ ያንኮራፋ ነበር፡፡ ከዋጠው ያለመታዘዝ ክኒን የተነሣ አሕዛብ እየጸለዩ እርሱ ያንኮራፋ ነበር፡፡ በዚህ አስጨናቂ ዘመን አሕዛብ ግንባራቸው እስኪላጥ ድረስ ወደ አምላካቸው እየተንበረከኩና እየጮኹ ስንቶቻችን እንደ ዮናስ ተኝተናል? እግዚአብሔር ግን እንዴት ግሩም እንደኾነ እናስተውል፡፡ ነቢዩን በአሕዛብ ያስገስጸው ነበርና፡፡ በመልአክ አይደለም፤ በሌላ ነቢይም አይደለም፤ በአሕዛብ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ማንን በምን መገሰጽ እንዳለበት ያውቃል፡፡ እርሱ ሲገስጽ እንዲህ ነውና፡፡ ሕዝቡን ሲገስጽ አሕዛብን ያሰለጥናል፡፡ በእምነት እንደ በለጥዋቸውም ያሳያቸዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁዳውያንን በከነናዊቷ ሴት ገስጾአቸዋል፡፡ በሳምራይቱ ሴት ገስጾአቸዋል፡፡ ፈሪሳዊዉን በቀራጩ ገስጾታል፡፡ አሁንም ነቢዩ ዮናስን በአሕዛብ ቋትለኞች (መርከበኞች) ይገስጸው፡፡ ተነሥቶ እንዲጸልይ በአሕዛብ ይቀሰቅሰው ነበር፡፡ በዚያ የጭንቅ ሰዓት እያንኮራፋ ነበርና፡፡ ዮናስ ምንም ሊነቃ አልቻለም፡፡ ነፋሱ ቢነፍስ፣ ማዕበሉ ከፍ ከፍ ቢል፣ መርከቢቱ እስክትሰበር ድረስ ስርግርግ ብትል ምንም ሊነቃ አልቻለም፡፡ ስለኾነም እግዚአብሔር የመርከቢቱን አለቃ ላከና ቀሰቀሰው፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ዛሬ ለጥ ብለን ከምናንኮራፋበት የኃጢአት አልጋ ለመቀስቀስ እግዚአብሔር ማንን ልኮ እየቀሰቀሰን ይኾን? እግዚአብሔርን በማያውቁ ሰዎች ይኾን? በመናፍቃን ይኾን? ወይስ ጭራሽ ቃለ እግዚአብሔርን አያውቁም በምንላቸው ሰዎች? እስኪ ኹላችንም ወደየምንውልበት ቦታ በዓይነ ኅሊናችን እንሂድና በማን እንደሚገስጸን ልብ እንበል ……… …… ……! በእውነት ልብ ይስጠን

ሌላው ከእነዚህ መርከበኞች የምንማረው እግዚአብሔር አጥብቀው ይሹት እንደነበር ነው፡፡ ምንም እንኳን ማን እንደኾነ በትክክል ባያውቁትም እንዳለ ግን ያውቃሉ፡፡ ምክንያቱም ዮናስን ሲቀሰቅሱትወደ አምላካችን ጩኽሳይኾንየፈጣሪህን ስም ጥራነውና የሚሉት፡፡ እውነተኛ አምላክ ማን እንደኾነ ባያውቁታም ይወዱታል፤ በትክክለኛ መንገድ ባይኾንም ያምኑበታል፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ንጹሕ ልቦናቸው አይቶ ራሱን የገለጠላቸው፡፡ መርከበኞቹ የጸሎት ብቻ ሳይኾን የእምነትም ሰዎች ነበሩ፡፡ ዕጣ ተጣጣሉ፡፡ ለምን? ያገኘቻቸው መከራ በማን ምክንያት እንደኾነ እግዚአብሔር ያሳውቃቸው ዘንድ፡፡ ምንም እንኳን የአሕዛብ መርከበኞች ቢኾኑም ማዕበሉ የመጣው በነፋሱ ወይም በአየር ፀባዩ መለወጥ ምክንያት ነው ብለው አላሰቡም፡፡ በአንድ ሰው ኃጢአት ምክንያት እንደ ኾነ አወቁ እንጂ፡፡ ስለኾነም ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ፡፡ ዕጣውም በዮናስ ወጣበት፡፡ አሕዛብ ቢኾኑም እግዚአብሔር ጥፋተኛ ማን እንደኾነ ነገራቸው፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ ምንም እንኳ ዕጣው በዮናስ ቢወጣም፣ ዮናስ ለሀገራቸው እንግዳ ሰው ቢኾንም፣ እነርሱ ሲጸልዩ እርሱ እያንኮራፋ የነበረ ቢኾንም፣ በእርሱ ምክንያት ንብረታቸውን ወደ ባሕሩ በመጣል ያጡ ቢኾንም ፈጥነው አልፈረዱበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዮናስ ምን እንደሚል፣ ማንን እንደሚያመልክ፣ ከወዴት እንደመጣ፣ ወዴትም እንደሚሄድ፣ ወገኖቹ እነማን እንደኾኑ ጠየቁት እንጂ፡፡ ልብ በሉ! በዚህ ሰዓት መርከቧ ልትስበር ትንሽ ነው የቀራት፤ እነርሱ ግን ይጠይቁት ነበር፡፡ ይኸውም የሰውን ነፍስ ለማጥፋት እንደምን ይፈሩ እንደነበር ያመለክታል፡፡ ዕጣው በዮናስ ወጥቶ ሳለ ጥፋቱ ራሱ እንዲያረጋግጥላቸው ይጠይቁት ነበር፡፡ ዮናስም፡- “ዕብራዊ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁአላቸው፡፡ እነርሱ ግን ይህን ባላቸው ጊዜ የባሰ ፈሩ፡፡ዮናስ ሆይ! አምላክህ ባሕርንም የፈጠረ ስለኾነ በፈጣሪህ እጅ ነው ያለነው ማለት ነው፡፡ አምላክህ የብሱንም የፈጠረ ስለኾነ ወደ የብሱ በሰላም እንዲያወጣን እንሻለንአሉት፡፡ ዳግመኛም ጠየቁት፡- “ታድያ ምን አድርገህ ነው?” አሉት፡፡ እርሱም ከፈጣሪው ኰብልሎ እንደመጣ ነገራቸው፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔር ዮናስን እንዴት እየገሰጸው እንደኾነ፣ ራሱንም ለመርከበኞቹ እንዴት እየገለጠ እንደኾነ ታስተውላላችሁን? አሁንም እነዚህ መርከበኞች ምንም እንኳን ዮናስ ጥፋቱን ቢነግራቸውም፣ ምንም እንኳን ማዕበሉ እየበረታ እየሄደ ቢኾንም ተጣድፈው ይጥሉት ዘንድ አልተቻኰሉም፡፡ ጥፋተኛ እንደኾነ ቢያውቁም፣ ሞት የሚገባው እንደኾነ ቢያውቁም፣ የንብረታቸው ኹሉ መጣል ምክንያት እርሱ እንደኾነ ቢያውቁም፣ ማዕበሉ እየበረታ ሕይወታቸውም ልትጠፋ እየተቃረበች እንደኾነች ቢያውቁም ወደ ባሕሩ ይጥሉትና ይሞት ዘንድ ከቶ አልተፋጠኑም፡፡ባሕሩ ጸጥ ይልልን ዘንድ ምን እናድርግ፤ መፍትሔ የምተለው ስጠን፤ ባሕሩ ፈጽሞ እየተነሣሣ ነውናአሉት እንጂ፡፡ ዮናስም፡- “እኔን አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፡፡ ይህ ጽኑ ማዕበል የተነሣሣባችሁ በእኔ ምክንያት እንደኾነ አውቂያለኹና ጣሉኝ፡፡ እኔን ከመጣል ውጪ ሌላ አማራጭ የላችሁምና ጣሉኝአላቸው፡፡ እነርሱ ግን እንዳይጥሉት ወደዱ፡፡ ርኅራኂያቸው እንደምን የበዛ እንደኾነ ታስተውላላችሁን? የችግሩ ምንጭ ማን እንደኾነ፣ መፍትሔውም ምን እንደኾነ ቢያውቁም ይጥሉት ዘንድ አልወደዱም፡፡ ወደ መሬት ይመለሱ ዘንድ አጥብቀው ቀዘፉ እንጂ፡፡ ዮናስን ከሞት ያድኑት ዘንድ የሚቻላቸውን ኹሉ አደረጉ፡፡ ኾኖም ግን ዮናስ ወደ ባሕሩ ይጣል ዘንድ ፈቃደ እግዚአብሔር ስለ ነበር ሳይቻላቸው ቀረ፡፡ ምንም እንኳን ማዕበሉ እየጨመረ ቢሄድም፣ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ብትኾንም በዚያች ሰዓት ስለ ዮናስ ይጸልዩ ነበር፡፡ እንዲህ እያሉም በአንድ ልብ ኾነው፡- “አቤቱ ነቢይህን ልንገድለው አንሻም፡፡ ኾኖም ቁጣህ ራሱ ተናግሮናል፡፡ አቤቱ እንደ ወደደህ እንደምታደርግ ከማዕበሉ አይተናልእያሉ ንጹሕ ደም እንዳያፈሱ እግዚአብሔርን ይለማመጡት ነበር፡፡ እውነተኛው ዮናስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ (እነ ጲላጦስ) ንጹሕ መኾኑን መሰከሩ፤ ሞትም የማይገባው መኾኑን ተናገሩ፡፡ እስራኤል ግን ይሰቀል ይሰቀል እያሉ ይጮኹ ነበር፡፡ ደሙም በእኛና በልጆቻችን ይሁን ይሉ ነበር፡፡ መርከበኞቹ እንዲህ ከጸለዩ በኋላ ዮናስን አንሥተው ከባሕሩ ጣሉት፡፡ ገፉት አይደለም፤ አንሥተው እንጂ፡፡ ታግለው አልጣሉትም፤ ወዶና ፈቅዶ እንጂ፡፡ ባሕርም ድርጐዋን ተቀብላለችና ጸጥ አለች፡፡ መርከበኞቹም ዮናስ የተናገረው እውነት እንደኾነ ከባሕሩ ዝምታ አይተው እግዚአብሔርን ፈጽመው ፈሩ፡፡ መሥዋዕትንም ሠዉ፡፡ በግ ወይም ፍየል አይደለም፡፡ እውነተኛ የኾነ መሥዋዕት እንጂ፡፡ ልቡናቸውን /መዝ.49 14/፡፡
ይቀጥላል

3 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛላችሁ

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር!

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount