(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ
የመቅረዝ ዘተዋሕዶ አንባብያን! እንደ ምን ሰነበታችሁ? መቼስ መቅረዝ ዘተዋሕዶ የጡመራ መድረካችን ከስንፍናዬ የተነሣ ጨለምለም
ካለች ወራት ተቆጥረዋል፡፡ እስኪ ደግሞ እግዚአብሔር እስከ ፈቀደልን ድረስ ዘይት እንጨምርባትና ታብራ፡፡ ለዛሬም የትምህርተ ሃይማኖት
ትምህርታችን ቀጣይ ክፍል ስለ ኾነው ስለ “ሰው ልጅ” ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
የሰው
ልጅ የሥነ ፍጥረት ኹሉ አክሊል ነው፡፡ ፍጥረታቱ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የተፈጠሩት ለሰው ነውና፡፡ በሰው ልጅና በሌሎች ፍጥረታት
አፈጣጠር ላይም ልዩነት አለው፡፡ እግዚአብሔር መግቦቱ፣ ጠብቆቱ፣ ፍቅሩ ለፍጥረታት ኹሉ ቢኾንም የሰው ልጅ ግን ከፍጥረት ኹሉ በላይ
ልዩ የኾነ ቦታ አለው፡፡
ምዕራበውያን
“ዘመነ አብርሆት” ከሚሉት ጊዜ አንሥቶ ግን ትክክለኛው የሰው ትርጉሙ እየተዛባ መጥቷል፡፡ የሰው እውነተኛ ትርጉሙ በጭምብሎች ተሸፍኖ
ዓለም ሰው እያለች የምትጠራው ጭምብሉን ኾኗል፡፡
ለምሳሌ
በዚህ ዓለም ከነገረ ሰብእ የትምህርት ዘርፎች አንዱ የኾነው አርኪኦሎጂ ስለ ሰው ልጅ ባሕል፣ ተረፈ ዐፅም፣ አመጋገብ ሥርዓት እና
የመሳሰሉትን ያጠናል፡፡ ሥነ ሕይወታዊ ነገረ ሰብእ (Biological Anthropology) ደግሞ ሰዎች የተለያዩ አከባቢዎችን
እንዴት መልመድ እንደ ቻሉ፣ የአንድ በሽታና ሞት መነሻው ምን እንደ ኾነ፣ ባሕልና ሥነ ሕይወት የሰው ልጅን ሕይወት ከመቅረጽ አንጻር
ምን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ፣ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ስለሚመሳሰሉባቸውና ስለሚለያዩባቸው ነጥቦች ያጠናል፡፡ ማኅበረ ሰባዊ
ነገረ ሰብእ (Social Anthropology) የተባለው ዘርፍም ሰዎች እንዴት በተለያዩ ቦታዎች እንደሚኖሩ፣ በዙሪያቸው ያለው
ዓለምም እንዴት እንደሚገነዘቡት፣ ከጎረቤታቸው ጋር ስላላቸው መስተጋብር እና ስለመሳሰሉት ያጠናሉ፡፡ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ሌላው
ዘርፍ (Linguistic Anthropology) ደግሞ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች እንዴት እንደሚግባቡ፣ ቋንቋ ከምናየው ጋር እንዴት
የተሰናሰለ እንደ ኾነ ያጠናሉ፡፡
እንግዲህ
ዓለም ስለ ሰው ያላት ዕውቀት እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የትምህርት መስኮች (Descriptive Anthropologies) የሚሰጧት
መረጃ ነው፡፡ ይህ በራሱ ጥፋት ባይኾንም ነገር ግን ቁንጽል ነው፡፡
ሎጥን
የምትመዝነው በሰዶም ሰዎች ነው፡፡ አብርሃምን የምትመለከተው በዑር ወይም በካራን ሰዎች መስፈርትነት ነው፡፡ አንድ ቅዱስ አትናቴዎስን
የምታየው በአርዮሳዊው ዓለም የተንሸዋረረ ዓይን ነው፡፡
ዘመናዊነት
(Modernity) ሰውን የሚመዝነው ከግላዊነቱ፣ በሥራ ከመጠመዱ፣ የዚህን ዓለም ኑሮን ከማሸነፉ፣ “አንተ እንደዚያ ታስባለህ፤
እኔ ግን እንደዚህ አስባለሁ” በማለት እውነታን እንደ እውነት ሳይኾን እንደ አንድ እይታ ከመመልከት እና ከመሳሰሉት አንጻር ነው፡፡
ዓለማዊነትም
(Secularism) ዋና ማእከሉን የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት ላይ በማድረግ “ሰውን ሰው የሚያሰኘው ቁሳዊ ሀብቱና ንብረቱ ነው”
የሚል ስብከቱን ይሰብካል፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ምድራዊ ሕይወት በቂ ምላሽ አይሰጥም በማለት የሰው መሠረታዊ ፍላጎቱ ምድራዊ ምግብ፣
ልብስና መጠለያ አድርጎት ያርፋል፡፡
ከቅርብ
ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩትን ዕቃ (ሮቦት) “ሰው” ብለው ለመጥራት እየተጣጣሩ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ
ዓለም ምን ያህል ከእውነታ ርቃ እንደ ኼደችና እኛም ምን ያህል በቀጥታም ይኾን በተዘዋዋሪ ነጽሮታችን እንደ ተዛባ የሚያመለክት
ነው፡፡
የዚህ
ጽሑፍ ዋና ዓላማም የሰው አማናዊ ትርጉሙ ከላይ የለበሰው ጭምብሉ ሳይኾን ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ጥብቅ አንድነትና ኅብረት መኾኑን
በማስገንዘብ ኦርቶዶክሳዊ መነጽርን ማሳየት ነው፡፡
ሀ) የሰው ልጅ አፈጣጠር
የሰው
አፈጣጠርን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ኹለት ሥፍራዎች ላይ ልዩ ቦታ ሰጥቶት ይናገራል፡፡ አንደኛው፡- “እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በአርአያችን በአምሳላችን እንፍጠር፤ … እግዚአብሔርም ሰውን በአርአያው
በአምሳሉ ፈጠረው” የሚል ሲኾን (ዘፍ.1፡26-27)፥ ኹለተኛው
ደግሞ፡- “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው
ኾነ፡፡ … እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ እንቅልፍ አመጣ፤ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አጥንቶች አንድ አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ
መላው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት፡፡ ያን ጊዜም አዳም አለ፡-
ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከባልዋ ተገኝታለችና ሚስት ትኹነኝ” የሚል ነው (ዘፍ.2፡7፣
21-23)፡፡
በእነዚህ
ኹለት ቦታዎች ላይ የሰው ልጅ ልዩ መኾን በደንብ ተብራርቶ ተቀምጧል፡፡ እስኪ ጥቂት ነጥቦችን እንመልከት፡-
ሀ.1) ሰውን ለመፍጠር እግዚአብሔር አሳብና ምክር
ነበረው (ዘፍ.1፡26)፡፡
ሌሎች
ፍጥረታትም ቢኾኑ በድንገትና ያለ እግዚአብሔር ምክርና አሳብ የተፈጠሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅን ሲፈጥሩ ሦስቱም አካላተ
ሥላሴ “እንፍጠር” ብለው ማሰባቸውና አስበውም መፍጠራቸው ግን የሰው ልጅ ምን ያህል በልበ ሥላሴ ልዩ ስፍራ እንዳለው የሚያስገነዝብ
ነው፡፡ እንደዚህ ተብሎ የተፈጠረ ፍጥረት የለም፤ መላእክትም ቢኾኑ በዚህ መንገድ የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ሥላሴ
“እንፍጠር” ብለው የሚፈጠሩት እንጂ በሰው አሳብና ምክር የሚፈጠር አለመኾኑን ነው፡፡
ሀ.2) የሰው ልጅ በእግዚአብሔር በገቢር የተፈጠረ ነው፡፡
ሌሎች
ፍጥረታት በኀልዮና በነቢብ የተፈጠሩ ሲኾኑ የሰው ልጅ ግን በገቢር በእጁ ተነክቶም ጭምር የተፈጠረ ነው፡፡ ይህም ምን ያህል ልዩ
ፍጥረት መኾኑን፣ ሰውን ሰው የሚያሰኘው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ጥብቅ ግንኙነት፣ ኃይላተ እግዚአብሔር (Divine
Energies) ከሚባሉት ጸጋዎች ጋር በሚኖረው ቀጥተኛ አንድነትና ኅብረት እነርሱንም ገንዘብ እያደረገ ማደጉን እንደ ኾነ የሚያስረዳ
ነው፡፡
ከምድር
አፈር ያውም ከትቢያ መፈጠሩ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚለው የሌሎች ፍጥረታት አክሊል እንደ መኾኑ ይህን አስቦ እንዳይታበይና
አፈር መኾኑን እንዳይረሳ ነው፡፡
ሀ.3) እግዚአብሔር ሰውን ልዩ አድርጎ ፈጥሮታል (ዘፍ.1፡27)፡፡
መላእክትን ጨምሮ ሌሎች ፍጥረታት እንደየራሳቸው ወገን
መልክ የተፈጠሩ ሲኾኑ (ዘፍ.1፡25)፥ የሰው ልጅ ግን በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረ ነው (ዘፍ.1፡26)፡፡ እግዚአብሔር
“በአርአያችን በአምሳላችን እንፍጠር” ብሎ መናገሩ በራሱ የሰው ልጅ በማን አርአያና አምሳል እንደ ተፈጠረ እንዲያውቅ፣ ዐውቆም
ጥንቱን ለተፈጠረበት ዓላማ እንዲኖር የተደረገ አምላካዊ ጥበብ ነው፡፡
ሀ.4) እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሕይወት የምትኾነው ነፍስ
እፍ ብሎ ሰጥቶታል (ዘፍ.2፡7)፡፡
በዕብራውያን
ብቻ ሳይኾን በአጠቃላይ በሴማውያን ባሕል በአንድ ሰው ፊት እፍ ብሎ መተንፈስ ማለት ትንፋሽን፣ የውስጥ ምሥጢርን፣ የራስ የኾነን
ነገር ለዚያ ሰው ማጋራት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርም ለሰው ልጅ እፍ አለበት ማለት የራሱ የኾነን ማንነት በጸጋ እንዳጋራው የሚያስረዳ
ነው፡፡
በመኾኑም
በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ኹለት ነገሮችን በአንድ ጊዜ ተቀብሏል፡፡ አንደኛው ሕያዊት ነፍስ ስትኾን ኹለተኛው ደግሞ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ
ነው፡፡
ሕይወት
የምትኾነው ነፍስ ሰጠው ሲባልም በፊት ሥጋ ፈጥሮ በኋላ ነፍስን አምጥቶ አሳደረበት ማለት አይደለም፤ ሥጋን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ
ነፍስንም እምኀበ አልቦ አምጥቶ ሲፈጥር ሲያዋሕድ አንድ ነው፡፡ የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ በተዓቅቦ ነውና፡፡ ስለ ነፍስ ጥቂት ቆይተን
እንነጋገራለን፡፡
ጸጋ መንፈስ
ቅዱስ ተሰጠው ማለት ደግሞ ሰውን ሰው የሚያሰኘው እጅግ ወሳኙና መሠረታዊው ነገር ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው አንድነትና ኅብረት
(Communion) መኾኑን መግለጽ ነው፡፡ አዳም ሲበድል “ትሞታለህ” መባሉም በዋናነት የሥጋና የነፍስ መለየትን ሳይኾን “ጸጋ
መንፈስ ቅዱስ ይለ’ይሃል፣ ይህን አንድነትና ኅብረት ታጣለህ” ማለት ነውና፡፡
ሀ.5) የሰው ልጅ ሌሎች ፍጥረታትን እንዲገዛቸው በእነርሱ ላይም የጸጋ ገዢያቸው ኾኖ ተሾሟል (ዘፍ.1፡28)፡፡
ይህም
ማለት እግዚአብሔር ፍጥረታትን የሚገዛቸው በፍቅር፣ በጠብቆት፣ በመግቦት፣ በትዕግሥት እንደ ኾነ ኹሉ፥ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር
መልክ ስለ ተፈጠረ እነዚህን ፍጥረታት ሊመለከታቸው የሚገባው በዚህ አኳኋን ነው ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሔርና በፍጥረታት መካከል
ያለው ግንኙነት የጌታና የባሪያ ዓይነት ግንኙነት እንዳልኾነ ኹሉ፥ የሰው ልጅም እንኳንስ ከሌላው ወንድሙ ከሰው ጋር ይቅርና ከግዑዛን
ፍጥረታትም ጋር ቢኾን ግንኙነቱ በኹኔታዎች ላይ ባልተገደበ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ሊኾን ይገባዋል ማለት ነው፡፡ እነዚህን ፍጥረታት
ይጠብቃቸው፣ ይንከባከባቸው እንጂ በጭካኔ፣ በአምባገነንነት፣ በመጨቆን አይመልከታቸው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታቱን የሚመለከትበት
ዓይን፣ የሚያደርግላቸውንም መግቦት ሰውም በተሰጠው ጸጋ ይህን ለእነዚህ ፍጥረታት እንዲያደርግላቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ክፋትን
ኃጢአትን እንዳልፈጠረ ኹሉ ሰውም እነዚህን ፍጥረታት ወደ ቅድስና ሊያመጣቸው የተጠራ እንደ ኾነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስ፡- “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና፡፡ ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና … ተስፋውም ፍጥረትራሱ
ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነጻነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚኾን ክብር ነጻነት እንዲደርስ ነው፡፡ ፍጥረት ኹሉ እስከ አሁን ድረስ
በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” እንዳለውም የሰው ልጅ በንጽህና በቅድስና ወደ እግዚአብሔር በቀረበ መጠን ፍጥረታትም ይቀደሳሉ
(ሮሜ.8፡19-22)፡፡
እንግዲህ
የሰው ልጅ ፍጥረታትን ኹሉ እንዲህ ሰብስቦ በንጽህና በቅድስና ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርብ ተጠርቶና ተሹሞ ሳለ ጭራሽ በዘርና
በቋንቋ ተቧድኖና ተከፋፍሎ ማየት ይህን መሠረታዊ ትምህርት በቀጥታ የሚቃረን መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከሰውነት መውረድ ነው፡፡
ሀ.6) መጨረሻ መፈጠሩ በራሱ ልዩ መኾኑን ያስረዳል፡፡
ቅዱስ
አፍሬም ሶሪያዊ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስና ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳሉት የሰው ልጅ መጨረሻ ላይ መፈጠሩ የክብሩ ልዕልና ያሳያል፡፡
ከፍጥረት ኹሉ መጨረሻ ላይ መፈጠሩ ስለ ተናቀ ሳይኾን ገና ከመፈጠሩ አንሥቶ በሌሎች ፍጥረታት ላይ ንጉሥ ስለ ኾነ ነው፡፡ አንድ
ሰው ጥቁር እንግዳ ወደ ቤቱ ከመቀበሉ በፊት እንግዳው የሚመገበውን ምግብ፣ የሚያርፍበትን ቦታ፣ ዓይኖቹን የሚያሳርፍባቸውን ኹሉ
አስውቦ እንደሚያዘጋጅ ኹሉ እግዚአብሔርም አዳምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ እርሱን የሚያገለግሉትን ፍጥረታት ፈጥሮ ሰውን እጅጉን አከበረው፡፡
ለ) አርአያና አምሳል
የሰው
ልጅ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረ ልዩ ፍጥረት ነው፡፡ እንዲሁ ፍጥረት ብቻ አይደለም፡፡
አርአያ
እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መልክ) የሚባሉት በእግዚአብሔር ዘንድ በምልአት ያሉት ለሰው ደግሞ ገና ሲፈጠር አንሥቶ እንደ ዓቅሙ
የተሰጡት ጸጋዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ማንም ሰው ሲፈጠር አንሥቶ ማሰብ ይችላል፡፡ ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ ዐዋቂነት አለው፡፡ ማፍቀርም
መፈቀርም ይችላል፡፡ አዲስ ፍጥረትን ባይፈጥርም ከተፈጠረው አንሥቶ አንድን ነገር በአዲስ አቀራረብ መፍጠር ይችላል፡፡ ንጽህናን
ቅድስናን መውደድ፣ ክፋትንም መጥላት ይችላል፡፡ አርአያ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መልክ) የሚባለው ይኼ ነው፡፡
አምሳል
(የእግዚአብሔር ምሳሌ) ማለት ደግሞ ልናገኘው ወይም ልንደርስበት የምንጋደልለት ቅድስና ወይም ጸጋ ነው፡፡ ይህን አምሳል እንድናገኝ
የሚረዳንም ይህ አስቀድሞ የተሰጠን “አርአያ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር መልክ” ነው፡፡ አርአያ እግዚአብሔር እግዚአብሔርን በመምሰል
እንድናድግ የሚያደርገን ዓቅም ወይም ዘር ወይም መነሻ ነው፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር መልክ ተነሥቶ ወደ እግዚአብሔር አምሳል ማደግም
በኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አጠራር ሱታፌ አምላክነት - ቴዎሲስ (Theosis) ይባላል፡፡
የሰው
ልጅ የተጠራው ለዚህ ነው - ከመለኮት ባሕርይ ተካፋይ ይኾን ዘንድ! ይህ ጥሪ ደግሞ ግዴታ የሌለበት ግብረ መልስ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር
ለዚህ ጥሪ የሚደረገው ምላሽ ከፍቅር የተነሣ እንዲኾን ያደረገውም ለዚህ ነው፡፡ ያለ ፍቅር የሚደረግ ነገር ግዴታ ነውና፡፡ በፍቅር
የሚደረግ ከኾነ ግን በውስጡ ምርጫም ጭምር አለበት - ወዶና ፈቅዶ እሺ ማለት ይቻላል፤ ልክ እንደ አዳም አይኾንም ማለትም ይቻላል፡፡
በውዴታና በምርጫ የማይደረግ ነገር ጥሪ አይባልም፡፡ ግዴታ ነው፡፡ የባሪያና የጌታ ግንኙነት ነው፡፡ በሰው ልጅና በእግዚአብሔር
መካከል ያለው ግንኙነት ግን የልጅና የአባት ግንኙነት ነው፡፡
አንድን
ነገር ወደንና ፈቅደን የማናደርግ ብንኾን ኖሮ ሰው መባላችን ቀርቶ አእምሮ የሌለን እንስሳት ነበርን የምንባለው፡፡ ነጻ ፈቃድ ያለን
መኾናችን የሚታወቀው ግን በዚህ ነው፡፡ ወደንና ፈቅደን ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ዓቅም አለንና፡፡ ወደንና ፈቅደን የመራቅ ዓቅምም
አለንና፡፡ በእኛና በእግዚአብሔር ያለው ግንኙነት በዚህ ፍቅር፣ በዚህ ነጻ ፈቃድና ምርጫ የተመሠረተ እንጂ እንደ ብረትና እንደ
ማግኔት ዓይነት በግዴታ የሚፈጸም አይደለምና፡፡
ቅዱስ
ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንደሚነግረን ግን እግዚአብሔር ይህን ነጻ ፈቃድ የሰጠን ለተጠራንለት ዓላማ ወደንና ፈቅደን እንድንፈጽምበት
እንጂ እንድንርቅበት አይደለም፡፡ ስንቀርብበት የምንሸለመው፣ ስንርቅበት ደግሞ እኛው ራሳችን ኃላፊነት ወስደን የምንቀጣ’ውም ከዚህ
የተነሣ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ነጻ ፈቃዳችን ከኃላፊነት ጋር ነው፡፡
ወደ እግዚአብሔር
ስንቀርብ ክርስቶስን ወደ መምሰል እንመጣለን፡፡ ነጻ ፈቃዳችንን በአግባቡ መፈጸም እንችላለን፡፡ እንደ ተፈጠርንለት ዓላማ በጎ ነገርን
መምረጥ እንችላለን፡፡ አማን በአማን ሰው የሚያስብለንም ይኸው ነው፡፡ ከእርሱ ስንርቅ ግን ሰው መባላችን ይቀራል፡፡ መልካችን ይቆሽሻል፡፡
እግዚአብሔርን መምሰላችን ይቀራል፡፡ ነጻ ፈቃዳችንን በአግባቡ ተጠቅመን በጎ ነገርን ለመምረጥ ዓቅም እናጣለን፡፡
ይኼን
ጊዜ በመግቢያችን ላይ እንደ ተነጋገርነው በእኛ ዘንድ የሚታየው እውነተኛው መልካችን ሳይኾን ያጠለቅነው ለምሳሌ የኃጢአት ጭምብል
ይኾናል፡፡ ጭምብል ደግሞ ጭምብል እንጂ ሰው አይደለም፡፡ የአንድ ተዋናይ እውነተኛ መልኩ ከመድረኩ ጀርባ እንጂ መድረኩ ላይ ያለው
እንዳልኾነ ኹሉ የአንድ ሰው እውነተኛ መልኩም ጭምብሉ ማለትም ቆሻሻው፣ ኃጢአቱ ተወግዶ ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ ያለው መልኩ ነው፡፡
የሰው
ልጅ እግዚአብሔርን የሚመስለው በነፍሱ ነው የሚል አመለካከት አለ፡፡ እነ ቅዱስ ሄሬኔዎስና ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እንደሚያስተምሩን
ግን ሰው የሚባለው “ነፍስና ሥጋ” ተብሎ ክልኤነት (dualism) ያለው ስላልኾነ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን የሚመስለው በነፍሱም
በሥጋውም በተዋሕዶ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን የሚመስለው በነፍሱ ነው ካልን ሰው ክልኤ ባሕርይ አለው ያሰኝብናል፡፡ ዳግማይ አዳም
የተባለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነውና አንድ ባሕርይ በተዋሕዶ ማለታችን ስሕተት ውስጥ
ይከተዋል፡፡ ዳግመኛም የነገረ ሰብእ ትምህርታችን ወደ አፍላጦናዊ (Platonic) ፍልስፍና ይኼዳል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡-
“እኔ ክርስቶስን እንደምመስል” ያለውን “እኔ በነፍሴ ክርስቶስን እንደምመስል” ማለት ነበረበት ያሰኝብናል (1ኛ ቆሮ.11፡1)፡፡
ሐ) የሰው ልጅ ውድቀትና ትንሣኤ
የሰው
ልጅ በምክረ ከይሲ ሲበድል ከአርአያ እግዚአብሔር ወደ እግዚአብሔር አምሳል ማደግ አቅቶት ለ5500 ዘመናት ቆይቷል፡፡ አርአያው
ሳይኾን አምሳሉ ተበላሽቶ ቆየ፡፡ ዘሩ ሳይኾን ዘሩ ፍሬ ማፍራት አቅቶት ተጎሳቁሎ ቆይቷል፡፡
ይህ ትምህርት
ከአውግስጢኖሳዊ አስተሳሰብ ጋር ፍጹም የተለየ መኾኑን መረዳት ያሻል፡፡ ምክንያቱም በአውግስጢኖስ አስተምህሮ የሰው ልጅ ሲበድል
እንደ ጥቁር ከሰል ሙሉ ለሙሉ መልኩን አጥቷል፡፡
ይህ ግን
በኦርቶደክሳውያን ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ፡- “በሰሌዳ ላይ የተሠራ ሥዕል ከውጭ በመጣ ቆሻሻ ሲዝግና
ሲበላሽ ሥዕሉ የእርሱ ምስል የኾነው ሰው ስለ ሥዕሉ ሲል ሰሌዳውን ይወለውለዋል፤ ይሰነግለዋል፡፡ ይህም ሥዕሉ ያለበትን ዕንጨት
በመጣል ሳይኾን ከውጭ መጥቶ ሥዕሉን ያበላሸውን ቆሻሻ በማስወገድ ወደ ጥንት ኹኔታው ይመልሰው ዘንድ የሚቻለውን ያደርጋል፡፡ ንጹሃ
ባሕርይ የኾነው የእግዚአብሔር ቃልምበአርአያው ተሠርቶ የነበረውን ሰው ያድሰው ዘንድ፣ በኃጢአቱ የጠፋውን ኃጢአቱን በማስተስረይ
ይፈልገው ዘንድ መጣ” እንዳለው መልኩ ቆሽሾ ቆየ፣ ማደግ አቃተው እንጂ ሙሉ ለሙሉ መልኩን አጥቷል አንልም (በእንተ ሥጋዌ፣
14፡1)፡፡
በመኾኑም
መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ተበላሽቶና ተቋርጦ የነበረው ወደ እግዚአብሔር አምሳል የማደግ ኹኔታ ተመልሶለታል፡፡ ከእግዚአብሔር
ጋር በሚኖረው አንድነትና ፍቅር፣ በምግባርና በትሩፋት የማደግ ዓቅሙ ክኂሉ ተመልሶለታል፡፡ ይኸውም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፡-
“መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ሕይወት የሚሠራው ሲኾን በጥምቀት የሚጀምር … ነው” እንዳለው ስንጠመቅ ያገኘነው ወይም የምናገኘው ነው፡፡
የሰው
ልጅ ሙሉ ለሙሉ ኃጢአት ካመጣው ሞት ነጻ የሚኾነው ግን በዳግም ምጽአት ነው፡፡ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ነገረ ድኅነትን አስመልክተን
በምንነጋገርበት ርእስ እንመለስበታለን፡፡
መ) በእንተ ነፍስ
ነፍስ
የምትባለው እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር ባበጀው ጊዜ በአፍንጫው እፍ ብሎ የሰጠው ናት፡፡ ይህቺ ነፍስ የረቀቀች፣ የማትታይ፣
በአምስት ሕዋሳት የማትዳሰስ ህላዌ ናት፡፡ የማትታይ የማትዳሰስ መኾኗ ግን የለችም አያሰኝም፡፡ ነፋስ፣ ሙቀትና ብርሃን መኖራቸውን
እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ስለማንዳስሳቸው የሉም አንላቸውም፡፡
ነፍስ
የማትዳሰስ፣ የማትጨበጥ፣ የማትታይ ትኹን እንጂ ሕያዊት አካል ናት፡፡ የምትታወቀውም በሦስት ነገሮች ነው፡- በልቡና (በለባዊነት)፣
በቃል (በነባቢነት) እና በሕይወት (በሕያዊትነት)፡፡
ነፍስን
በዚህ መልኩ ካልኾነ በቀር በባሕርይዋ ማወቅ ከባድ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አስመልክቶ፡- “የነፍስም [የባሕርይ ስሟ] እንዲሁ ነው [አይታወቅም]፡፡ ነፍስ ማለት የሥጋ ሕይወት
መኾኗን ብቻ ያስረዳል እንጂ የባሕርይ ስሟ አይደለምና፤ ለባሕርይዋ የሚታወቅ የሚስማማ ስም የላትም” ያለውም
ለዚህ ነው (ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 2፡179-198)፡፡
መ.1.) ዳይኮቶሚ እና ትራይኮቶሚ
ከዚህ
በፊት እንደ ተነጋገርነው በቤተ ክርስቲያን ሰው ስንል ነፍስም ሥጋም ያለው ማለታችን ነው፡፡ ይህም ዳይኮቶሚ ይባላል፡፡ ዳይኮቶሚን
አስመልክቶ አስፍቶ የሚያስተምረው አውግስጢኖስ ነው፡፡ ትራይኮቶሚስቶች ደግሞ መንፈስ የሚለውን ይጨምራሉ፡፡
እነዚህ
ኹለቱም አሳቦች መጽሐፍ ቅዱሳውያን ናቸው (ሮሜ.8፡10፣ 1ኛ ቆሮ.5፡5፣ 1ኛ ተሰ.5፡3፣ ዕብ.4፡12)፡፡ እርስ በእርሳቸውም
የሚጣሉ አይደሉም፡፡ ነፍስ ማለት ለባዊነትን ሲያመለክት መንፈስ ደግሞ ሕያውነትን ዘለዓለማዊነትን የሚያመለክት ነው (Fr.
Dr. Jossi Jacob, Dogmatic Theology, Course Material, p 92)፡፡
መ.2.) ስለ ነፍስ ተፈጥሮ
ስለ ነፍስ
ተፈጥሮ ሦስት አመለካከቶች አሉ፡-
v ነፍስ ቀድሞም የነበረች ናት (Pre-existence of Souls)፤ መዝገበ
ነፍስ በሚባል ትኖራለች፡፡ አንድ ሰው በተወለደ ጊዜም ከዚህ ትሰጠዋለች፡፡ ይህ የአርጌንስ አስተምህሮ ነው፡፡
v ነፍስ በየጊዜው ትፈጠራለች (Creationism)፡፡ አንድ
ሰው ሲፈጠር አዲስ ነፍስ ይፈጠርለታል፡፡
v ነፍስ አንድ ጊዜ የተፈጠረች በሥጋም ያደረች ናት
(Tradutionism)፡፡ ይህ የእነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ አስተምህሮ ነው፡፡
ኦርቶዶክሳዊው
አስተያየት ሦስተኛው ነው፡፡ ነፍስ አንድ ጊዜ የተፈጠረች ሲኾን በየጊዜው ትራባለች፣ ትባዛለች፡፡ ቀድሞ ነበረች ማለት ትክክል አይደለም፤
ፍጥረት በስድስት ቀን የተፈጠረ መኾኑን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚነግረንም በየጊዜው ትፈጠራለች የሚለው አያስኬድም፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ
ዘጋሥጫ እንዲህ ብሎ ግልጽ ያደርግልናል፡- “ጌታችንም ከማርያም ሰው በኾነ ጊዜ ከአዳም መፈጠር ጀምሮ ከአባቶች ባሕርይ ከመጣ በእናቱም
ላይ ካለው በቀር ሌላ የሕይወት እስትንፋስ ለራሱ አላደረገም” (መጽሐፈ
ምሥጢር፣ ምዕ.23፡27)፡፡
ማጠቃለያ
ውድ የመቅረዝ
ዘተዋሕዶ አንባቢዎች! ከላይ ለመግለጽ እንደ ተሞከረው ሰው የሚባለው ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትና ኅብረት ያለው ነው፡፡ ስለዚህ
ከላይ የለበስናቸው ጭምብሎች አውልቀን በእውነት ሰው ወደ መኾን ልናድግ ይገባናል፡፡ የኃጢአት ጭምብል በንስሐ በኑዛዜ ይወልቃል፡፡
እውነተኛ ሰውነት በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ይለበሳል፡፡ ይህ መልካችን ይበልጥ እየበራ፣ እየጠራ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን እየመሰለ
ወደ ክርስቶስ መልክ እየተመነደገ የሚኼደውም ወደ ሕይወት በሚመራ ሳይኾን ሕይወት በኾነው የጸሎት ሕይወት ነው፤ በምግባር በትሩፋት
በተጋድሎ ሕይወት (Ascetic Life) ነው፡፡ ይህን እንድናደረግ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱሳን ኹሉ ቃል ኪዳንና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment