በቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 20 ቀን
2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ሌሎች ሰዎችን ከማያድን ክርስቲያን በላይ
የከፋ ምንም የለም፡፡ አንተ ሰው! ድኻ ነኝ የምትለኝ ለምንድን ነው? ኹለት ዲናር የጣለችዋ ሴት ትፋረድባሃለች፡፡ ከምናምንቴ
ቤተ ሰብ እንደ ተወለድክ የምትነግረኝስ ለምንድን ነው? ሐዋርያትም ምናምንቴዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ታላላቅ መኾን ተችሏቸዋል፡፡
አለመማርህን ሰበብ አድርገህ አትንገረኝ፤ ሐዋርያትም ያልተማሩ ነበሩና፡፡
ባሪያ ብትኾንም እንኳ፣ ስደተኛ ብትኾንም
እንኳ ሥራህን መሥራት ይቻልሃል፤ ሌሎችን መርዳት ይቻልሃል፤ ሰዎችን ማዳን ይቻልሃል፥ አናሲሞስም እንደ አንተ ዓይነት ሰው
ነበርና (ፊልሞ.1፡10-11)፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ምን ወዳለ ማዕረግ ከፍ እንዳደረገውና ምን ብሎ እንደ ጠራው
አድምጥ፡- “በእስራቴ ስለ ወለድሁት፡፡”
ወዳጄ ሆይ! እኔ እንኳን ሕመምተኛ ነኝ
ብለህ አትንገረኝ፤ ጢሞቴዎስም እንደ አንተ ዘወትር ይታመም ነበር፡፡
ፍሬ የማያፈሩ ዛፎች እንደ ምን ብርቱዎችና
ተወዳጆች፣ ግዙፋንና ሐመልማላውያን እንደዚሁም ረጃጅም እንደ ኾኑ አላየህምን? የፍራፍሬ ቦታ ቢኖረን ግን ፍሬ የሚያፈሩት
ሮማንንና ወይራን እንተክላለን እንጂ እነዚህ ፍሬ የማይሰጡንን ዛፎች አንተክልም፡፡ ምክንያቱም እንዲሁ ለዓይን ማረፊያ ለማየት
ካልኾነ በስተቀር ሌላ ጥቅም የላቸውምና፡፡
የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚመለከቱ፣ ሌሎች
ሰዎችንም የማይረዱ ክርስቲያኖችም እንደ እነዚህ ዛፎች ናቸው፡፡ እንዲያውም ከእነዚህ ዛፎችም የባሱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ
ሰዎች የሚቆረጡት ለእሳተ ገሃነም ነው፡፡ ዛፎቹ ግን ቢያንስ ቢያንስ ጠረጴዛም ወንበርም ለመሥራት ይጠቅማሉ፡፡ ለቤት መሥሪያ
ይጠቅማሉ፡፡ አጥር ቅጥር ኾነው ያገለግላሉ፡፡
እነዚያ አምስቱ ደናግል እንደዚህ ነበሩ
(ማቴ.25፡1)፡፡ ርግጥ ነው ንጽህናቸውን የጠበቁ ነበሩ፡፡ ለሚያያቸው ኹሉ ግሩም የኾነ ጠባይ የነበራቸው ነበሩ፡፡ ሥርዓት
ያላቸው ነበሩ፡፡ ይህ ኹሉ ግን ምንም አልጠቀማቸውም፡፡ ወደ እሳተ ገሃነም ከመጣ’ል አልታደጋቸውም፤ ዘይት የተባለው ምጽዋት
አልነበራቸው’ማ! ክርስቶስን በነዳያን አማካኝነት የማይመግቡትም ዕጣ ፈንታቸው ጽዋ ተርታቸው ይኸው ነው - የሰነፎቹ ደናግል
ዕጣ!
አንተ ሰው ልብ ብለህ አስተውል! እነዚህ
ደናግል በግል ኃጢአታቸው አልተነቀፉም፡፡ በዝሙት ወይም በሐሰት ምስክርነት አልተወቀሱም፡፡ በፍጹም! ይልቁንም የተነቀፉትና
የተወቀሱት ሌሎች ሰዎችን ባለመጥቀማቸው ነው፡፡
እንደዚህ ከኾነ ታዲያ ሰዎች ክርስቲያን
ተብለው ሊጠሩ የሚችሉት በምን መመዘኛ ነው? እኮ በምን መስፈርት? አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ! በሊጥ ውስጥ የተጨመረ እርሾ
ሊጡን እንዲቦካ ካላደረገው እንዲሁ እርሾ ተብሎ መጠራት ብቻውን ምን ይረባዋል? ዳግመኛም ወደ እርሱ የቀረቡትን ሰዎች መዓዛው
ካልሸተታቸውና ቤቱን ካላወደው በቀር ከርቤ በከርቤነቱ ምን በቁዔት አለው?
ሌሎች ሰዎችን መርዳት አይቻለኝም ብለህ
አትንገረኝ፡፡ እንዲያውም ልንገርህ፤ አንተም ስማኝ፡- አንተ በእውነት ክርስቲያን ከኾንክ ሌሎች ሰዎችን አለመርዳት የማይቻል
ነው፡፡ ዕጣን መዓዛ እንዲኖረው፣ እርሾም ሊጥን እንዲያቦካ ተፈጥሮው እንደ ኾነ ኹሉ፥ አንድ ክርስቲያንም በስም ክርስቲያን
ከመባል አልፎ በእውነት ያለ ሐሰት ክርስቲያን ከኾነ ሌሎች ሰዎችን መርዳት መቻሉ፣ ሌሎችን የሚጠቅም ሥራ መሥራቱ ክርስቲያናዊ
ተፈጥሮው ነው፡፡
ስለዚህ አይኾንልኝም፤ አይቻለኝም በማለት
እግዚአብሔርን አታማርር፡፡ ፀሐይ ብርሃኗን በእኔ ላይ ማብራት አይቻላትም ካልክ ፀሐይን እየሰደብካት ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ
አንድ ክርስቲያንም ሌሎች ሰዎችን ሊጠቅማቸው አይችልም የምትል ከኾነ እግዚአብሔር እየሰደብክ [ሎቱ ስብሐትና] ሐሰተኛም
እያደረግኸው ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን ሌሎች ሰዎችን ካለመርዳትና ካለመጥቀም ይልቅ ፀሐይ ሙቀትና ብርሃን ባትሰጥ
ይቀላል፡፡ እንደዚህ ከሚኾን ብርሃን ወደ ጨለማ መቀየር ይቀላል፡፡
እናስ? እና’ማ አይቻለኝም አትበለኝ፡፡ የማይቻለው
መርዳት አለመቻል ነውና፡፡ አይኾንልኝም እያልክ በከንቱ እግዚአብሔርን አታማርር፡፡
ሕይወታችንን በአግባቡና በሥርዓቱ የምንመራ ከኾነ እነዚህን ነገሮች ኹሉ በቀላሉ ማድረግ ይቻለናል፤ እነዚህ
ነገሮች ሊደረጉ ግድ ነው፡፡ በመቅረዝ ላይ የተቀመጠ ሻማ ብርሃኑን መደበቅ እንደማይቻለው ኹሉ ክርስቲያንም የእውነት ክርስቲያን
ከኾነ ብርሃኑም መሸሸግ አይቻለውም፡፡ ስለዚህ እውነተኞች ክርስቲያኖች ከኾንን ሌሎች ሰዎችን መርዳት መጥቀምም ችላ አንበል፡፡
Enter your comment...kale hiwot yasemalen
ReplyDeleteye zarew melikt le ene new kale hiwotn yasemalin
ReplyDelete