Thursday, January 12, 2017

ይቅርታ



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 4 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱአምላክ አሜን!
… ከሠራተኞችህ አንዱ ከአንተ መቶ ቅንጣት ወርቆችን ተበደረ እንበል፡፡ ሌላ ሰው ደግሞ ከዚህ ሠራተኛህ የተበደረው ጥቂት ብር ነበረው፡፡ ከዚህ ሠራተኛህ የተበደረው ያ ሰውም ወደ አንተ መጥቶ ቸርነትን እንድታደርግለት ለመነህ፡፡ አንተም ሠራተኛህን ጠርተህ፡- “የዚህን ሰው ዕዳ ተውለት፤ ከእኔ ከተበደርከው ዕዳህም እቀንስልሃለሁ” ብትለውና ይህ ሠራተኛህ ከዚያ በኋላ በዚያ ሰው ላይ ቢጨክንና ቢከፋ ይህን ሠራተኛ ከእጅህ ሊያድነው የሚችል ሰው አለን? እጅግ እንደ ነቀፈህ አድርገህ ቈጥረህ ብዙ ግርፋትን አትገርፈውምን? [እንዲህ ብታደርግ] እጅግ ፍትሐዊ ነው፡፡ እግዚአብሔርም የሚያደርገው እንደዚህ ነው፤ በዚያች ዕለተ ምጽአት ላይ እንዲህ ይልሃልና፡- “አንተ ክፉና ተንኰለኛ ባሪያ ያንን ሰው ይቅር ብትለው ይቅርታው የአንተ ነበርን? ለእርሱ እንድታደርግለት የታዘዝከው ከእኔ የተበደርከውን ነበር፡፡ ያልኩህ ‘ዕዳዉን ብትተውለት እኔም እተውልሃለሁ’ ነው፡፡ በእውነት እንዲህ ይህን ኹኔታ ጨምሬ ባልነግርህም እንኳን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ዕዳዉን ትተውለት ዘንድ በተገባህ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ወዳጅ ኾኜ ውለታን ጠየቅሁህ እንጂ እንደ ጌታ አላዘዝኩህም፡፡ የጠየቅሁህ የእኔ ከኾነው ነው፤ ይህን ካደረግህም እጅግ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን እንደምሰጥህ ቃል ገብቼልህ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ልትሻሻል አልቻልክም፡፡”

ከዚህም በላይ ሰዎች እንደዚህ ሲያደርጉ የሚቀንሱት የዕዳ መጠን ሠራተኞቻቸው ላበደሩአቸው ሌሎች ሰዎች የቀነሱትን ያህል ነው፡፡ ለምሳሌ እንበልና አንድ ሠራተኛ ከአሠሪው መቶ ቅንጣት ወርቅን ይበደራል፡፡ ሌላው ሰው ደግሞ ከዚህ ሠራተኛ ዐሥር ቅንጣት ይበደራል፡፡ ሠራተኛው ዐሥር ቅንጣት ላበደረው ብድሩን ቢተዉለት አሠሪው ግን መቶ ቅንጣቱን አይተውለትም፤ የሚተውለት ዐሥር ቅንጣቱን ብቻ ነው፤ ሌላዉን እንዲመልስለት ይፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ አንተ ለባልንጀራህ ጥቂቱን ስትተውለት እግዚአብሔር ደግሞ ዕዳህን ኹሉ ይተውልሃል፡፡ ይህስ [መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ] የት ይገኛል? [ጌታችን] ስለ ጸሎት ባስተማረው ትምህርት ውስጥ አለ፡፡ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና” እንዲል (ማቴ.6፡14)፡፡ በ“መቶ ዲናር” እና በ“እልፍ መክሊት” መካከል ያለው ልዩነት ያህል ለሰው ይቅር የምንለው ዕዳና ከእግዚአብሔር ይቅር የሚባልልን ዕዳም አይነጻጸርም (ማቴ.18፡24፣28)!
እንግዲህ መቶ ዲናርን ዕዳ ይቅር ብሎ እልፍ መክሊትን የሚቀበል ኾኖ ሳለ ይህቺን ጥቂት ዕዳስ እንኳን ይቅር ሳይል ጸሎቱን በራሱ ላይ የሚያደርስ ይህ ሰው የማይገባው ቅጣት እንደ ምን ያለ ቅጣት ነው? ምክንያቱም “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” ብለህ እየጸለይክ ሳለ አንተ ግን ከዚያ በኋላ ይቅር የማትል ከኾነ እግዚአብሔር ምሕረቱን ወይም ቸርነቱን ኹሉ እንዲያርቅብህ ካልኾነ በቀር ሌላ ምንም እየለመንከው አይደለም፡፡ “እኔ ይቅር በለኝ ብቻ ነው እንጂ የበደሉኝን ይቅር እንደምል በደሌን ይቅር በለኝ ብዬ አልጸልይም” የሚል ሰው ደግሞ አለ፡፡ ታዲያ ይኼ ምንድን ነው? አንተ እንዲህ ብለህ ባትጸልይም እግዚአብሔር ግን እንዲህ አያደርግም፤ ይቅር የሚልህ አንተ ይቅር ስትል ነው፡፡ ይህም ከዚያ በኋላ እንዲህ ብሎ ግልጽ አድርጎታል፡- “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ የሰማዩ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም” (ማቴ.6፡15)፡፡ ስለዚህ ጸሎቱን ሙሉ ባትደግመው ወይም ዕለት ዕለት እንደዚያ ብለህ ስትጸልይ ፈርተህ ከባልንጀራህ ጋር እንድትታረቅ ብሎ እንድትጸልው ባዘዘህ መንገድ ሳይኾን ቈርጠህ ብትደግመው እንኳን ደገኛ መንገድ ነው ብለህ አታስብ፡፡
“ብዙ ጊዜ ለምኜዋለሁ፤ ተማጽኜዋለሁ፤ ማልጄዋለሁ፤ ሊታረቀኝ ግን አልቻለም” ብለህ አትንገረኝ፡፡ እስክትታረቀው ድረስ በፍጹም አታቁም፡፡ ጌታችን ሲናገር፡- “መባህን ትተህ ኺድ፤ ወንድምህንም ለምነው” አይደለምና፡፡ ያለው፡- “ኺድ፤ ታረቅ” ነው (ማቴ.5፡24)፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ለምነኸው ቢኾንም እስክታሳምነው ድረስ ግን ይህን ማድረግህን አታቋርጥ፡፡ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት ይለምነናል፤ እኛ ግን አንሰማውም፡፡ ኾኖም [አልሰሙኝም ብሎ] መለመኑን አላቋረጠም፡፡ ታዲያ አንተ ባልንጀራህን ለመለመን ትታጀራለህን? እንዲህ የምታደርግ ከኾነስ ልትድን የምትችለው እንዴት ነው?

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount