Saturday, May 2, 2015

ለክርስትና ሃይማኖት ግድ ያለው ሰው ኹሉ ሊያነበው የሚገባ መጽሐፍ!



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የተዘጋጀውና “መድሎተ ጽድቅ (የእውነት ሚዛን)” የተሰኘው ድንቅ መጽሐፍ በገበያ ላይ ዋለ፡፡
ይኽ መጽሐፍ ራሳቸውን “ተሐድሶ” ብለው የሚጠሩት አካላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ትምህርትን በተመለከተ በሐሰትና በስሕተት ላሠራጯቸው የስሕተት ትምህርቶች መልስ የሚሰጥ ድንቅ መጽሐፍ ሲኾን በአንጻሩም መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ የኾነው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርት በጥልቀትና በስፋት የቀረበበት መጽሐፍ ነው፡፡ በውስጡም፡-

Thursday, April 30, 2015

ስለ ጌጠኛ ልብስ

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ዕርቃናችንን የምንሸፍንበት ልብስ ብቻ ልንለብስ ይገባናል፡፡ ብዙ ወርቅን ብናደርግ ምንድነው ትርጉሙ? ብዙ ወርቅን ማድረግ በተውኔት ቤት ነው፤ ተዋንያን ብዙ ተመልካችን ለማግኘት ያደርጉታልና፡፡ ጌጠኛ ልብስ መልበስ የአመንዝራ ሴቶች ግብር ነው፤ ብዙ ወንዶች ይመለከቷቸው ዘንድ ይኽን ያደርጋሉና፡፡ እነዚኽን ማድረግ ልታይ ልታይ ለሚሉ ሰዎች ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የምትሻ ሴት ግን ይኽን ጌጥ ማድረግ አትፈልግም፡፡ ራሷን የምታስጌጠው በሌላ መንገድ ነው፡፡ እናንተም ይኽን ጌጥ ማድረግ የምትፈልጉ ከኾነ ማድረግ ትችላላችኁ፡፡ ተውኔት ቤትን የምትሹ ከኾነም ወርቀ ዘቦአችኁን የምታደርጉበት ሌላ ተውኔት ቤት አለላችኁ፡፡ ያ ተውኔት ቤትስ ምንድነው? መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ተመልካቾቹ ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ ይኽን የምናገረው በገዳም ለሚኖሩት መኖኮሳይያት ብቻ አይደለም፤ በማዕከለ ዓለም ለሚኖሩትም ኹሉ ጭምር እንጂ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ የተባለ ኹሉ የራሱ ተውኔት ቤት አለው፡፡ ስለዚኽ ተመልካቾቻችንን ደስ ለማሰኘት ራሳችንን ደኅና አድርገን እናጊጥ ብዬ እማልዳችኋለኁ፡፡ ለመድረኩ የሚመጥን ልብስን እንልበስ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! አንዲት ሴሰኛ ሴት ተውኔት ለመሥራት ብላ ብዙ ወርቋን አወላልቃ፣ ቄንጠኛ መጎናጸፍያዋን ጥላ፣ በሳቅ በስላቅ ሳይኾን ቁም ነገርን ይዛ፣ ተርታ ልብስን ለብሳ ወደ መድረኩ ብትወጣና ሃይማኖታዊ ንግግርን ብትናገር፣ ስለ ንጽሕና ስለ ቅድስና ብትናገር፣ ሌላ ክፉ ንግግርም ባትጨምር በተውኔት ቤቱ የሞላው ሰው አይነሣምን? ተመልካቹ ኹሉ የሚበተን አይደለምን? ሰይጣን የሰበሰበው ተመልካቹ የማይፈልገውን ነገር ይዛ ስለ መጣች ኹሉም የሚሳለቅባትና እንደ ትልቅ አጀንዳ የሚወራላት አይደለምን? አንተም በብዙ ወርቅ፣ በጌጠኛ ልብስ ተሸላልመኽ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ቅዱሳን መላእክት አስወጥተው ይሰዱኻል፡፡ ምክንያቱም በመንግሥተ ሰማያት የሚያስፈልገው ልብስ እንደዚኽ ዓይነት አይደለም፤ ሌላ ነው እንጂ፡፡ “ርሱስ ምን ዓይነት ነው?” ትለኝ እንደኾነም “ነፍስን በትሩፋት ማስጌጥ ነው” ብዬ እመልስልኻለኁ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት፡- “ልብሷ የወርቅ መጐናጸፍያ ነው” ያለውም ይኽንኑ ነው እንጂ በዚኽ ምድር የምንለብሰው ልብሳችንን ፀዓዳና አንጸባራቂ ስለ መኾን አይደለም /መዝ.45፡13/፡፡ ምክንያቱም “ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ኹሉ ክብሯ ነው” እንዳለ በዚያ (በመንግሥተ ሰማያት) መራሔ ተውኔቷ ርሷ ናት፡፡ እኅቴ ሆይ! ራስሽን መሸላለም ብትፈልጊ እንዲኽ አጊጪ፡፡ ከዚያም ከምረረ ገሃነም ትድኛለሽ፡፡ ባልሽንም ከማዘን ከመቆርቆር ትታደጊዋለሽ፡፡

Tuesday, April 28, 2015

የጉባኤ ጥሪ ከዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት

“ተዋሕዶ ሃይማኖታችን፣ ቤተ ክርስቲያን እናታችን” በማለታቸው በዓለማቀፉ አሸባሪ ቡድን በአይሲስ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ለማሰብ የመንበረ መንግሥት (ግቢ) ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ሚያዝያ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤ አዘጋጅቷል፡፡ በዕለቱ “ሰማዕትነት በዘመናችን” በሚል ዐቢይ ርእስ የምክክር ጉባኤ የሚደረግ ሲኾን ሚያዝያ 20፣ 21፣ እና 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከቀኑ 12፡00 ሰዓት ዠምሮ የጸሎት መርሐ ግብር ይካሔዳል፡፡

የመስቀሉ ሕዝቦች

      (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 በቅርቡ አይሲስ  የተባለው “ሃይማኖታዊ” ድርጅት “ክርስቲያን መግደል ገነት ያስገባል ፤ አላህ ደማቸውን እያየ ደስ ይለዋል” በሚል እንኳን መንፈሳዊነት ሰብአዊነት በጎደለው ፍፁም ሰይጣናዊ ትምህርት መነሻ በማድረግ ምንም የማያውቁትን ምስኪኖች በጭካኔ ግማሹን በተማሩት ትምህርት እንደበግ እያረዱ ግማሹን ደግሞ በጥይት እያርከፈከፉ ፈጅተዋቸዋል፡፡ በዚህም የኦርቶዶክሳውያን ልብ ፍፁም አዝኗል፤ አልቅሷል፡፡
ይሁን እንጂ ‹‹ መሳ ፲፬፡ ፰ - ፲፬ ከበላተኛው መብልን የሚያወጣ ››ጌታ ከእነዚህ አረመኔዎች አንድ አስደናቂ ቃል አሰምቶናል፡፡ ይኸውም እነዚህ አረመኔዎች ምስኪኖቹን ኦርቶዶክሳውያን ከማረዳቸው በፊት ሁሉንም በወል የጠሩበት ስም ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› የሚል ነው፡፡ መጽሐፍ  በ‹‹ዮሐ ፲፩ ፤ ፵፱ በዚያችም አመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው ‹ እናንተስ ምንም አታውቁም ፤ ምንም አትመክሩም ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ  ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናልና ›፡፡ ይህንም ከልቡ የተናገረ አይደለም ፤ ነገር ግን በዚያች አመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ፡፡››  እንደሚል ቀያፋን ክርስቶስ ለሰው ዘር በሙሉ በፈቃዱ ይሞት ዘንድ እንዳለው ትንቢት ይናገር ዘንድ ያደረገ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፤ ዛሬም እነዚህን አረመኔዎች አፋቸውን ከፍቶ ፊታቸውን ጸፍቶ ስለ ኦርቶዶክሳውያን ያስመሰከራቸው ቃል እንጂ ወደው አስበው የተናገሩት አይደለም፡፡ ለዚህም አንዳንድ ማሳያዎችን ላቅርብ፡፡

FeedBurner FeedCount