በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የአቡነ ቴዎፍሎስ ዝክረ-ሥምዕ በቤተ ክህነቱም በአዲሱ ትውልድም ዘንድ እየተዘነጋ ሄደ፡፡እኛ ስንዘነጋው ታሪካቸው በቆናጽላን (ተሐድሶዎች) እንዳልሆነ-እንዳልሆነ ተተረከ፡፡የአቡነ ቴዎፍሎስን በመሥዋዕትነት የከበረ ታሪክ የቤ/ክ ታሪክ አድርጎ ለማየት ፍላጎት ጠፋ፤ሰቆቃቸው የሚዲያ ሽፋን ተነፈገ፡፡እንዲያ ተሰማኝ!ይሕን ሁሉ ችለን ሕመማችንን እንዳናስታምም ወዲህ ከቤተ ክህነት፣ወዲያ ከአብዮታውያን ወገን ያሉ ትሩፋን አበው ጭራሽ አጽመ-ቴዎፍሎስን በግፍ በወደቀበት እንበለ-ርኅራኄ አነወሩ፡፡ሲሻቸው ለቀ.ኃ.ሥ ተቆርቋሪ መስለው፣ሲሻቸው የሲሶ ግዛትን ተረክ ከለላ በማድረግ ከ2 ወገን በሚወረወር የብዕር ፍላጻ መቃብሩን እየፈለሱ በወደቀበት አለሳርፍ አሉት፡፡መንበሩን በግፍ ከለቀቀ 40 ዓመት የደፈነው ግፉዕ እረፍት አጣ፡፡ አላስተኛ አሉት፡፡ዘለግ ያለችውና መቼቷ ከ1953-1971 ዓ.ም የሆነው የዚህች ክታብ ‹ምክንያተ-ጽሕፈት› ይኸው ነው--ሕማሙ፡፡የሚከተሉት አርእስት ለነዚህ ዐፅመ-ቴዎፍሎስን እንቅልፍ ለሚነሱ ልብ ሰባሪ ከሳሾች ‹‹እናንት የዛሬ ሕያዋን!ስለ ጉልበታችሁ አምላክ፤ሟች ሞቱን ይሙትበት፤ዐፅሙን ሰላም አትንሱ!›› ለማለት ያህል ከማስረጃ ጋር ተከረተሱ፡-
1. የሲሶ ግዛት ተረክ …‹‹ሲሶ ግዛት›› ወይስ ‹‹የቶፋ ሥርዓት››?!
2. አብዮታዊ ኢ-አማኒነትና የአቡነ ቴዎፍሎስ ምዕዳን!
3. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ… ቅድመ-ሞት፣ጊዜ-ሞት፣ድኅረ-ሞት...ሞትህ ደጅ አደረ!
4. ዝክረ-ቴዎፍሎስ በአፈ-ጳጳሳት ወሊቃውንት!
የሚሉ አርእስትን መራኅያን አድርጌ በተቻለኝ መጠን ስሜቴን ገትቼ (እንዲያው መግታቱ ከሆነልኝ) የመዛግብቱን ሀቅ ለማሳየት እሞክራለሁ፤ለዚህም የአምላከ ግፉዐን ረድኤትና ጥበቃ እንደማይለየኝ አምናለሁ፡፡