በአማን ነጸረ እንደ ጻፈው
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 07 ቀን፣
2010 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን!
ጥሎብኝ፣ ክርስቲያን ወንድሞቼ ስለ ቁራን በተቃርኖ ሲተረጉሙ መስማት ይጨንቀኛል፡፡ በራሴ ደርሶ ስላየሁት ይሆናል፡፡ የቤ/ክ ገድላትና ድርሳናት በማያምኑባቸው ሰዎች ሲተረጎሙ በአማኝ ዕዝነ ልቡና እያዳመጥኩ ብዙ ጊዜ ቅር ይለኛል፡፡ የባለቤትነትና የማንነት ስሜት በሌለህ እምነት ውስጥ ገብተህ ስትተረጉም እንደ ምዕመን ሳይሆን እንደ ፈላስፋ ሁሉን ነገር በአመክንዮ እየፈታህ ትገጥምና ጭርሱን እምነት የሚለውን ከአመክንዮ (ሎጂክ) በላይ የሆነ አስተሳሰብ ትዘነጋለህ፡፡ ያን ጊዜ መዘንጠል ይመጣል፡፡ ያለ አነባበቡ፣ ተነሺና ወዳቂ ሳይለይ የሚያነብ ሰው በድፍረት ንባቡን ሲሾፍረው ‹‹ኧረረረረረ ዘነጥልከው!›› ይላሉ የቤ/ክ አስነባቢዎች፡፡ ሰው የማያምነበትን ሲተረጉም ደግሞ ዝንጠላ የማያመልጠው ግድግዳ ይሆንበታል፡፡ ጥሎብኝ፣ ከዚህ ግድግዳ መላተም አልወድም፡፡