Thursday, August 17, 2017

“እስክመጣ ድረስ በማንበብ ተጠንቀቅ” (1ኛ ጢሞ.4፡13)፡፡



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እንደ መንደርደሪያ
ኃይለ ቃሉን የተናገረው በመንፈሳዊው ትምህርት ከሕግ መምህሩ ከገማልያል፣ በዚህ ዓለም ትምህርት ደግሞ በዘመኑ እጅግ ታዋቂ ከነበረው የተርሴስ ዩኒቨርሲቲ በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ ነው፡፡ የተናገረው ደግሞ በመንፈስ ለወለደው ልጁ ለሊቀ ጳጳሱ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ፡- “እስክመጣ ድረስ በማንበብ ተጠንቀቅ፤ በማንበብ ተወስነህ ኑር” በማለት መንፈሳውያን መጻሕፍትን እንዲያነብ ሲመክረውም ምክንያቱን ነግሮታል፤ እንዲህ ሲል፡- “ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ” (1ኛ ጢሞ.4፡16)፡፡
ስለዚህ መንፈሳዊ ንባብ ማለት ራሳችንንም የሚሰሙንንም ለማዳን - አስተውሉ! ለማዳን - መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ የአበው ድርሳናትን፣ ትርጓሜያትን፣ ምክሮችን፣ ገድሎችን፣ ታሪኮችን ማንበብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የማንበብ ግቡ እኛ ራሳችን እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እንድናድግ ሌሎችንም ወደዚህ ምንድግና እንዲመጡ ማድረግ ነው ማለት ነው፡፡ ንባብ ብቻ ሳይኾን የማንኛውም መንፈሳዊ ግብር ዓላማም ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትና አንድነት መፍጠር ነው፡፡
ከላይ ባነሣነው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል እንደምንመለከተው አንድ ኦርቶዶክሳዊ ኹልጊዜ በመደበኛነት ሊያነብ እንደሚገባው ያስረዳል፡፡ ጢሞቴዎስ ጳጳስ ነው፡፡ ቢኾንም ግን ማንበብ - ያውም ኹልጊዜ - መጻሕፍትን መመልከት እንዳለበት ተመከረ! ቅዱስ ጢሞቴዎስ ከሴት አያቱና ከእናቱ ከልጅነቱ አንሥቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲያነብ ያደገ ነው (2ኛ ጢሞ.3፡14-15)፡፡ አሁንም ቅዱስ ጳውሎስ ተቀብሎ ይበቃሃል ሳይኾን “በማንበብ ተጠንቀቅ” አለው፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ብዙ አበው ወእማት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የምታስተምረን እነዚህን ቅዱሳን አበው ወእማት በሕይወታቸው፣ በትምህርታቸው እንድንመስላቸው እንጂ እንዲሁ እንድንጠቅሳቸው፣ ወይም ጽሑፋቸውን እንድናጠና ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታበረታታን እነርሱ ክርስቶስን እንደመሰሉት እኛም እነርሱን እንድንመስል ነው፡፡
ከእነዚህ ቅዱሳን ኹሉ የመጀመሪያውን ስፍራ የምትይዘውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ካነሣነው ርእሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እጅግ አንባቢ እንደ ነበረች ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል፡፡ የሉቃስ ወንጌል 1፡47-55 ያለውን ኃይለ ቃል ብናነብ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዕውቀቷ እንደ ምን ጥልቅና ምጡቅ እንደ ነበረ መገንዘብ እንችላለን፡፡
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ በአራተኛው መ.ክ.ዘ. የነበሩ አባቶች ለምሳሌ እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሦስቱም የቀጰዶቅያ አባቶች፣ እነ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ መጻሕፍትን ዕለት ዕለት በማንበብ ተጠቃሾቹ መኾናቸውን እናስተውላለን፡፡ ከኢትዮጵያ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን፣ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ መምህር ኤስድሮስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እንዲያውም መምህር ኤስድሮስ እስከ ሦስት መቶ መጻሕፍት እንዳነበቡ የታወቀ ነው፡፡
እነዚህ ኹሉ ቅዱሳን ከተለያየ አከባቢ፣ ከተለያየ ባሕል፣ ከተለያየ ቤተ ሰብእ የተገኙ ቢኾኑም ቅሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ግን አለ፡፡ እንደየአገራቸው በዚያ ዘመን ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ለምሳሌ ፍልስፍናን፣ ሥነ ከዋክብትን፣ ሒሳብን፣ ፊዚክስን፣ እና ይህን የመሳሰለውን የተማሩ ቢኾኑም መንፈሳውያን መጻሕፍትን በማንበብ ረገድ ግን አንድ ናቸው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ክርስትናው ከተመለሰ በኋላ ገዳም ሲሔድ ይዞት የሔደው መጽሐፍ ቅዱስን ነበር፡፡ ሌሎችም አባቶች ለመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ዛሬ እንዲህ ስማቸው ገንኖ እንዲሰማ ያደረጋቸው መፍቀሪያነ መጻሕፍት ስለ ነበሩ ነው፡፡ የሕይወታቸው ምሥጢር መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፡፡ የሚጸልዩት መጽሐፍ ቅዱስን ነበር፤ ያውም በቃላቸው አጥንተዉት! በተለይ መዝሙረ ዳዊት እጅግ የተወደደ የጸሎት መጽሐፋቸው ነው፡፡
እነዚህ ቅዱሳን አባቶች ለመጻሕፍት የነበራቸው አመለካከት በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ እንደ እነርሱ እያንዳንዱ ምእመን በሚገባው ቋንቋ መጻሕፍት ማንበብ አለበት፡፡ በሔዱበት አገር ፊደል ላለው በፊደሉ፣ ፊደል ለሌለው ደግሞ ፊደል ቀርጸው አስቀድመው ማንበብ እንዲችል ያስተምሩት የነበረውም ለዚህ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ደረጃ ያለውን ስንመለከተውም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ከፊደላችንና ከቋንቋችን አንጻር የአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አስተዋጽኦ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ታሪክ በጻፉበት መጽሐፋቸው ላይ ቤተ ክርስቲያን ለአገር ምን እንዳበረከተች ሲገልጹ፡- “ሙሉ ትምህርት፣ ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ፣ ሥነ ጽሑፍ ከነጠባዩ ከነሙያው” ያሉትም ይህን ፍንትው አድርጎ የሚያስረዳን ነው፡፡
ነገር ግን ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ቤተ ክርስቲያን ይህን ያደረገችው የራሳችን ፊደል አለን፤ የራሳችን ቋንቋ አለን ብለን እንዲሁ እንድንኩራራ ሳይኾን እንድናነብ ነው - እንድናነብ!!!
ለመኾኑ እግዚአብሔር ለምን መጻሕፍትን ሰጠ?
ይህን በማስመልከት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስ ወንጌልን በተረጎመበት የመጀመሪያው ድርሳኑ ላይ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “ከእኛ ባሕርይ ጋር ይስማማ የነበረው የተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር አልነበረም፡፡ ከእኛ ጥንተ ተፈጥሮ ጋር ይስማማ የነበረው ንጽሐ ሕይወትን ገንዘብ ብናደርግ፣ ከመጻሕፍት ይልቅ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ራሱ ነፍሳችንን ቢመራት፣ መጻሕፍት ቀለም ተበጥብጦ ብራና ተዳምጦ እንደሚጻፉ ኹሉ መንፈሰ እግዚአብሔር በልቡናችን ሠሌዳነት ቃሉን ጽፎብን ብናነበው ደግሞም ብናደምጠው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ጸጋ ከእኛ እንዲርቅ አድርገነዋል፡፡ አድርገነዋልና ኹለተኛውን አማራጭ እንጠቀም ዘንድ ኑ፡፡ አዎ! ከኹለተኛው ይልቅ የመጀመሪያው አማራጭ የተሻለ ነበር፡፡ በዚያ እግዚአብሔር በቃልም በገቢርም ራሱን ይገልጥልን ነበርና፡፡ እግዚአብሔር ለኖኅ፣ ለአብርሃምና ለልጆቹ፣ ለኢዮብ፣ ለሙሴም ይገለጥ የነበረው በጽሑፍ አይደለም፡፡ ንጽሐ ልቡናቸውን ተመልክቶ ራሱን በራሱ ይገልጥላቸው ነበር እንጂ፡፡ ሕዝበ እስራኤል በክፋት ዐዘቅት ከወደቁ ወዲያ ግን ትእዛዘቱና ተግሣጻቱ በብራና እና በድንጋይ ጽላት ተጽፈው ተሰጡ፡፡”
የሚያሳዝነው ግን ይህ የኾነው በዘመነ ብሉይ ብቻ አይደለም፤ በዘመነ ሐዲስም ጭምር እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ለሐዋርያት አንዳች የተጻፈ ነገር አልሰጣቸውምና፡፡ ከዚያ ይልቅ “የነገርኋችሁን ኹሉ ያሳስባችኋል” በማለት የሚያስታውሳቸውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጣቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው እንጂ (ዮሐ.14፡26)፡፡”
“በርግጥም ይህ በእጅጉ ይሻል ነበር፡፡ ነቢያቱም ሐዋርያቱም ይህን በማስመልከት እንደ አንድ ልብ መስካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንዲህ ሲሉ መስክረዋል፡- “እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እኾናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይኾኑኛል” (ኤር.31፡31-33፣ ዕብ.8፡8-11)፤ “ልጆችሽም ኹሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይኾናሉ” (ኢሳ.54፡13፣ ዮሐ.6፡45)፡፡ ብጹዕ የሚኾን ጳውሎስም ከኹለቱ የትኛው እንደሚልቅ ሲያስተምር፡- “ሥጋ በኾነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ” አለ (2ኛ ቆሮ.3፡3)፡፡ በጊዜ ሒደት ግን አንዳንዶች በመሠረታዊው ትምህርተ ክርስትና ሌሎችም በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው ማለትም በምግባራቸው፥ ከእውነት ፈቀቅ ማለት ጀመሩ፡፡ እነዚህ ከእውነት ወደ ሐሰት፣ ከጣባቢቱ ወደ ሰፊይቱ መንገድ ፈቀቅ ያሉትን ለመመለስና ሌሎችም ወደዚያ እንዳይሔዱ ይህን ያስታውስ ዘንድ ቃሉ በጽሑፍ ይቀመጥ ዘንድ አስፈለገ፡፡”
ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት የበደላችንና የድካማችን ውጤቶች ናቸው፡፡ የተጻፉትም ይህ ድካማችንን ለመርዳት ነው፡፡ ዓላማቸው እኛ እንድንድንበት ብቻ ነው፡፡ እንደ ታሪክ ጸሐፊዎች፣ እንደ ሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች፣ እንደ አርኪኦሎጂስቶች እንዲሁ እንድናጠናው አይደለም፤ እንደ መናፍቃኑ እንድንከራከርበት አይደለም፤ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው እንድንድንበት ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን አባቶች ደጋግመው የሚጠቅሰት የቅዱስ ጳውሎስ አሳብ አለች፡፡ እርሷም፡- “እኛን… ሊገሥፀን ተጻፈ” የምትል ናት (1ኛ ቆሮ.10፡11)፡፡
እንዲህም በመኾኑ ኦርቶዶክሳውያን አበው፥ ምእመናን መጻሕፍትን እንዲያነቡ ዘወትር ይቀሰቅሷቸው፤ ያነሳሷቸው ነበር፡፡ በዘመናቸው በነበሩት ምእመናን አንጻርም እኛን ዘወትር ልናነብ እንደሚገባን መክረውናል፡፡ ለምሳሌ፡- አባ ሄሮኒመስ፡- “ስንጸልይ እግዚአብሔርን እናናግረዋለን፤ ስናነብ ደግሞ እግዚአብሔር ያናግረናል” ብሏል፡፡ ዳግመኛም ይህ አባ ሄሮኒመስ በንባብ “ርኩሳት ሕሊናት” እንደሚወገዱ በደቀ መዝሙሩ አንጻር ርኵሳት ሕሊናትን ለማስወገድ ንባብን ልንወድ እንደሚገባን ነግሮናል፡፡
መጻሕፍት ስናነብ ከጸሐፊዎቻቸው ጋር ፊት ለፊት እንደ መነጋገር ነው፡፡ ለምሳሌ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ የእነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ የእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ የእነ ቅዱስ ያሬድ መጻሕፍትን ስናነብ ከእነዚህ ቅዱሳን ጋር መነጋገር ነው፤ መጨዋወት ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን በመጻሕፍቶቻቸው አማካኝነት ወደ ቀናው መንገድ ይመሩናል፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን ጋር በፈለግነው ሰዓትና ቦታ መነጋገር፣ መመከር፣ መገሠጽ እንችላለን፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፡- “የቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያን ቅዱሳት መጻሕፍት ሳነብ መንፈሴና ሥጋዬ ብሩህ ይኾናል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የመንፈስ ቅዱስም እንዚራ እኾናለሁ፡፡ በኃይላተ እግዚአብሔር እገሠፃለሁ፤ መንፈሳዊ ምግብን አገኛለሁ፤ አዲስ ሰውም እኾናለሁ” ያለው ለዚህ ሕያው ምስክር ነው፡፡
ላለማንበብ የሚቀርቡ ምክንያቶች
ዘሪሁን አዲሱ የተባሉ ጸሐፊ አዲስ ፎርቹን ለተባለ በየሳምንቱ ለሚታተመው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ “A Nation of No Readers” በሚል ርእስ በጻፉት ጽሑፍ ላይ እንደ ገለጹት የአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የመልካም ባሕል ውድቀቶች የንባብ ውድቀታችን ውጤቶች ናቸው፡፡
እኚሁ ጸሐፊ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ ሰዎች የሚባሉት እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ ካርል ማርክስ፣ ሌሊን፣ ሊዮናርዶ ዳቬንቺ፣ ቶልስቶይ፣ ሼክስፒር፣ ቶማስ ኤዲሰን፣ አልበርት አንስታይን እንዲህ እንዲታወቁ ያደረጋቸውና የደረሱበትን ስኬት የደረሱት ትምህርት ቤት ገብተው ከተማሩት ይልቅ እጅግ አንባብያን እንደ ነበሩ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃም እነ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ አቤ ጉበኛ፣ ሐዲስ አለማየሁ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን፣ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ በዓሉ ግርማና ሌሎችም በዚህ የሚመደቡ ናቸው፡፡
የራሳችን ፊደል፣ የራሳችን ቋንቋ፣ እና የራሳችን ታሪክ ያለን ሕዝቦች ኾነን ሳለ ከሌሎች አፍሪካውያን ለምሳሌ ከጎረቤት ኬንያውያን አንጻር እንኳን ስንታይ በንባብ ልምዳችን ወደ ኋላ የቀረን ነን፡፡ ምንም እንኳን በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቈጠሩ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ቢኖሩንም ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ የሚያነቡት ግን በጣት የሚቈጠሩ ናቸው፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በተደረገው ጥናት ከኢትዮጵያ ሕዝብ 49.1 ከመቶ ወይም ኃምሳ ሚልዮን ሕዝብ ማንበብና መጻፍ የሚችል ሲኾን የንባብ ልምድ ያለው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እጅግ ተነቧል ተብሎ የሚታወቀው የእመጓ መጽሐፍ እንኳን እስከ አሁን ድረስ የታተመው ከሩብ ሚልዮን ቅጂ አያልፍም፡፡ ከኃምሳ ሚልዮን ማንበብና መጻፍ ከሚችለው ሕዝብ አንጻር እጅግ ጥቂት ነው፡፡
ከኦርቶዶክሳውያን አንጻር ስንመለከተውም የአብነት ትምህርት ስላለና ካለው የአስኳላ ትምህርት ጋር ተዳምሮ ከግማሽ በላይ ማንበብና መጻፍ የሚችል ነው ብለን መገመት እንችላለን፡፡ ይህም ኾኖ ግን የንባብ ልምድ ያለው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ከጥቂቶች በቀር አንድ ኦርቶዶክሳዊ መጽሐፍ ታትሞ በአማካኝ ከአምስት ሺሕ ቅጂ አያልፍም፡፡ ይህን አምስት ሺሕ ቅጂ ለመጨረስም እስከ አምስትና ስድስት ወራት ሊፈጅ ይችላል፡፡
ሌላውን ብንተወውና ግቢ ጉባኤያትን አልፈው የሚመረቁና የንባብ ጥቅምን ይረዳሉ ተብለው የሚታሰቡት ኦርቶዶክሳውያንም ከጥቂቶቹ በቀር ምን ያህል አንባብያን እንዳልኾኑ መገመት አያዳግትም፡፡
ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቀርቡ አያሌ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሉላዊነት ያመጣው የማኅበራዊ ድረ ገጾች፣ የስማርት ስልኮች፣ የኮምፒዩተር፣ የዜናና የፊልም ጣቢያ ቴሌቪዥኖች አብዮት የንባብ ልምዳችንን በተወሰነ መልኩ አቀጭጮት ይኾናል፡፡ እነዚህን እንደ ድንገቴ ነገር የመጡ ነገሮች እንዴት ማስተናገድ እንዳለብን አለመዘጋተቻን በእነርሱ እንድንጠመድ አድርገው “እንኳን ዘንቦብሽ” አድርገውብን ይኾናል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ምን ያህል ኢትዮጵያዊ ጋር ደርሰዋል ስንል ግምታችን እንዲያንስ ያደርገዋል፡፡ በመኾኑም የትምህርት ሥርዓታችን በትምህርት ቤት ለሚሰጠው ትምህርትና ለፈተና ለዚያውም በሽምደዳ ካልኾነ በቀር ከዚያ ውጪ የኾኑ መጻሕፍትን ወደ ማንበብ ከማሸጋገር አንጻር ደካማ እንደ ኾነ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡       
እንደ ግል አሳብ ስመለከተው የኢትዮጵያ ትንሣኤም ኾነ ውድቀት በኦርቶደክሳውያን እጅ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳውያን አንባብያንና ምሁራን ሲኖሩ አገሪቱ ወደ ቀደመ ልዕልናዋ ከዚያም በላይ መመለስ ትችላለች፡፡ እነ ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ራሳቸው መጻሕፍት ጽፈው፣ በየአጥቢያውም የንባብ ማእከላት እንዲከፈቱ ያደርጉ ነበር፡፡ አሁንም ትውልዱ ራሱንና ሌላውን የሚያድን እንዲኾን ከተፈለገ በኹሉም መስክ ያለን ኦርቶዶክሳውያን የንባብ ባሕላችን ከፍ ሊል ይገባል፡፡ የማያነብ ትውልድ በኹሉም ረገድ የተስተካከለ እይታ አይኖረውም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን እስከ መንግሥት ተቋማት ድረስ የምንመለከተው ብዙ ችግር የዚህ ያለማንበብ ውጤት ይመስለኛል፡፡ በመኾኑም አገሪቱ ከሚገጥማት ዘርፈ ብዙ ችግር አንጻር ብቻ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ከምንፍቅና እስከ ዓለማዊነት ተወስደው የሕይወት ግብ የኾነውን የዘለዓም ሕይወትን ረስተው መንጎዳቸው አይቀርም፡፡ ይህ አሁንም እያየነው ያለ ነገር ስለ ኾነ ብዙ ሐተታ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡
ለመኾኑ ግን ከላይ ከጠቀስነው በተጨማሪ መጻሕፍትን ላለማንበብ የሚቀርቡ ሌሎች ምክንያቶች ምን ምን ያካትታሉ? ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን መጠቆም ይቻላል፡-  
v  መጽሐፍ የለንም! መጽሐፍ የለንም የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡት ምክንያት ለመግዛት ዓቅም ስለማይኖራቸው ነው፡፡ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር ኃምሳ ብር፣ መቶ ብር አውጥቶ መጽሐፍ መግዛት እንደ ተቀዳሚ ፍላጎት አይታይም፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት የአንድ ዓመት ደመወዝ ነበር፡፡ ወደ አሁኑ ሰዓት አስልተን እናምጣው ብንልና አንድ ሰው ደመወዙ በአማካኝ ሦስት ሺሕ ብር ነው ብንል ይህ ሰው አንዲት መጽሐፍ ቅዱስን ለመግዛት ሠላሳ ስድስት ሺሕ ብር ያስፈልገው ነበር ማለት ነው፡፡ እንዲህም ኾኖ ግን እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ የሚለውን ሰው “አንተስ አታንበብ” አይሉትም ነበር፡፡ ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ ሊያነብ እንደሚገባው አብክረው ይመክሩት ነበር፡፡ አማራጮቹን ትንሽ ወረድ ብለን እንመለከታቸዋለን፡፡
v  ማንበብ አንችልም! እነዚህ ደግሞ “አልተማርንም፤ ማንበብም ኾነ መጻፍ አንችልም” የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡት ምክንያት ነው፡፡ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ብሎ ምክንያት ለሚያቀርብ ሰው “ይህ ምክንያት ነው፤ ሌላ ሰውም ቢኾን እንዲያነብላችሁ ማድረግ ትችላላችሁ” ይሉት ነበር፡፡
v  ሥራ ይበዛብኛል፤ መጽሐፍ ለማንበብ ጊዜ የለኝም! በተለይ ይህ የዘመኑ ነጽሮተ ዓለም ባመጣው ተጽዕኖ ምክንያት ብዙዎቻችን ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ በሥራ የተወጣጠርን ነን፡፡ በዚህ ውስጥ ኾኖ መጽሐፍ ማንበብ ጭንቅ ይኾንብናል፡፡
v  መነኮሳት አይደለንም! እነዚህ ደግሞ መጻሕፍት ማንበብ ለቀሳውስት ወይም ለመከነኮሳትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግሉ ብቻ እንደ ኾነ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች የሚያቀርቡት ምክንያት ነው፡፡  
v  የማነበው አይገባኝም! እነዚህ ሰዎች ከአፍአ ሲታዩ ማንበብ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን የሚያነቡት ስለማይገባቸው ማንበብ አይፈልጉም፡፡ ጠጠር ካለባቸው ይሰለቻሉ፤ ማዛጋት ይጀምራሉ፡፡ እገሌ እንደዚህ ኾነ፤ እገሌ እንዲህ አለ ሲባሉ ግን አሳድደው ያነባ’ሉ፡፡ ባይገባቸውም እንኳ እስኪ አስረዳኝ ብለው ነገሩን ለመረዳት ይሞክራሉ፤ ይወያያሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ለምሳሌ ትምህርተ ሃይማኖት ነክ ከኾነ ግን “የሚጻፉት መጻሕፍት ጋባዥ አይደሉም፡፡ ከቋንቋው ጀምሮ ከእኛ ሩቅ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ግንዛቤው ላላቸው እንጂ ለእኛ ለምእመናን የሚመጥኑ ስላልኾኑ ብናነበውም አይገባንም” ይላሉ፡፡ ይህ ምክንያት በተወሰነ መልኩ የራሱ የኾነ እውነታ አለው፡፡
v  ወደ ባለጸጐች ቤት ብንሔድና ብንመለከት ደግሞ በቤታቸው ውስጥ በጣም ብዙ ነገሮችን ለምሳሌ የልጆች ማጫወቻ፣ ጃኩዚ፣ ጂምናዝዬምና ሌሎችን በሥርዓት በሥርዓት ተሰናድቶ ማግኘት ብንችልም የመጻሕፍት መደርደሪያ (ሼልፍ) ማየት ግን እምብዛም ነው፡፡ አልፎ አልፎ ብናገኝም እንኳን ከጥቂቶቹ በቀር ለሀብታቸው መለኪያ እንጂ በዚያ የተደረደረው መጽሐፍ የሚያነቡት ኾነው አይደለም፡፡
ከዚህም በላይ የሚቀርቡ ሌሎች ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የመጻሕፍት ዋጋ ውድነት፣ መጻሕፍቱ የሚይዙት ቁምነገር አናሳነት፣ ምቹ የኾኑ የንባብ ቦታዎች አለመኖር፣ የመጻሕፍቱ ተደራሽነት ውስኑነት፣ ከዚህም በላይ ሌሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ በተጨማሪም ባሕላችን የቃል ባሕል ከመኾኑ የተነሣ “አሉ፤ ተባለ” የሚል እንጂ “አየሁ፤ አነበብኩ” የሚል ጥቂት ነው፡፡
ኹሉንም እንዘርዝር ቢባል አንድም ዝንጋዔ ማምጣት ይኾናል፤ አንድም ገና የንባብ ልምዳችንን እንዴት እናሳድግ እያልን መፍትሔውንም ሳይሰሙ እንዲሔዱና እንዲሰለቹ ላለማድረግ ወደ መፍትሔዎቹ ማለፍ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ እናስ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ማንበብ ያለበት እንዴት ነው?
እንዴት እናንብብ
1)  ከኹሉም አስቀድመን መገንዘብ የሚኖርብን ላለማንበብ ምክንያት ማቅረብ እንደሌለብን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እስክመጣ ድረስ በማንበብ ተጠንቀቅ” ያለው ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ብቻ ሳይኾን ለኹላችንም እንደ ኾነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው እነ ነቢዩ ዳንኤል እንደ እኛ ወጣት ነበሩ፤ እነ ሠለስቱ ደቂቅ እንደ እኛ ሕፃናት ነበሩ፤ እነ ዮሴፍ እንደ እኛ ስደተኞች ነበሩ፤ እነ ወንጌላዊው ሉቃስ ሐኪሞች ነበሩ፤ እነ ልድያ ነጋዴዎች ነበሩ፤ እነ ቆርነሌዎስ ወታደሮችና ፖሊሶች ነበሩ፤ እነ ጢሞቴዎስ “ሕመምተኞች” ነበሩ፡፡ እነዚህ ኹሉ ግን መጻሕፍትን ላለማንበብ ምክንያት አላቀረቡም፡፡ “ሥራ ይበዛብኛል - ቢዚ ነኝ” አላሉም፡፡ እኛም የምናነብበትን መንገድ ማመቻቸት እንጂ ላለማንበባችን ምክንያት ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ደጋግመን እንደ ተነጋገርነው መጻሕፍት ካለማንበባችን የተነሣ እጅግ የተወሳሰቡ ችግሮች በእኛ በግላችን ብሎም በቤተ ክርስቲያንና በአገር እየተከሰቱ ነው፡፡
2)  መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ማወቅ! አስቀድመን መሠረታዊ የኾኑ የዶግማና የቀኖና ትምህርቶችን ካወቅን በምናነባቸው መጻሕፍትም ኾነ በምንሰማቸው በምስል ወድምጽ የተዘጋጁ ሐሰተኛ ትምህርቶች አንወሰድም፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን ሌሎችም ተሳስተው እንዳይሔዱ፣ በአገሪቱ ላይ የሚከናወኑ ማናቸውም ነገሮች ኦርቶዶክሳዊ በኾነ መነጽር ስለምንመለከታቸው ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለአገሪቱ መጻኢ ኹኔታም የምናስብ የምንጨነቅ እንድንኾን ያደርገናል፡፡ በተለይ ይህ በእኛ ትውልድ እጅግ ገዝፎ የሚታይ ክፍተት ስለ ኾነ እጅግ ልናስብበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ትምህርትን ያልተገነዘቡ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ቤተ ክርስቲያን ጠበቆች አድርገው ማየት እየተለመደ መጥቷልና፡፡ ዳግመኛም የማነበው አይገባኝም ብሎ ንባብን መተው ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አልተማርነውም፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ያነበው የነበረው የትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ ፊልጶስ መጥቶ እስኪነግረውና እስኪያብራራለት ድረስ ያነብ ነበር እንጂ ዝም አላለም ነበር፡፡
3)  እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳትና ማንበብ! ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት የታነጸች ስለ ኾነች መጻሕፍትን ስናነብ እርሷ ከምታስተምረን ትምህርት የሚወጣ ጽሑፍ እንዳይኖር እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አተረጓጎም መረዳትና ማንበብ ግድ ይለናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በምልአት የተሰጠው ለእርሷ ስለ ኾነ የእግዚአብሔር አሳብ የሚገልጡ መጻሕፍትም ከእርሷ በላይ ማንም ይኹን ማን ሊተረጉመው አይችልም፡፡ ንዑድ ክቡር የሚኾን ጴጥሮስ፡- “ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም” ያለንም ይህንን ነው (2ኛ ጴጥ.1፡20)፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስም ይኹን፣ ማንኛውም መንፈሳዊውም ኾነ ያልኾነ መጽሐፍ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ጋር የማይቃረን መኾኑን በማስተዋል እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አተረጓጎን ማንበብና መረዳት ተገቢ ነው፡፡
4)  የግል ሕይወታችንን ማስተካከል! ቀደም ብለን እንደ ተነጋገርነው መጻሕፍትን ስናነብ የምንነጋገረው ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳን ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ጋር ለመነጋገር ልብን ንጹህ ማድረግ፣ የጸሎት ሕይወትን ከፍ ማድረግ ቀዳሚው ነገር ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት ወደ ቤተ ክርስቲያን፣ ወደ ሥርዓተ አምልኮው መጥለቅ ነውና፡፡ መግባት ነውና፡፡ እዚያ ውስጥ ሲገቡና የክርስቶስ አካል ሲኾኑ ደግሞ የክርስቶስን ልብ ማግኘት አይከብድም፡፡ የቅዱሳን አበው ልብ የምናገኘው እነርሱ የሌሉበት ስፍራ ጋር አይደለም፡፡ ያሉት ደግሞ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍትን ስናነብ መረዳት የምንችለው በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንጂ ከውጭ ኾነን እንዳልኾነ መገንዘቡ ተገቢ ነው፡፡
5)  የተጻፈው ለእኛ እንደ ኾነ አድርገን መረዳት! ቅዱሳን አበው የሰበኩአቸው ምእመናን እና እኛ በጣም የተለያየን ነን፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩት መናፍቃን እና በዚህ ዘመን ያሉት እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ የእነዚህ አበው ከላይ በተናገርነው መንገድ ልባቸውን ካገኘነው ለእኛ ዘመን በሚኾን መልኩ አድርገን መስበክ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን መጻሕፍት ስንመለከት መጽሐፍ ቅዱስን እርሱ ለነበረበት ዘመን ብቻ የተጻፈ ነው የሚያስመስለው፡፡ ይህም ማለት ምን ያህል ወደ ተግባር ያወርደው እንደነበር ነው የሚያስገነዝበው፡፡ ምን ያህል የክርስቶስን ልብ እንዳገኘው ነው የሚያስረዳው፡፡ ምን ያህል የቅዱስ ጳውሎስን አሳብ እንደ ተረዳው ነው የሚያሳየው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍን ስናነብ ወደ ራሳችን ማምጣት ተገቢ ነው፡፡
6)  አንድን መንፈሳዊ ጽሑፍ ስናነብ ሦስት ደረጃዎች እንዳሉት መረዳት! የመጀመሪያው ታሪካዊ ነው፤ የተደረገውን ድርጊት ብቻ ማወቅ ማት ነው፡፡ ኹለተኛው ደረጃ ግብረ ገብነታዊ መልእክቱ ነው፤ ለእኔ ብሎ ማጥናት ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ደረጃ ሥነ መለኮታዊ መልእክቱ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ደረጃችን ስለ ኾነ ዐቅማችን የትኛው ጋር ቢኾንም እንኳን ከአንዱ ወደ ሌላኛው የምንሸጋገረው ስናነብ ነው፡፡
መጀመሪያውኑስ ንባብን እንዴት እንልመድ?
·         የመጽሐፍ ጥቅምን መረዳት፡- በገጠር ሰይፍ የሚቀመጠው ከጣሪያ ሥር ነው፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ሲቀመጥ ታዲያ ቆሻሻ ሊይዝ ብሎ ሊዝግ ይችላል፡፡ ይህን የሚያውቅ ገበሬም ሰይፉን በየጊዜው እያወረደ ይወለውለዋል፤ ዘይት ይቀባዋል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሰይፍ የተባለው አእምሮ ዝገት በተባለ አለማንበብ ሊቆሽሽ ይችላል፡፡ መጻሕፍት ደግሞ ይህን ዝገት የሚያርቁ ዘይቶች ናቸው፡፡ ይህን ጥቅማቸው ካልተረዳን እነዚህን ዘይቶች ለማግኘት አንተጋም፡፡ መጻሕፍትን የማንበብ ጥቅሙን ካልተረዳነው ለማንበብ ጭንቅ ይኾንብናል፡፡ እግዚአብሔር ለምን መጻሕፍት እንደ ሰጠ ካልተረዳን አናነብም፡፡ መጻሕፍትን የማያውቁ ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንደሚስቱና ኃጢአት የተባለ ዲቃላ ልጅንም እንደሚወልዱ ግንዛቤው ካለን ግን ራሳችንንና ወንድማችንን ከዚህ ለመጠበቅ ስንል ማንበብ እንዳለብን እንረዳለን፡፡ ለማንበብ ተነሣሽነቱ ይኖረናል፡፡ የዘለዓለም ሕይወትን ከመስጠት አንጻር ብቻ ሳይኾን ከዚህ ዓለም ሕይወታችንም አንጻር ንባብ ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጤና አንጻር እንኳን ብናየው ማንበብ የመርሳት ችግርንና ጭንቀትን በመቀነስ ረገድ፣ የማስታወስ ችሎታንና የማሰብ አድማስን ከማስፋት አኳያ ዓይነተኛ መድኃኒት ነው፡፡ ዳግመኛም መጻሕፍት ማንበብ ለተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች የተሰጠ እንደ ኾነ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው፡- “ሚስትህ ታስቆጣሃለች፤ ልጅህ ያሳዝንሃል፤ ሠራተኛህ ያበሳጭሃል፤ ጠላትህ ያደባብሃል፤ ጓደኛህ ይቀናብሃል፤ ባልንጀራህ ይሰድብሃል፤ ድኽነቱ ያስጨንቅሃል፤ ገንዘብ ማጣቱ ያስተክዝሃል፤ ሀብት ያስታብሃል፡፡” እነዚህን ኹሉ ማስወገድ የምትችለው መጻሕፍትን በማንበብ በምታገኘው ብርታት ነው፡፡  
·         መጻሕፍትን ማግኘት፡- መጻሕፍት ሳያገኙ ማንበብ አይቻልምና፡፡ ስለዚህ በመግዛት፣ ወይም በመዋስ፣ ወይም ወደ ቤተ መጻሕፍት በመሔድ፣ ወይም በስልካችንም በላፕቶፓችንም በስስ ቅጂ (ፒዲኤፍ) የምናገኛቸውን በመጫን፣ ወይም በጡመራ መድረኮች የሚለጠፉትን በመከታተል ማንበብ እንችላለን፡፡ አንድ የ100 ብር መጽሐፍ ለመግዛት ዓቅም ባይኖረን በኃምሳ በር ከኹለት፣ በሃያ አምስት ብርም ከአራት ጓደኞቻችን ጋር ዕቁብ በመግባት ልንገዛው እንችላለን፡፡  
·         ጊዜና ቦታ መመደብ፡- ለመብል፣ ለመጠጥ፣ ለመኝታ፣ ለሥራ፣ ለሌላውም ጊዜና ቦታ እንደምንመድብ ኹሉ ለንባብም ጊዜና ቦታ መመደብ ተገቢ ነው፡፡ “በሳምንት ይኼን ይኼን አነባለሁ” ማለትን መልመድ ተገቢ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የታክሲ ተጠቃሚዎች ከኾንንና ከቤታችን ተነሥተን የሥራ ቦታችን ለመድረስ ሠላሳ ደቂቃ የሚፈጅብን ቢኾን በቀን ቢያን ለአንድ ሰዓት ያህል ማንበብ እንችላለን፡፡ በምዕራባውያን ዘንድ ይህ ልምድ እጅግ የዳበረ ከመኾኑ የተነሣ ጋዜጦችና መጽሔቶች በነጻ በመጓጓዣ ቦታዎች ይቀመጣሉ፡፡ ተሳፋሪዎችም እንደየፍላጎታቸው የሥራ ቦታቸው ወይም ቤታቸው እስኪደርሱ ድረስ እነዚህን ያነባሉ፡፡ አንብበውም በአግባቡ ለቀጣይ ተሳፋሪ በየፌርማታው አስቀምጠዉለት ይሔዳሉ፡፡ ስለዚህ ተነሣሽነቱ ይኑረን እንጂ ይህን ከራሳችን ነባራዊ ኹኔታ አንጻር አመቻችተን ልናዳብረው የምንችለው ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ስንመለከት ያነብ የነበረው በትራንስፖርት ውስጥ ኾኖ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚንስትር የነበረ ቢኾንም ሥራ ይበዛብኛል ብሎ ዐርፎ ሳይቀመጥ መጻሕፍትን ለማንበብ በተገኘው አጋጣሚ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስም ይህን ትጋቱን ተመልክቶ ፊልጶስን ልኮ አብራርቶለታል፡፡   
·         ከምንወደው፣ ከቀላልና ከአጭር መጽሐፍ መጀመር፡- እንዲህ ስናደርግ የምንወደው የመጽሐፍ፣ የጡመራ መድረክ፣ የመጽሔት፣ ወይም የጋዜጣ ዓይነት በመለየት ሊኾን ይችላል፡፡ ይህን በመለየት ረገድም ከንስሐ አባቶቻችን፣ ከሚያነቡ ጓደኞቻችንና አንባቢያን ከኾኑ የመጻሕፍት መደብር ባለቤቶች ምክር መጠየቅ እንችላለን፡፡ ረጃጅም ጽሑፍችን ለማንበብም ቀድመን አንሳነፍም፡፡
·         ከምንቀርባቸው ሰዎች፣ ከቤተ ሰብ ጋራ የመጻሕፍት ውይይት ማድረግ፡- በተለይ ይህ እጅግ በጣም ውጤታማ የንባብ ባሕልን የሚያስለምድ ዘዴ ነው፡፡ ምክንያቱም የመጽሐፉ ዋና ዋና ይዘት ከራሳችን ጋራ እያዋሐድን እንድናቀርበውና በተለያየ እይታም እንድንመለከተው እንዳንዘነጋውም የሚያደርገን ነው፡፡ ምናልባት ማንበብ የማይችል ሰው እንኳን ቢኾን ሌሎች ሰዎች እንዲያነቡለት ማድረግ ይቻላል፡፡ የምናውቃቸው ዐውነ ስዉራን ሌላ ሰው እንዲያነብላቸው የሚያደርጉት ጥረት ለእኛም ጥሩ ልምድ ሊኾነን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከቤተ ሰብ ውስጥ አንዱ እንዲያነብልን ማድረግ እንችላለን፡፡ በተለይ የሚያነቡልን ሕፃናት ቢኾኑ ደግሞ ጥቅሙ ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡
·         በአንድ መጽሐፍ ላይ የሚሰጡ ሒሶችን ማድመጥና ማንበብ፡- ይህም ያ የተሔሰውን መጽሐፍ ለማንበብ ያነሣሣናል፡፡ ሒሶች የትኛውን መጽሐፍ ማንበብ እንዳለብንም ጥሩ ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ “እንቶ ፈንቶ ናቸው፤ ቁም ነገር የላቸውም” ብለን በደፈናው ዘግተን ማንበብን ለተውን ይህን እንደ መፍትሔ መውሰድ ይቻላል፡፡
·         የመጻሕፍት ዐውደ ርእዮችን መሳተፍ፡- ለምሳሌ በአዲስ አበባ በዓመት አንዴ ቢኾንም “ንባብ ለሕይወት” ተብለው እንደሚዘጋጁት ዓይነት ዐውደ ርእዮችን ብንሳተፍ የምወዳቸው መጻሕፍትን ከማግኘትና እንድናነብም ከመጋበዝ አንጻር ከፍ ያለ ድርሻ አላቸው፡፡
·         የንባብ ጊዜያችንን የሚሻሙ የመገናኛ አውታሮችን ማየት መቀነስ፡- ለምሳሌ ለዜና፣ ለፊልም፣ ለማኅበራዊ ሚድያዎች የምናውለው ጊዜ ብንቀንስ ለንባብ ብቻ ሳይኾን ለሌላው መንፈሳዊ ሕይወታችንም ከሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ጊዜ መግዛት እንችላለን፡፡  
·         አንብበን ስንጨርስ ካነበብነው ጽሑፍ ተነሥተን ጸሎት ማድረግ! ለምሳሌ ዛሬ ያነበብነው የእመቤታችንን ጽንሰት የተመለከተ ነው እንበል፡፡ እመቤታችን በኃጢአት በፍትወት እንዳልተጸነሰች፣ ዓለም ኹሉ እርሷን ይጠብቅ እንደ ነበረ ስናነብ ቆይተን እንዲህ ብለን በመጸለይ ወደ ራሳችን ልናቀርበው እንችላለን፡- “ቅዱስ አባት ሆይ! ኢያቄምንና ሐናን እንደ ጎበኘሃቸው እኛንም በረድኤት በይቅርታ ጎብኘን፡፡ በነፍሷ ድንግል፣ በሥጋዋም ቅድስት ድንግልን እንደ ጸነሱ እኛም በልቡናችን ቅዱስ አሳብን ቅዱስ ምክርን እንድንጸንስ ብሎም እንድንወልድ እርዳን፡፡ በቃልህ ‘በዚያን ጊዜ ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው’ እንዳልክ ኃጢአትን አርግዘን ክፉ ግብርን ወልደን እሽርሩ ከማለት ጠብቀን፡፡ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን!” ይህም በንባብ ምን ያህል ጥቅም ማግኘት እንደምንችል፣ ለሌላ መንፈሳዊ ተግባርም እንደሚያነሣሣን መገንዘብ እንችላን ማለት ነው፡፡  
ማጠቃለያ
አባ ሄሮኒመስ እንደ ነገረን ስንጸልይ እግዚአብሔርን እናናግረዋለን፤ ስናነብ ደግሞ እግዚአብሔር እኛን ያናግረናል፡፡ ስንጸልይ ቅዱሳንን እናናግራቸዋለን፤ ጽሑፎቻቸውን ስናነብ ደግሞ ቅዱሳኑ እኛን ያናግሩናል፡፡ ታዲያ እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ ቅዱስ ቄርሎስ፣ እነ ቅዱስ ያሬድና እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እንዲያነጋግሩት ማይሻ ማን ጎስቋላ ሰው ነው? እግዚአብሔር እንዲያናግረው የማይፈልግ ማን ምስኪን ሰው ነው?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ በንባብ ተግተን ራሳችንም ሌሎችንም እናድን ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ኹሉ ቃል ኪዳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount