Monday, February 29, 2016

ቅዱስ ፖሊካርፐስ



በሥርጉተ ሥላሴ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 22 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ልጅነት
ቅዱስ ፖሊካርፐስ የተወለደው ከክርስቲያን ቤተሰቦች በ70 ዓ.ም. በጥንታዊቷ ሰምርኔስ ከተማ (ቱርክ ውስጥ የአሁኗ እዝሚር) ነው፡፡ ቤተሰቦቹን በልጅነቱ ስላጣ ካሊቶስ/ካሊስታ የተባለች ደግ ክርስቲያን አሳድጋዋለች፡፡ ከእርሷም በኋላ የሰምርኔስ ከተማ ጳጳስ ቡኩሎስ ወስዶ ትምህርተ ሃይማኖትን በሚገባ እያስተማረ አሳድጎታል:: ይህ ቅዱስ ቡኩሎስ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ስለነበር ቅዱስ ፖሊካርፐስ ዮሐንስ ወንጌላዊን እና ሌሎችንም ሐዋርያት የማግኘት ዕድል ነበረው:: ቅዱስ ቡኩሎስ ቅንዓቱንና ትጋቱን አይቶ ዲቁና ሾመው፤ ቀጥሎም ቅስናን ሾመውና የቅርብ ረዳቱ አደረገው:: ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ሐዋርያዊ ጉዞ በሚያደርግበት ወቅት አስከትሎት ይሄድ ነበር፤ ከሌሎች ሐዋርያት ረዘም ላለ ጊዜ በምድር ላይ ስለነበር ለብዙ ዓመታት የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ቅዱስ ቡኩሎስ ካረፈ በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ የሰምርኔስ ከተማ ጳጳስ አድርጎ ሹሞታል::

Wednesday, February 24, 2016

ትንቢተ ዮናስ - የመጨረሻው ክፍል



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ምዕራፍ አራት

ሰብአ ነነዌ ስለዳኑ በሰማያት ሐሴት ኾኗል፡፡ እግዚአብሔር ደስ ተሰኝቷል፡፡ መላእክት እርስ በእርሳቸው፡- “እንኳን ደስ ያለህ! እንኳን ደስ ያላችሁ! በአንዲት ቀን ብቻ መቶ ሀያ ሺሕ የነነዌ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ተመልሰዋልይባባላሉ፡፡ ዮናስ ግን ፈጽሞ አዝኗል፡፡ ከአፍአ (ከውጭ) ሲታይ ዮናስ አሕዛብ ስለዳኑ የተበሳጨ ይመስላል፤ ኾኖም ግን ደጋግመን እንደተናገርን ዮናስ እንዲህ የሚያዝነው ወገኖቹ እስራኤል ከእግዚአብሔር ኅብረት መለየታቸውን አይቶ ነው፡፡ ዮናስ በሕይወት ከመኖር ይልቅ ሞትን የሚመርጠው ወገኖቹን እስራኤልን እጅግ ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ ቅዱስ ጀሮም ነቢዩ ዮናስ ለምን እንዲህ ፈጽሞ እንዳዘነ ሲናገር፡- “ዮናስ እጅግ አዘነ፡፡ ኾኖም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ሰብአ ነነዌ ስለዳኑ አልነበረም፡፡ የአሕዛብ መዳን የወገኖቹ የእስራኤል መጥፋት መኾኑን ስላወቀ እንጂ፡፡ ከነቢያት ተለይቶ የወገኖቹን የእስራኤልን መጥፋት እንዲናገር በመመረጡ እንጂ፡፡ በመኾኑም ወገኖቹ እስራኤል ከሚሞቱ እርሱ ቢሞት ተመኘ፡፡ ይኸውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእስራኤል መጥፋት አይቶ እንዳለቀሰው ነው /ማቴ.2337/ ሐዋርያት በሥጋ የሚዛመድዋቸው ወገኖቻቸው ከክርስቶስ አንድነት ተለይተው በመቅረታቸው ስለ እነርሱ የተረገሙ እንዲኾኑ እንደጸለዩት ነው /ሮሜ.94-5/” ብሏል /St. Jerome, Commentary on the Book of Jonah, IV:1/፡፡

Monday, February 22, 2016

ትንቢተ ዮናስ - ክፍል ሦስት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ምዕራፍ ሦስት

ዓሣው ዮናስን በአንጻረ ነነዌ ተፋው፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደ መጀመርያው፡- “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ እኔ ከዚህ ቀደም አስተምር ብዬ እንደነገርኩህ አስተምራቸውአለው፡፡ ዮናስም መጀመርያ እንዳደረገው ከጌታ ፊት ለመሸሽ አልሞከረም፡፡ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ተነሥቶ ሄደ እንጂ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እስኪ የእግዚአብሔርን ፍቅር ቆም ብለን እናሰላስለው፡፡ ዮናስ ለወገኖቹ ለእስራኤል አዝኖ አልታዘዝ ብሎ ነበር፡፡ ባለመታዘዙ ምክንያትም ወደ ሌላ ኃጢአት ገብቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ይወዷል፡፡ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማሌላ ነቢይ ልላክአላለም፤ከእንግዲህ ወዲህ ዮናስን አልፈልገውምአላለም፡፡ እግዚአብሔር ዮናስን በቃል እንኳ የገሰጸው አይደለም፡፡ ዳግመኛምዮናስ ሆይ! ትእዛዜን ተላልፈህ የሸሸኸው ስለምንድነው?” አላለውም፡፡ በተግባር የደረሰበት ኹሉ በቂ ነውና፡፡ በመኾኑም አሁን ተጨማሪ የቃል ተግሳጽ አላስፈለገውም፡፡ ዳግመኛ በቃላት ቢገስጸው ዮናስ ምን ያክል ስሜቱ ሊጐዳ እንደሚችል ሰው ወዳጁ ጌታ ያውቃልና፡፡ እግዚአብሔር ስሜታችንን ምን ሊጐዳው እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል፤ በመኾኑም ይጠነቀቅልናል፡፡ ስሕተታችን ምን እንደኾነ በራሳችን አውቀን እንድንመለስ ኹኔታዎችን ያመቻችልናል እንጂ እየመላለሰ እንደ ሰው አይነዘንዘንም፡፡ ስሙ የተመሰገነ ይኹን! ወገኖቼ! ገና ስንጀምር እንደተናገርነው ይህቺ ከተማ ድሀ የሚበደልባት ጣዖት የሚመለክባት የሞት ከተማ ናት፡፡ ክፋትዋ ጽርሐ አርያም የደረሰ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ይወዳታል፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ያፈቅራታል፡፡ እግዚአብሔር የሚጠላው ፍጥረትስ ማን አለ? የቅዳሴ ማርያም ጸሐፊ አባ ሕርያቆስ እንደተናገረው እግዚአብሔር ያፈቅራል፤ እግዚአብሔር ባለሟል ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ዝቅ ብሎ እንደ ሰው ያናግራል፡፡ መልካም ስላገኘብን አይደለም፤ ባሕርዪው ፍቅር ስለኾነ እንዲሁ ያፈቅናል እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ይፈልገዋል፡፡ እግዚአብሔር ደካማውን ይፈልገዋል፡፡ እርሱ የሚጠላው ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛውን አይደለምና፡፡ እግዚአብሔር የሚጸየፈው የነነዌን ኃጢአት እንጂ የነነዌን ሰዎች አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሚጸየፈው እኛን አይደለም፤ ኃጢአታችንን እንጂ፡፡ አባት ልጁን እንዴት ይጠላል?

FeedBurner FeedCount