Pages

Monday, May 21, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የ13ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.2፡18-ፍጻሜ)!!

ወንጌላዊው “ስለዚህ አይሁድ መልሰው፡- ይህን ስለምታደርግ (የምንሸጠውን ስለምትገለባብጥ) ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት” በማለት ይቀጥላል /ቁ.18/። የሚገርም ነው! አይሁድ በዚህ ንግግራቸው፡- “ቤቱን የወንበዴዎች ዋሻ ማድረጋችን አግባብነት አለው፤ አንተ ይህን ቤት የአባቴ የጸሎት ቤት ነው ስትል ግን (ሎቱ ስብሐት) ሕግን ባታውቅ ነው፡፡ ከምድራውያን ነገሥታት ከሌዋውያን ካህናት ሳትሆን ይህን ስለምታደርግስ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ አቤት! ሰው በኃጢአት ሲደነዝዝ ለክፋቱም ምልክትን ይሻል፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሰነፎች፡- “አታጭሱ፤ አትቃሙ፤ አትጠጡ፤ በጾም ወራት ዓሣ አትብሉ… የሚል ጥቅስ የት አለ?” እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ ጌታም እዝነ ልቡናቸው ስለታወረ ለጊዜው አልገባቸውም እንጂ እንዲህ በማለት ምልክትን ይሠጣቸው ነበር፡- “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” /ቁ.19/።
 “ሁሉም ላይገባቸው (ደቀ መዛሙርቱም ጭምር) ለምን እንዲህ ማለት አስፈለገው?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስላችኋለን፡- ጌታ እንዲህ የሚያደርገው እርሱ ሁሉንም አዋቂ መሆኑን እንዲገነዘቡ ነው /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 23/፡፡ በእርግጥም ለጊዜው ግራ ቢገባቸውም (ደቀ መዛሙርቱ ተጠቅመው እነርሱ አልተጠቀሙበትም እንጂ) ከገደሉት በኋላ  ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶአቸዋል /ማቴ.26፡61፣ አርጌንስ Commentary on the Gospel of John 10:251-52/፡፡
እዚህ ጋር ሌላ የምንረዳው ቁም ነገር አለ፡፡ ይኸውም አንዳንድ መንፍቃን እንደሚሳደቡት ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ አለመሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ቃሉ እንደሚያስረዳን ነፍሱን የማኖርም የማንሣትም ሥልጣን እንዳለው “በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” እያለ በግልጽ እየነገረን ነውና /ዮሐ.10፡18፣ Hilary of Poitiers, On The Trinity 9:12/፡፡
 አሁንም እነዚህ አይሁድ ጌታ በሚናገራቸው ነገር የባሰ ግራ ተጋብተው፡- “ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታንጸዋለህን?” በማለት ይጠይቁታል /ቁ.20/። በሰሎሞን የታነጸው ቤተ መቅደስ የመጀመርያው ቤተ መቅደስ በ20 ዓመት ያለቀ ነው፡፡ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው በዘሩባቤል ዘመነ መንግሥት የተሠራው ግን አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶባቸዋል /ዕዝራ.6፡15/፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ሁሉም ባይገባቸውም ጌታ ማኅደር ስለሚባል ሰውነቱ እንጂ ስለዚያ ቤተ መቅደስ እየተናገረ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው እንኳን ወንጌሉን ጌታ ከተነሣ በኋላ ስለሚጽፈው የክርስቶስ ንግግር ምን ማለት እንደሆነ ሲያስረዳ፡- “እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር” የሚለው /ቁ.21/፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ጌታ ስለ ሰውነቱ እየተናገረ መሆኑን ለምን በግልጽ አልተናገረም?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም “ለጊዜው የሚነግራቸውን በቀላሉ ላይቀበሉት ስለሚችሉ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ተደናገሩት ለዚሁ ነው” ብለን እንመልስለታለን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/።
ስለዚህ ጌታ “ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ያላቸው ማኅደር ስለሚባለው ሰውነቱ እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ማለትም ይነሣል ብለው የተናገሩትን ነብያትንና ኢየሱስ ራሱ አነሣዋለሁ ብሎ የተናገረውን ቃል አመኑ” /ቁ.22/። አዎ! አስቀድመን እንዳልነው፡- “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱትና አባቴ ያነሣዋል” ሳይሆን “እኔ አነሣዋለሁ” እንዳላቸው አሰቡ፡፡ አባቱ አስነሣው ቢባልም የሚጣላ ነገር አይደለም፡፡ እርሱና አብ አንድ ናቸውና፡፡ ስለዚህ እንደተናገረው ተነሣ፤ እነርሱም አመኑበት፤ ሕይወትም ሆናቸው /ሮሜ.1፡4፣ቅ.አምብሮስ Tractes on the Gospel of John 10:11/፡፡
ወንጌላዊው ይቀጥልና፡- “ኢየሱስ በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ” ይለናል /ቁ.23/፡፡ “የትኛውን ምልክት?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ በቤተመቅደስ የነበሩትን ሻጮች ማስወጣቱን እንደ ምልክት አይቶት ሳይሆን ሌላ ያደረጋቸው ነገር ግን በዚሁ መጽሐፍ ያልተጻፉ ተአምራት እንዳደረገ ያስገነዝበናል /አርጌንስ Commentary on the Gospel of John 10:319/፡፡
“ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር” /ቁ.24/። “ለምን?” ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡ ጌታ እነዚህን ሰዎች ያልተማመነባቸው ከልባቸው አምነውበት ሳይሆን ባሳያቸው ተአምራት ለጊዜው በስሜት ተነድተው “አምነናል” እንዳሉ ያውቃልና፤ ልባቸው ብዙ አፈር የሌለበት ጥልቅ መሬትም እንደሌለው ጭንጫ እንደሆነ ያውቃልና /ማቴ.13፡5/፡፡
 አዎ! እርሱ ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡ “እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ” የሚያውቅ አምላክ ነው /ቁ.25፣ መዝ.32፡15/፤ ጠቢቡ እንዳለው “እርሱ ብቻ የሰውን ልብ ሐሳብ ያውቃል” /1ነገ.8፡39/፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሰዎች፣ በፍጥረታቱ ልብ የሚመላሰውንና የሚታሰበው ምን እንደሆነ ለማወቅ ሌላ ምስክር አይፈልግም፤ ራሱ ፈጣሪ ነውና ይህንን ለማወቅ አባቱን መለመን አያስፈልገውም /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ወንድሞቼ! ዛሬም “ክርስቶስ አምላክ አይደለም” የሚሉ ብዙ ልበ ስሑታን አሉና ይህን እውነት ልንመሰክርላቸው ያስፈልጋል፡፡ “የጾመው እሴተ ጾምን (የጾምን ዋጋ) የሚሰጥ ነው… የጸለየው ምልጃን የሚሰማ ነው… የተራበው የተራቡትን በቸርነቱ የሚያጠግብ ነው… የተጠማው የሕይወትን ውኃ የሚያድል ነው… የደከመው እርሱ ራሱ ሰንበት ነው… ያለቀሰው እርሱ ራሱ ያዘኑትንን ዕምባ የሚያብስ ነው…፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው ግን እኛንም እናተንም ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ እርሱ ዝቅ ዝቅ አድርገን ልናየው የሚገባው ጌታ ሳይሆን ለእኛ ብሎ ደሀ የሆነ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለምም አባት ነው፡፡ ስለዚህ እርሱን ለማመን አትቸገሩ” ብለን እንመስክርላቸው፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ በቸርነቱም መንግሥቱ እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡

No comments:

Post a Comment