Pages

Monday, May 21, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የአሥራ ሁለተኛው ሳምንት ጥናት!!

“ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” /ቁ.12/፡፡ በዚያ የነበሩት ሰዎች ወንጌለ መንግሥት መስማት ነበረባቸውና፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው “ወንድሞቹ” እያላቸው ያሉት የማን ልጆች ናቸው? እንዲህ ተብለው እየተገለጹ ያሉት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ዝምድና ያላቸው ናቸው እንጂ የእርሷ ልጆች አይደሉም፡፡ ይኸውም አብርሃም ለሎጥ /ዘፍ.13፡8/፣ ላባ ለያዕቆብ /ዘፍ.29፡15/ ወንድሜ እንደተባባሉት ዓይነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ወንደሞቼ እያለ ይጠራቸው እንደነበር ተገልጧል /ማቴ.14፡46-50፣ Augustine, On the Gospel of St. John, Tracte 10:2-3/፡፡ አንድም ዮሴፍ ከሚስቱ የወለዳቸውና ከጌታ ጋር አብረው ያደጉ ናቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
 “የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ” /ቁ.13/፡፡ ይህ ፋሲካ ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ የተደረገ የመጀመረያው ፋሲካ ነው፡፡ ሁለተኛው በሉቃ.6፡1፣ ሦስተኛው በዮሐ.6፡4፣ የመጨረሻው ደግሞ በዮሐ.11፡55 ተገልጸዋል፡፡  የሚገርመው ነገር ከዚህ በፊት ይህ ፋሲካ “የእግዚአብሔር ፋሲካ” ተብሎ ይጠራ ነበር /ዘጸ.12፡11/፡፡ አሁን ግን አይሁዳውያኑ የራሳቸው የሆነ ሰው ሠራሽ ወግና ልማድ ስለጨመሩበት ያ የድሮ ስሙ ተለውጦ “የአይሁድ ፋሲካ” ተብሎ እናየዋለን፡፡ በነብዩ እንዲህ እንደተባለ፡- “በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች” /ኢሳ.1፡14፣ Origen Commentary on the Gospel of John, Book 10:80-81/፡፡
“በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ” /ቁ.14/፡፡ እነዚህ ሻጮች እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደድ ቤተ መቅደሱን የንግድ ቦታ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ልብ ከእግዚአብሔረ ጋር ሳይሆን ከሚሸጡት ንብረትና ከሚያገብስብሱት ገንዘብ ጋር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጌታ ለመገዛት ሳይሆን እርሱን ለመሸጥ የሚሰበሰቡ ናቸው፡፡ ለእነሱስ በዚያ በሚሠዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ቢገዙ ይሻላቸው ነበር /አውግስጢኖስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 “ጌታችንም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ” /ቁ.15/፡፡ አስቀድመን እንደገለጥነው የእነዚህ አይሁዳውያን መሥዋዕት፣ በዓላት፣ ምናምቴን ጨምረው የሚያመጡት ቁርባን ደስ ስላላሰኘው ገለባብጦባቸዋል /ኢሳ.1፡11-15/፡፡ አንድ ነገር ግን ልብ በሉ! ጌታችን የገበያ ቦታውን ብቻ አልገለባበጠም፤ ይልቁንም መሥዋዕተ ኦሪቱም ጭምር እንጂ /Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 1.2:13-18/፡፡
“ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው” /ቁ.16/፡፡ ጌታችን ይህንን ሁሉ ሲያደርግ “የአባታችንን ቤት” ሳይሆን “የአባቴን ቤት” ሲል እንመለከተዋለን፡፡ ይኸውም አንዳንዶች እንደሚያናፍሱት የምንፍቅና ወሬ ሳይሆን እርሱ ዕሩይ ምስለ አብ በመለኰቱ (ከአባቱ ጋር የተካከለ መሆኑን) ያሳያል፡፡ “የአባቴን ቤት” የሚለውም አይሁድ አስቀድመው እግዚአብሔርን በአንድነቱ ብቻ ስለሚያውቁት ነው፡፡ አሁን ግን በባሕረ ዮርዳኖስ ግልጽ እንደሆነ በአንድነት በሦስትነት የሚመለክበት ቅዱስ ስፍራ ነው /ሉቃ.2፡49 St. Cyril of Jerusalem, Article 7:6/፡፡
 “ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ በመዝሙር 68፡10 ላይ እንደ ተጻፈ አሰቡ” /ቁ.17/።
ይህች ቅናት ጌታን እስከ መስቀል ድረስ ያደረሰች ቅናት ነች፡፡ ይህች ቅናት እርሱ ተዋርዶ እኛ የከበርንባት ቅናት ናት፡፡ ይህች ቅናት እርሱ ደሀ ሆኖ እኛ ባለጸጋ የሆንንባት ቅናት ናት፡፡ ወንድሞቼ! ዛሬ ይህች ቅናት ሁላችንም ልትበላን ያስፈልጋል! አኅቶቼ! ይህች ቅናት የአይሁድ ቅናት የመሰለች ክፉ ቅናት አይደለችም፡፡ ይህች ቅናት በውስጧ ተንኰል ያልተቀላቀለባት በንጹሕ ፍቅር የምትደረግ ቅናት ናት፡፡ ይህች ቅናት ዛሬ በተለይ አብዝታ ታስፈልገናለች፡፡ ፍቅር በቀዘቀዘበት ዘመን ይህች  ቅናት በቤታችን ታስፈልገናለች፤ መናፍቃን በበዙበት ዘመን ይህች ቅናት በቤተ ክርስቲያናችን ታስፈልገናለች፡፡
 ጌታ ዛሬም ይህች ቅናት ትበላዋለች፡፡ አማናዊው ቤተመቅደስ (ሰውነታችን) የነጋዴ ቤት፣ የክፋት ቤት፣ የሌቦች ቤት ሲሆን ጌታ ይህች ቅናት ትበላዋለች፡፡ ንጹሕ መሆን ሲገባን በተለያዩ ነገሮች ስንረክስ ዛሬም ያዝናል፡፡ ወደ ቤቱ እንመለስ፡፡ እግዚአብሔር ዛሬ በጅራፍ ሳይሆን በፍቅር ይጠራናል፡፡ እስክንከፍትለት ድረስም በበር ቆሟል፡፡ ወንድሞች እግዚአብሔርን “ማራናታ” እንበለው፡፡ ከዚያም ፈቃዳችንን ተመልክቶ እንዴት እንደሚያጠራን ራሱ ያውቅበታል፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ እኛን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!!

No comments:

Post a Comment