Pages

Friday, June 29, 2012

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለ2004 ዓ.ም. ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የዘማናችሁን ዐሥራት ሳይሆን መላ ዕድሜአችሁን ለወንጌል አገልግሎት የሰጣችሁ፣ ዘመናዊውን ዓለም ተላምዳችሁ ዘመናውያን ሰዎች ለመሆን ሳይሆን መንፈሳዊውን ዕውቀት ቀስማችሁ የዓለም ብርሃን ለመሆን በመንፈሳውያን ኰሌጆች ውስጥ እየተማራችሁ የምትገኙና የትምህርታችሁን የመጀመርያው ምዕራፍ አጠናቃችሁ በእግዚአብሔር ስም ልትመረቁ የበቃችሁ የተወደዳችሁ ልጆቼ! በፍቅሩ ቅመም አልጫውን ምድር ባጣፈጠው፣ ጨለማውን ዓለም በቃሉ ባበራው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰላም እላችኋለሁ፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቼ! እግዚአብሔር አምላካችን የአንድ ቀንን መታመን የማይረሳ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማገልገል ብቁዎች መሆን አለብን ብላችሁ ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የመጣችሁበትን የአንዷን ቀን ፍቅራችሁን የሚያስብ አምላክ ነው፡፡ ምንም እንኳን የጓዳውና የቤቱ ሥራ አስፈላጊና የማይታለፍ ቢሆንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከማርታ ይልቅ በማርያም ደስ ተሰኝቷል፡፡ ማርታ ያላትን ለትልቁ እንግዳ ልታቀርብ ባለቤቱን ጌታ እንደ እንግዳ ቆጥራ መባረክን ጀመረች፡፡ ማርያም ግን በቤቷም የሚያስተናግዳትን፣ የታዛዋ ብቻ ሳይሆን የሕይወቷም ራስ የሆነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልታደምጥ ከእግሩ ሥር ቁጭ አለች /ሉቃ.10፡38-42/፡፡ ጌታችን ለእርሱ ከማድረጋችን በፊት ያደረገልንን፣ ስለ እርሱ ከመናገራችን በፊት የነገረንን እንድናስተውል ይፈልጋል፡፡ የማርታ እኅት ማርያም ይህን የተረዳች ትመስላለች፡፡ እናንተም ደቀ መዛሙርት ያሳለፋችኋቸው ዓመታት ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብላችሁ ድምፁን የሰማችሁበት ዓመታት ናቸውና ደስ ይበላችሁ! ምንም እንኳን የዘወትር ትካዜአችን እንደ ቃሉ መኖር አለመቻል ቢሆንም በቃሉ የመኖርን ኃይል በንስሐና በጸሎት ልንለምን ይገባናል፡፡

  የተወደዳችሁ ደቀ መዛሙርት ልጆቼ! እስከ ዛሬ የሚታሰብላችሁ ልጆች ነበራችሁ፡፡ ዛሬ ግን የምታስቡ ወላጆች እንድትሆኑ ለወንጌል ሙሽራይት ቤተ ክርስቲያን ትድራችኋለች፡፡ በዘመናት ሁሉ እንደታየው ወንጌል ዝም ማለት የማትወድ ናት፡፡ ወንጌልም መክና አታውቅም፡፡ የወንጌል የማጌጫ ዘውዷ አክሊለ ሦክ፣ የሥልጣን ዘንጓም መስቀል፣ መገለጫዋም መገፋት ነው፡፡ የማትገድለው ወንጌል ለሰማዕትነት የጨከነች ናትና አዲሱ ኑሮአችሁን ቤተ ክርስቲያን ትመርቃለች፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቼ! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ያህል ካስተማራቸው በኋላ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ከልሎ ወደ ዓለም ልኳቸዋል፡፡ እናንተም ላለፉት ዓመታት የደቀ መዝሙርነት ትምህርታችሁን ተከታትላችኋል፡፡ ትምህርታችሁን በሞገስ ለሕዝብ እንዲደርስ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል የምታገኙት በጽሞናና በጸሎት በመቆየት ነው /ሉቃ.24፡49/፡፡ ቤተ ክርስቲያን እናንተን መምህራን አድርጋ ሳይሆን ደቀ መዛሙርት አድርጋ መርቃለች፡፡ ስለዚህ የሁል ጊዜ ተማሪዎች እንደሆናችሁ፣ ትምህርቱም የማያልቅ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባችኋል፡፡

  የተወደዳችሁ ልጆቼ! ምንም ብታስተምሩ፣ ምንም ብትጽፉ ዓለም አበባ ይዛ እንደማትቀበላችሁ እወቁ፡፡ ይህ በእናንተ የተጀመረ ሳይሆን የዓለም መገለጫዋ መሆኑን አትዘንጉ፡፡ ልዩ ልዩ ነቀፋና ስደት ሲመጣባችሁ ከዓለም እንደተጣላችሁ አትቁጠሩት፡፡ እንዲያውም ከዓለም ጋር እንደተዋወቃችሁ ቁጠሩት፡፡ ዓለም እንደዚህ ናትና፡፡ ጎበዝ የሚባለው ሳይቀር በመገፋት ውስጥ በኀዘን ይጐዳል፡፡ የሚታይ ተስፋ እያጣም በብቸኝነት ይንገላታል፡፡ ይሁንና ሰው መተማመኛ የማይሆን የሸምበቆ ምርኩዝ መሆኑን ቃሉ ይነግረናል /ኢሳ.36፡6/፡፡ ስለዚህ በሁሉም ነገር ውስጥ የጠራችሁን ጌታ ክርስቶስን ተመልከቱ /ዕብ.3፡1/፡፡ የተቀበላችሁትን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ያልተቀበላችሁትንም ለመስጠት ፈቃደኞች ሁኑ፡፡ ፍቅርን አላያችሁ ከሆነ ከእናንተ ይልቅ የፍቅርን ረሀብ የሚያውቅ የለምና ፍቅርን ስጡ፡፡ የሚያዝንላችሁ አባት አላገኛችሁ እንደሆነ ለሚጠጓችሁ እናንተ ደግሞ አዛኝ አባቶች ሁኑ፡፡ ተራራውን ስትጨርሱ መስክ እንደሚያጋጥማችሁ እያሰባችሁ በተራራው አትዘኑ፡፡ እናንተ ዱር መንጣሪዎች ናችሁና የተመቸ ቦታን ፍጠሩ እንጂ ምቹ ቦታን አትጠብቁ፡፡ የደረሰባችሁ ችግርም እስከ ዕድሜአችሁ ፍጻሜ የምትናገሩትን ትምህርት ይሰጣችኋልና አትበሳጩ፡፡ ከምትፈልጉት ነገር ይልቅ ያገኛችሁት ይበልጣል፤ እርሱም የሰማይ ዜጐች መሆናችሁ ነውና ደስ ይበላችሁ!

የተወደዳችሁ ልጆቼ! እግዚአብሔር የሚባርከው አሳባችሁን ሳይሆን ቃል ኪዳናችሁን ነውና አገልግሎታችሁን በቃል ኪዳን ያዙ፡፡ መጽናናትን የሚሹ ብዙዎች ኀዘንተኞች፣ በማዕበል የሚንገላቱ ብዙዎች ደካሞች እየጠበቋችሁ ነውና ፍጠኑ፡፡ እናንተን ኑ ለማለት አቅም የሌላቸው ብዙ አሉና ሳይጠሯችሁ ሂዱ፤ ወንጌል ሀገሯ እስከ ምድር ዳርቻ ነውና፡፡ ዘመናዊነትና ሥልጣኔ የማይሞላው የሕይወትን ክፍተት በወንጌል የምትሞሉ እናንተ ናችሁ፡፡ የያዛችሁት እንደ ቀላል አትቁጠሩት፡፡ የዓለምን ኃይልና ዕውቀት ሁሉ የምትማርኩ የዕውነት ዘማቾች ናችሁ፡፡ እንደማይፈለግ ሰው ራሳችሁን አትቁጠሩት፡፡ የሞተላችሁ ጌታ ውበቱ የማያረጅ፣ ዛሬም ያደመቃችሁ እርሱ ነው፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቼ! ዋጋችሁ በሰማያት እንደሆነ እያሰባችሁ በትንንሽ የምድር ዋጋ ክብራችሁን እንዳትጥሉ ተጠንቀቁ፡፡ እኔም በጸሎትና በአባታዊ ፍቅር ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በሰማያዊና በምድራዊ በረከቱ ይባርካችሁ! ዛሬ እንደ ያዕቆብ በሌጣ ወጥታችሁ፣ ለከርሞ ግን በብዙ ፍሬ ይመልሳችሁ! እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ! የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም ልጅ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ!”
      

No comments:

Post a Comment