Pages

Friday, June 29, 2012

የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ- የዮሐንስ ወንጌል የ29ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.6፡22-40)!



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“በነገው” ማለትም ኅብስቱን አበርክቶ ከሰጣቸው በኋላ፤ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቅፍርናሆም እንዲሻገሩ ግድ ካላቸው በኋላ፤ እርሱም ወደ ተራራ ፈቀቅ ብሎ ቆይቶ በማዕበሉ ላይ እየተረገጠ የጌንሴረጥ ዕጣ ወደ ምትሆን ወደ ቅፍርናሆም ከተሻገረ በኋላበባሕር  ማዶ” ማለትም ገና ወደ ቅፍርናሆም ሳይሻገሩቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች” ተመለከቱ፡፡ ግራ ገባቸው፡፡ ጌታችን በዚያ የለም፡፡ “ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ” አስተውለዋል /ቁ.22/፡፡  ይህ የእነርሱ ግራ መጋባት በምክንያት የተደረገ ነበር፡፡ ጌታችን ማዕበሉን እየተረገጠ መሻገሩ በግልጽ ሳይሆን በጭላንጭል እንዲያውቁ የተደረገ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ “ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ፡፡ ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ ሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ” /ቁ.23-24/። ጌታችንን አገኙት፡፡ አሁን ጥያቄው “ጌታ እንዴት ተሻገረ? በእግሩ ነውን?” የሚል መሆን ነበረበት፡፡ ምክንያቱም “በጀልባ ነዋ!” እንዳንል ወንጌላዊው “ደቀ መዛሙርቱ ከተሳፈሩባት ውጪ ሌላ ጀልባ አልነበረችም፤ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ” ብሎናልና፡፡ “ታድያ እንዴት ተሻገረ?” ሕዝቡ ይህን ሊጠይቁ በተገባ ነበር፡፡ ሆኖም ግን አመጣጣቸው ለሌላ፤ የጌታችንን ጌትነት በማመን ሳይሆን ስለ ሌላ ዓላማ ነበርና መጠየቅስ ይቅርና አላሰቡትምም፡፡ ለዚህም ነው በባሕር ማዶ ሲያገኙትመምህር ሆይ! ባሕሩን እንዴት ተሻገርክ?” ሳይሆን “መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?” የሚሉት /ቁ.25/። ምን ያህል ወላዋይ እንደሆኑ እናስተውል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ጌታችን ኅብስቱን አበርክቶ ሲሰጣቸውና ሲጠግቡ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣ ነቢይ ነው” ብለው ሲገረሙ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ነጥቀው ሊያነግሡት ሽተው ነበር፡፡ አሁን ግን እንደከዚህ በፊቱ አይደነቁም፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው ጌታችንን የሚፈልጉት ስለ በሉና ስለ ጠገቡ እንጂ ምልክትን ስላዩ አይደለምና /ቁ.26፣ Saint John Chrysostom Homilies on St. John, Hom.43:l./፡፡
 ሰው አፍቃሪው ጌታ ግን “እናንተ የሆድ ባርያዎች፤ እናንተ ሆድ አምላከቸው እስከ መቼ ድረስ እታገሣችኋለሁ?“ አይላቸውም፡፡ ይልቁንም እነርሱን በሚያቀርብ ጥበባዊ አነጋገር፡-ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና” ይላቸዋል እንጂ /ቁ.27/።  እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ልጆቼ! አመጣጣችሁ ምድራዊ መብልን ብቻ በመሻት አይሁን፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ክርስቶስ ለሚሰጣችሁ ደግሞም ለሚበልጠውና የዘላለምን ሕይወት ለሚሰጠው ለማያልፈው ምግብ እንጂ፡፡ አባታችን የምትሉት እግዚአብሔር አብ የእኔም የባሕርይ አባቴ ይህን ሰማያዊ መና እሰጣችሁ ዘንድ ልኮኛልና፤ ሾሞኛልና፤ አትሞኛልና /መዝ.45፡7/፡፡ ስለዚህ አስቀድማችሁ ኃላፊ ጠፊ የሚሆን መብልን ሳይሆን የዘላለምን ሕይወት የሚሰጥ መብልን ፈልጉ፤ ይህም ይጨመርላችኋል /ማቴ.6፡34/፡፡ እንዲህም ብዬ ስነግራችሁም ግራ የምትጋቡ አትሁኑ፡፡ እኔ የሰው ልጅ ስሆን እንደ እናንተ ዕሩቅ ብእሲ (ፍጡር) አይደለሁምና /ማቴ.16፡16/፡፡ ስለዚህ እኔ የምሰጣችሁ እንጀራ ሌላ ሰው እንደሚሰጣችሁ አይደለምና ይህን የማያልፈው መብል እሰጣችሁ ዘንድ ለምኑ” /St. Augustine: On the Gospel of St. John, tractate 25:11./፡፡
    እነርሱ ግን አሁንም በውስጣቸው የሚፈልጉት ያን ምድራዊ መብል ስለሆነ  እንግዲህ  የእግዚአብሔርን ሥራ (እግዚአብሔር የሚወደውን ሥራ) እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት /ቁ.28/።  ጌታም፡-ይህ የእግዚአብሔር ሥራ (እግዚአብሔር የሚወደው ሥራማ) እርሱ (አባቴ) በላከው (በእኔ) እንድታምኑ ነው” አላቸው /ቁ.29/። እነርሱ ግን አስቀድመን እንደተነጋገርነው አመጣጣቸው በጌትነቱ ለማመን ስላልነበረ ከአንድ ቀን በፊት የተደረገውን ምልክት (ተአምር) ረሱትና እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ቀድሞ አባቶቻችን በምድረ በዳ መናውን ተመግበዋልና” አሉት /ቁ.30-31/። እንዲህ ማለታቸው ነበር፡-“በእውነት አንተ አባታችን ሙሴ ይመጣል ብሎ የነገረን ነቢይ ከሆንክ እናምንብህም ዘንድ እርሱ ከሰማይ መና አውርዶ እንደመገባቸው ከደረቅ ዓለትም ውኋውን አፍልቆ እንዳጠጣቸው ለእኛም አድርግልን፤ እንዲህ ካልሆነ ግን እናምንብህ ዘንድ አይቻለንም፤ የምትነግረንን ለመስማትም ጀሮአችን ድፍን ነው፡፡” /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatian’s Diatessaron, 12:10/፡፡

  እንደነርሱ ሐሳብ ሙሴ ካደረገው የበለጠ ተአምር እንደሌለ በእርጠኝነት ይናገሩ ነበር፡፡ ጌታችን ግን እንደ ልማዱ ሰዎቹን ቀስ በቀስ ወደ እርሱ ያቀርባቸው ዘንድ ወድዶ በአንድ ጊዜ “እኔ ከሙሴ እበልጣለሁ” አይላቸውም፡፡ “እበልጣለሁ” ቢላቸው ምን ያህል ለቁጣ የፈጠኑ እንደሆኑ ያውቃቸዋልና፡፡ ስለዚህ ንግግሩን ሙሴ የተነገረለትን ታላቅ ተአምራት እንዲሠራ ወደ አስቻለው ምንጭ መለሳቸው፡፡ እንዲህም አላቸው፡- “በእናንተ ሐሳብ እስማማለሁ፡፡ ሙሴ ታላላቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ እንጂ በራሱ ኃይልና ሥልጣን መናን መስጠት ውኃን ከዓለት ማፍለቅ የሚችል አልነበረም፡፡ እግዚአብሔርን በሰማያት ማን ይተካከለዋል? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል? /መዝ.89፡6/ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፡፡ ያም ቢሆን የተሰጠው መና ሊመጣ ላለው እኔም ለምሰጣችሁ ለአማናዊው መና ጥላ ነበር፡፡ ከዚያ መና የተመገቡ ሰዎች ከዚያ ውኃ የጠጡ ወገኖች እንደገና ተርበዋልና፤ እንደገና በውኃ ጥም ተይዘዋልና፡፡ ስጦታው ጊዜአዊ ችግርን የፈታ እንጂ ዘለአለማዊ ደኅንነትን የሰጣችሁ አይደለም፡፡ አማናዊው የእግዚአብሔር እንጀራከሰማይ የሚወርድ (ደግሞም ለእስራኤል ዘሥጋ ብቻ ሳይሆን) ለዓለም (ለሰው ልጅ ሁሉ) ሕይወትን የሚሰጥ ነው” አላቸው /St. Cyril of Alexandria, Commentary on the Gospel Of John 3፡6/።  
  አሁንም በዚሁ ምድራዊ አስተሳሰብ ይንፏቀቃሉ፡፡ ስለ መንፈሳዊው መብል ቢነግራቸውም ስለ ሥጋዊ መብል የነገራቸው ስለመሰላቸው፡-ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን” ሉታልና /ቁ.34/።  ጌታ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡-የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው። ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ”።  እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ልጆቼ! አሁንም የምትጠይቁኝ ተራና ሥጋዊ መብል ነው፡፡ አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ያ ሥጋዊ መብል ጊዜአዊ ችግርን የፈታ እንጂ ዘላለማዊ ደኅንነትን የሰጣችሁ አይደለም፡፡ ወደ እኔ የሚመጣ ግን እንደገና አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ዳግመኛ አይጠማም፡፡ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝና፤ በእኔ ፈቃድ በአባቴ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ስለ ሰው ልጆች ሰው የሆንኩኝ ሰማያዊ እንጀራ እኔ ነኝና፡፡ ወደ እኔ ብትመጡ ከቶ አትራቡም፤ በእኔም ብታምኑ ከቶ አትጠሙም፡፡ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የተዘጋጀውን ቅዱስ ሥጋዬንና ክቡር ደሜን ብትቀበሉ ከሞት ወደ ሕይወት ትመለሳላችሁ፤ የተያዛችሁበት የባርነት ቀንበር ይሰበራል፤ የኃጢአት ሰንሰለታችሁ ይበጣጠሳል፤ ባሕረ እሳቱን ተሸግራችሁ ወደ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትነጠቃላችሁ፡፡ ሆኖም ግን ልታምኑብኝ አልወደዳችሁም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ “በአብ በሕልውና ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል ምስክሩም የሚቀበለው የለም” እንዳለ ልትቀበሉኝ አልወደዳችሁም /ዮሐ.3፡32/፡፡  አባቴ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ የሰጠኝ ሁሉ ግን በእኔ ያምናል፡፡ በእኔ ያመነም ከመንግሥተ ሰማያት አፍአ ወደ ገሃነም አላወጣውም፡፡ መንግሥተ ሰማያት ከገቡ መውጣት ካገኙ ማጣት የለምና፡፡ ከሰማይ የወረድኩት የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ ልዩ ሆኖ የእኔን ፈቃድ ብቻ ላደርግ አይደለም፡፡ ስለ እናንተ ድኅነት ስል በእኔ ፈቃድ በአባቴ ፈቃድ በባሕርይ ሕይወቴ በመንፈስ ቅዱስም  ፈቃድ ሞትን በፈቃዴ እቀበል ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ እኔን አይቶ ያመነብኝ ሁሉ የዘላለም ድኅነት ያገኛል፤ በመጨረሻው ቀንም ለሐሳር ሳይሆን ለሕይወት አነሣዋለሁ፡፡” /ቅ.ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፣ ዝኒ ከማሁ/፡፡
    አሜን ትንሣኤ ለዘክብር እንድንነሣ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን!!




No comments:

Post a Comment