Pages

Friday, June 22, 2012

“እኔ ነኝ አትፍሩ!” - የዮሐንስ ወንጌል የ28ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.6፡16-21)!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ሕዝቡ ከበሉና ከጠገቡ በኋላ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነብይ ነው” ብለው ነበር /ቁ.14/፡፡ ስለዚህም የመሲሑ ክርስቶስ ዓላማ ስላልተረዱ ሊያነግሡት አስበው ነበር፡፡ እንደ እነርሱ ሐሳብ ያከበሩትና ከፍ ከፍ ያደረጉት መስለዋቸው ነው፡፡ እርሱ ግን እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ ዓለምን በእጁ የጨበጠ፣ በፍቅሩም የሚመግባት፣ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜም ሰውን ከወደቀበት ለማንሣት የባርያውን መልክ ይዞ የመጣ ልዑለ ባሕርይ ነው /መዝ.24፡1/፡፡ ስለዚህም በኃይል ነጥቀው ሊያነግሡት እንደ ፈለጉ አውቆባቸው ብቻውን ወደ ተራራ ፈቀቅ ሊል ወደደ፡፡ በክፍል 27 እንደተነጋገርነውም ፈቀቅ ማለቱ ፈርቶ አልነበረም፡፡ ይልቁንም “ሰው የማያነግሠኝ ልዑለ ባሕርይ ነኝ፤ አመጣጤም እናንተን ልጆቼና ብልቶቼ አድርጌ ወደ ሰማያዊው ቤታችሁ ለመውሰድ፤ ወደ ጥንተ ተፈጥሮአችሁ ለመመለስ እንጂ እዚህ ምድር ላይ ለመንገሥ አይደለም፤ እኔስ ከዓለም አስቀድሜ ንጉሥ ነኝ” ሲላቸው እንጂ /መዝ. 73፡12፣ Saint Augustine, On the Gospel of St. John, tractate 25:1-2/፡፡


  ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ አስተሳሰብ ይወጡ ዘንድ “በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው” /ማቴ.14፡22/፡፡ እርሱም ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ተራራ ፈቀቅ አለ፡፡ “በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፤ በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር፡፡ አሁንም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር” /ቁ.16-17/፡፡ ወንጌላዊው የጊዜው መጨለም የጌታችንም አለመምጣት የሚነግረን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም የደቀ መዛሙርቱ ታዛዥነት ለማሳየት እንጂ፡፡ ከእናንተ መካከል “ስለምንስ እስከ አሁን ማለትም እስኪጨልም ድረስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሳይመጣ ቆየ?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- “አንደኛ ደቀ መዛሙርቱ ፈተና መቋቋምን መለማመድ ነበረባቸው፤ ሁለተኛ እርሱ ልዑለ ባሕርይ መሆኑንና ሙሴ ቅሉ እንደ እኔ ያለ ነብይ ያስነሣላችኋል ቢልም ክርስቶስ እርሱ ዕሩቅ ብእሲ አለመሆኑንና ከጥንት ጀምሮ ንጉሥ ሰውም የማያነግሠው ልዑለ ባሕርይ መሆኑን ማወቅ መረዳት ነበረባቸው” /Saint John Chrysostom, Homilies on St. John, Hom. 43:1./፡፡

   ከዚህ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳአቸው መጓዝ ከጀመሩ በኋላ “ብርቱ ነፋስ ነፈሰ፤ ባሕሩም ተናወጠ፡፡ ሀያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ” /ቁ.18-19/። አዎ! ሰዓቱን ቢያስቡት አራተኛው ሰዓተ ሌሊት ላይ ነው፣ ቦታውን ቢያዩት ገና ማዕከለ ባሕሩ ላይ ናቸው፤ ዋኝተው እንዳይሄዱ የብሱ ሩቅ ነው፤ ባሕሩን ቢመለከቱት ንውጽውጽታው ጨምሯል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ እርሱ መሲሑ ማዕበሉን እየተረገጠ ቢመጣ ምትሐት መሰላቸው፡፡ ስለዚህም ፈሩ፤ ደነገጡ /ማቴ.14፡26፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡

   ፍርሐትን የሚያርቅ ከዐቅማችንም በላይ እንድንፈተን የማይሻ ጌታ ግን፡-እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው፤ ሰላማቸውን መለሰላቸው፤ እንደፈለጉትም ዕረፍት ሆነላቸው፡፡ ድንቅ ነው! ፈተና ውስጥ ስንገባ፣ የመቻል አቅማችን የመጨረሻውን ጠርዝ ሲደርስ፣ ተስፋችንም ሲሟጠጥ ክርስቶስ ይደርሳል፡፡ ደርሶም ሰላማችንን ይመልሳል፤ ፍርሐታችንን ያርቃል፤ ተስፋችንን ይቀጥላል፤ አያልፍም ያልነውን አሳልፎም ውስጣችን በሐሴት ይሞላዋል፤ የሕይወታችንን ማዕበል እየረገጠ መጥቶም ነፋሱን (የሚያውከንን ሁሉ) ጸጥ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ግን ደቀ መዛሙርቱ ጌታችንን “በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ” እንዲል በማዕበል ስንናወጥ ወደ መርከባችን (ወደሚነዋወጠው ሕይወታችን) ለመግባት ውዴታችንን ይጠብቃል፡፡  ስንፈቅድ ግን፤ እግዚኦ አድኅነኒ- አቤቱ አድነን ስንለው ግን ፈጥኖ እጁን ይዘረጋል፤ ያወጣንማል፡፡ ከአሸናፊውም ጋር እናሸንፋለን፡፡ ማዕበል ውስጥ ሆነን (ከእነ ድካማችን በእርሱ እርዳታ!) ማሸነፋችን ደግሞ  እግዚአብሔርን የበለጠ እንድናመሰግነው ይረዳናል፡፡ ይህን ጕዞ እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻው ግን ሙሽራው ይመጣል፡፡ እንግዲያውስ አማኞች ሆይ! አትፍሩ! ማዕበል ንውጽውጽታ የሌለው የብሱ (ርስታችን መንግሥተ ሰማያት) ቅርብ ነውና /ቁ.20-21፣ St. Cyril of Alexandria, Commentary on the Gospel of John/፡፡

  
   “ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው” /ሰቆ.ኤር.3፡26/፡፡
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!


No comments:

Post a Comment