Pages

Tuesday, June 19, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- ክፍል አንድ!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!   
    ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ስለ ሊቀ ካህናችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በስፋትና በጥልቀት የምናገኘው በዕብራውያን መልእክት ነው፡፡ ሐዋርያው መልእክቱን የጻፈበት ዓላማም በአጭሩ እንዲህ ቀርቧል፡- በይሁዳ ሀገርና በብሔረ አሕዛብ ሁሉ ያሉ ዕብራውያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንና ደቀ መዛሙርቱን ወንጌልን በማስተማራቸው አጽንተው ይጠልዋቸው ነበር፡፡ ጌታ ካረገ በኋላ ግን በሐዋርያት ቃል የሚደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ ከእነርሱ ብዙዎች በጌታችን ስም አመኑ /ሐዋ.2 ሙሉውን ይመልከቱ/፡፡ ሆኖም ግን ሕገ ኦሪትን ከሕገ ወንጌል ይልቅ አብልጠው መጠበቃቸው አልተዉም፡፡ በሌላ አገላለጽ ሕገ ወንጌልን ለሕገ ኦሪታቸው ተጨማሪ ሕግ አድርገዋት ነበር፡፡

  ሐዋርያትም ሃይማኖተ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ እስኪስፋፋ ድረስ ኦሪትን ከወንጌል ጋር እንዲጠብቁ ተዋቸው እንጂ “ኦሪታችሁን ፈጥናችሁ ልቀቁ” አላልዋቸውም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ አይሁድ አሕዛብን ለጓደኝነት ይጸየፍዋቸው ምግባቸውም ከመብላት ይከለከሉ ነበር፡፡  ሐዋርያት ወንጌልን ሲያስተምርዋቸው ተአምራት ሲያደርጉላቸው አይተው ቢያምኑም ተገዘሩ፤ ሕገ ኦሪትን ጠብቁ ስላላልዋቸው ፍጹም ቅናት አደረባቸው፡፡ የኦሪታቸውና የሌዋውያን ክህነት የላሙን፣ የበሬዉን፣ የበጉን፣ የፍየሉን መሥዋዕትና በጠቅላላው የአባቶቻቸውን ሥርዓት ማለፍ ባሰቡ ጊዜ እጅግ አዘኑ፡፡ ከጥንት ጀምሮ ለእነርሱ ብቻ ይነገር የነበረው ተስፋ ለሁሉም እንደሆነ ባሰቡ ጊዜ እጅግ ታወኩ፡፡ ከዚህ በኋላ በአንድነት መከሩና ከአሕዛብ ወገን በወንጌል ያመኑትን “ወንጌል ያለ ኦሪት ጥምቀት ያለ ግዝረት አትረባምና ተገዘሩ ሕገ ኦሪትንም ጠብቁ” እያሉ ዓለምን የሚያውኩ ሐሰተኛ ወንድሞችን ወደ አንጾክያ ሰደዱ፡፡ የግብረ ሐዋርያት ጸሐፊ “ከይሁዳ ሀገርም የወረዱ ሰዎች እንደ ሙሴ ሕግ ካልተገዘራችሁ ልትድኑ አትችሉም እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር” እንዲል፡፡

  ስለዚህም በአንጾክያ ያሉ አሕዛብ እጅግ ታውከው ጳውሎስንና በርናባስን ተከራከሯቸው፡፡ ስለዚህ ክርክር ጳውሎና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ቀሳውስትም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ።

  ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ቀሳውስትም ተቀበሉአቸው፤ እግዚአብሔርም በአሕዛብ ዘንድ ተአምራት እንዳደረገላቸው አሕዛብም ሳይገዘሩ መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው ቢነግሯቸው ሐዋርያትና ቀሳውስቱ እጅግ ደስ አላቸው፡፡

  ከፈሪሳውያን ወገን አምነው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ግን ተነሥተው ወደ ሐዋርያት ሔዱና “ከአሕዛብ ያመኑትን ትገርዙአቸው ዘንድና ሕገ ኦሪትንም እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል” አሏቸው፡፡ ሐዋርያትና ቀሳውስት ግን በክርስትናው ታሪክ የመጀመርያው በሆነው በዚሁ ጉባኤያቸው “ከጣዖት ወደ ወንጌል በተመለሱ አሕዛብ ሸክም አታክብዱ፤ ሁላችንም በጸጋ እግዚአብሔር በወንጌል አንድ እንሆናለን እንጂ አባቶቻችን እኛም ያልቻልነውን ጽኑ ሸክም አታሸክሟቸው፡፡ ለጣዖት የተሠዋውን፣ ሞቶ ያደረውን፣ በደም የታነቀውን ከመብላትና ከዝሙት
እንዲከለከሉ በራሳቸው የሚጠሉትን በሌላ እንዳያደርጉት ብቻ ልናዛቸው ይገባል” ብለው እምቢ አሏቸው /ሐዋ.15 ሙሉውን ይመልከቱ/፡፡

  ከዚህ በኋላ በልቡናቸው ቅናት ስለሞላ አዝነውና ተክዘው ከሐዋርያት ተለይተው ከሽማግሎቻቸውም ጋር መክረው አሕዛብን “ተገዘሩ” እያሉ ያስትዋቸው ዘንድ በክፋት ከፊተኞች የበለጡ ቢጽ ሐሳውያውንን ላኩ /የገላትያን መልእክት ሙሉውን ይመልከቱ!/፡፡

  አይሁድንም ሕገ ኦሪት የከበረች እንደ ሆነች ለነቢያቸው ለሙሴ በመልአኩ እጅ ከእግዚአብሔር እንደተሰጠች፤ አባቶቻቸውም በእርሷ ከብረው ይኖሩባት እንደነበረ ያሳስብዋቸውና በጭራሽም ሊተዉዋት እንደማይገባና እንደማይቻል ያስጠነቅቅዋቸው ጀመረ፡፡

  ዳግመኛም የሌዋውያን የክህነታቸውን ሥርዓት የመሥዋዕቱን አኳኋን ቀድሞ በደብተራ ኦሪት ኋላም በቤተ መቅደስ ይደረግ የነበረውን ሁሉና በውስጧም ደም ተረጭቶ ኃጢአት ይሠረይ እንደነበረ ያሳስብዋቸዋል፡፡

 ይህን ሁሉ ዕንቅፋትና ጥርጥር በልቡናቸው በዘሩባቸው ጊዜ አምነው የነበሩት የአይሁድ ወገን ከሃይማኖተ ወንጌል ወደ ሃይማኖተ ኦሪት ከሕገ ወንጌል ወደ ሕገ ኦሪት ሊመለሱ ወደዱ፡፡
  ከዚህ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ሊያጽናናቸውና ሊገስጻቸው ወዶ ይህን መልእክት ጽፎላቸዋል፡፡ የቀደመች ሕገ ኦሪት ደካማ በመሆኗ ጥቅም አልነበራትምና ምንም የፈጸመችው ግዳጅ ስለ ሌለ ኦሪት በወንጌል መለወጧን ያስረዳቸዋል፡፡ ኦሪት ለወንጌል መርገፍ ጥላ እንደነበረች ያስገነዝባቸዋል፡፡ እግዚአብሔር በነብዩ ኤርምያስ አድሮ “ለቤተ እስራኤልና ለቤተ ይሁዳ አዲስ ሕግ እሠራለሁ፡፡ የምሠራውም ሕግ ከምድረ ግብጽ ባወጧኋቸው ጊዜ ለአባቶቻቸው እንደ ሠራሁት ሕግ ያለ አይደለም፡፡ እነርሱም በሕጌ ጸንተው አልኖሩም፤ እኔም ቸል ብያቸዋለሁና” ብሎ ከተናገረው ምስክር አምጥቶ የኦሪት ማለፏ በሚገባ እንደሆነ ሊያስረዳቸው ወደደ /ኤር.31፡31/፡፡ “በሌዋውያን ክህነት ፍጹም የሆነ ድኅነተ ነፍስ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ክህነቱ እንደ መልከ ጼዴቅ የሆነ ሌላ ሊቀ ካህናት ባላስፈለገ ነበር የክርስቶስ ክህነትም እንደ መልከ ጼዴቅ ሳይሆን እንደ አሮን ሹመት ይባል ነበር” እያለ የክህነታቸው ማለፍ የኦሪትን ማለፍ የሚያሳይ እንደሆነ ያስረዳቸው ነበር /ዕብ7፡11/፡፡

  ሊቀ ካህናት!
  የሐዋርያው መልእክት በአንድ ዐረፍተ ነገር ቢቀመጥ “ክርስቲያኖች በከባድ ተጽዕኖ ምክንያት ወደ ኦሪት በመመለስ ክርስቶስን እንዳይክዱ ማስጠንቀቅና ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቁ ማስገንዘብ ነው”፡፡ አዎ! በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔርን ከሕዝቡ ጋር ሕዝቡንም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኙ ማለትም የሚያስተራርቁ ብዙ ነብያትና ካህናት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ሙሴ በእግዚአብሔርና በሕዝበ እስራኤል መካከል ሆኖ ያገለገለ ታላቅ ነብይ ነበር /ዘዳ.5፡5/፡፡ እንደዚሁም አሮንና ከቤተ አሮን የሆኑ ካህናት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ሆነው ያገለግሉ ነበር /ዕብ.5፡1-4/፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎታቸው ሊመጣ ላለው ለሐዲስ ኪዳን ምሳሌና ጥላ ስለነበረ ዘላለማውያን አልነበሩም /ዕብ.8፡5/፡፡ ሞት ስለከለከላቸውም እንዲህ የተሾሙ ብዙዎች ናቸው /ዕብ.7፡23/፡፡ በዘመነ ሐዲስ ግን ሞት የማይሽረው ይልቁንም ሞትን በሞቱ የገደለ አንድ ሊቀ ካህን አለን፡፡ እርሱም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል /ዕብ.4፡14-15/፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው “የሃይማኖታችን ሐዋርያና ሊቀካህን” የሚለን /ዕብ.3፡1/፡፡ ቀሳውስት አባቶቻችን ጸሎታቸውን ሲጨርሱና ሲባርኩን፡- “ኃጢአትን የሚያስተሠርይ በደልን የሚደመስስ ካህን ሊቀካህናት የሆነው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ይበላችሁ፤ ይፍታችሁ፤ ያንጻችሁ፤ ይቀድሳችሁ” የሚሉንም ስለዚሁ ነው፡፡
  
   የብሉይ ኪዳን ካህናት በቤተ መቅደስ ውስጥ ያገለግሉ ነበር /ዘሌ.1፡5-7፡35/፡፡ አገልግሎታቸውም በየተራ ነበር /ሉቃ.1፡8-9/፡፡ ቤተ መቅደሱን የሚያስተዳድር፣ ካህናቱን የሚቈጣጠር፣ ሸንጐአቸውን በሊቀመንበርነት የሚመራ፣ የማስተስርያ ቀን በሚባለውና በዓመት አንድ ጊዜ በሚውለው በዓል ላይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ብቻውን በመግባት ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ መሥዋዕት የሚያቀርብ ደግሞ ሊቀ ካህናት ይባላል /ዕብ.9፡7፣ ዘሌ.4፡27-29፣ ዘሌ.16፡1-34/፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው ሊቃነ ካህናቱ ይሠዋው የነበረው ደመ በግዕ፣ ሥጋ በግዕ፣ ደመ ጠሊ፣ ሥጋ ጠሊ፣ ደመ ላህም፣ ሥጋ ላህም ይመጣ ዘንድ ላለው የዓለምንም ኃጢአት ለሚያስወግደው አማናዊው መሥዋዕት የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ነበር /ዕብ.10፡11-16/፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሊቀ ካህናት (ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ) እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት መሥዋዕትን (ራሱን) ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም /ዕብ.9፡25/፡፡

  ይህን እውነታ አጥብቃ የያዘች ርትዕት ሃይማኖት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቀ ካህናችን የኢየሱስ ክርስቶስ የማስታረቁ ትምህርት አብዝታ ታስተምራለች፡፡ ይህም ከሚከተሉት ምሳሌዎች መረዳት ይቻላል፡፡
©     “ለሐዲስ ኪዳንም አስታራቂ ሆነ” /ቅ.ኤፍሬም በእሑድ ውዳሴ ማርያም/፡፡
©     “ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር አቀረበን” /ቅ.ኤፍሬም በቅዳሜ ውዳሴ ማርያም/፡፡
©     “በእኛና በአባትህ መካከል ፍቅርን አደረግህ፤ በመካከልም ሆነህ አስታረቅኸን” /ኪዳን/፡፡
©     “ወደ አባቱ ለመሄድ መንገድ፣ ለመግባትም በር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ሰዓታት/፡፡
©     “የአብ ሊቀ ካህናት የሰውን ወገን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ” /አመክንዮ ዘሐዋርያት/፡፡
©     “ሰው የሆነው ዘመድ ሊሆነን ብቻ አይደለም፤ ፈጽሞ ይቅር አለን፤ ኃጢአታችንን ለማስተሥረይ ከአብ ጋር ለማስታረቅ ሊቀ ካህናትም ይሆነን ዘንድ ወደደ እንጂ፡፡ ስለዚህም ሰዎችን ሊመስላቸው ይገባል ባለው ነገሩ ላይ ጨምሮ በሁሉ አዛኝ የሕዝቡንም ኃጢአት ለማስተሥረይ በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነ አስታራቂ ይሆናቸው ዘንድ ወደደ አለ” /ሃይማኖተ አበው.63፡13/፡፡
©     “በጐ ሥራ ለመሥራት የምንቀና ደግ ወገን አድርጐ ገንዘብ አደረገን፤ ለእኛ ማልዶልናልና (ሐዋርያው ጳውሎስ) የምናምንበት ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) አለው” /ሃይማኖተ አበው 63፡26/፡፡
©     “እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስማማ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሁለቱንም አስታረቃቸው /ሃይማኖተ አበው. 68፡21/፡፡
©     “የሰው ሁሉ ነጻነት የተጻፈበት ቅዱስ ማኅፀን እንደምን ያለ ነው? በእኛ ሠልጥኖ የነበረ ሞትን የሚቃወመው የጦር ዕቃችን (ክርስቶስ) ያደረበት ብሩክ ማኅፀን እንደምን ያለ ነው? እንደ ዕፀ ሠሉስ (ማክሰኞ እንደተፈጠሩት ዕጽ) ያለ ዘር በባሕርዩ ሁሉን በሚያስገኝ በመንፈስ ቅዱስ ጌታን ያስገኘችልን የተመረጠች ገራህት (ማርያም) እንደምን ያለች ናት? እግዚአብሔር እንደ ቸርነቱና እንደ ይቅርታው እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ለማገልገል ሥጋን ለብሶ ባሕርዩ ሳይለወጥ ታላቅ ካህን የሆነበት መቅደስ እንደምን ያለ ነው? /ሃይማኖተ አበው. 112፡23/
ይቆየን! 
(ሳምንት ይቀጥላል!)

7 comments: