Pages

Thursday, August 2, 2012

ከማን እንማር? በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ!


  የትሕትናን ነገር ከወዴት እንፈልጋት? ከወዴት እናግኛት? ከማንስ እንማራት? ወደ ግብረ ገቦች ከተማ፣ ወደ ቅዱሳኑ በዓት፣ ወደ ተራራዎቹ፣ ወደ ዱር ዋሻው፣ ወደ ጋራውና ሸንተረሩ  እንሂድን? አዎ ወደዚያ እንሂድና የትሕትናን ብዛት፣ የትሕትናን ዋጋ፣ የትሕትናን ክብር ከመነኰሳቱና ከመነኮስያቱ ዘንድ እንመልከታት፤ መመልከት ብቻም ሳይሆን እኛም ገንዘብ እናድርጋት፡፡

  ወደዚያ ስንሄድ ቅዱሳኑ ግማሾቹ የሞቀ ወንበራቸውን (ሥልጣናቸውን)፣ ግማሾቹ የሞቀ ሀብት ንብረታቸውን ትተውና ንቀው ሁለንተናቸውን ዝቅ አድርገው በአለባበሳቸው፣ በአኗኗራቸው፣ በአገልግሎታቸውም ትሕትናን ሲለማመዷት ሲኖሯት እናገኛቸዋለን፡፡

 የትዕቢት ሐሳብ፣ ያማረ ልብስን የመልበስ ሐሳብ፣ የተዋበ ቪላን የመሥራት ሐሳብ፣ ብዙ ሠራተኞችን የማስተዳድር ልቡና እንዲሁም ሌሎች ወደ ትዕቢት የሚወስዱ ነገሮች በእነዚህ ቅዱሳን ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ እነርሱ ራሳቸው እሳቱን ያቀጣጥላሉ፣ እነርሱ ራሳቸው ምግባቸውን ያበስላሉ፣ እነርሱ ራሳቸውም የመጣውን እንግዳ ያስተናግዳሉ፡፡

 በእነዚህ ቅዱሳን ዘንድ የሚሳደብ የለም የሚሰደብም የለም፤ ትእዛዝ የሚቀበል የለም ትእዛዝ የሚሰጥም የለም፤ ከዚያ ይልቅ ሁሉም አገልጋዮች ናቸው፡፡ የመጣውን እንግዳ እግሩን ለማጠብ ይሽቀዳደማሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉም አስቀድመው የሰውዬውን ማንነት አይጠይቁም፡፡ ባርያም ይሁን ጌታም ይሁን በእነርሱ ዘንድ ልዩነት የለውምና፡፡ ሰው መሆኑ በቂያቸው ነውና፡፡ በእነርሱ ዘንድ ታላቅ የለም ታናሽም የለም፡፡ ለምን? ማወቅ ተስኖአቸው ተደነጋግሮአቸው ነውን? በፍጹም! ያንን የሚመለከቱበት ልብ ያንን የሚያደርጉበት ሕሊና ስለሌላቸው እንጂ፡፡ ከእነርሱ አንዱ በጣም ታናሽ ነኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ሌሎቹ እንደዚያ ታናሽ ነው ብለው አይመለከቱትምና፡፡ እነርሱ ራሳቸው ከእርሱ በታች ታናሽ እንደሆኑ የሚያስቡ ናቸውና፡፡

 ለሁላቸውም አንድ ማዕድ አላቸው፡፡ አገልጋዩም ተገልጋዩም አንድ ዓይነት ምግብ፤ አንድ ዓይነት ልብስ፤ አንድ ዓይነት በዓት፤ አንድ ዓይነት የአኗኗር መርሕ አላቸው፡፡ ትንሹን ሥራ የሚሠራ እርሱ በሁላቸውም ዘንድ ታላቅ ነው፤ የከበረ ነው፡፡ ይህ የእኔ ነው ያም የአንተ ነው የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ ለብዙ ሰዎች መጥፋት ምክንያት ለብዙ ዓለማቀፍ ጦርነቶች መነሻ የሆነው ይህ አገላለጽ (ይህ የእኔ ነው ይህ የአንተ ነው የሚል አገላለጽ) በእነርሱ ዘንድ ቦታ ካጣ ሰነባብቷል፡፡
 አንድ ዓይነት መዓድ፣ አንድ ዓይነት ልብስ፣ አንድ ዓይነት በዓት፣ አንድ ዓይነት የኑሮ መርሕ ስላላቸው ትደነቃላችሁን? ምን ይሄ ብቻ? ልባቸውም አንዲት ናት፤ ነፍሳቸውም አንዲት ናት፡፡ በተፈጥሮ እንዲያ ሆኖ አይደለም፤ በፍቅር ስለተሳሰረ እንጂ፡፡ አንዲት ነፍስ ካለቻቸውስ እንደምን አንዱ የበላይ አንዱ የበታች አድርጎ ሊያስብ ይችላል? አንዲት ነፍስ ለራሷ እኔ የበላይ ነኝ አንቺም የበታች ነሽ ልትል ትችላለችን? በፍጹም!

 በእነዚህ ቅዱሳን ዘንድ ባዕለ ጸጋ የለም ደሀም የለም፤ ክቡር የለም ሕሱርም የለም፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ከሌለስ ትዕቢትና ኩራት እንደምን መግቢያ ቀዳዳ ሊያገኙ ይችላሉ? በእውነቱ እነዚህ መነኰሳት መነኰሳይያትም ታናናሾችም ታላላቆችም ናቸው፡፡ ሆኖም ግን አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ይህ ነገር ለእነርሱ አይታያቸውም፡፡ ታናሽ
ነኝ ብሎ የሚያሰበው መነኰስ ማንም ታናሽ ነህ ብሎ የሚዘልፈው ስለሌለ እንደተናቀ አያስበውም፡፡ ይህን ይማሩ ዘንድ ሁሉም ትሑታን ናቸውና፡፡ በቃልም በገቢርም ይህን ያደርጉ ዘንድ የሚቻኰሉ የሚፋጠኑ ናቸውና፡፡ …

 ድለላ፣ ሽንገላ፣ በውሸት መካብ እዚያ ቦታ የለውም፡፡ ምን ማለት እንደሆነ ራሱ አያውቁትም፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን ሁሉም አንድ ስለሆኑ እንዲህ ያለ ነገር በእነርሱ ዘንድ የለም፡፡…
 ሁል ጊዜ ለሥራ የፈጠኑ ናቸው፡፡ አንዱ መሬት ይቆፍራል፤ አንዱ ውኃ ያጠጣል፤ አንዱ ዘንቢል ይሠራል፤ አንዱ ሽመናን ይሠራል፤ ሌሎቹም የተለያዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ ሁሉም እንዲህ ያለ ሥራ መሥራታቸው ትሑታን ይሆኑ ዘንድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎላቸዋል፡፡ እነዚህ ሥራዎች የሚያስታብዩ አይደሉምና፡፡ ስለዚህ ትሕትናን መለማመድ ለእነርሱ ቀላል ነው፡፡ ለእኛ ልበ ትሑታን መሆን የሚከብደን ያህል ለእነርሱ ቀላል ነው፡፡

 አጸዱ ሲንቀሳቀስ፣ አራዊቱ ሲጮሁ፣ ወፎች ሲበሩ፣ ዛፎች ሲወዛወዙ እንዲሁም የነፋስን ሽውታ ብቻ የሚሰማ ሰውስ እንዴት የትዕቢት ነገር ሊታሰበው ይችላል?

 ተወዳጆች ሆይ! “ታድያ እኛ እዚህ ከተማ እየኖርን ይህን እንዴት መኖር እንችላለን?” የምትሉኝ አትሁኑ፡፡ አብርሃም በከነዓናውያን መሀል እየኖረ “እኔ አመድና አፈር ነኝ” ብሏልና /ዘፍ.18፡27/፤ ዳዊት በሕዝብ መካከል እየኖረ “እኔ ግን ትል ነኝ፤ ሰውም አይደለሁም” ማለትን ተችሎታልና /መዝ.22፡6/፤ ሐዋርያው በዓለም መካከል እየኖረ “እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝ” ማለትን ተችሎታልና /1ቆሮ.15፡9/፡፡ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች አርአያዎች እያሉልን እንደምን “አይሆንልንም፤ አይቻለንም” እያልን ምክንያት እንሰጣለን? እነዚህ ቅዱሳን በፊታችን እንደተገለጡ መጻሕፍት ናቸው፡፡

 ታድያ የማንሻሻለው ስለምንድነው? ገድላቸውን አላነበብንምን? በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ዜና ሕይወታቸውን አላነበብንምን? በእውነቱ “አልሰማንም” የምንል ከሆነ ይህ ራሱ በጣም ያሳፍራል፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ጩኸቷ ይሄ ነውና (እንማርበት ዘንድ የቅዱሳንን ገድል በየዕለቱ ትናገራለችና)፡፡

 “እነዚህ አሁን ያልከን ቅዱሳን እኮ በአጸደ ሥጋ ያሉ አይደሉም፡፡ እንደምን ታድያ ሕይወታቸውን በተግባር ማየት እንችላለን?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ በእውነቱ አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ገድሎቻቸውን በማንበብ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ያነበባችሁትን በተግባር ለማየት ደግሞ ከላይ ወደነገርኳችሁ የቅዱሳን ከተማ ሂዱ፡፡ ኑ ተከተሉኝና ወደነዚህ ቅዱሳን ልውሰዳችሁ፡፡ በሕይወታችሁ ብዙ ጠቃሚ ነገርን ትማራላችሁና ኑ ተከተሉኝ፡፡ ኑና ጽድቃቸው በምድር ላይ ሁሉ ወደሚያበራው መነኰሳት ልውሰዳችሁ፡፡ በዚህ በረሐ መኖራቸው፣ በየጋራውና በየሸንተረሩ መኖራቸው ይህች ዓለም ጊዜአዊ ድንኳን መሆኗን በተግባር ወደሚያሳዩን ኑ እንሂድ፡፡ ሀገራችን ሰማይ መሆኑን ለማረጋገጥ ወደነዚህ አበው ወእማት እንሂድና የሚኖሩበትን በዓት እንመልከተው፡፡

 ጽሞናንና ተመስጦን የመንፈስም መታደስ ወደቤታችን ይዘን እንድንመጣ ኑና አብረን እንሂድ፡፡ ማዕበል ንውጽውጽታ ከበዛበት መኖርያችን ወደዚያ የጸሎትና የትሕርምት ቦታቸው እንሂድና ትንሽ እንረፍ፡፡ ፍቁራን ሆይ! አዘውትረን ወደ ገዳማቶቻቸው እንሂድና በጸሎታቸው ተባርከን፣ በምክሮቻቸው ተጠግነን፣ ትሕትናቸውን ተምረን በዚህ ዓለም ሳለን መልካም ሕይወትን በሚመጣው ዓለምም ዘላለማዊ ሕይወትን የምንወርስ እንሁን፡፡

ይህን እንድናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!

7 comments:

  1. egziabher yebarke kale hiwoten yasemalen

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይውት ያሰማልን በ የገዳማቱ የምናየው እውነታ ነው.

    ReplyDelete
  3. kale hiwot yasemalin

    ReplyDelete
  4. kale hiwoten yasemalen! Egziabher yestilen!
    አጸዱ ሲንቀሳቀስ፣ አራዊቱ
    ሲጮሁ፣ ወፎች ሲበሩ፣ ዛፎች
    ሲወዛወዙ እንዲሁም የነፋስን
    ሽውታ ብቻ የሚሰማ ሰውስ እንዴት
    የትዕቢት ነገር ሊታሰበው ይችላል?
    ተወዳጆች ሆይ! “ታድያ እኛ እዚህ
    ከተማ እየኖርን ይህን እንዴት
    መኖር እንችላለን?” የምትሉኝ
    አትሁኑ፡፡ አብርሃም በከነዓናውያን
    መሀል እየኖረ “እኔ አመድና አፈር
    ነኝ” ብሏልና /ዘፍ.18፡27/፤ ዳዊት
    በሕዝብ መካከል እየኖረ “እኔ ግን
    ትል ነኝ፤ ሰውም አይደለሁም”
    ማለትን ተችሎታልና /መዝ.22፡6/
    ፤ ሐዋርያው በዓለም መካከል
    እየኖረ “እኔ ከሐዋርያት ሁሉ
    የማንስ ነኝ” ማለትን
    ተችሎታልና /1ቆሮ.15፡9/፡፡
    እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች
    አርአያዎች እያሉልን እንደምን
    “አይሆንልንም፤ አይቻለንም”
    እያልን ምክንያት እንሰጣለን?
    እነዚህ ቅዱሳን በፊታችን
    እንደተገለጡ መጻሕፍት ናቸው፡፡ asteway lebona yesten!

    ReplyDelete
  5. kale hiwot yasemalen

    ReplyDelete
  6. ENEZIH KIDUSAN BEFITACHN ENDETEGELETU METSAHFT NACHEW! ABAT HOY YHN YETEGELETE METSHAF ENANEB ZEND ERDAN! Amen.

    ReplyDelete
  7. ጌታ ሆይ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን? ሉቃ 13:22-35
    በአገራችን የተለመደ ቀልድ አለ:: ሰውዬው ገሃነም ሲወርድ የንስሐ አባቱን ቀድመው ወርደው ያገኛቸዋል:: ደንግጦ አባቴ እርሶም እዚህ ሲላቸው እርሳቸውም ልጄ ዝም ብል ብፁዕ አባታችንም እዚህ ናቸው በማለት ጳጳሱም እዚህ መሆናቸውን ነገሩት:: ቀልድ ነው ነገር ግን ከፍ ያለ ቁም ነገር የያዘ ቀልድ ነው:: ለምዶብን የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድራዊ መመዘኛዎችና በአፍአዊ ድርጊቶች ለማስቀመጥ እንሞክራለን:: በመሆኑም ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር ቤት ሥፍራ የምንሰጣቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ አንዳችም ቦታ የሌላቸውን ነው:: በዚህ ቦታ ጌታ ከባድ ጥያቄ ተጠይቆአል:: የሚድኑት ጥቂቶች ናቸውን? ጌታ የመለሰላቸው በሁለት መንገድ ነው:: አንደኛ በሩ ጠባብ ስለሆነ ተጋድሎ የሚጠይቅ ነው:: ምን ዓይነት ተጋድሎ ብለን ብንጠይቅ መልሱ በንስሐ ራስን መመርመርና በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ መደገፍ ነው:: ሆኖም ግን ብዙዎች ወደዚያ የመዳን ሥፍራ ለመግባት ፈልገው እንደማይሳካላቸው ይነግረናል:: የቃል ኪዳን ልጆች ሆነው ከጸጋው ብርሃን ተቁዋዳሾች የሆኑ ማለትም ቃሉን የሰበኩ የዘመሩ በውጭ ሲጣሉ በአንጻሩ ደግሞ አመዛኙን የእድሜ ዘምናቸውን በኃጢአትና በዝሙት ያሳለፉ አመንዝራዎችና ቀራጮች እነዚያን የሃይማኖት ሰዎች ቀድመው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ይገኛሉ:: እድሜ ልካቸውን ስመ እግዚአብሔርን ሲጠሩ የነበሩትን አላውቃችሁም እናንት አመጸኞች ከኔ ወግዱ ሲላቸው እነዚያን ደካሞች የሥነ ምግባር ምስኪኖችን ግን እናንት ቡሩካን ይላቸዋል:: ልዩነቱ ምንድነው ብንል ንስሐ ነው:: ፊተኞች ኋለኞች የሆኑት የተከፈተላቸውን የጸጋና የምህረት በር በሃይማኖተኝነት ትምክሀት በሥሥትና በትዕቢት ስለዘጉት ነው:: ዓይናቸው በሌሎች ሰዎች ኃጢአት ላይ ስለሆነ የራሳቸውን ኃጢአት ለማየት አልቻሉም::

    ይህ የጌታ ማስጠንቀቂያ ምን ያሳስበናል? መለስ ብላችሁ እንደገና ጥቅሱን አንብቡት:: ጥያቄው የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው ወይ? ነው:: ጥቂት ያደረገው የብዙዎች በቀላሉ መንገድ መሄድ ነው:: ማስመሰል ቀላል ነው:: የባህርይ ለውጥ ከባድ ነው:: የባህርይን ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ከባድ ስልሆነብን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሊሰጠን ቃል ተገብቶልናል:: በመሆኑም በተከፈተውና ለእኛ በተሰጠን የጸጋና የምህረት ደጃፍ እንለፍ:: በጠባቡ መንገድ እንጋደል:: ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ( The Orthodox Life)kemibal blog yewesedkut new

    ReplyDelete