Pages

Sunday, August 5, 2012

ነገረ ዕርገት ዘድንግል ማርያም!


    ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም)፡- አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ነገረ ዕርገቷን እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እንናገራለን፡፡

  ተወዳጆች ሆይ! “አቤቱ ወደ ማረፍያህ ተነሥ፤ አንተም የመቅደስህ ታቦትም” እያለ መሰንቆውን ንጽሕት ክብርት ስለምትሆን ስለ ድንግል ማርያም ሲደረድር፣ ሲዘምር፣ ሲያመሰግን ስሙት፡፡ ሁሉም ምሳሌዎች ይገቧታልና ነብያትም መዝሙረኛውን መስለው በብዙ ሕብረ አምሳል አመስግነዋታል፡፡ ፍቁራን ሆይ! ከአዳም ጀምረው እስከ ዛሬ ድረስ በየዘመኑ የተነሡት ሁሉ እንደምን እንደተባበሩ የምንሰማ እንሁን፡፡ ነቢዩ ሰሎሞን “በየትውልዱ በጻድቃን ሕሊና ትመላለሳለች” እንዳለ ሁሉም መዋትያን ቢሆኑም ምስጋናዋ ግን አይሞትም፡፡ ልጇ ወዳጇም ምስጋናዋን በየዕለቱ ያዘጋጃል፤ የወንጌልን መንገድ በሚያቀኑ ልጆቹም ምስጋናዋን በአእምሮአቸው ሹክ ይላቸዋል፡፡ ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማሕፀኗ የተሸከመች ናትና፤ ኪሩቤል ሱራፍኤል ዙፋኑን በረዐድና በመንቀጥቀጥ የሚሸከሙትን ሰማያዊ መለኮት በዠርባዋ ያዘለች በክንዷም የታቀፈች ናትና፤ ሰማይና ምድር ከፊቱ የሚሸሹለትን የባሕርይ አምላክ እርሱን ከንፈሮቹን የሳመች ናትና፤ ፍጥረታትን ሁሉ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግበውን እግዚአብሔር ወልድ የድንግልና ጡቶቿን ያጠባች ናትና ብጽዕት፣ ንዕድት፣ ክብርት ነሽ ይሏት ዘንድ ሹክ ይላቸዋል፡፡ አዎ! ሥጋቸውን፣ ነፍሳቸውንና ሕሊናቸውን ከኃጢአት ያነጹት ሰዎች ሁሉ ክብራቸው ከድንግል ማርያም ክብር ጋር አይተካከልምና “ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስም የተባረከ ነው ብሎ እንዳመሰገነሽ እኛም ዋሕድ ቃል እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ፣ ከነፍስሽ ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ሆኗልና ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር፣ ምልዕተ ውዳሴ እመቤታችን ሆይ ደስ ይበልሽ” እያሉ ውዳሴዋን ይናገራሉ፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን በቅዱሳን ላይ የቅዱሳን ቅዱስ እግዚአብሔር ያድራል፤ ከእመቤታችን ግን በግልጽ ተወለደ፡፡ ቅዱሳንን ይመግባቸዋል፤ ድንግል ግን ሁሉን የሚመግበውን በጡቶቿ አሳደገችው፡፡ ለቅዱሳን ኃይላቸው እርሱ ነው፤ ድንግል ግን በጀርባዋ አዘለችው፡፡

   ይህች ንጽሕት ይህች ቅድስት በዚህች በእንግድነት ዓለም 64 ዓመት ቆይታ ዐርፋለች፡፡ ሆኖም ግን ባረፈችበት ቀን ጥር 21 በዚህ ምድር የተቀበረች አይደለችም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በክብር ለመሸኘት በጉዞ ላይ ሳሉ አይሁድ “ቀድሞ ልጅዋን ‘በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በ40ኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል’ እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብንል እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች ዐረገችም እያሉ ሊያወኩን አይደሉምን? እንግዲያውስ ኑና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥል” ብለው በክፋት ተነሣሱ፡፡ በተለይም ደግሞ በእመቤታችን ላይ በክፋትና በተንኰል ከተነሣሱት ከእኒህ አይሁድ መካከል ታውፋንያ የተባለው አማናዊት ታቦተ እግዚአብሔር የሆነችውን የድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ ያረፈበትን አልጋ ለመያዝ እጁን በድፍረት ዘረጋ፡፡ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ግን የአሚናዳብ ልጅ ዖዛ በታቦተ ጽዮን ላይ በድፍረት እጁን በመዘርጋቱ ምክንያት ተቆጥቶ እንደቀጣው ሁሉ /2ሳሙ.6፡6/ ታውፋንያንም በሰማያዊው መልአክ ሰይፍ እጁን ቀጣው፡፡ እመቤታችንንም ሐዋርያት ከተሸከሙት አልጋ ከፍቁረ እግዚእ ከዮሐንስ ጋር ነጠቃት፡፡ ከገነትም አደረሳት፡፡ በዚያም በዕፀ ሕይወት ስር ተቀመጠች፡፡ ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ወንድሞቹ ወዳሉበት ኢየሩሳሌም ደረሰ፡፡ በጽኑዕ ረሀብና ጥም በትሕርምት ቆዩ፡፡ ካረፈች ጀምሮ እስከዚያች ዕለት እንደዚያ ቆዩ፡፡ ሁለት መቶ አራት ቀንም ጾመው ጨረሱ (ልብ ይበሉ! ከጥር 21 እስከ ነሐሴ 14 ቢቆጠር 204 ቀን ይሆናል፡፡ ከማዘን ከመጾም ባለፈ ሱባዔ ገብተው ስለ እመቤታችን ሁኔታ ፈጣሪያቸውን የጠየቁት ግን ከነሐሴ አንድ እስከ አስራ አራት ነው!)፡፡

 ከዚህ በኋላ በዚህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብሩህ ደመና ተቀምጦ ኃይላት (መላእክት) ሁሉ እያመሰገኑት ወደ እናቱ መጣ፡፡ ጻድቃን፣ ማኅበረ ነቢያት፣ ሰማዕታትም ሁሉ ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ በቀኙም የድንግል ማርያም ሥጋ ነፍሷም በእቅፉ ነበሩ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው እያሉም ኢየሩሳሌም ደረሰ፡፡ ቶማስ ግን ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ ጌታም፡- “ደቀ መዛሙርቴ ሆይ! ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ በአይሁድ በኒቆላውያን አማካኝነት በእናንተ ስለተደረገው ነገር አትፍሩ፡፡ ቂመኛ አይደለሁምና የእናቴን ሥጋ ወስዳችሁ ገንዙት፤ እንደ ሰው ሁሉም ቅበሯት፡፡ እኔም ሥጋዋንና ነፍሷን አዋሕጄ አሳርጋታለሁ፤ በረከቷም በእናንተ ላይ ይሁን” አላቸው፡፡

 ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ ለገናናነቱ ምስጋና አቀረቡ፡፡ ሥጋዋንም ወስደው በፍጹም ምስጋና ገነዟት፤ በተገነዘችበት ቦታ በቤተልሔምም ታላቅ ግርማ ሆነ፡፡ ፍጥረታት ሁሉም ምስጋና አቀረቡ፡፡

  የአዳም ልጆች በየነገዳቸው መጡ፡፡ “አቤቱ ፈጣርያችን ሆይ! ምእመናን ወደ ምታሳርፍበት መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ” እያሉ አመሰገኑ /መዝ.131፡8/፡፡ ከጧት እስከ ማታ እንዲህ ምስጋና ሆነ፡፡ ቅድሰት ድንግል ማርያምንም በጌቴሰማኒ ቀበሯት፡፡ ደቀመዛሙርቱ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ በሦስተኛው ቀንም ጌታችን እናቱን ነፍሷን ከሥጋዋ ጋር አዋሕዶ አነሣት፤ ከእርሱ ጋርም ከሦስተኛው ሰማይ በላይ አሳረጋት፡፡

  ቶማስም ከሀገረ ስብከቱ ከህንድ በደመና ተጭኖ ሲመጣ በአየር ባለው ደመና እመቤታችን ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛትና “ምን ሆንሽ?” አላት፡፡ እርሷም “ወንድሞችህ ገንዘው ቀበሩኝ መምህርህም አነሣኝና እነሆ እንደምታየው ወደ ቦታው አሳረገኝ፡፡ ከሞትሁ ሰባት ወር ከአስራ ስድስት ቀኔ ነው፡፡ እንደነገርኩህ በወንድሞችህ ተገንዤ ተቀበርሁ እነሆም ተነሣሁ፡፡ የዕርገቴ ቀንም እንደምትመለከተው ዛሬ ነው” አለችው፡፡

  ቶማስም “በምትገነዢበት ጊዜ ልጅሽ መጣን?” አላት፡፡ እርሷም “አዎ! በመላእክት ፊት ተገነዝሁ፤ ስለ እኔም ፍጥረታት ሁሉ አመሰገኑ” አለችው፡፡

  ቶማስም ከተባረከች እመቤታችን አንደበት ይህን በሰማ ጊዜ ተጨነቀ፤ ወዮልኝ እያለ አለቀሰ፡፡ “ኃጢአቴ ከወንድሞቼ ለየችኝ፤ ልጅሽ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ ጊዜ ከሁሉም በኋላ ታየኝ፡፡ በመጀመርያ ያዩትንም አልተቀበልኋቸውም፡፡ በዚህ ምክንያትም ሃይማኖተ ጎደሎ ተባልኩ፡፡ ዛሬም ኃጢአቴ ከሞትሽ ሰርግ በግንዘትሽ ከተደረገው መንፈሳዊ በረከት የጠፋሁ ሆንኩ” ብሎ ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ከሐዘኑ ብዛት የተነሣም ራሱን ያጠፋ ዘንድ ወደደ፡፡

 ድንግልም እጇን ዘርግታ ያዘችው፡- “ብትወድቅም ልጄ ካልፈቀደ ባልሞትህ ነበር፡፡ ነገር ግን ቶማስ ሆይ! ተስፋ አትቁረጥ፡፡ ተስፋ መቁረጥ ከኃጢአት ሁሉ ይበልጣልና፡፡ የንጹሐኑስ ተወውና ኃጢአተኞችም የመዳን ፍሬ የለንም ካሉ ጥፋቱ የከፋ ነው፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ሰው በእውነተኛነቱ ይመካ ዘንድ ይገባል፡፡ ኃጢአተኛም በኃጢአቱ ምክንያት የንስሐ ተስፋን የሚቆርጥ አይሁን፤ የእግዚአብሔር ሥራ ድንቅ ነውና፡፡ ነገር ግን ሰው የሆነ ሁሉ ሰውነቱን ዝቅ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር ምሕረት ይማጸን፡፡ በዚያም የእግዚአብሔር ማዳኑን ያያል፡፡ ቶማስ ሆይ! የልጄ ጥበብ ከባሕር ጥልቅ ይልቅ ጥልቅ ነውና ከሰጠመበት የሐዘን ባሕር ልቦናህ ይወጣ ዘንድ በቅጽበትም ይፈወስ ዘንድ ነገሬን ስማ፡፡ ልጄ ወዳጄ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ ጊዜ በኋላ የታየህ መጀመርያ እንደምትክድ በኋላ ግን እንደምታምን ስለሚያውቅ ነው፡፡ መጀመርያ መካድህ በኋላም ማመንህ ለክርስቲያኖች የሃይማኖታቸው ምሰሶ (ምስክር) ናት፡፡ አሁንም ከአንተ በቀር ትንሣኤዬን ያየ የለም” ብላ አጽናናችው፡፡ ይህን እንዲነግራቸውም ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን /መግነዟን/ ሰጥታው ዐረገች፡፡
 ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ “እመቤታችንን እኮ ቀበርናት” ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አንተ እንጂ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን?” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መቃብር ይዘዉት ሄዱ፡፡ ሆኖም ግን መቃብሯን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት ይሆን ዘንድ የሰጠችውን ሰበኗንም አሳያቸው፡፡ እነርሱም ሰበኗን ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡

 ሐዋርያትም “እርሱ (ቶማስ) ትንሣኤሽንና ዕርገትሽን አይቶ እኛ ለዚህ ዕድል እንዴት ሳንበቃ እንቀራለን?” በማለት አዝነው በዓመቱ ሁሉም ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በመጨረሻም ነሐሴ 16 ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን መንበር፣ ራሱን ሠራዒ ቄስ፣ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ረዳት ካህን፣ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ ዕርገቷን ለማየት አብቅቶአቸዋል፡፡  

  ይህን ሐዋርያዊ ትውፊት ተከትላ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዐበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ብዙዎች ምእመናንም ከቤታቸው ተለይተው፣ በመቃብር ቤት ዘግተው፣ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው፣ ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑ ፍቅርም ያሳያሉ፡፡ በመጨረሻም “ተንሠአት እሙታን ማርያም ድንግል ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል- ልጇ ወዳጇ ሙስና መቃብር ሳያገኘው መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሦስተኛው ቀን በሥልጣኑ እንደተነሣ ድንግል ማርያምም ሙስና መቃብር ሳያገኛት የልጇ ሥልጣን ኃይል ሆኗት በሦስተኛ ቀን ተነሣች” እያሉ ደስታቸውን ሐሴታቸውን እስከ ነሐሴ 21 ቀን ይለዋወጣሉ፡፡   
 እመብርሃን ከልጇ ከወዳጇ ታማልደን! አሜን!!

2 comments: