Pages

Monday, September 3, 2012

እኔም አልፈርድብሽም- የዮሐንስ ወንጌል የ36ኛ ሳምንት ጥናት(8፡1-11)


 
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ ከሚያከብሩት የዳስ በዓል በኋለኛው ቀን “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፡፡ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወትን ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” ብሎ አሰምቶ ከነገራቸው በኋላ፣ አለቆቹና ካህናትም ክርክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ /7፡53/ “ወደ ደብረ ዘይት ሄደ” /ቁ.1/። ካስተማርን፣ ከገሰጽን፣ ከመከርን በኋላ የራሳችን የሆነ የጽሞናና የጸሎት ጊዜ ሊኖረን እንደሚገባ ሲያስተምረን አንድም ማደርያው በዚያ ነበርና ወደ ደብረ ዘይት ሄደ /St. John Chrysostom/፡፡

  ከዚያ ሲጸልይ አድሮም እንደ ልማዱ ገስግሶ ወደ መቅደስ ሄደ /ቁ.2/፡፡  የመልካም አገልጋይ ባሕርይ እንዲህ ነው፡፡ መልካም አገልጋይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል አገልግሎቱን በፍቅር ይፈጽማል፡፡ ስለዚህ ጌታ የሚወዳቸውን ልጆቹ ያገኝ ዘንድ ወደ ምኵራብ ገባ፡፡ “ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ”፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ “ሕዝቡም ሁሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው በመቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር” እንዲል ትምህርቱን ያስተምራቸው ጀመር /ሉቃ.21፡38/፡፡

   በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ሕዝቡ የጌታን ትምህርት ያደምጡ ዘንድ እንዴት በጧቱ እንደተሰበሰቡ አዩ፡፡ ውስጣቸውም በቅንአት ተቃጠለና ትምህርቱን ያደናቅፉ ዘንድ ስትሴስን ያገኟትን አንዲት ሴት አስረው ይዘዋት መጡ፡፡ አምጥተውም ጌታ ካለበት ጉባኤ መካከል አቆሟት /ቁ.3/፡፡ ከዚያም “መምህር ሆይ!” ይሉታል /ቁ.4/፡፡ መምህርነቱን አምነውበት አልነበረም /7፡47/፡፡ አመጣጣቸው ለተንኰል ስለ ነበር እንጂ፡፡ ስለዚህ “ይህች ሴት ስታመነዝር ስትሴስን ተገኝታ ተያዘች (አግኝተን ያዝናት)፡፡ ሙሴም እንደዚህ ያሉት (አንድ ወንድ ለአንድ ሴት፤ አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ይሁን የሚለውን ሕግ ተላልፈው ቢገኙ) እንዲወገሩ አዘዘን፤ አንተስ ምን ትላለህ (ምን ትፈርዳለህ)?” አሉት /ቁ.5/፡፡  እንደነርሱ ሐሳብ ይህች ሴት ስትሴስን ስለ ተገኘች በዚህ ምድር በሕይወት መኖር “የማይገባት” ሴት ነች፡፡ የሚደንቀው ግን ይዘዋት የመጡት ወደ ይቅርታ አባቷ ወደ እግዚአብሔር መሆኑን አለማወቃቸው ነው፡፡ ይዘዋት የመጡት በዓለም ላይ እንዲፈርድ ሳይሆን ዓለምን እንዲያድን ወደ መጣው ጌታዋ
መሆኑን አለመረዳታቸው ነው፡፡ ይዘዋት የመጡት እርሷን ብቻ ሳይሆን እነርሱም ጭምር በደሙ ሊገዛቸው ወደ መጣው አፍቃሪዋ መሆኑን አለመገንዘባቸው ነው፡፡ አልገባቸውም እንጂ ይዘዋት የመጡት ከቀድሞ ባሎቿ (ከአጋንንት) አፋትተው ከእውነተኛው የነፍሷ ሙሽራ ጋር ነበር /St. Jerome, letter to Eustochum, Letter 22:1/፡፡

  እንደ እነርሱ ሐሳብ (ሎቱ ስብሐትና) ጌታችን “ትደብደብ” ወይም “አትደብደብ” ከማለት ውጪ ሌላ መልስ የለውም በማለት ነበር፡፡ “ልትደበደብ አይገባትም” ቢል “የሙሴን ሥርዓት አፈረሰ” ብለው ለመክሰስ፤ “ትደብደብ” ቢል ደግሞ “የሰው ችግር ያሳዝነኛል ይላል፤ ደግሞም ተደብድባ ትሙት ብሎ በጭካኔ ይፈርዳል” ብለው ለማጣላት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው፡- “በእርሱ ላይ የሚከሱበት የሚያጣሉበት ምክንያት ለማግኘት እንጂ ስለ ሕጉ አዝነው አይደለም” የሚለን /ቁ.6፣ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱን ወደ መሬት ጐንበስ አደረገ፡፡ መሬት መሬቱንም ያይ ጀመር፡፡ ከዚያም አስቀድሞ አሥርቱን ትእዛዛት በጣቱ ጽፎ እንደሰጣቸው አሁንም ይህን ትእዛዝ መተላለፋቸውን ይገልጽላቸው ዘንድ በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንደ ቀድሞ በድንጋይ የጻፈው አይደለም፤ ከተመለሱ በቀላሉ ሊጠፋ ሊደመሰስ በሚችል በመሬት ላይ እንጂ፡፡ እነርሱ ግን አሁንም ቁመው ይጠይቁታል፡፡ መልሰው መላልሰውም “መልስ ስጠን እንጂ!” ይሉታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓይኑን ወደ እነርሱ ቀና አድርጎ፡- “ከእናንተ መካከል እርሷ የሠራችውን ኃጢአት ያልሠራ ሰው ካለ አስቀድሞ እርሱ ድንጋይ ይጣልባት፤ ከዚያ በኋላ እንደ ሕጋችሁ እንደ ሥርዓታችሁ ወግራችሁ ግደሏት አላቸው /ቁ.7/። እንደ ሕጋቸው አንድ ሰው ወንጀለኛ ሆኖ ከተገኘ አስቀድመው እጁን ወደኋላ አድረገው ያስሩታል፡፡ አንድ ዓይኑንም ይሸፍኑታል፡፡ ከዚህ በኋላ ከ10 እስከ 12 ሜትር ርዝመት ባለው ገደል አፋፍ ላይ ያቆሙታል፡፡ ቀጥለውም ሁለት የተመረጡ ምስክር የሚሆኑ ሰዎች ወንጀለኛውን በኃይል ገፍተው ወደ ገደሉ ይወረውሩታል፡፡ ወንጀለኛው እንዲህ ወደ ገደሉ ከተወረወረ በኋላ ካልሞተ ከምስክሮቹ አንዱ በትልቅ ድንጋይ አድርጎ ደረቱን ይመታውና ይገድሏል /Fr. Tadros Malaty, Commentary on the Gospel of John, pp384/፡፡

  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አሁንም ደግሞ ጐንበስ አለና በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ነበር /ቁ.8/፡፡ ከባቴ አበሳ ነውና ሁሉም የየራሳቸው የነፍሳቸው ኃጢአት ብቻ እያዩ እንዲያውቁ ያደርግ ነበር፡፡ “ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሆይ! ኃጢአታችሁ ከዚህች ሴት ኃጢአት የባሰ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ ታውቁት ትረዱት ዘንድም አሁን ሕሊናችሁን መርምሩ፡፡ ስለዚህ እናንተው ራሳችሁ ወንጀለኞች ሳላችሁ በዚህች ሴት ላይ የምትፈርዱ አትሁኑ፡፡ ይልቁንም እርሷን ከመውቀሳችሁ ከመክሰሳችሁ በፊት ራሳችሁን የምትወቅሱ ሁኑ፡፡ እርሷ ተወግራ እንድትገደል የምትፈርዱ ከሆነ ግን እናንተም ከዚያ ነጻ አይደላችሁም” ይላቸው ነበር /St. John Chrysostom/፡፡   

  እነርሱም ይህን ዘለፋ በሰሙ ጊዜ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና በፊት ከገቡት ጀምሮ በኋላ እስከ ገቡት ድረስ ወይም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድረስ አንድ አንድ እያሉ እየወጡ ሄዱ /ቁ.9/፡፡ “የሰው ኃጢአት እንገልጻለን ብለን የራሳችንን ኃጢአት አየን” ብለው ሹልክ ሹልክ እያሉ ወጥተው ሄዱ፡፡

 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ንጹሐ ባሕርይ ነውና (ከሳሽ አልነበረምና) ብቻውን ቀረ፡፡ ሴቲቱም ተፈርዶባታልና እዛው ቆማ ቀረች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓይኑን ወደዚያች ሴት ቀና አድርጎ እየተመለከተ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ፡- “አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርስዋም፡- “ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ” አለች። ኢየሱስም፡- “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” አላት /ቁ.10-11/።  እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “አንቺ ሴት! የመፍረድ ሥልጣን የእኔ እንጂ የሰዎች ሥልጣን አይደለም፡፡ በአንቺ ላይ መፍረድ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን አሁን ዓለም በእኔ እንዲድን እንጂ እፈርድበት ዘንድ አልመጣሁም /ዮሐ.3፡17/፡፡ ስለዚህ አልፈርድብሽም፡፡ ሂጂ! አሁን ኃጢአትሽን ይቅር ብዬሻለሁ! ሆኖም ግን ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ደግመሽ ኃጢአት ስንፍናሽን የምትደግሚ አትሁኚ” /ምሳ.26፡11፣ 2ጴጥ.2፡22፣ St. John Chrysostom/፡፡

 ተወዳጆች ሆይ! ይህን ትእዛዝ ስንቴ አፈረስነው? ስንቴስ ወደ ትፋታችን ተመለስን? አሁንም ቢሆን ግን የፍርድ ዙፋን ከመምጣቱ በፊት በጸጋው ዙፋን ፊት በንስሐ ልቆም ይገባናል፡፡ ያኔ ከምናፍር አሁን ብናፍር ይሻለናል፡፡ ያኔ ጥቅም የሌለው ዋይታና ለቅሶ ከምናለቅስ አሁንኑ በንስሐ እንባ ብናለቅስ ይሻለናል፡፡ ይህን እንድናደርግ አማኑኤል ይርዳን አሜን!!

3 comments:

  1. Betam astemari tsihuf new gin wedenisiha sinikerib mejemeriya erasachinin wedekedimo hatiyat lalememeles mazegajet alebin ye hatiyatin sir nekilen metal alebin yihen hatiyat sir yemibalewin degmo lemenkel gize wesaj yihonal ena enisiha sanigeba degmo mot yikedmenal.

    Hulem Egziyabheren yemileminew neger binor kehatiyat yemilakekibetin yetsena lib endisetegnina Nisiha endigeba new. Egziyabher yerasu egnan lemadireg haile alew ersu becherinetu wede ersu yakiriben. Amen.

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን! በጣም ጥሩ ትምህርት ነው:: ወንጌል እንዲህ ሲብራራ እንዴት ይጣፍጣል!

    ReplyDelete
  3. btaemi turu yehone xhuf new . can u post tgrinya more please if can gebrezabhier

    ReplyDelete