Pages

Tuesday, September 4, 2012

እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎችን ለመንግሥቱ ሌሎችን ደግሞ ለገሃነም ወስኗልን?


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አንዳንድ ወገኖች የሰው ዕድል ፈንታው ጽዋዕ ተርታው ከጻድቃን ወይም ከኩንኖች መሆን አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተወሰነ ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ቅድመ ውሳኔ /Predestination/ ሐሳባቸውም አስረጅ አድርገው የሚያቀርቧቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች አሏቸው /ሮሜ.911-21 ኤፌ.14/፡፡ ከዚህም በመነሣት ድኅነት የሚገኘው ከዘመናት በፊትእግዚአብሔር በወሰነው መሠረት እንጂ ሰው በሚፈጽመው ሥራ የማይሰጥ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እስኪ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ጉዳይ ምን ብላ እንደምታስተምርና የእነዚህ ሰዎች አስተምህሮ የሚያመጣው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተፋልሶ ምን እንደሆነ እንመልከት!

             1.አስቀድሞ ሁሉን ማወቅ ወይስ አስቀድሞ መወሰን?
 እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት እስከ ዓለም ፍጻሜ ሊሆን ያለውን ነገር ምንም ሳይሰወርበት ሁሉን ያውቃል፡፡ አንድ ሰው ከቅዱሳን ወገን አልያም ከኃጥአን ወገን እንደሚሆን አስቀድሞ ያውቃል /ሮሜ.828-30/፡፡ ሆኖም ግን የተወሰኑትን ለመንግሥተ ሰማያት የተወሰኑትን ደግሞ ለገሃነም ለኩነኔ አልፈጠራቸውም፡፡ እንዲህ ቢሆንስ ኖሮ እግዚአብሔር አንድስ እንኳ ይጠፋ ዘንድ እንደማይፈልግ ባለተናገረ ነበር /2ጴጥ.39/ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ለድኅነት መጥራት ባላስፈለገ ነበር /ማቴ.2819 ሮሜ.819/ ሰዎች ሁሉ ይድኑ እውነትንም ያውቋት ዘንድ ባልወደደ ነበር /1ጢሞ.24/፡፡ በመሆኑም ሰው ከእግዚአብሔር በተቀበለው ነጻ ፈቃዱ ተጠቅሞ ወይ ርትዕት በሆነች የሕይወት መንገድ ይጓዛል አሊያም የሞት መንገድ በምትሆን በኃጢአት መንገድ ይሄዳል፡፡ ድኅነት ለሁሉም የተሰጠ ቢሆንም የሰው ድኅነቱ በራሱ መሻትና የነጻ ፈቃድ ምርጫ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሄሬኔዎስ የተባለ አባትም፡- ጥቂቶች በተፈጥሮ ክፉ ቢሆኑ ሌሎችም መልካም ቢሆኑ መልካሞቹ ስለ መልካምነታቸው መልካም ሠሩ ተብለው ምስጋና የተገባቸው አይሆኑም፡፡ ሲፈጠሩ እንዲህ ሆነው ነውና፡፡ ክፉዎቹም ስለ ክፋታቸው ነቀፌታን ባላገኛቸው ነበር፡፡ ጥንቱንም ሲፈጠሩ እንዲህ ሆነዋልና ብሏል /Iraneus, Book IV, Chap.37/፡፡ 

             2. እግዚአብሔር አያዳላም ፍርዱም ርቱዕ ነው!
 እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት ሌሎችን ደግሞ ለገሃነም አስቀድሞ ወስኗል ማለት ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁንና እግዚአብሔር ያዳላል እንደማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ ታላቅ አምላክ፣ ኃያልም፣ የሚያስፈራም፣ በፍርዱም የማያዳላ፣ መማለጃም የማይቀበል ነው /ዘዳ.1017/ እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያዳላ በእውነት አየሁ /ሐዋ.1034/ ከእግዚአብሔር ዋጋችሁን እንደምትቀበሉ ታውቃላችሁ፤ ለክርስቶስ ትገዛላችሁና፤ የሚበድል ግን ፍዳውን ያገኛል እርሱም አያደላለትም ይላል /ቈላ.323/፡፡  

           3.አስቀድሞ መወሰን አለ ከተባለ ትእዛዛት ለምን ተሰጡ?
 እግዚአብሔር የተወሰኑትን ሰዎች ለመንግሥተ ሰማያት የተወሰኑትን ደግሞ ለገሃነም ፈጠረ ከተባለ ሰዎች በአእምሮ ጠባይ መሪነት፣ በሥነ ፍጥረት አስተማሪነት፣ በሕገ ልቡና አዋቂነት መልካም ሥራ መሥራት
ሲያቅታቸው በየዘመናቱ ነቢያትን፣ ነገሥታትን፣ ካህናትን እያስነሣ መላኩ (ሎቱ ስብሐትና) ለከንቱ ነውን? ሐዋርያትና ሊቃውንት እንዲሁም ሰባክያን ለትምህርት ለተግሳጽ መላካቸው ምን ፋይዳ አለው /ማቴ.2819 2ቆሮ.58/? 

         4. የተወሰኑትን ቀድሞ ለድኅነት ከወሰነ ሥጋዌ አድልዎ ነበረበታ!
አስቀድሞ መወሰን ከሥጋዌው ዓላማ ጋር የሚቆም አይደለም፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸዋትወ መከራን ተቀብሎ የሞተው ለመላው ዓለም እንጂ ለተወሰኑት ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ይህን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡- በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው አንድያ ልጁን ለቤዛ ዓለምና ለካሳ ሰጠ /ዮሐ.316/ እርሱም የኃጢአታችን ማስተሥርያነው ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም ነገር ግን ለዓለም ሁሉ ኃጢአት እንጂ /1ዮሐ.22/ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ /1ጢሞ.25/ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ /2ቆሮ.514/፡፡ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኰትም፡- የጽድቅ ልጅ ለሁሉም ተገልጧል፤ ለሁሉም ኑሯል፤ ለሁሉም ሞቶ ተነሥቷል በማለት ሥጋዌው ለሕዝብም ለአሕዛብም መሆኑን ገልጧል፡፡ ምንም እንኳን ድኅነት ለሁሉም የተሰጠ ቢሆንም የመስቀሉ ጠላቶች ሆነው አሻፈረኝ ላሉት ቅጣት ቢያገኛቸው የፈቃድ ምርጫቸው ውጤት ስለሆነ ሓላፊነቱን የሚወስዱ ራሳቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የሚያስረክበው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም በመገረፉ ቁስል ተፈወስንአለ እንጂ አስቀድሞ ለመንግሥተ ሰማያት የወሰናቸውን በመገረፉ ቁስል ፈወሳቸው አላለም /ኢሳ.535/፡፡  የዕዳ ደብዳቤአችንን የቀደደው የሁላችንም እንጂ ለተወሰኑት ሰዎች ብቻ አይደለም /ቈላ.214/፡፡ እንኳንስ ሰዎች ሰይጣንም ለገሃነም የተፈጠረ አይደለም፡፡ 

         5. እግዚአብሔር በንስሐ የተመለሱትን ይቅር ማለቱስ?
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ንስሐን መስጠቱ ኃጢአትን በመውደዱ አይደለም፡፡ ሰውን በመውደዱ እንጂ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ኃጥእ ከክፉ ሥራው ተጸጽቶ ከተመለሰና ንስሐ ከገባ ይቅር እንደሚባል ይናገራል /ሕዝ.3314-17 ኤር.187-8 ሚል.57 ያዕ.48/፡፡ በራሳቸው ክፉ ምርጫና በኢተነሳሒ ልቡናቸው ምክንያት ብዙዎች የውርደት ዕቃ እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዘለአለማዊ ቅጣትን አስገኘ አንልም፡፡ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጥእ ምክንያት በሰማይ ደስታ እንደሚሆን ነግሮናልና፡፡ ከቀደመ ክፉ ግብራቸው ተጸጽተውና ተመልሰው ምሕረትን ያገኙ ብዙ ሰዎች አሉ /2ዜና.331-6/፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር የበደለውን በንስሐ ወደ ክብር ዕቃነት የሚመልስ ከሆነ የቅድመ ውሳኔ ትምህርት ተአማኒነት ወዴት አለ? ተወዳጆች ሆይ! መዳናችን ወይም መኰነናችን በእኛ የፈቃድ ምርጫ የሚወሰን መሆኑን ከተመለከትን ዘንዳ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን ሐሳብ አንቀበለው፡፡ 

         6.ቅድመ ውሳኔ አለ ከተባለ ነጻ ፈቃድ መሰጠቱ ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንዲህ ይላል፡- ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ። በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ። ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም ፈጽማችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመናችሁን አታስረዝሙም። በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ /ዘዳ.3015-19/ እጅህን በመረጥኸው ትጨምር ዘንድ እነሆ እሳትንና ውኃን አኖረልህ፤ ሕይወትና ሞትም በሰው ፊት ናቸው ከእነርሱም የመረጠውን ይሰጡታል /ሲራ.1511-17/ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንድ በእግዚአብሔር ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡ ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው፤ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም /ዮሐ.318-20/፡፡ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ከሌለው ለሚሠራው ሥራ ተጠያቂ አይሆንም፡፡

እንግዲያውስ እነዚህንና ተመሳሳይ አስረጂዎችን ይዘን እግዚአብሔር ሰዎችን አስቀድሞ ለጽድቅ ወይም ለኩነኔ ወስኖአቸዋል ከማለት እንጠበቅ፡፡

   ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
(ዋቢ ድርሳን፡- ሐመረ ተዋሕዶ- የሐመር መጽሔት ልዩ ዕትም፣ 2001 .)     

13 comments:

  1. I read it all carefully and I get a good knowledge especially before this time i raised one question for you it related with this topic i hope u remember it. And now i get the right answer. God bless you.

    ReplyDelete
  2. Egziabher yakbirlin.betam tiru mabrariya new.

    ReplyDelete
  3. ምኞቴ ጥያቄዎቼን ለህዝብ እንድታስነብብልኝ ሳይሆን እንደተገለጸልህ መጠን መልስ እንድትሰጥበት ነው፡፡

    ሰው ነጻ ፈቃድ እንዳለው አምናለሁ ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ደግሞ በራሱ የሚመርጣቸውና የራሱን መንገድ የሚያስዛቸው አሉ ፡፡ አስረጅዎቼን ከወንጌል ተመልከትልኝ ፡-

    1. ጌታ ከዝሙት ስለመታቀብና ስለ ጃንደረባነት በሚያስረዳበት ወቅት “ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥” ማቴ 19፡ 11–12 /የእግዚአብሔር ምርጫና ስጦታ እንዳለበት ልብ በልልኝ/
    2. ሐዋርያው ጳውሎስም ገና ሳይወለዱ በማኀፀን ህይወት ስላለው መመረጥ ሲገልጽ “ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለላት። ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።” ሮሜ 9 ፡ 12 – 13
    3. አሁንም ሐዋርያው ለጌታ ማገልገል በመጀመሪያ ምርጫው አልነበረም ፡፡ ነገር ግን ከምድር አንደባሎ ፣ ከአፈር ደባልቆ ኃያልነቱን ስለገለጸለትና ማንነቱን ስላስረዳው ራሱን ኋላ ባርያ እስከማለት ደረሰ ፡፡ ሥራ 9፡ 3-6
    4. ያዕቆብና ዮሐንስ በመንበሩ ግራና ቀኝ ለመሆን ሲመርጡ ፣ ጌታ “በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም ብሏቸዋል ማር 1ዐ ፡ 39–4ዐ

    ስለዚህም የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ቢኖረውም ፣ እግዚአብሔርም ሊገለገልበትና ማንነቱን ሊገልጽበት ሲፈልግ ራሱ ይመርጣልም የሚል ግንዛቤ አለኝ ፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛልህ/ሽ የተከበርክ/ሽ “አነኒመስ”! ከላይ በዋናው ጽሑፉ ለመግለጽ እንደተሞከረው እግዚአብሔር በራሱ የሚመርጣቸው ሰዎች አስቀድሞ ስለሚያውቃቸው እንጂ አስቀድሞ ስለሚወሰናቸው እንዳልሆነ በቀላሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት እንችላለን፡፡
      1.በማቴ.19፡11-12 ያቀረብከውን ማስረጃ እስከመጨረሻ ብታነበው መልሱን እዛው ታገኘው ነበር፡፡ ምክንያቱም ወረድ ብሎ “ሊቀበለው የሚችል ይቀበል አላቸው” ይላልና፡፡ ይህም ማለት በተፈጥሮ (ከእናት ማኅጸን ጀምሮ) ወደዚህ የሕይወት መልካም የሕይወት መንገድ ቢመጡ ወይም ደግሞ ሌላ ሰው ምክንያት ሆኖአቸው ወደዚህ ጃንደረባነት የመጡ ቢኖሩ በምርጫቸው ይህን የሕይወት መስመር ሊቀበሉት እንደሚገባ ሲያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህ ከእናት ማኅጸን ጀምሮ የተሰለበ ሰው ካለ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ የተጠራለትን ዐላማ የመከተል ምርጫ አለው፡፡ ሰውዬው አልቀበልም ካለ እግዚአብሔር አያስገድደውም፡፡ ምክንያቱም “ሊቀበለው የሚችል ይቀበል” ነውና፡፡
      2.ሮሜ.9፡12-13 የጠቀስከውም ምን ማለት እንደሆነ ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር የያዕቆብንና የዔሳውን የሕይወት ፍጻሜ አስቀድሞ በማወቁ “ያዕቆብን ወደድሁ ዔሳውን ጠላሁ” ቢል ወሰናቸው አያስብልም፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ ከተወሰኑ ያዕቆብ መመስገን ዔሳውም መነቀፍ ባልተገባቸው ነበርና፡፡ አንተ ራስህ ወደህና ፈቅደህ ላልሰራኸው መልካም ነገር አትመሰገንም፤ ክፉውንም ወደህና ፈቅደህ ካልሠራህ አትነቀፍም፡፡ ከመጀመርያው በራስህ ምርጫ ሳይሆን በእግዚአብሔር ለዚያ ተወስነሀልና፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ አይደለም፡፡ በነጻ ፈቃዳቸው ተጠቅመው ያዕቆብና ዔሳው ፈቃደ ነፍሳቸው ወይም ፈቃደ ሥጋቸውን እንደሚያስበልጡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያውቃል፡፡ በሌላ አገላለጽ ዔሳው ነፍሰ ገዳይ እንደሚሆን ያዕቆብ ደግሞ ለወላጆቹ ታዛዥ፣ ታጋሽና መልካም ነገርን እንደሚወድ አስቀድሞ ያውቃል፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ዔሳው ለምስር ወጥ ብሎ ብኩርናውን እንደሚሸጥ ያውቃል፡፡ ያዕቆብ ደግሞ መንፈሳዊ በረከትን የሚሻ መሆኑን አስቀድሞ ያውቃል፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር ያዕቆብ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ መልካም ነገርን እንደሚወድ ስለሚያውቅ ወደደው፤ ዔሳው ግን መንፈሳዊ በረከቱን አቃልሎ ለምስር ወጥ እንደሚሸጥ ስለሚያውቅ ጠላው /ዘፍ.25፡27-37/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የበለጠ ሲያብራራልን እንዲህ ይላል፡- “ስለ አንድ መብል በኩርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ” ይላል /ዕብ.12፡16/፡፡ ዔሳው በራሱ ፈቃድ እንጂ እግዚአብሔር ሽጠው ብሎት መንፈሳዊ ብኩርናውን አልሸጠም፡፡ እግዚአብሔር ያዕቆብን መልካም የሆነውን ብቻ እንዲሠራ አላስገደደውም፤ ዔሳውንም ክፉ እንዳያደርግ አልከለከለውም፡፡ ከእናታቸው ማኅጸን ጀምረው የተመረጡት ሌሎች እነ ኤርምያስና እነ ዮሐንስ መጥምቅም ቢሆኑ ወደፊት እግዚአብሔርን ለማገልገል ያላቸውን በጎ ሕሊና በጎ ፈቃድ ስለሚያውቅ እንጂ አስቀድሞ ለዚያ ስለወሰናቸው አይደለም፡፡
      3.ጌታችን በዮሐ.16፡2 እንደተናገረው ሳውል ክርስቲያኖችን የሚያሳድደው እግዚአብሔርን ያገለገለ ስለመሰለው ነው፡፡ የሳውል ቅናት የፈሪሳውያንና የጸሐፍት ዓይነት ቅናት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እነዚያ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ሕዝቡ ከእነርሱ ይልቅ ጌታን ሰለወደደና ስላከበረ እነርሱም ክብራቸውን ስለቀነሰባቸው እንጂ ለሕጉ ተጨንቀው አልነበረም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ከኢየሩሳሌም ስንኳ ርቀው ሊሄዱ አልወደዱም፡፡ ሳውል ግን ውስጡ እግዚአብሔርን የማገልገል ቅናት ስላለው እስከ ደማስቆ ድረስ ወጣ፡፡ መኸል ላይ ግን ጌታ ብርሀነ ክብሩን ገለጠለት፡፡ ሆኖም ግን ጌታ “በእኔ እመን” ብሎ አላስገደደውም፡፡ ምርጫውን አቀረበለት እንጂ፡፡ በፍጹም ፍቅር በፍጹም ትሕትና “ስለምን ታሳድደኛለህ” አለው እንጂ፡፡ ክርስቲያኖችን ማሳደድ ክርስቶስን ማሳደድ ነውና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆችን ማሳደድ እግዚአብሔርን ማሳደድ ነውና፡፡ ከዚህ በኋላ ሳውል “ጌታ ሆይ ማን ነህ” ብሎ ጠይቋል፡፡ ጌታም እርሱ ኢየሱስ መሆኑን ነግሮታል፡፡ ሳውል ሲገባው ደግሞም ጌታ ያደረገለትን ነገር እያደነቀ “ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ” ብሎ ነጻ ፈቃዱን አሳልፎ ለጌታው ሰጥቶ ገለጠ (ታዘዘ)፡፡ ይህ ከአንድ ፈሪሳዊ የማይጠበቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ደም ከሚጠማቸው ከጸሐፍት ወገን የማይጠበቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ድምጽና ነጐድጓድ አላመኑበትም አልተጠቀሙበትም እንጂ ለእነዚያ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን መጥቶ ነበር /ዮሐ.12፡29/፡፡ ሳውል ግን ተጠቀመበት፡፡ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ከእነዚያ ይልቅ ተጠቀመበትና ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ ብሎ ፈቃዱን ገለጠለት፡፡ ስለዚህ ፍርሐቱን ብቻ እንዲህ እንዲል ያደረገው አይደለም፡፡ ነጻ ፈቃዱንም ጭምር እንጂ፡፡ ዛሬም እንዲህ ነው፡፡
      4. “በቀኝና በግራ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው ነው” ብሎ ሲናገርም አስቀድሞ ከመወሰን ጋር ሳይሆን አስቀድሞ ከማወቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እዚህ ጋር በግራና በቀኝ መቀመጥ ሲል ዝም ብሎ መቀመጥ አይደለም፡፡ ከዐውደ ንባቡ መረዳት እንደምንችለው በጌታ ግራና በቀኝ መሰቀልን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ መስቀል የተዘጋጀው ኢሳይያስ “ከዓመጸኞችም ጋር ተቈጥሮአልና” /ኢሳ.53፡12/ ብሎ እንደተናገረው ዓመጸኞች ተብለው ለተቀሉት ለሁለቱም ወንበዴዎች ነው፡፡ ሐዋርያው እንዳለው የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፡፡ ሁሉም ሰው በመሰቀል ብቻ የእግዚአብሔርን የሚወርስ አይደለም፡፡ የዘብዴዎስ ልጆች ፈቃዳቸውን ተጠቅመው መክሊታቸውን የሚያበዙበት እግዚአብሔርን የሚያከብሩበት መንገድ ሌላ ነው፡፡ በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴም ጌታን የሚያከብርበት ደግሞም መንግሥቱን የሚወርስበት መንገድ ሌላ ነው፡፡
      በአጠቃላይ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ እንደተጠበቀ ሆኖ ፈቃዳቸውን ሳይጋፋ እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለሚያውቅ ለዚያ አገልግሎት ይሾማቸዋል፡፡
      የእግዚአብሔር ፍቅር ከአንተ ጋር ይሁን አሜን!

      Delete
    2. ጌታ ይባርክህ ፤ እጅግ አመሰግንሃለሁ ፡፡

      Delete
  4. ውድ ወንድማችን ፣ ለመገንዘብ የሚያስቸግረኝን ርዕስ ስለሆነ ለማስረዳት የጀመርከው አሁንም ትገልጽልኝ ቢሆን በማለት ሌላውም ከመጽሐፍ ቃል የተዛመደ ጥያቄዬ እንዲህ ይነበባል፡-

    - ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርኩም ፡፡ ገላ 1፡ 15 – 16 /መዳረሻችን የምርጫችን ውጤት ብቻ ከሆነ ፣ በጸጋው የጠራኝ ፣ እግዚአብሔርም በወደደ ጊዜ ለምን ይለዋል ? ጸጋ ከሆነ ከምርጫችን ውጭ ያለ ስጦታ ስለሚሆን ማለቴ ነው /

    - በሮሜ 1፡1 መልዕክቱም ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ፣ ሐዋርያ ልሆን ተጠራሁ ይላል ፡፡/መጠራት ማለት አሁንም ከፈቃድ ውጭ የሆነ ትእዛዝ መሆኑን አያመላክተንም ? ሲጠሩ መልስ መስጠት ተገቢ ስለሚሆን ማለት/

    - በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። ….እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ ኤር 1፡ 5–8 ይኸን ጥበቡን እያስረዳን ለምን ከነውርደታችንና ኃጢአታችን ዝም ብሎ ይፈጥረናል ? ወይስ በቅድስና ተፈጥረን ሳለ ፣ ክፋትን በምርጫችን ከማኀፀን ከወጣን በኋላ እንለምዳታለን ማለት ይሆን ?

    በቅድሚያ ምስጋናዬ ትድረስህ

    ReplyDelete
  5. ሰላምህ ይብዛ ውድ ወንድሜ! በእርግጥ እንዳልከው ብዙ ሰዎች ለመገንዘብ የሚያስቸግራቸው ርእስ ነው፡፡ ቢሆንም አንድ ነገር እመክርሀለሁ (ከትሕትና ጋር)፡፡ ዋናውን ጽሑፍ አስቀድመህ ጸልይና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያመሳከርክ ከማስተዋል ጋር አንብበው፡፡ በመቀጠል አሁን እንዳብራራልህ የጠየቅከኝን ጥያቄዎች ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡
    -በገላ.1፡15-16 የጠቀስከው ጥቅስ እግዚአብሔር ጳውሎስን አስቀድሞ ሲፈጥረው ለወንጌል መምህርነት እንደሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ትላንት ለመግለጥ እንደሞከርኩት ጳውሎስ ገና ከሳውልነት ሲቀየር ፈቃዱን አሳይቷል፡፡ ማለትም ጌታችን በዮሐ.16፡2 እንደተናገረው ሳውል ክርስቲያኖችን ሲያሳድድ የነበረው እግዚአብሔርን ያገለገለ ስለመሰለው እንጂ እንደ ሌሎቹ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ከሌላ ዓላማ የመነጨ አልነበረም፡፡ የሳውልን ልብ የሚያውቅ ጌታም ሳውል ለምን ዓላማ እንደዚያ እንደሚያደርግ ስለሚያውቅ የተፈጠረበትን ዓላማ ይፈጽም ዘንድ አሳሰበው፡፡ ሳውልም “ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ” ብሎ ፈቃዱን አሳየ (ታዘዘ)፡፡ ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለበት ተነገረውና (ሐዋ.9፡6) ምንም ሳያመነታ (ከሥጋውና ከደሙ ጋር ሳይማከር) በፍጹም ልቡ በፍጹም ፈቃዱ ገና ከእናቱ ማኅጸን ሳለ ለተፈጠረለት ዓላማ ተዘጋጀ (ገላ.1፡15-16)፡፡ እኛም ብንሆን ገና ዓለም ሳይፈጠር የተፈጠርንበት ዓላማ አለ፡፡ ምርጫችንን ተጠቅመን እሺ ብለን እግዚአብሔርን ከታዘዝን እንደ ጳውሎስ እንባረካለን፡፡
    -ሮሜ 1፡1 ላይ የጠቀስከው ደግሞ ጳውሎስ ሐዋርያነትን ያገኘው “እኔ እንዲህ መሆን እፈልጋለሁ” ብሎ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥሪ በእግዚአብሔር ምርጫ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ የሚያስብልን ሁሉ መልካም ነው፡፡ ሆኖም ግን እግዚአብሔር ጳውሎስን ለሐዋርያነት ጠራው የሚሻለውን አሳየው እንጂ ሐዋርያ ሁን ብሎ አላስገደደውም፡፡ ጳውሎስም ራሱ እንደሚነግረን ከሥጋውና ከደሙ ጋር ሳይማከር በሙሉ ልቡ በሙሉ ፈቃዱ በመታዘዙና እሺ በማለቱ እንጂ ከፈቃዱ ውጪ እንደዚያ የሆነ አይደለም፡፡ ይህን የበለጠ ግልጽ ሲያደርግልን ራሱ እንዲህ ይላል፡- “ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ” /ሮሜ.1፡7/፡፡ ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ሁላችንም ለቅድስና ተጠርተናል፡፡ ነገር ሁሉም ግን ለዚህ ጥሪ እሺ የማለትም ያለ ማለትም ምርጫችን እንደተጠበቀ ነው፡፡ ጳውሎስ እሺ በማለቱ ሐዋርያ እንደሆነ እኛም ለተጠራንበት ዓላማ እሺ ብለን ብንታዘዝ ዛሬ የምናየውን ዓይነት ሰው (ግማሹ አማኝ ግማሹ የማያምን) ባላየን ነበር፡፡ ዛሬ ዓለሙን ሁሉ የምናየው ይህን የቅድስና ጥሪ ትቶ የራሱን ምርጫ ስለተከተለ እንጂ እግዚአብሔር ለዚያ ስለወሰነው አልነበረም፡፡
    -በኤር.1፡5-7 የጠቀስከው ጥቅስም ኤርምያስ ለወደፊት እግዚአብሔርን ለማገልገል የተመቸ ሕሊና እንዳለው ስለሚያውቅ እንጂ አስቀድሞ ለዚያ ስለወሰነው አይደለም፡፡ ፍጹም ልንረሳው የማይገባ ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ውስንነትና መለወጥ ባሕርዩ አይደለም፡፡ ጊዜና ቦታ አይወስነውም፡፡ ወደ ፊት ሊሆን ያለውን ድርጊት አሁን የተፈጸመውን ያህል በግልጥ ያውቃል፡፡ እንኳንስ እርሱ መንፈሱን የሰጣቸው ነቢያትም ወደፊት የሚሆነውን ያውቃሉ፡፡ ሁላችንም በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የምንፈጽመውን ያውቃል፡፡ ኤርምያስንም የመረጠው ከዚህ አንጻር ነው፡፡
    -በመጨረሻ የገለጽከው አገላለጽ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ መጽሐፍ “እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር”፤ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” ነው የሚለው /ዘፍ.1፡27፣ 31/፡፡ ስለዚህ ለውርደት የተፈጠረ ሰው የለም፡፡ አንተ እንዳልከው እኛው ራሳችን በምርጫችን የቅድስናን መንገድ፣ የእግዚአብሔር ትእዛዝ በመተው በፍቃዳችን ክፋትን እንለማመዳታለን እንጂ፡፡ የክፋት አባት የተባለው ዲያብሎስም ቢሆን /ዮሐ.8፡44/ እኛ ካልወደድን በቀር ክፋትን አያለማምደንም፡፡ አዳምና ሔዋን ወደውና ፈቅደው በሉ እንጂ ዲያብሎስ አስገድዶ አላጎረሳቸውም፡፡
    በአጠቃላይ ሁላችንንም እግዚአብሔር ንጹሐን አድርጎ ፈጥሮናል /ዘፍ.1፡27/፡፡ በፈቃዳችን ብንበድልም መልሶ እንዲሁ አድኖናል /ዮሐ.3፡16/፡፡ ዓለም ሁሉ (ሕዝቡም አሕዛቡም) ድኗል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም የሚጠበቅበት ነገር አለው፡፡ “አሜን” ብሎ በፈቃዱ ለተጠራለት ዓላማ እሺ ማለትን፡፡ የተጠራበት ዓላማም ግማሹ ለኩነኔ ግማሹ ለጽድቅ ሳይሆን ሐዋርያው እንዳለው ሁሉም “ቅዱሳን ለመሆን” ነው /ሮሜ.1፡7/፡፡
    የእግዚአብሔር ፍቅርና ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን አሜን!!

    ReplyDelete
  6. እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልህ ፡፡
    እንዲህ እንዳንተ የተማረው ወገን ለማናውቅና በጨለማ ላለነው የያዘውን ብርሃንን ቢያበራልን እጅግ እንጠቀም ነበር ፡፡ ያለመታደል ሆኖ ብዙ የሚያውቁት እንዲህ ከሚያስተምሩ ይልቅ ወቀሳን ስለሚያበዙብን ያስከፉናል ፤ በጥሞና እንዳናነብም ቃላቸው ያስቀይመናል ፡፡ እኔ በግል ንባብ መጽሐፍትንና የጸሐፊዎችን ትምህርት ለመረዳት የምታገል ተራ ምእመን ነኝ ፡፡ እንደናንተ በአእምሮና በዕውቀት ባይሆንም በዘልማድ ለተዋህዶ እምነቴም ቀናተኛ ነኝ ፡፡ በንባብ የተረዳሁትን ያህል ደግሞ ለሰዎች ለማካፈልም ባመቸኝ ሁሉ እሞክራለሁ /እንዲህ እንደ አሁኑ ማለት/፡፡ በዚህም ምክንያት በርዕስ ያነሳኸውን ጉዳይ ከላይ እንዳስቀመጥኩት ዓይነት ግንዛቤ ስላለኝ ምናልባትም በሃሳብ ልውውጥ መሃል ሳልጠቀምበት አልቀረሁምና /ድክመት ቢሆን ንስሃ ብለህ ቁጠርልኝ/ ፡፡ እግዚአብሔርም የድክመቴ ምንጭ ምን መሆኑን ስለሚረዳ ይቅር እንደሚለኝ ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡

    ካላሰለቸሁ አሁንም ለመጨረሻ ጊዜ ላስቸግር ፡፡
    ምናልባት በአገላለጽ ድክመት ወይም በቋንቋ ውሱንነት ካልሆነ በስተቀር እግዚአብሔር በአፈጣጠሩ አዳልቷል ፣ እኛንም ለመጉዳት አበላልጧል ፣ ለእኛ ያለውም እቅድ ተመሳቅሏል ወይም ተበላሽቷል የሚል መንፈስ የለኝም ፡፡ ሁላችንም ለበጎ ተፈጥረናል እንጅ ለኩነኔ አልተዘጋጀንም ፡፡ ይህ እንዲህ መሆኑን ብቀበልም ፣ ከኛው መሃል ግን ጸጋውን የሚያበዛላቸው ምርጦች ፣ ሊጠቀምባቸው የሚያስነሳቸው አገልጋዮች ፣ ቸርነቱን ሊያሳይባቸው የሚወዳቸው ቅዱስ ዕቃዎች አሉት ፡፡ ደፈርክ ብለህ አትኰንነኝ እንጅ ለምሳሌም ቅድስት ድንግል ማርያም ከሴቶች መሃከል ቀዳሚዋ ናት /ወስብሐት ለእግዚአብሔር/ ፡፡ የአምላክ እናትነት ዕድል ለማንም ለሌላ ሴት ሊሰጥ አልታቀደምና ነው ፡፡ ሊገለገልባት ምርጫው ከርሱ የመጣ ሲሆን ፣ ፈቃዱን በመቀበል ደግሞ ታዛዥነቷን አሳይታለች ፡፡ እርሱ በሚያውቀው ባይመርጣት ኖሮ ግን በራሷ ፍላጐትና ፈቃድ ምንም ለመሆን አትችልም ነበር ፡፡ ይኸንን ነው ጸጋውን ስለሚያበዛላቸው ብዬ ለማስረዳት የፈለግኩት ፡፡

    ጌታ የተጠቀመበትን ምሳሌም ከማቴዎስ 2ዐ ልጥቀስ ፡፡ የወይን እርሻው ባለቤት ፣ ሠራተኞቹን ለዕለቱ የሚከፍላቸውን ደሞዝ አስረድቶ ማለዳ ቀጠራቸው ፡፡ ሌሎቹን ደግሞ በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት እንዲሁ ተነጋግሮ ቀጠራቸው ፡፡ በመጨረሻው ስንብት ላይ ግን ሁሎችንም እኩል ከፈላቸው ይለናል ፡፡ ሁሎችም በአንድ እርሻ ተሰማርተው ሳለ የገበሬው ችሮታ መለያየትና ማበላለጡን አስተውልልኝ ፡፡

    የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ስለሆነ /1 ቆሮ 12 ፡ 4/ ለአንዱ በልሳን የመናገር ችሎታን ሲሰጠው ፣ ለሌላው ደግሞ ትንቢት የመናገርን ያድለዋልና ሁሉም እኩል ወታደር ወይም አስተማሪ መሆን አይችልም ፡፡ እንዲህ ማለያየቱ ማዳላቱ ሳይሆን እኛን ወደ አቀደልን መንገድ ለመመለስና ለመጥቀም ነው ፡፡ ለምሳሌም አሁን በእኔና አንተ መካከል እንኳን የሚደረገው የጽሁፍ ልውውጥ የጸጋው ልዩ መሆንን የሚያሳይ ነው ፡፡ አንተን ብርሃኑን አሳይቶ ምስጢሩን ስለገለጸልህ እኔን አልበደለኝም ፡፡ ይልቁንም በአንተ ብዙ እንድጠቀም አደረገኝ እንጅ ፡፡ ሃሳቤን በምችለው ያስረዳሁ ስለመሰለኝ በዚሁ ላብቃ ፡፡ በብሎግህ ከምትጽፋቸው እጅግ ብዙ ተምሬአለሁ ፡፡ እግዜአብሔር ይርዳህ ፤ ፍጻሜውንም ያሳምርልህ ፡፡

    ውድ ጊዜህን ወስደህ ፣ እኔ ደካማውን ለመርዳት በማዋልህ እግዚአብሔር ልፋትህን ያስብ !!!
    በረከቱንና ምሕረቱን ለሁላችንም ያድለን !!! አሜን ፡፡

    ReplyDelete
  7. የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላም ለአንተ ይሁን ወንድሜ! ከሁሉም በፊት አንድ ነገር ላስታውስህ፡፡ መጠራጠር (ያውም ስላልገባህ!) ኃጢአት አይደለም፡፡ ኃጢአትነቱ እውነቱ ሲነገርህ አልቀበልም ብለህ በዚያው ጥርጥርህ ጸንተህ ስትቀር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቱን እየነገረህ ሕሊናህን እያዳመጥክ በዚያው መቅረት ነው፡፡ ስለዚህ የምታነሣቸው ጥያቄዎች (በቅድስት ድንግል ማርያም ላይም ቢሆን) ስላላወቅክ እንጂ እንደዚያ ለማለት ፈልገህ እንዳልሆነ ሙሉ ለሙሉ እረዳልሀለሁ፡፡ ስለዚህ የሀገሬ ሰው “መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ” እንዲል ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል፡፡
    ወደ ጥያቄህ ስመለስ የአምላክ እናትነት ለማንም አልተሰጠም፡፡ ለምንድነው ያልተሰጠው? እግዚአብሔር ከሌሎች ሴቶች ይልቅ እናትነቱን ለእርሷ ስለሰጣት ነውን? መልሱን እዛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታገኘዋለህ፡፡ መልአኩ በታላቅ አክብሮት “ደስ ይበልሽ! ጸጋን የተመላሽ ሆይ” ብሎ ሲያመሰግናት እመቤታችን ከሌሎች ሴቶች ይልቅ ንጽሕናዋን፣ ቅድስናዋን፣ ክብሯን፣ ልዕልናዋን ጠብቃ ስለተገኘች ነው /ሉቃ.1፡28/፡፡ እመቤታችን እንደ ሌሎች ሴቶች እዚህ ምድር የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ሆኖም ግን እንደ ሌሎች ሴቶች ወደ ሥጋዊ ፈቃዷ አላዘነበለችም፡፡ እንኳንስ በሥጋዋ በሐሳብዋም እንዲህ አላደረገችም /ሉቃ.1፡29፣ 34/፡፡ ቅዱሱ እግዚአብሔር ይኸን ቅድስናዋ ሲመለከት አንድ ልጁን ለተዋሕዶ ላከው /ሉቃ.1፡26-27/፡፡ ከሊቃውንት አንዱ አባ ሕርያቆስም እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችን ሁሉ በእውነት ተመለከተ፤ ተነፈሰ፤ አሻተተም፤ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ የአንቺ መዐዛ ወደደ፤ የሚወደውን ልጁንም ወደ አንቺ ላከ” /ቅዳሴ ማርያም ቁ.24/፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እመ አምላክነትን በግድ የሰጣት አይደለም፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ይህን የበለጠ ሲያብራራልን እንዲህ ይላል፡- “እነሆኝ! የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች” /ሉቃ.1፡38/፡፡ ከዚህ መረዳት እንደምንችለው እግዚአብሔር አስቀድሞ የእርሷን ፈቃድ ጠይቋል፡፡ እርሷም ሙሉ ፈቃዷን “እነሆኝ የጌታ ባርያ” ብላ በፍጹም ትሕትና ገልጣለች፡፡
    በአጠቃላይ የእመቤታችንም ቢሆን እግዚአብሔር ንጽሕናዋን አስቀድሞ ስለሚያውቅ እንጂ አስቀድሞ ለዚያ ስለወሰናት አይደለም፡፡ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ እኛም ከትውለድ ውስጥ ገብተን ባላመሰገንናት ነበር፡፡
    የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን!!

    ReplyDelete
    Replies
    1. ስላስተማርከኝና ስላስተማርከን አመሰግናለሁ

      Delete
  8. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
    Replies
    1. mekrez
      God bless you your work.
      I have one question
      what is "KIBAT RELIGION"?

      Delete